ዝክረ ቅዱሳን ዘወልደ ዋህድ


Channel's geo and language: not specified, not specified
Category: not specified



Channel's geo and language
not specified, not specified
Category
not specified
Statistics
Posts filter


Video is unavailable for watching
Show in Telegram
የ3 ደቂቃ መልእክት ናት እባካችሁ አድምጡት።










❤ "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤

❤ ጥቅምት ፫ (3) ቀን።

❤ እንኳን ለእስክንድርያ ለአባቶች ሊቃነ ጳጳሳት ሃምሳ አንተኛ ለሆነ ሊቀ ጳጳሳት ለአባ ስምዖን ለዕረፍት በዓል፣ ለሐዲስ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ለምስክርነቱ መታሰቢያ በዓልና ለታላቁ ቴዎዶስዮስ ልጅ ለሆነ ለንጉሥ አርቃድዮስ ለወለዳት ለቅድስት ታኦድራ ለመታሰቢያ በዓል በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከኒኀዋ ከወገን ከነገዱ ከመቃርስና ታኦፊላ፣ ከአውመራና ከአርማንያ ሊቀ ጳጳሳት ከአባ ጎርጎርዮስ ከመታሰቢያቸው እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።

+ + +
❤ የእስክንድርያ ሃምሣ አንደኛ ሊቃነ ጳጳሳት አባ ስምዖን፦ ይህም አባት ከእስክንድርያ ከታላላቆች ተወላጅ የሆነ ወላጆቹም ሃይማኖታቸው የቀና ነው እርሱም ከታናሽነቱ የሃይማኖት ወተትን ጠጥቶ አደገ ስለዚህም የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ተማረ።

❤ የምንኵስናንም ልብስ ሊለብስ በልቡ አስቦ ወደ አስቄጥስ ገዳም በመሔድ ከእርሱ አስቀድሞ ሊቀ ጳጳሳት በሆነ በአባ ያዕቆብ ገዳም መነኰሰ በየጊዜው በሚጨመር ተጋድሎም ሥጋውን እያደከመ አብዝቶ በመጋደል በእርሱ ዘንድ ኖረ። ዳግማዊ አባ ማርቆስም ሊቀ ጵጵስና በተሾመ ጊዜ ይህን አባ ስምዖንን ስለ በጎ ተጋድሎውና ስለ አገልግሎቱ ከአባ ያዕቆብ ዘንድ ወሰደው እያገለገለውም ከእርሱ ጋር ኖረ። አባ ማርቆስም በዐረፈ ጊዜ አባ ያዕቆብ ተሾመ ያን ጊዜም እያገለገለው ከአባ ያዕቆብ ጋር ኖረ።

❤ ከዚህም በኋላ አባ ያዕቆብ በዐረፈ ጊዜ ብዙዎች ካህናትና ኤጲስቆጶሳት የሀገር ታላላቆች ሁሉም ይህን አባት አባ ስምዖንን መረጡት። ትሩፋቱንና የአማረ ሥራውን በእነዚህ በሁለቱ ሊቃነ ጳጳሳት ዘንድ በነበረበት ጊዜ ስለተመለከቱ አምላካዊ ፍቅር አነሣሥቷቸዋልና በወንጌላዊ ማርቆስ መንበር ላይ ይዘው ሊቀ ጵጵስና ሾሙት።

❤ ከዚህም በኋላ በሹመቱ ጸንቶ መልካምን ጉዞ ተጓዘ እግዚአብሔርንም አገለገለው የሃይማኖትንም ሕግ በማስጠበቅ የክርስቶስን መንጋዎች ጠበቀ። በሹመቱ ወራትም ቤተ ክርስቲያን በጸጥታና በሰላም ኖረች።

❤ ከዚህም በኋላ እግሮቹን በጽኑዕ ደዌ ታመመ ፈጣሪ እግዚአብሔርንም ከዚህ ደዌ ያሳርፈው ዘንድ ለመነው። ክብር ይግባውና ጌታችንም ልመናውን ተቀብሎ በሰላም በፍቅር አንድነት አሳረፈው የሹመቱ ወራትም አምስት ወር ከዐሥራ አምስት ቀን ነው። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ስምዖን ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።

+ + +
❤ "ሰላም እብል ለብፅዕት ታኦድራ። ወለተ አርቃድዮስ ንጉሥ ለማርያም ፍቁራ። ዘበቃላ ጥዕምት ወሠናይት በምግባራ። ኀበ ተዓየኑ ጉባኤ ቅዱሳን ማኅበራ። ዘክሮተነ ኢትፍልጥ እምዝክራ"። ሊቁ አርከ ሥሉስ አርኬ የጥቅምት 3።

+ + +
❤ የዕለቱ የማኅሌት ምስባክ፦ "ተከልከ ሥርዊሃ ወመልዕተ ምድረ። ወከደነ አድባር ጽላሎታ። ወአእፁቂሃኒ ከመ አርዘ ሊባኖስ"። መዝ 79፥9-10። የሚነበበው ወንጌል ዮሐ 15፥1-12።

+ + +
❤ የዕለቱ የቅዳሴ ምስባክ፦ "አዋልደ ንግሥት ለክብርከ። ወትቀውም ንግሥት በየማንከ። በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኊብርት"። መዝ 44፥9። የሚነበቡት መልዕክታት ቲቶ 2፥1-9፣ 1ኛ ጴጥ 5፥2-5 እና የሐዋ ሥራ 16፥8-16። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 20፥28-31። የሚነበበው ወንጌል ሉቃ 10፥38-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ የሠለስቱ ምዕት ቅዳሴ ነው። መልካም የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የጽንሰት በዓልና የጾም ጊዜ ለሁላችንም ይሁንልን።









❤ የአባ ጊዮርጊስ ሌላው ተማሪ የነበረው ዐፄ ይስሐቅ በ1399 ዓ.ም መንግሥቱን ሲይዝ አባ ጊዮርጊስን ከግዞት አውጥቶ ወደ ጋሥጫ መለሰው፡፡ በዚያ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ እድሜው 42 ዓመት ሲሆን በስደትና በጤንነት መታወክ የተነሣ ከባድ ጉዳት ደርሶበት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜውን በጾም፣ በጸሎትና በድርሰት ያውለው ነበር፡፡ አንድ ቀን ቴዎድሮስ የተባለ መስፍን፣ ዳግመኛም የጦሩ አዛዥ የሚሆን፣ አባ ጊዮርጊስን ስለ ርትዕት ሃይማኖት በጠየቀው ጊዜ አባ ጊዮርጊስም "ፍካሬ ሃይማኖት" የተባለውን መጽሐፍ ደርሶ ሰጠው፡፡ ንጉሡና የምሥጢር ሊቃውንት የሆኑ ካህናት ይህንን በተመለከቱና ባነበቡ ጊዜ "በእውነት ዮሐንስ አፈወርቅና አፈ በረከት የሆነው ቄርሎስ በዘመናችን ተነሥተዋል፡፡ ኢትዮጵያም ቍስጥንጥንያን መስላለች፣ ከእስክንድርያም በላይ ከፍ ከፍ ብላለች" ብለው አደነቁ፡፡

❤ ይህም ፍካሬ ሃይማኖት የተሰኘው ድንቅ ድርሰቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምታምነውንና የምታወግዘውን በግልጽና በዝርዝር የጻፈበት መጽሐፍ ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስ በፍካሬ ሃይማኖት ድርሰቱ ላይ የዘረዘራቸው የመናፍቃን ስሞችንና ክህደታቸውን ስንምለከት በዘመኑ የነበሩ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ስለ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ያላቸውን ዕውቀት በግልጽ ያሳየናል፡፡ አባ ጊዮርጊስ መከራ ያልተለየው አባት በመሆኑ አሁንም በቤተ መንግሥት የነበሩ ሰዎች የእርሱን መከበርና መወደድ አይፈልጉትም ነበር፡፡ በተለይም "ፍካሬ ሃይማኖት" የተሰኘውን መጽሐፍ በመጻፉ በዚህም ዝናው የበለጠ ስለተነገረ እነርሱ በሁሉም ዘንድ መከበሩን አልወደዱትም ነበር፡፡ ስለዚህም ነገር ሠርተው ከዐፄ ይስሐቅ ጋር አሁንም አጣሉት፡፡

❤ ዐፄ ይስሐቅ አባ ጊዮርጊስን አሳስሮ ውኃ ወደማይገኝበት ዓለታማ ቦታ አጋዘው፡፡ በዚያም በመከራ ለብዙ ጊዜ ኖረ፡፡ በዚያ እያለ ዘወትር በጸሎት አብዝቶ ይተጋ ነበር፡፡ እግዚአብሔርም ዐፄ ይስሐቅ ወደ ልቡናው እንዲመለስ አደረገ፡፡ ንጉሡ በአባ ጊዮርጊስ ላይ የፈጸመው ነገር ሁሉ ስለፀፀተው አገልጋዮቹን ጠርቶ አባ ጊዮርጊስን እንዲያመጡት አዘዘ፡፡ ነገር ግን እነዚያ ተንኮል ሠሪዎች የአባ ጊዮርጊስ መምጣት ተንኮላቸውን ስለሚያጋልጠው "አባ ጊዮርጊስ ሞቷል" ብለው አስወሩ፡፡ ይህንን ሲሰማ ዐፄ ይስሐቅ ፈጽሞ አዘነ፡፡

❤ አባ ጊዮርጊስም ሞቷል እየተባለ መወራቱን ከደቀ መዝሙሩ ስለ ሰማ በሕይወት የመኖሩን ዜና ጽፎ ለዐፄ ይስሐቅ እንዲያደርስለት መልእክቱን በአውሎ ንፋስ አሳስሮ ላከለት፡፡ አውሎ ንፋሱ ለአባ ጊዮርጊስ በመታዘዝ ደብዳቤውን ተሸክሞ በመሄድ ዐፄ ይስሐቅ በድንኳን ተቀምጦ በነበረ ጊዜ ጉልበቱ ላይ አስቀመጠው፡፡ ንጉሡ ምትሐት የተሠራበት ስለመሰለው ደነገጠና መኳንንቱንና ሕዝቡን ሰብስቦ ጉዳዩን ገለጠ፡፡ ወዲያውም ነፋሱ ያመጣለትን መልእክት እሳት አስነድዶ ከዚያ ውስጥ ቢጥለው ሊቃጠል አልቻለም፡፡ ወደ ውኃም ቢጨምረው አልጠፋም፡፡ በዚህ ተደንቆ ወረቀቱን ከፍቶ አነበበው፡፡ ደብዳቤው ከአባ ጊዮርጊስ የተላከ መሆኑን ሲያውቅ ዐፄ ይስሐቅ ደነገጠ፡፡ እነዚያን መልእክተኞች ይዞ ወደ ወኅኒ ከጨመራቸው በኋላ አባ ጊዮርጊስን ከግዞት ያወጡት ዘንድ ላከ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ወደ ቤተ መንግሥቱ ሲመጣ ንጉሡ በደስታ ተቀብሎ ማረኝ ብሎ ለመነው፡፡ አባ ጊዮርጊስም ይቅር አለው፡፡ ከዚህም በኋላ ደብዳቤውን በማን እጅ እንደ ላከው ጠየቀው፡፡ አባ ጊዮርጊስም ደብዳቤውን በሰው ሳይሆን በእግዚአብሔር ፈቃድ በነፋስ እንደ ላከው አስረዳው፡፡

❤ አባ ጊዮርጊስ ከግዞት ከተመለሰ በኋላ እመቤታችን ተገልጣለት መከራው ሁሉ እንደ ሐዋርያት መሆኑን ገለጠችለት፡፡ አእምሮውን ብሩህ፣ ልቡናውን ትጉኅ የሚያደርግ እጅግ ብዙ ምሥጢርም ነገረችው፡፡ ተሰናብታው ከሄደች በኋላ "እጅግ ብዙ መብራት አቅርቡ አምስት ፈጣን ጸሐፊዎችንም አምጡ" ብሎ አዘዘ፡፡ ከዚህም በኋላ እርሱ እየነገራቸው እነርሱ እየጻፉ እረፍት ሳያደርጉ ሦስት ቀን ሙሉ አጽፎ "መጽሐፈ ምሥጢር" የተሰኘውን መጽሐፍ ፈጸመ፡፡ አምስቱ ጸሐፍትም የየድርሻቸውን አጠናቅቀው በአንድ አደረጉት፡፡ አባ ጊዮርጊስም ይህን ተመልክቶ በእጅጉ አደነቀ፡፡ "እኔ የዚህን መጽሐፍ ቃል አልተናገርኩም፤ መንፈስ ቅዱስ በእኔ አፍ ተናገረ እንጂ" ሲል በወቅቱ መስክሯል፡፡ የመጽሐፉንም ስም "መጽሐፈ ምሥጢር" ብሎ የሰየመው ራሱ ነው፡፡ የጻፈው በ1409 ዓ.ም እድሜው 52 በደረሰ ጊዜ ሲሆን በወቅቱም የዚህ መጽሐፍ ቅጅ በነጋድያን እጅ እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ ሄዶ ነበር፡፡

❤ ዐፄ ይስሐቅ ለአባ ጊዮርጊስ "ምድረ ሰዎን" የተባለውን የጳጳሳት መቀመጫ የነበረውን ሀገር በርስትነት ሰጥቶት ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ በምድረ ሰዎን ንጉሥ ይስሐቅ ክረምቱን ያሳልፍበት በነበረው ቦታ ላይ ቤተ ክርስቲያን ሠራ፡፡ በዚያም በማስተማርና በጾም በጸሎት ይተጋ ነበር፡፡ በጋሥጫ እያለ ዐፄ ይስሐቅ አስጠራው፡፡ በዚያ ጊዜ ንጉሡ የመናገሻ ማርያምን ቤተ ክርስቲያን አሠርቶ ስለነበር እንዲባርክለት ፈልጎ ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ ምንም እንኳን በዚያ ጊዜ ታሞ የተኛም ቢሆን ወደ ንጉሡ ተጓዘ፡፡ እዚያ ሲደርስ በጣም ተዳክሞ ነበር፡፡ ሥርዓቱን ለመፈጸምም አቅም አልነበረውም፡፡ ስለዚህም ንጉሥ ይስሐቅ በአልጋ ተሸክመውት እንዲዞሩና ቤተ ክርስቲያኗን እንዲባርካት አድርጓል፡፡ ቡራኬውን ከፈጸመ በኋላ ደቀ መዝሙሮቹን ሰብስቦ "ከሞትኩ አባቴ በጸሎተ ሚካኤል መከራ ወደ ተቀበለባትና እኔም ቤተ ክርስቲያን ወዳነፅኩባት ቦታ ወስዳችሁ ቅበሩኝ" ሲል አዘዛቸው፡፡ ለደቀ መዛሙርቱ በቀናች ሃይማኖት እንዲጸኑ የመጨረሻ የስንብት ትምህርቱን አስተማራቸው፡፡ እነርሱም በአልጋ ተሸክመውት ወደ ጋሥጫ እያመሩ ሳለ በመንገድ ላይ ሐምሌ 7 ቀን 1417 ዓ.ም በ60 ዓመቱ ዐረፈ፡፡ ከአባታችን ከአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎቱ ይማረን!። ምንጭ፦ መዝገበ ቅዱሳን።


እንደማይቀር አመላካች ነው፡፡

❤ የመጀመርያውን ድርሰቱን አርጋኖንን እመቤታችን አብዝታ ስለወደደችለት ዚማት በሚባለው ሀገር በነበረ ጊዜ "ከድርሰቶችህ ሁሉ እንደ አርጋኖን የምወደው የለም" ብላዋለች፡፡ ከዚህ በኋላ የደረሰው ድርሰት ውዳሴ መስቀል ይባላል፡፡ ቀጥሎም መጽሐፈ ስብሐት ዘመዓልት ወዘሌሊት የተባለውን ወይም እርሱ ራሱ መጽሐፈ ብርሃን ብሎ የሰየመውን መጽሐፍ አዘጋጅቷል፡፡ መጽሐፉም የእግዚአብሔርን የምስጋናውን መንገድ ያበራል፣ አብርቶ ያመለክታልና፣ ልዑላነ ብርሃን የሆኑትን የማኅበረ ቅዱሳንንና የትጉኃንን የምስጋናቸውን መንገድ ያመለክታልና፣ የእመቤታችንንም የምስጋናዋን ጣዕም ይገልጣልና መጽሐፉ "መጽሐፈ ብርሃን" ተባለ፡፡ በዘመኑ በነበረው ልማድ ካህናቱ ቍርባን በሚያቀብሉ ጊዜ ሕዝቡ ወደ ካህናቱ መጥተው ሲቀበሉ ንግሥቲቱ ግን ካለችበት ድረስ ካህናቱ ሄደው ነበር የሚያቆርቧት፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን "ይህ ቁርባን ንጉሠ ነገሥት ነውና ንግሥቲቱ ወደዚህ መጥታ ልትቀበል ይገባታል እንጂ እኛ መሄድ የለብንም" ሲል ተቃወመ፡፡ ይህ ነገር ንግሥቲቱንና አባ ጊዮርጊስን ስላጋጫቸው ዐፄ ዳዊት ችግሩን ለመፍታት አባ ጊዮርጊስን ወደ ሀገረ ዳሞት ንቡረ እድነት ሾሞ ላከው፡፡

❤ ከዚህ በኋላ አባ ጊዮርጊስ ዋናው ትኩረቱ በድርሰቱ ላይ በማድረግ ወደ ጳጳሱ ወደ አቡነ በርተሎሜዎስ ዘንድ በመሄድ የቅዳሴ ድርሰት ለመድረስ እንዲፈቀድለት ጠይቆ ሲፈቀድለት የቅዳሴ ድርሰት ማዘጋጀት ጀመረ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ነገረ ሃይማኖትን ጠንቅቆ የተረዳና የሚያስረዳ ስለነበር በዘመኑ የተነሡ የሃይማኖት ክርክሮች ሁሉ እርሱ ከሌለ አይሳኩም ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ በሸዋ በይፋት ራሳቸውን ቤተ እስራኤል እያሉ የሚጠሩ አይሁድ ነበሩ፡፡ ከአቡነ ዜና ማርቆስ ጀምሮ ብዙ መምህራን ወደነዚህ ሕዝቦች እየተሠማሩ ወንጌልን አስተምረዋል፡፡ አቡነ ዜና ማርቆስ ወደ ክርስትና ለተመለሱት ቤተ እስራኤላውያን በእመቤታችን፣ በቅዱስ ሚካኤል፣ በአባ ኖብና በሰማዕቱ በጊጋር ስም አራት አብያተ ክርስቲያናትን አሠርተው ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ቢሆንም ቤተ እስራኤላውያኑ ሙሉ በሙሉ ወደ ክርስትና አልተመለሱም ነበር፡፡

❤ ከእነዚህ አይሁድ መካከል አንዱ ከክርስቲያኖች ጋር በነገረ ሃይማኖት ለመከራከር ጥሪ አቀረበ፡፡ "ክርስቲያኖች ከረቱኝ ወደነርሱ ሃይማኖት እገባለሁ እኔ ከረታኋቸውም ወደኔ ሃይማኖት ይገባሉ" ሲል ነገሩን ጥብቅ አደረገው፡፡ ዐፄ ዳዊት ይህን ጉዳይ ሲሰማ በጣም ስለ ተናደደ ሊቃነ ካህናቱን፣ ንቡራነ እዱንና የመጻሕፍት ዐዋቂዎችን ሁሉ ከየሀገሩ እንዲሰባሰቡ አዘዘ፡፡ ነገር ግን በዚህ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ ታሞ አልጋ ላይ ነበር፡፡ አይሁዳዊው በአንድ ወገን መምህራኑ በአንድ ወገን ሆነው ክርክሩን ጀመሩ፡፡ የመጀመርያው እድል የተሰጠው ለአይሁዳዊው በመሆኑ ቀጥሎ ያለውን ጥያቄ አቀረበ፡- "እናንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነው የምትሉት ይሄ ክርስቶስ እውነት የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ፣ ወደ ቢታንያ በመጣ ጊዜ አልዓዛር የተቀበረበትን ቦታ ሳያውቅ ቀርቶ "አልዓዛርን የት ቀበራችሁት?" ብሎ እንደ ጠየቀ በወንጌላችሁ ተጽፏል፡፡ ለዚህ መልስ ስጡኝ፣ እኔንም ከመጽሐፈ ኦሪቴ ጠቅሳችሁ ጠይቁኝ?" ሲል የመከራከርያ ነጥቡን አቀረበ፡፡

❤ ሊቃውንቱም በዚህ ጊዜ ታሞ አልጋ ላይ የነበረውን አባ ጊዮርጊስን እንዲመጣላቸው ፈልገው "እንዲህ ያለው ነገር ያለ እርሱ አይሆንምና አባ ጊዮርጊስ ይምጣ" ሲሉ ለዐፄ ዳዊት ጥያቄ አቀረቡ፡፡ አባ ጊዮርጊስም በአልጋ ላይ እያለ እንዲመጣ ተደርጎ በአልጋ ላይ ሆኖ በጉባኤው ላይ ተገኘ፡፡ ጉባኤተኞቹ የቀረበውን ጥያቄ በነገሩት ጊዜ አባ ጊዮርጊስ የሰጠውን መልስ እንዲህ የሚል ነው፡- "እኔ ግን በወንጌል ሳይሆን በኦሪት እከራከርሃለሁ፡፡ የምኩራብ መጻሕፍት ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን የታወቁ ናቸውና፡፡ ምኩራብ ዘራች ቤተ ክርስቲያንም አጨደችው፤ ምኩራብ ፈተለችው ቤተ ክርስቲያን ለበሰችው፤ አዳምን በገነት ሳለ አዳም ሆይ ወዴት ነህ? ብሎ የጠየቀው ማነው? አብርሃምንስ ሚስትህ ሣራ ወዴት ናት? ብሎ የጠየቀው ማነው? እስቲ መልስልኝ? ሰይጣንንስ ከወዴት መጣህ? ብሎ የጠየቀው ማነው? እግዚአብሔር አብ አይደለምን?" እያሉ የጥያቄ ዓይነት ባሽጎደጎዱለት ጊዜ አይሁዳዊው መልስ አጥቶ ዝም አለ፡፡ መልስ በማጣቱም አፈረ፡፡ ንጉሡ፣ ሊቃውንቱና መኳንንቱም እጅግ ተደሰቱ፡፡

❤ አባ ጊዮርጊስ ሌላው ያጋጠመው ክርክር ቢቱ ከተባለው ሰው ጋር ያደረገው ክርክር ነበር፡፡ ቢቱ "በምጽዓት ጊዜ የሚመጣው ወልድ ብቻውን እንጂ አብና መንፈስ ቅዱስ አይመጡም" የሚል ኑፋቄ ማስተማር ጀምሮ ነበር፡፡ ቢቱ ከዚህ ኑፋቄው በተጨማሪ የጥንቆላ ሥራም ይሠራ ነበር፡፡ ቢቱ በጥንቆላ ሥራው የተነሣ በቤተ መንግሥቱ ተቀባይነት የነበረው ሰው ነበረ፡፡ ይህን መሰሉን ተግባር አጥብቆ የተዋጋው ዘርዐ ያዕቆብ እስኪመጣ ድረስ ነገሥታቱ ምንም ክርስቲያኖች ቢሆኑ በዚህ መሰሉ ስንኩል ሕፀፅ ይዋጡ ነበር፡፡ ቢቱና አባ ጊዮርጊስ ወደ ንጉሥ ዳዊት ቀርበው በጉዳዩ ላይ መነጋገር እንደሚፈልጉ ገለጡ፡፡ ዐፄ ዳዊትም ጳጳሱና ሊቃውንቱ ባሉበት እንዲነጋገሩ ስለወሰነ ጳጳሱ እንዲመጡ አዘዘ፡፡ በዚህ ጊዜ ተንኮለኛው ቢቱ ከአባ ጊዮርጊስ ጋር ከተከራከረ እንደሚሸነፍ ስላወቀ "ንጉሡ የአባቶቻችንን ሃይማኖት ክዷልና አትምጣ" የሚል ደብዳቤ በአባ ጊዮርጊስ ስም ጽፎ ጳጳሱን ሊጠሩ በሄዱት መልእክተኞች እጅ ላከ፡፡ ወድያውም ለዐፄ ዳዊት ይህንን ነገር አሳበቀ፡፡ ዐፄ ዳዊትም ፈጣን መልእክተኞች ልኮ የፊተኞቹ መልእክተኞች እንዲመለሱ አደረገና ደብዳቤው ተነበበ፡፡ የቢቱ ተንኮል ያልገባው ንጉሥ ዳዊት ይህን ደብዳቤ ሲመለከት አባ ጊዮርጊስን በደም እስኪነከር ድረስ እንዲደበደብ አድርጎ ወደ እስር ቤት አስገባው፡፡

❤ ዐፄ ዳዊት እስኪሞትና ልጁ ቴዎድሮስ እስኪነግሥ ድረስም በዚያ ቆየ፡፡ ቢቱ ግን በመልአክ ተቀስፎ ሞተ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን በወኅኒ ቤት እያለ የከበሩ ቅዱሳን ሐዋርያት ጴጥሮስና ጳውሎስ እየመጡ ያጽናኑት ነበር፡፡ "ውዳሴ ሐዋርያት" የተሰኘውንና ከሐምሌ 5 ጀምሮ በ12ቱም ወራት የሚመሰገኑበት የሐዋርያትን ምስጋና የያዘውን መጽሐፍ ያዘጋጀው በወኅኒ ቤት ሆኖ ጴጥሮስና ጳውሎስ ከጎበኙት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡

❤ አንድ ጊዜ አባ ጊዮርጊስ በእስር ላይ ሳሉ ንጉሡ ዐፄ ዳዊት መሞታቸው ተሰማ፡፡ ሰዎችም ወደ አባታችን መጥተው "ያሳሰረህ ንጉሥ ሞቷል" በማለት ነገሩት፡፡ ይህንንም ተቻኩለው የነገሩት ያሰረው ንጉሥ መሞቱን ሲሰማ ይደሰታል ብለው ነበር፡፡ ነገር ግን አባ ጊዮርጊስ በታላቅ ሀዘን ውስጥ ሆኖ የሰጣቸው መልስ "አይ ንጉሡ ባይሞት እኔም እንደታሰርኩ ብቀር ይሻል ነበር፡፡ ንጉሡ ዐፄ ዳዊትኮ እኔን ባይወደኝ የአምላክን እናት እመቤታችንን ይወዳት ነበር" አላቸው፡፡

❤ ዐፄ ቴዎድሮስ አባ ጊዮርጊስን ከወኅኒ ቤት አውጥቶት በጥንቱ ቦታ አስቀመጠው፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን የቤተ መንግሥትን ነገር ለመሸሽ ስለ ፈለገ በጋሥጫ ከመቀመጥ ይልቅ ርቆ ጥንት ወደ ነበረበት ወደ ዳሞት በመሄድ ማስተማር ጀመረ፡፡ ወደ ዳሞት ሲሄድ እግረ መንገዱን ወደ ደብረ ሊባኖስ ገብቶ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን መቃብር ተሳልሟል፡፡ በዚያ ጊዜ የደብረ ሊባኖሱ አበ ምኔት እጨጌ ዮሐንስ ከማ ነበሩ፡፡ እርሳቸውም ሰባተኛው የደብረ ሊባኖስ እጨጌ ነበሩ፡፡ አባ ጊዮርጊስን በዕውቀቱ የሚቀኑበት፣ በችሎታው የሚመቀኙት ሰዎች ነገር ሠርተው ከንጉሥ ቴዎድሮስ ጋር ስላጣሉት እልም ካለ በረሃ እንዲጋዝ ተደረገ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ከግዞት የወጣው ዐፄ ቴዎድሮስ ሲሞት ነበር፡፡


አምስቱንም ቃላት በልቡ መዝገብነት ሰወራቸው፤ ሊገልጣቸው እግዚአብሔር አልፈቀደላትምና በተረዳ ነገር ግን መዝሙረ ዳዊት ነው፡፡ የገነትን ፍሬዎች ሁሉ የሰበሰበ መዝሙረ ዳዊት የገነት አምሳል ነውና አጋንንትን ያሳድዳል መላእክትንም ያቀርባል፡፡ እመቤታችንም ከእርሱ ተለይታ ካረገች በኋላ ከዚያችም ሰዓት ጀምሮ የልቡ ዓይን ተከፈተለት፡፡ ኅሊናውም በመንፈስ ቅዱስ ክንፎች ተመሰጠ፡፡ ወደ አብም ደረሰ፤ በዚያም ኢየሱስን በአባቱ ቀኝ ተቀምጦ ጰራቅሊጦስንም በአንድ አኗኗር አገኘው፡፡

❤ ከዚህ በኋላ በሐይቅ እስጢፋኖስ የዜማ የቅኔና የመጻሕፍትን ትርጓሜ ትምህርቱን በሚገባ ተምሮ አጠናቀቀ፡፡ በዕውቀቱም ቀድሞ የሚያውቁት ሁሉ ይደነቁበት ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ የያሬድን ዜማ ከአቡነ ሳሙኤል ተማረ፡፡ በዚያ ዘመን በዐፄ ዳዊት አማካይነት በሰሜን ኢትዮጵያ የያሬድ ድጓ ዋና ማዕከል በሆነው በደብረ ነጎድጓድ ተሾሞ ያስተምር ነበር፡፡ የማስተማር ሥራውን የጀመረው በዚያው በሐይቅ እስጢፋኖስ ነበር፡፡

❤ ከሐይቅ በኋላ በዚያ ዘመን ሸግላ በመባል ትጠራ ወደ ነበረችው ወደ ትውልድ ሀገሩ ወደ ጋሥጫ ተጓዘ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ወደ ሸግላ ሲመጣ አባቱ በጣም አርጅቶና መንኲሶ ነበር፡፡ ስለዚህም በአባቱ እግር ተተክቶ በቤተ መንግሥቱ ያለችውን ሥዕል ቤት እንዲያገለግል ወደዚያው አስገቡት፡፡ በቤተ መንግሥቱም የንጉሡን ልጆች ከማስተማሩም በላይ በቤተ መንግሥቱ ዙርያ ከነበሩት ሊቃውንት መካከል አባ ጊዮርጊስ አንዱ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ግብፃዊው ጳጳስ አቡነ በርተሎሜዎስ "ሥላሴን አንድ ገጽ" ብለው ያምናሉ ተብለው በተከሰሱ ጊዜ ነገሩን እንዲያጣሩ ከተመረጡት ከቄስ ዐፄ ተከሥተ ብርሃንና ከሐይቁ መምህር ከዐቃቤ ሰዓት ዮሴፍ ጋር አብሮ ተልኮ ነበር፡፡ እነዚህ ሦስት አበው ጳጳሱን ካነጋገሩ በኋላ ክሱ ውሸት መሆኑን በማረጋገጥ ስለ ምሥጢረ ሥላሴ የሚገልጠውን የጳጳሱን እምነት በጽሑፍ ይዘው መጡ፡፡

❤ በቤተ መንግሥቱ በነበረ ጊዜ የንጉሡን ልጆች ይስሐቅን፣ ቴዎድሮስን፣ እንድርያስን፣ ሀብተ ኢየሱስን፣ ሕዝቅያስን፣ ኢዮስያስን፣ ዘርዐ ያዕቆብንና ሴት ልጁን እሌኒን በምግባርና በሃይማኖት ቀርጿቸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ዘርዐ ያዕቆብ በድርሰቱ ሲመስለው ቴዎድሮስ ደግሞ በሕይወት መስሎታል፡፡ ዐፄ ዳዊት የአባ ጊዮርጊስን ሊቅነትና መልካም ሥነ ምግባር በሚገባ ስላወቀ በጋብቻ ሊዛመደው ወዶ ስለነበር ልጁን እንዲያገባ ዘወትር ይጠይቀው ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን በድንግልና ጸንቶ ለመኖር እንደሚፈልግ ከመግለጽ አልተቆጠበም፡፡ የዐፄ ዳዊት ጥያቄ ስለበዛበት ወደ አቡነ በርተሎሜዎስ ሄዶ ቅስናን ከተቀበለ በኋላ ወዲያው መነኰሰ፡፡

❤ ከመነኰሰ በኋላ ወደ ሸግላ በመምጣት ለነገሥታትና በቤተ መንግሥቱ ለነበሩ ካህናት እንዲሁም በቤተ መንግሥቱ ለነበሩ ታላላቆች፣ ለንቡራነ እድና ለመኳንንት፣ ለመሳፍንትና በቤተ መንግሥቱ ለነበሩ ባለሟሎች ሁሉ መምህር ሆነ፡፡

❤ አባ ጊዮርጊስ በሸግላ በነበረ ጊዜ በወባ በሽታ ታምሞ ሊሞት ደርሶ ነበር፡፡ ታምሞ በነበረ ጊዜ አንድ ሌሊት የከበሩ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ጳውሎስ ተገልጠውለት "ከእኛ ጋር ትኖር ዘንድ ልንወስድህ መጣን" አሉት፡፡ እርሱም "የድርሰት ሥራዬን ሳልሠራና እግዚአብሔርንም አብዝቼ ሳላመሰግነው አሁን አትውሰዱኝ" ሲል ለመናቸው፡፡ እነርሱም ልመናውን ተቀብለውት ከሕመሙ ፈውሰውት ሄዱ፡፡ ለዚህም ነው ከበሽታው እንደ ተፈወሰ ወድያው የድርሰት ሥራውን የጀመረው፡፡ የመጀመርያ መጽሐፉን ጽፎ እንደ ጨረሰ ጠፍቶበት ነበር፡፡ በማግሥቱ በዚያው ላይ ሊጨምር በወደደ ጊዜ የተጻፈበት ጥራዝ ቀለሙ ጠፍቶ ነጭ ሆኖ አገኘው፡፡ ስለዚህም የተሰረቀ መስሎት ልቡ አዘነ፡፡ የተስተካከሉ ጥራዞችንም በቈጠረ ጊዜ ደኅና ሁነው አገኛቸው ሁለተኛም በድጋሚ ጻፈ፡፡ በማግሥቱም እንደ መጀመሪያው ነጭ ሁኖ አገኘው እስከ ሦስትና ዐራት ቀንም እየተደጋገመ እንዲሁ ሆነ፡፡

❤ ከዚህ በኋላ አባታችን ወደ እመቤታችን ይጸልይ ጀመረ፡፡ "ይህ የሆነ በኃጢአቴ ነውን? ወይስ አይደለም? ግለጭልኝ" አላት፡፡ አንድ ቀንም በሌሊት እኩሌታ ወደ ቤተ ክርስቲያን ለጸሎት ሲሄድ እመቤታችን በድንገት በማይነገር ክብር ለጊዮርጊስ ተገለጠችለት፡፡ ከእርሷም ጋር የቅዱሳን ማኅበር ሁሉ ነበሩ፡፡ በእጇም ከፀሐይና ጨረቃ የበለጠ የሚያበራ መጽሐፍን ይዛ ነበር፡፡ ጊዮርጊስም ባየ ጊዜ ወደ መሬት ወደቀ፡፡ እንደ በድንም ሆነ፡፡ እመቤታችንም አነሣችውና "ሳትጠይቀኝ መጽሐፌን ትጽፍ ዘንድ ለምን ደፈርህ?" አለችው፡፡ "እኔ ወድጄህ ከእናትህስ ማኅፀን መርጬህ ለጴጥሮስ፣ ለጳውሎስና ለዮሐንስ አደራ ሰጥቼህ የለምን?" አለችው፡፡ አባ ጊዮርጊስም "እመቤቴ ሆይ ይቅር በይኝ፣ ደስ የሚያሰኝሽ መስሎኝ ይህን ባለማወቅ ሠርቼዋለሁና" አላት፡፡ እመቤታችንም "ወዳጄ ሆይ ይቅር ብየሃለሁ" አለችው፡፡ "ልትጽፈው የወደድኸው መጽሐፍም እነሆ በእጄ አለ፣ ከአሁን በኋላ የተወደደ ልጄ በአንደበትህ ሊገልጸው ወዷል፡፡ ነገር ግን ከአርያም ከሰማይ ኀይልን እስክትለብስ ድረስ አትቸኩል"፡፡ ይህንም ብላው ከእርሱ ተሰወረች፡፡ ያን ጊዜም ልቡ እንደ ፀሐይ በራ፣ የመለኮትም ባሕር በኅሊናው አበራ፡፡ በመንፈስ ቅዱስም መስተዋትነት የተሰወረውን ሁሉ አየ፡፡

❤ የመጀመርያው ድርሰቱ አርጋኖን የተሰኘውና በቅኔ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሚያመሰግነው መጽሐፉ ነው፡፡ እግዚአብሔርን በሚወድ በንጉሥ ዳዊት ዘመንም አርጋኖን መጽሐፍን ይደርስና ይጽፍ ጀመረ፡፡ በሦስትም ስሞች ጠራው እነዚህም አርጋኖና ውዳሴ፣ መሰንቆ መዝሙር፣ ዕንዚራ ስብሐት ናቸው፡፡ ስለ መጽሐፉም ጣፋጭነት ንጉሡ ዐፄ ዳዊት ድርሰቱን በጣም ከመውደዱ የተነሣ በወርቅ ቀለም አጻፈው፡፡ ወርቁን የሚያንጸባርቅበት ድንጋይ (ዕንቊ) ባጣ ጊዜ እመቤታችን ማርያም በሌሊት ራእይ ዘማት በሚባል አገር እንዳለ ለጊዮርጊስ ነገረችው ኅብሩንም አሳየችው፡፡ አባታችን ጊዮርጊስም ከደረስኳቸውና ከተናገርኋቸው ድርሳናት ሁሉ አርጋኖን ውዳሴ ይጣፍጣል ይበልጣል አለ፡፡

❤ እንደዚሁም በፈጣሪው ቸርነት በእመቤታችን ረድኤት ብዙ ድርሳናትንና የጸሎት መጻሕፍትን ደረሰ፡፡ የእሊህም ድርሳናት ስማቸውና ቁጥራቸው በሊቃውንት ዘንድ የታወቀ ነው፡፡ እሊህም ውዳሴ መስቀል፣ መጽሐፈ ብርሃን፣ መጽሐፈ ሰዓታት የመዓልትና የሌሊት፣ መጻሕፍተ ቅዳሴያት ናቸው፡፡ ጸሎተ ፈትቶ (የፍታቴ ጸሎት) የሐዋርያት ማኅሌት፣ መልክአ ቊርባን፣ እንዚራ ስብሐት፣ አርጋኖን ውዳሴ፣ ፍካሬ ሃይማኖት፣ ውዳሴ ሐዋርያት፣ ኖኅተ ብርሃን ይኸውም ከመጽሐፈ አርጋኖን ጋር አብሮ የታተመው ነው፡፡ ፍካሬ ሃይማኖት፣ መጽሐፈ ምስጢር፣ ሕይወታ ለማርያም፣ ተአምኆ ቅዱሳን፣ ጸሎት ዘቤት ውስተቤት፣ ውዳሴ ስብሐት፣ ሰላምታ፣ ጸሎተ ማዕድ፣ ቅዳሴ እግዚእ ካልእ፣ መዝሙረ ድንግልና የመሳሰለው ነው፡፡ ቅዱስ ገድሉ እንደሚናገረው የአባ ጊዮርጊስ "ድርሳናት ስማቸውና ቁጥራቸው በሊቃውንት ዘንድ የታወቀ ነው" ብሎ ከጀመረ በኋላ በቁጥር የተወሰኑትን ድርሰቶቹን ብቻ ጠቅሶ መጨረሻ ላይ "… እና የመሳሰለው ነው" ብሎ ይደመድመዋል፡፡ ሊቀ ብርሃናት መርቆሬዎስ አረጋ ደግሞ የአባ ጊዮርጊስ ድርሰቶች ከ12 ሺህ በላይ ቢሆኑም ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እየሰጡ ያሉት በጣም ጥቂቶቹ ብቻ መሆናቸውን በቅዱሳን ታሪክ መጽሐፋቸው ላይ ጠቅሰውታል፡፡ ሌሎች ሊቃውንት አባቶቻችንም የአባ ጊዮርጊስን ድርሰቶች ከግምት ባለፈ ሁኔታ በቁጥር ወስኖ ለማስቀመጥ አስቸጋሪ መሆኑን ይገልጣሉ፡፡ ይኸውም ወደፊት ራሱን የቻለ በቂና ብዙ ጥናት ማድረግ ሳያስፈልገን


❤ "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤

❤ ጥቅምት ፫ (3) ቀን።

❤ እንኳን ለታላቁ ሊቅ ከመጽሐፈ ሰዓታት ውጭ እጅግ ብዙ ድርሰቶችን ለደረሰ ፈላስፋም ጻድቅም ደራሲም መናኝ ባሕታዊም ለሆነ ድርሰቶቹንም ለቅዱሳን በነፋስ ጭኖ ይልክላቸው ለነበረ ለቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ ኩራት ለሆነ ለኢትዮጵያዊው ቄርሎስ ለአባታችን አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ለጽንሰት በዓል በሰላም አደረሰን።



+ + +
❤ ታላቁ ሊቅ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፦ አባቱ ሕዝበ ጽዮን ዘትግራይ እናቱ አምኃ ጽዮን ዘወለቃ ይባላሉ፡፡ ስለሆነም ሀገሩ ትግራይና ወሎ ቦረና ነው፡፡ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ በመባል የሚታወቀው ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በድርሰቱ ከቅዱስ ያሬድ ቀጥሎ ስሙ የሚነሣ ታላቅ መመኪያችን የሆነ ጻድቅ አባታችን ነው፡፡ አባ ጊዮርጊስ ከመናኝ ጻድቅነቱ በተጨማሪ በመላእክትም ዘንድ የተመሰከረለት ታላቅ ፈላስፋና ደራሲም ነው፡፡ በድርሰቱ ላይ ስለ ሰማይ፣ ስለ መብረቅ፣ ስለ ደመና፣ ስለ ዝናብ አፈጣጠር፣ ስለ አራቱ ዓለማትና ስለ ሰባቱ ሰማያት… በእነዚህና በመሳሰሉት በመንፈሳዊው በሚገባና እጅግ በሚያስደንቅ መንገድ ተፈላስፎባቸዋል፡፡

❤ ጻድቁ ድርሰቶቹን እርሱ ካለበት ወደ ሌላ ቦታ ለመላክ ንፋስ ይታዘዝለት ነበር፡፡ ስለ ጾምና ስለ በዓላት የደረሰውን ድርሰቱን ለሸዋው ንጉሥ ደብዳቤ ጽፎ በነፋስ ጭኖ ልኮለታል፡፡ አስደናቂ ገደሙ ወሎ ቦረና ውስጥ ይገኛል፡፡ ጋስጫ በድሮ ስሟ ደብረ ባሕርይ ትባላለች፡፡ በአጠገቡም ራሱ አባ ጊዮርጊስ የፈለፈላቸው ብዙ ዋሻዎች አሉ፡፡ ከአባ ጽጌ ድንግል ጋር ለመገናኘት እንዲያመቻቸው ብለው የሠሩት ድልድይ "የእግዜር ድልድይ" ይባላል፡፡ በእግር 5 ሰዓት የሚያስኬድ መንገድ ነው፡፡ የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ገዳም የአውሬ ሰጋጅና ባሕታዊ ያለበት አስደናቂ ገዳም ነው፡፡ በየዓመቱ የስቅለት ዕለት ቁመቱ 60 ክንድ የሆነ ዘንዶ ከመቅደሱ ወጥቶ ግብረ ሕመማት ከሚነበብበት ከአትሮንሱ ሥር ሆኖ ተጠምጥሞ እራሱን ቀና አድርጎ ሲሰግድ ውሎ ካህኑ ሲያሰናብት ማታ ተመልሶ ወደ መቅደሱ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ የተሰኘውን የዚህን ድንቅ አባታችንን ዜና ሕየወቱን በደንብ መመልከቱ ተገቢና አስፈላጊ ነው፡፡

❤ የተወለደው በ1357 ዓ.ም በወሎ ክፍለ ሀገር በቦረና ወረዳ ሰግላ በተሰኘች ቦታ ነው፡፡ የተወለደው በቅዱስ ዑራኤል አብሳሪነት ጥምቀት 3 ቀን ተጸንሰው ሐምሌ 7 ቀን ተወለዱ፡፡ ወላጆቹ አስቀድሞ ልጅ አልነበራቸውምና በስለት ነው ያገኙት፡፡ አባ ጊዮርጊስ በመጀመርያ እናቱ ፈሪሐ እግዚአብሔርን እያስተማረች በጥበብና በዕውቀት አሳደገችው፡፡ ቀጥሎም የመጀመርያውን የቤተ ክርስቲያን ትምህርት የተማረው ከአባቱ ነበር፡፡ ሊቅ የነበረው አባቱ ካስተማረው በኋላ በ 1341 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ ከመጡትና እስከ ዐፄ ዳዊት ዘመነ መንግሥት ጳጳስ የነበሩት ከአቡነ ሰላማ መተርጕም ዘንድ ወስዶ ዲቁና አሹሞታል፡፡

❤ ዲቁና ከተቀበለ በኋላ ለትምህርት ወደ ሐይቅ እስጢፋኖስ ወሰደው፡፡ አባ ጊዮርጊስ በሐይቅ እስጢፋኖስ ትምህርት አልገባው ብሎ ለሰባት ዓመታት ተቀምጦ ነበር፡፡ አብረውት የሚማሩት ተማሪዎች "ይህ ትምህርት የማይገባው ስለ ምንድን ነው? በእርሱ ኃጢአት ነው ወይስ በወላጆቹ?" ይሉት ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ የሐይቁ መምህር የነበረው ዐቃቤ ሰዓት ሠረቀ ብርሃን ለአባቱ "ልጅህ ትምህርት አይገባውምና የቤተ መንግሥት ነገር አስተምረው" ብሎ መለሰው፡፡ አባቱ ሕዝበ ጽዮን ግን "አንድ ጊዜ ለእግዚአብሔር ሰጥቼዋለሁ፤ እዚያው ገዳሙን ያገልግል" ብሎ እንደ ገና ወደ ሐይቅ ላከው፡፡

❤ አባ ጊዮርጊስ ከቀለም ትምህርቱ ይልቅ በሥራ እየደከመ የገዳሙን አባቶች ይረዳ ጀመር፡፡ በገዳሙ እንጨት ይሰብር ውኃ ይቀዳ ይልቁንም ደግሞ አብዝቶ እህል በመፍጨት ያገለግል ነበር፡፡ አባ ጊዮርጊስ እህል ይፈጭበት የነበረውን የድንጋይ ወፍጮና ንፍሮ ይቀቅልበት የነበረው የድንጋይ ትልቅ ማሰሮ አሁንም ድረስ በሐይቅ ገዳም በክብር ተጠብቀው ይገኛሉ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ግን ትምህርቱን ለመረዳት የዘገየ ሆነ፣ የእግዚአብሔር ቃልም አልገባውም ነበር፡፡ ይህም ስለ ኃጢአቱ አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ሥራና ጌትነቱ በእርሱ ላይ ይገለጥ ዘንድ ነው እንጂ፡፡ ጸጋ ያለመከራ አይሰጥምና ያለመፈተንም ማብዛት አይቻልም፡፡ ጌታችንን ዕውር ሆኖ ስለተወለደው ሕፃን ደቀ መዛሙርቱ በጠየቁት ጊዜ "ይህ ሕፃን ዕዉር ሆኖ የተወለደው በማን ኃጢአት ነው? በራሱ ነውን ወይስ በወላጆቹ?" አሉት፡፡ ጌታችንም "እርሱም አልበደለም፣ ወላጆቹም አልበደሉም፣ የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ ላይ ይገለጥ ዘንድ ነው እንጂ" አላቸው፡፡ ዮሐ 9፡1፡፡ ሐዋርያትም መንፈስ ቅዱስ እስኪወርድላቸው ድረስ በትንሽ ዕውቀት ነበሩ፡፡ "በመጻሕፍት ያለውን ገና ዐላወቁምና" ተብሎ እንደተጻፈ እንዲሁ አባ ጊዮርጊስም ዕውቀት ስለ ተሰወረውና ጓደኞቹ በትምህርት ሲቀድሙት ባየ ጊዜ እጅግ አዘነ፡፡ ስለዚህም በጾምና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር መጮኽ ጀመረ፡፡

❤ ሁልጊዜም በሥዕለ ማርያም ሥር እየተንበረከከ ጥበብን እንዲሰጠው ወደ እግዚአብሔር አብዝቶ በመለመን እንባንም በማፍሰስ ይጸልይ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ እመቤታችን ተገለጠችለትና አረጋጋችው፡፡ ዳግመኛም እንደምትመጣ ቀን ቀጥራው ከእርሱ ተሰወረች፡፡ በሰጠችውም ቀጠሮ መሠረት በነሐሴ 21 ኛው ቀን እመቤታችን ቅዱስ ሚካኤልና ቅዱስ ገብርኤል በቀኝና በግራ ሆነው ኪሩቤልንና ሱራፌልን አስከትላ ተገለጠችለትና "አይዞህ ዕውቀት የተሰወረብህ ትምህርት ስለማይገባህ ሳይሆን የእግዚአብሔር ድንቅ ሥራ እንዲገለጥ ነው" አለችው፡፡ "የመረጥሁህ የልጄ ወዳጅ ጊዮርጊስ ብላ በስሙ ጠራችው፡፡ ከዕውቀት ወንዝ የመጣና ከጥበብ ምንጭ የተገኘ ከመለኮት ባሕር የተቀዳ ይህን ንጹሕ ጽዋ ንሣ ጠጣ" በማለት ጽዋዓ ልቡናን አጠጣችው፡፡

❤ ይኸውም ጽዋዕ ልቦና በዮሴፍ ቤት በጽርሐ ጽዮን ሐዋርያት የጠጡት መንፈሳዊና ሰማያዊ መጠጥ ነው፤ በበዓለ ሃምሳ ከጠጡት ያልተለየ ነው፡፡ ይኸውም የሚናገር እሳት፣ የሚያድን እሳት፣ መለኮታዊ እሳት ነው፡፡ ከዚህም በኋላ አባ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያንን ያስጌጠበት የመጻሕፍትን ምስጢራት፣ የማኅሌትንና የድርሳናትን ቃል፣ ምስጋናዎችንም ሁሉ እመቤታችን ገለጠችለት፡፡

❤ እመቤታችን ማርያም ለብፁዕ ጊዮርጊስ ጽዋውን ካጠጣችው በኋላ ያን ጊዜ አምስት የምሥጢር ቃላትን አስተማረችው፡፡ የኅሊናን ዓይኖች ያበራሉና የልቡናንም ጆሮዎች ይከፍታሉና፡፡ ከዚህ በኋላ ከእርሱ ተሰወረች፤ ከማይተኙ ከትጉሃን መላእክትም ጋር ወደ ሰማይ ዐረገች፡፡ የአምስቱ የምሥጢር ቃላት ትርጉምም ዕውቀትን የተመሉ መንፈሳውያን አባቶቻችን እንደ ነገሩን ከእመቤታችን ማርያም እጅ በተሰጠው በመንፈስ ቅዱስ ስጦታ ትምህርት ሳይማር በአንድ ቀን የዳዊትን መዝሙር ማጥናት ነው፡፡ መዝሙረ ዳዊትን ግን ዕብራውያን በአምስቱ የስሜት ሕዋሳት ቁጥር ለአምስት ከፍለውታል፡፡ እነዚህም መስማት፣ ማየት፣ ማሽተት መቅመስና፣ መዳሰስ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ክፍል መጨረሻው 40ኛው መዝሙር ነው፤ የሁለተኛው ክፍል መጨረሻው 71ኛው መዝሙር ነው፡፡ ሦስተኛው ክፍል መጨረሻው 88ኛው መዝሙር ነው፤ አራተኛው ክፍል መጨረሻው 105ኛው መዝሙር ነው፡፡ አምስተኛው ክፍል መጨረሻው 150ኛው ነው፡፡ የእነዚህም ክፍላት መጨረሻ ለይኩን ለይኩን ባለ ጊዜ ይታወቃል፡፡ አባ ጊዮርጊስም የእነዚህን ምስጢር በልቡ ጠበቃቸው፡፡


ስንክሳር ዘወርሃ ጥቅምት ሁለት(፪)




❤ በአንዲት ቀንም ወደ አስቄጥስ ገዳም ደረሰ በመጻተኛ መነኲሴ አምሳልም ወደ አባ መቃርስ ቤተ ክርስቲያንም ገባ በዚያንም ጊዜ ቄሱ ዕጣንና ቁርባንን ሊአሳርግ ጀመረ እንደ ሥርዓቱም እየዞረ ዐጠነ። የሐዋርያትንም መጻሕፍት የጻፉአቸውን መልእክቶች የከበረ ወንጌልንም ከአነበቡ በኋላ እጆቹን ታጥቦ ማኅፈዱን በገለጠው ጊዜ በጻሕሉ ውስጥ የቊርባኑን ኅብስት አላገኘውም ደንግጦም አለቀሰ።

❤ ከዚህም በኋላ ወደ ሕዝቡ ተመልሶ እንዲህ አላቸው "ወንድሞቼ እነሆ የቊርባኑ ኅብስት ተሠውሮ በጻሕሉ ውስጥ አላገኘሁትምና ይህ የሆነ በእኔ ኃጢአት ወይም በእናንተ ኃጢአት እንደሆነ አላወቅሁም"። በዚያንም ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦለት እንዲህ አለው "ይህ የሆነ በኃጢአትህ ወይም በሕዝብ ኃጢአት አይደለም ሊቀ ጳጳሳት አባ ሳዊሮስ እያለ መሥዋዕትን ለማሳረግ በመድፈርህ ነው እንጂ" ቄሱም መልአኩን "ጌታዬ ሊቀ ጳጳሳት መኖሩን አላወቅሁም" አለው አባ ሳዊሮስም ወደ ቆመበት ቦታ አመለከተው።

❤ ቄሱም ወደ አባ ሳዊሮስ ሒዶ ከእግሩ በታች ሰገደ ቡራኬም ከእርሱ ተቀበለ። ሊቀ ጳጳሳት አባ ሳዊሮስም የጀመረውን የቅዳሴውን ሥርዓት እንዲፈጽም ቄሱን አዘዘው። እርሱንም በታላቅ ክብር ወደ ቤተ መቅደስ አስገቡት ከዚህም በኋላ ቄሱ ወደ መሠዊያው በወጣ ጊዜ የቁርባኑን ኅብስት በጻሕሉ ውስጥ አገኘው ካህናቱና ሕዝቡም ሁሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑት።

❤ የቁርባኑንም ሥርዓት ከተፈጸመ በኋላ ካህናቱና ሕዝቡም ሁሉ ከሊቀ ጳጰሳት አባ ሳዊሮስ ቡራኬ ተቀበሉ። ከዚያም ወጥቶ ወደ ሀገረ ስሐ ሔደ ስሙ ዶርታዎስ ከሚባል እግዚአብሔርን ከሚወድ ባለ ጸጋ ሰው ደርሶ ከእርሱ ዘንድ ተቀመጠ። ምእመናንንም እያስተማራቸውና በቀናች ሃይማኖት እያጸናቸው እስከሚአርፍባት እስከ የካቲት ወር ዐሥራ አራት ቀን ኖረ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በአባ ሳዊሮስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የጥቅምት 2 ስንክሳር።

+ + +
❤ "ሰላም ለዘአብደርከ ስደተ። ሳዊሮስ እምትክሀድ
ሃይማኖተ። ክርስቶስ ርትዕተ። ወአመ አዕረገ ቀሲስ ቊርባኖ እንዘ አፍኣ መቅደስ አንተ። ተኀብኦትከ እምጻሕል ኅብስተ ቊርባን ከበተ። ወተከሥቶትከ ኪያሁ ከሠተ"። ሊቁ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የጥቅምት 2።

+ + +
❤ የዕለቱ ምስባክ፦ "በእግዚአብሔር ተወከልኩ እፎ ትብልዋ ለነፍስየ። አዐይል ውስተ አድባር ከመ ዖፍ። እስመ ናሁ ኀጥአን ወሰቁ ቀስቶሙ"። መዝ 10፥1-2። የሚነበቡት መልዕክታት 2ኛ ቆሮ 4፥7-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 5፥5-12 እና የሐዋ ሥራ 20፥1-7። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 5፥10-17። የሚቀደሰው ቅዳሴ የእመቤታችን የማርያም ቅዳሴ ነው። መልካም የአባ ሕርያቆስና የአቡነ ማትያስ የዕረፍት በዓልና የጾም ጊዜ። ለሁላችንም ይሁንልን።


❤ "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤

❤ ጥቅምት ፪ (2) ቀን።

❤ እንኳን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ቅዳሴ ለደረሰው ለብህንሳ አገር ኤጲስቆዾስ ለታላቁ አባት ለአባ ሕርያቆስ ለልደትና ለዕረፍት በዓል፣ ለአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ለቅዱስ አቡነ ሳዊሮስ ወደ ግብጽ አገር ተሰዶ ለመጣ መታሰቢያ ቀን በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰበው፦ ከሰማዕቱ ከቅዱስ ቴክላ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።

+ + +
❤ ሊቁ አባ ሕርያቆስ፦ ይህም አባት ክርስቲያን ሆኖ እመቤታችንን የሚወድ ሰው ሁሉ ይህንን አባት ያውቀዋል። አባ ሕርያቆስ ተወልዶ ያደገው በምድረ ግብጽ ሲሆን አካባቢው ብህንሳ (ንሒሳ) ይባላል። ይህቺ ቦታ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን ጨምሮ በርካታ ቅዱሳንን ያፈራች ናት።

❤ አባ ሕርያቆስን በዚህ ዘመን ነበረ ተብሎ ትክክለኛውን ዓ.ም ለመናገር ይከብዳል። ከቤተ ክርስቲያን ትውፊት መረዳት እንደሚቻለው ግን የነበረበት ዘመን 4ኛው ወይም 5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደ ሆነ መገመት ይቻላል።

❤ ቅዱሱ በዘመኑ የተለየ ማንነት የነበረው ሰው ነው። ገና ከልጅነቱ እመ ብርሃንን የሚወዳት በመሆኑ ቅን የዋህና ገራገር ነበረ። መቼም እመቤታችን ይወዳል ሲባል እንደ ዘመኑ በአፍ ብቻ እንዳይመስለን። ቀንና ሌሊት ለፍቅሯ የሚተጋ ማዕበለ ፍቅሯ የሚያማታው ሰው ነበር እንጂ።

❤ የእመቤታችን ድንግል ማርያምን ስም ሲጠራ ምስጥ ብሎ ልቡናው ይሰወርበት ነበር ዘወትር የእርሷን ፍቅር ከማሰብ በቀር ሌላ ሥራ አልነበረውም። የልጅነት ጊዜው ሲያልፍም ድንግልንና ቸር ልጇን ያገለግል ዘንድ መነነ።

❤ ዘመኑ ዘመነ ሊቃውንት እንደ መሆኑ ሁሉም ለትምሕርት ሲተጉ እርሱ ግን ለጸሎትና ለደግነት ብቻ ነበር የሚተጋው። ከትምሕርት ወገንም የሰሞን ጉዋዞችን አንዳንድ ቅዳሴያትንና የዳዊትን መዝሙር ተምሮ ነበር።

❤ በተለይ ግን የዳዊትን መዝሙር እየጣፈጠው መላልሶ መላልሶ ያመሰግንበት ነበር። ከዳዊት መካከል ደግሞ መዝሙር 44ን ፈጽሞ ይወዳት ነበር። ይህቺ ጥቅስ የምትጀምረው "ጐስዐ ልብየ ቃለ ሠናየ" ብላ ነው። የውስጧ ምሥጢርም ስለ ድንግል ማርያምና ስለ ክርስቶስ ነው።

❤ አባ ሕርያቆስ ይህቺን መዝሙር በቃሉ አጥንቶ? ቁሞም ተቀምጦም ተኝቶም ተነስቶም ያለ ማቁዋረጥ ይላት ነበር። እየጣፈጠችው "ልቡናየ በጐ ነገርን አወጣ" እያለ ይዘምር ነበር። በወቅቱ ታዲያ የብህንሳ ኤዺስ ቆዾስ በማረፉ ምትክ ሲያፈላልጉ መንፈስ ቅዱስ አባ ሕርያቆስን መረጠ።

❤ ምንም አለመማሩ ቢያሰጋችቸውም 'በጸሎቱ በደግነቱ ሃገር ይጠብቃል ብለው ሾሙት ነገር ግን ምንም በሥልጣን የበላያቸው ቢሆን ተማርን የሚሉ ሰዎች ይጠሉት ይንቁትም ነበር። እርሱ ግን እንደ ጠሉኝ ልጥላቸው እንደ ናቁኝ ልናቃቸው ሳይል በፍቅር ያገለግል ነበር።

❤ አንድ ቀን ታዲያ መንገድ ይወጣል። በበርሃ ብቻውን እየተራመደ "ጐሥዐ ልብየ ቃለ ሠናየ" እያለ እየዘመረ ተመሥጦ ቢመጣበት መንገድ ሳተ። እርሱ በምስጋናው ሲደሰት እግሩ ግን ከገደል ጫፍ ደርሶ ነበር። ገደሉን ልብ አላለውም ነበርና ሳይታወቀው ወደ ገደሉ ውስጥ ተወረወረ።

❤ በዚህ ጊዜ ደንግጦ ቢመለከት እጅግ ጥልቅ በሆነ ገደል ውስጥ ራሱን አገኘው። ነገር ግን አንድም አካሉ አልተነካም። ልብሱም አልቆሸሸም። ለራሱ ተገርሞ ዙሪያ ገባውን ሲመለከት እርሱ ቁጭ ያለበት ብርሃንን የተሞላ የልብስ ዘርፍ ነበር። "እመ ብርሃን" ብሎ ሲጮህ የሰማይና የምድር ንግሥት የሆነች እመቤታችን ከፊቱ ቁማ ታየችው። እመ አምላክን በገሃድ ቢያያት እንደ እንቦሳ ዘለለ።

❤ የሚገርመው ደግሞ የተቀመጠበት የድንግል ማርያም የቀሚሷ ዘርፍ ነበር። እመቤታችን አነጋገረችው ባረከችው። ፍቅሯ ቢመስጠው ከሰው ሳይገናኝ ምግብም ሳይበላ እዚያው ገደሉ ውስጥ ለ1 ዓመት ያህል በተመስጦ ቆይቷል።

❤ በኋላ እመ ብርሃን መጥታ ከገደሉ አውጥታ ወደ ሐገሩ መለሰችው። ከጥቂት ጊዜ በኋላም አንድ ፈተና ገጠመው። አንድ ቀን እመቤታችን በተወለደችበት ግንቦት 1 ቀን ቅዳሴ "ማን ይቀድስ" ሲባል ሰዎቹ "አባ ሕርያቆስ ይሁን" አሉ።

❤ እርሱ ግን "እኔ አይቻለኝም እናንተ ሊቃውንት ቀድሱ" አላቸው። "አይሆንም" ብለው እርሱኑ አስገቡት። ይህንን ያደረጉት ለተንኮል ነበር። ልክ ወንጌል ተነቦ ፍሬ ቅዳሴ ሲመረጥ እርሱ "እግዚእን (የጌታ ቅዳሴን) ልቀድስ" ቢል እነርሱ "የሚቀደሰው የሊቅ ቅዳሴ ነው" አሉት።

❤ ይህንን ያሉት እርሱ የሊቃውንቱን ቅዳሴ አያውቅምና በሰው ፊት እንዲዋረድ ነው። እንዲህም ብለው ባለመማሩ ተሳለቁበት። አባ ሕርያቆስ ግን እያዘነ ወደ መንበሩ ዞረ። ድንግልንም "እመቤቴ መናቄን መገፋቴን ተመልከች" አላት።

❤ ወዲያው ግን ድንግል ማርያም ወርዳ ቀጸበችው (ጠራችው)። በዘርፋፋው ቀሚሷ ላይም ረቂቅ የሆነ ቅዳሴን አሳየችው። ደጉ ሰው ደስ ብሎት "ጐሥዐ ልብየ" ሲል 2ቱ እግሮቹ ከመሬት ከፍ አሉ። እርሱም "ወአነ አየድእ ቅዳሴሃ ለማርያም" ብሎ እስከ ኃዳፌ ነፍሱ ድረስ አደረሰው።

❤ ሕዝቡና ካህናቱ በሆነው ነገር ሲደነቁ አንዳንዶቹ "ዝም ብሎ ነው የቀባጠረ" አሉ። ቅዱሱ ግን ቅዳሴ ማርያምን በብራና ጠርዞ በሕዝቡ መካከል ድውይ ፈወሰበት። እሳት ሳያቃጥለው፣ ውሃ ሳይደመስሰው ቀረ።

❤ መጽሐፈ ቅዳሴው ሙትንም አስነስቷል። ከዚህች ሰዓት ጀምሮ በዘመኑ ቁጥር 1 ሊቅሙ ሆነ። ብዙ መጻሕፍትን ሲተረጉም አጠቃላይ ድርሰቶቹም እልፍ (10,000) ናቸው። ሊቁ እንዲህ በንጹሕ ተመላልሶ ዐርፏል። ይህቺ ቀን ለቅዱሱ የልደቱና ዕረፍቱ መታሰቢያ ናት። ከአባታች ከአባ ሕርያቆስ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን በጸሎቱም ይማረን!። ምንጭ፦ ከዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ።

+ + +
❤ "ሰላም ለሳዊሮስ ሊቀ ጳጳሳት ዘተጰጰሰ በሃይማኖት"። ትርጉም፦ በቀናች ሃይማኖት የጳጳሳት አለቃን ኾኖ ለተሾመ ሳዊሮስ ሰላምታ ይገባል። ሊቁ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በተአምኆ ቅዱሳን ላይ።

+ + +
❤ የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ አቡነ ሳዊሮስ ወደ ግብጽ አገር ተሰዶ መምጣት፦ ይህም የሆነው በመናፍቁ ንጉሥ በዮስጥያኖስ ዘመን ነው እርሱም ንጉሡ በኬልቄዶን ሃይማኖት የሚያምን ነው ሚስቱ ንግሥት ግን ሃይማኖቷ የቀና ነው ቅዱስ አባ ሳዊሮስን ትወደዋለች ታከብረዋለችም ንጉሡም በሥውር ሊገድለው ይሻዋል።

❤ ቅዱስ አባ ሳዊሮስንም በሥውር ይገድለው ዘንድ ንጉሥ እንደሚሻው ንግሥት በአወቀች ጊዜ ከአንጾኪያ አገር እንዲወጣና ነፍሱን እንዲአድን ወደ አባ ሳዊሮስ ላከች። እርሱ ግን መሸሽ አልፈለገም ለንግሥትም እንዲህ አላት እኔ ክብር ይግባውና ስለጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ለሞት የተዘጋጀሁ ነኝ ንግሥቲቱም ብዙዎች ምእመናንም አብዝተው በለመኑት ጊዜ ከሀገር ወጣ ከእርሱም ጋር ከምእመናን አብረውት ወደ ግብጽ አገር የተሰደዱ አሉ።

❤ ንጉሡም በፈለገው ጊዜ አላገኘውም ፈልገውም ወደርሱ ያመጡት ዘንድ ወታደሮቹን ላከ ክብር ይግባውና ጌታችን ስለ ሠወረው እነርሱም በቅርባቸው ሁኖ በመካከላቸው ሲጓዝ አላገኙትም። በአንድ ቦታም አብሮአቸው ሲያድር እርሱ እያያቸው እነዚያ የንጉሥ ጭፍሮች አያዩትም እርሱንም አጥተው ተመለሱ። ወደ ግብጽ አገርም በደረሰ ጊዜ ከቦታ ወደቦታ ከደብር ወደ ደብር በሥውር የሚዘዋወር ሆነ እግዚአብሔርም በእጆቹ ላይ ታላላቅ የሆኑ ድንቆች ተአምራትን አደረገ።






❤ "በስመ አብ ወወልደ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን"። ❤

❤ የተባረከ የጥምት ወር የቀኑ ሰዓት ዐሥራ አንድ ነው ከዚህም በኋላ ይቀንሳል።

❤ ጥቅምት ፩ (1) ቀን።

❤ እንኳን ከሮሜ አገር ለሆነች በገድል ተጠምዳ ለኖረች በጨካኙ ንጉሥ በዳኬዎስ ወታደሮች እጅ ሰማዕትነት ለተቀበለች ለቅድስት አንስጣስያ ለዕረፍት በዓልና ለዓላአዛር እኅት ለቅድስት ማርያም ለመታሰቢያ በዓሏ በሰላም አደረሰን። በተጨማሪ በዚች ቀን ከሚታሰቡ፦ ከኅርጣንና ከድንግል ቅድስት ሶስና ከመታሰቢያ እግዚአብሔር አምላክ ረድኤትና በረከትን ያሳትፈን።

+ + +
❤ ሰማዕቷ ቅድስት አንስጣስያ፦ ይችም ቅድስት መስተጋድልት ከሮሜ አገር ናት ወላጆቿም ክርስቲያኖች ናቸው ጠቃሚ የሆነ ትምህርትን በማስተማር ክብር ባለው በመልካም ሥርዓት አሳደጓት።

❤ በአደገችም ጊዜ ወላጆቿ ሊያጋቧት ፈለጉ እርሷ ግን ይህን ሥራ አልፈለገችም የምንኲስናን ልብስ መልበስ ፈለገች እንጂ፤ ከታናሽነቷም መንፈሳዊ ገድልን መረጠች። ስለዚህም በሥውር ሒዳ በሮሜ ካሉ ገዳማት ወደ አንዱ ገዳም ገባች ታናሽ ስትሆንም የምንኲስና ልብስን በመልበስ በጾም በጸሎት በረኃብ በጽምዕ በመጠመድ የዚህን ዓለም ሐሳብ ሁሉ ከልቡናዋ ቆርጣ በመተው በመጋደል ሥጋዋን አደከመች።

❤ በቀኑ ርዝመትም ሁሉ የምትጾም ሆነች በየሁለት ቀኖችም ታከፍላለች በጌታችን ጾም ግን ያለ ሰንበታት ቀን የምትመገበው የለም። በሰንበታትም የምትመገበው ከቀትር ጸሎት በኋላ ነው። በነዚያም በምንኲስናዋ ወራት በእሳት ያበሰሉትን ወጥ አልቀመሰችም።

❤ በገዳሟ አቅራቢያም ሌላ የደናግል ገደም አለ የዚያ ደብር በዓልም በደረሰ ጊዜ እመ ምኔቷ በዓሉን ለማክበር ይቺን ቅድስት አንስጣስያን ከእኅቶቿ ደናግል ጋር አስክትላት በአንድነት ተጓዙ። ሲጓዙም የንጉሥ ዳኬዎስን ወታደሮች አየቻቸው። ከእርሳቸውም ጋር የታሠሩ ክርስቲያኖች አሉ ወታደሮቹም አሥረው በቁጣ ይጎትቷቸው ነበር። ልቧም በሃይማኖቷ ፍቅር ነደደና ያን ጊዜ እንዲህ ብላ ዘለፈቻቸው "የእውነት ፈጣሪን የካዳችሁ ልባችሁ የደነዘዘ እግዚአብሔር በመልኩና በአምሳሉ በፈጠራቸውና ስለእነርሱም ነፍሱን ለሞት አሳልፎ በሰጠላቸው ላይ ለምን እንዲህ ትሠራላችሁ"።

❤ ይህንንም በአለቻቸው ጊዜ ወታደሮች ተቆጡ ይዘውም ወደ መኰንኑ አቀረቧት እርሱም እንዲህ ብሎ ጠየቃት "በእውነት አንቺ የተሰቀለውን የምታመልኪው ክርስቲያን ነሽን?" እርሷም "ስለእኛ የተሰቀለውን ክብር ይግባውና እርሱን አመልከዋለሁ" ብላ መለሰችለት።

❤ በዚያን ጊዜም ጽኑ ሥቃይን አሠቃያት በሥጋዋም እሳትን ጨመረ ከዚህም በኋላ ዘቅዝቆ ሰቀላት ከበታቿም አጤሱባት ከሃይማኖቷም ባልተናወጸች ጊዜ ራሷን በሰይፍ ይቆርጡ ዘንድ አዘዘ። በዚህ በታላቅ ሥቃይም ውስጥ ሳለች ራሷን በሰይፍ ቆረጧት። በመንግሥተ ሰማያትም የሰማዕትነት አክሊልን ተቀበለች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በበሰማቷ ቅድስት አንስጣስያ ጸሎቱ ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን። ምንጭ፦ የጥቅምት 1 ስንክሳር።

+ + +
❤ "ሰላም ለማርያም ለዓላአዛር እኅቱ። እንተ አንሥኦ ክርስቶስ እምነ መቅበርቱ። በሀሊተ ብካይ ጊዜ ተቀበሎቶ ሎቱ። ሶበሰ እግዚእየ ሀሎከ በዝንቱ። እመኢትውህበ እኅየ ለሞቱ"። ሊቀ አርከ ሥሉስ (አርኬ) የጥቅምት 1።

+ + +
❤ የዕለቱ ምስባክ፦ "ተዘከር እግዚኦ ከመ መሬት ንሕነ። ሰብእሰ ከመ ሣዕር መዋዕሊሁ። ወከመ ጽጌ ገዳም ከማሁ ይፈሪ"። መዝ 102፥14-15። የሚነበቡት መልክታት 1ኛ ቆሮ 7፥32-ፍ.ም፣ 1ኛ ጴጥ 3፥1-5 እና የሐዋ ሥራ 17፥10-13። የሚነበበው ወንጌል ማቴ 6፥25-ፍ.ም። የሚቀደሰው ቅዳሴ የቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ ቅዳሴ ነው። መልካም የጾም ጊዜና በዓል ለሁላችንም ይሁንልን።

20 last posts shown.

304

subscribers
Channel statistics