✝የግለ ወሲብ ሀጢያትን ለማቆም የሚረዱ አምስት መፅሐፍ ቅዱሳዊ መንገዶች✝
...ካለፈው የቀጠለ
2.የዲያቢሎስን ሀሳብ በእግዚአብሔር ሀሳብ መተካት
በስሜት ፈተና ላይ የበላይ ሆኖ ለማሸነፍ አንዱ መንገድ የስሜቱ ቀስቃሽ የሆነውን ሀሳብ ምላሽ ሳይሰጡ መመልከትና አቻ በሆነ መልካም ሀሳብ መተካት ነው፡
"ክፉን በመልካም አሸንፍ" ሮሜ 12፡21
ባለፉት ክፍሎች ግለ ወሲብ ሁልጊዜም የሚጀምረው በአዕምሮ ላይ መሆኑን አይተናል። በመሆኑም ከዚህ በኋላ ይህ ተግባር "ሀጢያት ነው ወይስ አይደለም?" ብሎ ከራስ ጋር መሟገት አስፈላጊ አይደለም። ምክንያቱም አሁን መፅሐፍ ቅዱስ ሀጢያት መሆኑን ነግሮናል። ነገር ግን አዕምሯችን እንዲሁ ሀጢያት እንደሆነ በፊትም ያውቀዋል። ለዚህም ነው ድርጊቱ ከፈፀሙት በኋላ ጭንቀት ላይ የሚጥለው... ለፀፀትም የሚዳርገው።
ዲያቢሎስ ይህንን የሀጢያት ተግባር ለማስፈፀም በመጀመርያ ወሲባዊ በሆኑ ሀሳቦች ይዋጋል። የሚቃወመው ካላገኘ አዕምሮን ይቆጣጠራል። መዋጊያ ጦሩ ብዙ ነው። ጭንቀትና ድብርት መላክ አንዱ መንገዱ ሲሆን፣ ከእግዚአብሔር ቤት የሸሹትን ወይም እግዚአብሔርን የረሱትን (ለብቸኝነት፣ ለጭንቀት፣ ለድብርት፣ ለመረበሽ፣ ለስጋት) በቀላሉ የሚጠቁትን አድኖ በመያዝ የዚህ አላማው ማስፈፀሚያ ያደርጋቸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ለወጣቱ ወሲብ ቀስቃሽ የሆኑ ፊልሞችንና ምስሎችን በማሳየት፤ ያላገቡትን ደግሞ ከዝሙት ለመራቅ በሚል የተሳሳተ ምክንያት፤ እንዲሁም ያገቡትን በእግዚአብሔር አይን ትክክል እንደሆነ በማስመሰል በትዳር አጋሮቻቸው ላይ ላለመሰልወት በሚል ምክንያት በዚህ ሀጢያት ስር ይማርካቸዋል።
እህቶችና ወንድሞች፦ ይህንን ፅሑፍ የምታነቡ በጠቅላላ...፦ የክፉ ሀሳብ ምንጭ የሀጢያት አባት የሆነው ዲያቢሎስ ነው ብለናል። ይህንን ዘወትር ማስተዋልና ማስታወስ ተገቢ ነው። ታዲያ የእሱ የሆኑት እነዚህ ክፉ ሀሳቦች በአዕምሯችን ውስጥ ሲቀሰቀሱ ለሀሳቦቹ ተግባራዊም ሆነ ስሜታዊ አፀፋ ከመመለስ ይልቅ ሀሳቦቹን በጥንቃቄ የመመልከት፤ ምንነታቸውን፣ ጉዳታቸውን፣ ወደ ተግባር ከተለወጡ በኋላ የሚያመጡትን ጭንቀትና ፀፀት፤ ወደ ተግባር ባይለወጡ የሚያስገኙትን ሰላምና እረፍት... ከተለያየ አቅጣጫ አጠቃላይ ይዘታቸውን የመመርመር... ወዲያውኑም የእግዚአብሔር በሆነ አዲስ ሀሳብ የመተካት ልምምድ ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህ መንገድ ግለ ወሲብን ጨምሮ ማንኛውንም ሀጢያት ጅምር (የተላከ...ነገር ግን ተቀባይ የሌለው) ሀሳብ ብቻ ሆኖ እንዲቀር በማድረግ የሀጢያቱን ህልውና በሒደት ሙሉ በሙሉ ማጥፋት ይቻላል። ልምምዱ ቀላል ነው። እሱም ዘወትር መፅሐፍ ቅዱስን የህይወት መመርያ ማድረግና የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈፀም ነው። የእግዚአብሔር ፈቃድ ምንድነው? ታውቁታላችሁ። የሰይጣን ያልሆነው በሙሉ የእግዚአብሔር ነው።
የዲያቢሎስን ሀሳብ በእግዚአብሔር ሀሳብ የመተካት ልምምድ ሁልጊዜ ማድረግ ለሌሎች የህይወት ችግሮቻችንም መፍትሄ ይሰጠናል። ጭንቀትንና ድብርትን ያስወግዳል፤ ከፍተኛ የሆነ ንዴትን ያበርዳል፤ ወደ እግዚአብሔር ያስጠጋል... ከብዙ ሀጢያቶች ይጠብቃል... ። ስለዚህ ይህንን ልምምድ "አሁኑኑ" መጀመር ከምንም በላይ አስፈላጊ ነው። ነገ ዛሬ አትበሉ... 'አሁን!'
...
3. ራሳችሁን መቆጣጠር ተለማመዱ
ያላገባችሁ ከሆናችሁ በአንድ ነገር እመኑ። የዛሬው ራሳችሁን የመግዛትና መስዋዕት የማድረግ ጥረታችሁ የወደፊት ህይወታችሁን በትልቅ ደስታና እርካታ እንደሚሞላው ሁልጊዜ አስቡ። ስለዚህ ከሰይጣን ሀሳብ ጋር እልህ ውስጥ ከመግባት ይልቅ እግዚአብሔር ለወደፊት ህይወታችሁ ያየላችሁን መልካም እቅድ ዘወትር ማሰብን መማር ይኖርባችኋል። በተጨማሪም ግለ ወሲብ ከጋብቻ በኋላ ያለውን ደስታችሁን ሊያበላሸው እንደሚችል ማስታወስ ተገቢ ነው። ራሳችሁን በመግዛት ሀጢያት የሆነውን ነገር ሁሉ እንደ ምናምንቴ ተጠየፉት... አጥብቃችሁ ተቃወሙት። ምክንያቱም ሀጢያትን የበለጠና የበለጠ እየተቃወማችሁትና አየራቃችሁት ስትሄዱ መዳረሻችሁ ወይም ማረፊያችሁ እግዚአብሔርና የእግዚአብሔር ሰላም ስለሚሆን ነው።
4. አስፈላጊ የሆኑ ተግባራዊ እርምጃወችን ከመፈፀም ወደ ኋላ አትበሉ
ግለ ወሲብን ለመፈፀም የምትነሳሱት በምን ሰአት ነው? ያችን ሰአት ለብቻችሁ አትሁኑ። በቤት ውስጥ ለብቻችሁ የሚትሆኑበት ሁኔታ ላይ ከሆናችሁ ከቤት ውጡና ሌሎች ነገሮችን በመስራት አሳልፉ። የእግር ጉዞ አድርጉ... ከሰወች ጋር ተቀላቀሉ... ጓደኞቻችሁን አግኙ።
ወሲብ ቀስቃሽ የሆኑ ፊልሞችና ምስሎች የግለ ወሲብ ሀሳብ ዘሮችን በአዕምሮ ላይ ለመዝራት እጅግ በጣም ፈጣኖችና ስኬታማ ናቸው። ስለዚህ አሁን እነዚህን ምስሎችና ፊልሞች ማየት አቁሙ። ምንጊዜም ቢሆን የወሲብ ሀሳቦችን በአዕምሮ ላይ የሚፈጥሩትን ማንኛውንም አይነት የምክንያት ሰንሰለቶች የምትበጣጥሱበትን ዘዴ ከማውጠንጠን መቦዘን የለባችሁም። የግለ ወሲብ ሀጢያትን ከህይወታችን እስከመጨረሻው ቆርጦ የመጣል ሒደት መንፈሳዊ ጦርነት ቢሆንም እንኳን እነዚህን ተግባራዊ እርምጃዎች ከመከወን መቆጠብ የለባችሁም።
5. በኢየሱስ ክርስቶስ አይን አሁን እናንተ እነማን እንደሆናችሁ ዘወትር አስታውሱ።
"ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤
አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።" 2ኛ ቆሮ. 5፡17
በዚህ ሀጢያት ስር የወደቃችሁ ሁላችሁም ከአሁን ጀምራችሁ በቀሪ የህይወታችሁ ዘመናት... አዲሱን ማንነታችሁንና መልካሙን መገለጫችሁን ወደ ህይወታችሁ የመሳብ ልምምዳችሁን ትጀምራላችሁ።
ይህንን ሀጢያት እስከመጨረሻው ከህይወታችሁ ለማስወገድ የምትፈልጉ ከሆነ ... በእጃችሁ ያለውን መፅሐፍ ቅዱስ ከጊዜያዊ ስሜታችሁ አብልጣችሁ ልትይዙትና ልታምኑት ይገባል። ሁልጊዜም ለራሳችሁ በየጊዜውና በየሰአታቱ "እኔ በኢየሱስ ክርስቶስ አዲስ ፍጥረት ነኝ... ከዚህ ሀጢያት አሁን ነፃ ነኝ። ከእንግዲህ ወዲህ በመንገዴ ሁሉ እግዚአብሔርን ማስደሰት ነው የምፈልገው... እንደ ፍላጎቴም ሆኖልኛል" እያላችሁ ለራሳችሁ በእምነት ውስጥ ሆናችሁ "አሁኑኑ" ድገሙት። በወረቀት ላይም ፅፋቸሁ ያዙትና ባገኛችሁት አጋጣሚ ሁሉ ዘወትር አንብቡት። ይህንን ድግምት/ፀሎት ይበልጥ ለራሳችሁ እየተናገራችሁት በሔዳችሁ ቁጥር እምነታችሁ ሳታስቡት ያድግና የአስተሳሰባችሁ አንድ አካል ሆኖ መላ አካላችሁን ይቆጣጠረዋል... ከዚያም በእግዚአብሔር ድንቅ አሰራርና ጥበብ እንዴትና መች እንደሆነ ሳታውቁት ወደ እውነታነት ይለወጣል። አዲስ ሰው ትሆናላችሁ... አዲስ ህይወት ትጀምራላችሁ። ሆኖም ግን እግዚአብሔር ጥያቄያችሁን የሚመልስበት የራሱ ጊዜ እንዳለው ታውቃላችሁና ትዕግስትን ገንዘባችሁ አድርጉ። ሁሉን ማድረግ የሚያስችል የእግዚአብሔር ሀይል ከ'ጎናችሁ' ነው።
@Orthodoxess@orthodoxess@orthodoxess