"ልጆቼ የቤተክርስቲያንን ነገር አደራ"


Гео и язык канала: не указан, не указан
Категория: не указана


@Dan12bot
ለአስተያየትዎ ይህን ይጠቀሙ እናመሠግናለን

Связанные каналы

Гео и язык канала
не указан, не указан
Категория
не указана
Статистика
Фильтр публикаций


#ኹሉንም_ነገር_ለእግዚአብሔር_እንስጠው

ወርቅን የሚያነጥር ሰው አንዲትን የወርቅ ቅንጣት ወደ እሳት ውስጥ ጨምሮ እጅግ ንጹህ እስክትኾን ድረስ ይጠብቃታል፡፡ እግዚአብሔርም ልክ እንደዚሁ ሰዎች እስኪነጹ፣ እስኪለወጡና ባገኛቸው ነገር ጥቅም እስኪያገኙ ድረስ ፈተና ውስጥ እንዲቆዩ ይፈቅዳል፡፡ ይህ ደግሞ ከጥቅምም እጅግ ከፍ ያለ ጥቅም ነው፡፡

ስለዚህ ፈተና ሲገጥመን ውስጣችን ሊረበሽ ወይም ተስፋ ሊቈርጥ አይገባውም፡፡ ያ ወርቅን የሚያነጥር ሰው በእሳት ውስጥ የጨመራትን የወርቅ ቅንጣት እዚያ ውስጥ ምን ያኽል ጊዜ መቆየት እንዳለባት ያውቃል፤ መቼ ከእሳቱ ሊያወጣት እንደሚገባውም ያውቃል፡፡ እንዲሁ እስከ መጨረሻው በእሳቱ ውስጥ ተጥላ እንድትቀርና በዚያ እንድትቃጠል አይፈቅድም፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ ይህን ከወርቅ አንጣሪው በላይ ያውቃል፡፡ መቼ ከርኵሰታችን እንደምንነጻ ያውቃል፡፡ በመኾኑም ራሳችንን በመጣልና ተስፋ በመቁረጥ በክፋት ላይ ክፋት እየጨመርን እንዳንሔድ ሽቶ መቼ ከዚያ ፈተና እንደሚያወጣን ያውቃል፡፡ ስለዚህ ድንገት ያላሰብነው ነገር ቢገጥመን በፍጹም የምናማርር፣ ወይም ተስፋ የምንቈርጥ ልንኾን አይገባንም፡፡ ከዚህ ይልቅ የእነዚህ ነገሮች ምንነትን የሚያውቅ እግዚአብሔርን መጠበቅ፣ እርሱ እስከ ፈቀደው ጊዜ ድረስም ልቡናችንን በእሳት እንዲፈተን ማድረግ ይገባናል፡፡ ምክንያቱም ይህ ነገር በእኛ ላይ እንዲኾን የፈቀደው ለእኛ ጥቅምና በዚያ ውስጥ ኾነን በምናሳየው ጥረት ይበልጥ ሊያከብረን ስለሚወድ ነው፡፡

ይህን በማስመልከትም ጠቢቡ ሰው እንደዚህ ሲል መክሮናል፡- “ልጄ ሆይ! ለእግዚአብሔር ትገዛ ዘንድ ብትሔድ ሰውነትህን ለመከራ አዘጋጅ፤ ልብህን አቅና፤ ኹልጊዜ ታገሥ፤ አታወላውልም፤ በመከራ ብትጨነቅም አትጠራጠር” /ሲራ.2፥1-2/፡፡ “ኹሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ስጠው፡፡” ለምን? እግዚአብሔር ከዚያ መከራ መቼ እኛን ማውጣት እንዳለበት ያውቃልና፡፡ ስለዚህ ኹሉንም ለእርሱ ልንሰጥ፣ ዘወትር እርሱን ልናመሰግን፣ ኹሉንም ነገር - ጥቅምም ይኹን ቅጣት - በአኰቴት ልንቀበል ይገባናል፤ ይህም ቢኾን ለእኛ ረብሕ የሚኾን ነውና፡፡ አንድ ሐኪም፥ ሐኪም የሚባለው ታካሚውን ገላዉን ሲያጥበውና ሲመግበው እንዲሁም ደስ ወደሚያሰኝ ስፍራ ሲወስደው ብቻ አይደለም፤ በእርሱ (በታማሚው) ሰውነት ላይ የቀዶ ጥገና ምላጭና ቢላ ሲያሳርፍም ጭምር ሐኪም ነው፡፡ አባትም አባት የሚባለው ልጁን ሲንከባከብ ብቻ አይደለም፤ የገዛ ልጁን ከቤት ሲያስወጣው፣ ሲገሥጸው፣ ሲገርፈውም ያው አባት ነው፡፡ ስለዚህ እኛም እግዚአብሔር ከሐኪሞችም በላይ ሰውን ወዳጅ እንደ ኾነ በማወቅ፥ ምን ዓይነት የሕክምና ዓይነት እንደሚሰጠን በጥልቀት አንጠይቅ፤ ወይም ደግሞ ለደረሰብን መከራ እርሱን ተጠያቂ አናድርግ፡፡ ከዚህ ይልቅ እርሱ የወደደውን ነገር - ቅጣትም ይኹን ቅጣት የሌለው ነገር - ብቻ ምንም ይኹን ምን በአኰቴት ልንቀበል ይገባናል፡፡ በየትኛውም መንገድም ቢኾን የእርሱ ፈቃድ እኛ እንድንድንና ከእርሱ ጋር አንድ እንድንኾን ነውና፡፡ የትኛው መንገድ ለእኛ እንደሚጠቅምም እርሱ ያውቋል፡፡ እያንዳንዱ ሰው የትኛው መንገድ ወደ እርሱ እንደሚመልሰው ያውቃል፡፡ ኹላችንም እንዴትና በምን ዓይነት መንገድ ልንድን እንደምንችል ያውቃል፡፡ በመኾኑም የሚመራን በዚህ እኛ በምንድንበት መንገድ ነው፡፡ ስለዚህ ወደየትኛውም መንገድ ቢወስደንም - ልክ እንደ መጻጉዑ - እርሱ እንደሚያዘ’ን ተከትለን መሔድ እንጂ ትልቁ ጉዳያችን በለስላሳና በቀላል አልያም ደግሞ በከባድና በሸካራ ጎዳና እንድንሔድ የሚያዘ’ንን ትእዛዝ መኾን የለበትም (ልንሔድበት የሚገባ’ው መንገድ እርሱ ስለሚያውቀው እንዲሁ መታዘዝ እንጂ የመንገዱን ከባድነት ወይም ቀላልነት የእኛ አጀንዳ ሊኾን አይገባውም፡፡)

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ
#ወደ_ኦሎምፒያስ_የተላኩ_መልእክታት መጽሐፍ
#በገብረ_እግዚአብሔር_ኪደ ከተተረጎመው


🔮 ምክረ ቃል 🔮

🔅 አንድ ሰው በጾም ወራት በየዕለቱ ጥሩ ጥሩ ምግቦች እየበላና የሚናፍቀውን ምግብ ለሰውነቱ እየሰጠ የሥጋውን ፈቃድ እንዴት ሊቆጣጠር ይችላል? አይችልም። መንፈሳዊው ሰው የጾም ትክክለኛ ፍቺ ሥጋን በማዋረድ የምግብን ፋላጎት ድል ለማድረግ ካበቃ በኋላ ከቁሳዊው ዓለም በላይ ከፍ የሚያደርግ መሆኑን ያውቃል። በመሆኑም የጾም ምግቦችን መብላት ብቻ መሆን የለበትም እርሱ በሚጾምበት ጊዜ ግድ የሚለው መታቀብ ነው ። ይህም ማለት የሚመገበው ሙሉ ለሙሉ የጾም ምግብ ቢሆንም ሥጋው ሊያገኛቸው የሚናፍቃቸውን ነገሮች በሙሉ መከልከል ማለት ነው ።

🔅 ብዙ ሰዎች የሚጾሙት በልምድ ወይም በፊደል ስለሆነ ምንም የሚጠቀሙት ነገር የለም ። እነዚህ ሰዎች ጾምን መለኮታዊ ዓላማውን በመገንዘብ ስለማይጀምሩት ወደ ጾም መንፈሳዊነት ወይም ስለ ትእዛዙ መንፈሳዊነት ሊገቡ አይችሉም። በመሆኑም ሰውነታቸው ይጹም እንጂ መንፈሳቸው አይጾምም።
   ✨💧✨💧✨💧✨💧

  ✍  አቡነ ሸኖዳ


“#መንፈሳዊው_ገበሬ”
(ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)

“አንድ ገበሬ ዘር መዝራት ስላለበት ብቻ እንዲሁ አይዘራም፡፡ አስቀድሞ መሬቱን ማረስ፣ ማለስለስ አለበት፡፡ ካረሰ ካለሰለሰ በኋላ ዘሩን ይዘራዋል፡፡ አሁንም ግን መዝራቱ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ የዘራውን ዘር አፈር ሊያለብሰው ይገባዋል፡፡ እንዲያ ካላደረገ ወፎች መጥተው ይለቅሙታልና፡፡

ልክ እንደዚሁ እኛ ክርስቲያኖችም በእኛ ላይ የተዘራውን ዘር (ቃለ እግዚአብሔር) በየጊዜው እንደ ገበሬው የማንከታተለው ከሆነ በአየር ላይ እንደተዘራ ዘር ይሆንብናል፡፡ ሰይጣን ይለቅምብናል፤ የራሳችን ስንፍና እንዲጠወልግ ያደርጓል፤ ፀሐይ ያደርቋል፤ ጐርፍ ይወስዷል፤ እሾክ አንቆ ይይዟል፡፡

ስለዚህ ዘር ዘርቶ ዞር ማለት አያስፈልግም ማለት ነው፡፡ በየጊዜው መኮትኮት፣ ወፎችን ማባረር፣ የበቀለ አረም ካለ ማረም፣ ጭንጫ የበዛበት አከባቢ ካለ የለሰለሰ አፈር መጨመር፣ በየጊዜው መከታተል፣ አጥር ማጠር፣ እንዲሁም ማንኛውም የተዘራውን እህል ሊያበላሹ የሚችሉ ነገሮችን ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ ምናልባት በሰብሉ እርሻ የገበሬው ትጋት ብቻ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡ ምክንያቱም መሬቱ ግዑዝ ነገር ስለሆነ፡፡

በመንፈሳዊው እርሻ ግን እንዲህ አይደለም፡፡ ኃላፊነቱ የገበሬው ማለትም የመምህሩ ብቻ አይደለም፡፡ ከግማሽ ወይም ከዚያ በላይ የደቀመዝሙሩ (የምእመኑ) ኃላፊነት ነው፡፡ በርግጥ መምህሩ ዘሩን መዝራት አለበት፡፡ ነገር ግን ደቀ መዝሙሩ የተነገረውን ቃል ሁል ጊዜ መስማት ብቻ ሳይሆን ማድረግም አለበት፤ በግብር ፍሬ ማፍራት አለበት፤ የበቀሉ አረሞች ካሉ በየጊዜው መንቀል አለበት፡፡…የገበሬ ልጆች በሰብሉ መካከል የበቀለ አረም ካለ እንዲሁ ጫፍ ጫፉን ብቻ አይቈርጡትም፡፡ ከሥር ይነቅሉትና በመጨረሻም በእሳት ያቃጥሉታል እንጂ፡፡ በእኛ ላይ የበቀሉ አረሞችም (ጥርጥሮች፣ ክሕደቶች፣ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ማነቆ የሆኑብንን ነገሮች…) ከሥራቸው ነቅለን ልናቃጥላቸው ይገባናል።


በዓለ መንፈስ ቅዱስ / ጰራቅሊጦስ

ይህች ታላቅ ዕለት ከቅድስት ሥላሴ አንዱ አካል የሆነው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለቅዱሳን ሐዋርያት፣ ለቅዱሳን አርድእትና ለቅዱሳት አንስት የተገለጠባት ዕለት ናት፡፡ እነዚህ ሁሉ በጸሎት ተግተው በሚጸልዩበት ወራት መንፈስ ቅዱስ በተከፋፈሉ የእሳት ልሳን አምሳል የወረደበት ቅዱስ ቀን ነው፡፡ አስቀድሞ ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳን ሐዋርያት ደብረ ዘይት በተባለ ታላቅ ተራራ ላይ ሳሉ እንዲህ ብሎ አስተምሯቸው ነበር “ኃይልን ከአርያም እስክልክላችሁ ድረስ በኢየሩሳሌም በጸሎት ቆዩ፡፡”/ሉቃ 24፡36/ መቶ ሃያው ቤተሰብም በኢየሩሳሌም ሀገር በምትገኝ በቤተ መቅደስ በአንድነት ሆነው በጸሎት በመትጋት ቆዩ፡፡ 120ው ቤተሰብ የሚባሉት 12ቱ ሐዋርያት፣ 72ቱ አርድእት/አገልጋዮች/ እና 36ቱ ቅዱሳን አንስት/ሴቶች/ ናቸው፡፡

ከዕርገት በኋላ በአሥረኛው ቀን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ሐዋርያት ወዳሉበት፣ በጸሎትና በምሥጋና ወደ ሚተጉበት ሥፍራ በእሳት አምሳል /ምሳሌ/ ወርዶ በእያንዳንዳቸው ላይ ተቀመጠባቸው፡፡ ይሄንንም ሁኔታ ተከትሎ ምስጢር ተገለጠላቸው፣ ይፈሩ የነበሩት ሐዋርያትም ወንጌልን ለማስተማር ደፋሮች ሆኑ፣ በተለያየ ቋንቋዎች እንዲናገሩ እውቀት ተሰጣቸው፤ የእግዚአብሔርንም ጸጋ ተቀበሉ፡፡ ይህንን ታላቅ ኀይል እና ሰማያዊ ስጦታን የሰጣቸውን እግዚአብሔርን በታላቅ ዝማሬና እልልታ አመሰገኑት፡፡

በዚያም ዕለት  በዓለ ሃምሳ የሚባለውን የአይሁድን በዓል ለማክበር ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ቁጥራቸው በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሐዋርያቱን ታላቅ የዝማሬና የእልልታ ድምፅ ሰሙ፡፡ ከመቶ ሃያው ቤተሰብ መካከል አንዱ የሆነው ቅዱስ ጴጥሮስ የተሰበሰቡት ሁሉም እንዲሰሙት ድምፁን ከፍ አድርጎ ቃለ እግዚአብሔርን እንዲህ ብሎ አስተማራቸው፡፡ “እናንተ የእስራኤል ሰዎች ሆይ እኛን የሰው ልጆችን ለማዳን እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር መጥቶ ከክፉ ሥራ ተመለሱ፣ ኀጢአትን አታድርጉ፣ በቅድስና ኑሩ፣ ወደ እኔም ተመለሱ ቢላችሁ፤ እናንተ ግን ምንም በደል ሳይኖርበት ገረፋችሁት፣ አንገላታችሁት፣ በመስቀል ላይም ሰቀላችሁት፡፡ እርሱ ግን እግዚአብሔር ነውና ሞትን ድል አድርጎ ተነሣ፡፡ እርሱ ግን አሁንም ይቅር ባይ ነውና ከኀጢአታችሁ ተመለሱ ንስሐም ግቡ፡፡” በማለት አስተማራቸው፡፡ የተሰበሰቡት ሰዎች ሁሉ ተገረሙ፡፡ ምክንያቱም ሐዋርያት በፊት የሚያውቁት አንድ ቋንቋ ብቻ ነበረ፡፡ በዚህ ሰዓት ግን ሰባ ሁለት ቋንቋን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ገልጦላቸው ለሁሉም በየቋንቋቸው አስተማሯቸው፡፡ ይህንንም ድንቅ ተአምር ከተመለከቱት ብዙዎች እግዚአብሔርን አመሰገኑት፡፡ ወደ ሐዋርያትም ቀርበው “አባቶቻችን እናንተ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ናችሁና ምከሩን፡፡ እንደ እናንተ የእግዚአብሔር ልጆች እንድንሆንና በቅድስና እንድንኖር ምን እናድርግ?” በማለት ጠየቁ፡ በዚያች ቀን ቁጥራቸው ሦስት ሺ ያህል ሰዎች በቅዱስ ጴጥሮስ ትምህርት አምነው ክርስቲያን ለመሆን ቀረቡ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም እንዲህ አላቸው፡፡ “እነሆ ሁላችሁም ንስሐ ግቡ፡፡ በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት አምናችሁ ተጠመቁ፡፡” አላቸው በዚያው ዕለትም ሦስት ሺ ሰዎች ወደ ሐዋርያት በመቅረብ ኀጢአታቸውን ተናገሩ፤ ሐዋርያትም እግዚአብሔር ይፍታችሁ እያሉ ልጅነትን የሚያሰጣቸውን ጥምቀት አጠመቁዋቸው፡፡
ከዚያ ቀን ጀምሮም በየዓመቱ ይህችን ታላቅ የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን የምትባለውን በዓለ ጰራቅሊጦስን ክርስቲያኖች በታላቅ ደስታና ምሥጋና እናከብራታለን፡፡

በጽርሐ ፅዮን የወረደው የአብ በረከት፣ የወልድ ፍቅር ፣ የመንፈስ ቅዱስ አንድነት ከሁላችንም ጋር ይሁን!!!


✝✞✝ እንኩዋን ለሐዋርያው ቅዱስ ቶማስ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል በሰላም አደረሳችሁ ✝✞✝

+"+ ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ +"+

=>ከ12ቱ ቅዱሳን ሐዋርያት አንዱ የሆነው ቅዱስ ቶማስ ብዙ መከራን በማሳለፉና የጌታችንን ጐን በመዳሰሱ ይታወቃል::

+ቅዱስ ቶማስ እንደ ሌሎቹ ሐዋርያት በእሥራኤል ተወልዶ በዚያውም በሥርዓተ ኦሪት አድጐ ገና በወጣትነቱ የሰዱቃውያንን ማሕበር ተቀላቅሏል:: ሰዱቃውያን ሰው ከሞተ በሁዋላ አይነሳም (አልቦ ትንሳኤ ሙታን) የሚሉ ናቸው::

+መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ማስተማር ሲጀምር ግን ቅዱስ ቶማስ ከነበረበት ማሕበር ወጥቶ ጌታችንን ተከተለ:: ጌታችንም ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ ይሆን ዘንድ ሾመው:: የቀደመ ስሙ ዲዲሞስ ሲሆን ጌታችን ቶማስ ብሎታል::

+ቅዱስ ቶማስ ጌታ አልዓዛርን ለማስነሳት በሔደ ጊዜ ሌሎች ሐዋርያት ጌታን "አይሁድ ይገድሉሃል ቅር" ሲሉት እርሱ ግን "እንሒድና አብረን እንሙት" ሲል ፍቅሩን አሳይቷል:: (ዮሐ. 11:16)

+ጌታችን ትንሳኤውን ለደቀ መዛሙርቱ በገለጠ ጊዜ ያልነበረው ቶማስ ካላየሁ አላምንም አለ:: ምክንያቱም:-

1.ለጌታችን ከነበረው ፍቅር የተነሳ እውነት አልመስልህ ቢለው
2.አንድም ሌሎቹ ሐዋርያት ትንሳኤውን አየን እያሉ ሲያስተምሩ እኔ ግን ሰማሁ ብየ ማስተማሬ ነው ብሎ በማሰቡ ነበር::

+ለጊዜው ጌታ ተገልጾ ቢገስጸው "እግዚእየ ወአምላኪየ (ጌታየና አምላኬ)" ብሎ ፍጹም ሃይማኖቱን ገልጿል:: ለፍጻሜው ግን የጌታችንን ጎን (መለኮትን) ይዳስስ ዘንድ ባለቤቱ እንዳደለው ያጠይቃል:: መለኮትን የዳሰሰች ይሕቺ ቅድስት እጁ ዛሬም ድረስ ሕያው ናት:: በሕንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥም በክብር ተቀምጣለች::

+ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ሐገረ ስብከት ሲከፋፈሉ ለቅዱስ ቶማስ ሕንድና በዙሪያዋ ያሉ ሃገራት ደረሱት:: ከዚህ በሁዋላ ነው እንግዲህ ዘርዝረን የማንጨርሰውን ተጋድሎ የፈጸመው:: ቅዱሱ በነበረው ፍጹም ትጋት አባቶቻችን "ዘአሠርገዋ ለብሔረ ሕንደኬ (ሕንድን በወንጌል ያስጌጣት)" ሲሉ ያከብሩታል::

+ቅዱስ ቶማስ ንጉሥ ሉክዮስንና የሃገሩን ሕዝብ ለማሳመን በችንካር መሬት ላይ ወጥረው ቆዳውን ገፈውታል:: ቆዳውንም እንደ ገና ሰፍተው: አሸዋ ሞልተው አሸክመውታል::

+በየመንገዱ የተገፈፈ ገላውን ጨው ቢቀቡት በጎች መጥተው ግጠው በልተውታል:: በዚሕ ምክንያት:-
"ኩሉ የአኪ እንዘ የአኪ ዘመኑ:
አባግዒሁ ለቶማስ እስመ አራዊተ ኮኑ" ብለዋል ሊቃውንቱ::

+በሁዋላ ግን ከፎቅ ወድቃ የሞተችውን የንጉሡን ሚስት በተገፈፈ ቆዳው በማዳኑ ሁሉም አምነው ተጠምቀዋል::

+ቅዱሱ ሐዋርያ ልክ እንደ ቅዱስ ዻውሎስ አንዳንዴ በፈሊጥ: ሌላ ጊዜም በመከራ ለወንጌልና ለቤተ ክርስቲያን ተጋድሏል:: ያለ ማቁዋረጥም ከሕንድ እስከ ሃገራችን ኢትዮዽያ ድረስ ለ38 ዓመታት ወንጌልን ሰብኩዋል::

+በመጨረሻም በ72 ዓ/ም በዚሕች ቀን በሰማዕትነት አርፏል:: መቃብሩና ቅድስት እጁ ዛሬ ድረስ ሕንድ ውስጥ አሉ:: ከኘሮቴስታንቶች በቀር መላው ዓለም ያከብረዋል::

+እንደ አባቶቻችን ትርጉም ቶማስ (ቶማስስ) ማለት ጸሐይ (ኦርያሬስ) እንደ ማለት ነው:: በተሰጠው የወንጌል ጸጋ በሃገረ ስብከቱ አብርቷልና::

=>ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአገልጋዩ ቅዱስ ቶማስ ጸጋ በረከት ይክፈለን::

=>ግንቦት 26 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ቶማስ ሐዋርያ (ከ12ቱ ሐዋርያት)
2.ቅድስት አርሶንያ (የቅዱስ ቶማስ ተከታይ)
3.አቡነ ሐብተ ማርያም ጻድቅ

=>ወርሐዊ በዓላት
1.አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ዘሐይቅ
2.ቅዱሳን ሰማዕታተ ናግራን
3.አቡነ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን

=>+"+ ደጆች ተዘግተው ሳሉ ኢየሱስ መጣ:: በመካከላቸውም ቆሞ "ሰላም ለእናንተ ይሁን" አላቸው:: ከዚያም በሁዋላ ቶማስን "ጣትህን ወደዚህ አምጣና እጆቼን እይ:: እጅህንም አምጣና በጐኔ አግባው:: ያመንህ እንጂ ያላመንህ አትሁን" አለው:: ቶማስም "ጌታዬ አምላኬም" ብሎ መለሰለት:: ኢየሱስም "ስላየኸኝ አምነሃል:: ሳያዩ የሚያምኑ ብጹዓን ናቸው" አለው:: +"+ (ዮሐ. 20:26-29)

>


ሰው ሆይ! የሚጎዳህ ሀብትህ አይደለም፤ ድኽነትህም አይደለም። ሰውን የሚጎዳው ክፉ ልብ ነው። ክፉ ልብ ደግሞ በሀብትም፣ ሀብት በማጣትም የሚመጣ አይደለም። ክፉ ልብ ሌሎች ክፉ ልቦችን ይወልዳል። እሳት እሳትን እየወለደ ብዙ እንጨቶችን እንደሚበላ ኹሉ ክፉ ልብም እንደዚህ ነው።

አንተ ሰው! ይህን ማወቅ ትወዳለህን? ክፉ ምግባር ወይም በጎ ምግባር በተፈጥሮ የሚገኙ አይደሉም። እነዚህ ኹለቱ ከክፉ ልብ ወይም ከመልካም ልብ የሚገኙ ናቸው።

(ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ
አምስቱ የንስሓ መንገዶች፥ ገጽ 9)


ጾም ሙሽሪትን ትመስላለች፤ ሙሽሪትን በሠርግ አዳራሽ ኾነው የሚቀበሏት ሰዎች ቤቱን ያስጌጡታል፤ ይሸልሙታል፡፡ ወደ ሠርጉ አዳራሽ የሚገባውን ሰው የሠርግ ልብስ ለብሶ እንደኾነ፣ የቆሸሸ እንዳልኾነ አይተው ያስገቡታል፡፡

እኛም እንዲኽ ልንኾን ይገባናል ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡ ልቡናችንን በማንጻት፣ ልል ዘሊል ከመኾን በመራቅ፣ የክፋት እርሾን በማስወገድ፣ ከጾም ጋር አብረው የሚመጡትን የሚያጅቧትን መልካም ምግባራትንም ለመቀበል የልቡናችንን ውሳጤ በመክፈት የምግባር እናት፣ የማስተዋል እንዲኹም ለሌሎች ምግባራት ኹሉ ንግሥት የምትኾን ጾምን ልንቀበላት ይገባናል ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡ ይኽን ያደረግን እንደኾነ ታላቅ ሐሴት እናደርጋለን፤ ርሷም ቁስለ ነፍሳችንን ትፈውስልናለች፡፡

በሌላ አገላለጽ ብነግራችኹ ሐኪሞች በአንድ ታማሚ ሰውነት ውስጥ ያለውን ቆሻሻ፣ መርዘኛ ፈሳሽን ማስወገድ ሲፈልጉ መጀመሪያ የሚያደርጉት ነገር ቢኖር ታማሚው ምግብ ከመውሰድ እንዲቆጠብ ነው፡፡ ታማሚው ለጊዜው ምግብን ከመብላት ካልተከለከለ ሐኪሞቹ የሚሰጡት መድኃኒት እንደተፈለገው ውጤት አይሰጥም፡፡ እኛም ቁስለ ነፍስ ቁስለ ሥጋ የምትፈውሰውን ጾም ስንቀበላት ከዚኽ በላይ ልንኾን ይገባናል ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡

ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስን የምንሻ ከኾነ ልቡናችንን ንጹሕና ንቁ በማድረግ ልንወስዳት (ልንቀበላት)ይገባናል፡፡ እንዲኽ ካልኾነ ግን ከጥቅሟ ይልቅ ጉዳቷ ያመዝናል፡፡

#ቅዱስ_ዮሐንስ_አፈወርቅ


🔮 ምክረ ቃል 🔮

🔅 በሕይወታችን ውስጥ እግዚአብሔር የራቀ ፣ ሌላው ቀርቶ ከእኛ አጠገብ የማይገኝ የሚመስልበት ጊዜ አለ።  እነዚህ ጊዜያት እምነታችን ደካማ የሚመስልበት እና እግዚአብሔር ለእኛ በእውነት እንደሚያስብልን ለማመን የምንታገልበት ወይም ምናልባት እግዚአብሔር መኖሩን እንኳን መጠራጠር የምንጀምርበት ጊዜ ነው።  በምዕራባዊው የክርስትና ባህል እነዚህ ጊዜያት ብዙውን ጊዜ የነፍስ ጨለማ ምሽት(The dark night of the soul) ብለው ይጠሩታል።እግዚአብሔር ከእኛ የራቀ ይመስላል እኛም ከእምነታችን ጋር እንታገላለን።

🔅 በእንደዚህ ዓይነት ጊዜያት እግዚአብሔር ከራሳችን እስትንፋስ ይልቅ ወደ እኛ እንደሚቀርብ እና እኛ ብቻ ግን እሱ እንደሌለ እንደሚሰማን ማስታወሱ ጥሩ ነው።  እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ባለን ግንኙነት ውስጥ እንድንሠራ ለማድረግ እንዲህ ያሉትን ወቅቶች በሕይወታችን ይጠቀማል።  ስንታገል እንጠነክራለን።  እግዚአብሔር ራሱን ያገለለ በሚመስልበት ጊዜ አንድ ህፃን በእግሩ ቆሞ እንዲሄድ ጥቂት ርቀት ላይ ሆኖ እንደሚጠብ ወላጅ አይነት ነው። ልጁ የመጀመሪያውን እርምጃውን ብቻውን እንዲራመድ ያበረታዋል። ወላጁም ህፃኑ ከወደቀበት ለመድረስ ዝግጁ ነው። ነገር ግን ህፃኑ የመጀመሪያውን እርምጃ እንዲራመድ ወላጅ መፍቀዱ  ለልጁ እድገት አስፈላጊ ነው። በሕይወታችን ውስጥ የእግዚአብሔርን መገኘቱ የምንገነዘበው በትጋትና ተጋድሎ ነው ነው፣ እና የበኩላችንን እስካደረግን ድረስ፣ የእግዚአብሔር ጸጋ በብዛት ይፈስልናል።
✨💧✨💧✨💧✨💧✨

  ✍ አባ ትሪፎን


''ስትጸልይ በማክበር ውስጥ መሆንን ተለማመድ፣ የልብና የሥጋ ማክበር ይኑርህ፣ የስሜቶች ሰላምም እንዲሁ። ቀስ በቀስ መዝሙራትን፣ ወንጌላትንና የዘወትር ጸሎቶችን አጥና። በሁሉም ጊዜ ውስጥ ጸሎት መጸለይን ተለማመድ፣ ስትሠራ፣ ስትራመድና ከሌሎች ሰዎች ጋር ስትቀመጥ እንኳ፣ ዘወትር ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እኔ ኃጢአተኛውን ማረኝ እያልህ መጸለይን ተለማመድ።

በማንኛውም ጊዜ ለሌሎች ሰዎች መጸለይን ተለማመድ፣ ለሁሉም ሰዎችም ፍቅር አሳይ፣ ለጠላቶችህና አንተን ለሚሰድቡህ ሰዎች እንድትጸልይ የሚያዝህን የእግዚአብሔር ትዕዛዝ ተለማመድና ተግባራዊ አድርግ።"

#አቡነ_ሺኖዳ_ሣልሳዊ


#ደብረ_ምጥማቅ  (ግንቦት_21)

ግንቦት ሃያ አንድ በዚች ዕለት አምላክን የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በደብረ ምጥማቅ በስሟ በተሠራች ቤተ ክርስቲያን ጉልላት ላይ በብርሃን መርከብ ተቀምጣ ፊቷ በግልጥ ስለመታየቱ የክርስቲያን ወገኖች ሁሉም ታላቅ በዓልን ያደርጋሉ።

እርሷም በልጅዋ የመለኮት ብርሃን የተጐናጸፈች ናት በዙሪያዋም የመላእክት ሠራዊት የመላእክት አለቆችም በየማዕረጋቸው ክንፋቸውን ዘርግተው ይቆሙ ነበር ይጋርዷታልም። ሱራፌልም ማዕጠንታቸውን ይዘው ለንግሥዋ ገናናነት ይሰግዳሉ በየስግደታቸውም እንዲህ እያሉ ያመሰግኗታል። አብ በሰማይ ሁኖ ተመለከተ እንደ አንቺ ያለ አላገኘም አንድ ልጁንም ልኮ ከአንቺ ሰው ሆነ።

ሁለተኛ ሰማዕታትም በየማዕርጋቸው ረቂቃን በሆኑ ፈረሶቻቸው ተቀምጠው እየመጡ መጀመሪያ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአምባላይ ፈረሱ ወርዶ ይሰግድላታል እንዲሁም ባልንጀሮቹ ሰማዕታት መጥተው ይሰግዱላታል ።

ከእርሱ በኋላ የሚመጣው በዱሪ ፈረስ የሚቀመጥ ይህ መርቆሬዎስ ነው። ከዚህም በኋላ ሰማዕታት ሁሉ በመከታተል መጥተው ይሰግዱላታል ምስጋናም ያቀርቡላታል። ሁለተኛም ደግሞ የጻድቃን አንድነታቸው መጥተው በፊቷ ሰግደው ይመላለሳሉ።

ሄሮድስ የገደላቸው ሕፃናትም መጥተው ይሰግዱላታል በፊቷም እየዘለሉ አንዱ በአንዱ ላይ እየዘለለ በመተቃቀፍም ይጫወታሉ የተሰበሰቡትም በአዩ ጊዜ ደስታ ይመላባቸዋል በሰማይም ያሉ ይመስላቸው ነበር።

እናትና አባቱም የሞቱበት ቢኖር ወይም ከዘመዶቹ ወይም ባልንጀራዉ ቅድስት ድንግል እመቤቴ ሆይ ዕገሌን አሳዪኝ ብሎ በሚለምናት ጊዜ ቀድሞ በነበረበት መልኩ ያን ጊዜ ታመጣዋለች። ደግሞ መሀረባቸውን ወደላይ ይወረውሩላታል የወደደችውንም በእጇ ተቀብላ መልሳ ትጥልላቸዋለች ለበረከትም በየጥቂቱ ይካፈሉታል።

እንዲህም አምስት ቀን ሁሉ ክርስቲያንም እስላሞችም አረማውያንም ያይዋታል። ወደ ቤታቸውም ለመሔድ ሲሹ በፊቷ ሰግደው ይሰናበቷታል እርሷም ትባርካቸውና ይመለሳሉ።

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም አምላክን በወለደች በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ይማረን በረከቷም ከእኛ ጋር ይኑር ለዘላለሙ አሜን::

(#ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት)


ጌታችን ሆይ በሰውነታችን ውስጥ በሚፈጠር አለመስማማት ምክንያት እንዳንስት፤ እኛን ለማገዝ ስትል መንፈሳዊ እርዳታህን አድርግልን፡፡

ከአንተ ጋር ኅብረት ከሌለን በቀር ከስሜቶቻችን እስረኝነት በቀላሉ ማምለጥ የማይታሰብ ነው፡፡ ፈቃዳችንን ገርተን እንድንኖር መንፈሳዊ በረከቶችን በምናገኝባቸው ተግባራት እንድንተጋ የአንተ ፍቅር በልቦናችን ውስጥ ይፍሰስ፡፡

መልካም የሆነው ጸጋህን እንቀበልና ጆሮአችን ወደ አንተ አዘንብሎ እንዲሰማ ፈቃዳችንን እንሰጥህ ዘንድ አድርገን፡፡

              [ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ]

መልካም ቀን ❤️


"ሰንበት ከሁሉ ዕለት ትበልጣለች ሰውም ከሁሉ ፍጥረት ይበልጣል ኖኀ በታቦት (በመርከቡ) ውስጥ ከፍ ከፍ አደረጋት አብርሃምም በመሠዊያው አከበራት ሙሴ ደግሞ ሕዝበ እስራኤል ሰንበትን በአንድነት ሆነው በእውነት እንዲያከብሩዋት አዘዛቸው፡፡"
       ሊቁ ቅዱስ ያሬድ
መልካም ዕለት ሰንበት!!!


"#እባክህን_ከእሳቱ_ላይ_አትውረድ"
  
አንድ ወንድም አባ ጴሜንን "ምከረኝ" ብሎ ጠየቀው። አባ ጴሜንም "ድስት በእሳት ላይ እያለ ምንም አይነት ተባይ ሊቀርበውና ሊያበላሸው አይችልም። ከእሳት ወጥቶ ሲቀዘቅዝ ግን ነፍሳት ሁሉ ለመግባትና ለማበላሸት ይቻላቸዋል። ክርስቲያንም ከመንፈሳዊ ተግባር ካልራቀ ጠላት የድቀት ምክንያት አያገኝበትም" አለው።

ወዳጄ ሆይ ሕይወት ቀዝቅዛብሃለችን? ከእሳቱ ወደ መሬት ወርደህ በርደሃልን? የሕያውነትህ ሙቀት እሳት በማጣት ተንዘፍዝፏልን? ድስት የተባለ ሰውነትህ ክረምት የሚያህል ጉድን ተሸክሟልን? ዙሪያ ገባህ ፀሐይ እንደማትወጣበት ምእራብ ጨለማን የሚጠራ ሆኗልን? ማንነትህ እሳት እንዳጣ ምግብ ጥቃቅን ነፍሳት በተባሉ ኃጢአቶች (ቁጣ፣ ቸልተኛነት፣ ስስት፣ አልታዘዝ ባይነት፣ ጭንቀት፣ ሁሉን የመናቅ ስሜት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ...) ተወርሮ፣ መዓዛ ቅድስና ተለይቶት እጅ እጅ ብሏልን? ሞቅ የሚያደርገው አጥቶ በዓለማዊነት ሻግቷልን? የተባዮች መጫወቻ፣ የተውሳኮች መቀለጃ ሆኗልን? እንግዲያውስ በቶሎ ወደ እሳቱ ውጣ፡፡

ወዳጄ ሆይ ሃይማኖት በተባለችና ከሰማይ በወረደች ልዩ እሳት (ሉቃ.12፥49) ላይ ተቀምጠህ የድስትነትህን ሙቀት መልስ፡፡ እምነት፣ ተስፋና ፍቅር (1ቆሮ.13፥13) በተባሉ ሦስት ጉልቻዎች ላይ በምቾት ተጥደህ የሕይወትህን የኃጢአት ብርድ አስወግድ፡፡ ንስሐ በተባለች ነበልባል ውበትነት የክረምትህን ጽልመት በምስራቃዊ በጋነት ድል ንሳ፡፡ በሥጋ ወደሙ ፍምነት ድስት የተባለ ሰውነትህን በከዊነ እሳትነት ቀድስ፡፡ እባክህን በቶሎ ወደ እሳቱ ውጣ፡፡

ሃይማኖት የተባለ እሳትን ተባይ አይቀርበውም፡፡ እምነት ተስፋና ፍቅር የተሰኙ ጉልቻዎችን ተውሳኮች ሽቅብ አይወጡአቸውም፡፡ የነበልባለ ንስሐን ብርሃንና ሙቀት ነፍሳተ ጽልመት መቋቋም አይችሉም፡፡ ስለዚህ በእሳቱ ላይ እስካለህ ድረስ (በመንፈሳዊ ተግባራት እስከጠነከርክ ድረስ) አንተ ሁሌም ከተባይና ከነፍሳት ብልሽት (ከአጋንንት) የራቅክ ነህ፡፡

ወዳጄ እባክህን ከእሳቱ ላይ አትውረድ፡፡ እሳቱ በደንብ ይነድ ዘንድ ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት የተባሉ እንጨቶችንና ምጽዋት የተባለ ጋዝን መጨመርህን እንዳትዘነጋ፡፡ እንዲህ ከሆነ ዘንዳ ድስትነት ሁሌም የሞቀ ይሆናል፡፡ እጅ እጅ ከማለት፣ ከመሻገትና የተባይ መጫወቻ ከመሆን ትድናለህ፡፡

ወዳጄ ሆይ እባክህን ከእሳቱ ላይ አይትውረድ፡፡

በኃጢአት "እጅ እጅ '' ከማለትና በበደል ከመሻገት እግዚአብሔር ይሠውረን! አሜን!

(ሕሊና በለጠ ዘኆኅተብርሃን)


#ዕርገተ_እግዚነ_ወመድኃኒነ_ኢየሱስ_ክርስቶስ!!

በዚህች ዕለት የክብር ባለቤት ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእኛ በነሣው ሥጋ ከአባቱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ወደአለው የአንድነት አኗኗሩ ከሰማያት በላይ ያረገበት ሆነ።

እርሱም በረቀቀ ጥበቡ በመከራው በሞቱና በመነሣቱ ሥራውን ከፈጸመ በኋላ አርባው ቀን ሲፈጸም በነፋሳት ክንፍ ላይ ሆኖ ዐረገ።

ያን ጊዜ በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ ወጣ በነፋሳትም ክንፎች ላይ ሁኖ ወጣ ያለው የዳዊት ትንቢት ተፈጸመ። በዚህም ዕርገቱ ለሚያምኑበት በልዕልና ወደሚኖሩበት የሚዐርጉ መሆናቸው ተረዳ ተረጋገጠ ራስ በአለበት ሕዋሳት ሊኖሩ ይገባልና ።

አዳም አስቀድሞ በምድራዊ ርስቶች በሲኦልም እንደኖረ መኖርንም እንደ ቀደመ እንዲሁ ዳግማዊ አዳም ጌታ በመንግሥተ ሰማያት ርስት መኖርን ቀደመ። የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ዕርገቱን ከትንሣኤው አከታትሎ ወዲያውኑ አላደረገም መናፍቃን ዕርገቱ ምትሐት ናት ብለው እንዳያስቡ።

ጌታችንም በረቀቀ ጥበቡ የደቀ መዛሙርቱን ተሸብሮ የነበረ ልቡናቸውን እያጽናና መነሣቱንም እያስረዳቸው ከትንሣኤው በኋላ አርባ ቀን ኖረ። በጌታችንም ዕርገት የዳንኤል ትንቢት ተፈጸመ እንዲህ የሚል ሌሊት በራእይ አየሁ እነሆ ታላቅ እንደ ሰው ልጅ የሆነ መጣ ዘመናትን ወደሚያስረጃቸው ደረሰ ከፊቱም አቀረቡት።

የዘላለም አገዛዝ ጌትነት መንግሥት የዘላለም ሥልጣን ተሰጠው ሕዝቡና አሕዛቡ ሁሉ መንደር መንድረው የሚኖሩትና ነገዱም ነገሥታቱም ሁሉ ይገዙለታል አገዛዙም የዘላለም አገዛዝ ነው መንግሥቱም የማያልፍ የማይጠፋ ነዋሪ ነው።

#ስንክሳር_ዘወርኀ_ግንቦት_8




ግንቦት 16 በዓሉ ለቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ

በዚህ ዕለት ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በብዙ ምክንያቶች ዓመታዊ መታሰቢያ ክብረ በዓሉ እንደሆነ የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት ያስረዳሉ

1 በእስያ በኤፌሶን በዙሪያው ሁሉ ዞሮ ወንጌልን ማስተማሩ  መስበኩ ተዝካረ በዓል ለስብከቱ ነው (መጽሐፈ ስንክሳር የግንቦት 16 ንባብ)

2 በትምህርቱ በአምልኮተ ጣዖት የነበሩትን እስኪመልሳቸው ከሰይጣን ወጥመድ እስኪያድናቸው ድረስ በክፉዎች እጅ የተቀበለው መከራ ይታሰብበታል
በመጽሐፈ ገድሉ እንደተጻፈው ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ወንጌልን ለመስበክ ወደ ኤፌሶን ሲሄድ ጀምሮ ከደቀ መዝሙሩ ከአብሮኮሮስ ጋር ብዙ መከራዎችን ተቀብለዋል በዚህ ዕለት ይህን እናስባለን

3 ሦስቱ ወንጌላውያን ያስቀሩትን በማካተት ወንጌልን መጻፉ ይታሰባል
ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌሉን  ከሁሉ መጨረሻ የጻፈ በመሆኑ ሦስቱ ወንጌላውያን ያላካተቱትን የጌታን ትምህርቶች እና ተአምራቶች አካቶ ልዩ ወንጌል ጽፎልናል
ከመጽሐፈ ስንክሳር ጋር አብሮ የሚገኘው የምስጋና መጽሐፍ መጽሐፈ አርኬ ላይ እንዲህ ተብሎ ተጽፏል

ሰላም ለከ ሶበ ሰማዕከ ዐዋዴ፡
እምቃለ ወንጌል ዘወርቅ እንበለ ተምያን ወመፍዴ፡
ዮሐንስ ዘኮንከ በእንተ ጽድቅ ነጋዴ፡
መኒነከ እመ ወላዲተ ወአበ ወላዴ፡
ምስለ ነዳያን ነበርከ በዴዴ፡፡
(አዋጁን በሰማህ ጊዜ ያለ ግብዝነትና ያለ ክፍያ ወርቃማ ስለሆነው የወንጌል ቃል ብለህ የምትወልድ እናትና የሚወልድ አባትን ትተህ ስለጽድቅ ነጋዴ የሆንክና ከነዳያን ጋር በደጅ የኖርክ ዮሐንስ ሆይ ሰላም ላንተ ይሁን)

4 ራእዩን ያየበት ዕለት መታሰቢያ ነው
ሊቃውንት ቅዱስ ዮሐንስን ከሚጠሩባቸው ስያሜዎች መካከል አንዱ አቡቀለምሲስ ነው ባለራእይ ማለት ነው የሐዲስ ኪዳን የትንቢት መጽሐፍ የሚባለውን ራእይ ዮሐንስን የጻፈ ወደ ፊት የሚሆነውን አስቀድሞ በራእይ  የተመለከተ በመሆኑ የተሰጠ ስያሜ ነው

5 በእስክንድርያ ሀገር ውስጥ ቤተክርስቲያኑ የከበረችበት ቀን ነው
የግንቦት 16 ስንክሳር የአርኬ ምስጋና ላይ

ሰላም ለቅዳሴ ቤትከ በእለእስክንድርያ ሀገር፡
እለ ሐነፅዋ ኬነዉት ወጠበብተ ምክር፡
ወእንዘ ትበውእ ዮሐንስ ውስተ መቃብር፡
ተኀባዕከ ወተሠወርከ በሥልጣነ ኀይል መንክር
ባሕቱ ልብስከ ዘተርፈ ለዝክር፡፡

ተጠባቢዎች በጠቢባኑ ምክር በእስክንድርያ ሀገር ላነፁት ቅዳሴ ቤትህ ሰላም እላለሁ፤ ዮሐንስ [ሆይ] ወደ መቃብር በገባህ ጊዜ ለመታሰቢያ እንዲሆን ልብስህ ብቻውን ቀርቶ በሚደንቅ ኃይል ባለው ስልጣን ተሰውረህ ታጣህ) ተብሎ እንደተጻፈ ቅዳሴ ቤቱ የከበረበትን ዕለት በዓል አድርገን እናከብራለን

♦ በአዲስ አበባ በሐዋርያው ስም በተሰየመው ብቸኛ ደብር በደብረ ነጎድጓድ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን በዓሉ ታቦት ወጥቶ በንግስ ባይከበርም ለሊት በማሕሌት ጠዋት በቅዳሴ ማታ በልዩ የሠርክ ጉባኤ  ታስቦ ይውላል

የሐዋርያው አባታችን ምልጃ እና ጸሎት አይለየን


“በቤት ውስጥ በሚስትህ ምክንያት አንድ ደስ የማያሰኝ ስሕተት ቢፈጠር ‘አይዞሽ’ ልትላት ይገባል እንጂ ኀዘኗን ልታባብሰው አይገባህም፡፡ ኹሉንም ነገር ብታጣም እንኳን ከጎኗ ኹን፡፡ እርግጥ ነው ለባልዋ ደንታ ከሌላት ሚስት በላይ ምንም አሳዛኝ ነገር የለም፡፡ በእናንተ መካከል ጸብ ክርክር ከሚፈጥር የሚስትህ ጥፋት በላይ አሳዛኝ ነገር የለም፡፡ ስለዚሁ ዋና ምክንያት ግን ለእርስዋ ያለህ ፍቅር እጅግ ጽኑዕ ሊኾን ይገባዋል፡፡ እኛ ክርስቲያኖች አንዳችን የሌላችንን ሸክም እንድንሸከም የታዘዝን ከኾነ፥ ከዚህ በላይ ደግሞ አንተ የሚስትህን ሸክም ልትሸከም ይገባሃል፡፡ በመኾኑም ድኻ ብትኾን ስለዚሁ ምክንያት በፍጹም አትናቃት፡፡ ሰነፍ ብትኾን ስለዚሁ ምክንያት አስተካክላት እንጂ አታዋርዳት፡፡ እርስዋ አካልህ ነችና፤ አንተም አካልዋ ነህና፤ አንድ አካል ናችሁና፡፡ ‘ክፉ ነች፤ ቁጡ ነች፤ ራስዋን መቈጣጠር የማትችል ግልፍተኛ ነች’ ልትለኝ ትችላለህ፡፡ ስለዚሁ ጠባይዋ እጅግ ልታዝን ይገባሃል፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ይህን ጠባይ ያርቅላት ዘንድ ጸልይላት እንጂ አንተም መልሰህ አትቈጣት፡፡ ልታሳምናት ሞክር እንጂ ወደ ሙግት አትግባ፡፡ እነዚህን ክፍተቶችዋን ከእርስዋ ለማራቅ ኹሉንም ዓይነት በጎ ዘዴዎችን ተጠቀም፡፡”

“ይህን እንደማድረግ ሚስትህን የምትመታትና የምታሠቃያት ከኾነ ግን እነዚህ ሕመሞችዋ እንዲድኑ አታደርጋቸውም፡፡ ኃይለኝነት የሚወገደው በጭካኔ ሥራ ሳይኾን በየውሃት ነውና፡፡ ከዚሁ በተጨማሪም ሚስትህ በየውሃት ስትይዛት ከእግዚአብሔር ዘንድ ሹመት ሽልማት እንደምታገኝ አስታውስ፡፡ ከአሕዛብ ፈላስፎች አንዱ ክፉ፣ መራራና ሥርዓት የለሽ ሚስት ነበረችው ይባላል፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን ለምን ከእርስዋ ጋር እንደሚኖር (ለምን እንደማይፈታት) በተጠየቀ ጊዜ ጠቢቡ ሰው በገዛ ቤቱ ውስጥ የፍልስፍና ትምህርት ቤት እንዳለው ነበር የመለሰው፡፡ ‘ዕለት ዕለት በዚህ ትምህርት ቤት የምማር ከኾነ ከሌሎች ሰዎች ይልቅ ታጋሽ እኾናለሁ’ ነበር ያለው፡፡ በዚህ ተደነቅህን? እኔ ግን መላእክትን እንዲያውም ከእነርሱም በላይ የዋሃን ኾነን እግዚአብሔርን እንድንመስለው ከታዘዝነው ከእኛ ይልቅ አረማውያን ሰዎች ጠቢባን ኾነው ስመለከታቸው ፈጽሜ አለቅሳለሁ፡፡ ያ ፈላስፋ ሚስቱን እንዳይፈታት ምክንያት የኾነው የእርስዋ ክፉ ጠባይ ነው፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ሰዎች ‘ይህ ፈላስፋ ይህቺን ሴት ሚስት ትኾነው ዘንድ ያገባት ይህን ለማግኘት ብሎ ነው’ ይላሉ፡፡ አንተም ዕጮኛ ስትመርጥ በምርጫህ ተሳስተህ ክፉ ሚስት አግብተህ ከኾነ (ብታገባ) ቢያንስ ቢያንስ ይህን አረማዊ ፈላስፋ አብነት አድርገው፡፡ ሚስትህን ለማስተካከል የተቻለህን አድርግ፡፡ ክፋትዋን በሌላ ክፋት አትመልስላት፡፡ ከእርስዋ ጋር ኾነህ የትዳርን ቀንበር የምትሸከም ከኾነ ሌሎች ብዙ ረብ ጥቅሞችንም ታገኛለህና፤ መንፈሳዊ ተግባራትን ለመተግበር ቀላል ይኾንልሃልና፡፡” 

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ


🍂  አቡነ አረጋዊ   

አባታቸው  ✥ ንጉስ ይስሐቅ
እናታቸው  ✥  እድና

🍂በቀደመ ስማቸው ዘሚካኤል ሲባሉ ከዘጠኙ ቅዱሳን መካከል አንዱ ናቸው። የንጉስ ልጅ ሆነው ሳለ የዓለምን ነገር ስለናቁ ወደ አባ ጳኩሚስ ዘንድ በመሄድ በአስራ አራቱ ዓመታቸው ስርዓት ምንኩስናን ተቀብለዋል።

🍂እናታቸውም ንግስት እድና የምናኔው ሕይወት ስለሳባት ወደ ገዳሙ በመምጣት እንደ ልጇ መንኩሳለች።

🍂ስለ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ በመጻሕፍት ስላነበቡ እንዲሁም ለእመቤታችን ድንግል ማርያም የአስራት ሀገር ሆና መሰጠቷን ከተረዱ በኋላ ይህችን ቅድስት ሀገር ለመጎብኘ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ጎብኝተው ወደ ሮም ተመለሰዋል።

🍂ከዚያም ተመለሰው ለስምንት ባልንጀሮቻቸው ሃገርስ ባሳየኋችሁ ሐዋርያ ሳያስተምራት በህጉ በስርዓቱ ጸንታ የምትኖር ብለው ከስምንቱ ጋር ከኬልቄዶን ጉባኤ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል ።

🍂አባታችን አቡነ አረጋዊ በዓት ፍለጋ ለብዙ ጊዜ ደክመዋል ኋላም በእግዚአብሔር ፍቃድ ደብረ ዳሞ በሚባለው ቦታ ደርሰዋል፤ በተራራውም ጫፍ ብርሃን ቢታያቸውም ተራራማ ስለነበር መውጫው ቢቸግራቸው የታዘዘላቸው ዘንዶ ተራራው ጫፍ አውጥቷቸዋል።

🍂ዘጠና ዘጠኝ አመት ሲሞላቸው ጌታችን በመንፈቀ ሌሊት ተገልጾላቸው ምድራዊ መንግስትን ትተህ ስላገለገልኝ ህልፈት ሽረት የሌለባትን ሰማያዊ መንግስቴን አወርስሀለው ብሎ ቃል ኪዳን ገብቶላቸዋል።

🍂በስምህ የተማጸነውን እስከ አስራ አምስት ትውልድ ድረስ እምርልሀለው አንተም ከሞት ኃይል ትሰወረላህ ብሏቸዋል። እነደ ተነገራቸውም አንደ ሄኖክና ኤልያስ ሞትን ሳያዩ ተሰውረዋል።

🙏 የጻድቁ አባታን አቡነ አረጋዊ ረድኤት በረከት አይለየን 🙏


ፍልሰተ ሥጋሁ ለአቡነተክለሃይማኖት
ግንቦት12
እንኳን አረሳችሁ አደረሰን !!

ግንቦት ፲፪ ቀን የጻድቁ አባታችን የአቡነ ተክለሃይማኖት ፍልሰተ ሥጋ የጻድቁ አባታችን የአቡነ ተክለሃይማኖት የዕረፍት ጊዜያቸው ሲደርስ

ጌታ እመቤታችንን መላእክትን ነቢያትን ሐዋርያትን ጻድቃን ሰማዕታትን አስከትሎ መጥቶ ወዳጄ ሆይ ልመናህን ሰምቻለው ከድካምህ ላሳርፍህ መጣሁ መንፈሳዊ ደስታ ካለበት ትኖራለህ በተስፋህ ያመነውን በቃል ኪዳንህ የተማጸነውን ሥጋህን ቆረስክበትን ደምህን ያፈሰስክበትንም ቦታ እጅ የነሳውን ሁሉ ከሞተ ነፍስ አድንልሀለሁ ከዚህ ቦታ በተስፋ ጸንተው በኪዳንህ ተማጽነው የሚኖሩ ልጆችህን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛልሀለሁ በ፶፯ ዘመን በኋላ ደቀ መዛሙርትህ ቤተ ክርስቲያን አንጸው ሥጋህን ወደዚያ ያፈልሱታል ብሎ ቃል ኪዳን ገብቶላቸው ነበር፡፡

ጊዜው ሲደርስ ለአበ ምኔቱ ለአባ ሕዝቅያስ ተገልጾ ጌታዬ የነገረኝን ተስፋ ሊፈጸም ጊዜው ደርሷልና በሩቅም በቅርብም ያሉ ደቀ መዛሙርቴን ሰብስበህ በ፲፪ (አስራ ሁለቱ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ደቀመዛሙር በተለያየ ቦታ ቃለ ወንጌልን የሰበኩ ያስተማሩ በነገሥታቱ ፊት በጽናት የመሰከሩ ቅዱሳን ናቸው) ሥጋዬን አፍልሱ እኔም ከቅዱስ ሚካኤል ጋር እመጣለሁ ምልክት ይሆንህ ዘንድ ስትገባ መብራቶቹን አጥፋ እኛ ስንመጣ ይበራል አሉት፡፡

እንዳሉትም ደቀ መዛሙርቶቻቸውን ከሩቅም ከቅርብም ሰብስቦ በዚህ ዕለት ሥጋቸው ካረፈበት ከመካነ አስቦ /ጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት ቢገቡ እንደ ሽቶ መዓዛው አምሮ አግኝተው ተሸክመው ወደ ቤተ መቅደስ አመጡት፡፡

አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖትም ከቅዱስ ሚካኤል ጋር መጥተው ከመንበሩ ተቀመጡ ሲመጡም የጠፉት መብራቶች በርተው ተገኝተዋል ::

እኒያም በእልልታ በደስታ አጽማቸው ከእግረ መንበሩ ሥር አኑረውታል፡፡

ጸሎታቸውና በረከታቸው ረድኤታቸውና ምልጃቸው በመላው ሕዝበ ክርስቲያን ላይ አድሮ ይኑር ለዘለዓለሙ አሜን።


የይቅርታ  እናት  ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ   !

✍️-የቅድስት ክርስቶስ ሠምራ የተጋድሎ ታሪክ እንደ ባሕር አሸዋ፣እንደ ሰማይ ክዋከበት ተቆጥሮ ተሰፍሮ ከማያልቀው ነገረ ቅዱሳን  መካከል አንዱ ነው።
      -ነገረ ቅዱሳንን መረዳት፣ማስረዳት ፣ማወቅና ማሳወቅም የወንጌልን አዝመራ መሰብሰብ ነው።
     - ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ በዚህ ዓለም ከከበሩ እግዚአብሔርን ከሚፈሩ ደጋግ ባልና ሚስት የተገኘችና የተመረጠች እናት ናት።
✍️የቅድስት ክርስቶስ ሠምራ የአባቷ ስም ደራሳኒ፣የእናቷም ስም እሌኒ ይባላሉ። በሸዋ ክፍለ ሀገር በቡልጋ አውራጃ ጌየ በተባለች አካባቢ እንደ ተወለደች ታሪኳ ያስረዳል።(#ገድለ ክርስቶስ ሠምራ ዘወርኃ መስከረም -ቊጥር-፪ )

    ደረሳኒ እና ዕሌኒ ልጃቸውን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራን በሃይማኖታዊና ሥነ-ምግባራዊ ሥርዓት አሳደጓት(ገድለ ክርስቶስ ሠምራ ዘመስከረም -ቊጥር፬ ) መጽሐፈ ገድሏ" ልጅቱ ክርስቶስ ሰምራ ባደገችና ዐቅመ ሔዋን በደረሰች ጊዜ የንጉሥ ባለሟል የሆነ••••የኢየሱስ ሞዓ ልጅ ለሠምራ ጊዮርጊስ በሕግ አጋቧት"ይላል።( ገድለ ክርስቶስ ሠምራ ዘመስከረም -ቊጥር፮ )እግዚአብሔር በረድኤት ከሚገለጥባቸው የቅድስና መንገዶች አንዱ ቅዱስ ጋብቻ ነው።

✍️- ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ለሠምረ ጊዮርጊስ ፲፩ ልጆች ወለደችለት ከነዚህም መካከል ፱ ወንዶች፣ ፪ቱሴቶች ነበሩ።(ገድለ ክርስቶስ ሠምራ ዘመስከረም -ቊጥር- ፲፬) ልጆቿንም ሕገ እግዚአብሔርን እያስተማረች በክብርና በሥርዓት አሳደገቻቸው።

✍️- ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ የትዳሯ ሰላማዊነት፣የባሏ አክብሮትና ፍቅር፣የልጆቿ መብዛት ፣የሀብትና ንብረቷ መድለብ እየሠመረ ቢሄድም የቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ልብ ግን የሚያስበው ግን ምናኔ ነበር።ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ፣ከዚያም በኋላ ልብሰ ምንኲስናዋን፣ ማለትም ቆቧን፣ ቀሚሷን፣ አጽፏን፣መታጠቂያዋን፣ አዘጋጀች።

✍️ ያልተለመደ ነገር ሲደረግ የተመለከቱት ቤተሰቦቿ ለምን እንደ ምታዘጋጀው ፣ለጠየቋት ጥያቄ " #ሃይማኖት ያስተማሩኝ አባቴ ልብስ አልቆባቸዋል፣ሲሉ ሰምቼ ለእርሳቸውም ነው የማዘጋጀው ፣"አለቻቸው።

      ከዚህ ላይ ሃይማኖታዊ ጥበብ ያልተከሰተላቸው አስመሳዮች ለምን የሌላ ነው አለች" ሊሉ ይችላሉ።ይህ ሥርዓት ግን ለ፪ ነገር ይጠቅማል።

፩•የምናኔ ጉዞ ገና ሳይጀመር በውዳሴ ከንቱ ላለመጠለፍ፣
፪•ይህን ርምጃዋን ዲያብሎስ በተለያዩ ሰዎች አድሮ ሊያደናቅፈው ስለሚችል ከዓላማዋ ሊገታት ስለሚችል መልካም ጥበብ ነው።በሌላ በኩል ልማደ መጻሕፍትም ነው።
-✍️ ከዕለታት አንድ ቀን ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ አገልጋዮችን " ወደ ቤተ ክርስቲያን እንሂድ" ብላ ይዛቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄደች ።የምናኔው መጀመሪያ ነበር።

✍️- ከዚያም ቤተ ክርስቲያን ጥቂት እንደምትቆይ ለቤተሰቦቿ አንዲት ፣ሠራተኛና አንድ ሕፃን ብቻ አስቀርታ
ሌሎችን አሰናብታ ምናኔው ተጀመረ፣የወላድ መናኝ የሚያልፈውን በማያልፈው ዓለም ለመለወጥ ልጇን አዝላ እግሬ አውጭኝ ብላ ገሠገሠች።እግሮቿ በደም ታጠቡ፣የራስ ፀጒሯ ተላጭቶ ወደቀ።የገዳማውያን አለባበሷን ለብሳ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ገባች።ማቴ 10÷37 በተግባር ላይ ሲተረጎም ተመለከትን።

✍️የተጋድሎ ሕይወቷ እየቀጠለ ኼዶ ከመከራዋ ብዛት ከገድሏ ጽናት ሰውነቷ ተበሳስቶ የዓሣ መመላለሻ እስኪሆን ድረስ ከባሕሩ ገብታ ወደ ግራና ቀኝ ሳትል ፲፪ ዓመት ሙሉ በጣና ባሕር ውስጥ ቆማ ትጸልይ ዘንድ ኃይለ እግዚአብሔር ተሰጣት።፲፪ ዓመት ሙሉ በባሕር ውስጥ መቆየት የሚቻለው ማነው? የሚል ጎደሎ እምነት ያለው ወገን ካለ: ባሕረ ኤርትራ እንደ ግድግዳ ቆሞላቸው እስራኤላውያን ማሻገር ይችላሉ ወይ?" ለሚያምን ሁሉ ይቻላል"(ማር 9÷22)

✍️መሴ በሲና ተራራ 40መዓልትና 40 ሌሊት ያለምግብ መቆየት ይችላል ወይ?ሠለስቱ ደቂቅ እሳት ውስጥ ገብተው ሳይቃጠሉ መውጣት ይችላሉ ወይ? ብሎ መጽሐፍ ቅዱስን መጠየቁ የተሻለ ይሆናል።

✍️" ከአቤል ጀምሮ እስከ ዛሬ የሞቱት ከዛሬም በኋላ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የሚሞቱትን አቤቱ ማራቸው ይቅርም በላቸው "አለችው ( ገድለ ክርስቶስ ሠምራ ዘግንቦት -ቊጥር፲፯ )

√ የአማላጅነት ጸጋዋ:
የቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ሕይወት የቅድስና ሕይወት በመሆኑ ለአማላጅነት የተመቸ ነው።

✍️ጌታ ምን አደርግልሽ ዘንድ ትሻለሽ? አላት ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ " አቤቱ ፈጣሪየ ሆይ ! ፈቃድህስ ቢሆን የአዳም ልጆችን ከሥቃይ ከኵነኔ ይድኑ ዘንድ ዲያብሎስን ይቅር ትለው ወይም ትምረው ዘንድ እለምንሃለሁ:የኃጥእን መመለሱን እንጂ የጥፋቱን አትወድምና አለችው ፣ የምለምንህ ወይም ማረው የምልህ ዲያብሎስን ወድጄው አይደለም ነገር ግን እሱ ከተማረ በአዳም ልጆች ላይ ሥቃይና ኵነኔ ሊኖር አይችልም ብየ በመገመት ነው እንጂ " ( ገድለ ክርስቶስ ሠምራ ዘግንቦት -ቊጥር36 -38 )ይህን ልመና ጌታችን የሚያስደንቅ ልመና ብሎታል።ይህ መልካም ሐሳብ የሚመነጨው የእምነት ፍቅር ካላቸው ሰዎች ልብ ውስጥ ብቻ ነው።
- የዲያብሎስን ተንኮል የሚያውቅ መድኃኔዓለም የቅድስት ክርስቶስ ሠምራን የአማላጅነት ነጻነት አልገደበውም።
√ የተሰጣት ቃል ኪዳን
✍"ሥጋሽን እንደ እናቴ እንደ ድንግል ማርያም ሥጋ እቀድሰዋለሁ" ማለት የእመቤታችን ሥጋ በኅሊና አምላክ የተቀደሰ ሲሆን የቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ሥጋ ደግሞ በገድል ፣በትሩፋት ተቀጥቅጦ ማኅደረ መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ያመልክታል።ነሐሴ 24 የዕረፍት መታሰቢያዋ ይከበራል።
  
በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ወርቃማዋ ፎገራ(The Golden lans scape of Fogera)  በደሴተ ጓንጉት ደብረ ምሕረት ቅድስት ክርስቶስ ሰምራ ክብረ በዓል ዓመታዊ በዓሏ በየዓመቱ ግንቦት ፲፪ ቀን በድምቀት ይከበራል፡፡ከወረታ ከተማ በስተ ምዕራብ በኩል  25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ጣና ዳር ዋገጠራ ቀበሌ ትገኛለች ፡

- የቅድስት ክርስቶስ ሠምራ  በረከቷ ፣ረድኤቷ ፣አማላጅነቷ አይለየን!
#ምንጭ
- ሐመር መጽሔት ግንቦት /ሰኔ 1997ዓ/ም
- ነገረ ቅዱሳን -፪ ( ገጽ-68)
- ገድለ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ(በትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት- 1992ዓ/ም )
- ልሳነ ተዋሕዶ ዘኦርቶዶክስ ሚያዝያ 7ቀን 1993 ቁ 53

              
መ/ር ተመስገን ዘገዬ
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የገነተ ኢዩሱስ ገነተ ማርያም  ቤተ ክርሰቲያን ሰባኬ ወንጌል !

Показано 20 последних публикаций.

1 394

подписчиков
Статистика канала