ከዱኒያ በላጮቹ ቀናቶች እነሆ ተጀምረዋልና አትዘናጉ ለዒባዳ ነቃ ነቃ በሉ!!—————
የመጀመሪያዎቹ
አስር የዚል-ሒጃ ቀናቶች—————
አምላካችን አላህ ችሮታውና እዝነቱ ሰፊ ስለሆነ ለባሪያዎች በመልካም ስራ ላይ የሚሽቀዳደሙባቸውን ቦታዎችና ቀናቶችን አንዱን ከሌላው በማበላለጥ እድሉን አስፍቷል። እለተ ጁምዓ ከሌሎች ቀናቶች በላጭ እንዲሆን አድርጓል። የረመዷንን ወር ከሌሎች ወራቶች በላጭና መልካም ስራዎች ውድ የሚሆኑበት ልዩ ወር አድርጎታል። ከረመዷን ወር ውስጥም የመጨረሻዎቹ አስር ቀናት ልዩና አማኞች ለመልካም ስራ በተለየ መልኩ ወገባቸውን ጠበቅ አድርገው በመታጠቅ መልካም ስራዎችን የሚሰሩባቸው ታላቅ ቀናት አድርጓቸዋል።
ልክ እንደዚሁ ከቀናቶች ውስጥ የመጀመሪያዎችን የዚል-ሒጃ ቀናት ውድና በእነዚህ አስር የመጀመሪያ የዚል-ሂጃ ቀናት የሚሰራን ስራ ከሌላው ጊዜ ሊወዳደር የማይችል ከፍተኛ ደረጃ የሰጠባቸው ውድ ቀናት አድርጓቸዋል።
ይህ የአላህ ለባሮቹ የዋለው ውለታና ትሩፋት ነው። ምክንያቱም የሰው ልጆች በተለያየ ምክንያት ተዘናግተው መልካም ስራ ውድና ልዩ ደረጃ የሚያስገኝበት ጊዜ ቢያመልጣቸው እድሜ ሰጥቷቸው በሌላው ጊዜ ከደረሱ ተሽቀዳድመው እንዲጠቀሙ ይረዳቸዋል። በሌሎች ጊዜዎች በአግባቡ ሳያመልጣቸው ተጠቅመው ከሆነም በውድ ጊዜዎች በመልካም ስራ ላይ መልካም ስራ በመጨመር ጌታቸው ዘንድ ተወዳጅ እንዲሆኑ ይረዳቸዋል።
ታዲያ በሌሎች ጊዜዎች ሁሉ ከሚሰሩ መልካም ስራዎች በላጭና ውድ የሚሆንባቸው ልዩ ቀናት የዚል-ሂጃ የመጀመሪያዎቹ አስር ቀናት ናቸውና ነፍሲያችንና ሸይጧንን አሸንፈን በአግባቡ ልንጠቀምባቸው ይገባል።
ከኢብኑ ዐባስ (ረዲየላሁ ዐንሁማ) ተይዞ የአላህ መልእክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ:-
“በየትኛውም ቀን የሚሰራ መልካም ስራ ከነዚህ ቀናት የበለጠ ስራ ከየት አለ?!፣” አሉ፣ ጂሃድም ቢሆን? ተብለው ተጠየቁ፣ “አዎ ጂሃድም ቢሆን” አይበልጥም፣ አሉና አክለውም እንዲህ አሉ:- “አንድ ሰው (ለጂሃድ) ራሱም ንብረቱም ወጥቶ በዚያው ራሱም ንብረቱም ያልተመለሰ ከሆነ እንጂ።” አሉ። ቡኻሪ 969 ላይ ዘግበውታል።
ይህ ማለት:- አንድ ሰው ለጂሃድ ወጥቶ በዚያው ሸሂድ ሆኖ ከነ ንብረቱ የቀረ ከሆነ ይህ ተግባር ከነዚህ አስሩ የዙል-ሒጃ ቀናት ከሚሰራ ዒባዳ ይበልጣል እንጂ ሌላ የሚበልጥ ነገር የለም ማለታቸው ነው።
ታላቁ ሸይኽ ሙሀመድ ኢብኑ ሷሊህ አል-ዑሰይሚን (ረሂመሁላህ) እንዲህ አሉ:-
"በአስሩ የዚል-ሒጃ ቀናት መልካም ስራ ሲባል ፆምም ይካተታል፣ (እንደ አጠቃላይ ደግሞ) በአስሩ የዚል-ሒጃ ቀናት የሚሰራ መልካም ስራ ከረመዷን ወር የመጨረሻዎቹ አስር ቀናት የበለጠ አላህ ዘንድ ተወዳጅ ነው። ይህ ከመሆኑም ጋር ግን በዙል-ሒጃ በመጀመሪያዎቹ አስር ቀናት ሰዎች መልካም ስራ ከመስራት ይዘናጋሉ። ሰዎች እንደ ቀድሞው ልማዳቸው የተዘናጉ ሆነው አስሩ የዚል-ሒጃ ቀናት ያልፋሉ። ቁርኣን በመቅራት ላይ የተሻለ ሆነው አይታዩም፣ በሌሎች የዒባዳ ዘርፎች ላይም የተሻለ ንቃት ሲኖራቸው አይታዩም። ከፊሎች ተክቢር ማለትን ሁሉ ሲሰስቱ ትመለከታለህ።" [ሸርሁል ሙምቲዕ 6/470]
ኡድሂያ እርድ ለማረድ የነየተ ሰው ከዚል-ሒጃ የመጀመሪያ ቀን ከመግባቱ በፊት ካለው ሌሊት ጀምሮ አስረኛው የእርዱ ቀን ደርሶ ኡድሂያውን እስኪያርድ ድረስ ከሰውነቱ ማንኛውንም ነገር መቁረጥም ሆነ መንቀል አይፈቀድለትም!። ጥፍርም ሆነ ፀጉር እንዲሁም ከቆዳው ክፍልም ቢሆን መቁረጥም አይፈቀድለትም!።
ከኡም ሰለመህ (ረዲየላሁ ዐንሃ) ተይዞ ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል:-
“አንዳችሁ ኡድሂያ ማድረግ ከፈለገ አስሩ የዚል-ሒጃ ቀን ከገባ ከሰውነቱም ሆነ ከፀጉሩ አንድም ነገር አይንካ!።” በሌላ ዘገባ ደግሞ እንዲህ ብለዋል:- “አስሩ የዚል-ሒጃ ቀን ከገባ እርሱ ዘንድ ኡዱሂያ ማድረግ የሚፈልገው ነገር ካለ ፀጉርንና ጥፍሩን አይንካ።” ሙስሊም ዘግበውታል።
ከዒባዳዎች ሁሉ በላጭ በሆነው ዒባዳ ቁርኣንን በማንበብ፣ የወላጆች ሀቅ በመጠበቅ ወላጆችን በማስደሰት፣ በዱዓ ላይ በመጠንከር፣ በዚክር፣ በሶደቃ፣ ዝምድናን በመቀጠል… በሌሎች የተለያዩ በርካታ ዒባዳዎች ላይ በመበርታት አደራ!! የሰሩትን መልካም ስራ ከሚያዳክሙ ስህተቶችና ወንጀሎችም መቆጠብ ነው። አላህ ሁላችንም ለመልካም ነገር ይወፍቀን!!
✍🏻ኢብን ሽፋ: ዚል_ሒጀህ 1/1442 ዓ. ሂ
#join ⤵️
የተለያዩ ት/ቶችን ለማግኘት የቴሌግራም ቻናላችን ⤵️ #join ያድርጉና ይቀላቀሉ
https://telegram.me/IbnShifahttps://telegram.me/IbnShifa