የነገ ትናንት ላይ ናችሁ አይደል....ዛሬ ላይ ማለቴ ነው...እኔ ግን የዛሬ ትናንት ላይ ነኝ....
ነገ....
ዛሬ....
ትናንት....
የ"ነገ" እና የ"ዛሬ" ሆሄያት አጥረው የ"ትናንት" ሆሄያት ለምን ረዘሙ....ነገ እና ዛሬ በሁለት ፊደል ስለተዋቀሩ አልያም ትናንት የሚለው ቃል ላይ አራት ፊደላት ስላሉ ነው ትናንቴ የሚከተለኝ...ነገዬ አጥሮ ነው ያልክ የራቀኝ...ቆይ ዛሬዬስ....
ከራሴ ጋር ጥልቅ ጭውውት ይዣለሁ...ትናንቴ ሙጫ ሆኖብኛል...የረሳሁት ሲመስለኝ መልኩን ቀይሮ አለሁ ይለኛል....ትናንት ጠባሳ ሆኖ ያለቀ ነገር ነው ብዬ ሳልጨርስ እንደ አዲስ ይመረቅዛል...ጠባሳ ያማል እንዴ...
...ከመቼ ጀምሮ...እንጃ ብቻ ያመኛል...
ችግሩ ጠባሳ ያልኩት ትናንቴ ገና ጠፈፍ ያላለ ቁስል መሆኑ ላይ ነው...ለዛ ነው በተነካ ቁጥር የሚያመኝ...
መች ጨረስኩ...አሁንም ጭውውቴን ቀጥያለሁ..."እንደዛ ባይሆን ኖሮ እንዲህ አይሆንም ነበር" እላለሁ ለሆነ ነገሬ...ቁስሉ እንደ አዲስ መድማት ይጀምራል...የነገ ትናንት ላይ ነኝ....ዛሬ ላይ ማለቴ ነው...ግን ጭንቅላቴ ዛሬ ላይ ሳይሆን የዛሬ ትናንት ላይ ነው...እናንተ እኮ አታፍሩም..."move on ምንድን ነው...በቃ አለፈ እኮ ..."...ትሉኝ ይሆናል...እሱ መች ጠፋኝ...ማለፉን ጠንቅቄ አውቃለሁ...ችግሩ ምን አድርጎኝ ነው ያለፈው የሚለው ነው....
የደማው ቁስሌን ከማከም ይልቅ "ደማባት እኮ ስታሳዝን" ብሎ የሚያልፈኝ በዛ....ደሜ እንዳይነካው ደሜን ዘሎ የሚያልፍም አልጠፋም...ቁስሌ መሽተት ሲጀምር እንዳይሸታቸው አፍንጫቸውን ይሸፍናሉ....አንዳንዶቹም አይናቸውን...ያኔ ነው የገዛ ቁስሌን ለማከም የሰነፍኩት...ያኔ ነው ለራሴ ቁስል አይኔን የሸፈንኩት...ሲቆይ እኔም እንደ እነርሱ አፍንጫዬን ሸፈንኩ...ሽታው ይረብሸኝ ጀመር...ትናንቴን አለባበስኩት....ንፋስ እንዳይገባው ጠፍሬ አሰርኩት...ለዛ ነው ዛሬ ላይ ሳይሆን የዛሬ ትናንቴ ላይ የቀረሁት...
የታፈነ ቁስል በእንጨት እስኪነካ አይጠብቅም...በትንሽ ሽንቁር ውስጥ ሽው የምትል ንፋስ ትበቃዋለች...ያማል...በጣም ያማል...ያኔ ነው ያሰርኩት ቁስሌን ማደንዘዝ የጀመርኩት...."ለምን ቆይ...አንቺ እኮ ራስሽን ማከም ትችዪ ነበር...ልክ አልሰራሽም..."....ይላሉ ገና ደከመኝ ከማለቴ... በጨርቅ የተሸፈነ አፍ ለወሬ ሲሆን ይበረገዳል....ሁሉም አስተያየት ሰጪ ይሆናል...ሁሉም አልቃሽ ይሆናል...አይናቸውን እንዳልጨፈኑ አይናቸውን ከፍተው ያነባሉ...
...ስለ እነርሱ ማሰብ ይብስ ነፍሴን ያቀጭጫታል....
ስለ እነርሱ ትቼ ስለ ሆሄያቱ ባሰላስል ሳይሻል አይቀርም ብዬ ወደ ቀደመው ነገሬ ተመለስኩ...
"ትናንት"....ላይ ሆሄያት በዙ..."ዛሬ"...እና "ነገ" ላይ ግን አነሱ....ለዛም ነው ትናንቴ የተጣበቀብኝ የሚል ድምዳሜ ላይ ከመድረሴ አንድ የቴሌዥጅን ማስታወቂያ ከጭውውቴ አባነነኝ.......
"ከብዛት ጥራት እንዲሉ የተለያዩ እቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ...."....እያለ የሚጀምር ማስታወቂያ ነው...."ከብዛት ጥራት...."....ጋር ቀረሁ....ትናንት ሆሄው ስለበዛ "ጌታ" ዛሬ ደግሞ ሆሄው ስላነሰ "ባሪያ" አይደሉም አልኩት ለራሴ....
አንዳንዴ ፈጣሪ በምን በኩል አድርጎ ወደ እቅፉ እንደሚመልስ አይታወቅም አይደል....አዎ ካልጠራ ትናንቴ የጠራው ዛሬን ሊያኖረኝ ቢሆንስ... በቁስሌ በኩል አይቶኝ ቢሆንስ.....የፈራሁት ቁስሌን እርሱው እየፈታው ቢሆንስ.....በራሱ መንገድ እያደሰኝ ቢሆንስ...
እንዲያድሰኝ መፍረስ ግድ ከሆነስ....እንኳን አመመኝ....😊
✍Shewit
https://t.me/shewitdorka