ከሸቀጥ ዕቃዎች የሚወጣ ዘካ
የሸቀጥ ዕቃዎች ማለት ትርፍ ለማግኘት ለሽያጭ የተዘጋጁ ዕቃዎች ናቸው:: ከሸቀጥ ዕቃዎች ዘካ ማውጣት ዋጂብ ለመሆኑ ማስረጃው አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይላል፡-
خُذْ مِنْ أَمْوَالِهِمْ صَدَقَةً تُطَهِّرُهُمْ وَتُزَكِّيهِم بِهَا
ከገንዘቦቻቸው ስትኾን በእርሷ የምታጠራቸውና የምታፋፋቸው የኾነችን ምጽዋት ያዝ።(አት-ተዉባ 103)
وَالَّذِينَ فِي أَمْوَالِهِمْ حَقٌّ مَّعْلُومٌ,لِّلسَّائِلِ وَالْمَحْرُومِ
እነዚያም በገንዘቦቻቸው ላይ የታወቀ መብት ያለባቸው የኾኑት። ለለማኝ ከልመና ለሚከለከልም (መብት ያለባቸው የኾኑት)፡፡(አል-መዓሪጅ 24-25)። አብዛኛው ገንዘብ የሸቀጥ እቃ ስለሆነ በአንቀጹ ጥቅላዊ ትርጓሜ ዉስጥ ይገባል፡፡ ይህ ከሰሓቦችም ተዘግቧል፡፡
ሸይኹልኢስላም ኢብኑ ተይሚያ “አራቱ ኢማሞችና ሌላውም ኡመት - ጥቂት ያፈነገጠ ሰው ሲቀር - ዘካ ከሸቀጥ እቃ እንደሚወጣ ተስማምተዋል” ብለዋል፡፡
ከሸቀጥ እቃዎች ዘካ ማውጣት ዋጂብ የሚሆነው በሚከተሉት ሸርጦች ነው:-
1) እቃዎቹ ከሁለቱ ገንዘቦች ማለትም ከወርቅና ከብር ባንዱ ተገምተው ኒሳብ መሙላት።
2) አንድ ዓመት መሙላት - ለዚህም ማስረጃው ቀደም ሲል ተወስቷል፡፡ ነገር ግን በገንዘብ ወይም በሸቀጥ ኒሳብ ግምቱ ኒሳብ የሚሞላ ሸቀጥ ከገዛ የሚታሰበው የገዛበት ገንዘብ ዓመት ነው [እንጂ የተገዛው እቃ ከተገዛበት ቀን ጀምሮ ዓመት እንዲሞላ አይጠበቅም]።
ማስገንዘቢያ፡- የሸቀጥ እቃዎች ዘካ አወጣጥ፡- ዓመት ሲሞላቸው ከሁለቱ ገንዘቦች - ከወርቅና ከብር ባንዱ ይገመታሉ፡፡ በዚህ ላይ ለድሆች ይበልጥ የሚጠቅመው ግምት ይወሰዳል - (ከወርቅ ወይም ከብር ግምት)፡፡ ከሁለቱ ገንዘቦች ባንዱ ተገምቶ ግምቱ ኒሳብ ከሞላ የግምቱ አንድ አስረኛ ሩብ ይወጣል፡፡ የተገዛበት ገንዘብ መጠን ግምት ዉስጥ አይገባም፡፡ የሚታየው ዓመቱ ሲሞላ የተገመተበት የገንዘብ መጠን ነው፡፡ ለባለሸቀጡም ሆነ ለዘካ ተቀባዩ ፍትሃዊ የሚሆነው ይህ ነው፡፡
ዘካ የሚያወጣው ሙስሊም ባለሸቀጥ ከሸቀጡ ዘካ ሲያወጣ ሸቀጡን በትከክል መቁጠርና ስስታም የሆነ ሸሪክ ሸሪኩን በሚተሳሰበው ዓይነት ራሱን መተሳሰብ ዋጂብ ይሆንበታል፡፡ ያሉትን ሸቀጦች በሙሉ በዓይነታቸው መቁጠርና ፍትሃዊ የሆነ ግምት መገመት ይጠበቅበታል፡፡ ለምሳሌ የአንድ ሱቅ ባለቤት በሱቁ ዉስጥ በፓኬቶችና በዓይነቶች ተከፋፍለው ለሽያጭ የተዘጋጁትን ሁሉንም መቁጠር ይኖርበታል፡፡ ለሽያጭ የቀረቡ የተለያዩ ማሽኖች፣ የማሸኖችና የመኪናዎች መለዋወጫዎች ባለቤት በትክከል ይቆጥራቸውና በጅምላ የሚሸጥ ከሆነ በጅምላ ዋጋ በችርቻሮ የሚሸጥ ከሆነ በችርቻሮ ዋጋ ይገምታቸዋል፡፡
ማስገንዘቢያ፡- ለኪራይ የተዘጋጁ ቤቶችና መኪናዎች በራሳቸው ዉስጥ ዘካ የለባቸውም፡፡ ዘካ ማውጣት የሚወጅበው ባለቤቱ ከነዚህ ከሚያገኘው ኪራይ ዉስጥ ነው - ከኪራይ ዉሉ ቀን ጀምሮ ዓመት ከሞላው፡፡
ማስገንዘቢያ፡- መኖሪያ ቤቶችና (ለንግድ ሳይሆን) ለመጠቀም የተያዙ መኪናዎች ዘካ የለባቸውም፡፡ እንደዚያውም የቤት ቁሳቁሶች፣ የሱቅ ቁሳቁሶች፣ የነጋዴው መጠቀሚያ እቃዎች - እንደ መለኪያዎች፣ መስፈሪያዎች፣ ሚዛኖች፣ መያዣ እቃዎች እነዚህ ሁሉ ዘካ የለባቸውም - የሽያጭ እቃዎች አይደሉምና፡፡ አቡ ሁረይራ ባስተላለፉት ሐዲሥ ነብዩ ሶለሏሁ አለይሂ ወሰለም “አንድ ሙስሊም በባሪያውና በፈረሱ ዉስጥ ሰደቃ (ዘካ) የለበትም፡፡” ብለዋልና - ሙት-ተፈቁን ዐለይህ፡
ወሏሁ አዕለም
t.me/IbnuHashm