MIKRE AIMRO | ምክረ-አዕምሮ™


Kanal geosi va tili: Butun dunyo, Amharcha


አስተሳሰባችንን ለመጠበቅ፣
አዕምሯችንን በአዎንታዊ ሀሳቦች ለማነፅ፣
ወደ ከፍታው የሚያሻግሩ ምክረ ሀሳቦችን ለማጋራት ለሁላችን የተዘጋጀ ቻናል ነው።
@mikreaimro
ይቀላቀሉን ዘንድ በአክብሮት ተጋብዘዋል!
ለወዳጅዎ ማጋራትዎን እንዳይረሱ!
🏠Welcome to your Home! 🏘
Personal Contact: @epha_aschalew
Insta: instagra.com/epha_aschalew

Связанные каналы  |  Похожие каналы

Kanal geosi va tili
Butun dunyo, Amharcha
Statistika
Postlar filtri


ማብቂያ አብጅለት!
➡️➡️➡️🗣️🗣️
በድለውህ ይከሱሃል፤ አቁስለውህ ሸንጎ ፊት ያቆሙሃል፤ ጎድተውህ ተጎጂ ለመሆን ይጥራሉ፣ አሰቃይተውህ ሲያበቁ አዛኝ ተንከባካቢ ለመምሰል ይሞክራሉ። ዝምታህ ሞኝነት፣ ትዕግሥትህም ቂልነት ሊመስላቸው ይችላል። ፈቅደህ በተዋሃደህ ማንነት ቢዘባበቱብህ፣ በየዋህነትህ ምክንያት ጥለው ሊሻገሩህ ቢሞክሩ፣ በዝምታህ ምክንያት ሴራ ቢያሴሩብ እስኪያጠፉህ ግን አትጠብቅም፤ እስኪጫወቱብህ ግን ዝም አትልም።

አዎ! ጀግናዬ..! አስመሳይነታቸውን ግታው፣ በደላቸውን አስቁም፤ እያየህ እንዳለየ፣ እያወክ እንዳለወክ ማለፉን ተው። እርምጃ መውሰድህ እራስህን ለመከላከል፣ እራስህን ለማዳን ብቻ አይደለም የእነርሱንም እውነተኛ ማንነት ለማጋለጥ ነው። መብትህን ሲጋፉ፣ ነፃነትህን ሲገፉ፣ አንተነትህን ሲያዋርዱ፣ ማንነትህን ሲያንቋሸሹ፣ ክብርህን ሲያረክሱ፣ ስብዕናህን ሲያሳንሱ ትዕግስትህ መፈተኑ፣ ስሜትህም መነካቱ አይቀርም። ነገር ግን እያንደንዱ ተግባር የእራሱ ገደብና ልኬት አለው። ከቀይ መስመርህ ባሻገር የሚመጣብህን ጫናና በደል የመጋፈጥ፣ የመመለስ የውዴታ ግዴታ አለብህ። ሚዛናዊ መሆንህ ቢያስከብርህ እንጂ አያዋርድህም፣ ቢያስሞግስህ እንጂ አያሳንስህም። እያወቁ አለማወቅም ገደብ አለው፣ በእራስ ማንነት ሲቀለድ ዝም ማለት አንድ ቀን ዋጋ ማስከፈሉ አይቀርም።

አዎ! ማብቂያ አብጅለት፤ ለሚደርስብህ የትኛውም አይነት እንግልትና ነቀፋ፣ ለሚወረወርብህ ክብረ ነክ ተግባር ፍፃሜ ስጠው። እራስህን ባታስከብር የሚያከብርህ አይኖርም፣ ለእራሰህ ባታስብ የሚያስብልህ የለም። ዋጋ የምትከፍለው ለእራስህ ብለህ ነው፤ ከወዳጅ መሳይ ተጣቶችህ የምትርቀው ለክብርህ፣ ለደህንነትህ ብለህ ነው። ከአስመሳዮች ተነጠል፣ የሚጠቅሙህ መስለው ዋጋህን ከሚያሳንሱ፣ ጥቅምህን ፈልገው ከተቆራኙህ፣ በወዳጅነት ሰበብ ከሚጫወቱብህ፣ በበግ ለምድ ከተሸፈኑ አታላዮች እራስህን አድን። በየዋህነትህ መጎዳት፣ በቅንነትህ መሰበር ይብቃህ፤ በልበሙሉነት ቀና ብለህ እራስህን ማስከበር፣ ለእራስህም ተገን መሆን ጀምር።
ግሩም ድንቅ ቀን ይሁንልን! 🏞🌞🌅
✍️ (Epha A.)
ምክረ-አዕምሮ ለተሻለ ነገ! 🦋
#SHARE እንዳይረሳ ቤተሰቦች!

YouTube አማራጭ ይቀላቀሉን!
🔺🔻 SUBSCRIBE NOW
https://www.youtube.com/channel/UCIZv4h3iDx2C7CGbv9WIkVg?sub_confirmation=1
ምክረ-አዕምሮ/ @mikre_aimro 😊 💪


ይቅርብህ!
➡️➡️🗣️
ፍቅር ሰጪ እንጂ ተቀባይ አይደለም፤
ፍቅር ስጦታ እንጂ ብድር አይደለም፤
ፍቅር ቀሪ እንጂ ተመላሽ አይደለም። እራስህን ጠይቅ፦ መቼ ነው የፍቅር ህይወት ሊኖረኝ የሚገባው? አሁን ለፍቅር ህይወት ብቁና ዝግጁ ነኝን? እንዴት ላስኬደው እችላለው? ከሁሉም በላይ ለሌላ ሰው የሚሆን፣ በደስታ የማካፍለው፣ በነፃነት የማጋራው የተሟላ ፍቅር ውስጤ አለን? ብለህ ጠይቅ።

አዎ! ጀግናዬ..! የምትሰጠው ከሌለህ ይቅርብህ። ጠባቂነት ይጎዳሃል፤ ተቀባይነት ያሳምምሃል፤ ያሰቃይሃል። ከምንም በላይ የወደድከው ሰው መዓት ያወርድሃል፤ በመከራና ስቃይ ውስጥም ሆነህ በእልህ መውደድህን አንድታቆም አይፈቅድልህም፤ ባዶነትህን ከእርሱ ውጪ የሚሞላልህ ያለ አይመስልህም፤ በእራስህ ላይ ማዘዝ እስኪሳንህ እንደፈለገው እንዲጫወትብህ ፈልገህ ትፈቅዳለህ። በፍፁም በባዶነትና በተረጂነት ስሜት ሆነህ ፍቅርን አትጀምር። ይህን አደረክ ማለት ጉዳትህን ለማባባስ ቆርጠህ ተነስተሃል ማለት ነው። ከእራስህ አውጥተህ መስጠት ስትችል ብቻ ወደ ፍቅር ህይወት ግባ። ለእራስህ ያለህ ፍቅር ለሌላውም እንደሚገባው ስታምን ብቻ የፍቅር አጋር ይኑርህ።

አዎ! ጀግኒት..! የምወደው ሰው ክፍተቴን ይሞላዋል፣ ባዶነቴን ያስረሳኛል ብለሽ ሳይሆን እኔ በፍቅሬ አክመዋለሁ፣ አበረታዋለሁ፣ እደግፈዋለሁ ብለሽ ፍቅርን ጀምሪ። ምንም እንኳን የጠበቅሽው ባይቀር በዘገየ ወቅት እንዳትጎጂ እራስሽን አቅቢ። ፍቅር ሙሉ ህይወት ነውና በእራስሽ ሙሉ ሳትሆኚ እንዳትገቢበት፣ ብቁነት ሳይሰማሽ ክፍተትሽን፣ ጉዳትሽን ይዘሽ እንዳትጀምሪው። ትኩረትሽን መስጠት ላይ እንጂ መቀበል ላይ አታድርጊ። እራስህን መውደድ፣ ማፍቀር፣ ማክበር፣ መንከባከብ፣ መጠበቅ፣ ማኩራት ስትጀምር፣ ይህን ማንነት የምታጋራው፣ የምታካፍለው ሰው ትፈልጋለህ፤ ካንተ ሙሉነት የምታቋድሰው፣ ለእራስህ የምታደርገውን በኩራት የምታደርግለት የእራስ ሰው የምትለውን ሰው ያኔ በልበሙሉነት ታገኘዋለህ።
ውብ ምሽት ይሁንልን! 🌘🌒💫✨
✍️ (Epha A.)
ምክረ-አዕምሮ ለተሻለ ነገ! 🦋
#SHARE እንዳይረሳ ቤተሰቦች! 🙏😍

YouTube አማራጭ ይቀላቀሉን!
🔺🔻 SUBSCRIBE NOW
https://www.youtube.com/channel/UCIZv4h3iDx2C7CGbv9WIkVg?sub_confirmation=1
ምክረ-አዕምሮ/ @mikre_aimro 😊 💪




ወደኋላ አትመልከቱ!
➡️➡️➡️🗣️🗣️🗣️
አንዴ አይደለም ሁለት ሶስቴና ከዛ በላይ በተደጋጋሚ ተጎድታችኋል፣ እየታመማችሁ የህመማችሁ ምክንያት ከሆነ ሰው ጋር ለረጅም ጊዜ ቆይታችኋል፣ የኔ በምትሉት ሰው ስቃይ ተደራርቦባችኋል፣ ግንኙነታችሁን ለማስተካከል ብዙ ጥራችኋል። ነገር ግን ነገሮች ሁሉ ከአቅማችሁ በላይ እንደሆኑ ከተሰማችሁ አንድ ልታደርጉት የሚገባ ወሳኝ ነገር አለ። መልካሙን ሁሉ ተመኙላቸው፣ ጀርባችሁን ስጧቸው፣ ፊታችሁን አዙሩ ከዛም እነርሱን ትታችሁ ወደፊት ተጓዙ። ህይወታችሁ የስቃይና የመከራ ይሆን ዘንድ የፈረደባችሁ አካል የለም። የሚበጃችሁን እያወቃችሁ የማይበጃችሁ መርዛማ ከባቢ ውስጥ አትቆዩ። ከዚህ ከባቢ ለመውጣት ከወሰናችሁ በፍፁም ወደኋላ እንዳትመለሱ። ልፍስፍስነት ማንንም አስከብሮና ነፃ አውጥቶ አያውቅም። ሰውን ሰው የሚያደርገው ከባዱ ውሳኔው ነው። ከምትወዱት ሰው ለመለየት መወሰነ ከባድ ነው፤ ነገር ግን የጋራ ጥቅም ካለው ከማድረግ ውጪ ሌላ አማራጭ የላችሁም። ውሳኔው ለጊዜው መራር ነው ለዘላቂው ግን ፈውስና ጣፋጭ ነው።

አዎ! ወደኋላ አትመልከቱ! ያለፈ ጠባሳችሁ እንዲሽር፣ ሰላማችሁ እንዲመለስ፣ ውስጣችሁ እንዲታደስ፣ ነፃ መሆንንና መረጋጋትን ከፈለጋችሁ በፍፁም ጥላችሁ የመጣችሁትን ሰውም ሆነ ሁኔታ ወደኋላ አትመልከቱ። በማይበጃችሁ የትኛውም ነገር ላይ ጨካኝ መሆንን ልመዱ፣ ከየትኛውም ጎጂ ነገር ውስጥ ለመውጣት ቆራጥ ሁኑ። ፈውስ ያለው በባዶ ምኞት ወይም በባዶ ፍላጎት ውስጥ አይደለም። ይልቅ ፈውስ ያለው በቆራጥ ውሳኔና በተጨባጭ ተግባር ውስጥ ነው። ምንም ነገር አስቀድሞ የእናንተ አልነበረም ዘላለምም የእናንተ  ሆኖ አይቆይም። ዋናው ጉዳይ ህመም አልባ ወይም ነፃ ህይወት መኖር ሳይሆን በህመምና በስቃይ ውስጥ ወደሚበጀው አቅጣጫ በፅናት መጓዝ ነው። ወደዳችሁም ጠላችሁም እውነታውን ፊትለፊት እስካልተጋፈጣችሁ ድረስ ምንም ነገር አያበቃም። ግንኙነቱ አልሰራላችሁም? ስራችሁ በፈለጋችሁት መንገድ አልሔደም? ህይወታችሁ አልሰመረም? እውነታው የማትፈልጉት ቢሆንም በሚገባ ተቀበሉት፣ አዲስ የተለየ መንገድን ጀምሩ፣ ወደኋላ አትዙሩ፣ በፊት ለጣላችሁ መሰናክል ዳግም ራሳችሁን አሳልፋችሁ አትስጡ።

አዎ! ጀግናዬ..! አሁን እየሆነብህ ያለውን ታውቃለህ፣ ታያለህ፣ ትሰማለህ ስለወደፊቱ ግን እርግጠኛ አይደለህም። የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል ነውና አባባሉ የትኛውም ነገር እንደሚሆንህና እንደሚሳካልህ ከሁኔታዎች ያስታውቃል። የምታየው ነገር ካላማረህ ውጤቱ ሊያምር እንደማይችል ተገንዘብ። የነገሮች ፍፃሜ ስቃይ ሊመስል ይችላል፣ ከለመዱት ሰውም ሆነ ሁኔታ መለየት ከባድ ሊመስል ይችላል ነገር ግን ስቃዩም ሆነ ክብደቱ ጊዜያዊ እንጂ ዘላቂ አይደለም። ጊዜያዊው ስቃይ የዘላቂው ፈውስ በር ከፋች ነው፣ ጊዜያዊው ህመም ለነፃነት መንገድ ጠቋሚ ነው። ከባድ ውሳኔዎችን ወስን፣ የሚያስፈራህን ነገር አድርግ፣ የተውከው ቦታ አትመለስ፣ ራስህን ከማንም በላይ ውደድ። መሔድ ያለበት ይሒድ ማንንም እንዲቆይ አትለምን፣ መምጣት የሚፈልግም ይምጣ ማንንም እንዲመጣ አታስገድደው። ለራስህ ነፃነት ስጥ፣ የልብ መሻትህን አዳምጥ፣ በከባባድ ውሳኔዎች ራስህን አሳድግ።
ግሩም ድንቅ ቀን ይሁንልን! 🏞🌞🌅
✍️ (Epha A.)
ምክረ-አዕምሮ ለተሻለ ነገ! 🦋
#SHARE እንዳይረሳ ቤተሰቦች!

YouTube አማራጭ ይቀላቀሉን!
🔺🔻 SUBSCRIBE NOW
https://www.youtube.com/channel/UCIZv4h3iDx2C7CGbv9WIkVg?sub_confirmation=1
ምክረ-አዕምሮ/ @mikre_aimro 😊 💪


በእልህ ታደርገዋለህ!
➡️➡️➡️➡️🗣️🗣️
አንዳንድ ሁኔታዎች የመጨረሻ አማራጫቸው ሽንፈት ነው፤ አንዳንድ ሁኔታዎች የመጨረሻ መዳረሻቸው ውድቀት ነው፤ አንዳንድ ጉዞዎች ውስጥ ከእያንዳንዱ እርምጃቸው ስር እሾህ አለ፣ ከምንም በላይ ማንነትን ይፈትናሉ፣ እውቀትንና ማስተዋልን በብዙ ይገዳደራሉ። ነገር ግን ከሚሰጡህ የመጨረሻ በላይ የእራስህን አማራጭ ማስቀመጥ ትችላለህ። በእራስህ ስትተማመን ብቻ ጊዜያዊ ሽንፈቶችን አምነህ ትቀበላለህ፣ ውስጥህን ስታሳምን ብቻ ከእያንዳንድ ከባድ ችግር በላይ እራስህን ብቁና ዝግጁ አድርገህ ትገኛለህ፣ በእርግጥም የሚቀጣጠል የስኬታማነት አምሮት ውስጥህ ሲኖር የምትችለውን ሁሉ መሱዓትነት ስትከፍል እራስህን ታገኘዋለህ። ወቀሳዎች ጫና ውስጥ ይከቱሃል፣ ከውጭ የሚመጡ የበታችነት አመለካከቶች ያስጨንቁሃል፣ ውስጥህን ይረብሸዋል ነገር ግን እራስህን ከመሆን አያግዱህም።

አዎ! ጀግናዬ..! በእልህ ታደርገዋለህ! በሚቀጣጠለው ውስጣዊ መሻትህ ምክንያት እስከ ጥግ ትፋለማለህ፣ ለእራስህ በገባሀው ቃል ምክንያት ሃላፊነትህን በሚገባ ትወጣለህ፣ ምርጫህን ከማንነትህ ጋር ታዋህዳለህ፣ መነቃቃትን የተለተለት ተግባርህ ታደርገዋለህ፣ እራስህን ለመግዛት ንቁና ቆራጥ ትሆናለህ፣ ላመንክበት ነገር እስከመጨረሻው ለመፈተን እራስህን ታዘጋጃለህ። ባመንክበት ጉዳይ ውድቀትህ እንደማያቆምህ ልብህ ያውቀዋል፣ ለምትወደው ጉዞ ምንም ነገር መሱዓት ማድረግህ አይጎረብጥህም። እራስህን በተረዳሀው ልክ እራስህን ብቁ ለማድረግ ሁሌም መትጋትህ የግድ ነው። ሁላችንም የየእራሳችን የመዳረሻ ከፍታ አለን፣ እያንዳንዳችን የየእራሳችን የአስተሳሰብ ገደብ፣ የእምነት ገደብና የእውቀት ገደብ አለን። በእራሳችን ብንተማመንም የማያምኑብን ይኖራሉ፣ ሃላፊነታችንን የመወጣት አቅም ቢኖረንም አምነውን ሃላፊነትን የሚጥሉብን ሰዎች  ላናገኝ እንችላለን። 

አዎ! በውጫዊው አለም የሚሰጠን ቦታ ውስጣዊ እምነታችንን እስኪሸረሽር ልንጠብቅ አይገባም፤ በአካባቢያችን ዘንድ የተሰጠን ስፍራ እንዲረብሸንና መረጋጋትን እንዲነሳን መፍቀድ የለብንም። ቅርፅ አልባው ውሃ የተቀመጠበትን እቃ ቅርፅ ይይዛል፣ እራስህን እንደ ውሃ ተመልከት ከየትኛውም ከባቢ ጋር የመላመድና እራስህን የማስማማት አቅም ይኑርህ። ውጦ ከሚያሰምጥህ፣ አደናቅፎ ከሚሰብርህ፣ ተስፋህን ከሚያጨለመው፣ ጥረትህን በዜሮ ከሚያባዛው፣ ረዕይህ እንደማይቻል ደጋግሞ ከሚነግርህ፣ መፅሐፍ ማሳተም ማሰብህን ከሚያደንቀው ይልቅ የወረቀትን ዋጋ ንረትና የመፅሐፍህን አለመሸጥ ከሚነግርህ ሰው እራስህን ነጥል። ያንተ እይታ ማንም ጋር የለም፣ ያንተ የመረዳት ልክ፣ ያንተ ውስጣዊ እምነትና መነሳሳት በማንም ዘንድ የለም። ለእራስህ የሚስፈልግህን፣ የሚገባህን በሚገባ ታውቀዋለህ። ባወከው ልክም ማድረግ ያለብህን እራስህን ሰተህ በእልህ ታደርገዋለህ።
ውብ ምሽት ይሁንልን! 🌘🌒💫✨
✍️ (Epha A.)
ምክረ-አዕምሮ ለተሻለ ነገ! 🦋
#SHARE እንዳይረሳ ቤተሰቦች! 🙏😍

YouTube አማራጭ ይቀላቀሉን!
🔺🔻 SUBSCRIBE NOW
https://www.youtube.com/channel/UCIZv4h3iDx2C7CGbv9WIkVg?sub_confirmation=1
ምክረ-አዕምሮ/ @mikre_aimro 😊 💪




ቀና በሉ!
➡️➡️🗣️
ካቀረቀራችሁበት፣ አንገታችሁን ከደፋችሁበት፣ ከተሰበራችሁበት ነገር ላይ ቀና በሉ፤ በስህተታችሁ ደጋግማችሁ ከመጎዳት፣ እራሳችሁን ባላንጣ አድርጎ መኖርን፣ እራሳቹን ችላ ማለትን አቁሙ፣ በምትኩ ቀና ብላችሁ ለእራሳችሁ ፈውስ ሁኑ፣ ቀና ብላችሁ ማንነታችሁ ላይ ስሩ፣ ዋጋችሁን ጨምሩ፣ ወደፊታችሁን አስተካክሉ፣ ስህተታችሁን አርሙ፣ ለክብራችሁ ቦታ ይኑራችሁ። ፈርቶ ያቀረቀረ፣ ለእራሱ የሚሰጠውን ዋጋ አሳንሶ አንገቱን የደፋ፣ ለእራሱ መብት መሟገት የማይችል፣ ደጋግሞ እራሱን በተመሳሳይ አዙሪት ውስጥ የሚከት ሰው ሁሌም እንደተጎዳ፣ ሁሌም እንደተጨቆነና አብዝቶ ዋጋ እንደከፈለ ነው። ለስሜታችሁ በመገዛት የህመማችሁ ምክንያት እራሳችሁ ከመሆን ተቆጠቡ፣ ለሰዎች ቅድሚያ በመስጠት እራሳችሁ እራሳችሁን መሰበርና ማጎሳቆል አቁሙ።

አዎ! ጀግናዬ..! ለእራስ መቆም፣ እራስን መጠበቅ፣ ለእራስ መወገን መብት ቢሆንም ግዴታዎችም እንደሚያካትት አስተውል። የምትፈልገውን ህይወት ለመኖር ከሁሉ የሚቀድመው ተግባር እራስን መጠበቅ፣ እራስን ማዳንና ለእራስ መቆም መቻል ነው። ተሰብረህ ስብራትህን ለማከው ሌላ ሰው እንዲመጣልህ አትጠብቅ፣ አቀርቅረህ፣ አንገትህን ደፍተህ፣ እራስህ ላይ ጨክነህ፣ ህይወትህ ላይ ጥላ አጥልተህ፣ ስህተቶችህ ላይ አተኩረህ፣ ከችግሮችህ ጋር ተዳብለህና ከፈተናዎችህ ጋር ተዋህደህ እየኖርክ ማንም አንተን ከዚህ ሁሉ አጣብቂኝ ውስጥ ቀና ሊያደርግህ አይመጣም፣ ማንም አንተን ሊታደግ ዋጋ አይከፍልም። ቀና ብለህ መፋለም ላለብህ ነገር ተፋለም፣ እራስህን ሰተህ ለእራስህ ቁም፣ መብትህን ለማስከበር እራስህን አጠንክር፣ ውስጥህን አበርታ።

አዎ! ቀና በሉ፣ ዙሪያችሁን ተመልከቱ፣ አካባቢያችሁን ቃኙ። ከሚጎዳችሁ፣ አላስፈላጊ ዋጋ ከሚያስከፍላችሁ፣ ደጋግሞ ከሚያሳምማችሁ ከባቢ እራሳችሁን ነጥሉ፣ ገለል በሉ፣ ወደ እራሳችሁ ተመለሱ። ቀና ማለት እስራትን ይፈታል፣ ቀና ማለት በእራስመተማመንን ይጨምራል፣ ቀና ማለት አካባቢያችንን እንድንቃኝ ያደርገናል፣ ቀና ማለት ፈተናዎችን ተሻግሮ ለማለፍ ያዘጋጀናል። ቀና ብላችሁ ለእራሳችሁ ተፋለሙ፣ ቀና ብላችሁ ወደፊት ተራመዱ፣ ቀና ብላችሁ ለእራሳችሁ ችግር መፍትሔ ፈልጉ። ማብቃት ያለበት ጉዳይ እንዲያበቃ፣ መጀመር ያለበትም ጉዳይ እንዲጀመር ቀና ብላቹ ፊት ለፊት ተጋፈጡ፣ ውስጥ ውስጡን እራሳችሁን መጉዳታችሁን አቁሙ። ቀና በሉ ለመብታችሁ ቁሙ፣ ለእራሳችሁም ከለላ ሁኑ።
ግሩም ድንቅ ቀን ይሁንልን! 🏞🌞🌅
✍️ (Epha A.)
ምክረ-አዕምሮ ለተሻለ ነገ! 🦋
#SHARE እንዳይረሳ ቤተሰቦች!

YouTube አማራጭ ይቀላቀሉን!
🔺🔻 SUBSCRIBE NOW
https://www.youtube.com/channel/UCIZv4h3iDx2C7CGbv9WIkVg?sub_confirmation=1
ምክረ-አዕምሮ/ @mikre_aimro 😊 💪


በጥቅምሽ አትጎጂ!
➡️➡️➡️🗣️🗣️
ሁላችንም የየእራሳችን የህይወት መንገድ አለን። ስህተት ይሁን ትክክል፣ የውድቀት ይሁን የስኬት፣ የደስታ ይሁን የሃዘን፣ የማጣት ይሁን የማግኘት ሁላችንም የየእራሳችንን ምርጫ እንመርጣለን። በእራሳችን እይታ ጥሩ በመሰለን መንገድ እንጓዛለን፣ በመረዳታችን ልክ ይወዱናል፣ ያከብሩናል፣ ይቀበሉናል ከምንላቸው ሰዎች ጋር ወዳጅነትን እንፈጥራለን። ያለማንም ጣልቃገብነት ለወሰናቸው እያንዳንዱ ውሳኔዎችና ለመረጥናቸው ምርጫዎችም ሃላፊነቱን የመውሰድ ግዴታ አለብን። አንቺ ሄደሽ፣ እርሱም መጥቶ በመውደድ፣ በፍቅር፣ በመረዳዳት ተጣምራችሁ ሳለ በመሃከላቹ ለሚፈጠረው የትኛው ክፍተት ሃላፊነቱን የመውሰዱ ግዴታ የሁለታችሁም ነው። ለጊዜው ለሚሰማችሁ ከባድ አስጨናቂ ስሜት ተጠያቂው ማንም ሳይሆን እራሳችሁ ናችሁ።

አዎ! ጀግኒት..! በጥቅምሽ አትጎጂ፣ በትርፍሽ ዋጋ አትክፈይዪ፣ ለጊዜያዊ ደስታሽ ማንነትሽን አትጪ። ማንም ከህይወትሽ ቢወጣ መውጣት ስላለበት ይወጣል፣ ማንም ላንቺ ስሜትና ፍላጎት ግድ ባይኖረው ምርጫው የእራሱ ነው። ከእርሱ ለመጠቀም ብለሽ እራስሽን አትጉጂ፣ ከፍቅሩ ለማትረፍ ብለሽ እራስሽን አትጪ፣ እርሱ ጥሎሽ ስለሔደ እራስሽ ላይ አትጨክኚ። በግድ ወዳጅሽ የምታደርጊው ሰው የለም፣ ባንቺ ፍላጎት ብቻ ህይወትሽ ውስጥ የምታቆይው፣ የህይወት ዘመን አጋርሽ የምታደርጊው፣ እንደ ደጋፊና አበርታችሽ የምትቀበይው ሰው የለም። ህይወታችን ምርጫ እንደሆነች አስታውሺ። አንቺ ከብዙዎች እርሱን እንደመረጥሽው እርሱም ከብዙዎች ካንቺ ውጪ ሌላን የመምረጥ ሙሉ መብት እንዳለው አስተውይ። ሰዎች ወደ ህይወታችን ሲመጡ አንድም ለህይወት ዘመን አጋርነት፣ ሌላም ለትምህርት ሊሆን እንደሚችል አስቀድመን ልናምን ይገባል። የማይገባሽን ጥቅም ፍለጋ እራስሽን እንዳታጪ ተጠንቀቂ።

አዎ! ጀግናዬ..! የህይወት ፈተና በአጠቃላይ ያልጎዳህን ጉዳት አንድ የምትወደው፣ የምታከብረውና ከልብህ ያፈቀርከው ሰው ይጎዳሃል፣ ደጋግሞ ያሳምምሃል፣ በጣም ከባድ ዋጋ ያስከፍልሃል፣ ጠባሳው ለረጅም ጊዜ የማይሽር ዱላን ያሳርፍብሃል። ፈልጎም ይሁን ሳይፈልግ፣ ደስ እያለውም ይሁን እያዘነ ለስቃይህ ምክንያት ሆኖ ታገኘዋለህ። ነገር ግን ከሁሉም በላይ አንድ ነገር ተረዳ የምትመታበትን ዱላ እራስህ ካልሰጠሀው ማንም በእራሱ ዱሉ ከምትችለው ምት በላይ ሊያሳርፍብህ አይችልም። ምንም እንኳን አለመፈለግ፣ ትኩረት አለማግኘት፣ ፍቅርን መነሳት፣ በሚፈልጉት ሰው ህይወት ውስጥ ዋጋ ማጣት ቢያሳዝን ቢያስከፋም፣ ነገር ግን ማንም ይህን የማድረግ ምርጫ እንዳለው ማመን ይኖርብናል። ለአካባቢህ ተጠንቀቅ፣ ወደ ህይወትህ የሚገቡ ሰዎችን ከመግባታቸው በፊት በሚገባ እወቃቸው፣ ለህይወትህም ውበትና አስደሳችነት የሚጠበቅብህን ሁሉ ለማድረግ ለእራስህ ቃል ግባ፣ ከቃልም በላይ ለእራስህ ህይወት ደህንነት ብቁ መሆንህን በተግባር አሳይ።
ውብ ምሽት ይሁንልን! 🌘🌒💫✨
✍️ (Epha A.)
ምክረ-አዕምሮ ለተሻለ ነገ! 🦋
#SHARE እንዳይረሳ ቤተሰቦች! 🙏😍

YouTube አማራጭ ይቀላቀሉን!
🔺🔻 SUBSCRIBE NOW
https://www.youtube.com/channel/UCIZv4h3iDx2C7CGbv9WIkVg?sub_confirmation=1
ምክረ-አዕምሮ/ @mikre_aimro 😊 💪




ውሎህ ምርጫ ነው!
➡️➡️➡️🗣️🗣️
ዛሬ ምርጫህ ሳትሆን ስጦታህ ነች። ስጦታህን የመጠቀምና የማባከን ምርጫው ግን ያንተ ነው። እንደ ስጦታ የምንጠቀመውና እንደምርጫ የምናልፍበት የህይወት መንገድ አለ። መረጥክም አልመረጥክም የመረጥከውን ትኖራለህ፤ ወደድክም ጠላህም በወደድከው መንገድ፣ ሚዛን በደፋልህ ጎዳና ትጓዛለህ። ሳልፈልገው አረኩት፣ ሳይመቸኝ መረጥኩት የሚባል ነገር የለም። ለፍላጎትህ መክፈል የሚገባህን ዋጋ ስላልከፈልክ የማትፈልገውን እያደረክ ትኖራለህ፤ ስላልተመቸህ ሌላ አማራጭ ለመሞከር ዝግጁ አልነበርክምና ባልተመቸህና ስሜት በማይሰጥ ሁኔታ ውስጥ እራስህን ታገኛለህ።

አዎ! ጀግናዬ..! ውሎህ ምርጫ ነው። ማድረግ የሚገባህን ለማድረግ፣ መተው፣ መሻገር፣ ማለፍ የሚገባህን ለማለፍ ሁሌም ነፃ ነህ። ምንም እንኳን ቀንህ ስጦታ ብትሆንም የምታሳልፍባት መንገድ ግን ምርጫ ነው። በሚጠቅምህ ተግባር ማሳለፍ፣ በወደድከው ምርጫ መኖር፣ በሚመችህ አኳሃን ትርፋማ ማድረግ ያንተ ምርጫ ነው። ህልምህን እንደምትኖር የምታረጋግጠው በቀናት በሚደጋገሙ ተግባራትህ ነው። አንተ ዋጋ ሳትሰጠው፣ ትኩረት ሳታደርግበት፣ ጊዜ እንኳን ሳትመድብለት፣ ወደ ተግባር ሳትገባ የሚቀይርህ፣ የሚያሳድግህ፣ የሚያነሳህ በፍቃዱ የሚሰራለህ ቀን፣ ላንተ ብሎ የሚኖር ሃሳብም ሆነ ምኞት የለም።

አዎ! ለቀንህ ስሜት ይኑርህ፤ ለውሎህ ተጠንቀቅ። የተሻለ ነገን ማለምህን ቀጥል ስራህን ግን ዛሬ ጀምር፤ ብሩህ ወደፊት ማለምህን ቀጥል እርምጃህን ግን አሁን አሃዱ በል። ዋጋ ያልተሰጣት ቀን በምንም ተዓምር ዋጋዋን ማሳደግ፣ ትርፋማ መሆንና ለውጤት መብቃት አትችልም። ዛሬ ህልምህ ላይ የምትዘምትበት መሳሪያህ ነው፤ አሁን የነገህን በር የምትከፍትበት ሁነኛ ቁልፍ ነው። ባለቤቱ ያላከበረውን ስጦታ አካባሪ አይላክለትምና ቀንህ ያንተ እንደሆነች አስብ፤ ትርጉም በመስጠት አክብራት፤ በቻልከው ልክ ጣርባት፤ እንዳስፈላጊነቱ እረፍባት፣ ፋታ ውሰድባት። ነገር ግን ሁሌም የትርፋማነትህ ግብዓት አድርጋት።
ግሩም ድንቅ ቀን ይሁንልን! 🏞🌞🌅
✍️ (Epha A.)
ምክረ-አዕምሮ ለተሻለ ነገ! 🦋
#SHARE እንዳይረሳ ቤተሰቦች!

YouTube አማራጭ ይቀላቀሉን!
🔺🔻 SUBSCRIBE NOW
https://www.youtube.com/channel/UCIZv4h3iDx2C7CGbv9WIkVg?sub_confirmation=1
ምክረ-አዕምሮ/ @mikre_aimro 😊 💪


ወቀሳህ ነፃ አያወጣህም!
➡️➡️➡️➡️🗣️🗣️🗣️
በተበላሸ የአሰራር ስረዓት ውስጥ ልንኖር እንችላለን፣ የማይመቸን ስፍራ ልንገኝ እንችላለን፣ በማንወደው ሁኔታ ውስጥ እራሳችንን ልናገኝ እችላለን፣ በማይረዱን፣ በማያበረታቱን፣ በማይወዱንና በማያነቃቁን ሰዎች ልንከበብ እንችላለን፣ የመንግስትም ይሁን የመስሪያቤታችን አሰራር ላይመቻን ይችላል ነገር ግን እነዚህን ሁሉ ነገሮች እየደረደርን እያንዳንዱን አካል ብንወቀስ፣ በእነርሱ ብናሳብብ፣ በእነርሱ አለመመቸት ውድቀታችንን ብናመካኝ አንዳች የምናገኘው ነገር የለም። ላንተ ውድቀት ማንንም ብትወቅስ፣ ለእራስህ ስንፍና ምንም ምክንያት ብትደረድር፣ ህልምህን ላለመኖርህ የጓደኞችህን ተፅዕኖ እንደ ሰበብ ብትጠቅስ አንተም በነበርክበት ትቀጥላለህ፣ ምክንያቶችህም ደረጃና ከፍታቸውን ጨምረው ታገኛቸዋለህ።

አዎ! ጀግናዬ..! ወቀሳህ ነፃ አያወጣህም፤ ምክንያት መደርደርህ ወዴትም ፈቀቅ አያደርግህም፤ ለትንሹም ለትልቁም ሰበብ ማብዛትህ አንዳች ነገር በህይወትህ ላይ አይጨምርም፤ ዛሬ ነገ ማለትህ፣ ሰዎችን መጠበቅህ፣ በሌሎች መተማመንህ ወዴትም አያሻግርህም። ለእራስህ ህይወት ማንም ሃላፊነት ሊወስድልህ አይችልም፤ ላንተ ለውጥና እድገት ማንም መሪ ሊሆን አይችልም። ስቃይ ምክንያት በመደርደር ውስጥ አለ፤ ስቃይ ከምክንያቶችህ በላይ ለመሆን መጣር ውስጥ አለ፤ ስቃይ በተዳፈነው የምኞት ዓለም፣ በጨለመው የአማራሪነት ድግግሞሽ ውስጥ አለ። የትኛው ስቃይ የሚገባህን ነፃነት እንደሚያጎናፅፍህም ካንተ በላይ ማንም አያውቅልህም።

አዎ! ማንም ሰው አታላይ ማንነት ውስጡ አለው፣ ማንም ሰው ደጋግሞ የሚሸውደው፣ እያወቀ የሚያታልለው ማንነት አለው። ምክንያት የምትደረድረው እራስህን ለማሳመን ሳይሆን ሰዎችን ለማሳመን እንደሆነ ታውቃለህ፣ ሰበብ የምታበዛው ከማንም አንሰህ ላለመታየት እንደሆነ ልብህ ያውቀዋል። ኢጎ ሲመራን በምንም ነገር መበለጥን አንፈልግም፤ ምንም ላይ ከእኛ የሚሻል ሰው እንደሌለ እናስባለን፤ ሁሉን አዋቂ፣ በሁሉም ፈርቀዳጅ መሪ ሆነን ለመታየት እንጥራለን። ማንንም ለማሳመን የምትሆነውን ሰው እራስህን ለማሳመን ሁነው፤ ሌሎችን ለማስደሰት የምትፈነቀለውን ድንጋይ ለእራስህ ደስታ ብለህ ፈንቅለው። ለዘመናት የምታፍርበት ቦታ ቆመህ ለመቅረትህ ማንንም አትውቀስ፣ በትናንቱ መገኛህ ዛሬም በመገኘትህ ማንም ላይ ጣትህን አትቀስር። ወቀሳህን አቁምና መስራትን ጀምር፤ ሰበብ መደርደርህን ተውና እራስህን ወደማሻሻሉ ተመለስ።
ውብ ምሽት ይሁንልን! 🌘🌒💫✨
✍️ (Epha A.)
ምክረ-አዕምሮ ለተሻለ ነገ! 🦋
#SHARE እንዳይረሳ ቤተሰቦች! 🙏😍

YouTube አማራጭ ይቀላቀሉን!
🔺🔻 SUBSCRIBE NOW
https://www.youtube.com/channel/UCIZv4h3iDx2C7CGbv9WIkVg?sub_confirmation=1
ምክረ-አዕምሮ/ @mikre_aimro 😊 💪




የመረጠችህን ምረጥ!
➡️➡️➡️🗣️🗣️🗣️
ብዙ ሴት ታውቃለህ፣ ከብዙዎቹ ጋርም የተለያየ ግንኙነት ይኖርሃል። ከነዚህ መሃል ግን አንዲት ሴት ፈልጋና ወዳህ ወደ ህይወትህ ትገባለች። ይህቺ ሴት በተለየ መንገድ ከጎንህ ትቆማለች፣ እሴትን ትጨምርብሃለች፣ ዋጋህን ከፍ ታደርጋለች፣ ከማንም በተለየ ትረዳሃለች ታግዝሃለች፣ በእርሷ ካንተ ጋር መሆን ነገሮች ሁሉ ምንያህል መቀየር እንደቻሉ ታስተውላለህ። ይህቺ ሴት ልቧን ትሰጥሃለች፣ ክብሯን፣ መዓረጓን፣ ማንነቷን፣ ሁለመናዋን አሳልፋ ትሰጥሃለች፣ ታምንብሃለች። ምንም በሌለህ ሰዓት አብራህ ነች፣ የምትፈልገው አንተን እንጂ አንተ ያፈራሀውን ንብረት ወይም የተሰጠህን ዝና አይደለም። ይህቺ ሴት እውነተኛዋ ሴት ነች፣ ይህቺ ሴት ያንተ ሴት ነች፣ ይህቺ ሴት መርጣህ መጥታለችና ብታቆያት ታተርፋለህ ከተለየሃት ግን ብዙ ነገር ታጣለህ። ከመረጠችህና ከመረጥካት ሴት የትኛዋ ህይወትህን ልታጣፍጥ እንደምትችል አስቀድመህ ተረዳ። ምናልባትም ያንተ ምርጫ የማትፈልግህ ሴት ላይ ወድቆ ሊሆን ይችላል። እርሱ ደግሞ ምንያህል ከባድ ሁኔታ ውስጥ እንደሚከትህ አንተ ታውቃለህ።

አዎ! ጀግናዬ..! ብልጥ ሁን፣ ወዳጅህን በጥበብ ምረጥ። ወዳጅ ሲባል የአጭር ጊዜ ወዳጅ አይደለም፣ ወዳጅ ሲባል ዛሬ አግኝተህ ነገ የምትተወው ወዳጅ አይደለም። እውነተኛዋን የህይወት ዘመን ወዳጅህን በጥንቃቄ ምረጥ። ብዙ ሰው ልታውቅ ትችላለህ ብዙ ሰው ሊቀርብህ ይፈልግ ይሆናል ነገር ግን ሁሉም ፈላጊህ የልብ ወዳጅህ አይደለም፣ ሁሉም ጠላትህም የህይወት ዘመን አሳዳጅህ አይደለም። ሰው መቼ እንደሚቀየር አታውቅምና የመረጠችህን ምረጥ፣ ከወደደችህ ተጠጋ፣ ከፈለገችህ ጋር አንድ ሁን። ጊዜያዊ ደስታህን ብቻ ለማርካት እዚም እዛም አትበል። ህይወትህ የተገደበ ነው፣ በጊዜው ቁብነገር ያስፈልገዋል። ያየሀው ቢያምርህ አንዱንም ሳታገኝ ልትቀር እንደምትችል እወቅ። ጉጉትህን ገድበው፣ ስሜትህን ሁሉ አትስማ፣ የመረጥካትን ስታሳድድ የመረጠችህን እንዳታጣ ተጠንቀቅ። ቁብነገረኛ መሆን በሚኖርብህ ጉዳይ ስትቀልድ ብትገኝ ህንወትም በተራዋ ስትቀልድብህ ትመለከታታለህ። የህይወት ዘመን አጋርህ የህይወት አቅጣጫህን የመቀየር ትልቅ አቅም እንዳላት አስተውል። ነገሮችን ዛሬ ላይ ማስተካከል እየቻልክ ለነገ ቁጪት ራስህን አታመቻች።

አዎ! ጀግኒት..! ብዙ ምርጫ ቢኖርሽም መሆን የምትችይው ግን ከአንድ ሰው ጋር ነው፤ ብዙ ሰው ብታውቂም ያንቺ ብቻ ሊሆን የሚችለው አንዱ ብቻ ነው። ደጋግሞ የሚያስብሽ፣ የተለየ ቦታ የሰጠሽ፣ በልቡ ላይ ያነገሰሽ ሰው እያለ የማያስታውስሽን፣ በንቀት አይን የሚመለከትሽን አይንሽን ለአፈር ያለሽን ሰው እየተለማመጥሽ ጊዜሽን አታባክኚ። ሰው ወዶ እንጂ ተገዶ በፍቅር ሊወድቅ አይችልም፣ መርጦ እንጂ ተመርጦ ደስታን ሊሰጠን አይችልም። ራስሽን አታሳዝኚ፣ ውስጥሽን አታውኪ፣ ልብሽን አታድክሚ። ዓለም እንጂ ህይወት ዘጠኝ አይደለችም። ያንቺ ሰው እያለ ሌላ ሰው ጋር አትሂጂ፣ እንደ ልዕልት የሚንከባከብሽ እያለ እንደ ባሪያ የሚያሰቃይሽ ጋር አትሂጂ። ህይወትሽ ሲዖልንም ሆነ ገነት ይሆን ዘንድ ወሳኟ አንቺ እንደሆንሽ አስተውይ። ለህይወትሽ የሚሆን ትክክለኛ ሰው ምረጪ፣ በምርጫሽም የመረጠሽን ምረጪ። ከገዛ ስሜትሽ ቀደም በይ፣ በአስተውሎት ተራመጂ፣ ወሳኝ ውሳኔዎችን በአንክሮ አሳልፊ።
ግሩም ድንቅ ቀን ይሁንልን! 🏞🌞🌅
✍️ (Epha A.)
ምክረ-አዕምሮ ለተሻለ ነገ! 🦋
#SHARE እንዳይረሳ ቤተሰቦች!

YouTube አማራጭ ይቀላቀሉን!
🔺🔻 SUBSCRIBE NOW
https://www.youtube.com/channel/UCIZv4h3iDx2C7CGbv9WIkVg?sub_confirmation=1
ምክረ-አዕምሮ/ @mikre_aimro 😊 💪


በምክንያትህ ተመራ!
➡️➡️➡️🗣️🗣️🗣️
ህመሙን እለፈው፣ ስቃዩን ተሻገረው፣ ውድቀትህን ተጠቀም፣ በመገፋትህ እራስህን ስራው፣ በመከዳትህ ለእራስህ ታመን፣ በኋሊት ጉዞህ እራስህን መርምር፣ በውጤት አልባው ጥረትህ እራስህን ገንባ፣ በተለተለት የግል ጦርነትህ ብቁ ሆነህ ተገኝ። ሽንፈትህ ተስፋህን እንዳይገድለው፣ ስህተትህ ዋጋህን እንዳያሳንስ አስቀድመህ ለሽንፈትና ለስህተት ያለህን አመለካከት አስተካክል። ውድድሩ ውስጥ ስለገባህ ልትሸነፍ ትችላለህ፣ ስለሞከርክ ልትሳሳት ትችላለህ፣ በመጣርህ ብቻ ልትሰበር ትችላለህ አመለካከትህ ግን ይህን ሁሉ ድካምና ውጤት ሊያስታርቅልህ ይችላል። እራስህን ስለሰጠሀው ብዙ ነገር ፈጥኖ ፍሬ እንደሚያፈራ ልትጠብቅ ትችላለህ ነገር ግን አንዳንድ አካሔዶች ገና ከጅምራቸው ስህተት ነበሩና ምንም እንኳን አጥብቀህ ብትታገልላቸው፣ ዋጋ ብትከፍልላቸው፣ እራስህን አሳልፈህ ብትሰጥላቸው እንኳን ውጤት አይኖራቸውም።

አዎ! ጀግናዬ..! የጉዞ አቅጣጫህን፣ የትግልህን ምክንያት፣ የጥረትህን የኋላ መነሻ በሚገባ እወቀው። ለምን እየታገልክ ነው? ምን እንዲፈጠር እየጣርክ ነው? ለምንስ ይህን እልህ አስጨራሽ ጉዞ ጀመርክ? ስሜትህን ወደጎን በለው፣ የሚወራብህን ወሬ ከቁብ አትቁጠረው፣ በቀደመ ስህተትህ አትሸበር፣ ውድቀትን አትፍራ፣ በሌሎች ኪሳራ እራስህን አታስፈራራ። በምክንያትህ ተመራ፤ በጥበብ ተራመድ፣ በእውቀት ወደፊት ተጓዝ፣ በምርጫህ ፅና፣ በውሳኔህ ተማመን። ማንም በአመለካከትህ ላይ ስልጣን የለውም፣ ማንም በግል አቋምህ፣ በግል ውሳኔህ ላይ ጣልቃ የመግባት መብት የለውም፣ ማንም በምርጫህ ምክንያት ጫና ውስጥ ሊከትህ አይችልም። በመረጥከው፣ ባመንከውና በወደድከው ፅንፍ ከማንም በላይ እስከ ጥግ መጓዝን ብትፈልግ ማን ሊያስቆምህ ይችላል? ማንም! እምነትህ ወደፊት ይመራሃል፤ ደጋግመህ በአይነ ህሊናህ በምናብህ የምትመለከተው መዳረሻህ መንገዱን ሁሉ ያቀናልሃል።

አዎ! ወደፊት ስትጓዝ፣ በፅናት ስትራመድ፣ እራስህን ብቁ ለማድረግ ስትጥር የተዘጉ የሚመስሉ እድሎች ሁሉ እየተከፈቱ ይመጣሉ፣ በፊት በጨለማ የተሞሉት መንገዶችህ የብረሃን ጭላንጭል እየታየባቸው ይመጣል፣ ተስፋ የቆረጥክባቸው፣ "ዋጋ የላቸውም፣ አይጠቅሙም" ያልክባቸው የግልና የሃገርህ ጉዳዮች የምርም የለውጥና የእድገትህ ምክንያቶች ሲሆኑ ትመለከታለህ። ይህን የቻይኖች አባባል አስታስ፦ "አንድ ችግር ስትፈታ ብዙ መቶ ችግሮችን ታርቃለህ።" ችግር ሁሉም ቦታ አለ፣ ካንተም ይሁን ከሌላ አካል መፍትሔ የሚፈልግ ጉዳይ በየቦታው፣ በየደረጃው የትም አለ። አንተ ግን የእራስህን ሃላፊነት ብቻ ተወጣ፣ ወደፊት እየተራመድክ የእራስህን ችግር ብቻ ፍታ፣ እራስህን ለውጥ፣ እራስህን አሳድግ። የእድገት ጉዞህ በእራሱ የብዙዎችን ችግር እንድትፈታ ያደርግሃል፤ የለውጥ መንገድህ አይነተኛ ተመረጫ የመፍትሔ ሰው ያደርግሃል። በምክንያትህ ተመራ፣ በውጤትህም አሸብርቅ።
ውብ ምሽት ይሁንልን! 🌘🌒💫✨
✍️ (Epha A.)
ምክረ-አዕምሮ ለተሻለ ነገ! 🦋
#SHARE እንዳይረሳ ቤተሰቦች! 🙏😍

YouTube አማራጭ ይቀላቀሉን!
🔺🔻 SUBSCRIBE NOW
https://www.youtube.com/channel/UCIZv4h3iDx2C7CGbv9WIkVg?sub_confirmation=1
ምክረ-አዕምሮ/ @mikre_aimro 😊 💪




ጭንቀትህ የለም!
➡️➡️➡️🗣️🗣️
ሰውነት ማሰብ መገለጫው ነው፤ ማሰላሰል፣ ማመዛዘን መለያው ነው፤ ማስተዋል፣ መወሰንና በተግባር መግለፅ የማንነቱ መለኪያ ነው። በሰው አምሳል ምድር ላይ መመላለስ ብቻውን ሰው ሊያስብል ቢችልም እውነተኛውን ትክክለኛ ተፈላጊ ሰው ግን ሊያስብል አይችልም። ሰውነት ውስጡ ጥበብ አለ፣ ሰውነት በጉያው የአምላክን ድንቅ ሃይል ይዟል፣ ሰውነት በትንሹም በትልቁም የሚደነግጥና እንቅልፍ የሚያጣ፣ በተጨበጠውም ባልተጨበጠውም በጭንቀት የሚባክን አይነት አይደለም። የሰውነትን ምንነት ስትረዳ እራስህን በሚገባ ማክበር ትጀምራለህ፣ ማንነትህን ስታውቅ የምርም በጊዜያዊ ሀሳብና ጭንቀቶች መሸበርህን ታቆማለህ። ለማን ብለህ ነው ውሎህን በሚያውክ ሃሳብ ተጠምደህ የምትውለው? ማንን ደስ እንዲለው ነው ባልተጨበጠ ወሬ ምክንያት የውስጥ ሰላምሽን የምታጪው?

አዎ! ጀግናዬ..! ጭንቀትህ የለም! ስራህን በአግባቡ እንዳትሰራ ያደረገህ፣ ትምህርትን እንዳታጠና የከለከለህ፣ በሰዎች ፊት ሃሳብህን እንዳትገልፅ ያደረገህ፣ የእራስህን አዲስ ስራ እንዳትጀምር አስሮ የያዘህ፣ ከሱስህ እንዳትላቀቅ ፋታ የነሳህ የገዛ ጭንቀትና ስጋትህ ነፍስ የለውም፣ ምንም ሊያመጣብህ አይችልም። ያላንተ ይሁንታ ብቻውን ምንም ሊያደርግህ አይችልም፤ በውስጥህ የተፈጠረው አለመረጋጋት፣ ዘወትር የሚያውክህ አሉታዊ ስሜት፣ ሰላምህን የሚነሳህ የሰዎች ሃሳብና አስተያየት ካንተ ፍቃድ በቀር ምንም ሊያስከትልብህ አይችልም። አምነህ የተቀበልከው ስጋት መረጋጋት ይነሳሃል፤ እውነት የመሰለህ የሰዎች አስተያየት ውስጥህን ይረብሸዋል፤ ይሉኝታ ዘመንህን ሙሉ በጭንቀትና በፍረሃት አንድ ቦታ ላይ እንድታሳልፍ ያደርግሃል።

አዎ! ማንም ያስባል፣ ማንም በውስጡ ነገሮችን ያሰላስላል፣ ግፋ ሲልም ይጨነቃል፣ ይሸበራል። ከልክ በላይ ማሰብን ትርጉም ብነሰጠው በአጭር አማርኛ ጭንቀት ማለት እችላለን። ሃሳብ ሃሳብን ሲወልድ፣ በሂደትም በመላምቶችና መሰረት አልባ ትርክቶች ሲታገዝ መዳረሻውን እንቅልፍ ነሺ ጭንቀት ሆኖ እናገኘዋለን። አብዝተን እናስባለን ነገር ግን ምንም ተጨባጭ ነገር አናመጣም፤ እናወጣለን እናወርዳለን ነገር ግን ምንም አይነት እርምጃ አንወስድም። በገዛ ፍቃዳችን አዕምሮችን ላይ ሸክም እናበዛለን፣ ህሊናችንን በሌለ ነገር ደጋግመን እንፈትናለን። ጭንቀት አዲስህ አይደለምና ከዚህ በፊት ተጨንቀህ ምን እንዳመጣህ አስታውስ፤ አብዝተህ ስላሰብክ ምን እንዳተረፍክ ተረዳ። ስለጭንቀትህ መጨነቅ አቁምና እርምጃ መውሰድ ባለብህ ልክ እርምጃ ውሰድበት። ባልተጨበጠ ሃሳብ ውስጣዊ ሰላምህን እንዳታጣ ሃሳቦችህን ጠብቃቸው።
ሰላማዊ ምሽት ይሁንልን! 🌘🌒💫✨
✍️ (Epha A.)
ምክረ-አዕምሮ ለተሻለ ነገ! 🦋
#SHARE እንዳይረሳ ቤተሰቦች! 🙏😍

YouTube አማራጭ ይቀላቀሉን!
🔺🔻 SUBSCRIBE NOW
https://www.youtube.com/channel/UCIZv4h3iDx2C7CGbv9WIkVg?sub_confirmation=1
ምክረ-አዕምሮ/ @mikre_aimro 😊 💪




ረፍዶ አያውቅም!
➡️➡️➡️🗣️🗣️
ራሳችሁን ከልክ በላይ አታስጨንቁ፣ አዕምሯችሁን አትወጥሩት፣ "የኔ ጊዜ አልፏል፣ አብቅቷልኛል፣ ከዚህ ቦሃላ ምንም ባደርግ አይሳካልኝም፣ አቅሜን ጨርሼአለሁ፣ የቀደመ ተነሳሽነቴ ተመልሶ አይመጣም።" ብላችሁ ራሳችሁን አሳስራችሁ አታስቀምጡ። በህይወት እስካላችሁ ድረስ የፈለጋችሁትን የማድረግ ጊዜ እንዳላችሁ አስቡ፣ እየተንቀሳቀሳችሁ እስከሆነ ድረስ በመረጣችሁት መንገድ የመጓዝ አቅሙ እንዳላችሁ እመኑ። በገዛ ፍቃዳችሁ ነገሮችን አታወሳስቡ፣ ፈልጋችሁ ለዝንጉነት ቦታ አትስጡ። በቀን ውስጥ ሁሉም ሰው 24 ሰዓት አለው፣ ይህ 24 ሰዓት ግን ለሁሉም እኩል ውጤትን አያመጣም። የጊዜያቸው ውድነት የገባቸው ሰዎች ጊዜን በገንዘብ ይገዛሉ፣ የጊዜያቸው ውድነት ያልገባቸው ሰዎች ደግሞ እንዲሁ በቀላሉ ያባክኑታል። ትናንት በየትኛውም አልባሌ ነገር ውስጥ አሳልፉ፣ ጊዜያችሁ እንዴትም ይባክን፣ ፍላጎታችሁም ሳይሳካ ይቅር አሁንም ግን በቂ ጊዜ አላችሁ። ያለፈ ጊዜ ውስጥ ምንም ተመላሽ ጊዜ የለም፣ በትናንተ ላይ አንዳች የሚፈፀም ተግባር አይኖርም። ለሁሉም እኩል በተሰጠው ጊዜ ምክንያት ተስፋ አትቁረጡ።

አዎ! ረፍዶ አያውቅም፤ እንደ ጨለመ ቀርቶ አያውቅም፣ ጀምበሯ እንዳዘቀዘች፣ ብረሃኗን እንደነፈገች፣ ዓለምም ፊቷን እንዳዞረች አትቀርም። በአምላኩ ድንቅ አድራጊነት ለሚያምን ሰው ሁሌም የበረከት በሮች ክፍት ናቸው። ዕዴሜው ጨመረ፣ ሰውነቱ ዛለ፣ ተነሳሽነቱ ቀነሰ፣ አቅመቢስ ሆነ፣ ሱስ አደከመው የሚባሉ ነገሮች አይሰሩም። ልባችሁ ብረሃን፣ ውስጣችሁ ንቁ፣ በፈጣሪ ስራ የምታምኑ ከሆነ ባለፈ ታሪክ ምክንያት ወደፊታችሁን ጨለማ አድርጋችሁ አትመለከቱም። ማድረግ ያለባችሁን ነገር አሁን አድርጉት፣ መጀመር ያለባችሁን ጉዳይ አሁን ጀምሩ። ለዓመታት ቀጠሮ ማብዛታችሁ ዛሬ እንደ ረፈደባችሁ እንድታስቡ አድርጓችኋል፣ ትናንተ ላይ ቸልተኛ መሆናችሁ ዛሬ ደካማና ልፍስፍስ አድርጓችኋል፣ ባለፈ ጊዜ አላማቢስ መሆናችሁ ዛሬ እጅጉን የተመሰቃቀለ ህይወት እንድትኖሩ አድርጓችኋል። ነገር ግን አሁንም አልረፈደም፣ ወደ ትክክለኛው መንገድ ለመመለስ፣ ጥፋታችሁን ለማረም፣ ቀና ብሎ ለመራመድ፣ የህይወት አላማን አግኝቶ ለመኖር በፍፁም አልረፈደም። "ረፍዶብኛል፣ ጊዜው የእኔ አይደለም።" ብላችሁ ከምትጨነቁ "ጊዜው የእኔ ነው፣ አሁንም በራሴ ላይ ስልጣን አለኝ፣ እርሱንም የምፈልገውን በማድረግ አሳያለሁ።" ብላችሁ ተግባሩን ጀመሩት።

አዎ! ጀግናዬ..! ያለፈን እድል እያሰቡ መቆዘም እድሉን አይመልስም። አባባሉ እንደሚለው "በድሮ በሬ ያረሰ የለም።" ማረስ ከፈለክ አዲስ በሬ ጠምደህ እረስ፣ የምርም ወደፊት መጓዝ ከፈለክ ትናንትህን ሽረህ ዛሬህ ላይ ተደገፍ። ታሪክህ በብዙ አስከፊ ነገሮች ተበላሽቶ ይሆናል አዲስ የተለየ ታሪክ የመፃፍ አድልህ ግን በእጅህ ነው። ነገሮችን በራስህ ላይ ማዳፈን አቁም፣ የነካሀው ሁሉ እንደሚሰበር፣ ያሰብከው ሁሉ እንደማይሳካ ማመን አቁም። በትናንት ማንነትህ ራስህን ወቀስክ አልወቀስክ፣ ጥፋትህን አጎላህ አላጎላህ፣ በራስህ ተበሳጨህ አልተበሳችሁ  ካንተና ከፈጣሪ በቀር ማንም ስላንተ ሃሳብና ጭንቀት ግድ እንደሌለው አስታውስ። ከራስህ ጋር ሰላም ፍጠር፣ በቀላሉ የሚረበሽ ሰው አትሁን፣ ተስፋህን አርቀህ ስቀለው፣ ስሜትህን ለማንም አታሳይ፣ የግል ዓለምህን ከልለው። አንተ ራስህ ላይ ከጨከንክ ማንም ሊያዝንልህ አይችልም፣ አንተ ልብህን ካስጨነካት ማንም ሊያዳምጣት አይችልም። ውጥረትህን ቀንስ፣ ጭንቀትህን ግዛ፣ ብዙዎች ረፍዷል ብለው በተዘናጉበት ወቅት አንተ ካለፈው ጊዜ በላይ በዛሬውና በነገው ተማምነህ ያለህን ጊዜ በስስት ተጠቀም።
ግሩም ድንቅ ቀን ይሁንልን! 🏞🌞🌅
✍️ (Epha A.)
ምክረ-አዕምሮ ለተሻለ ነገ! 🦋
#SHARE እንዳይረሳ ቤተሰቦች!

YouTube አማራጭ ይቀላቀሉን!
🔺🔻 SUBSCRIBE NOW
https://www.youtube.com/channel/UCIZv4h3iDx2C7CGbv9WIkVg?sub_confirmation=1
ምክረ-አዕምሮ/ @mikre_aimro 😊 💪

4k 0 26 2 63

ያለማቋረጥ አጥቃ!
➡️➡️➡️🗣️🗣️
ባለህበት ቆመህ ማን የሚፈልግህ ይመስልሃል? አምና ካቻምና ስትሰራ የነበረውን እየሰራህ ማን የሚመርጥህ ይመስልሃል? ባለፈው ስራህን እደምትሰራው አሁንም ብትሰራ እድገት የምታገኝ ይመስልሃል? በአረጀ አመለካከት፣ ባፈጀ እይታ የምትለወጥ ይመስልሃል? በየጊዜው ካልተሻሻልክ እንዲሁ እንደቀላል ህይወት የእድገትን እድል የምትሰጥህ እንዳይመስልህ። ማንም በአጋጣሚ ህይወቱን የቀየረ፣ ኑሮውን ያሻሻለ፣ ደረጃውን የጨመረ፣ ከከፍታው የደረሰ ሰው የለም። እያንዳንዱ ነገር የብዙ እንቅልፍ አልባ ምሽቶች ውጤት ነው፤ እያንዳንዱ ከፍታ ክህሎትን ከማሻሻል ቦሃላ የመጣ ነው፤ እያንዳንዱ እርካታ ጨክኖ እራስን ከመግዛት ቦሃላ የተከሰተ ነው፤ የትኛውም ስኬት ለእራስ ከሚሰጥ ቦታና ፍቅር የሚመነጭ ነው።

አዎ! ክህሎትህን አሳድግ፤ እውቀትህን ጨምር፤ መረዳትህን አስፋ፤ ግንዛቤህን አጎልብት። አቋም ይኑርህ፣ እራስን የማስቀደም አቋም፣ ለእራስ የመታገል አቋም፣ እራስን ነፃ የማውጣት፣ እስከጥግ የመፋለም፣ ዋጋ የመክፈል፣ እራስን የመግዛት፣ ህመምን፣ ስቃይን፣ መከራን የመቻል አቋም፣ በእሾህ ጋሬዛ ውስጥ፣ በማያልቁ መሰናክሎች መሃል፣ እረፍት በማይሰጡ ትቺቶች ውስጥ፣ አበርታች፣ አጋዥ፣ ደጋፊ በሌለበት መንገድ መሃል በፅናት የመጓዝ አቋም ይኑርህ። 4030 ፑል አፕ በ17 ሰዓት ከ16 ደቂቃ በመስራት የአለምን የፑል አፕ ሪከርድ (world's pull up record) በእጁ ያስገባው፣ 5000KM መሮጥ የቻለውና የአለማችንን የምንጊዜውም ጠንካራው ሰው የተባለው ደቪድ ጎጊንስ (David Goggins) ስለ አዕምሯዊ ጥንካሬ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ "አንድን ነገር ለማድረግ ከመረጥከው አጥቃው።"

አዎ! ያለማቋረጥ አጥቃ! ፋታ ሳትሰጥ ስራበት፣ ቀን ከሌሊት እራስህን ገንባበት፣ ያለምንም የአቋም መዋዠቅ እስከመጨረሻው ታገለው፤ እስክትነግስበት በፍፁም እንዳታቆም። እራስህን ከወደድከው ዋጋ ክፈልለት፤ ለእራስህ ክብር ካለህ ጨክንበት፤ የምርም ደስታህን የምትፈልግ ከሆነ፣ በእርግጥ እርፍት እንዲያደርግ የምትመኝ ከሆነ እያወክ ስቃይ ውስጥ ክተተው፣ ያለማቋረጥ አስተምረው፣ አሰራው፣ አሳድገው። ምንም ዋጋ ሳይከፍሉ ዋጋ ያለው ትርፋማ ህይወት መኖር አይቻልም፤ እየቀለዱና እያሾፉ ተመራጭ ተፈላጊ ሰው መሆን አይቻልም። ለመለወጥ ጊዜ አትውሰድ፤ ለእድገትህ ቀጠሮ አታብዛ፤ ከፍታህን አታዘግየው፤ ስኬትህን ወደኋላ አትግፋው። "የመጣው ቢመጣም ለእራሴ አላንስም፤ ምንም ማድረግ ቢጠበቅብኝ ማድረግ ያለብኝን አድርጌ ነፃነቴን እጎናፀፋለሁ" የሚል የማይናወፅ አቋም ይኑርህ።
ውብ ምሽት ይሁንልን! 🌘🌒✨
✍ (Epha A.)
ምክረ-አዕምሮ ለተሻለ ነገ! 🦋

YouTube አማራጭ ይቀላቀሉን!
🔺🔻 SUBSCRIBE NOW
https://www.youtube.com/channel/UCIZv4h3iDx2C7CGbv9WIkVg?sub_confirmation=1
ምክረ-አዕምሮ/ @mikre_aimro 😊 💪



20 ta oxirgi post ko‘rsatilgan.