#Update #ራይ
" ግጭቱ ከ20 ደቂቃ በላይ አልፈጀም፤ በግጭቱ የሞተ ሰውም የለም " - በትግራይ ደቡባዊ ዞን የራያ ጨርጨር አስተዳዳሪ አቶ ግደይ ካልኣዩ
" የአማራ ታጣቂዎች በትግራይ ግዛት ውስጥ የፈፀሙት ትንኮሳ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እንዲያስቆመው ተደርጓል " - የትግራይ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ረዳኢ ሓለፎም
የትግራይ እና አማራ ክልሎች የይገባናል ጥያቄ በሚያነሱበት የራያ አላማጣ አካባቢ ግጭት መነሳቱን አንድ የራያ አላማጣ እና አካባቢው አመራር ለቲክቫህ ኢትዮጵያ መግለፃቸው ይታወሳል።
አመራሩ ፥ " ህወሓት የፕሪቶሪያውን ስምምነት በመጣስ ጦርነት ከፍቷል፤ የሰው ህይወት ጠፍቷል፣ የተኩሱ መነሻ በራያ እና ወልቃይት በትምህርት ስርዓቱ ካርታ ላይ ተካተዋል የሚል ነው " ብለው ነበር።
በትግራይ በኩል ምን ምላሽ ተሰጠ ?
ቲክቫህ ኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በትግራይ ደቡባዊ ዞን የራያ ጨርጨር አስተዳዳሪ አቶ ካልኣዩ ግደይና የክልሉን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ረዳኢ ሓለፎም ጠይቋል።
አቶ ካልኣዩ ግደይ በፅሁፍ በሰጡት ምላሽ ፥ " ግጭቱ የተከሰተው መጋቢት 17 /2016 ዓ.ም ቀን ነው። በር ተኽላይና ዶዶታ በተባለ አከባቢ ነው። ቶክሱን የጀመሩት የአማራ ታጣቃዎች ሲሆኑ በትግራይ የፀጥታ ሃይሎች ላይ ቶክስ የከፈቱት በአለማጣ ከንቲባ አቶ አበራ ሃይሉ ጥሪ የተደረገላቸው የአማራ ክልል ታጣቂዎች ናቸው " ብለዋል።
ግጭቱ 20 ደቂቃ በላይ አልፈጀም ያሉት አስተዳዳሪው በግጭቱ የሞተ ሰው የለም ብለዋል።
" ግጭቱ ሆን ተብሎ ፦
- የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ለማደናቀፍ
- የትግራይ ማህበረሰብ ተወካዮች ከጠቅላይ ሚንስተር ዶ/ር አብይ አህመድ ያደረጉት ውይይትና የአማራና የትግራይ ፕሬዚዳንቶች በፕሪቶሪያ ውል አተገባበር ዙሪያ የፈጠሩት መድረክን ተከትሎ 'ውሉ ተግባራዊ ይሆናል' የሚል ስጋት ስለፈጠረባቸው ነው " ብለዋል።
አቶ ካልኣዩ አክለው " የአማራ ክልል ታጣቂዎች ለቀጣይ ትንኮሳ በመዘጋጀት ላይ መሆናቸው ደርሰንበታል " ብለዋል።
የመቐለ ቲክቫህ ቤተሰብ አባል የራያ ጨርጨር ወረዳ አስተዳዳሪ በፅሁፍ የሰጡት መረጃ እንዲያረጋግጡለት ፤ የትግራይ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ረዳኢ ሓለፎም አግኝቶዋቸዋል።
አቶ ረዳኢ ሓለፎም ፥ የራያ ጨርጨር ወረዳ አስተዳዳሪ መረጃ ' ልክ ነው ' ብለዋል።
ከዚህ ባሻገር ፤ " የአማራ ታጣቂዎች በትግራይ ግዛት ውስጥ የፈፀሙት ትንኮሳ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እንዲያስቆመው ተደርጓል " ሲሉ ተናግረዋል።
" የፌደራል መንግስት በትግራይ ግዛት ውስጥ በመግባት ተደጋጋሚ ግጭት በመፍጠር ላይ የሚገኙ የአማራ ክልል ታጣቃዊች በዘላቂነት እንዲያስታግስ እና በሃይል ከያዙት ግዛት ለቀው እንዲወጡ የሚያስገደደው የፕሪቶሪያ የሰላም ውል እንዲተገብር ደግመን ደጋግመን እንጠይቃለን " ብለዋል።
መረጃው በመቐለ የቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰብ አባል ተዘጋጅቶ የተላከ ነው።
@tikvahethiopia @seleeewnet