Dildiy - (ድልድይ)


Kanal geosi va tili: ko‘rsatilmagan, ko‘rsatilmagan
Toifa: ko‘rsatilmagan


“Let's build bridges, not walls.” Martin Luther King, Jr.

Visit my blog: https://dildiy.net/

ድልድይ - ግላዊ እይታና ጥልቅ የመሻገሪያ እሳቤዎች የሚጋሩበት ከንባብ፣ ከኑረት እና ከምናብ የሚቀዱ ንሸጣዎች መድረክ ነው።
-
ሃሳቦቹ ከየትኛውም የአስተሳሰብ ጎራ (ism) አይወግኑም!!

Concern & Concept

D.S.

Связанные каналы  |  Похожие каналы

Kanal geosi va tili
ko‘rsatilmagan, ko‘rsatilmagan
Toifa
ko‘rsatilmagan
Statistika
Postlar filtri


እስኪ እጆችህን ዘርጋና መዳፎችህን ተመልከታቸው... እንዲህ አድርገህ ካየሃቸው ሰነባብተሃል አይደል?... 
__

ዘርግተህ ስታያቸው ምን ተሰማህ?... ጠባቂነት፣ ሰጪነት ወይስ ብርታት?...

ሰዎች...

@ የሌሎችን ምጽዋት በመጠበቅ ወይም ከሌሎች እጅ ለመንጠቅ እጆቻቸውን ይዘረጋሉ፤
@ ለሌሎች አንዳች ለመስጠት እጆቻቸውን ይዘረጋሉ፤
@ በራሳቸው እዲስ ታሪክ ለመስራት እጆቻቸውን ይዘረጋሉ...
__

አንተ ግን...

ከሌሎች ጠብቀህ ያጣኸው አንድ ነገር እንዳለ ሲሰማህ እጆችህን ዘርጋና እንዲህ በል:


"...የሕይወት ፈተና ምን ቢበዛ የምቀበለውን ሁሉ የምትጠብቀው ከኒህ እጆች ብቻ ነው..."
__

@bridgethoughts


የመሰብሰብ ጉጉትህ ላይ እስካልሰለጠንክ ድረስ የሚበቃ ነገር የለም፤ ጊዜ በጨመረ - ቀን በተቆጠረ ልክ የፍላጎት አድማስ እየሰፋ፣ የመጨመር ሃሳብ እየተንሰራፋ ይቀጥላል...

የመጨመር ጉጉት ጉድለት ላይ ብቻ ከመቆዘም የሚፈጠር ህመም ነው፤ በቃኝ አለማወቅ ልክን የመሳት አባዜ ነው... ምን 'ሀብታም' ብትሆን በፍላጎትህ ላይ ገዢ እስካልሆንክ ድረስ የደስታን ደጅ አትረግጥም...

በሕይወት ውስጥ በቃኝ የማለትን ያህል ምልዓት የለም!!

ብዙ ሰው "ያለኝ ይበቃኛል" እያለ ያጣቅሳል - እንደ ጥቅሱ ግን አይኖርም፤ ጥያቄው ታዲያ 'ያለው ስንት ሲሆን ነው የሚበቃው?' የሚለው ነው፤

የኑሮ ቅንጦት የበዛበትም፣ መኖር ቅንጦት የሆነበትም እኩል 'ያለኝ ይበቃኛል' ካለ ልክ አይሆንም... ስሜትም አይሰጥም።

ቁምነገሩ 'ያለህ መብቃቱ' ሳይሆን ባለህ መብቃቃቱ ነው... 

ሁሉም ሰው 'ያለኝ ይበቃኛል' ሲል 'የሚገባውን' ብቻ ይዞ ላይሆን ይችላል... የተትረፈረፈለትም - ትራፊ ያጠጠበትም አንድ ሊሆን አይችልም... ግና የሚብቃቃ ሰው በውስንነት ውስጥ ሆኖም ጉድለት አይሰማውም...

ስትብቃቃ ያለህ ምንም ያህል ይሁን ደስታ ሳይርቅህ ትኖራለህ፤ ስታግበሰብስ ግን ምድሪቱ ሙሉ ስጦታ ሆና ብትቀርብልህ እንኳ በቃኝ አያውቅህም...

___
አንተ ዘንድ የበዛው ከሌላው ጎድሎ ነው፤ በማትፈልገው ጊዜ በስብሶ ሳትጥለው በሚፈልገው ጊዜ ለሚጠቀመው ስጠው!!
___
@bridgethoughts


እጅግ የተራቀቁ የጦር መሳሪያዎች - በጣም የተራራቁ ልቦች፣

እጅግ የዘመኑ የመገናኛ አውታሮች - ከርሞ የመነመኑ አብሮነቶች፣

ሰማይ ጠቀስ የድንጋይ ንብርብር - ከጠጠር ያነሰ ስነምግባር፣

እልፍ አዕላፍ 'የፍቅር' ሙዚቃ - አርቴፊሻል ከአንገት በላይ ቋንቋ
___
@bridgethoughts


ሁሌም ቢሆን መድረስን እንጂ በመዳረሻው ጉስቁልና ውስጥ ማለፍን ከቶ አንፈልግም… 

የብዙ ውብ ሕልሞቻችን ሰንደቅ ከከፍታው ወጥቶ ሳይውለበለብ ተረጋግጦ የሚቀረው አናት ድረስ የሚገፋን ጽናት ከውስጣችን ስለሌለ ነው… 

አንዳንዴ ቁልቁለት በወረድንበት ቅለት ዳገት መውጣት ያምረናል…
 
ኑረት ግና እንዲህ አይደለችም - ለእያንዳንዱ ምንዳ ተስተካካይ ፍዳ ታዘጋጅልሃለች… 

"No pain - No gain"
___
@bridgethoughts


እነርሱ...

አቋምህን ያያሉ - ስለ ቁመናና መልክህ ሚዛን ያበጃሉ፣
አለባበስህን ያያሉ - ስለ ኑሮ ደረጃህ ግምት ይወስዳሉ፣
ስትናገር ይሰማሉ - ስለ እውቀትህ ልክ ይደሰኩራሉ፣
አብረውህ ይውላሉ - አውቀው እንደጨረሱህ ያስባሉ።

እናም ...

ልብህን አያውቋትምና - የሕልምህ ከፍታ አይገባቸውም፤
ውስጥህን አያነቡምና - ደስታና ሃዘንህ አይሰማቸውም፤
ሃቂቃህን አይረዱምና - ፍርድ ለመስጠት ይቸኩላሉ፤
ተራራህን አልወጡምና - በኮረብታህ ልክ ያፌዛሉ...
___
የሆነስ ሆነና...

'እኔህ' በአንተ ዘንድ ዋጋው ስንት ነው??
___
@bridgethoughts


ትንሽ ከሚመስሉህ ነገሮች የሚቀዳ ደስታ ከሌለህ "ትልቁ" እስኪመጣ ሃዘን ይወርስሃል፤ ሃሳብህ በ 'ነገ' ላይ ተመስጦ በየቅጽበቱ የሚፈልቀውን ውበት ቸል ስለሚል ለደስታ ቀጠሮ ትሰጣለህ፤ 
_
በይመጣል ምኞት ዕልፍ ቅጽበት የሰዋህለት ነገር እጅህ ሲገባ ደግሞ ከግምትህ አንሶ ያበሳጭሃል፤ በእርምጃህ ልክ የሚፈነጥቀው ብርሃን ካልታየህ ከመዳረሻህ ጽልመት ይከብሃል፤ 
_
ልብህ ደስ የሚላት እንደምታስበው 'ከባድ' በሚባል ነገር አይደለም፤ ሙዚቃ፣ የሕፃን ፈገግታ፣ የንፋስ ሽውታ፣ የደጅህ አበባ፣ የወፎቹ ጺውጺውታ፣... የደስታህ ምንጭ ናቸው፤ አንዱም አይከፈልበት፣ አንዱም ቁስ አይደለ።
_
ባገኘሁት ብለህ ቋምጠህ - አገኘሁት ስትል ደስታ ካልሰጠህ የአንተ አልነበረም ማለት ነው፤
_
ከጥበቃ ነፃ ውጣ - ላይመጣም ይችላል፤ ደስታን ከውጭ አታስስ - ከውስጥ ያለው ይበልጣል።
___
@bridgethoughts


ቤተሰብህ መላ ሕይወቱን ሰጥቶ ላንተ ደስታ ሲኖር ፊቱ የፈገግታ ፀሐይ ሳታይ ኑረት ትቋጫለች፤
_

አንተ ወዲያ ቤተሰብህን ወዲህ ልጆችህን በማየት ተጠምደህ ሳቅ ከማለትህ በፊት የዕለታትህ ጀምበር ትጠልቃለች፤
_

ልጆችህ በተራቸው የራሳቸውን ኑሮ ማቅናትን ከመለማመዳቸው በፊት የአንተን ውለታ በማሰብ ድካም ትከሻቸው ትጎብጣለች፤
_

በየዘመኑ 'ራሱን የሚሸከም አንገት' የማናይበት የሆነ የተሳሳተ ነገር ያለ አይመስልህም?...
___
@bridgethoughts


____
በማግኘት ላይ ከተመሰጡ ሰዎች መዝገበ-ቃላት ሁሌም የምትጎድል አንድ ገጽ አለች - "በቃኝ" የታተመባት።
--

በረከቶቹን የማይቆጥር ሰው ኪስ ቀዳዳ ነው፤ ይጨምራል - ሞልቶለት ግን አያውቅም።
--

ደስታ - ባለው ከመብቃቃት እንጂ 'ጉድለት' ላይ ከመብሰልሰል መንጭቶ አያውቅም።
--
@bridgethoughts


ስላልተረዱህ ሃቅ የለህም ማለት አይደለም፣ 
ስላልሰሙህ አልተናገርክም ማለት አይደለም፣ 
ጆሮ ቢነፍጉህ ቁምነገር አጥተህ አይደለም፣ 
ጊዜ ባይሰጡህ ተሰልቺ ሆነህ አይደለም...
---
እንድ የሳትካት ጥበብ አለች:

"ዳኛ ሳለ - ተናገር
ውሃ ሲጠራ - ተሻገር"
___
@bridgethoughts


___
ሐይማኖቶች - ጠላት ያውቃሉ - ሰይጣን ይሉታል፤ በደሎቻቸውን በሙሉ ያላክኩበታል።
___
መሪዎች - ጠላት ያውቃሉ - ተቃዋሚ ይሉታል፤ የዕድገት ጸር - የጠብ ምንጭ አድርገው ይስሉታል።
___
ምንትስ ጎሳ - ጠላት አለው - ምንትስ ይለዋል፤ የሆነውን ሁሉ የሆነው በእርሱ ምክንያት እንደሆነ የተነገረውን እያመነ ይረግመዋል።
___
ሃገራት፣ ትውልድ፣ አንተ፣ ቤተሰብህ፣ አያት ቅድመ-አያትህ... ብቻ ሁሉም 'ጠላት አለኝ' ባይ... ሁሉም ግን ከራሱ ውጭ ነው።
___
እኔ ግን እልሃለሁ - ሰው ከራሱ ሃሳብ በላይ ጠላት የለውም።
___
@bridgethoughts


ከምታውቀው ገሃድ - የማታውቀው ዓለም ይገዝፋል፣ 
አውቀዋለሁ ካልከው - ያልተረዳኸው ይሰፋል፣ 
ከተረዳኸው ውስጥ - ያልተዛለቀህ ይበዛል፣ 
ገባኝ ካልከው እውነት - ያልገባህ ነጥብ ይረቃል፣ 
ከምታየው ጥቂት - ያልታየህ ነቁጥ ይልቃል፣ 
ደረስኩበት ያልከው - በሌላ ሃቲት ይተካል፣ 
ያረጋገጥከው 'እውነት' - ከርሞ በስህተት ይለካል...
__

ከቶ ሰው በምድር ላይ የሚያውቀው ነገር ምንድነው?
__
አንፃር ብቻ!!
__
@bridgethoughts


ይዘህ ልታቆይ ከማትችለው ነገር ጋር መጋመድ በጉዞህ ውስጥ ያለ እንቅፋት ነው፤ ማለፍ ዕጣው ከሆነ ነገር ጋር መቋለፍ 'የጉድለት' ታማሚ ያደርግሃል።
_
ሃብትና ቁስ ይጠፋል፣
-
ዝናና ስልጣን ይረሳል፣
-
ሰዎች ይለወጣሉ፣
_
'የኔ' ያልከው ሁሉ ያልፋል!!
---
ያለን በመኖሩ ልክ ጠብቀው እንጂ አትጣበቅበት - ሲሄድ ይዞት በቆየው ቦታ ልክ አትጎድልምና!!
__
@bridgethoughts


ሌሎች አንተን በሚረዱበት መንገድ ላይ ውሳኔ የማሳለፍ ስልጣን የለህም። ሁሉም እንደ ንሸጣው ነው የሚገነዘብህ።
__

ሰው ...

ካንተ እልፍ ማስረጃ በላይ ስንጥር መረዳቱ የምታሳምነው፣

ከጽኑ ህመምህ በላይ ጥቂቷ ጭረቱ የምትቆጠቁጠው፣

ኖረህ ከመዘንከው በላይ ሰምቶ የቆየው ልክ የሚመስለው፣

ከመርሕ ይልቅ ስሜት - ከፍትሕ ይልቅ ጥቅም የሚጋልበው ነው።
__

እናም...

ማንንም ለማስገረም አትልፋ፤ ማንንም ለማሳመን አትድከም።
___
የመጨረሻው ጠቃሚ ነገር አለመቆምህ ብቻ ነው - ሂድ!!!
__
@bridgethoughts


አማረኝ
.
.
.
እንደ ወፍ በርሬ - ከመሸበት ማደር
ድንበር ሳይገድበኝ - ጎጆዬን መሰደር
~
የኑረት ዝክንትል - ከማይደርስበት ጫፍ
የሰው ክፋት ጣሪያ - ከሌለበት አፋፍ
ያላንዳች ጠያቂ - በዘለቅሁ ከሕዋ
አድማሱን ባካለልኩ - በሆንኩኝ ጥላዋ

ደግሞም...
.
.
እንደ ንብ ከንፌ - ካበባ ላይ ማረፍ - ጣፋጭ ቃና መቅሰም
ውለታ ሳልጠብቅ - ማር ወለላ መስጠት - ለማያውቀኝ መድከም

ወይም...
.
.

የልጅነት ምናብ - የልቡና ውቅር - በሰጠኝ ጥሞና
ፍርድ የለሽ ማንነት - ትውስታ አልባ አዕምሮ - ፍጹም ንጽሕና
.
.
.
ቢሆን...
.
.

መከባበር ሕጉ - መተሳሰብ ጥጉ - ሰውነት ጠገጉ
ምድር ትልቅ ነበር - ከጀነት ከገነት - ከአብርሆት ወጉ።
__

@bridgethoughts


ተስፋ ማድረግ መልካም ነው፤ 'ነገ መልካም ይሆናል' ብሎ ማሰብም ችግር የለውም...
__

© የማይመጣ 'ነገን' መጠበቅ ግን ችግር አለው፤

© 'ነግ' ይሉትን ቅዠት እውነት ብሎ ለደስታ ቀጠሮ መስጠት ግን ችግር አለው።

© እልፍ 'ነገ' ቃል እንደተገባለት ሰው በደል መስራትም ችግር አለው፤
___
አስተውል...

'ነገ' ውስጥ መጠበቅ፣ 'አሁን' ውስጥ ግን መኖር አለ፤ 

በጉዞህ ውስጥ መጠበቅን የሚያህል ሕመም፣ መኖርን ያህል ደስታ የለም።
___
ጥያቄው... 'ትኖራለህ?' ወይስ 'ትጠብቃለህ?' ነው!!
___
@bridgethoughts


መራር እውነት
___
ፍለጋ ስትወጣ ሁሌም የምታገኘው ሰው ራስህን ብቻ ነው፤ ለእኔህ ያለኸው የመጨረሻው ሰው አንተ ነህ። 
~
ሌሎች ካንተ ጋር ሁሌ አይኖሩም፣ ቢኖሩም ከትርፍ ጊዜያቸው እንጂ ከጥቅማቸው ላይ ሸርፈው አይሆንም። 
~
እኔታህ ግን በየትኛውም ጊዜ፣ ቦታ እና ሁኔታ ውስጥ ከአንተ ጋር ነው፤ እስከ መጨረሻዋ ትንፋሽ...
~
እናስ... ለወትሮአዊው አንተ ስጦታህ ምንድነው?
__
@bridgethoughts


ከራስ ኑረት ጎድሎ
ከራስ ባዶ አሟጦ - ለልጅ እንደመኖር
ከራስ መሻት ቆርሶ
የራስ ህመም ትቶ - ቤዛን እንደመቸር፤
.
በታጠፈ አንጀት
ለራስ ቁራሽ ሳስቶ - ለልጅ ሆድ መቃተት
ምርኩዝ ተደግፎ
ድኩም ገላ ይዞ - 'አይዞህ በርታ' ማለት፤
.
የልጅነትን ወዝ...
የውርዝና ጣዕም - የጉልምስና ወግ፣
ዕድልና ጊዜ...
ውበትና ተስፋን - ሰውቶ መጠውለግ፣
.
.
.
እናት
.
.
.
የምድር ስጦታ ...
.
.
ልክ አልባ በረከት - የከፍታ ፈለግ፣
ፍጹማዊት ወዳጅ - የፍቅር ሁሉ ጠገግ።
___
Rewritten
___
@bridgethoughts


መስሎኝ
____
የእኛ ያልነው ጽዋ ... በፍቅር ሰይመን
የመላነው ገንቦ ... ከየራስ ሰውተን
‘እንቅመሰው’ ያልኩሽ ... ገጥሞ አፍሽ ካ’ፌ
አንድ ነን ብዬ ነው ... በስሜት ከንፌ
.
.
.
ደግሞም ቢመስለኝ ነው ... የጠፋ ልዩነት
የፍቅር አውድማችን...
‘እኔ’ ‘አንቺ’ ሲበራይ ... ‘እኛ’ የሆነበት
.
.
.
ግና የመውደድ ሕግ ... በየራስ ነው ካልሽኝ
መሶቡን ጣጥለሽ ... ኩርማን ካቆየሽኝ
ነጠልሽኝ!!
ለየሽኝ!!
ከአዳራሽ ገፋሽኝ!!
.
.
.
~
ምን ቀረ እንግዲህ ... ከነበር ከቃልሽ 
እንፋሎት ሆነብኝ ... ይብቃን እኔም ተውኩሽ
ትርፉ ራስ ማጣት ነው 
ደጅ ላደረ ፍቅር - የስሜት ቀን ሲመሽ።
_
@bridgethoughts


ምራቅ ንጹህ የሚባለው አፍህ ውስጥ እስካለ ድረስ ነው፤ ከተፋኸው በኋላ ንጽህናው ይቀራል።
~
ክፉ ቃል እንደተተፋ ምራቅ ነው - ባወጣኸው ቅጽበት ንጽህናህን ያስቀራል!!
__
@bridgethoughts


የሰው መልክ
____

~
በኑሮ ዳገት ላይ ~ ሊሆን አከንባሎ
ውድቀት ፈተናውን ~ እጅ ሊያሰጥ ጥሎ
አለ ሽቅብ የሚያይ ~ የሚገፋ ቶሎ፤
____

~
ደልዳላው ላይ ደርሶ ~ ወደላይ ’ሚቃጣ
የሚሻ አዲስ ዳገት ~ ለከርሞ ’ሚወጣ
አለ አንዳንድ ሰው ~ ፍርሃቱን የቀጣ፤
____

~
ደግሞም አለ ከላይ ~ የሚማትር ቁልቁል
መውጣት ያታከተው ~ የኑሮን መሰላል
ለመመለስ ቋምጦ ~ ቆሞ ’ሚያሰላስል፤
____

~
ሌላም ከንቱ አለ ~ ከተራራ እግርጌ
አዘቅት ላይ ቆሞ ~ የሚመኝ አሮጌ
የሰበብ ከረጢት ~ የስንፍና እጅጌ፡፡
__
bridge thoughts

20 ta oxirgi post ko‘rsatilgan.

365

obunachilar
Kanal statistikasi