በረመዳን ምን ይጠበቅብናል?
የመጨረሻው ክፍል
6.የሰዎችን ጉዳይ መፈፀም
ከታላላቅ በጎ ተግባሮች ውስጥ ለሰዎች ጉዳይ መሮጥና ስለሰዎች መጨነቅ አንዱነው።ስለዚህ ምንዳውም የተግባሩ አምሳያ ነው። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህብለዋል፡-
“ከሠዎች መሀል አላህ ዘንድ ተወዳጁ ለሠዎች ጠቃሚ የሆነ ነው። አላህ ዘንድ ተወዳጅ ሥራ ሙስሊም ልብ ውስጥ የምታስገባው ደስታ የምትገላግለው ጭንቅ፣ ከዱንያ የምትፈፅምለት ጉዳይ ወይም የምትገፈትርለት ረሀብ ነው።
በአላህ እምላለሁ መስጂድ ውስጥ ወር በሙሉ ኢዕቲካፍ አድርጌ ከምቀመጥ ለሙስሊም ወንድሜ ጉዳይ ብሮጥ እመርጣለሁ።ቁጣውን የሚደብቅ አላህ ነውሩን ይሸፍንለታል።ቁጭቱን የዋጠ ሰው የቂያም ቀን አላህ ልቡን በውዴታው ይሞላለታል።
የሙስሊም ወንድሙ ጉዳይ እስኪፈፀም ድረስ የተንቀሳቀሰ የሰዎች እግር በሚስትበት ቀን አላህ እግሩን (በሲራጥ ላይ) ያረጋለታል። ጥፉ ስብእና ልክ ኮምጣጤ ማርን እንደሚያበላሽ መልካም ሥራን ያበላሻል።”
ባለቤታቸው የሞተባቸው ሴቶችንና ሚስኪኖችን መንከባከብ የተለየ ምንዳ እንደሚያስገኝ ነብያዊ ሐዲሶች አበክረው ይጠቁማሉ። የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ይላሉ፡-
الساعي على الأرملة والمسكين كالمجاهد في سبيل الله أو القائم الليل الصائم النهار
“ባላቸው ለሞተባቸው ሴቶች እና ለሚስኪን ጉዳይ የሚሮጥ በአላህ መንገድ ላይ እንደሚታገል (ሙጃሂድ) ወይም ለሊት እንደሚቆምና ቀን እንደሚፆም ሠው ነው።”
7.የነፍስ አድን ጥሪ!
ኢብሊስ ብዙ ሰዎችን ማጥመም ችሏል። ከጌታቸው አምልኮ ጋረዳቸውና በዱንያ ጌጦች እንዲታለሉ አደረገ። ወደ እሳት የሚወስዳቸውን መንገድም መራቸው። እና እኛስ እነዚህን ሰዎች እንተዋቸው፤ ይጥፉ!?
አላህ እንዲህ ብሏል፡-
وَمَنْ أَحْسَنُ قَوْلًا مِّمَّن دَعَا إِلَى اللَّهِ وَعَمِلَ صَالِحًا وَقَالَ إِنَّنِي مِنَ الْمُسْلِمِينَ
“ወደ አላህ ከጠራና መልካምንም ከሠራ፣ ‘እኔ ከሙስሊሞች ነኝ’ ካለም ሰው ይበልጥ ቃሉ ያማረ ማን ነው?” (ፉሲለት 41፤ 33)
እነዚህን ሚስኪኖች ማዳን አለብን። ዳዕዋ ልናደርግላቸው ይገባል። አላህ ዳዕዋ እንድናደርግ አዟል።
ይህን ትእዛዝ የሚተገብሩ ሰዎችን ደረጃ ከነብያትና ከመልእክተኞች ደረጃ ጋር የሚስተካከል አድርጓል። ምንዳው ደግሞ ድንበር የለውም። ታዲያ ውድ ወንድምና እህቶች ይህን ደረጃ ለማግኘት አንጓጓም!?…
ዛሬ ረመዳን ላይ ሰይጣኖች ታስረዋል። ነፍሶችም ታዛዦች ናቸው። ታዲያ ይህን አጋጣሚ ለዚህ ኃላፊነት መጠቀም ብልህነት አይደለምን!?… የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ ብለዋል፡-
لئن يهدي الله بك رجلاً واحداً خير لك مما طلعت عليه الشمس
“ፀሀይ የወጣችበት ሁሉ ከሚኖርህ አላህ አንድን ሰው ወደ ቀና መንገድ ቢመራልህ ይሻልሀል።”
በሉ ሁላችንም እንነሳ ሰዎች እንዲመሩ ሰበብ ለመሆን እና ነፍሶችን ለማዳን እንቁም! የዘነጋን ለማስታወስ፣ የተደናገረን ለመምራት፣ የጠመመን ለማቅናት፣ የተኛን ለማንቃት… እንነሳ!
ከቅርብ ዘመዶቻችን እጀምር። የዱንያን ምንነት እናስረዳቸው። እጃቸውን ይዘን ወደ መስጂድ እንውሰዳቸው። በረመዳን ብቻ መስጂድ የሚገቡ ወንድሞችና እህቶችን ትክክለኛው መንገድ ወዴት እንደሆነ እንጠቁማቸው። ይህን የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ዱዓ ደጋግመን እናድርግ።
“አል-ላሁም-መ ኢጅዐልና ሁዳተን ሙህተዲን”(አላህ ሆይ /ወደ ቀና/ የተመሩና ሰዎችን ወደ ቀና መንገድ የሚመሩ አድርገን።)
የክፍል ❶❷ ማጠቃለያ
የእድል ወይም የሰዐዳ መሰረት እና መሽከርከሪያ ምህዳር ሁለት ነገሮች ላይ ይንጠለጠላል፤
አላህን በኢኽላስ በማምለክና
ለፍጡራን መልካም በመዋል።
የበጎ አድራጎት በሮች ሰፊ ናቸው። ዋናው ነገር በልብ ተነሳሽነት እና በትጋት ተግባር ላይ መሳተፍ ነው። በተለይም ረመዳን በጎ አድራጎትን ለመልመድ መልካም አጋጣሚ ነውና ይህን ወርቃማ ጊዜ እንጠቀምበት።
ለትዳር አጋር መልካም መዋል፣ ልጆችን ማስደሰትና መንፈሳዊ ህይወታቸውን መከታተል… ከጠቀስናቸው ውስጥ ናቸው። በየቀኑ ከቤተሰቦች ጋር የሚደረግ ስብሰባ ይህን ሊያሳካ እንደሚችል ዘክረናል።
ዝምድናን መቀጠል፣ ምግብ ማብላት፣ ስጦታ ማብዛት፣ የሰዎችን ጉዳይ መፈፀም፣ ሰዎችን ማስታረቅ… የጠቀስናቸው የበጎ አድራጎት ደጃፎች ናቸው። ኑ በነዚህ ደጃፎች ወደ አላህ እንግባ!!!
ምክራችን
በመጨረሻም እነዚህ ተግባሮች ለመፈፀም ሁላችንም ለነፍሳችን ቃል እንድንገባ እንጠይቃለን። አላህ እንዲህ ብሏል፡-
إِن يَعْلَمِ اللَّهُ فِي قُلُوبِكُمْ خَيْرًا يُؤْتِكُمْ خَيْرًا
“አላህ በልቦቻችሁ ውስጥ በጎን ነገር ቢያውቅ የተሻለን ይሰጣችኋል።” (አል-አንፋል 8፤ 70)
የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) “…መልካምን አጥብቆ የሚሻ ሰው አላህ ይሠጠዋል።”
ምናልባት አላህ እውነተኛ ፍላጎታችንን አይቶ ከፍላጎታችን ጫፍ ያደርሰን ይሆናል። ልመናችንንም ያሟላልናል። “ስጦታ የሚሰጠው በዝግጅታችን መጠን ነው!”
ነፍስ ታካች ናት። እረፍት በሰጠሀት ቁጥር ጨምርልኝ ትላለች። የረመዳን ወር በቁጥር የሚለኩ ሰዓታት ድምር ነው። ስለዚህ ያሳለፍናቸውን ተግባራት ለመፈፀም በነፍስህ ላይ ቃልን ያዝ። ከአላህ እርዳታ ለምን። እንዲቀበልህም ተማፀን።
❶የቀን እንቅልፍ እንቀንሳለን።
❷ምግብና መጠጥ እንቀንሳለን።
❸ንግግርና ሳቅ አናበዛም።
❹ቁርአንን ማስተንተንና በዘነጋ መንፈስ ያነበብነውን መድገም።
❺ቢያንስ በቀን ሃያ ጊዜ ሞትን ማስታወስ አለብን።
❻ መስጂድ ውስጥ ብዙ መቆየት መልካም ነው።
❼በጊዜ ወደ ጀመዐ ሶላት መሄድ እናዘውትር።
❽ቤታችን የሚመች ከሆነ ለሚስትና ለልጆች የሚሆን የመስገጃ ስፍራ (መስጊድ) እንወስን።
❾በየቀኑ ከትዳር አጋር እና ከልጆች ጋር የሚደረግ ለክትትልና ለንባብ የሚሆን ፕሮግራም እንወስን።
❿ከፈጅር በፊት ተነስተን ተሀጁድ መስገድ፣ ዱዐ እና ኢስቲግፋር ማብዛት አለብን።
❶❶ምርጥ ወቅቶችን መጠቀም አለብን። በእንቅልፍና መሰል ነገሮች ማባከን የለብንም።
❶❷ልባችንን ሰብስበን ዱዐ ማብዛት አለብን። በተለይም ለዱዐ የተመረጡ ወቅቶችን አጥብቀን እንያዝ!
❶❸ ቤታችን ውስጥ ሶደቃችንን የምናጠራቅምበት ሳጥን እናስቀምጥ እና ውስጡ ላይ የየቀን ሶደቃችንን እንክተት።
❶❹ዚክራችንን ከፊክር ጋር እናቆራኝ። የምንሰራቸውን ዒባዳዎችና በጎ ሥራዎች ከኢኽላስ ጋር እናስተሳስር።
❶❺በቀን ለአንድ ሰዐትም እንኳን ቢሆን ኢዕቲካፍ እናድርግ። የመጨረሻዎቹን አስር ቀናት ደግሞ ጠቅልለን እንድንገባ አደራ።
❶❻በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ስለፈፀምነው ኃጢያት እና ስህተት ነፍሳችንን መተሳሰብ አለብን።
❶❼በጎሥራዎችን ማብዛት አለብን።
❶❽ለወዳጆቻችንና ለሚስኪኖች ምግብ ማብላት አለብን።
❶❾ለሙስሊሞች ጉዳይ መሯሯጥ አለብን።
❷0የበደለንን ይቅር ማለት እና ልባችንን ማስፋት አለብን።
❷❶ ወደ አላህ መንገድ ሠዎችን መጥራት አለብን።
በመጨረሻ፡-
ውድ አንባቢዎች! ሁላችንም የተለያየ ሁኔታ ላይ የምንኖር ሠዎች ነን። በድንገት ረመዳን ወጥቶብን ግራ እንዳንጋባ የየቀን ፕግራሞቻችንን አሁኑኑ አውጥተን እናጠናቅቅ።
መልካም ረመዳን!! አላሁመ ባሪክ ለና ፊ ረመዳን!!
🔂 ሼር 🔂 ሼር 🔂 ሼር 🔂
🍀 ዲነል ኢስላም Tube
🔑"ለመልካም ነገር ቁልፍ ሁን!!"
http://t.me/Dinel_Islam_Tube