Dr. Eyob


Channel's geo and language: not specified, not specified
Category: not specified


Life skill development!
You can contact me
@DrEyobmamo

Related channels  |  Similar channels

Channel's geo and language
not specified, not specified
Category
not specified
Statistics
Posts filter


አራቱ የእድገት ዘርፎች

ክፍል አራት - በገንዘብ ብቃት ማደግ

እድገት የግድ የመሆኑንና ሁለንተናዊ ሊሆን እንደሚገባው አንድን ሃሳብ ጀምረን ነበር፡፡ እስካሁን፣ በራእይ የማደግን፣ በእውቀት የማደግንና በስሜት ብቃት የማደግን ሁኔታ ተመልክተናል፡፡ ዛሬ የመጨረሻውን ክፍል፣ ማለትም፣ በገንዘብ ብቃት የማደግን አስፈላጊነት በጥቂቱ እናያለን፡፡

ምንም አይነትነት አስገራሚና አሳማኝ ራእይ ቢኖርህና አስፈላጊው አይነት የእውቀትና የስሜት ብቃትን ብታዳብር ያንን ራእይህን ተግባራዊ ለማድረግ በቂ ገንዘብ ከሌለህ የትም አትደርስም፡፡ በዚህ ምድር ላይ ከገንዘብ ውጪ ብዙም እንቅስቃሴ ማድረግ እንደማትችል እወቅ፡፡

በገንዘብ ብቃት ማደግ በአንድ ጎኑ ራእይህ የሚጠይቀውን ወጪ በመሸፈን ተግባራዊ የማድረግ ብቃት ሲሰጥህ በሌላ ጎኑ ደግሞ የእለት ኑሮህን ለመግፋትና ይህንና ያንን ቀዳዳ ለመድፈን ስትታገል ራእይህን ከመከታተል እንዳትገታ የገንዘብ ነጻነትን ይሰጥሃል፡፡

በገንዘብ ለመበልጸግ መፈለግ ምንም እንከን የማይወጣለት ምኞት ነው፡፡ ጥንቃቄ ሊወሰድበት የሚገባቸው ጉዳዮች ገንዘብን ለማግኘት የምንጠቀምበት መንገድ ላይና ገንዘቡ ከመጣ በኃላ ለምን እንዳዋልነው ነው፡፡ በገንዘብ ብቃት ለማድግ መመለስ ያሉብን ጥያቄዎች ከዚህ በታች ይገኛሉ፡፡

ራስን የማሻሻል ጥያቄ:- “የገንዘብ ገቢ የማግኛና ገቢዬንም የማሻሻያ እውቀት አለኝ?”

በብቃት ሳላድግ በገንዘብ ማደግ አልችልም፡፡ ስለዚህም፣ በእውቀትና በሙያ የማድግበትን መንገድ ማመቻቸት አለብኝ፡፡ ማንነቴን ሳሳድግና ተፈላጊነቴ ሲጨምር ሰዎች እኔንና በእኔ ውስጥ ያለውን እውቀት ለማግኘት ምንም አይነት ገንዘብ ለመክፈል ዝግጁ ይሆናሉ፡፡:

የእቅድ ጥያቄ:- “በእጄ ያለውን ገንዘብ የመጠቀሚያ የበጀት እቅድ አለኝ?”

ገንዘብ በእጅ ማስገባት አንድ ነገር ነው፣ ያንን ገንዘብ በተገቢው መንገድ ተገቢው ነገር ላይ ማዋል ደግሞ ሌላ ነገር ነው፡፡ የአንዳንድ ሰዎች ችግር ገንዘብ ማግኘት አይደለም፣ ገንዘቡ እጃቸው ከገባ በኋላ ግን የት እንደገባ በማያውቁት መንገድ ባክኖ ያዩታል፡፡

የጤናማነት ጥያቄ:- “ገንዘብን ለማግኘት ባለኝ ትጋት የግሌንና የማህበራዊ ጤንነቴን የምጠብቅበት ብስለት አለኝ?”

አንዳንድ ሰዎች ገንዘብን ለማግኘት የሚሄዱበት ጎዳና ከጦርነት ተለይቶ አይታይም፡፡ ገንዘብ አግኝተው በሂደቱ ውስጥ ግን ራሳቸው የሚያጡ ሰዎች፣ ገንዘብን ሰብስበው በምንም የማይለወጡ ወዳጆቻቸውን የሚበትኑ ሰዎችም ቁጥር ጥቂት አይደለም፡፡

በሌላ ሃሳብ እስከምንገናኝ የሁለንተናዊ እድገትን ጎዳና ይዘህ ቀጥል!




አራቱ የእድገት ዘርፎች

ክፍል ሶስት - በስሜት ብቃት ማደግ

እድገት የግድ የመሆኑንና ሁለንተናዊ ሊሆን እንደሚገባው አንድን ሃሳብ ጀምረን ነበር፡፡ በመጀመሪያው ክፍል ከሁሉ በፊት ሊቀድም የሚገባውን በራእይ የማደግን አስፈላጊነት፣ በመቀጠልም በእውቀት የማደግን ሁኔታ ተመልከተናል፡፡ ዛሬ በስሜት ብቃት የማደግን ሁኔታና አስፈላጊነት በጥቂቱ እናያለን፡፡

በሕይወታችን በፍጹም ልንተማመንባቸው ከማንችላቸው ነገሮች አንዱ ስሜት የተሰኘው ነገር ነው፡፡ እንደምንሰማው፣ እንደምናየውና እንደምናሰላስላቸው ሃሳቦች የተለያዩ ስሜቶች ሲፈራረቁብን ራሳችንን እናገኘዋለን፡፡ የትናንት ስሜታችንን ዛሬ፣ የዛሬው ደግሞ ነገ አናገኘውም፡፡ ይህንን ተለዋዋጭ የስሜት ሁኔታ በተሳካለት መልኩ ለመያዝ በስሜት ብቃት ማደግ የግድ ነው፡፡

በስሜት ብቃት ማደግ ማለት ስሜትን የመቆጣጠርና ከስሜት ይልቅ መርህን የማስቀደም ብቃት ማለት ነው፡፡ ስሜት ሲለዋወጥ፣ ስሜት ሲጎዳና አጉል ስሜትን የሚያነሳሱ ሁኔታዎች ሲከሰቱ በስሜት ብቃት የበሰለ ሰው የጊዜውን ስሜት ለማርካት ብሎ ዘላቂውን ራእዩን አይጥልም፡፡ በዚያ ፈንታ ከትኩረቱ የማይወጣበትን መንገድ ይፈልጋል፡፡ በስሜት ለመብሰል የሚጠቅሙንን ጥቂት ልምምዶች እንመልከት፡፡

በተግባር መጽናት::
ስሜትህ ከፍና ዝቅ ሲል ከተግባሮችህና ከአላማህ የማትመለስ ሰው ልትሆን ይገባል፡፡ በስሜት ብቃት የበለጸግህ ሰው ለመሆን ከፈለክ እንደ አየሩ ጸባይና እንደ እለቱ ስሜትህ ከመነዳት መቆጠብ አለብህ፡፡ በተቃራኒው የስሜትህን ግፊትና ንዝረት ገታ በማድረግ ውስጥህ ባመነበት እውነታ መንቀሳቀስ አስፈላጊ ነው፡፡

ሰዎችንና ሁኔታዎችን መታገስ::
ስሜታዊ ምላሽን የሚጋብዝ ሰውና ሁኔታ ሲያጋጥምህ እዚያው በጋለ ስሜት ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ተረጋግተህ ትክክለኛውን ምላሽ አስበህ ምላሽን የመስጠትን ልማድ አዳብር፡፡ አንድን ነገር ተናግረህና አድርገህ በኋላ መዘዙን ለመቀልበስ ከመጣጣር ይልቅ አስበህና ግራና ቀኙን አይተህ ምላሽ መስጠት የተሻለ ውጤት አለው፡፡

ምክርን መስማት::
አንዳንድ ስሜታዊነቶችህ ለአንተ ግልጽ ሆነው አይታዩህም፡፡ አንተ የማታስተውለው፣ ሌላው ሰው ግን በግልጽ የሚያየው ባህሪ እንዳለህ አትዘንጋ፡፡ በተለይም የትዳር ጓደኛህ ወይም በቅርብ የሚያውቁህ ወዳጆችህ በዚህ ጉዳይ ላይ ግሩም መረጃ ሊሰጡህ ይችላሉና ልቦናህን ክፍት አድርግ፡፡ ኋላ ቀር እንዳትሆን ተከላካይና አልሰማ ባይ አትሁን፡፡

በሚቀጥለው ክፍል ሌላ የእድገት እውነታን ይጠብቁ፡፡




አራቱ የእድገት ዘርፎች

ክፍል ሁለት - በአእምሮ እውቀት ማደግ

እድገት የግድ የመሆኑንና ሁለንተናዊ ሊሆን እንደሚገባው አንድን ሃሳብ ጀምረን ነበር፡፡ በመጀመሪያው ክፍል ከሁሉ በፊት ሊቀድም የሚገባውን በራእይ የማደግን አስፈላጊነት ተመልከተናል፡፡ ዛሬ የአእምሮን እውቀት አስፈላጊነት በጥቂቱ እናያለን፡፡

አእምሮአችን አስገራሚ የሆነ የፈጣሪ ስጦታ ነው፡፡ ለተጠቀሙበት ምንም ገደብ የሌለው እስኪመስለን ድረስ የሚፈጥራቸው ነገሮችና የሚያገኛቸው ግኝቶች አስደናቂ ናቸው፡፡ ለተውትና ችላ ላሉት ደግሞ ካለበት እልፍ የማይል፣ ምናልባትም ወደታች የሚያዘቅጥ የማንነት ክፍል ነው፡፡

አንድ ሰው ሊከተለው የሚፈልገውን ራእይ በቅጡ ካወቀ በኃላ በመቀጠል ሊያደርገው የሚገባው ነገር ያንን ራእይ በሚገባ ለማከናወን የሚያስፈልገውን እውቀት ማዳበር ነው፡፡ ራእይ ሳይኖር የሚከማች እውቀት ስኬታማ የማድረጉና እርካታን የመስጠቱ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው፡፡ የእውቀትን አይነት አከማችተው በማእበል እንደተመታች መርከብ ከዚህና ከዚያ የሚዋዥቁ ሰዎች ቁጥር እጅግ ብዙ ነው፡፡ ካለማቋረጥ በአእምሮ እውቀት የማደግ ሂደት ውስጥ ለመግባት የሚከተሉትን እውነታዎች ማጤን እንችላለን፡፡

የተከፈተልህን ለይ::
በቀላሉ የሚበራልህንና አእምሮህ የተከፈተለትን የእውቀት አይነት በመለየት ከራእይህ አንጻር ራስህን አዘጋጅ፡፡ ራእዬ ነው ብለህ የምታስበው ነገርና አእምሮህ የተከፈተለት ነገር አልጣጣም ካሉህ ምናልባት ከጊዜአዊ ምኞትህና በጊዜው ስሜትሀን ባነሳሳው ሁኔታ አንጻር ብቻ ተነስተህ ራእይህን መስርተህ እንዳይሆን ራእይህን መፈተሸ አስፈላጊ ነው፡፡

አንብብ::
መጽሐፍ የማንበብ ልማድህ እንዴት ነው? በወር ውስጥ ስንት ምእራፍ ታነባለህ? ጀምረህ የጨረስካቸው መጽሐፍቶች ምን ያህል ናቸው? እነዚህን ጥያቄዎች በቁም ነገር ጠይቅና ራስህን በማየት ለውጥን አድርግ፡፡ መጽሐፍትን ስትመርጥ አጠቃላይ አላማህን በሚያግዙና ራስህን ለማሳደግ በሚጠቅሙህ መጽሐፍቶች ላይ ትኩረት ስጥ፡፡

የተግባር ሰው ሁን::
እውቀትህን በተግባር ካላዋልከው ከመረጃነት አያልፍም፡፡ ይህንን አስታውስ፣ መረጃ ብቻውን እውቀት አይደለም፡፡ ያዳበርካቸውን እውቀቶች ወደ ተግባር ማዋል ወይም ያንን ለማድረግ በማቀድ ላይ መሆን አለብህ፡፡ “አውቃለሁ” ለማለት ያህል አትወቅ፡፡ ያንተን ያህል ሳያውቁ ከአንተ የበለጠ ያከናወኑ ሰዎች እንዳሉ አትዘንጋ፡፡

በሚቀጥለው ክፍል ሌላ የእድገት እውነታን ይጠብቁ፡፡




አራቱ የእድገት ዘርፎች

ክፍል አንድ - በራእይ ማደግ

በማንኛውም የሕይወት መስኮቻችን እድገት ወሳን ጉዳይ ነው፡፡ እድገት ማለት ዛሬ ከትናንትናው የተሻለ ደረጃ ላይ የመድረስን፣ ነገ ደግሞ ከዛሬው የላቀ ደረጃ ላይ የመድረስን ሁኔታ ጠቋሚ ነው፡፡ እድገት ሙሉ እንዲሆን ሁለንተናዊ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ማለትም፣ በአንድ አቅጣጫ ብቻ አድገን በሌላለው ዘርፍ ካላደግን፣ የኋላ ኋላ ያላደግንበት ዘርፍ ያደግንበትን ዘርፍ ይዞት ይወርዳል፡፡

ሁለንተናዊ እድገት ዘርፈ-ብዙና በርካታ ሁኔታዎችን የሚነካ ጉዳይ ነው፡፡ ዛሬን ጀምሮ በሚቀጥሉት ቀናት የተወሰኑትን ዋና ዋና እድገት የሚጠይቁ ሁኔታዎችን እንመለከታለን፡፡

ማንኛውም ልናከማቸውም ሆነ ልናዳብረው የምንፈልገው ነገር መግቢያው በር ራእይ ሊሆን ይገባዋል፤ አለዚያ ከኋላ የምንጀምር ሰዎች እንሆናለን፡፡ ከኋላ መጀመር ማለት አንድን ነገር ከጨበጥን በኋላ በዚህ እጃችን በገባው ነገር፣ “ምን ላድርግበት?” ብሎ ማሰብ ማለት ነው፡፡ ይህ አመለካከት ስልታዊ አይደለም፡፡

አንዳንድ ሰዎች ገንዘብንና ሌሎች ነገሮች ለምን እደሚሰበስቡ ሳያውቁትና አስቀድመው ሳያስቡበት በእጃቸው ካስገቡ በኋላ በዚያ እጃቸው በገባው ነገር ምን እንደሚያደርጉ ለማወቅ ሲጨናነቁ ራሳቸውን ያገኙታል፡፡ የስልታዊ አመለካከት ቅደም-ተከተል ግን መነሻው፣ ለመሆንና ለማከናወን ከፈለግነው ነገር አንጻር ሊሆን ይገባዋል፡፡ በመጀመሪያ ራእያችንን ማብሰልና በመቀጠልም ከዚያ ራእይ አንጻር በተለያዩ የሕይወት አቅጣጫዎች ማደግን ይጠቀልላል፡፡ የራእይ ሰው መሆንህን ለመገምገም የሚከተሉትን እውነታዎች አስብ፡፡

አንደኛ እውነታ፡- የምትሞትለት ራእይ ከሌለ የምትኖርለት ራእይ አይኖርህም!

የራእይን እውነተኛነት የማወቂያ ቀላል ጥያቄ፣ “ይህንን ራእይ መክፈል ያለብኝን መስዋእትነት አስከመክፈል ድረስ እከታተለዋለሁ?” የተሻለ እድል እስኪገኝ ድረስ ወይም አንድ ገጠመኝ እስኪጋፋን ድረስ ብቻ የምንከተለው ራእይ በእውነትም ራእይ አይደለም፡፡ ትክክለኛ ራእይ የጨበጠ ሰው በሆነ ባልሆነ ምክንያት አይወላውልም፡፡

ሁለተኛ እውነታ፡- ሳይከፈልህ የምታከናውነው ራእይ ከሌለ ቢከፈልህም የምታከናውነው ራእይ አይኖርህም!

የራእይን ትክክለኛነት የማወቂያ ሌላ ጥያቄ፣ “ይህንን ራእይ ቢከፈለኝም ባይከፈለኝም እከታተለዋለሁ?” የምንኖርበት ዘመን ሰዎች ለራሳቸው የሚጠቅም ስልጠናን ለመውሰድ እንኳ ገንዘብ እንዲከፈላቸው የሚጠብቁበት ጊዜ ነው - አሳዛኝ አመለካከት! እውነተኛ ባለ ራእይ ምስጋናም ሆነ ጥቅማ ጥቅም ባያገኝ እንኳ ወደ ፊት ይዘልቃል፡፡

ሶስተኛ እውነታ፡- በራስህ መነሳሳት የምትከተለው ራእይ ከሌለህ በሰው ግፊት የምትከተለው ራእይ አይኖርህም!

የራእይን እውነተኛነት ለመለየት መጠየቅ ያለብን ሌላ ጥያቄ፣ “ይህንን ራእይ ካለምንም የውጪ ግፊት እከታተለዋለሁ?” እውነተኛ ባለ ራእይ የሚደግፈውና የሚያበረታታው ሰው አገኘም አላገኘም በውስጡ የተቀጣጠለውንና ሆኖ ማየት የሚፈልገውን ነገር ከመከተልና የሚያስፈልገውን ከማድረግ ወደ ኋላ አይልም፡፡

በሚቀጥለው ክፍል ሌላ የእድገት እውነታን ይጠብቁ፡፡




ወጣት-ነክ ስህተቶችና ጸጸት (ክፍል ሁለት)

የጸጸቱ አይነትና ደረጃ ይለያይ እንጂ፣ ማንም ሰው ከጸጸት ስሜት ውጪ መኖር አይችልም፡፡ ሁል ጊዜ ከመንቀሳቀስና ከመጓዝ ስለማናቆም ከዚያው ጋር ስህተት ሊመጣ ስለሚችል ጸጸት ይከተላል፡፡ አንድን መንገድ ተጉዘን አሁን የደረስንበት ደረጃ ከደረስን በኋላ ያልተጓዝንበትን ሌላ ጎዳና የማሰብ ዝንባሌ የጸጸት መነሻው ነው፡፡ ስለዚህም ጸጸት ማለት ያደረግነውን ነገር ወይም ያላደረግነውን ነገር በማሰብ ውጤቱን ካሰላን በኋላ “ባደረግሁት ኖሮ ወይም ባላደረግሁት ኖሮ” በማለት፣ ሌላ መንገድ ብንከተል ኖሮ ሊመጣ ከሚችለው የተሻለ ውጤት አንጻር ጠንካራ ስሜት ውስጥ መግባት ማለት ነው፡፡

ትክክለኛ ምላሽ የተሰጠው ጸጸት ለትምህርት ሲለወጥ፣ ትክክለኛ ምላሽ ያልተሰጠው ጸጸት ደግሞ ለጉዳት ያጋልጣል፡፡ በጸጸት ምክንያት በኃዘንና በተስፋ መቁረጥ ውስጥ መኖር የጸጸት ጎጂ ገጽታ ሲሆን፣ ጸጸት ለጥቅም የሚውለው ጊዜው ሳይዘገይ ትክክለኛው ምላሽ ሲሰጠው ብቻ መሆኑን ማስታወስ አለብን፡፡ ከዚያ እጅግ የላቀው መንገድ ደግሞ ነገ ለጸጸት ከሚዳርጉን ሁኔታዎች ዛሬውኑ መጠንቀቅ ነው፡፡
ባለፈው ጽሑፌ በዚህ ርእስ ስር ወጣቶች የኋላ ኋላ ሊጸጸቱባቸው የሚችሏቸውን ሁለት ነጥቦች ማንሳታችን የሚታወስ ነው፡፡ እነዚህን ሃሳቦች አንድ እርምጃ በመውሰድ ተጨማሪ ነጥቦች እንመልከት፡፡

የተቀባይነት ዓለም::
የኋላ ኋላ እንዳትጸጸት በልጅነትህም ሆነ በወጣትነት እድሜህ ሰዎች ስለገፉህ፣ ፍቅርንና ተቀባይነትን ስለነፈጉህና ስለጣሉህ በመራራነት በመሞላትና ከመስመር በመውጣት የራስህን ህይወት አትጉዳ፡፡ መገፋት፣ ተቀባይነት ማጣትና ያለመወደድ ስሜቶች ለተለያዩ ላልታሰቡ ውሳኔዎች ከሚገፋፉህ የስሜት አይነቶች መካከል በቀንደኛነታቸው ይታወቃሉ፡፡

ሰዎች ተቀባይነትንና መወደድን ለማግኘት ሲሉ ምንም ነገር ከማድረግ አይመለሱም፡፡ መገፋት ከሚያመጣባቸው የስሜት ጫና ይልቅ የማይፈልጉትን ከማድረግ የሚመጣውን ያለመመቸት ስሜት ቢታገሱ ይሻላቸዋል፡፡ መጨረሻው ግን እንደማያምር የሚደርሱበት ብዙ ዘመን ካቃጠሉ በኋላ ነው፡፡ ቤተሰብህ፣ የቅርብ ጓደኞችህና ፍቅረኛ ስለገፉህና ስላልተቀበሉህ ስህተተኞች የመሆናቸው እውነታ በመራራ ውሳኔህ ምክንያት ከሚመጣ የወደፊት ጸጸት አያድንህም፡፡

የስሜት አለም::
የኋላ ኋላ እንዳትጸጸት አንተ ስሜትህን የምትመራበት እንጂ ስሜትህ አንተን የሚመራበት ሕይወት አያስፈልግህም፡፡ በመጠጥና በተለያዩ አደንዛዥ እጾች የተተበተበ ስሜት ካለህ፣ ትክክለኛና እቅድ የሞላው የሕይወት ዘይቤ ለመምራት ወደማትችልበት የስሜት እስራት ውስጥ ይጨምርሃል፡፡ ካልቀመስከኝ ወይም ካላሸተትከኝ አትንቀሳቀስም የሚልህና ስሜትህን በማሰር ጥገኛ አድርጎ የሚያስቀምጥ ማንኛውም እጽ ለአንተ አይመጥንህም፡፡

በተጨማሪም፣ ምግባረ-ብልሹ የወሲብ ምስሎችና ፊልሞች አንድ ጊዜ ስሜትህን ከተቆጣጠሩት ዲሲፕሊን ያለውን የሙያና የስራ፣ እንዲሁም የፍቅርና የቤተሰባዊ ሕይወት እንዳትመራ ጠንቅ ይሆኑብሃል፡፡ ይህንን አስታውስ፣ በጊዜው ያለህ፣ “ሰውን እስካልጎዳሁ ድረስ ምን አለበት” የሚለው ፍልስፍናህ ከነገ ጸጸት አያድንህም፡፡

ከነገ ጸጸት ለመዳን የዛሬ ውሳኔህ ወሳኝ ነው!!!

በርእሰ-ጉዳዩ ላይ የጠለቀና ተግባራዊ እውቀት ለመገንባት ከፈለክ “የሕይወት ጸጸቶች” የተሰኘውን መጽሐፌን ማንበብህን አትዘንጋ፡፡




ወጣት-ነክ ስህተቶችና ጸጸት (ክፍል አንድ)

አንድ ሰው በሕይወት በኖረባቸው አመታቶቹ በርካታውን ስህተት የሚሰራው በልጅነቱ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ከዚያ በመቀጠል በርካታ ስህተት የሚሰራባቸው አመታት የወጣትነት አመታት ናቸው፡፡ እንዲህ እያለ በእድሜ በገፋ ቁጥር የስህተቱ ቁጥር እየቀነሰ እንደሚሄድ ይጠበቃል፡፡ ይህ ቀላል ስሌት የሚጠቁመን ትክክለኛውን ከስህተት የመማር ሂደት የሚከተል ሰው ሁኔታ ነው፡፡

የልጅነት ስህተት በአብዛኛው ያለማወቅና ያለመብሰል ስህተት ነው፡፡ የወጣትነት ስህተት በመጠኑ ያለመብሰል ስህተት ቢገኝበትም በአብዛኛው የድፍረትና “የቅብጠት” ስህተት ነው፡፡ የአዋቂነት ስህተት ግን በአብዛኛው ካለፈው ስህተት ያለመማርና ለማደግ ፈቃደኝነትን የማጣት ስህተት ሊሆን ይችላል፡፡

ለመነጋገር ወዳሰብኩት የወጣትነት ስህተት ስናተኩር ማንኛውም ወጣት ከጸጸት ለመዳን ከፈለገ የተለየ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባው አቅጣጫዎች በርካታ የመሆናቸውን ጉዳይ እንድናስብ እፈልጋለሁ፡፡ ከዚህ በታች የምንጠቅሰው የተወሰኑትንና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወጣቶች መንደርደሪያ እንዲያገኙ የሚረዷቸውን የስህተት አይነቶች ነው፡፡

የእውቀት ዓለም
የኋላ ኋላ እንዳትጸጸት የትምህርትን ጉዳይ በምንም አትለውጠው፡፡ አንድ ሰው ከልጅነት አልፎ ወደወጣትነት ሲሻገር የራሱ የሆነን ዝንባሌ ወደማዳበር እንደሚያድግ ግልጽ ነው፡፡ አንዱ የሚከተለውን መንገድ ሌላኛው አይከተለውም፡፡ ያም ሆኖ ግን ከማንኛውም ወጣት አጀንዳ ውስጥ ትምህርትን የመማር እቅድ በፍጹም ሊፋቅ አይገባውም፡፡ ለመከተል የፈለከውን የሕይወት አቅጣጫ ከማወቅ ውጪ እምቅ ብቃትህ ላይ ልትደርስ እንደምትችል በሚገባ መቀበል አለብህ፡፡

አለማወቅ ጨለማ ነው፡፡ አለማወቅ ኋላ ቀርነት ነው፡፡ የአለማወቅህን መዘዝ ደግሞ የምታውቀው ጊዜው ካለፈ በኋላ ነው፡፡ ጊዜያዊ ጨዋታ፣ ገንዘብን የማግኘት ፍላጎት፣ “ትምህርት አይገባኝም” የሚል ሰበብና የመሳሰሉት ምክንያቶች ባለመማርህ ምክንያት ነገ ከሚመጣብህ ጸጸት በፍጹም አያድንሁም፡፡

የአቻዎች ዓለም
የኋላ ኋላ እንዳትጸጸት የእድሜ አቻዎችህ የተለያዩ ከመስመር የሚያወጡ ነገሮችን እንድታደርግ ሲጋብዙህ፣ በእነሱ ግፊት ተነሳስተህ ወይም ከቡድናቸው እንዳያገልሉህ ብለህ ራስህን አትሽጥ፡፡ በወጣትነት ዘመን ያላመንንበትን የሕይወት መስመርና የስህተት ጎዳና እንድንከተል ከሚጫኑን ኃይሎች መካከል የአቻ ግፊት (Peer Pressure) ቀንደኛው ነው፡፡ በአለም ላይ በሚልየን የሚቆጠሩ ሰዎች በመካከለኛው የእድሜ ክልላቸውና አልፎም በእርጅናው አመቶቻቸው ሲባንኑ ደስ በማያሰኛቸው ሁኔታ ላይ ራሳቸውን ያገኙታል፡፡ ምክንያቱን ሲፈልጉት በአብዛኛው በወጣትነት ዘመናቸው ለአቻ ግፊት እምቢ አለማለት እንደሆነ ይደርሱበታል፡፡

ምንም እንኳን ጊዜያዊ ግፊት ቢበዛብህና ራስህን በመገደድ ስሜት ውስጥ ብታገኘውም ዛሬ “ደስ” ብሎህ ነገ ከምትጸጸት ዛሬ ራስህን ገታ አድርገህ ለነገ ብታጠራቅም ይሻልሃል፡፡ አንድ ነገር በፍጹም አትዘንጋ፣ የአቻዎችህ ጭብጨባና “ጎሽ” ባይነት ነገ ከመጸጸት አያድንህም፡፡

ይቀጥላል . . .




የተሰበረ ልብ!

በአንድ ግር ግር በሞላበት ከተማ መካከል አንድ የተለያዩ ጥገናዎችን የሚዲርግ ቤት ለማስታወቂያነት የሰቀለው ታፔላ እንዲህ ይላል፡- “ከተሰበረ ልብ በስተቀር ሁሉንም ነገር እንጠግናል”፡፡ እውነት ብለዋል፡፡ ብዙ ነገር በሚጠገንበት በዚህ የተሸሻለ ዘመን ውስጥ ልብን የሚጠግን ሰው ፈልጎ ማግኘት ከባድ ነው፡፡

የልብ ስብራት! የብዙ ሰዎች የዘመኑ ችግር! ልብ አንዴ ከተሰበረ ለመጠገን ጊዜ ይፈጃል፡፡ ልብ መሰበሪያ መንገዱ ደግሞ ብዙ ነው፡፡ ያፈቀርነው ትቶን ሲሄድ፣ ያመንነው ሲከዳን፣ ያበደርነው “ሲበላን”፣ የእኔ ነው ያልነው ሲከዳን፣ ያልጠበቅነው ነገር ሲሆን፣ የጠበቅነው ነገር ሲቀር . . . ልብ መሰበሩ አይቀርም፡፡ ከእነዚህ ማሕበራዊ ሂደቶች ውጪ መኖር ስለማንችልና ሁል ጊዜ ተጋላጮች (Volnerable) ስለሆንን ልባችንን የሚሰብር ነገር አይጠፋም፡፡

በዚህ ምድር ላይ አይቀሬ የሆነውን የልብን መሰበር አልፎ የመሄድን ብልሃት ያዳበረ ሰው በሚልየን የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደኋላ ያስቀረን በሽታ እንዳሸነፈ ሊቆጥረው ይችላል፡፡

ሁለት ወሳኝ ነገሮች . . .

1. ከመሰበሩ በፊት ልብን መጠበቅ
ለተለያዩ ሰዎች የተለያዩ እቃዎችን በአደራ ሰጥተሃቸው በሚገባ ይዘውት መልሰውልህ ያውቁ ይሆናል፡፡ ሰዎች ግን የሌላውን ሰው ልብ በሚገባ መያዝ ስለማይችሉ፣ ልብህን ለማን እንደመትሰጥ መጠንቀቅ አስፈላጊ ነው፡፡ ልብ ቀድሞውኑ ከመሰበሩ በፊት ነው ጥንቃቄ የሚያስፈልገው፡፡ የምታምነውንና የማታምነውን ሰው በጥንቃቄ መምረጥ፣ ማንን በምን አይነት ሁኔታና በምን ያህል ጥልቀት ማመን እንደሚገባህ በተረጋጋ ሁኔታ ማጤን . . . እና የመሳሰሉትን መንገዶች መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡

ሆኖም፣ ተጠንቅቀን እንኳን ልብን የሚሰብር ነገር አይጠፋም፡፡ ስለዚህ፣ ልብ ከተሰበረ በኋላ ማድረግ ስሚገባን ነገርም በሚገባ ማሰብ አስፈላጊ ነው፡፡ ስለሆነም፣ ልብ ሲሰበር ደግሞ

2. የተሰበረውን ልባችንን ማከም
አንድ ጊዜ ልብ ከተሰበረ የጥገናው ስራ በጥንቃቄ ሊደረግ ይገባዋል፡፡ የመጀመሪያው እርምጃ አመለካከታችንን ማስተካከል ነው፡፡ አሁን ልባችንን ከሰበረው ሁኔታ ውጪ ኖረን እንደምናውቅና አሁንም ከዚያ ሁኔታ ውጪ መኖር እንደምንችል ማስብ አለብን፡፡ አምነኸውና ልብህን ሰጥተኸው አሁን ግን ከሕይወትህ ስለተለየህና ስለጎዳህ ሰው አስብ፡፡ ከዚህ በፈት ከዚህ ሰው ውጪ ሙሉ ሆነህ ኖረህ ታውቃለህ፡፡ ምንም እንኳን በመካከሉ በዚያ ሰው ላይ ልብህን ጥለህ ብትጎዳም፣ አሁን ከዚያ ሰው ውጪ ሙሉ ሰው እንደሆንክ አትርሳ፡፡

“ከእንግዲህ ወዲህ . . . በፍጹም . . .” ከሚል ከጉዳት ከሚመጣ ውሳኔ ቆጠብ በማለትና ካሳለፍነው ልምምድ የምንማረውን ትምህርት በመልቀም ወደፊት መሄድ ይገባናል እንጂ ተስፋ መቁረጥ የለብንም፡፡

የአንድ ሰው መሄድ የአለም መጨረሻ አይደለም፡፡ የአንድ ሁኔታ አለመሳካት የሕይወታችን ማብቂያ አይደለም፡፡ የአንድ ክፉ ነገር በሕይወታችን መከሰት የጉዟችን መደምደሚያ አይደለም፡፡ ሰዎችና ሁኔታዎች ሲያቆሙ፣ አንተ ግን ጉዞህን ቀጥል!!!




ማኖርን ምረጥ!
የሞት ነጋዴው ታሪክ

ከመቶ አመታት በፊት አንድ ሰው የዕለቱን ዜና ለማንበብ ጋዜጣውን ሲዘረጋ አንድ አስደንጋጭ ነገር አነበበ፡፡ በዚያ ጋዜጣ አንድ አምድ ውስጥ የራሱን ስም ተመለከተና ግራ ገባው፡፡ በእለቱ ጋዜጣው ሊዘግበው የፈለገው የሌላን ሰው ሞት ሆኖ ሳለ በስህተት ግን የእርሱን ስምና ታሪክ አስፍሮ ነበር፡፡ በርእሰ አንቀጹ ከተጻፉት ጽሑፎች መካከል እንዲህ የሚሉ ሃሳቦች ይገኙበታል - “የዳይናማይትና የቦምቡ ንጉስ . . . የሞት ነጋዴው ሞተ” ይላል፡፡ ጽሑፉ ላይ፣ “ይህ ሰው ሚሊየነር የሆነው ሰዎች እርስ በርሳቸው የሚገዳደሉበትን ነገር በመፈልሰፍና በመሸጥ ነው” ይላል፡፡

ይህ ሰው አልፍሬድ ኖቤል (Alfred Nobel) ነው - ዳይናማይትንና ሰዎች ለጦርነት የሚጠቀሙበትን የፈንጂ ንጥረ ነገሮች የፈለሰፈ የስዊድን ሳይንቲስት፡፡ የሞተው ሌላ ሰው ነው፣ ጋዜጣው ግን በስህተት የእሱን ታሪክ ነበር የጻፈው፡፡ ኖቤል ያንን ጽሑህ ካነበበ በኋላ እጅግ ደነገጠ፡፡ ለራሱ እንዲህ ሲል ነገረው፣ “ለካ ስሞት ሰዎች በዚህ ሁኔታ ነው የሚያስታውሱኝ? ህይወቴን ለመልካም ነገር በማዋል ማሳለፍ አለብኝ”፡፡ ኖቤል ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አመለካከቱ እንደተለወጠ ይነገራል (ምንጭ:- www.chabad.org);;
ኖቤል ከዚህ በመነሳት “ኖቤል ፕራይዝ” የተሰኘውን በፊዚክስ፣ በኬሚስትሪ፣ በህክምና፣ በስነጽሑፍ፣ በሰላምና በሳይንስ የላቀ ስራ ላበረከቱ ሰዎች የሚሰጠውን ሽልማት መሰረተ፡፡ ይህ ሽልማት ከተጀመረበት በፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1901 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በመቶዎች የሚቆጠር ጊዜ ሽልማት ተሰጥቷል፡፡ ኖቤል ከዚህ አለም በሞት ሲለይ በሚልየን የሚቆጠር ዶላር ለዚሁ ሽልማት እንዲውል ኑዛዜ አድርጎ ነው የሞተው፡፡

ከዚህ ዓለም ሳልፍ ሰዎች በምን እንዲያስታውሱኝ እፈልጋለሁ? ከእኔ በፊት የነበሩት ሰዎች እንዳለፉ ሁሉ፣ እኔም ነገ ማለፌ ካልቀረ ካለፍኩ በኋላ ሰዎች በምን እዲያስታውሱኝ እንደምፈልግ የመወሰኛው ጊዜ አሁን ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች በዚህ ምድር ላይ ያላቸውን ሕይወት ለእነሱ ብቻ በተመቻቸው መንገድ እስከኖሩ ድረስ ካለፉ በኋላ ሰዎች ስለእነሱ የሚያስቡት ነገር ትርጉም እንደሌለው ያስባሉ፡፡

ሌሎች ደግሞ በዚህ ምድር ላይ የኖሩት ኑሮ ለዓመታት የሚቆይን ተጽእኖ ጥሎ እንደሚያልፍ በማሰብ ጥንቃቄ የሞላውን ሕይወት ለመምራት ይጥራሉ፡፡

የሚያስገርመው እውነት፣ ሰዎች ስለእኛ የሚያስቡትን ትክክለኛውን ሃሳባቸውንና እይታቸውን በግልጽ የሚናገሩት እኛ ካለፍን በኋላ መሆኑ ነው፡፡

የምትኖረው ለምንድን ነው? ሰውን ለማጥፋት ወይስ በሕይወት ለማኖር? ሰውን ለማባላት፣ ወይስ ወደ አንድነት ለማምጣት? ሰውን ለመብላት፣ ወይስ ሰውን ለማብላት? ለዘረኝነት፣ ወይስ ዘር-ዘለል ለሆነ አንድነትና ፍቅር? በልቶና በዝብዞ ለማምለጥ፣ ወይስ ለእውነት ኖሮ ለእውነት ለመሞት? አስብበት!!!




ተማር እንጂ አትማረር!

ለጠራራ ጸሃይ የተጋለጡ ሁለት ነገሮችን አስባቸው፡፡ አንዱ በረዶ ነው፣ አንዱ ደግሞ ገና የተቦካ ሲሚንቶ፡፡ በረዶውን ጸሐዩ ሲያገኘው ያቀልጠዋል፡፡ ሲሚንቶውን ሲያገኘው ደግሞ ያጠነክረዋል፡፡ በረዶው ስለጸሐይ ማንነት ቢጠየቅ፣ “አቅላጩ” ብሎ ነው የሚጠራው፡፡ ሲሚንቶው ተመሳሳይ ጥያቄ ቢጠየቅ፣ “አጠንካሪው” ብሎ ይጠራዋል፡፡

ሁለቱም ተመሳሳይ ለሆነው የጸሐይ ባህሪይ ነው የተጋለጡት፡፡ ሆኖም፣ አንዱ የቀለጠበተን፣ ሌላው ደግሞ የጠጠረበት ምክንያት የግላቸው ማንነትና ባህሪይ ነው፡፡
የቀለጠው በረዶ አልፎ ተርፎ ሌላውን ነገር ሲያበሰብስና ሲያለሰልስ፣ የጠነከረው ሲሚንቶ ደግሞ ለተነካካው ነገር ሁሉ የጥንካሬ ምክንያት ይሆናል፡፡

በእኛም ሕይወት እውነታው ተመሳሳይ ነው፡፡ ሁለት ሰዎች ለተመሳሳይ ሁኔታ ተጋላጭ ከሆኑ በኋላ አንዱ “ሲቀልጥና ሲሟሟ” ሌላው ግን እንዲያውም ሲበረታና አልፎም ሌላውን ሲያበረታ ይታያል፡፡ ይህ የሚሆነው ልምምድን ለመልካም ለመለወጥ ካላቸው አመለካከትና ግንዛቤ የተነሳ ነው፡፡

መጎዳትህ ለተጎዱት፣ መራብህ ለተራቡት፣ መታመምህ ለታመሙት፣ መገፋትህ ለተገፉት መፍትሄን የሚሰጥን ራእይ በውስጥህ እንዲጭር የምትፈቅድ አይነት ሰው ስትሆን ከተለመደውና በየሁኔታው “ከሚቀልጠውና ከሚሟሟው” ማንነት ትወጣና ጠንክሮ አጠንካሪ ትሆናለህ፡፡ በተቃራኒው ግን፣ ማማረር፣ ተስፋ መቁረጥና ከአላማ መገታት፣ እንዲሁም ደግሞ “እኔ እንደተቸገርኩ እነሱም ይቅመሷት” የሚለው አመለካከት የጠንካሮች ልምምድ አይደለም፡፡

መከራ፣ ጠንካራ ወይም መራራ ያደርግሃል፡፡ ልክ የጸሃይ ሙቀት በረዶን ሲያቀልጠውና ሲያጠፋው፣ ሲሚንቶን ግን ሲያጠነክረውና አንድን ነገር ለመገንባት እንደሚለውጠው ማለት ነው፡፡ በመከራ የሚቀልጥና የሚጠፋ ማንነት ሳይሆን የሚጠነክርና የሚበረታ ማንነትን ለማዳበር ተግተህ አስብበት፡፡




“ለምን?” ብለህ ጠይቅ

ለመሻሻልና ለመለወጥ ከፈለክ፣ “ለምን?” ብለህ ከመጠየቅ አትረፍ!

• “አሁን የምኖረውን ኑሮ በዚህ መልኩ የምኖረው ለምንድን ነው?”
• “ገቢዬ ለምን በዚህ ብቻ ተወሰነ?”
• “አምኜ የተቀበልኩትን የሕይወቴን ሂደት ለምን ተቀበልኩት?”
• “የማደርገውን ነገር በዚህ መልኩ የማደርገው ለምንድን ነው?”
• “በሕይወቴ መሻሻል የሚችል ነገር አለ ወይ? ካለስ ለምን አላሻሽለውም? እንዴትስ ላሻሽለው እችላለሁ?”

እነዚህና እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎችን መጠየቅ ይህ ነው የማይባል የአእምሮ መነቃቃት ያመጣል፡፡ የተለመደውን የኑሮውን ሂደት “ለምን?” በማለት የማይጠይቅ ሰው በአንድ ቦታ ለመርጋት ራሱን ያዘጋጀ ሰው ነው፡፡

አንድ ሰው ለመሻሻልና ለመለወጥ አእምሮውን ሊያነቃቃና የተለመደውን የየእለት የኑሮውን ዑደት “ለምን?” ብሎ ሊጠይቅ ይገባል፡፡ ይህ ከተነቃቃ አእምሮ የሚነሳ ራስን የማሻሻልና የመለወጥ ጉዞ ባሉበት ሳይረኩ ከዛሬ ሁኔታ የተሻለ ነገር ውስጥ ለመግባት አስፈላጊውን ነገር ወደማድረግ ይወስደናል፡፡ እንዲሁ የመጣውን ሁሉ በመቀበልና በማስተናገድ በእድል ለመሻሻል ከመሞከር፣ አእምሮዬ እንዲሻሻል ማንበብ፤ የገቢዬ ምንጭ እንዲሻሻል ሙያዬንና ብቃቴን ማዳበር፣ ማሕበራዊ ኑሮዬ እንዲሻሻል ደግሞ ባህሪዬን ማጤንና ማሻሻልን ይጠይቃል፡፡

አንድን እውነታ መዘንጋት የለብኝም፣ የእኔነቴና የብቃቴ መሻሻል ዙሪያዬንና ሁኔታዎቼን ሁሉ ለመልካም የመለወጥ ብርታትና ተጽእኖ አለው፡፡ ስለዚህም፣ ማንነቴ፣ ብቃቴና ችሎታዎቼ መድረስ የሚችሉበት ደረጃ እስኪደርሱ ድረስ መጠየቅና መንቀሳቀስን አለማቆም ተገቢ ነው፡፡

አንዳንድ ዝም ብለህ ልትቀበላቸው የሚገቡህ ነገሮች የመኖራቸው እውነታ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሁሉንም ነገር ግን ዝም ብለህ በጭፍንነት አትቀበል - “ለምን?” ብለህ ጠይቅ!!!



20 last posts shown.

7 766

subscribers
Channel statistics