የእንጀራው አይን
እንጀራው ቀርቦልኝ፣ወጡ እስኪጨመር፡
ቡዝዝ ያሉ አይኖቹን፣ጀመርኩኝ መመርመር፡
የሱ ሺ አይኖች፣ከኔ ሁለት አይን፡
ወጡን እረስተነው፣በጥልቀት ተያየን፡
አይኖቹ ደፍርሰው፣እምባ አቅረው ሳይ፡
አልበላህም አልኩት፣ምንድነው ብሶትህ እስቲ እንወያይ፡
-------------------------
እንጀራ፦
ይገርማል ከጥንት ጀምሮ፣እስከዛሬ ድረስ፡
ማንም ልብ አላለ፣ያይኔን እምባ ማፍሰስስ፡
በሰማ ምጣድ ላይ፣ባሰፋችሁት ሊጥ፡
እቺን አለም ላያት፣አይኖቼን ስገልጥ፡
አይን አትይ አይባል አየው
ደሳሳ ጎጆ ውስጥ፣ትሪ ላይ አንጥፈውኝ፡
ሽሮ እያጣቀሱ፣በፍቅር ሲጎርሱኝ፡
መሬት ብወድቅ እንኳን፣በሽሚያቸው መሀል፡
አፈሩን አራግፈው፣ስመው ይበሉኛል፡
ደሞ አንዳንድ ቤት፣ከሚበሉት በላይ በብዛት ጋግረውኝ፡
ባይኖቼ ቀዳዳ ጥጥ እያስበቀሉ፣እኔን ሲያሻግቱኝ፡
አይን አትይ አይባል አየው
ስለ እምብርሀን ሲል፣በር ላይ የኔ ቢጤው፡
ለነፍሳቸው ያደሩ፣እንጀራ ሊሰጡት ከመሶብ አውጥተው፡
እኔም ደስ ብሎኝ፣የደሀ አንጀት ላርስ ጉዞ ተጀመረ፡
እንጀራ አልፈልግም፣ሳንቲም ይሁን ሲል ግን ቅስሜ ተሰበረ፡፡
ቢሆንም ግን
እምባ ስታይ አይኔ ላይ፣ብሶት ቢመስልህም፡
የደስታም እምባ ነው፣ሀዘን ብቻ አይደለም፡
በላባቸው ሰርተው፣ቤታቸው ሲያስገቡኝ የሚሰማኝ ደስታ፡
ከደሀ ቀምተው እንጉረስህ ሲሉኝ፣ጭንቄ ሲበረታ፡
ዝብርቅርቅ ስሜት ነው፣ባይኖቼ ላይ ያለ፡
ሀዘን ከደስታ ፣ባንድ የቀላቀለ፡
እናም ስማኝ ጓዴ፣ለሌሎችም ንገር፡
ሊበሉኝ ሲያስቡ፣ከየት እንዳመጡኝ እንደምመረምር፡፡
(አድናቆት ክፍሌ የብርቱካን)
ለአስታየቶ
@Adnakothttps://t.me/joinchat/AAAAAFIkf-kJGHVIki3yuw