"አላህ እንጂ ኮሮና አይገድልም" (ሌላኛው የገመዱ ጫፍ)
~~~~~~~~~~~~~~~~~~
ትላንት በኮሮና ወረርሺኝ የተነሳ ሰሞኑን እየታዩ ያሉ ሁለት ጫፍ የያዙ ዝንባሌዎችን አንስቼ ሰለ መጀመሪያው ጫፍ በስሱ ከዳሰስኩ በኋላ ለሌላኛው ጫፍ ቀጠሮ ይዤ ነበር። የዛሬው ዳሰሳየ ስለዚህኛው ይሆናል።
ሌላኛው እየተስተዋለ ያለው ጫፍ የሰበብ እርምጃዎችን ማጣጣል ነው። ይሄ እምነት የአእምሮን ጤነኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው። ለዚያም ነው ሸይኹል ኢስላም ኢብኑ ተይሚያ ረሒመሁላ፞ህ “የሰበቦችን ሰበብነት መካድ የአእምሮ ጉድለት ነው” ያሉት። [አልፈታዋ፡ 1/131]
ሌላው ቢቀር ሰው እንዴት የራሱን የእለት ከ’ለት ህይወት አይመለከትም? በየቀኑ የሚበላው የሚጠጣው በህይወት ለመቆየት አይደል? የሰበብ እርምጃዎችን የሚያጣጥል ሰው ለምን ከምግብና ውሃ ታቅቦ “ሐስቢየላ፞ህ” አይልም? ስለዚህ ወንድሜ! መብላትህ እንዳትራብ ሰበብ እንደሆነ ታውቃለህ ማለት ነው። ለዚያም ነው “እሱ ከፈቀደ ያበላኛል” ብለህ መብላት ያላቆምከው። “ረሃብ ሰው አይገድልም። የሚገድለው አላህ ነው” የሚል እጅ እጅ የሚል ፍልስፍና ውስጥ አልገባህም። ማግባትህ ለልጅ ማግኘት ሰበብ እንደሆነ በፅኑ ታምናለህ። ስለሆነም “ፈቃዱ ከሆነ ልጅ ይሰጠኛል" ብለህ እጅህን አጣጥፈህ አልተቀመጥክም። “ልጅ የሚገኘው በትዳር አይደለም፣ አላህ ሲሰጥ ነው እንጂ” የሚል የቀን ቅዠት ውስጥ አልገባህም። ታዲያ ምን ነክቶህ ነው መተላለፊያ መንገዶቹ በውል የታወቀን በሽታ እንድትጠነቀቅ ሲነገርህ “እባክህ ዋናው የአላህ ውሳኔ ነው!” እያልክ ከኢማንና ከተወኩል ኋላ ልታደፍጥ የምትሞክረው? ሕይወትህ ባጠቃላይ፣ ውሎ አዳርህ እንዳለኮ ከሰበቦች ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው። ዙሪያ ገባህን ተፍ ተፍ ማለትህን ሁሉ ለምን እንደሆነ እራስህን ጠይቅ እንጂ!!
ስለዚህ “ቢላዋ አይቆርጥም”፣ “እሳት አያቃጥልም”፣ “በሽታ አይገድልም” አይነት ቂላቂል ፍስፍና አታራምድ። አላህ ቢላዋን ሲፈጥረው የመቁረጥ አቅሙን አብሮ ሰጥቶታል። እሳትን እንዲያቃጥል አድርጎ ነው የፈጠረው። “የሰበቡን ፈጣሪ አትዘንጋ” ማለት “ነገሮች ተያይዘው የተፈጠሩበትን ሰበብ ችላ በል” ማለት አይደለም። “በአላህ ላይ ያለህን ተወኩል አጠንክር” ማለት አጥፊ ወደሆኑ ሰበቦች አይንህን ጨፍነህ ዘው ብለህ ግባ ማለት አይደለም። ይሄ እንዲያውም አላህን መፈታተን ነው። “ተወከልቱ ዐለላ፞ህ” እያልክ መኪናህን ወደ ገደል ብትነዳ “ከተወከልክበት” ጌታ ዘንድ ከተጠያቂነት የምትተርፍ ይመስልሃል እንዴ?!
ደግሞስ መመሪያዎቻችን ቁርኣንና ሱና፞ አይደሉ?! ታዲያ እኮ ሁለቱም ለተለያዩ ጉዳዮች ተጨባጭ ሰበቦችን እንድናደርስ አዕላፍ መልዕክቶችን ይዘዋል።
① የታዘዝነውን የምንፈልፅመው እና ከሐራም የምንርቀው ጀነትን ለማግኘት እና ከእሳት ለመራቅ ሰበብ እንዲሆነን ነው።
جَزَاءً بِمَا كَانُوا يَعْمَلُونَ
ይህ ምን ማለት እንደሆነ አስተውል።
② ከፍ ያለው ጌታ አላህ እንዲህ ይላል:–
(وَلَا تُلۡقُوا۟ بِأَیۡدِیكُمۡ إِلَى ٱلتَّهۡلُكَةِ وَأَحۡسِنُوۤا۟ۚ إِنَّ ٱللَّهَ یُحِبُّ ٱلۡمُحۡسِنِینَ)
“በእጆቻችሁም (ነፍሶቻችሁን) ወደ ጥፋት አትጣሉ። መልካም ስራንም ስሩ። አላህ መልካም ሰሪዎችን ይወዳልና።” [አልበቀራህ: 195]
ይህንን አምላካዊ ትእዛዝ በመጣስ እራሱንም ሌሎችንም ለአደጋ እያጋለጠ ከዚያ ይህም ጥፋቱ አልበቃ ብሎት ጭራሽ ይህንን እንዝህላልነቱን በተወኩል ስም ሲያቀርብ ብታዩ ምን ትላላችሁ?! እንዲህ አይነት ነገር ነው ዛሬ እያስተዋልን ያለነው።
③ ነብዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል:–
لو أنكم تتوكلون على الله حق توكله لرزقكم كما يرزق الطير، تغدو خماصاً وتروح بطاناً
“እናንተ በአላህ ላይ እውነተኛ የሆነን መመካት ብትመኩ ኖሮ ወፎችን እንደሚለግሰው ይለግሳችሁ ነበር። ሆዷ ተጨራምቶ ማልዳ ትወጣና ከሰዓት በኋላ ሆዷን ሞልታ ትመለሳለች።” [ቲርሚዚ: ቁጥር 2344]
እውነተኛ ተወኩል ማለት ይሄ ነው። ሰበብ እያደረሱ በአላህ ላይ መመካት። ወፏ ከጎጆዋ ወጥታ እንደምትንከራተተው የምታልመውን ለማሳካት መጣር፣ ሰበብ ማድረስ ይጠበቅብሃል።
④ ነብዩ ﷺ ዘመቻ ሲወጡ አካላቸውን ከጦር የሚከላከሉበት ጥሩር እና ጭንቅላታቸውን ከጠላት ጥቃት የሚጠብቁበት የብረት ቆብ (ሚጝፈር) ይለብሱ ነበር። ይህ ለምን ይመስልሃል ወንድሜ? መቼም አላህ የወሰነው እንደሚደርስ ጠፍቷቸው ነው አትልም? ወይም ተወኩላቸው ስለሳሳ ነው አትልም። ስለዚህ ሰበብ ማድረስን ከሳቸው እንማር።
⑤ ነብዩ ﷺ አንድ ሰው ግመሉን ‘አስሪያት ልወከል ወይስ ለቅቄያት ልወከል’ ብሎ ቢጠይቃቸው እንዲህ ሲሉ ነበር የመለሱለት፡-
«اعْقِلْهَا وَتَوَكَّلْ»
“እሰራትና ተወከል።” [ሶሒሑል ጃሚዕ፣ አልባኒ፡ 1068]
ይህንን ወርቃማ ንግግር ከጭንቅላትህ ውስጥ በደማቁ አስምርበት። ዛሬ ሰበቦችን ስለማድረስ ሲነገረው “እባክህ አላህ ነው የሚጠብቀን” የሚል ሰው ምሳሌው ግመሉን ፈቶ ከለቀቀ በኋላ “ሐስቢየላ፞ህ ወኒዕመል ወኪል” እንደሚል ሰው ነው። ግመል ጠባቂ ቢሆን በፍለጋ ነጭ ላብ በእግሩ ይንቆረቆር ነበር። ዛሬም እንደምትዘናጋበት ጉዳይ ዋጋ ትከፍልበታለህ። ጣጣህ አንተ ላይ ቢያልቅ ምንም አልነበረም። ችግሩ ጦስህ ወደ ሌላ የሚሻገር መሆኑ ነው።
⑥ አሁንም ነብዩ ﷺ እንዲህ ብለዋል፡-
«إِذَا سَمِعْتُمْ بِالطَّاعُونِ بِأَرْضٍ فَلاَ تَدْخُلُوهَا، وَإِذَا وَقَعَ بِأَرْضٍ وَأَنْتُمْ بِهَا فَلاَ تَخْرُجُوا مِنْهَا»
“በአንድ ሃገር ወረርሺኝ መግባቱን ከሰማችሁ ወደሷ አትግቡ። ባላችሁባት ሃገር ከተከሰተ ከሷ አትውጡ።” [ቡኻሪና ሙስሊም]
ወንድሜ ሆይ! ከዚህስ በኋላ የሚቀርህ እንጥፍጣፊ ማመሃኛ ይኖርህ ይሆን?
⑦ በተጨማሪ ነብዩ ﷺ ለቃል ኪዳን የመጣን ተላላፊ በሽታ ያለበት ሰው “ቃል ተጋብተነሃል። ወደ መኖሪያህ ተመለስ” ነው ያሉት። [ሙስሊም]
•
ማጠቃለያ:–
ስለዚህ ወንድሜ ሆይ! ሰበቦችን ስለማድረስ የሚደረግን ጥሪ ፈፅሞ አታጣጥል። እንዲያውም ብታስተውል እዚህ ዱንያ ላይ ነገሮች እንዳለ ከሰበብ ጋር በጥብቅ የተሳሰሩ ናቸው። ይሄ ፍንትው ያለ የእምነታችን አስተምህሮት ነው። ለዚህም ነው ሸይኹል ኢስላም አሕመድ ኢብኑ ተይሚያ ረሒመሁላ፞ህ “ሰበቦችን ከነጭራሹ ችላ ማለት ሸሪዐን ማጉደፍ ነው” ማለታቸው። [አልፈታዋ፡ 1/131]
ርእሳችንን ከወቅታዊው የኮሮና ጉዳይ ጋር ስናገናኘው በጤና ባለሙያዎች እየተሰጡ ያሉ ምክሮችን በጥብቅ በመከተል እራሳችንንም ወገናችንንም የመጠበቅ ሰበብ እናድርስ። በሰዎች ቸልተኝነት ሰበብ ነው ዛሬ በተለያዩ ሃገራት እልቂት እየደረሰ ያለው። ችግሩ እኛም ዘንድ ሰተት ብሎ ከመግባቱ በፊት አቅማችን የሚችለውን ሁሉ በጊዜ ልናደርግ ይገባል። እንዝህላልነታችን ከኛ አልፎ ሌሎችም ላይ ጉዳት አድርሶ በሚቀጣጠለው የጥፋት ሰንሰለት ከአላህ ዘንድ ተጠያቂ እንዳንሆን በጊዜ እንመከር።
||
https://t.me/IbnuMunewor