#የማለዳ_ስንቅ
#መንፈሳዊ_ቤትቤት በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ሰው የሚያርፍበትና የሚያድርበት ቤት ከሌለው አያርፍም፡፡ ሰው ቤት ካለው ደግሞ ነፃነቱ ይበዛል፡፡
እንዲሁም እግዚአብሄር የሚንቀሳቀስበት ፣ የሚናገርበት ፣ የሚገኝበት ፣ የሚያርፍበትና በጎነቱን የሚያስተላልፍበት ቤት ይፈልጋል፡፡ ቤት ሰፋ ባለ ቁጥር ፣ ቤት ንፁህ በሆነ መጠንና ቤት ጠንካራ በሆነ መጠን ለመኖርም ፣ እንግዳን ለመቀበልም ፣ ለማረፍም እንዲሁም ለማደር ያበረታታል፡፡ ቤት ግን በደንብ ካልተሰራ ፣ ንፅህናው በደንብ ካልተጠበቀ ፣ ጠንካራ መሰረት ላይ ካልተመሰረተ ፣ ውበት ከሌለው ለመኖር ፣ ለማረፍና እንግዳ ለመቀበል አይመችም፡፡
እኛም ንፁህ ሰፊ ጠንካራ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ራሳችንን ሰጠንና በተሰራን መጠን እግዚአብሄር በቀላሉ ፣ በደስታና በእረፍት በእኛ ይኖራል በእኛ ይታያል ፣ በእኛ ይናገራል ፣ በእኛ ይወቅሳል ፣ በእኛ ሌሎችን ይደርሳል ፣ በእኛ ያርፋል ፡፡
እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ። 1ኛ ጴጥሮስ 2፡5
ቤት ማረፊያና መደሰቻ እንደመሆኑ መጠን የእግዚአብሄር ማረፊያና መደሰቻ ለመሆን እለት በእለት በእግዚአብሄር ቃል መሰራት ይኖርብናል፡፡ ሰው ሌላ ቦታ ቢያዝን ቤቱ ግን ማዘን የለበትም፡፡ ሰው ሌላ ቦታ ቢታመፅበት በቤቱ የሚነገረው ነገር ሁሉ እርሱን የሚያከብርና እርሱን የሚያስደስተው ብቻ መሆን አለበት፡፡
. . . ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ። ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ። ኤፌሶን 4፡29-30
ቤት መገኛ አድራሻ እንደመሆኑ መጠን የእግዚአብሄር በጎነት የሚገኝበት ፣ የእግዚአብሄር ምህረት የማይታጣበት ፣ የእግዚአብሄር ይቅርታ በልግስና የሚከፋፈልበት ፣ የእግዚአብሄር ፍቅር የማይጠፋበት መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሰሩ፡፡
እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፥ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ። ኤፌሶን 4፡32
ቤት ንፁህ ነገር ብቻ የሚገኝበት እንደመሆኑ መጠን የእግዚአብሄር ነገር ብቻ የሚገኝበት ከሰይጣን ሃሳብና ከሃጢያት ምኞት የፀዳ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሰሩ፡፡
የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ።1ኛ ቆሮንቶስ 3፡16-17
ቤት ከምንም አስቀድሞ አስተማማኝ በሆነ አለት መሰረት ላይ እንደሚገነባ ሁሉ በቃሉ መሰረት የእግዚአብሄር ቤት ለመሆን ተሰሩ፡፡
ስለዚህ ይህን ቃሌን ሰምቶ የሚያደርገው ሁሉ ቤቱን በዓለት ላይ የሠራ ልባም ሰውን ይመስላል። ማቴዎስ 7፡24
ሰው ከምንም በላይ ቤቱን በከበረ ነገር እንደሚያስውበው መጠን በየዋህነትና በዝግተኝነት የተዋበ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሰሩ፡፡
ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ዋጋው እጅግ የከበረ የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ያለውን የማይጠፋውን ልብስ ለብሶ የተሰወረ የልብ ሰው ይሁንላችሁ። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡4
ቤት የሚስብ ትህትና የሚታይበት ቦታ እንደመሆኑ መጠን በትህትናና በተሰበረ ልብ ለእግዚአብሄር መኖሪያ ቤት ለመሆን ተሰሩ፡፡
እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሰማይ ዙፋኔ ነው፥ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድር ነው? እነዚህን ሁሉ እጄ ሠርታለችና እነዚህ ሁሉ የእኔ ናቸው፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን ወደዚህ ወደ ትሑት፥ መንፈሱም ወደ ተሰበረ፥ በቃሌም ወደሚንቀጠቀጥ ሰው እመለከታለሁ። ኢሳይያስ 66፡1-2
" ኢየሱስም መለሰ አለውም። የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን።"
(የዮሐንስ ወንጌል 14:23)
@SelahWeekly
@SelahWeekly