ስለ ውክልና በጠቅላላው
ሰዎች በተለያዩ የንግድ፣የአስተዳደር እና የአገልግሎት ተግባራቶች ላይ መሳተፋቸው አይቀሬ ነው፡፡ሰዋች( የተፈጥሮ ወይም በሕግ ሰውነት የተሰጣቸው) የዕለት ተዕለት ኑሮአቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሥራውን በራሳቸው ለመከወን የማይችሉባቸው ምክንያቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ከምክንያቶቹም የተወሰኑት ሰዋች በጤናቸው ላይ በሚገጥማቸው እክል ወይም ሥራው ከሚከናወንበት ስፍራ መራቅ፣ስለ ሥራው በቂ የሆነ እውቀት እና ልምድ ማጣት እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ በነዚህ ምክንያቶች ሊያጡ ከሚችሉት መብት እና ጥቅም አንፃር ሥራው በሌላ ሰው እንዲፈጸምላቸው ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ በመሆኑም ሥርዓት ባለው፣በህግ በሚመራ እና መብት እና ግዴታን በግልጽ በሚያቅፍ የውክልና ግንኙነት ውስጥ መግባት ያስፈልጋል፡፡
ውክልና ማለት በፍ/ብሄር ሕግ ቁጥር 2199 መሰረት ተወካይ የተባለ አንድ ሰው ወካይ ለተባለው ሰው እንደራሴ ሆኖ አንድ ወይም ብዙ ህጋዊ ሥራዎችን በወካዩ ስም ለማከናወን ግዴታ የሚገባበት ውል ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት ወካዩ( የተፈጥሮ ሰው ወይም በህግ ሰውነት የተሰጠው አካል) ከውል የመነጨ ግንኙነት ወይም በህግ ለተወካይ በሚሰጠው አንድ ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ህጋዊ ተግባራትን የመፈፀም ስልጣን ወይም ተወካዩ በወካዩ ስም ወካዩን ሊያስገድድ የሚችል ስምምነትን ከ3ኛ ወገኖች ጋር እንዲዋዋል የሚያስችለው የህግ ማዕቀፍ ነው፡፡ ፍትሃብሔር ሕግ አንቀፅ 2179 ውክልና አንድም ከህግ በሌላ መልኩ ደግሞ ከውል ሊመነጭ እንደሚችል አመልክቷል፡፡
የውክልና ዓይነቶች
1. ጠቅላላ ውክልና - በጠቅላላ አነጋገር የተደረገ ውክልና ሲሆን ለተወካዩ በፍትሃብሄር ሕግ አንቀፅ 2204 ላይ የተቀመጡትን አስተዳደር ሥራዎች ከመፈፀም ውጭ ሌላ ሥልጣን አይሰጠውም( ፍ/ብ/ሕ/ቁ 2203)፡፡
2. ልዩ ውክልና -ወካዩ ተወካዩ ከአስተዳደር ስራ ውጪ የተለየ ስራን እንዲያከናውንለት ሲፈልግ ልዩ ውክልና መስጠት የሚኖርበት ሲሆን( በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2205(1) ይመለከቷል) ተወካዩም ተለይተው በዝርዝር እንዲከውናቸው የተሰጠውን ጉዳዮችንና እንደ ጉዳዩ አይነትና እንደ ልማድ አሰራር ከጉዳዩ ጋር ተከታታይነትና ተመሣሣይነት ያላቸው ነገሮችን ማከናወን ይችላል ማለት ነው ( ፍ/ብ/ህ/ቁ 2206(1))፡፡
@Lawyer_eleni@Lawyer_elsa@Lawyer_hawi