✝✝✝ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ፩ አምላክ ፡፡ አሜን ፡፡ ✝✝✝
✞✝✞ እንኳን አደረሳችሁ ✞✝✞
@sebhhobekhlotu@sebhhobekhlotu@sebhhobekhlotu✝ጥር 11 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት
+✝ በዓለ ኤዺፋንያ ✝+
=>'ኤዺፋንያ' የሚለው ቃል ከግሪክ (ጽርዕ) ልሳን
የተወሰደ ሲሆን በቁሙ 'አስተርእዮ: መገለጥ' ተብሎ
ይተረጐማል::
በነገረ ድኅነት ምሥጢር ግን ኤዺፋንያ ማለት 'የማይታይ
መለኮት የታየበት: እሳተ መለኮት በተዋሐደው ሥጋ
የተገለጠበት' እንደ ማለት ነው::
"ዘኢያስተርኢ ኅቡዕ እስመ አስተርአየ ለነ:
እሳት በላዒ አምላክነ" እንዲል:: (አርኬ)
አንድም: ምሥጢር ሆኖ የቆየ አንድነቱ: ሦስትነቱ
የተገለጠበት ቀን ነውና ዕለተ ጥምቀቱ ኤዺፋንያ
ይሰኛል:: መድኃኒታችን
ክርስቶስ አዳምንና ልጆቹን ያድን ዘንድ ከሰማያት ዙፋኑ
ወርዶ: እንደ ሰውነቱ በሥጋ ማርያም ለ33 ዓመታት
ተመላልሷል::
+ጊዜው ሲደርስም በፈለገ ዮርዳኖስ: ከዮሐንስ ዘንድ
ሊጠመቅ ሔደ:: መድኃኒታችን ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ
የወረደው ጥር
10 ቀን አመሻሽ ላይ ሲሆን በፍጹም ትሕትና ተራ
ሲጠብቅ አድሮ ሌሊት 10 ሰዓት ላይ ደረሰውና ሊጠመቅ
ቀረበ::
+10 ሰዓት መሆኑም ርግብ (መንፈስ ቅዱስ) ሲወርድ
ሰዎች ሥጋዊት ርግብ ናት ብለው እንዳይጠራጠሩ ነው::
ርግብ በሌሊት
መንቀሳቀስ አትችልምና::
+መድኃኒታችን ወደ ቅዱስ ዮሐንስ ሲጠጋ አምላክነቱን
ተረድቶ "እንዴት ፈጣሪየ ወደ እኔ ትመጣለህ? እንዴትስ
በእኔ እጅ
ትጠመቃለህ?" አለው:: ትህትና ለእናትና ልጅ ልማዳቸው
ነውና:: (ሉቃ. ማቴ. ) ጌታ ግን "ጽድቅን ሁሉ ልንፈጽም
ይገባል" ሲል እንዲያጠምቀው ፈቀደለት::
+ቅዱስ ዮሐንስም "ስመ አብ በአንተ ሕልው ነው:: ስመ
ወልድ ያንተ ነው:: ስመ መንፈስ ቅዱስም በአንተ ዘንድ
ሕልው
ነው:: በማን ስም አጠምቅሃለሁ?" ሲል ጠየቀው::
+ጌታ "ወልዱ ለቡሩክ ከሣቴ ብርሃን ተሣሐለነ:: አንተ
ካህኑ ለዓለም በከመ ሲመቱ ለመልከ ጼዴቅ እያልክ
አጥምቀኝ"
አለው:: ትርጉሙም "የቡሩክ አብ የባሕርይ ልጁ ብርሃንን
የምትገልጥ ሆይ ይቅር በለን! አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ
ሹመት
የዓለም ካህኑ ነህና" እንደ ማለት ነው::
+ከዚያም ጌታ ወደ ዮርዳኖስ ሲገባ ባሕር አይታ
ደነገጠች: ሸሸችም:: (መዝ) ዮርዳኖስ ጨንቆት ግራ ቀኝ
ተመላለሰ::
እሳተ መለኮት ቆሞበታልና ውሃው ፈላ:: በጌታ ትዕዛዝ
ግን ጸና::
+ጌታ ተጠምቆ: ሥርዓተ ጥምቀትን ሠርቶ: ዮርዳኖስን
ብርህት ማሕጸን አድርጐ: የእዳ ደብዳቤአችንም ቀዶ
ከወጣ በኋላ
ሰማያት ተከፈቱ:: ማለትም አዲስ ምሥጢር ተገለጠ::
+አብ በደመና ሆኖ "የምወደው: የምወልደው: ሕልው
ሆኜ ልመለክበት የመረጥኩት የባሕርይ ልጄ ይህ ነው!"
ሲል በአካላዊ
ቃሉ ፍጹም ተዋሕዶን መሰከረ:: መንፈስ ቅዱስም
በአምሳለ ርግብ ወርዶ በራሱ ላይ ተቀመጠ:: ራሱንም
ቆንጠጥ አድርጐ
ያዘው:: በዚህም የሥላሴ አንድነቱ: ሦስትነቱ ታወቀ:
ተገለጠ::
+ቅዱስ ዮሐንስ "መጥምቀ መለኮት" የሚባልበትን
ታላቁን ክብር ሲያገኝ ዮርዳኖስ የልጅነት መገኛ ቅዱስ
ባሕር ሆነ::
✞✞ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ✞✞
✞✞ ቅዱስ ወንጌል ላይ ቅዱስ ሉቃስ "ዘካርያስ ካህኑና
ቅድስት ኤልሳቤጥ በሰውና በእግዚአብሔር ፊት ያለ ነቀፋ
የሚኖሩ
ጻድቃን ነበሩ" ይላቸዋል:: (ሉቃ. 1:6)
+እሊህ ቅዱሳን ባልና ሚስት ግን መካኖች በመሆናቸው
ልጅ ሳይወልዱ ዘመናቸው አልፎ ነበር:: እንደ ቤተ
ክርስቲያን
ትውፊት ዕድሜአቸው የኤልሳቤጥ 90 የዘካርያስ 100
ደግሞ ደርሶ ነበር::
*ፍጹም መታገሳቸውን የተመለከተ ጌታ ግን በስተ
እርጅናቸው ከሰው ሁሉ በላይ የሆነ: ትንቢት ለብቻው
የተነገረለት (ኢሳ.
40:3, ሚል. 3:1) ታላቅ ነቢይን ይሰጣቸው ዘንድ
መልአከ ብሥራት ቅዱስ ገብርኤልን ላከላቸው::
*ቅዱስ ዘካርያስ ሰው ነውና ከደስታ ብዛት በመከራከሩ
ድዳ ሆነ:: ቅድስቲቷ ግን መስከረም 26 ቀን ታላቁን ሰው
ጸንሳ
ለ6 ወራት ራሷን ሠወረች:: በ6ኛው ወር የፍጥረት ሁሉ
ጌታ በተጸነሰ ጊዜ የአርያም ንግሥት ድንግል እመቤታችን
ደጋ
ደጋውን ወደ ኤልሳቤጥ መጣች:: ሁለቱ ቅዱሳት
የእህትማማች ልጆች ናቸው::
*የአምላክ እናቱ ስትደርስና "ሰላም" ስትላቸው መንፈስ
ቅዱስ በእናትና ልጅ ወርዶ ኤልሳቤጥ በምስጋና: ዮሐንስ
ደግሞ
ገና በማሕጸን ሳለ በደስታ ዘለለ (ሰገደ):: ከዚህ በኋላ ሰኔ
30 ተወልዶ: አባቱ ዘካርያስ "ዮሐንስ" ሲለው አንደበቱ
ተፈትቶለታል::
*ቅዱስ ዮሐንስ ከተወለደ 2 ዓመት ከ6 ወር በሆነው ጊዜ
ሰብአ ሰገል በመምጣታቸው በእሥራኤል ምድር የሚገኙ
ሕጻናትን
ሔሮድስ ቁዝ አስፈጀ:: ትንሽ ቆይቶም አይሁድ ለሔሮድስ
ስለ ቅዱሱ ሕጻን ነገሩት:: "ሲጸነስ የአባቱን አንደበት
የዘጋ:
ሲወለድ ደግሞ የከፈተ 'ዮሐንስ' የሚባል ሕጻን አለና
እሱንም ግደል" አሉ::
*እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥ ይዛው ስትሸሽ ካህኑን
ዘካርያስን ግን በቤተ መቅደስ መካከል ገድለውታል::
አረጋይት ኤልሳቤጥም
ሕጻኑን እያሳደገች በገዳመ ዚፋታ ለ3 (5) ዓመታት
ቆይታለች:: ቅዱስ ዮሐንስ 5 (7) ዓመት ሲሞላው ግን
እዚያው
በበርሃ እናቱ ዐረፈች:: ከሰማይ ዘካርያስና ስምዖን ወርደው
ቀበሯት::
*ሕጻኑ ዮሐንስ ሲያለቅስ ድንግል ማርያም ስንት አገር
አልፋ ሰማችው:: እርሷም ስደት ላይ ነበረችና:: ከጌታ ጋር
በደመና ሒደው ድንግል አቅፋ አጽናናችው:: ጌታንም
"እንውሰደው ይሆን?" አለችው:: ጌታችን ግን
"ለአገልግሎት
እስክጠራው እዚህ ይቆይ" አላት:: ባርካው: አጽናንታውም
ተለያዩ::
*ቅዱስ ዮሐንስ ከዚህ በኋላ በዚያ ቆላ የግመል ጠጉር
ለብሶ: ጠፍር ታጥቆ ተባሕትዎውን ቀጠለ:: ለ25 (23)
ዓመታትም
በንጽሕና ሲኖር ከምድር አራዊትና ከሰማይ መላእክት
በቀር ማንንም አላየም:: ይሕችን ዐመጸኛ ዓለምም
አልቀመሳትም::
*ከዚህ በኋላ 30 ዘመን ሲሞላው እግዚአብሔር ከሰማይ
ተናገረው:: "ሒድ! የልጀን ጐዳና ጥረግ" አለው:: ነቢያት
ስለዚህ ነገር ተናግረው ነበርና:: (ኢሳ. 40:3, ሚል. 3:1)
አባቱ ዘካርያስም "ወአንተኒ ሕጻን ነቢየ ልዑል
ትሰመይ: እስመ ተሐውር ቅድመ እግዚአብሔር ከመ
ትጺሕ ፍኖቶ" (ሉቃ. 1:76) ብሎ መንገድ ጠራጊነቱን
ተናግሮ ነበርና::
*ቅዱስ ዮሐንስ በዚያ ጊዜ በኃይለ መንፈስ ቅዱስ
እየገሰገሰ ከበርሃ ወደ ይሁዳ መጣ:: ያዩት ሁሉ ፈሩት:
አከበሩት::
ቁመቱ ቀጥ ያለ: ጽሕሙ እንደ ተፈተለ ሐር የወረደ: ጸጉሩ
የቁራ ያህል የጠቆረ: መልኩ የተሟላ: ግርማው
የሚያስፈራ
ገዳማዊ ነውና::
*ፈጥኖም ሕዝቡን ለንስሃ ሰበከ: ለንስሃም በርካቶችን
አጠመቃቸው:: በዚህ አገልግሎት ለ6 ወራት ቆይቶ
ጌታችን ወደ
እርሱ ዘንድ መጣ:: ዮሐንስ ሰማይን ከነግሱ: ምድርን
ከነልብሱ የያዘ ፈጣሪ 'አጥምቀኝ' ብሎ ሲመጣ ደነገጠ::
የሚገባበትም ጠፋው::
*"እንቢ ጌታየ! አንተ አጥምቀኝ" አለው:: ጌታ ግን
"ፈቅጄልሃለሁ" አለው: አጠመቀው:: በዚህ ምክንያት
ይሔው እስከ
ዛሬም "መጥምቀ መለኮት" ሲባል ይኖራል:: ቅዱስ
ዮሐንስ በመጨረሻ ሔሮድስን ገሰጸው:: ንጉሡም ተቀይሞ
ለ7 ቀናት
አሠረው::