ለግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይሰጥ የነበረው አዲስ ፈቃድ፤ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆም ተደረገ
-- ---------------------------------------------------------------------
በአማኑኤል ይልቃል
የፌደራል የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን፤ ለአዲስ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፈቃድ መስጠት አቆመ። ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ፈቃድ መስጠት ያቆመው፤ ለግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እያዘጋጀ ያለውን “አዲስ የመመዘኛ መስፈርት” የማውጣት ስራን እስኪያጠናቀቅ መሆኑን አስታውቋል።
በኢትዮጵያ የትምህርት እና ስልጠና ጥራትን የማረጋገጥ ኃላፊነት የተጣለበት ይህ የፌደራል ተቋም፤ በሀገሪቱ ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ ማንኛውም የመንግስት እና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፈቃድ የመስጠት ስልጣን በማቋቋሚያ ደንቡ ተሰጥቶታል። ተቋሙ ፈቃድ በሚሰጣቸው የትምህርት ተቋማት ላይ ቁጥጥር የሚያደርግ ሲሆን፤ ባገኘው ውጤት መሰረትም ዕውቅና የመስጠት፣ የማደስ እና የመሰረዝ ስልጣን አለው።
ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ በመላው ሀገሪቱ ፈቃድ ከሰጣቸው 360 ገደማ የሚሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ፤ 60 በመቶ ያህሉ የተከፈቱት “በቅርብ ዓመታት” ውስጥ መሆኑን በተቋሙ የፈቃድ እና ጥራት ኦዲት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ውብሸት ታደለ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በብዛት እየተከፈቱ መሆናቸው ዘርፉ ባለሀብቶችን እየሳበ ስለመሆኑ ማሳያ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ውብሸት፤ ሆኖም በሚሰጧቸው ትምህርቶች ጥራት ረገድ ከፍተኛ ችግር እንደሚስተዋል አስረድተዋል።
በተጨማሪም የተቋማቱ መብዛት እና የሚቀበሏቸው ተማሪዎች ቁጥር ከተፈቀደላቸው “በብዙ እጥፍ” የበለጠ መሆኑ፤ ተቋሙ የሚያከናውነውን የቁጥጥር ስራ “አዳጋች” እንዳደረገው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። “ይህንን መግታት እና ጥብቅ የሆነ ቁጥጥር ማድረግ የሚቻለው፤ የተቋማቱ ቁጥር ሲቀንስ ወይም ባለበት ሲገታ ነው” የሚሉት አቶ ውብሸት፤ በዚህም ምክንያት አዲስ ለሚከፈቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፍቃድ መስጠት በማቆም፤ ያሉትን የማጥራት ስራዎች ላይ ትኩረት መደረጉን አስታውቀዋል።
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን “ክትትል ያላደረገባቸው፣ ፍቃዳቸው ያልታደሰ እና ፈቃድ ሳይኖራቸው የሚሰሩ ተቋማት” እንዳሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል። ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ በ2014 በጀት ዓመት ብቻ፤ “የመመሪያ ጥሰት ፈጽመዋል” ባላቸው ከ350 በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታውቆ ነበር። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ፈጽመዋቸዋል ከተባሉ ጥሰቶች ውስጥ፤ ፈቃድ ባልተሰጠባቸው የትምህርት መስኮች፣ ካምፓሶች እና የትምህርት አሰጣጥ ክፍለ ጊዜዎች ላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር ይገኙባቸዋል።
ባለሥልጣኑ ካለፈው ወር ህዳር 30፤ 2015 ጀምሮ ደግሞ አዲስ ለሚከፈቱ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፈቃድ መስጠት ማቆሙን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። የትምህርትና ስልጠና ባለሥልጣን በአዲስ ፈቃድ ላይ እገዳ ጥሎ በሚቆይባቸው ጊዜያት ውስጥ፤ ከዚህ ቀደም ፈቃድ ያገኙ ተቋማት ፈቃድ ያገኙበትን መንገድ፣ የተቋሞቹን ባለቤቶች ማንነት እና ያሉበትን ሁኔታ የመፈተሽ እቅድ ይዟል። የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ከዚህም ባሻገር፤ አዲስ ፈቃድ የሚያገኙ ተቋማት እና ተቋማቱን የሚከፍቱ ባለሃብቶች ምን አይነት መስፈርቶችን ማሟላት እንደሚጠበቅባቸው የሚደነግጉ መመሪያዎችን እየዘጋጀ ነው።
የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚያስጀምሯቸው የትምህርት ፕሮግራሞች፤ ፈቃድ ለማግኘት ማሟላት ያለባቸውን አዲስ የመመዘኛ መስፈርቶች (ስታንዳርዶች) የማዘጋጀት እና ያሉትን መመዘኛዎች የመከለስ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አቶ ወብሸት አስረድተዋል። ከእነዚህ ዝግጅቶች መጠናቀቅ በኋላ፤ ከዚህ ቀደም ፈቃድ ያላቸው የግል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሙሉ በመመዘኛ መስፈርቶቹ መሰረት ምዝገባ መፈጸም ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
እንደ አዲስ ምዝገባ የሚፈጸም መሆኑ ተቋማቱን “ለማጥራት እና እርምጃ ለመውሰድ” እንደሚረዳ የገለጹት አቶ ውብሸት፤ ከዚህ ሂደት በኋላ ከተቋማቱ እና ከተማሪዎቻቸው ጋር የተያያዙ ውሳኔዎች እንደሚሰጥባቸው ተናግረዋል። ውሳኔዎቹን ለመስጠት በሚያስፈልገው ጊዜ ምክንያትም፤ በተያዘው ዓመት አዲስ ፈቃድ የመስጠት ስራ ይጀምራል የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)