ከቦታና ከቤት ግብር ገቢ 1.98 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ
👉 ክፍያ እስከ የካቲት 30 ቀን መፈፀም ይኖርበታል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የቦታና የቤት ግብር የመክፈያ ጊዜ በበጀት ዓመቱ እስከ የካቲት 30 ቀን 2017 ዓ.ም መሆኑን አሳስቧል።
ቢሮው በ2017 በጀት ዓመት 5 ወራት ከቦታና ከቤት ግብር ለመሰብሰብ ከታቀደው ገቢ 1.98 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን በቢሮው የግብር አወሳሰን ድጋፍ ክትትል ቡድን አስተባባሪ አቶ ኸይሩ ሁሴን ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
የቦታና የቤት ግብር አዋጅ ቁጥር 80/1968 መሰረት ማንኛውም ባለይዞታ የቤትና የቦታ ግብር እንዲከፍል የሚደነግግ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ ሚያዚያ 2015 ዓ.ም በተደረገ የክፍያ ማሻሻያ መሰረት ግብሩ እየተሰበሰበ መሆኑን አስታውቋል ።
በአዋጁ በተቀመጠው መሠረት የቦታና የቤት ግብር የመክፈያ ጊዜ በበጀት ዓመቱ እስከ የካቲት 30 ቀን 2017 ዓ.ም መሆኑን የጠቀሱት አቶ ኸይሩ የይዞታ ባለቤቶች መጨረሻ ከሚፈጠር መጨናነቅና ቅጣት ለመዳን የሚጠበቅባቸውን ትክክለኛውን የቦታና የቤት ግብር ከወዲሁ መክፈል እንደሚገባቸው አሳስበዋል ።
በቢሮው በበጀት ዓመቱ 5 ወራት ከቤትና ከቦታ ግብር 2 ነጥብ 72 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 1 ነጥብ 98 ቢሊዮን ብር ወይም የዕቅዱን 73ነ ጥብ 25 በመቶኛ ተሰብስቧል።
ቢሮው መረጃዎችን በማጥራት ከዚህ በፊት ተለክተው ክፍተት ያለባቸውን ይዞታዎች በድጋሚ የመለካትና ከዚህ በፊት ያልተካተቱትን ደግሞ ልኬት በመስራት ወደ ግብር ስርአት እያስገባ መሆኑ ተገልጿል።
በበጀት ዓመቱ ቢሮው ከቦታና ከቤት ግብር በአጠቃላይ 8 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ሊሰበሰብ እንደታቀደ ተጠቁሟል።
@Ewunet_Media