⭕️ግጥም⭕️
ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድኅን
በራ የመስቀል ደመራ
የአደይ ችቦ እየፋመ÷ እየጋመ
ኢዮሃ እያስገመገመ እየተመመ
የመስቀል ደመራ
በራ፡፡
በራ የአዲስ ዘመን ችቦ
በመስከረም ሰብል አብቦ
ከዋክብቱን ፈነጠቀ
ርችቱን አንጸባረቀ
ተኳለ አዲስ ደመቀ
መስኩን በቀለም አዝርእት÷ በጥበብ አጥለቀለቀ
ሸለቆው ተንቆጠቆጠ÷ ተራራው አሸበረቀ
ኢዮሃ ኢዮሃ አበባዬ! ምድር ሕይወት አፈለቀ
ነጋ÷ የአዲስ ዘመን ችቦ
ፈካ÷ ፀደይ አረብቦ
ሌሊቱ እንደጎሕ ቀደደ÷ ጨለማው እንደቀን ጠራ
እንደውቅያኖስ ዕፀዋት÷ እንደጠፈር ኮከብ ደራ
ምድር ሥጋጃ ለበሰ÷ የጌጥ አልባሳት ተቀባ
ሰማይ በእልልታ አስተጋባ
ኢዮሃ መስከረም ጠባ፡፡
ነጋ÷ የአዲስ ዘመን ችቦ÷ ምድር ሕይወት አፈለቀች
የምሥራች አዝርእቷን÷ አዲስ ቡቃያ ወለደች
የአደይ አበባን ለገሠች
ለአዲስ ዘመን አዲስ ብርሃን÷ አዲስ መስከረም ገበየች
ነጋ÷ የአዲስ ዘመን ችቦ
ፈካ÷ ፀደይ አረብቦ
በራ÷
የመስቀል ደመራ፡፡
ጸጋዬ ገብረ መድኅን
መስከረም ፲፱፷፫ - መስቀል አደባባይ
ይግቡ ⤵️⤵️⤵️
🦅
@pilasethiopia 🦅
🦅
@pilasethiopia 🦅
🦅
@pilasethiopia