የመራጮች ምዝገባን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ የጊዜ ሰሌዳን አውጥቶ ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነ ይታወቃል። ከዚህም መካከል በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ ያለው የእጩዎች ምዝገባ አንዱ ሲሆን በጊዜ ሰሌዳው መሰረት ተከታዩ ዋና ተግባር የመራጮች ምዝገባን ማከናወን ነው።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ተግባራትን ማከናወን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ካጋጠሙት ተግዳሮቶች መካከል የምርጫ ክልል ቢሮዎች ዝግጅት መዘግየት እና አስፈጻሚዎች ሰልጥነው ከተሰማሩም በኃላ ቢሆን ቢሮዎች ዝግጁ ሆነው ባለመገኘታቸው የቢሮ መከፈት መዘግየቱ፣ በተወሰኑ ክልልሎች አስፈላጊው ቢሮዎች ተዘጋጅተው ባለማለቃቸው የእጩዎች ምዝገባ በጊዜ ሰሌዳው መሰረት መጀመር አለመቻሉ እና ለሁለት ዙር መከፈሉ፣ ለምርጫ ቁሳቁሶች ስርጭት የትራንስፖርት እጥረት እና የገለልተኛ አስፈጻሚዎች ምልመላ ሂደት ከፍተኛ ጥንቃቄ እና ጊዜ የሚወስድ ተግባር መሆኑ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።
በዚህም መሰረት ቦርዱ የእጩዎች ምዝገባ ሂደትን በመገምገም ተጨማሪ ቀናት እንደሚያስፈልገው በመረዳት በመጀመሪያ ዙር የእጩዎች ምዝገባ በተጀመረባቸው ክልሎች ለ4 ቀናት ያራዘመ ሲሆን፣ በሁለተኛ ዙር የእጩዎች ምዝገባ የተጀመረባቸው ክልሎችም ላይ የቢሮዎች ዝግጅት የመጀመሪያዎቹ ቀናት ላይ ችግር ሆኖ እንደነበር ተረድቷል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የገለልተኛ ምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ ተግባርንም እያከናወነ እንደሆነ ይታወሳል፤ 140 ሺህ በላይ እጩ የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚነት የሚሰሩ ግለሰቦችን አዘጋጅቶ ገለልተኝነት ማጣራትን እያከናወነ ሲሆን፣ ይህም ከተጠበቀው ጊዜ በላይ ሊወስድ ችሏል። በመሆኑም ከክልሎች የሚገኘው የቢሮዎች ትብብር በመዘግየቱ፣ የእጩዎች ምዝገባ ቀናት ከተጀመሩም በኋላ ዝግጁ ያልሆኑ የተወሰኑ ቢሮዎች የነበሩ በመሆኑ ፣ ፓለቲካ ፓርቲዎችም ተጨማሪ ቀናት በመጠየቃቸው እና የእጩዎች ምዝገባ በመራዘሙ፣ እንዲሁም በእጩዎች ምዝገባ ወቅት ያጋጠመው የቁሳቁስ ማጓጓዝ ተግዳሮቶች በመገምገም እና የእጩ አስፈጻሚዎችን ገለልተኝነት የማጣራት ስራን በተሻለ ጥራት ለማከናወን የመራጮች ምዝገባን ከተያዘለት ቀን የካቲት 22 ቀን 2013 ዓ.ም ወደ መጋቢት 16 ቀን 2013 እንዲዘዋወር ወስኗል።
በመሆኑም የ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከመጋቢት 16- ሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ የሚከናወን ሲሆን ቦርዱ ለወደፊትም ከመራጮች ምዝገባ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ መረጃዎችን የሚያቀርብ ይሆናል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
የካቲት 22 ቀን 2013 ዓ.ም