የፌዴራል ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ ሆነው የሚቆይቡት ጊዜ ተራዘመ
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የኮሮና ቫይረስ (COVID 19) ስርጭትን ለመከላከል ቀጣይ የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ በማስፈለጉ ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ ሆነው የቆዩበትን ጊዜ ለተጨማሪ 22 የስራ ቀናት አራዘመ፡፡
የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከመጋቢት 10 /2012 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ በከፊል ዝግ ሆነው አፋጣኝ የፍርድ ቤት ውሳኔና ትእዛዝ የሚፈልጉ ገዳዮችን በተረኛ ችሎቶች በማስተናገድ አገልግሎት እንዲሰጡ መወሰኑ ይታወቃል፡፡
በዚህ ጊዜ የፌዴራል ዳኞች በየምድብ ችሎቱ በተደራጁ ተረኛ ችሎቶች እየሰሩ ቆይተዋል፡፡ በቤትና በቢሮ ለውሳኔ፤ ለብይንና ለትዕዛዝ የተቀጠሩ መዛግብትን በማቃለል ከፍተኛ ውጤት በማስገኘት ላይም ናቸው፡፡ በተጨማሪም የተረኛ ዳኞችን ቁጥር በመጨመር ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር ተያይዞ የሚቀርቡላቸውን ጉዳዮች በመስራት ላይ ሲሆኑ በተሰጡ ውሳኔዎች ላይ የሚቀርቡ የይግባኝ አቤቱታዎችም በየደረጃው ባሉ ፍርድ ቤቶች በመታየት ላይ ናቸው፡፡
ዓለምን እያስጨነቀ ያለው የኮሮና ቫይረስ (COVID 19) ወረርሽኝ በሃገራችን ስርጭቱ እንዳይስፋፋ ለመገደብ እየተወሰደ ያለው የጥንቃቄና የመከላከል ስራ አሁንም ትኩረት የሚፈልግና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በመንግስት እየተገለጸ ይገኛል፡፡ ይህንንም ጥረት ለማገዝና በየዕለቱ በትንሹ 18 ሺህ ያህል ባለጉዳዮች የሚስተናገዱባቸውን ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ ማድረግ ባለጉዳዮች በቤት እንዲቆዩና አካላዊ ርቀትን እንዲጠብቁ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ከግንቦት 3/2012 ዓ.ም ጀምሮ ለ22 የስራ ቀናት ማለትም እስከ ግንቦት 30/2012 ዓ.ም ድረስ አሁንም ለሶስተኛ ዙር በከፊል ዝግ ሆነው እንዲቆዩ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ፡-
• በየፍርድ ቤቱ ለምርመራ እና ለውሳኔ የተቀጠሩ ውዝፍ መዛግብት ተለይተውና እንደየሁኔታው ታይተው እልባት የሚሰጣቸው ይሆናል፡፡ ውዝፍ መዛግብት የሌለባቸው ችሎቶች ውዝፍ መዛግብት ያለባቸውን ችሎቶች እንዲያግዙ ይደረጋል፡፡
• በማረሚያ ቤት ያሉ ባለጉዳዮችን በተመለከተም ከማረሚያ ቤት አስተዳዳሪዎች ጋር በመወያየትና መርሃ ግብር በማዘጋጀት በቪዲዮ ኮንፈረንስ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት ይደረጋል፡፡
• ፍርድ ለተሰጠባቸው ጉዳዮች በቂ የውሳኔ ግልባጮች ከወዲሁ ተዘጋጅተው ባለጉዳዮችን እንዲጠብቁ ይደረጋል፡፡
• ባለጉዳዮች በአካል ፍ/ቤት ቀርበው በመደበኛው አካሄድ የመሰማት እድል ሊሰጣቸው ይገባል የሚያስብሉ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ በሪጅስትራር ተለይተውና የሚመለከተውን አካል በማስፈቀድ ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል፡፡
• አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም ተግባራዊ እየተደረጉ ካሉ መመሪያዎች ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ ጉዳዮች በአፋጣኝ እልባት ማግኘት የሚገባቸው በመሆኑ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በተረኛ ችሎቶች የዳኞች ቁጥር እንዲጨምር ይደረጋል፡፡ ከእነዚህ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ የይግባኝ አቤቱታዎችም በአፋጣኝ ታይተው እልባት የሚሰጣቸው ይሆናል፡፡
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በሰጠው የስራ አቅጣጫ እጅግ አስገዳጅ አገራዊና ኢኮኖሚያዊ እንድምታ ያላቸው አስቸኳይ መፍትሄ ለሚፈልጉ ብርቱ ጉዳዮች እንደ ሁኔታው በየደረጃው የሚገኙ የፍ/ቤት አመራሮች እና የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር ኃላፊዎች ፈጣን ምላሽ እንዲሰጡ አሳስቧል፡፡ እንዲህ ያሉ ጉዳዮች መታየት ሲኖርባቸውም ከሚኒስትሮች P COVID Task Force አስፈላጊው ፈቃድ እንደሚጠየቅም ገልጿል፡፡
በተመሳሳይ ወደ ፍርድ ቤት በአካል የሚመጣ ማንኛውም ሰው የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል (Mask) ማድረግ ግዴታ መሆኑን፤ እጅን በተዘጋጀ ንጽህና መጠበቂያ ውሃና ሳሙና መታጠብ እንዳለበት እንዲሁም በባለሙያዎች እና በተገልጋዮች መካከል፤ በአገልግሎት ሰጪ እና አገልግሎት ተቀባይ መካከል ያለውን አካላዊ ርቀት መጠበቅ እንደሚገባም ፍርድ ቤቱ ባሳለፈው ውሳኔ ጨምሮ አሳስቧል፡፡
============= // ============
https://www.facebook.com/The-Federal-Supreme-Court-of-Ethiopia-265784033571676/?__tn__=kC-R&eid=ARCO5D2C29ldENOA65_tSWVap4TZFnMPrZtHeNbTJaTU0948NPkb9CuK72CjP8VKq7vB4eXdMsaae605&hc_ref=ARTfTfNijGxLWI7qB6KR797Dy3qG5HGQ2Tvo8s1tfaTDp8zqK_LC5vbMx_9Z7t52hXA&fref=nf&__xts__%5B0%5D=68.ARAwJ82Sla185RZLoWueyWnYSKpFnCSbs8c30sFADTDpAEWCbAzXREXh88nz3vyPkXX9hAylPTHOI4Hzi5bulZ_NHhHXpowZh0QmntGX8vaerlxO0pPRcFNqqRBmPa_uZ7HajcnzUoRrjSdHABcdb8Lze5_tCN3kTbHihx3iK8omlH-v7HkNOyC4-Z91Q2-AigchwdEBVHHqBZuH96C__WpiXXydr5fkqmYEverbtjaUxk7T_ohNFnvMghKsdmUfmlqftvgsH-n7y9_gB88ZNcUmZwukDWfEvuI3jBDPoYIVHQD4rMKbxERWLYopi2DncqrnxWcsQ9SQk88PFGp9xwbfQg የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት