የሕይወት እምሻው ወጎች/ Hiwot Emishaw


Гео и язык канала: не указан, не указан
Категория: не указана


ሕይወት እምሻው የተወዳጆቹ ባርቾ፣ ፍቅፋቂ፣ ማታ ማታ እና ለእርቃን ሩብ ጉዳይ መፅሐፍት ደራሲ ናት። በዚህ መድረክ ወጎችን እና ልብ ወለዶችን ታቀርባለች።

Связанные каналы  |  Похожие каналы

Гео и язык канала
не указан, не указан
Категория
не указана
Статистика
Фильтр публикаций


‹‹ይመስገን በደሌ››

÷÷÷÷÷÷÷÷÷


ምሽት አስራ ሁለት ሰአት፡፡

‹‹ሰለቸኸኝ›› ብላ በድላኝም የሚያዳላላት ልቤ ላይ ተረማምዳ በሄደች በዓመቱ ተመልሳ መጣች፡፡


‹‹ናፈቅኸኝ- እንዳንተ የሚወደኝ አጣሁ›› ብላ፡፡


ያኔ እንደዋዛ ትተውኝ የሄዱ እግሮቿን እንደዋዛ ወደእኔ ስትመለስባቸው…



ካለ እሷ ያሳለፍኩትን ገሃነምን ገነት የሚያስመስል አመት አውቃ አይደለም፡፡

ምን ነካው እስክባል አብራኝ ሳትሆን ስሟን የጠራሁበትን፣
በየጎዳናውና በየአደባባዩ ያለምክንያት ስንጠራወዝ ሳላያት የተከተልኳትን፣
በናፍቆትዋ ብዛት ለለየለት እብደት አምስት ጉዳይ የደረስኩበትን ጊዜ አታውቀውም፡፡

የእሷን ጠረን ያጣሁበት አመት አስራሁለቱም ወር ክረምት ሆኖ መውጣቱን አታውቅም፡፡


የጉዳቴን ጥልቀት ሳትጠይቅ፣ የስብራቴን ልክ ሳትረዳ…


ዛሬ፣በምሽት ልክ ላንሰራራ ስንጠራራ፣ ልድን ዳር ዳር ስል ‹‹ናፈቅከኝ›› ብላ መጣች እንጂ ለዚህ ሁሉ ግድ የላትም፡፡



ይሄው በሬ ላይ ቆማ ስትቅለሰለስ፣ በሽታዬ አገርሽቶብኝ፣ ጨክኜ ልመልሳት ጉልበት ሳጣ፣ ያለ ይሉኝታ ገፍተር አድርጋኝ ቤቴ ከመግባቷ፣



የገረጣ ፊቴን አይታ ሳትደነግጥ፣ የከሳ ገላዬን ተመልክታ ሳትሳቀቅ፣

‹‹እንዴት ከርምህ?›› እንኳን ሳትለኝ፣


አልጋው ላይ እንደ ኳስ ወርውራኝ ከተጠመጠመችብኝ በኋላ፣
እንክትክት አድርጋው ሄዳ ወጌሻ አጥቶ የከረመ ልቤን ትንፋሽ ባሸነፋቸው ቃላቶችዋ ታባብለዋለች፤
በእጦቷ የተጎዳ ሰውነቴን ተጠግታ ክፉኛ ፣ በአደገኛ ሁኔታ ትተሻሸኛለች፡፡




ካልበረታሁ፣ በዚህ ሰበበኛ ገላዋ ጎትታ ለአንድ አመት ወደነበርኩበት ሲኦል ልትመልሰኝ ነው፡፡
እምቢ ካላልኩ፣ የዚህች ሴት ገላዋ ረጅም ገመድ ነው፡፡

የምወደው፤ የምሞትለት ግን ደግሞ ወደ መቀመቅ የሚያወርደኝ ረጅም ገመድ፡፡


‹‹በናትሽ ተይ›› አልኳት ጉልበቴን ሰብስቤ- ስማኝ ትንፋሽ ሊያጥረኝ ሲቃጣ፡፡
‹‹ለምን….አልናፈቅኩህም?›› አለችኝ መሳምና መተሻሸቷን ጨምራ፡፡


ከአልጋው ላይ ተስፈንጥሬ ተነሳሁና ብቸኛዋ የቤቴ ወንበር- በርጩማ ላይ- ቁጭ አልኩና ዝም ብዬ እያየኋት፣
‹‹ለዚህ አይደለም የናፈቅሽኝ›› አልኳት፡፡


ያልኳት እንዳልገባት የገባኝ ግን ቸኩላ እንዲህ ስትለኝ ነበር፡፡

‹‹እሺ ምንም አናደርግም…ና ወደ አልጋው…ስለናፈቅከኝ ብቻ አንተ ጋ…እዚህ ልደር››

ጠባቡና ያልተነጠፈ አልጋዬ ላይ በደልዳላና የሚያስጎመጅ ግማሽ እርቃን ሰውነቷ ስትቅበጠበጥበት አንደበትዋ ብቻ ሳይሆን መላ ሰውነቷ የሚለማመጠኝ መሰለኝ፡፡


ና…ና….

ዲ-ያ-ቢ-ሎ-ስ፡፡

‹‹አይሆንም…እደሪ ብልስ የት ትተኛለሽ?›› አልኩ የገዛ ቤቴን እንደ አዲስ እየቃኘሁ፡፡


ከአልጋዬ በስተቀር የሚተኛበት ነገር የለም፡፡


ከሷ ጋር አልጋዬን መጋራት ደግሞ ገደል አፋፍ ላይ እንደመቆም ነው፡፡
ጫፌን ነካ ካደረገችኝ ተምዘግዝጌ መውደቄ ነው፡፡
እንደዚያ ለማድረግ ምኔን መንካት እንዳለባት ደግሞ አሳምራ ታውቃለች፡፡

‹‹በመሃል ትራስ እናደርጋለን…ብዙ ትራስ›› አለችኝ አሁንም ቅብጥብጥ ሰውነቷን መቆጣጠር ባቃታት መልኩ እየሰራት፡፡

በእኔና እሷ የተነፋፈቀ ገላ መሃከል እንኳን የትራስ ክምር ቀይባህር ቢዘረጋም ለውጥ የለውም፡፡
ዋናው ቁምነገር ግን እሱ አይደለም፡፡



ለአንድ አመት የከፈልኩት ከባድ ዋጋ በአፍታ ደስታ እንዲሰረዝ አልፈልግም፡፡
ያ ሁሉ እሷን የመርሳት ስቃዬን እሷን በማግኘት ድል እንዲመታ አልፈቅድም፡፡


ለእኔ ይሄንን ገላ አቅፎ መተኛት ማለት….


በስንት መከራ ሲጋራ አቁሞ ከሱስ የተላቀቀ ሰው ከሲጋራ ሱስ መላቀቁን በማስመልከት ሲጋራ ቢያጨስ ማለት ነው፡፡ ምን አይነት እብደት ነው…?


ልክ ይሄን ሳስብ…
ነቃሁ፡፡ በረታሁ፡፡

ከበርጩማዬ ሳልነሳ እንድትሄድ ጠየቅኳት፡፡
በአፏ ሳይሆን አይኖቿ፣ በዳሌዋ፣ በጭኖቿ፣ በጡቶቿ እምቢ አለችኝ፡፡


ያን ጊዜ የናፍቆቷ አይነት ተለይቶ ተገለጠልኝ፡፡


መክሳት መጎሳቆሌን እያየች አንዴት ነህ ሳትለኝ የእሷው ገመምተኛ የሆነ ገላዬን ማቀፍ የፈለገችው ናፍቆትዋ ምን አይነት ቢሆን እንደሆነ ገባኝ፡፡

ጭካኔዋ፡፡ ራስ ወዳድነቷ፡፡



ይሄን ሳውቅ …
ቅድም ያባበለኝ መቅበጥበጥዋ፣ ቅድም ያማለለኝ ገላዋ ወጥመድ ሆኖ ታየኝ፡፡

ያኔ ይበልጥ በረታሁና ከመጠየቅ አልፌ እንድትሄድ አዘዝኳት፡፡
እምቢ ብላ ስትሞላፈጥ ገፍትሬ ማስወጣት ሲቀረኝ ገፍቼ አስወጣኋትና በሬን ቆለፍኩ፡፡

ልክ ያኔ …

ከሄደች በሃዘን ጭጋግ ታፍኖ የከረመው ቤቴ በምሽት ከየት መጣ ባልኩት ብርሃን ሲጥለቀለቅ ፣
አመት ሙሉ ተርበው ሲጠብቋት የነበሩት አይኖቼ በማገገሜ የደስታ እምባ ሲያቀርሩ ተሰማኝና


‹‹አሁን አገገምኩ፡፡ እንኳንም ተመልሳ ምንም እንዳልጎደለብኝ አሳየችኝ…›› አልኩ፡፡


አሁን…


‹‹እንዳንተ የሚወደኝ ሰው አጣሁ›› ብላ የምትመለስ ሴት ሳትሆን፣
‹‹እንዳንተ የምወደው ሰው የለም›› ብላ አብራኝ የምቆይ ሴት እንደምትገባኝ ስለገባኝ፡፡


‹‹ለመቁረጥ በመታደሌ- ይመስገን በደሌ›› እያለ የዘፈነው ማን ነበር!?


"ቁርጥ"

========

ያኔ በፍቅር ብን ሲሉ እሱ ገና ለጋ  ወጣት ሳለ፣ የአስራ አምስት አመት ታላቁ ነበረች፡፡



ለቁጥር የሚያዳግቱ ምሽቶችን እጆቻቸውን አቆላልፈው በጎዳና ላይ በመንሸራሸር አሳልፈዋል፡፡
ስንቱን ወሬ አፍ ለአፍ ገጥመው አውርተውታል፤ በስንቱ ነገር አውካክተዋል፡፡
ዓለም ከተፈጠረች አንስቶ ፍቅረኞች ያደረጉትን ሁሉ፣  የሚያደርጉት ነገር ሁሉ አድርገዋል፡፡



ስትስቅ መስመር እያወጣ እድሜዋን የሚያጋልጥ ብዙ ያየ ፊቷን ከእሱ የልጅነት ድምቡሽቡሽ ገጽታ ጋር እያስተያዩ አንገቶቻቸው እስኪጣመሙ ዞር ብለው ከሚገላምጡዋቸው እልፍ አይኖች፣ 
በሽሙጥ ከሚጣመሙ አፎች ፣
ለወሬ ከሰሉ ምላሶች መዋደዳቸውን ልትሸሽግ ከመድከሟ ውጪ ፍቅራቸው እንከን አልነበረውም፡፡




ፍቅር ከጀመሩ ሁለተኛ ዓመታቸውን ባከበሩ ማግስት ግን ቻው እንኳን ሳትለው በድንገት ከአይኑ ተሰወረች፡፡


እልም ብላ ጠፋች፡፡


ቆይቶ ቆይቶ አቻዬ ያለችውን ሰው እንዳገባች በወሬ ወሬ ሰማ፡፡

ባሏ የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ነው ሲሉም ሰምቷል፡፡
በሚወዱት መከዳትን የማያውቀው መንፈሱ ተሰብሮ፣ ሰባራ ልቡን ይዞ ለብዙ ጊዜ፣ በየሄደበት፣ ላገኘው ሰው ስሟን እያነሰ ረገማት፡፡

‹‹ ሴትን ያመነ…›› እያለ፡፡


---
ከአስራ ስድስት አመታት በኋላ፣ በአንዱ ተራ አመሻሽ ዓለም ሲኒማ ጋር፣ እሷ ከምትሄድበት ከተቃራኒው አቅጣጫ ቦርሳውን መስቀለኛ አንግቶ ጠደፍ ጠደፍ እያለ ሲመጣ  ፊት ለፊት አየችው፡፡ 



‹‹ጌታ እየሱስ ድረስልኝ! …ብሩክ በሃይሉ…እውነት አንተ ነህ?›› ብላ ጮኸች፡፡


ስሙን ሲሰማ፣ድንገት ቆመ፡፡

ለአፍታ ፊቷን ቢመረምራትም ማንነቷ ጠፋበት፡፡



ክፉኛ አረጀችበት፡፡


በለጋነቱ እንደ ኳስ የተንደባለለበት ለግላጋ ገላዋ ገረጀፈበት፡፡

‹‹እንዴ! ወይንሸት…? በስመአብ! ከየት ተገኘሽ?”


ጠጋ ብላ ፊቷን ለመሳም ስትሰጠው በጉንጩ ፈንታ እጁን ሰጣት፡፡


ጨበጠችው፡፡



“አዲሳባ መጣሁ እኮ! ” አለችው አፈር ብላ.፡፡ “እዚህ ነው የምኖረው”
“ተይ እንጂ!” ፊቱ ላይ የትህትና ፈገግቶ ሰርቶ መለሰላት፤ ከዚያ ግን ወዲያው በአይኖቹ መሃከል በመኮሳተር የተፈጠረ ጉብታ እየታየ፡፡



“ወይ ብሩክ! ሁሌ አስብሃለሁ…የት ገብቶ ይሆን እያልኩ››
‹‹አይቲ ነው የምሰራው አሁን›› መለሰላት፡፡ ‹‹ክፍያ የሚባል ካምፓኒ ነው የምሰራው፡፡ ለገሃር አካባቢ››
‹‹ትዳርስ…?አገባህ?››
‹‹አዎ፡፡ ሁለት ልጆች አሉኝ››
‹‹ጎሽ…ጎበዝ››



በአዲስ መልክ ተምቦርቅቆ የተሰራውና ተቀራርበው የቆሙበት ጎዳና በሰዎች መሞላት ጀመረ፡፡
ከስራ ወደቤታቸው የሚሄዱ ሰዎች በግራም በቀኝም እያለፏቸው ይሄዳሉ፡፡
የጥቅምት ብርድ ምሽቱን ተገን አድርጎ አጥንት መሰርሰር ጀምሯል፡፡



‹‹አንቺስ…ባለቤትሽ ደህና ነው?›› ጠየቃት፡፡
‹‹ደህና ነው፡፡ ሶስት ልጆች አሉን›› መለሰችለት፡፡
‹‹እዚህ የከፈተው…ማለቴ የከፈትነው ትምህርት ቤት ነው የምሰራው አሁን…ምናልባት ታውቀው ይሆናል …ችልድረንስ ፓራዳይዝ?››

ትኩር ብሎ እያያት ነበር፡፡


‹‹እንዴ እሱማ በጣም ፌመስ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ክፍያውም ከባድ ነው ደግሞ…በጣም…እ…በጣም ተለወጥሽ…›› አላት፡፡


ተለወጥሽ ሲላት ሊላት የፈለገው አረጀሽ፣ ጨረጨስሽ ነው፡፡


እሷም ገብቷታል፡፡

እንዲህ ሲላት፣ አጠገቡ ቆማ፣ በሰው ጎርፍ መሃል ሆና ብቸኝነት ተሰማት፤ በጫጫታ እና ውክቢያ መሃከል አውቶቢስ ወይ አውሮፕላን ሳትሳፈር ወደ ድሮ ተመለሰች፡፡



ያን ጊዜ ፣ አዋሳ ሲገናኙም የስንት ታላቁ ነበረች፡፡
ግን በአንጻራዊ ሁኔታ ያኔ ወጣት ነበረች፡፡



ፊቷ ጥርት ሰውነቷ ጥብቅ ያለ ነበር፡፡
እሱ የአንደኛ አመት የዩኒቨርስቲው ተማሪ፣ እሷ ደግሞ ስንቱን ያየች የዩኒቨርስቲው አስተዳደር ክፍል ተቀጣሪ፡፡



አሁን ግን…ወጣትነቷና ውበቷ ተያይዘው፣ ላይመለሱ ጥለዋት ሄደዋል፡፡ ብሩክ ግን ወጣት ነው፡፡ አሁንም ወጣት፡፡



‹‹አያት አካባቢ ነው ቤታችን›› አለችው ባይጠይቃትም በመሃከላቸው የተሰነቀረው ዝምታ አስጨንቋት፡፡
‹‹እስቲ ና እና ጠይቀኝ…ጠይቀን…››
‹‹ደስ ይለኛል›› መለሰላት፡፡
‹‹አንቺና ባልሽ ደግሞ እኛ ቤት ትመጣላችሁ…የእኛም ቤት ሰሚት ነው…ቅርብ ለቅርብ ነን…ሉሲንም በዚያው ትተዋወቂያታለሽ››


ምሽቱ ደንገዝገዝና ቀዝቀዝ ሲል በመሃላቸው የነበረው ስሜትም ያንኑ መሰለ፡፡


‹‹ እኔም ደስ ይለኛል›› አለችው ታግላ፡፡
‹‹ልጆቼንም ታያቸዋለሽ፡፡እንዴት አሪፍ ልጆች መሰሉሽ!››



በድንገት የጎዳናው አዳዲስ የመንገድ መብራቶች ሁሉ በአንድነት ፏ ብለው በሩ፡፡

የአስራ ስድስት አመት የእድሜ ሰምበርን የተሸከመው ፊቷ ለብሩክ ፈራጅ አይኖች ይበልጥ ተመቻችቶ ሲሰጥ ተሰማት፡፡



ያበሩትን እጆች በሆዷ ረገመች፡፡



‹‹ይሄኔ ስንቱ ቤት እንጀራ መጋገሪያ መብራት የለም…ስንቱ ቤት ጨለማ ወርሶታል..ልጆች የቤት ስራ መስራት አልቻሉም እነሱ እዚህ እኔ ፊት ላይ ሚሊዮን ፓውዛ ያበራሉ…መብራት ሃይሎች…እርጉሞች…›› አለች አሁንም በሆዷ፡፡


‹‹በል ልሂድ›› አለች በድንገት፡፡

‹‹መኪና ደርቤ ነው ያቆምኩት፡፡ ይሄኔ ልጁ እየተበሳጨብኝ ነው….ስልክ እንኳን አልሰጠሁትም ፤ ቶሎ እመጣለሁ ብዬ››
‹‹እሺ በይ ቻው›› የቅድሙን እጁን ዘረጋላት፡፡



‹‹ታዲያ መቼ…›› ብላ ከመጀመሯ ግን እጇን ጥሎ ጉዞ ጀመረ፡፡

ቅድም ቦግ ያሉት መብራቶች አንዴ ብልጭ አንዴ ፍዝዝ ማለት ጀመሩ፡፡
ቃላት ለማውጣት አፏን ከፈተች ግን እምቢ አላት፡፡
‹‹ቻ…ው›› አለች ቆይታ፡፡ ጮክ ብላ፡፡


ብሩክ አልዞረም፡፡ መንገዱን አቋርጦ ወደ ሚሊኒየም አዳራሽ የሚወስደውን ጎዳና ይዞ በፍጥነት መራመድ ጀመረ፡፡

የተሻገረውን ሁለት መንገዶች ብዙ መኪኖች፣ እሷ ቆማ የቀረችበትን የእግረኛ ጎዳና ደግሞ ብዙ አላፊና አግዳሚ ከዚህም ከዚያም ሲሞላው በመሃላቸው ያለው ርቀት ሰፋ፡፡


ብሩክ ከአይኗ ተሰወረ፡፡



ያን ጊዜ ‹‹እንገናኛለን›› ተባባሉ እንጂ አድራሻ እንዳልተለዋወጡ፣ ስልኳን እንዳልሰጠችው አስታወሰች፡፡

ከዚያ ደግሞ የበኩር ልጇ፣
አስራ አምስት አመት የሞላው ጎረምሳ ልጇ፣ ቁርጥ እሱን እንደሚመስል ለብሩክ እንዳልነገረችው አስታወሰች፡፡

2.2k 1 13 22 89

Видео недоступно для предпросмотра
Смотреть в Telegram
ሽሙንሙን እሁድ !


አበባ ለሚስቴ
====


‹‹እስቲ እንደ ወንዶቹ አበባ ግዛልኝ!›› ፤

የሚስቴ የሁልጊዜ ንጭንጭ ነው፡፡
‹‹ምናለ አንድ ቀን እንኳን እቅፍ አበባ ገዝተህልኝ የሴት ወግ ብታሳየኝ?›› ፤

የዘወትር ንትርኳ ነው፡፡


ለሚስት አበባ የመግዛት ጥቅሙ ገብቶኝ አያውቅም፡፡
አበባ በየፓርኩ፣ በየመንገዱ፣ በየሱቁ አለ፡፡

በነጻ የሚታይን፣ ደፈር ሲሉም እንደዋዛ የሚቀጠፍን ነገር በብር ገዝቶ፣ አሳሽጎ እንቺ ማለት ምንድነው ትርጉሙ?

በአበባ አሳብባ በተነጫነጨች ቁጥር እንዲህ እላታለሁ፡፡


‹‹ባል ለሚስቱ አበባ ካልሰጠ አይወዳትም ያለሽ ማነው…? ማነው ይሄንን የፈረንጅ የውሸት የፍቅር መግለጫ ለትዳር ዋና ጉዳይ ነው ብሎ ነው ያሳመነሽ…? ደግሞ እኮ  ምኑም እኛን አይመስልም፡፡ ምኑም ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ አይሸትም፡፡ እወድሻለሁ፡፡ እንከባከብሻለሁ፡፡ ደም እስክተፋ የምሰራው ላንቺና ለልጆቼ ነው፡፡ አበባ ከፈለግሽ ራስሽ ገዝተሸ ቫዝ ሙሉ ውሃ ውስጥ ዘፍዝፊ››


አንተ ደግሞ አበዛኸው ምናምን የምትሉና ለእሷ ቲፎዞ የምትገቡ እንዳላችሁ ይገባኛል (አብሶ ሴቶች)፡፡ 

እንዲህ የምላት  ለክፋትና (ወይ ለገንዘቤ ሰሰቼ) አይደለም፡፡
ሚስቴ እኔ ናት፡፡
በራስ ላይ ይከፋል?
ለራስ ይሰሰታል?
ከራስ ይቆጠባል?

አባቴ ለእናቴ አንድም ቀን አበባ ገዝቶላት አያውቀም፡፡ ግን አርባ አንድ ዓመት በትዳር ኖረዋል፤ ብዙውን ጊዜ ደስ ብሏቸው፡፡

ሚስቴ ግን እንዲህ እንዲህ ስላት ይባስ ታኮርፋለች፡፡

‹‹አንተ በቃ ካልመሰለህ ግትር ነህ፡፡ የምልህ አይገባህም!›› ብላ ትወቅሰኛለች፡፡
እውነትም በአበባ ጉዳይ የምትለው ነገር ገብቶኝ አያውቅም፡፡

እስከዛሬ፡፡

ከዚህ ሁሉ የእምቢተኝነት አመታት በኋላ ዛሬ ሲያቅፉት የሚያንገዳግድ የአበባ እቅፍ ገዛሁላት፡፡

ረጃጅም፣ እምቡጥና ለአይን የሚያሳሱ ቀያይ ጽጌረዳ አበቦችን እና አጃቢዎቻቸውን፡፡

አጃቢዎቹ አረንጓዴ፣ ሰፊና ቀጭን ቅጠሎች፣ ነጫጭ ነካ ሲያደርጓቸው የሚቦኑ አበቦች ናቸው፡፡
በውድ ዋጋ ነው የገዛኋቸው- ከተማው ውስጥ አለ የተባለ ቦታ ሄጄ፡፡


የሸጠችልኝ ሴትዮ በትክክል ውሃ ውስጥ ከተቀመጡ ሁለት ሳምንት፣ ትንሽ ጨው ከተጨመረባቸው ደግሞ ከዚያም በላይ ሊሰነብቱ እንደሚችሉ ነገረችኝ፡፡

ለገበያዋ ስትል ደልላኝና አጋና ይሆናል ግን ስለእሱ ግድ የለኝም፡፡

ዋናው ነገር ሚስቴ ትውደዳቸው፡፡

በወደደቻቸው፡፡


አስራ ስምንቱን ረጃጅምና ውብ ቀይ የጽጌረዳ አበቦችን (በትዳር የኖርንባቸውን አስራ ስምንት አመታት በማስመልከት) ከነብዙ አጃቢዎቻቸው (ሶስት ልጆቻችን እና ብዙ ደስታችንን እንዲወክሉ)  አድርጌ ካዘጋጀሁ በኋላ ሚስቴ ጋር ስደርስ፣


‹‹እመቤቴ፣ በግትርነቴ እንዲህ የምትወጂውን ነገር ለማድረግ ይሄን ያህል ዘመን ስለፈጀሁ ይቅርታ አድርጊልኝ፡፡ ለካስ የፍቅር ሌላው ትርጉሙ ሌላኛው የሚወደውን ነገር ለራስ ስሜት ባይሰጥ እንኳን ያለ ጥያቄ ማድረግ ነው? ገና አሁን ገባኝ፡፡ እህስ…አበቦቹ እንዴት ናቸው…? ወደድሻቸው? ›› አልኩ በዝግታ መቃብሯ ላይ እያስቀመጥኳቸው፡፡

2k 0 44 33 142

‹‹አእምሮሽም እንደ መልክሽ ያምር ዘንድ››


--
ከአሮጌ ተራ መጽሐፍትን ስገዛ የሚያስደስተኝ ነገር ብዙ ነው፡፡



የጠፋ፣ ተስፋ ቆርጨ የተውኩትንና የሚቆጨኝን መጽሐፍ ማግኘቱ፣
ሽሮ ገጾቹን እየገለጥኩና በአቧራው እያስነጠስኩ ማንበቡ፣
በሙቅና እግዜር ብቻ በሚያውቀው ሌላ ነገር የተጣበቁ ገጾችን እያላቀቁ ከገጽ ወደ ገጽ መሄዱ፣
በልጅነት አእምሮዬ ላይ ተነቅሰው የቀሩ እንደ ስጋ ዘመድ የምወዳቸው ገጸ ባህሪያት ጊዜ ሳይለውጣቸው ተከርቸም ሰንብተው ማግኘቱ…

ምኑ ቅጡ!


ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ሁሌም የሚያስደስተኝና የሚያዝናናኝ፣ አልፎ አልፎም የሚያስቅና የሚያሳዝነኝ ግን በመጽሐፍቱ ላይ የማገኛቸው የማላውቃቸው ሰዎች የእጅ ፅሁፍ ማስታወሻዎች ናቸው፡፡


ከእነዚህ ማስታወሻዎች አንዳንዶቹ የቤተሰብና የግለሰብ ታሪክን የመዘገቡና ከዚያ ቤተሰብ ሊወጡ የማይገቡ ትዘታዎችን የያዙ ስለሆኑ፣ ይሄኔ ይሄ መጽሐፍ ጠፍቶባቸው በቁጭት የሚንገበገቡ አባትና እናት፣ ወራሽ ልጆችና የልጅ ልጆች አሉ ብዬ ሳስብ ሃዘን ይሰማኛል፡፡


ምናልባት የቤቱ ዱርዬ ልጅ ለሲጋራ ወይ ጫት መግዣ በርካሽ ሸጦት ይሆን?
አንዱ ዘመድ ነኝ ባይ ተውሶ አቅልጦት ይሆን?
ባለቤቶቹ ሲሞቱ ከሌላ ንብረታቸው ጋር ለየልጆቻቸው ተከፋፍሎ ሲያበቃ ሰነባብቶ ከእጃቸው ወጥቶ ይሆን ? እያልኩ ከዚያ ቤተሰብ እጅ የወጣበትን መንገዶች አስባለሁ፡፡



ለምሳሌ አንዱ እጄ የገባ ከገበያም ከአይንም የጠፋ ውድ የታሪክ መጽሐፍ የመጀመሪያ ገፅ ላይ፣ ርእሱን በድጋሚ ከያዘው ከውስጥ የሽፋን ገፁ ስር እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፡፡


‹‹ለምሳሳልህ ልጄ ዓረፈአይኔ ተክላይ፣ አድገህ ታሪክ ከማንበብ ባሻገር ታሪክ ሰሪ እንደምትሆን አልጠራጠርም፡፡ አባትህ ተክላይ ገ/መድህን›› ይላል፡፡


ዓረፈአይኔ ዛሬ የት ይሆን…?
እንደ አባቱ ምኞት ታሪክ ሰርቶ ይሆን…?


ይህንን የመሰለ ታላቅ የአባት መልእክት ያዘለ መጽሐፉስ እንዴት ከእጁ ወጣ…?

በማልመልሳቸው ጥያቄዎች እጨናነቃለሁ፡፡


አንዳንዴ ደግሞ መጽሐፉን የገዙበትን አጋጣሚ ቁልጭ አድርገው መዝግበው የሚያስቀምጡ አንባቢዎች ይገጥሙኛል፡፡
ለምሳሌ ‹‹የደራሲ ፍዳ›› የተባለው በአበባው ተክሌ የተተረጎመ መፅሐፍ መታሰቢያ ስር እንዲህ የሚል ፅሁፍ ሰፍሯል፡፡

‹‹ከ6-10/6/87 ዓ.ም. በአዋሳ የከፍተኛ ካድሬዎች ስብሰባን ምክንያት በማድረግ የተሸመተች መፅሐፍ››
(ዝልግልግ ፊርማና ዓ.ም )


አንድ ጊዜ የተገጠመችኝ ግን አሳቀችም አስደነገጠችኝም፡፡

‹‹ለምወድሽ ሙሉጌጥ፣ አእምሮሽም እንደመልክሽ ያምር ዘንድ አንብቢያት!!! ጉግሳ ኃ/ሚካኤል›› ትላለች፡፡


አሁን እስቲ ሙሉጌጥ በአቶ ጉግሳ ተደነቀች/ተበረታታች ወይስ ተሰደበች?



እንዳልኳችሁ፣ ከአሮጌ ተራ መጽሐፍትን ስገዛ የሚያስደስተኝ ነገር ብዙ ነው፡፡

የሰዎችን ታረክና ትዝታ በራሳቸው የእጅ ጽሁፍ ማንበብ ግን ከሁሉ የላቀው ደስታዬ ነው፡፡

2.9k 0 10 13 153

‹‹ትንንሽ ደስታዎች››
(በገብረክርስቶስ ደስታ ‹‹የሚያፅናኑ›› ላይ ተመስርቶ የተጻፈ)
-------



ሆድ ሲብስ 'ሚያባብሉ፣
ከዓለም ጣጣ- ለአፍታም ቢሆን 'ሚከልሉ

በፈተና 'ሚያጸኑ፣
በግርግር 'ሚያረጋጉ፣
ከኑሮ ውክቢያ- ለአንዲት ቅፅበት 'ሚታደጉ…

ነገር ሲመር 'ሚያጣፍጡ…




እነሆ ትንንሽ ደስታዎች…
ሽርፍራፊ እርካታዎች…
ብጥስጣሽ እፎይታዎች





የፍቅር ውጥን
የሚያጓጓ፣  ልብ 'ሚያግል

ቀጭን ደሞዝ…
ለአምስት ቀናት- እንደንጉስ 'ሚያንቀባርር

ሚጢጢ ቤት
እንደልብህ 'ምትሆንባት
ኡፎይ ብለህ 'ምታርፍባት


አዲስ ልብስ
ፕ-ስ-ስ-ስ!


አዲስ ጫማ
ላረማመድ የሚስማማ…


ቆንጆ ጭልፋ፣ ማንቆርቆሪያ
ብርጭቆ፣ ድስት፣ አዲስ ቂጣ መጋገሪያ


የተቆላ ቡና፣ ፈልቶ ሲወርድ፣ ሲጨስ እጣን
ትኩስ ቄጠማ ተጎዝጉዞ ያለው ጠረን



ሻይ በስኳር ከአምባሻ ጋር
ምሳ ሽሮ- እራት ምስር


ኮልታፋ ህጻን ነፍስ የማያውቅ
ያለ ሰበብ ስቆ 'ሚያስቅ


ሳያስቡት በድንገት
የሚደውል ወዳጅ ዘመድ
እንዴት ነህ ብቻ ለማለት…



ውብ የራስጌ መብራት

መጽሐፍት!  መጽሐፍት! መጽሐፍት!


ዘፈን! ዘፈን! ዘፈን!
የጂጂ፣ የቴዎድሮስ፣ የአስቴር፣ የመሐሙድ፣
የፍቅርአዲስ እና የጥላሁንዘፈን!


መታቀፍ መታቀፍ…!
በሚያፈቅሩት እቅፍ እንደሞቁ እንቅልፍ

እንቅልፍ! እንቅልፍ! እንቅልፍ!



ሆድ ሲብስ 'ሚያባብሉ፣
ከዓለም ጣጣ ለአፍታም ቢሆን  'ሚከልሉ

በፈተና የሚያጸኑ፣
በግርግር 'ሚያረጋጉ
ከኑሮ ውክቢያ ለአንዲት ቅፅበት 'ሚታደጉ…

ነገር ሲመር ሚያጣፍጡ…




እነሆ ትንንሽ ደስታዎች…
ሽርፍራፊ እርካታዎች…
ብጥስጣሽ እፎይታዎች

3k 0 23 19 116

‹‹ አስማተኛ››
((((+++++)))))



ልጅ እያለች፣ እናቷ አንድም ቀን አሻንጉሊት ገዝታላት አታውቅም፡፡


በዚህ የተነሳ ፣ የጎረቤት ልጆችና የጓደኞቿን መጫወቻ አሻንጉሊቶች በቅናት ስታይ ውላ በምሬት ስታለቅስ ያመሸችባቸው ቀናት ጥቂት አልነበሩም፡፡ 

እናቷ የቡና አጣቢ ደሞዟን ለአንድ ወር ስትለጥጥ አራት የሙት ልጆቿን ሆድ በመሙላትና አሻንጉሊት በመግዛት መካከል መምረጥ ነበረባት፡፡


ረሃብ እረፍት አይሰጥም፣ አሁንም አምጣ አምጣ፣ ነዝናዛ እና አትርሱኝ ባይ ነው፡፡  አሻንጉሊት ማጣት ግን ለጊዜው ቢያስለቅስም ቆይቶ ይዘነጋል፡፡
ስለዚህ ልጆችዋን ማብላት መረጠች፡፡


በተረፈው ብልኃቷ ደግሞ ልጇ በጓደኞቿ መጫወቻ አሻንጉሊቶች እንድትደሰት ትገፋፋት ነበር፡፡

‹‹ሂጂ በሚሚ አሻንጉሊት ተጫወቺ›› ትላታለች ቀስ ብላ፡፡ ‹‹እናቷ ገላዋን እያጠበቻት ነው››
‹‹ማክዳ አጠገብ ቁጭ በይና እስቲ አንዱን መጫወቻሽን አውሺኝ በያት፡፡ ብዙ እኮ ነው ያላት›› እያለች፡፡


ልጅቱ ግን የልጆቻቸውን ሆድ ሞልተውም አሻንጉሊትም በሚገዙ ወላጆች ትቀናለች፡፡
እንዲህ ያሉት ወላጆች፣ ልዩ ፍጡር፣ አስማተኛ ይመስሏታል፡፡

የአሻንጉሊት ለማኝ መሆኗ ውስጥ ውስጥዋን ይበላው፣

በተለይ ሚሚና ማክዳ ገና ስትመጣ እንዳዩ አሻንጉሊቶቻቸውን ሲደብቁ ወይ ሰብስበው ሲያቅፉ፣ ፊታቸውን አጥቁረው ሲጠብቋት በእናቷ ታፍርና ትናደድ ነበር፡፡ 

ብዙውን ጊዜ፣ በስንት ምልጃና ልምምጥ ቢሰጧትም
ቶሎ አምጪው፣
አቆሸሽው፣
የራስሽን አስገዢ እያሉ ክፉኛ ሲያሸማቅቋት እምባዋን እያዘራች ወደቤቷ ትመለሳለች።

‹‹እናትሽ የማትገዛልሽ?›› ሲሏት መልሷ ሁሌም አንድ ነው፡፡
‹‹የእኔ እናት እንደናንተ እናት አስማተኛ አይደለችም››
‹‹አባትሽስ?››
‹‹አባት የለኝም››


ግራ ተጋብተው፣ ‹‹ለመሆኑ ግን አስማተኛ ምንድነው?›› ሲሏት
‹‹ሁሉንም ነገር ማድረግ የሚችል ሰው›› ትላቸዋለች፤ ሲባል የሰማችውን፡፡



በተለይ በማክዳ ባርቢ ዶል ፍቅር ተጠምዳ ነበር፡፡ የሚያብለጨልጭ ሮዝ ቀሚሷ፣ ረጅምና ዧ ብሎ የሚወርደው ወርቃማ ፀጉሯ! ባርቢ እሷ በዓለም ላይ የምትመኘውን ነገር ሁሉ የያዘች አሻንጉሊት ነበረች፡፡ የእሷ ፀጉር ከርዳዳና አጭር ነው፤ ልብሶቿ ደግሞ ቀዳዳ የማያጣቸው ሰልቫጅ፡፡


,,,




ከዓመታት በኋላ አድጋና ባለሥራ ሆና ከእናቷ ቁጡና ፈራጅ አይኖች ለመራቅ የራሷን ቤት ስትከራይ ከድስትና መጥበሻ፣ ከስኒና ኩባያ፣ ከሰሃንና ወጥ ማውጫ በፊት ቤቷን በምን ሞላች?

በአሻንጉሊቶች፡፡

ከአራት በአራት አንድ ክፍሏ አንደኛው ግድግዳ በእንጨት መደርደሪያ ተይዟል፡፡
ለመጽሐፍት አይደለም- ለአሻንጉሊቶች፡፡

ተጠንቅቃ ነበር የደረደረቻቸው፡፡ ትንሽ፣ መሃከለኛ፣ ትልቅ፣ በጣም ትልቅ፡፡ ሶፋዋ አናት ላይ የሶስት አመት ወፍራም ልጅ የሚያህል ሮዝ ቴዲ ቤር፣ ቴሌቪዥኗ ላይ እግሮቹ ፈርከክ ያሉ ትልቅ ቀጭኔ፡፡


እናቷ ልትጎበኛት በመጣች ቁጥር  የአሻንጉሊት ክምሯን ‹‹የሕፃን ስራ›› ብላ ታጣጥለው ነበር፡፡


‹‹ሽሮ በርበሬ ከእኔ እያስቋጠርሽ አንቺ በገንዘብሽ ተጫወቺ›› እያለች፡፡


በእናቷ ንግግርና ተግሳጽ ሳትከፋ ትስቃለች።
እናቷ እነዚህ አሻንጉሊቶች ምን እንደሚወክሉና ምኗን እንደሚያክሙ ሊገባት አይችልም፡፡


ባይገባትም ግድ የላትም፡፡ ስለዚህ እንዲህ ነው እንዲያ ነው ሳትል የእናቷን የዘወትር ቁጣ ሳቅ ብላ ታልፈዋለች፡፡


ዛሬ ላይ በእናቷ አይኖች በአሻንጉሊት የምትጫወት የህጻን ትልቅ ብትሆንም፣


በዚህ ሁሉ መጫወቻ የምታባብላት አልቃሻ ህጻን ውስጧ እንዳለች ብታውቅም፣  የኑሮን ነገር አድጋ ስታየው፣ ኖራ ስትመረምረው፣ ጠልቆ የገባት አንድ እውነት ግን አለ፡፡
ባደገችበት ሰፊ ሰፈር ብቸኛዋ አስማተኛ የእሷ እናት ነበረች፡፡

3k 0 11 4 168

ዓሳውን አንሁን!
----——————-


ልጅ ሆኜ…




ክፍለሃገር ዘመዶቻችን ለመጠየቅ ስንሄድ ደስታዬን አልችለውም ነበር፡፡



ምን ያደርጋል!

ገና ጥቂት ቀናትን እንዳደርን እማዬ፣

‹‹ተነሱ ወደ ቤታችን እንሂድ›› ብላ ታዋክበናለች፡፡



‹‹እማ ምናለ ግን ትንሽ ቀን ብንቆይ?›› ስንላት ሁሌ የምትለን ነገር ነበር፤

‹‹ልጆች ዓሳና እንግዳ ከሶስት ቀን በኋላ መሽተት ይጀምራል››


ምን ማለቷ እንደሆነ አይገባኝም ነበር፡፡



አሁን አሁን ፣ በዚህ እድሜዬ፣

በዓለም ላይ ካለ ነገር ሁሉ አስበልጨ ዋጋ የምሰጠው ብቻዬን ለማሳልፈው ጊዜ ነው፡፡

ሰላሜና ‹‹የእኔ ብቻ›› የምላትን ጊዜዬ በዋጋ አትተመንም ፡፡


እድሜ ሲቆጥር ጊዜን ከማይወዱት ሰው ጋር ወይም በማይወዱት ነገር ላይ ማባከን ክፉኛ ያሳቅቃል።




ጠባያችሁ ከእኔ የሚገጥም ካላችሁ፣

እንግዳ ቤታችሁ ከመጣ በኋላ፣ ብዙ ሰአት ስንጫወቱ አሳልፋችሁ ስታበቁ ልትሸኙት ስትፈልጉ ምን ታደርጋላችሁ?

እኔ፣ ከሁሉ በፊት

አብሬው ውዬ ‹‹አሁን ብንለያይ ጥሩ ነው›› የሚሉ በትህትና የተለወሱ ምልክቶቼን የማያስተውል ሰው ሲገጥመኝ እኔም ለሌላ ሰው እንዲህ አይነት ‹‹በይ አሁን ንኪው›› ምልክቶች ቶሎ የማይገቡኝ ገገማ እንዳልሆንኩ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡


የእኔን ያህል እድሜ ከሰው ጋር ያጠፋ ሰው ይሄ ይሄ ነገር ይጠፋዋል ማለት ግን ዘበት ይመስለኛል፡፡ ምልክቶቹ አሻሚ አይደሉማ!



እርግጥ ነው፤ ባህላችን ዛሬም ድረስ እንዲህ ባለው ጉዳይ ቀጥተኝነትና ግልብነትን ስለማይወድ ዙሪያ ጥምጥም መሄዱ ግድ ነው፡፡ መቼም እንደ ፈረንጅ ብድግ ብላችሁ ‹‹በል አሁን ብቻዬን መሆን እፈልጋለሁ፤ ሄድልኝ›› አትሉ ነገር፡፡

ቢሆንም የሰውየውን ሁኔታ ላስተዋለው ሰው መልእክቱ ግልጽ ነው፡፡


ለምሳሌ፣
ብዙ ጊዜ የሚገጥመኝን ነገር ላጫውታችሁ፡፡



እኔ ቤት ነን፡፡

መሽቷል- ከምሽቱ ሶስት ሰአት ሊሞላ ትንሽ ነው የቀረው፡፡

ከእንግዳዬ ጋር ግማሹን ቀን አብረን በደስታ አሳልፈናል፡፡


እንግዲህ አራተኛው የእድሜዬ አንጓ ላይ እንደመሆኔ (ስለ አራተኛው አንጓ ብዙ የማጫውታችሁ አለ ሌላ ጊዜ) በሃያዎቹ ጊዜ የነበረኝ ጉልበት የለም፡፡




ብቻዬን ብሆን በዚህ ሰአት አልጋዬ ውስጥ ነበርኩ፤ ሶስተኛውን የህልም እርከን ለመንካት እየቀረብኩ፡፡

ድክም ብሎኛል ስለዚህ እንዲህ ብዬ ለዘብተኛ ምልክት አቀብላለሁ፡፡



መጀመሪያ… በቀስታ አዛጋለሁ፡፡
እንግዳዬ አይገባውም፡፡


ቀጥዬ ደግሜ አዛጋለሁ፣ አሁን ግን ጫን ብዬ፡፡


አሁንም አልገባውም፡፡



ከዚያ፣ ‹‹በስማም መሸ አይደል…ስንት ሰአት ሆነ?›› ብዬ እጠይቃለሁ- የቅድሟን ለዘበተኛ ማዛጋት አከል አድርጌ፡፡


እንግዳዬ ስልኩን አይቶ፣ ‹‹ገና ሶስት ሰአት እኮ ነው›› ካለኝ ወጥመድ ውስጥ እንደገባሁ ይሰማኛል፡፡


ገና…? ገና ሶስት ሰአት እኮ ነው?


በጨዋነት ከሌላ ፍጡር ጋር የመጫወት ባትሪዬ ሙጥጥ ብሎ አልቋልና እሰጋለሁ፡፡



እንግዳዬ አሁንም ነገሬ ሳይገባው ባለበት ከቀጠለ ባንድነት አዛጋለሁ፣ እንጠራራለሁ፣ አፍ አውጥቼ ‹‹ደከመኝ›› እላለሁ፡፡



ከዚያ ደግሞ -
‹‹ነገ በጠዋት ስራ ገቢ ነኝ…ገላን ሄጄ የታመመች አክስቴን እጠይቃለሁ፣ ከጥርስ ሃኪም ጋር ቀጠሮ አለኝ›› አይነት ነገር እደራርባለሁ፡፡

አንዱ ከወጥመዴ እንዲያወጣኝ፡፡

እንግዳዬ ግን አሁንም የምወደው ሶፋ ላይ ተመቻችቶ ተቅምጦልኛል፡፡ ይሄን ጊዜ ተጨማሪ ሰራ እንደሚጠብቀኝ አውቅና ወደ ምእራፍ ሁለት የማጥቃት ዘመቻዬ እገባለሁ፡፡



‹‹እህስ…አሁን ታዲያ ምን እናድርግ?›› ብዬ እጠይቀዋለሁ፡፡
ከመመለሱ በፊት ግን፣

‹‹ብቻዬን ብሆን ይሄኔ ተኝቼ ህልም እያየሁ ነበር›› እላለሁ፡፡

ይሄን ጊዜ ተነስቶ በመሰናበት ፈንታ፣

‹‹ ለምን ኔትፍሊክስ ላይ ምንትስ ፊልምን አናይም?›› ብሎ በቆይታችን ላይ አንድ ሰአት ተኩል ለመጨመር ከሞከረ ተስፋ ወደ መቁረጡ እቀርብና የመጨረሻዋ ካርታዬን እመዛለሁ፡፡


‹‹የእኛ ሰፈር እኮ ሩቅ ስለሆነ በጣም ከመሸ ራይድ አይገኝም…አሳሰብከኝ እኮ›› እላለሁ፡፡
‹‹ግዴለም የማውቀው ባለ ታክሲ አለ›› ምናምን ብሎ ከመለሰልኝ ግን…ያኔ አይን አይኑን እያየሁት ወደ ጸሎት እገባለሁ፡፡
ሌላ ምን ላደርግ እችላለሁ?


እንዳልኳችሁ
ልጅ ሆኜ ከአዲሳባ ውጪ ያሉ ዘመዶቻችን ለመጠየቅ ሄደን እማዬን ትንሽ እንቆይ ብለን ስንለምናት እንዲህ ትለን ነበር፤

‹‹ልጆች ዓሳና እንግዳ ከሶስት ቀን በኋላ መሽተት ይጀምራል››


ሁላችንም ያንን ዓሳ ከመሆን ይሰውረን፡፡

2.8k 0 16 10 121

ጀምበር- አንቺም?


ቅዳሜ ለታ ‹‹በመላው ሃገሪቱ የሃይል አቅርቦት ተቋረጧል›› ሲባል፣
‹‹ሁሉም ቦታ ከሆነ ይሁን›› አልን፡፡ (ሁሌም በጨለማ ያለ ሰው አይዞህ እኔም እንዳንተው ጨለማ ውስጥ ነኝ መባል ስለሚያፅናናውና ሁሉም ቦታ ሲሆን ቶሎ ይሰራል በሚል ቀቢፀ ተስፋ)

አመሻሹን ‹‹አሁን በአብዛኛው ቦታ ሃይል ተመልሷል›› ሲባል አሁንም ሃይላቸው ካልተመለሰላቸው መደመራችን ቢከነክነንም የእኛም ይመጣል ብለን ተፅናንተን ሻማችንን እፍ ብለን አጥፍተን አደርን፡፡

በነጋታው እሁድ ‹‹ዛሬ ሁሉም ቦታ መብራት መጥቷል›› ቢባልም እኛ ጋር ባለመምጣቱ ኩም ብለን ንጭንጭ ጀመርን፡፡

ምሬታችንን ‹‹ይሰሙ ከሆነ ›› ብለን በዚህም በዚያም ተናገርን፡፡
ፌስቡክ ላይ አቤት አልን፡፡ በስልክ አለቃቀስን፡፡ በቴሌግራም ገጻቸው ላይ ተቆጣን፡፡

‹‹የእናንተ መስመር ተሰርቆ ነው፡፡
የእናንተ መስመር ለስራ ሲቆፈር ወድሞ ነው፡፡
የእናንተ መስመር እንዲህ ሆኖ ነው›› የሚሉ እርስ በእርስ የሚጣለዙ መልሶች ተሰጥቶን፣ ‹‹አሁን ግን እየተሰራ ነው፤ እስከማታ ታገሱና ጠብቁ ተባልን››
ምን ምርጫ አለን!

ማጉረምረማችንን በተስፋ ለውሰን ጠበቅን፡፡

ሳይመጣ መሸ፣ ነጋ፤ ሰኞ ሆነ፡፡
አሁንም መብራት የለም፡፡

አሁንም ደወልን፡፡
ጻፍን፡፡
ኡኡ አልን፡፡

‹‹ዛሬ ይሰራል፣ እየተረባረብን ነው ዛሬ በጨለማ አታድሩም›› በሚል ደለሉን፡፡


ግን…

ገምታችኋል!

በጨለማ አደርን፡፡

ጭራሽ ሳይመጣ ነጋ፡፡

ማክሰኞ ሆነ፡፡

ተስፋ የቆረጥነውና አንጀታችን እርር ብሎ ሳይረፍድ ቻርጅ የሚደረጉ ነገሮች ሁሉ ተሸክመን ስደት የወጣንና በየቢሮው ያለን ሰዎች ቤት ካሉ ሰዎች ተደውሎ ‹‹መጣች›› ተባልን፡፡


ኡፎይ ብለን ሳንጨረስ እነዚያው ሰዎች መልሰው ደውለው ደግሞ ሄደች አሉን፡፡

አንገታችንን ደፍተን ወደቤት ስንገባና ስንቀመጥ ደግሞ ‹‹ብልጭ እንቁልልጭ›› አለች፡፡
አሁንም ደስ ብሎን ሳናበቃ ሰላሳ ደቂቃ ሳትቆይ ድረግም፡፡

እና….

እኛ ሰፈር እስካሁን፣ ለአራት ቀናት መብራት የለም፡፡

እነሆ….
የገና ጀምበር ደግሞ ለመብራት ሃይል ተደርባ በሚመስል ሁኔታ ገና አስራ ሁለት ሰአት ሳይሞላ ቤቷ ለመግባት እየሮጠች ነው፡፡

ከየመስኮቶቻቸው አንገቶቻቸውን በቁዘማ አስግገው የሚያዩዋት የሰፈሬ ሰዎች በትዝብት
‹‹ጀምበር- አንቺም?›› የሚሏት ይመስላሉ፡፡


‹‹የኤፍሬም ሸክም››
÷÷÷÷÷÷



እሁድ ረፋዱ ላይ፡፡

አዲሶቹ ሙሽሮች እንደተለመደው በጣም አርፍደው ከአልጋቸው ተነሱ፡፡

በምሳ ሰአት ቁርስ ከመብላት ቀጥታ ምሳ እንብላ ብለው እንደተስማሙ ሚስት ምን ልስራ ስትል፣

‹‹ስጋ ይኑርበት እንጂ ምንም ስሪ›› ብሎ ሳም አደረጋትና ወደ ኩሽና ገባች፡፡


እሷ ምሳ ለመስራት ስትንደፋደፍ ቸርነት ውሃ በብርጭቆ ያዘና ወደ አፓርታማቸው በረንዳ ወጣ፡፡ ቆሞ ውሃውን ሲጎነጭ ከእነሱ በላይ፣ ሁለተኛ ፎቅ ላይ የሚኖረው ጎረቤታቸው አቶ ኤፍሬም መአት ነገር ከመኪናው እያወረደ አየው፡፡

‹‹እንዴት አደርክ ኤፍሬም…ምንድነው ይሄ ሁሉ ነገር በጠዋት?›› አለው ካለበት ዝቅ ብሎ እያየው፡፡
‹‹እንዴት አደርክ አልከኝ…? አይ ቸርነት…እንዴት ዋልክ አይሻልም…? ገና መነሳትህ ነው እንዴ…ስድስት ሰአት ሞላ እኮ!›› አለው ኤፍሬም ቀና ብሎ እያየው፡፡

ቸርነት ሳቅ አለና፣ ‹‹ብቻህን ብዙ እቃ እያወረድክ ነው፡፡ ወርጄ ላግዝህ እንዴ?›› አለው፡፡
‹‹ከቻልክ ደስ ይለኛል›› አለ ኤፍሬም ሳይግደረደር፡፡



ቸርነት ሚስቱን መጣሁ ብሎ ኤፍሬም ወዳለበት ቦታ በፍጥነት ወረደ፡፡


ደርሶ እቃውን ማውረድና ማስተካከል ሲረዳው ኤፍሬም ሃያ ኪሎ የሚሆነውን በማዳበሪያ ያለ ዱቄት እንዳይወድቅ መሬቱ ላይ እያመቻቸ ወሬ ጀመረ፡፡



‹‹እይ እንግዲህ ልዩነት! አንተ ሚስትህን አቅፈህ እንቅልፍህን ስትለጥጥ አርፍደህ ገና መነሳትህ ነው፡፡ እኔ በሌሊት ተነስቼ ከነቤተሰቤ ቤተክርስትያን ሄድኩ፤ ከዚያ ተመልሰን ቁርስ በላን፡፡ ከዚያ ሚስቴ ስትነተርከኝ ስለነበር ልገላገል ብዬ ኤሌክትሪሻኑን ከቤቱ ድረስ ይዤ መጥቼ የተበላሸ ምጣዷን አሰራሁላት፣ ከዚያ ወጥቼ ከካራ ስጋ፣ ከጎሮ ደግሞ ይሄን ሁሉ የወር አስቤዛ ገዝቼና ተሸክሜ መጣሁ…አሁን ደግሞ ገብቼ ልጆቹን የቤት ስራ አሰራለሁ››

በራሱ ንግግር የተደነቀ ይመስል ጭንቅላቱን በመገረም እየነቀነቀ፡፡


ቸርነት የይሉኝታ ፈገግታ ፈገግ አለና ሁኔታዬ ገብቶት ይህንን ወሬ በቀየረ የሚል በሚመስል የልምምጥ ሁኔታ ሲያየው ኤፍሬም ግን ቀጠለ፡፡


‹‹ጎረምሳው….ጊዜህ ነው….እንግዲህ እኛ ድሮ ያጣጠምነውን ሕይወት ተደሰትበት፡፡ ሳያልፍብህ…ሳያልቅብህ›› አለ በድንችና ቲማቲም የተሞላውን ኩርቱ ፌስታል እንደ ማስረጃ እየጠቆመ፡፡

ቸርነት አሁንም በምናለ ቢተወኝ ፈገግ አለ፡፡



‹‹ቀልዴን አይደለም፡፡ በደንብ ስማኝ፡፡ አሁን አንተ ያለህበት ጊዜ…እስከፈለግክ ሰአት የመተኛት…ባሰኘህ ሰአት መውጣትና መግባት…ደቂቃ አይቆይም…የአፍታ ደስታ ነው፡፡ ከዚያ ትክክለኛው የትዳር ጊዜ ይመጣል፡፡ ሙሽርነትህ ሲያልቅ የእሾህ አሜኬላህን ትደፋለህ፡፡ ሌሊት በልጅ ለቅሶ ተቀስቅሶ መነሳቱ፣ በየቀኑ እነሱ ከተነሱ እሁድ የለ…ቅዳሜ የለ አብሮ መነሳቱ…ሁሌ የሚበላሽ የተሰበረ ነገር አይጠፋም እሱን ጠግን ወይ አስጠግን ተብሎ መነትረኩ…ወጣህ ገባህ እየተባልክ ጭቅጭቁ…የተሰበረ መስታወት፣ የተበላሸ ምጣድ፣ የተቃጠለ አምፖል፣ የቆሸሸ ዳይፐር… ሕይወትህ በሙሉ ይሄ ይሆናል፡፡ ውጊያ ነው ቸርነት፡፡ የማያልቅና መቼም የማታሸንፍበት፣ እስቲ አንዴ ልረፍና ትንፋሽ ልሰብስብ የማትልበት ሩጫ፡፡ አሁን አንተ ሚስት አለህ እንጂ ላጤ ነህ…ኑሮህ ስኳር ስኳር የሚልህ ለዚህ ነው…ግን ይሄ ማታለያ ጊዜ ነው…እሷን አሳይተው ያስገቡንና የጭቃ ጅራፋቸውን ያመጡታላ….ስለዚህ አሁን ያለችህን ጊዜ አጣጥማት ልልህ ነው››

ቸርነት ሳቁ ሊያመልጠው ዳዳው፡፡

በሆዱ፣ ኤፍሬም ደግሞ ምንስ ቢሆን ምነው ሁሉን ነገር እንዲህ አካበደው እያለ፡፡


ምሬት ከተለወሰው ጨዋታና ከኤፍሬም ጋር ተለያይቶ ወደ አፓርታማው ሲመለስ ሚስቱ ትሪ ሙሉ የስጋ ፍርፍር አቅርባ እየጠበቀችው ነበር፡፡
‹‹ምን ሆነህ ነው እንደዚህ የቆየኸው?›› ብላ ጠየቀችው፡፡
‹‹ ለካስ ኤፍሬም ብዙ የሚያራግፈው ሸክም ነበረው…ለእዚያ ነው የቆየሁት›› ብሎ መለሰላት፡፡

2.8k 0 17 8 104

‹‹ስንገናኝ››
(ክፍል ሁለት)
----



የመጀመሪያ ቀን ስንገናኝ ያለኝን ከቁምነገር ፅፌ የቡናውን ካልከፈልኩ አልኩ፡፡


ከለከለኝ፡፡


‹‹በሚቀጥለው ስንገናኝ ትከፍያለሽ›› አለኝ፡፡


ድጋሚ ስንገናኝ አሁንም ለቡናው እኔ ካልከፈልኩ ብዬ አቧራ አስነሳሁ፡፡ እምቢ አለኝ፡፡


‹‹በሚቀጥለው ስንገናኝ ትከፍያለሽ›› ብሎ፡፡




ከዚህ በኋላ ፣ ለአንድ አመት ከስምንት ወር ለቡና ስንገናኝ፣ አብረን ምሳ ስንበላ፣ እራት ስንጋራ፣ ወይን ስንጎነጭ ያቺን ስልክ ያስደወለበትን የቡና ግብዣ አስመልክተን መቃለድ ቋሚ እኔና እሱ ብቻ የምናውቀው፣ ሁልጊዜ የሚያስደስተን፣ ሁልጊዜ እንደ አዲስ የሚያጃጅለን ቀልድ ሆኖ ቆይቶ፣ ስንት ሺህ ጊዜ ‹‹በሚቀጥለው ስንገናኝ ትከፍያለሽ ›› እያለ ግብዣዬን ሳይቀበለኝ ፍቅር አድርተን፣ ተጫጭተን ተጋባን፡፡




ታክሲ ላይ ያገኘሁት መልከ-ቀና ብስል ወጣት ከማስኮረፍ በስተቀር አምርሮ ሳያስከፋኝ፣ ጠባዩን እንደ ሸሚዞቹ ሳይለዋውጥብኝ፣ ስደሰት እንደልቤ የምስቅበት ቤት፣ ስከፋ ተደግፌ የማለቅስበት ትከሻ ሰጥቶኝ፤ ደስ ብሎን መኖር ጀመርን፡፡



----


ምን ያደረጋል! ዓለም ጨካኝ ናት፡፡ ዓለም ቆሻሻ ናት፡፡

‹‹እነዚህ ሰዎች ተዋደዋል፡፡ እሰቲ ትንሽ ጊዜ ይኑሩ፣ ትንሽ ጊዜ ይፈንጥዙ፤ ልተዋቸው›› ብላ አትራራም፡፡

የሰው ልጅ ደግሞ ሲደሰት ይዘናጋል፤ ሲሞላለት ሁሉን ይረሳል፡፡
የመከፋትና የሃዘን እንጂ የደስታና የተድላ ፣ የፌሽታ ጊዜ የሚያልፍ አይመስለውም፡፡



መደሰቴ መከፋት መኖሩን እንድዘነጋ አዘናግቶኝ፣  የሞላልኝ የጎደለብኝን አስረስቶኝ፣
ሳቄ ከእምባ ሩቅ ነሽ ብሎ አታሎኝ፣ ሃሳቤ ባረፈበት፣ ልቤ በተደላደለበት ሰአት..



ክፉ ቀን አሳብሮ መጣብኝ፡፡
ጃንጥላዬ የት እንዳለ ሳላውቅ በረዶ ዘነበብኝ፡፡




በተጋባን በሁለተኛ ዐመቱ ያንን ሁሉ ውበትና ደግነቱን ይዞ …ባሌ በመኪና አደጋ ሞተብኝ፡፡


----


ይሄው አሁን…

ድምፄ እስኪያልቅ አልቅሼ አፈር ባለበስኩት ሰልስት፣ 

ሰዉ ሁሉ ‹‹አትሂጂ›› ብሎ ቢያከላክለኝም ፈንጠር ብለው ከቆሙ አጃቢዎች ጋር መጥቼ፣



‹‹ አልፈልግም…እዛው ሁኑ…አትጠጉኝ..ባሌን ብቻዬን ላውራው….ብቻችንን ተዉን››  ብዬ መቃብሩ አጠገብ ለብቻዬ ኩምትር ብዬ ከተቀመጥኩ በኋላ  ጮህ ብዬ እንዲህ ብዬ እያወራሁት አነባሁ፤





‹‹ሶፊ፤ ሆድዬ….ተመቸህ…ለመድከው…. ? እኔማ ገና በሶስት ቀኔ ካላንተ መኖር እንደማልችል ቁርጤን አወቅኩት…አቅቶኛል ሶፊዬ…በደመነፍስ ነው ያለሁት….

……አለች ይሉኛል እንጂ እኔም እዚህ ካንተ ጋር ተቀብሬያለሁ… አንተ ካመለጥከኝ ወዲህ….እስትንፋስ እንጂ ሕይወት…..ቀልብ የለኝም እኮ  ሆድዬ…….ገና ካሁኑ ሁሉ ነገር ተማታብኝ….አረ እንዴት አባቴ  ነው አንተ የሌለህባት ዓለም ውስጥ የምኖረው…እንዴት ሶፊዬ….እንዴት ነው አጠገቤ አለመኖርህን የምለምደው…እንዴት…….?  ብቻ እንጃ…በሆዴ ብዙ አለ….አልጨቅጭቅህ አሁን….ሌላ ሌላውን ደግሞ በሚቀጥለው ስንገናኝ እነግርሃለሁ እሺ ሶፊዬ….በሚቀጥለው ስንገናኝ….››




በለቅሶዬ መሃል ከሩቅ በጭንቀት የሚያዩኝ ቤተሰቦቼና ጓደኞቼ፣  ‹‹በቃ ለየላት›› እያሉ ሲያንሾካሹኩ ይሰማኛል፡፡




ይለይልኛ፤ ምን ችግር አለው?

3.3k 0 9 25 151

‹‹ስንገናኝ››
------
ጨልሟል፡፡

ከአርባ ደቂቃ በላይ የተሰለፍኩለት ታክሲ ደራርቦ አጭቆን ሲያበቃ ጉዞ ጀመርን፡፡

ኡፎይ፡፡

ይሁን፤ ዋናው መሄዳችን ነው፡፡ በዚህ አያያዝ መንገድ ቢዘጋጋ እንኳን ሁለት ሰዐት ሳይሞላ እደርሳለሁ፡፡

ጠዋት ስራ ረፍዶብኝ ስርበተበት ስልኬን ቤት ረስቼ ወጣሁ፡፡ 
ከዚህ በላይ ከመሸ ሆደ ባሻዋ እናቴን ለማረጋጋት ለመደወል አልችልም፡፡ ይሄ ነው ያስጨነቀኝ፡፡

አይ እድሌ!


ገና ትንሽ ፈቀቅ ከማለታችን ቀጥ አልን፡፡



ዐይኔ ውስጥ የገባው ከፊታችን ያለው መንገድ በሙሉ በቆሙ መኪናዎችና ትእግስት አጥተው ጡሩምባቸውን በሚያምባርቁ ሹፌሮች ተሞልቷል፡፡
የተቀመጥኩት የመጨረሻው ወንበር ጥግ ላይ ነው፡፡ መስኮቱን ተደግፌ፡፡ ሶስት ሰዎች አጠገቤ ቢቀመጡም ለአራታችንም ቅጥነት ምስጋና ይግባውና እምብዛም አልተጣበብንም፡፡



የመንገዱን ሁኔታ ስመለከት ሳላስበው ቃል አውጥቼ- ‹‹ኤጭ›› ብዬ፣ በረጅሙ ተንፍሼ ኖሯል፡፡  እስካሁን ያላስተዋልኩት ከእኔ ጎን የተቀመጠና በቅላቱ የሶርያ ስደተኛ የመሰለ መልከ መልካም ወጣት፤

‹‹ምነው በሰላም?›› አለኝ በዐይኖቹ ፈተሽ እያደረገኝ፡፡
‹‹ ውይ ይቅርታ…ለራሴ ማውራቴ ነበር›› ብዬ መለስኩለት አፈር ብዬ፡፡
‹‹ምን ችግር አለው…በሰላም ነው ግን?›› አለኝ፡፡
‹‹ሰላም ነው እሱስ…መንገዱን አይቼ ነው…ስለመሸ…እናቴ እንዳትጨነቅ…››
‹‹መንገዱማ ምን ችግር አለው የለመድነው ነው… ይልቅ ለእናትሽ ብትደውይ ይሻልሻል››

ብዙ ጊዜ እንደሚያውቀኝ አይነት ነው አወራሩ፡፡


‹‹እህ…እደውል ነበር ግን ስልክ…ስልኬን ቤት ትቼ ነው የወጣሁት…እሷ ደግሞ መንገድ እንደሚዘጋም እያወቀች ትጨነቃለች…ለእዛ ነው …››

ምንም ሳይለኝ ስልኩን አውጥቶ በአይኖቼ ልከተለው ባልቻልኩት ፍጥነት የመክፈቻ ቁጥሮቹን አስገባና፣
‹‹ታዲያ ምን ችግር አለው…? ደውይላቸዋ!›› ብሎ አቀበለኝ፡፡

ይሄ ልጅ ‹‹ታዲያ ምን ችግር አለው›› ብሎ ነው እንዴ አፉን የፈታው?

በነገሩ ተገርሜ ባላበቃም እናቴን አስጨንቃለሁ ከሚለው ጭንቀት መገላገል ስለፈለግኩ ሳልግደረደር ተቀብዬው ለእናቴ ደወልኩና ወሬዬን አጣድፌ ስሰጠው፣

‹‹ምነው ቸኮልሽ…ቀስ ብለሽ ብታናግሪያቸው ምን ችግር አለው?››

አሁን አልቻልኩም፡፡ በሃይል ሳቅሁ፡፡

‹‹ምነው?›› አለኝ ያለ ምንም የቅያሜና የድንጋጤ ስሜት፡፡
የዋህ ይመስላል፡፡


‹‹አይ…እንደው ቢገርመኝ ነው…ይታወቅሃል ግን?›› አልኩት
‹‹ምኑ?››
‹‹ስንት ጊዜ ምን ችግር አለው እንዳልከኝ…?››

አብሮኝ ሳቀ፡፡


እኔም አብሬው ስቄ ስናበቃ፤
‹‹ለምዶብኝ ነው… …ይልቅ ግን…በእማዬ ስልክ ደውዬ ከማስበላሽ ስልክሽን ብትሰጪኝ ምን ችግር አለው…?›› ሲለኝ ድጋሚ ሳቅኩ፡፡

የሆነ አሁን አሁን በየመንገዱ የማይገኝ የመንፈስ ንጽህና፣ ጠጋ በይው ጠጋ በይው እያለ የሚገፋፋ አንዳች ነገር ነበረው፡፡

‹‹ለምን?›› አልኩት እንዳልገባው፡፡
‹‹ እንዴ…ስልክ የደወልሽበትን ክፍያ እንደትሰጪኝ ነዋ››
‹‹ስልክ ነው እንጂ ያልያዝኩት ብርማ አለኝ..›› ወደ ትልቁ ቦርሳዬ እንደሚገባ ሰው እየሰራኝ፡፡


ሳቀ፡፡ ሳቅኩ፡፡

‹‹ክፍያው በብር አይደለም››
‹‹እናስ ታዲያ በምንድነው?››
‹‹ቡና እወዳለሁ፡፡ ቡና ትጋብዢኛለሽ››

የስልክ ቁጥሬን ሰጠሁት፡፡

(ይቀጥላል)

(ክፍል ሁለት ነገ በዚሁ ሰዓት)

2.9k 0 8 17 117

ምን ዋጋ አለው?
______--------______

ቢሮው ሰፊ፣ ምቹና ቄንጠኛ ነው፡፡

መጽሐፍት መጽሐፍት፣ ውድ ሽቶ ውድ ሽቶ ይሸታል፡፡


ሙሉ ግድግዳውን ይዞ የተሰራው ረጅምና ሰፊ የመፅሐፍት መደርደሪያ ላይ በአማርኛ፣ በእንግሊዝኛና በፈረንሳይኛ የተጻፉ መጽሐፍት ተገጥግጠዋል፡፡


አብዛኞቹ ሕግ ነክ ናቸው፡፡


ስሙን የያዙት ብዙ የምስክር ወረቀቶች ወፋፍራም ጥቁርና ወርቃማ ከፈፍ ባላቸው ፍሬሞች ተደርገው ከመደርደሪያው በቀረው ግድግዳ ላይ ተኮልኩለዋል፡፡

የሐርቫርድ ዩኒቨርስቲ የሕግ ዶክትሬቱ መሐል ላይ፣ ከእሱ በስተቀኝና በስተግራ ደግሞ ከአውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ከአፍሪካ ሕብረት፣ ከተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት የተሰጡት ታላላቅ የምስክር ወረቀቶች ይገኛሉ፡፡

አብላጫዎቹ የተለያዩ ግጭቶች ለመፍታት በማሸማገል ያደረጋቸውን ፍሬያማ ጥረቶች የሚያወድሱ ናቸው፡፡ አንደኛው ግን ከሁሉ ጎልቶ ይታያል፤ ‹‹የኢትዮጵያን ህጋዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተደረገው የናይል ቤዚን ድርድር ሃገርዎን ወክለው ላደረጉት ጉልህ አስተዋፅኦ የተሰጠ ›› ይላል፡፡


በምስክር ወረቀቶቹ መሃከል ደግሞ ፎቶግራፎች ይገኛሉ፡፡


ከቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ጋር በፈገግታ ሲጨባበጥ፣ ጆርጅ ደብሊው ቡሽ አጠገብ ቆሞ፣ የቢቢሲው ጆናታን ዲምቢልቢ በመራው ፓናል ውይይት ላይ ማይክራፎን ይዞ ሲናገር የሚያሳዩ አሉበት፡፡


ለአይን የሚለሰልሰው ምቹና ባለጎማ የቆዳ ወንበሩ ላይ እንደተቀመጠ ዓይኖቹ የኤደን እና ሳሙኤል ፎቶግራፍ ላይ አረፈ፡፡

ተቃቅፈው ነው የተነሱት ነው፡፡

እዚህ ፎቶ ላይ ኤደን ሰባት፣ ሳሙኤል አራት አመታቸው ነበር፡፡ የኤደን መስቃላ ቁጥርጥር ጸጉር፤ የሳሙኤል ጥርስ የበዛበት የሚያሳሳ ሳቅ፡፡ ጉንጮቻቸው ተነካክተው፡፡


አሁን ትልቅ ሰው ናቸው፡፡ ኤደን ሰላሳ ሁለት አለፋት፣ ሳሙኤል ሃያ ሰባት አመት ሞልቶታል፡፡

በዓይነስጋ ካያቸው አመታት ተቆጥረዋል፡፡

እርግጥ ነው ፤ በስልክ ያወራሉ፣ አልፎ አልፎ ቪዲዮ ተጨምሮ፡፡

ግን ወሬያቸው አጭር፣ ምቾት የሚነሳና በማይተዋወቁ ሰዎች መሃከል የሚከናወን አይነት ነው፡፡
ሃይ አባባ እንዴት ነህ?
እኔ ደህና ነኝ፡፡ ጤናህ እንዴት ነው…?
ስራስ እንዴት ነው…?
Is Addis still peaceful?
We are good here.

ሁሌም እንዲህ ነው፤ ጥያቄዎቹ አንድ አይነት፣ መሃል የሚሰነጉት ጸጥታዎች አስጨናቂ፡፡ ልጆቹ (እሱ ቢጠይቅም ) ከዚህ ያለፈ ነገር አያጫውቱትም፡፡
እንደ ቤተሰብ፣ እንደአባትና ልጅ የሆድ የሆድን ዘረግፎ ለመጫወት ያለ መገናኘት ያለፉት ብዙ አመታት አይፈቅዱም፡፡ ድልድዩ እንዳይጠገን ሆኖ ተሰብሯል፡፡ ርቀቱ ክፉኛ ሰፍቷል፡፡

ዛሬ አፍሪካና አሜሪካን ከለያያቸው አትላንቲክ ውቂያኖስ ይልቅ የሚሰፋውና የሚጠልቀው ከልጆቹ ጋር ያለው ርቀት እንዴት እንደተፈጠረ ለማስታወስ ሞከረ፡፡

ከሚስቱ ጋር ሲፋታ በፊትም የነበረው ክፍተታቸው ሰፍቶ፣ አለመጣጣማቸው አይሎ ነገሮች በፍጥነት ጎመዘዙ፡፡
‹‹አንተ ያለህበት ሃገር አልኖርም›› ብላ ወደ አሜሪካ ለመሄድ ስትቆርጥ ልጆቹንም እንደ ሻንጣዎቿ አንጠልጥላ ሄደች፡፡

የሚያምር ቤተሰቡን መበተን ለመርሳት፣ የአንድ ፍሬ ልጆቹን ካይኖቹ መራቅ ለመቋቋም ሕይወቱን በሙሉ ስራው አደረገ፡፡
ክፍተቱ ሰፋ፡፡
እሱም ከእሷ ጋር መነታረኩን በመፍራት እያደር እንዲንቦረቀቅ ፈቀደለት፡፡

አሁን ልጆቹን አያውቃቸውም፡፡
እነሱም እናታቸው ከልጅነታቸው አንስታ ያሻትን ገፅታ ሰጥታ ከምትነግራቸው የተበረዘ ማንነቱ ውጪ የሚያውቁት አይመስለውም፡፡

ፊት ለፊቱ ያለውን ፎቷቸውን ደግሞ አየው፡፡


ቢሮውን ያጨናነቀው ይሄ ሁሉ የስኬት ሃተታ፣ ማስትሬት እና ዶክትሬት፣ ይሄ ሁሉ የጉብዝና ምስክር ወረቀት፣ ከሃያል ሰዎች ጋር የተነሳቸው ፎቶዎች፣ ከስንቱ ባለስልጣን የተበረከቱለት ዋንጫዎች ትርጉም አልባ ሆኑበት፡፡


“አንድ ሰው በስኬቱ ዓለምን ሁሉ ቢያስጨበጭብ የገዛ ልጆቹን ፍቅር ካጣ ምን ትርፍ አለው?”
“አንድ ሽማግሌ ስለሰራው ስራ ስንቱ ሚዲያ በየእለቱ ቢለፍፍ ቢመሰክርለት የወለዳቸው ልጆቹ ግን ከእናካቴው ካላወቁት ምን ዋጋ አለው?” ብሎ አሰበ፡፡

3.4k 0 5 18 122

‹‹መደረግ ያለበት ነገር›
ክፍል ሶስት- የመጨረሻው ክፍል)

------00000000000000--------------
ቤታችሁ ስርአትና ፅዳቱ የልጅ ቤት አይመስልም፡፡
ካለቦታው የተቀመጠ የልጅ መጫወቻ እንኳን የለም፡፡
ደግሞ የሆነ የሚስብ፣ የሚያቅፍ፣ የሚመች መንፈስ አለው፡፡
ደምበኛ የቤተሰብ ቤት፡፡ ሳሙኤል ሲ(ቢ)ያገባኝ ቤቱን እንዳንቺ ልይዝለት ይቻለኝ አይመስለኝም፡፡
ግን አሁን ስለዚህ ማሰብ አልፈልግም፡፡


ከዚያ ወደ ሳሎኑ መራሽኝና ክሬም ቀለም ወዳለው ክፍለከተማ የሚያህል ሶፋችሁ ጠቁመሽ እንድቀመጥ ጋበዝሽኝ፡፡
ከመቀመጤ፣
‹‹ቡና ትጠጪያለሽ?›› አልሽኝ፡፡ መልስ ለመስጠት ድምጼን ስፈልግ ጊዜ ሳትሰጪኝ ወደ ኩሽናው ሄድሽና፣

‹‹ሻሼ! እሰቲ ከሳሚ የተረፈውን ቡና አምጪ!›› አልሽ፡፡

ከሳሚ የተረፈውን፡፡

‹‹አይ..ቡና እንኳን…›› ብዬ ብቀጥልም ከዚህ ርቀት እንደማትሰሚኝ ሲገባኝ በተቀመጥኩበት ከትልቁ ቴሌቪዥን በላይ የተለጠፉ ፎቶዎችን ማማተር ያዝኩ፡፡

ሳሙኤል፣ አንቺና ልጆቻችሁ ተሰድራችሁ ያላችሁበት ፎቶ፡፡ ያንቺና የሳሙኤል የሰርግ ፎቶ፡፡ ሳሚ ሁለቱም ላይ ደስተኛ ይመስላል፡፡

ፖስታዬን እንደያዝኩ በተቀመጥኩበት ብዙ ነገር አስባለሁ፡፡

ፖስታውን ጠረጰዛው ላይ ጥዬላት ልሂድ?
ፎቶዎቹና አልትራሳወንዱ ማወቅ ያለባትን ነገር ይንገሯት?
ከዚያ ግን እዚህ ድረስ ከመጣሁ አይቀር ላደርግ የመጣሁትን መፈፀም አለብኝ ብዬ ወሰንኩ፡፡
ቢያንስ ለልጄ ስል፡፡
--
ሻሼ በቡና የተሞላ ትንሽ ስኒ ፊት ለፊቴ አስቀምጣ ሄደች፡፡ አሁን አንቺም ፊት ለፊቴ ተቀምጠሽ ከኩሽና ይዘሽ የመጣችውን ቡና ፉት አልሽና ስኒውን እዚያው ጠረጴዛ ላይ አስቀመጥሽ፡፡

እጆቼ መንቀጠቀጣቸው ባሰ፡፡ ቡናውን ፉት ልበል እንኳን ብል አምልጦኝ ሊደፋ ነው፡፡


አይ አይ፡፡ ይቅርብኝ፡፡

‹‹ይቅርታ›› አልኩ ሳላስበው፡፡ ቃላቱ አምልጠው ያለፈቃዴ ነው ከአፌ የወጡት፡፡
‹‹ለምንድነው ይቅርታው?›› አልሽ በዚያ ቆፈን በሚለቅ እርጋታሽ፡፡


ፖስታውን ከፍቼ ውስጡ ያለውን ነገር ሁሉ አውጥቼ ፊት ለፊትሽ- የቡና ስኒዎቻችን ያሉበት የመስታወት ጠረጴዛ ላይ ዘረገፍኩት፡፡
ሊገናኙ የማይገባቸው ሰዎች ተገናኝተው የተነሷቸውን (ነውረኛ) ፎቶዎች፣ ሊፈጥሩ የማይገባቸውን ፅንስ ፈጥረው ፅንሱ የተነሳውን አልትራሳውንድ ምስል ለእይታሽ አቀረብሁ፡፡

ፎቶዎቹን አይተሽ ስታበቂ ምንም ምላሽ አልሰጠሸም፡፡


አልተናደድሽም፡፡
አልጮህሽም፡፡
አላለቀስሽም፡፡
ቀና አልሽና በርጋታ ስትመለከቺኝ ያበጠው ይፈንዳ ብዬ፣
‹‹አርግዣለሁ›› አልኩኝ፡፡

ጭንቅላትሽን በ‹‹ገባኝ›› ነቀነቅሽና ጠረጴዛ ላይ የተዘረገፉትን ፎቶዎች አየት አደረግሽ፡፡


ማብራራት ያለብኝ መሰለኝ፡፡

‹‹ከባለቤትሽ…ከሳሙ- የሳሙኤል ልጅ ነው…›› አልኩኝ፡፡
የተቀመጥሽበት ሶፋ ላይ እየተመቻቸሽ ‹‹ገባኝ›› አልሽኝ፡፡

እስክትናደጅ፣ እስክትጮሂ፣ የሚገባኝን ስድብ እስክታጠጪኝ ብጠብቅም አንዱንም ነገር አላገኘሁም፡፡


ያኔ ነው ለስንቱ ስሜት ስሰናዳ ለእርጋታሽ፣ ለስምምነትሽና ለዚህ የሚስፈራ ቀዝቃዛ ምላሽሽ እንዳልተዘጋጀሁ የገባኝ፡፡

እንደሳልኩሽ አይነት ሴት ልትሆኚልኝ አልቻልሽም፡፡
ባለጌ አትይኝም? ..ስድ አደግ ብለሽ አትሰድቢኝም?…ደፋር ነሽ ብለሽ አታንባርቂብኝም?

ጭራሽ ምንም ሳትይ ብድግ አልሽና ረጅም ቀሚስሽን ላይሽ ላይ እያስተካከልሽ ፣ ወደ በሩ እያመላከትሽኝ-

‹‹በይ እንግዲህ…አሁን ብትሄጂ ሳይሻል አይቀርም›› አልሽኝ፡፡

ተወዛገብኩ፡፡

‹‹እንዴ…? ቆይ እንጂ…በቃ…ይሄው ነው? …ምንም አትይም…ምንም አታደርጊም ማለት ነው?›› አልኩ እየተንተባተብኩ፡፡

አንቺ ወደ በሩ መንገድ ጀምረሻል፡፡ በደመ ነፍስ ተከተልኩሽ፡፡

በሩ ጋር ስትደርሺ ሰፋ አድርገሽ ከፈትሽውና ድቡልቡሉን እጀታ በቀኝ እጅሽ እንደያዝሽ፣
‹‹ምን እንድል ነው የፈለግሽው?›› አልሽ በዚያው ሽብር በሚለቅ እርጋታሽ፡፡
‹‹ልትነግሪኝ የፈለግሽውን ነገር ነገርሽኝ፡፡ የመጣሽበትን ጨርሰሻል፡፡ ቀጥሎ መደረግ ያለበት ነገር አንቺን አይመለከትም›› ብለሽ ጨመርሽበት፡፡

በቆምኩበት እግሮቼ እንዳይከዱኝ እየፀለየሁ፤


‹‹ግን እኮ ልጁ የእሱ ነው…›› አልኩ፡፡
አሁን ፊትሽ ላይ የንዴት ሳይሆን የሃዘን ስሜት ተስሎ ፣

‹‹ሳሙኤል እንዲህ ሲያደርግ የመጀመሪያው ይመሰልሻል?›› አልሽኝ ዝቅ ባለ ድምፅ፡፡
‹‹ሌላ ሴትን አፈቀርኩሽ ብሎ በትዳሩ ላይ ሲማግጥ፣ ሌላ ሴት ሲያስረግዝ የመጀመሪያው ነው ብለሽ ነው?›› ብለሽ ጨመርሽ፡፡

ጉሮሮዬ ላይ የሆነ ነገር የተሰነቀረ መስሎኝ በትግል -
‹‹ም..ን?›› አልኩሽ፡፡
‹‹የባሌን ጠባይ አውቀዋለሁ፡፡ የእኔ እናት…እንዲህ ያደረጋት የመጀመሪያዋ ሴት አንቺ አይደለሽም…እርግጠኛ ነኝ የመጨረሻዋም አትሆኚም፡፡ ያንቺን ለየት የሚያደርገው ልትነግሪኝ እዚህ ድረስ መምጣትሽ ብቻ ነው››

የሎጥ ሚስት መች የጨው አምድ ሆና ቀረች?
እኔ በለጥኳት፡፡ አስከነዳኋት፡፡
‹‹እንደዚህ ያደርጋል ብዬ….›› አልኩ ደርቄ በቆምኩበት፡፡
‹‹እንዲህ ያደርጋል ብለሽ አላሰብሽም›› አረፍተ ነገሬን ጨረስሽልኝ፡፡
‹‹አውቃለሁ፤ ቃሉን አምነሽ ሚስቱን ይፈታል፡፡ ትዳሩን አፍርሶ ከእኔ ጋር ይኖራል ብለሽ ነበር ያሰብሽው ግን ቁርጥሽን እወቂ፡፡ አድርጎት አያውቅም፡፡ አያደርገውም፡፡ ››

ልሟገትሽ ፈልጌ ነበር ግን እውነቱ ውስጤ ገብቶ በላኝ፡፡ እኔ ለሳሙኤል በተርታ ካሉ ሴቶች መሃከል አንዷ እንጂ ልዩ ሴት አይደለሁም፡፡

‹‹በይ አሁን ሂጂ››አልሽኝ እናት ልጇን እንደምታወራው ለስለስ ብለሽ፡፡
‹‹ስለ ፅንሱ መደረግ ያለበትን ነገር ቶሎ እንዲያደርግ አደርጋለሁ፡፡ የለመድኩት ነው፡፡ አንቺ ግን የማይመጣን ወንድ በመጠበቅ እድሜሽን አትፍጂ፡፡ በጊዜ ቢጤሽን ፈልጊ፡፡ አጃቢ ከመሆን ዋና መሆን አይሻልም?››

‹‹‹ስለ ፅንሱ መደረግ ያለበትን ነገር እንዲያደርግ አደርጋለሁ› ስትይ ምን ማለትሽ ነው ብዬ ልጠይቅሽ ፈልጌ ነበር ግን አላደረግሁትም፡፡
ሁኔታሽ እንዳልጠይቅሽ፣ እንዳልከራከርሽ አሰረኝ፡፡ ወሬያችን በዚሁ አብቅቶ የሳሎን በርሽን ከጀርባዬ ስትዘጊው ልቤ በሃዘን ቆስሎ ነበር፡፡
--
ከሰአት በኋላ- ከማልቀስ ብዛት ራሴን አሞኝ ቤቴ በተኛሁበት- ስትደውይልኝና የባንክ ቁጥሬን ስትጠይቂኝ ነው ሃዘኔ በሚንቀለቀል ንዴት የተተካው፡፡
ለምን የባንክ ቁጥሬን ጠየቅሽኝ ስልሽ ፣‹‹ከሳሚ ጋር ተነጋግረን ነበር ፡፡ የፅንሱን ነገር በጊዜ መላ እንድትይው ብለን ነው›› አልሽኝ፡፡

እሱስ ወንድ ነው፡፡
ወንድ ማታለል ልማዱ ነው፡፡ የሚጠበቅ ነው፡፡
አንቺ ግን በጭራሽ መልካም ሴት አይደለሽም፡፡

3.9k 1 24 46 118

‹‹መደረግ ያለበት ነገር ››
(ክፍል ሁለት)
----
ግንቦት ሃያ ነበር፡፡ ስራ ስላልነበር ቤት ነበርኩ፡፡

አልጋዬ ላይ ሆኜ ፊልም እያየሁ የሆነ ጭስ ነገር አፈነኝ፡፡ ስወጣ ለካ ጎረቤቴ እትዬ እታለማሁ ቤቷ ውስጥ በኩበት ድፎ ዳቦ ጋግራ ነገር ተበላሽቷል፡፡ ፈጣሪ ባይረዳን ሙሉ ህንጻውን ልታነደው ነበር፡፡
ከሌሎች ሰዎች ጋር ቤቷ ስንገባ ጭሱ አፍኗት ራሷን ስታለች፡፡ አፋፍሰን አጠገባችን ያለ ትልቅ የግል ክሊኒክ ስንወስዳት እንግዳ መቀበያው ጋር ማንን አገኛለሁ?
ባልሽን፡፡
ቤት ቤት ስሆን እንደምለብሰው አጭር የቱታ ቁምጣና ጠባብ ቲሸርት ለብሼ ነበር፡፡
‹‹ሳሙኤል ገብረማርያም!›› ብዬ ጠራሁት፡፡

ያኔ ስሙን በደንብ አጥንቼዋለሁ፡፡

በኋላ እንደነገረኝ አንገቱን ለመጨረሻ ጊዜ ሊታይ መጥቶ ነው፡፡

‹‹ለምን ወጪውን እንዳግዝህ አልደውልክም?›› ስለው ድጋሚ ሳቀብኝና ከላይ እስከታች አበጥሮ አየኝ፡፡

እውነቴን ነው፣ ያን ቀን ነው አሮጌ መኪናዋ ከዘመናዊ መኪናው ከተጋጨ ሴት ባለፈ አይን ያየኝ፡፡
አይኖቼን ሲያይ ያዝኩት፡፡ ከጠቀመሽ፣ የእኔ አይኖች ደግሞ ደማቅ ቡናማ ናቸው፡፡

ይሄውልሽ፤ ይሄንን ግራ የሚያጋባ ታሪክ ነው ይዤ ልመጣ ያሰብኩት፡፡ ገና ቤትሽ አልደረስኩም፡፡ መንገድ ላይ ነኝ፡፡

ግን ታሪኩን ለራሴ መልሼ ስነግረው ቀለለብኝ፡፡ እና ምን ይጠበስ?
----
አሁን ቤታችሁ ደርሼ አጭርና የሚያምር ፊልም ላይ የምናየው ነጭ የእንጨት አጥራችሁ ፊት ለፊት ቆሜያለሁ፡፡
መጀመሪያ አይኔ ውስጥ የገቡት የመንታ ልጆችሽ /ልጆቻችሁ ሁለት የመኪና ውስጥ መቀመጫዎች ነው፡፡ በስርአት በተያዘው ግን ጠበብ ባለው ግቢያችሁ መሃል ተሰይመዋል፡፡


ወደ ላይ እንደማለት አለኝ፡፡
ምን እያደረግሁ ነው?
ምን አስቤ ነው እዚህ ድረስ ስበር የመጣሁት?
ስሚኝማ፣ ይቅርታ ግን ባልሽን ስላፈቀርኩት ጎጆሽን ላፍርሰው፣ ልጆችሽን ልበትን ነው ልልሽ ነው?

ግን እኮ እሱም እንደሚያፈቅረኝ ነግሮኛል፡፡
ከሁለት አመታት በላይ ይሄንኑ በተደጋጋሚ ሲነግረኝ ከርሟል፡፡ ሚስቴን ፈትቼ ካንቺ ጋር መሆን እፈልጋለሁ ካለኝ ሰነባብቷል፡፡ እና ታዲያ በእሱ ፍላጎት ላይ ለመወሰን እኔ ምን ቤት ነኝ?

ባለጉዳዩ እሱ፡፡ ባለትዳሩ ራሱ፡፡

እኔ እንደውም ያዴትና እና ያኔት (አዎ፣ የመንትዮቻችሁን ስም አውቃለሁ) ከፍ እስኪሉ እንድንታገስ ፈልጌ ነበር፡፡ ግን ምን ያደርጋል? ያልጠበቅኩት ነገር ተከሰተ፡፡
ጊዜ የማይሰጥ፡፡
የሚያጣድፍ፡፡
ገብቶሻል፡፡


የእኔም ልጅ አባት ያስፈልጋታል፡፡ እንግዲህ ሳሙኤል ለእኔ ልጅ አባት እንዲሆን ያንቺ ልጆች ያለ አባት ማደግ አለባቸው…?

እሱ ያንቺ ውሳኔ ነው፡፡

ግን ያው እኔም እንደየትኛዋም እናት ቅድሚያ የምሰጠው ለራሴ ልጅ ነው፡፡

እርግጠኛ ነኝ እናት ነሽና በዚህ አትቀየሚኝም፡፡

ዛሬ አንቺ ጋር መጥቼ ነገሩን ሁሉ ለማፍረጥረጥ ያሰብኩትም ለልጄ ስል ነው፡፡ ሳሙኤል ዞሬ ዞሬ ያንቺ ነኝ ቢለኝም ዙረቱ ግን ረዘመብኝ፡፡ አጠር አድርገነው ነገሩ ፈር እንዲይዝልኝ ብዬ ነው፡፡
ለልጄ ስል፡፡

----
በዚህ ሃሳብ እንደያዝኩ ቀድሞ የተከፈተውን አጭር የአጥር በር በቀኝ እጄ ገፋ አድርጌ ጠባቡን ግቢ በፍጥነት አቋረጥኩና ግዙፍና ነጣ ያለ ቡናማ የሳሎን የእንጨት በርሽን በለሆሳስ አንኳኳሁ፡፡

ይቅረታ ግን ቀለሙ የሳሚን አይኖች አስታወሰኝ፡፡







በሩ ተከፈተ፡፡ ፊት ለፊት ቆመሻል፡፡ ከነ ሙሉ ግርማሽ፡፡ ሳሙኤል ከነገረኝ በላይ ውብ ነሽ፡፡


አልዋሽሽም፤ ‹‹ድሮ የደስ ደስ ነበራት፡፡ አሁን ግን ምኗም አያምር›› ብሎ አቃሎሽ ነበር፡፡

ትንሽ ደንገጥ እና ግር የማለት ስሜት ያለው ፊት ብጠበቅም ያንቺ ፊት ግን ከእርጋታና ከውበት ውጪ ሌላ ነገር አይታይበትም፡፡

የምላትን ነገር ቀድማ አውቃ በንዴት እየተንጨረጨረች ትጠብቀኝ ይሆን የሚለው ስጋቴ በቀዝቃዛውና እርጎ በሆነው አኳሃንሽ ተሰረዘ፡፡

በቀኝ እጅሽ ጨርሶ ከመከፈት ያቆምሽውን በር፣ በግራ እጅሽ ደግሞ ጎንሽ ላይ ያቀፍሻትን ልጅሽን ታፋ ይዘሽ ቆመሻል፡፡

ሆዴ ተገላበጠ፡፡
‹‹ሰላም›› አልኩኝ ድምጼ ካሰብኩት በላይ እየተቆራረጠ፡፡
ፎቶና ሌሎች ማስረጃዎችን የያዘውን ትልቅና ቡናማ ፓስታዬን በእጄ አጥብቄ ይዣለሁ፡፡ አሁን ግን በውስጡ ብሎኬት የያዘ ያህል ከበደኝ፡፡ ጣቶቼ ተንቀጠቀጡ፡፡ እንዳይወድቅ ከበፊቱ የባሰ አጥብቄ ያዝሁት፡፡

‹‹ሰላም›› ብለሽ መለሽልኝ፡፡ ፈገግ ብለሻል፡፡ አይኖችሽ ግን አይስቁም፡፡
‹‹ግቢ››

ገባሁ፡፡


ቤታችሁ ቡና ቡና ይሸታል፡፡ ትንሽ የእጣን ሽታም አለው፡፡
ሳሙኤል ቡና በእጣን እንደሚወድ አውቃለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ ቤቴ መጥቶ እንደሚወደው አድርጌ ሳፈላለት ‹‹አመሰግናለሁ የእኔ ወርቅ፡፡ ሚስት ተብዬዋ እንደዚህ የምወደውን ቡና በእጣን እንኳን ከከለለችኝ ስንት ዘመኗ!›› ይለኝ ነበር፡፡

አሁን ግን ጠዋት ተነስቶ ስራ ከመሄዱ በፊት ያፈላሽት ቡናና እጣን ትራፊ ይመስላል የተቀበለኝ፡፡

አሄሄ፡፡
(ይቀጥላል)

3.2k 1 21 11 102

መደረግ ያለበት ነገር
(ክፍል አንድ)

------
አሁን ሳስበው ባልደውልልሽ ይሻል ነበር መሰለኝ፡፡  መደወሌ ጥፋት ነው፡፡
እያዋራሁሽ ልጆችሽ ሲጫወቱ ይሰማኛል፣ ለስለስ ባለ ድምፅሽ እሱን አትጣይ፣ እሱን አንሺ፣ እንደእሱ አትዝለይ፣ እንደ እሱ አትበይ እያልሽ ስታወሪያቸው ይሰማኛል፡፡ ደግ እና እንስፍስፍ እናት ትመስያለሽ፡፡
ባትሆኚ ነበር ለእኔ የሚሻለኝ፡፡

ልክ ባልሽ እንደሳለሽ አይነት ነትራካና ለባሏ የሚስትነት ፍቅር የሌላት ደረቅ ሴት ብትሆኚ ይሻለኝ ነበር፡፡
ግን እንደእዚያ አይነት ሴት አትመስይም፡፡ ሁለት የሁለት አመት መንታ ልጆችሽን እንደዚያ በፍቅርና በትእግስት ስታወሪና ስታርቂ ስሰማ ስላንቺ የነገረኝን ነገር ማመን ከበደኝ፡፡

ነጭናጫ ናት ይልሻል፣ ደሞዝ የሌላት የቤት ሰራተኛ፣ ልጆችዋን ብቻ የምትነከባከብ እናት እንጂ ሚስቴ መሆን ካቆመች ሰነበተች ብሎ ያወራብሻል፡፡

አልጋ ከለየን ቆይተናል፣ መንታ ልጆቻችን ከፍ እስኪሉ ጠብቀን መለያየታችን አይቀርም፡፡ ሃብት ክፍፍሉም መከራ ነው ምናምን እያለ ስንት ጊዜ ስንት ነገር ነግሮኛል፡፡ አሁን ግን ለዚህች ደቂቃ ድምፅሽን ስሰማና ሳወራሽ ባልሽ ከሚገልፅሽ ተቃራኒ ሆነሽ አገኘሁሽና ስላንቺ የነገረኝን ሁሉ ጠረጠርኩ፡፡

ለማንኛውም ወደዋናው ጉዳዬ ልመለስ፡፡ ዋናው ጉዳይ ምንድነው?


ያደረግኩትን ነገር እንዴት ብዬ ነው የምነግርሽ የሚለው ነው፡፡
መልካም ሴት አይደለሽ?
‹‹የማዋይሽ ብርቱ ጉዳይ አለኝና እንገናኝ›› ስልሽ ያለምንም ማንገራገር እሺ አልሽኝ፡፡  ‹‹አንቺ አታውቂኝም እኔ ግን አውቅሻለሁ›› ስልሽ እንኳን ጥርጣሬ ሽው ብሎሽ ወደ ኋላ አላልሽም፡፡ ‹‹እሺ›› ብቻ አልሽኝ፡፡
ነገ ከጠዋቱ ሶስት ሰአት ላይ  ቤትሽ መጥቼ ለመገናኘት ተስማማን፡፡ ልክ ባልሽ ስራ እንደሄደ፡፡ ሶስት ሰአትን- ባልሽ ከሄደ በኋላ- ለመገናኘት መምረጤን ያስተዋልሽ አትመስይም፡፡ ስለ ሰአቱ ምንም አይነት አስተያየት ሳትሰጪ፤  ‹‹ቴሌግራም ላይ ሎኬሽኑን ልላክልሻ?›› አልሽኝ፡፡
‹‹ግዴለም ቤቱን አውቀዋለሁ›› ስልሽ እንኳን ከ ‹‹ነው…? መልካም›› ውጪ ምንም አላልሽ፡፡
እውነትም መልዐክ ቢጤ ነሽ፡፡
አሁን ስለነገ በማሰላሰል ላይ ነኝ፡፡ እንዴት እንዴት አድርጌ ነው ይሄን ነገር የምነግርሽ?

የሚያስፈልጉኝን መረጃዎች በሙሉ በማሰናዳት መጀመር ይኖርብኛል፡፡
ፎቶዎቹን፡፡ አልትራሳውንዱን፡፡ ሁሉንም በስርአት አንድ ቦታ ሰብስቤ እይዛለሁ፡፡

ከዚያ(  በኋላ የሚፈጠረውን ስለማላውቅ ባልነዳ ይሻላል) ራይድ እጠራና የሚያምረው የፍሊንትስቶን ግቢ ውስጥ የሚገኘው ታውን ሃውሳችሁ ጋር እወርዳለሁ፡፡
ስለማልቆይ ሹፌሩን እንዲጠብቀኝ ልጠይቀው እችላለሁ፡፡ ቡና እና ቡና ቁርስ እያልኩ አብሬሽ አልቆይ መቼስ፡፡ ግን ትንሽ ጊዜ ደግሞ ያስፈልገናል፡፡ የምልሽን ብዬሽ እስክታምኚ…ስሜትሽን እስክትገልጪ፡፡ አይ አይ…የሚያደርሰኝን ሹፌር ሸኝቼ ስጨርስ ሌላ ብጠራ ነው የሚሻለኝ፡፡

ከየት እንደምጀምርልሽ ነው ግራ የገባኝ፡፡ ከውልደቴ ልጀምር ይሆን?
አሰላ ነው የተወለድኩት ብዬ ልንገርሽ?  አርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ መማሬን ላጫውትሽ?
አይ፡፡ ቀጥታ ወደ ጉዳዬ ብሄድ ይሻላል፡፡ 

ከሁለት አመት ተኩል በፊት ጥር 22 ላይ እጀምርና ሁሉንም ነገር እነግርሻለሁ፡፡
ጥር 22 እኔና ባልሽ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘንበት ቀን ነው፡፡
መኪናዎቻችን ተጋጭተው፡፡ ግጭቱ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም ግን አድራሻ፣ የታርጋ ቁጥርና የኢንሹራንስ መረጃዎችን ተለዋወጥን፡፡
የማልዋሽሽ ነገር ይሄን ሁሉ መረጃ ስቀበለው ከሁሉም ነገር ልብ ያልኩት አይኖቹን ነበር፡፡ ፈዛዛ ቡናማ ብሌኖቹ፡፡ ከዚያ ደግሞ ወንዳወንድ ድምፁ፡፡ የጋብቻ ቀለበት እንዳጠለቀም አይቻለሁ፡፡ አይዞሽ፡፡ ቀለበቱን አልደበቀም ነበር፡፡ ደብቆ አያውቅም፡፡



በምወደው እምልልሻለሁ ይሄ በሆነ ከሶስት ሳምንት በኋላ ድጋሚ በአጋጣሚ ባንገናኝ ኖሮ ምንም አይፈጠርም ነበር፡፡

የሚደንቅ አጋጣሚ ነበር፡፡

እኔ ጓደኛዬ ፍርቱና አዲስ ትራሶች ካልገዛሁ ብላ ለምናኝ አንድም ቀን ሄጄ የማላውቅበት ቦሌ የሚገኝ ትልቅ ሱፐር ማርኬት ሄጄ ነበር፤ ላጋዛት፡፡ ለወትሮው እንደዚህ ያለው ቦታ አልመጣም፡፡ ዋጋውን አልችለውም፡፡ ከዚያ የምትገዛውን ይዘን ለመክፈል ሰልፍ ላይ ሆነን ከፊት ለፊት ማንን አያለሁ? ባልሽን፡፡

የልጆች ወተትና ዳይፐር እየገዛ ነበር፡፡
እሱ እንደሆነ ከማወቄ በፊት ያስተዋልኩት ነገር አንገቱ ላይ ያደረገውን ነገር ነበር፡፡ ያ ሰዎች አደጋ ገጥሟቸው አንገታቸውን ለማቅናት የሚያደርጉት ነገር የለም? ስሙን እንጃ፡፡ እሱን አድርጎ ነበር፡፡ አጠገቡ ሄጄና ሰላምታ ተለዋውጠን ስናበቃ ለምን አንገቱ እንደተጎዳ እንዳልነገረኝ ጠየቅኩት፡፡

‹‹ቆይተህ ልትከሰኝ እና እስር ቤት ልታስገባኝ ነው እንዴ?›› አልኩት፡፡
ከት ብሎ ሳቀና፣ ‹‹አይ ለማንኛውም ብዬ ነው እንጂ አልተጎዳሁም›› አለኝ፡፡


ከዚህ ቀጥሎ የምነግርሽ ሌላ አጋጠሚ ባይፈጠር ኖሮ ነገሩ በዚህ ያበቃ ነበር፡፡ ግን ምን ያደርጋል? እንደገና ተገናኘን፡፡ እንዴት አትይኝም?

(ይቀጥላል)

3k 1 35 13 86

‹‹ስታገግም››
=======



ሶስት ሰዎችን የሚይዘው የሆስፒታሉ ወጥና የብረት የእንግዳ መቀበያ ወንበር ላይ አጠገብ ለአጠገብ ተቀምጠናል፡፡

በስልኩ ተጠምዷል፡፡
ቴሌግራም መሰለኝ፡፡

ያለሁበት ጭንቀት ስልኩ ላይ ምን እንደሚሰራ እንዳስተውል አልፈቀደልኝም፡፡



እኔ ለራሴ ስንት ሃሳብ አለብኝ፡፡
ውስጥ ከገባች አርባ አምስት ደቂቃ አለፋት፡፡ ከአስራ አምስት ደቂቃ በላይ አይፈጅም ብለው ነበር፡፡
ዶክተሩ ስለሚደረገው ነገር ሲያወራት አብሬያት ነበርኩ፡፡



‹‹ቀላል ነገር ነው፡፡ የተለመደ ፕሮሲጀር ነው፡፡ ብዙ አትጨነቁ›› ብሎ ነበር፡፡



ከጨረሰች በኋላ መጠነኛ የሆድ ቁርጠት እና የደም መፍሰስ እንደሚኖር ግን ‹‹ኮምፕሊኬሽን›› ከሌለ ከከባድ ፔሬድ በላይ እንዳማያማት ነግሮን ነበር፡፡

‹‹እሱም ቢሆን ከ48 ሰአት በላይ አይቆይም›› ብሎ ጨምሮ፡፡




ለነገሩ እንግዳ ስለነበረች እጅግ ፈርታ ነበር፡፡
እኔም ብፈራም ለእሷ ስል በረታሁና አበረታኋት፡፡


አሁን ከእሱ ጋር እዚህ ተቀምጠናል፡፡

ትወጣለች ከተባለው ጊዜ ግማሽ ሰአት አልፎ ማንም አንድም ነገር ሳይነግረኝ መቀመጤ ጭንቀቴን አባሰው፡፡


ትህትናዋን ስለወደድኩት አንደኛዋን ነርስ ደጋግሜ ብጠይቃትም ‹‹ስትወጣ እነግርሻለሁ፣ ጠብቂ›› ከማለት በስተቀር ምንም አልረዳችኝም፡፡


ከእሱ ጋር ጭራሽ አንተዋወቅም፡፡
ገና ዛሬ መገናኘታችን ነው፡፡ እዚሁ ሆስፒታል፤ ለዚሁ ጉዳይ፡፡ 

እኔ ከእናካቴው አልወቀው እንጂ እሷም ስታውቀው አምስት ወር አይሆናትም፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ ያገናኘን አጋጣሚ ይሄ መሆኑ ወሬ ለማድራት አመቺ ባይሆንም ትኩረቱ ከመጣን ጀምሮ ከስልኩ አለመላቀቁ ግን ምቾት አልሰጠኝም፡፡ 

አንዴም አላወራኝ፤ እንዲያውም የጨነቀውም አይመስልም፡፡

ወይ ደግሞ ተጨንቆ ይሆናል፤ አንዳንድ ሰው መጨነቁን ላለማሳየት ራሱን በአንድ ነገር መጥመድ ይወዳል፡፡

እንዳልኳችሁ ሰውየውን አላውቀውም፡፡


ከአስራ አምስት እንደ ቀናት ከረዘሙ ደቂቃዎች በኋላ ጉዳይዋን ጨርሳ ማገገሚያ ክፍል አንደገባች ተነገረኝ፡፡

ሊፍቱን የመጠበቅ ትእግስት አጥቼ ደረጃዎቹን ባንዴ ሁለት ሁለት እያደረግኩ ዛቅኩና ልቤ እየመታች ሶስተኛ ፎቅ ላይ ያለችበት ክፍል ገባሁ፡፡

የማይመች የሚመስል አልጋ እንዳልተመቻት በሚያስታውቅ ሁኔታ  ተኝታለች፡፡
ከሁለቱም አይኖቿ እምባ ይወርዳል፡፡

የእኔ እናት፡፡


‹‹በቃ አሁን እኮ አለፈ…አታልቅሺ›› አልኳት አልጋዋ አጠገብ የሚገኝ የተሰነጠቀ ፕላስቲክ ወንበር ላይ ተቀምጬ እጆችዋን ያዝኩና፡፡


እምባዋን አብሼ ሳልጨርስ፣
‹‹የት ነው?›› ብላ ጠቀችኝ፡፡
‹‹ታች›› መለስኩላት፡፡





‹‹ስለማታውቂው ነው እንጂ ጥሩ ሰው ነው…ሁሉንም ነገር የከፈለው እሱ ነው…ታያለሽ…ስትግባቡ-››

አቋረጥኳት፡፡

‹‹አሁን ስለእሱ የምናወራበት ሰአት አይደለም…ይደርሳል፡፡ ይልቅ እረፊና ወደቤት እንሂድ..ቤት ምን አልሻቸው…ፔሬድ?›› አልኳት፡፡
‹‹አዎ…›› አለችኝ ቅዝዝ ብላ፡፡

ወዲያው ‹‹ጥሪውና ልየው››  ስትለኝ፣ ‹‹ይየኝ ማለትሽ ነው›› አልኳት፡፡
ልዩነቱ የገባት አልመሰለኝም፡፡ ወይ ደግሞ እኔ አልገባኝም፡፡


‹‹በአንድ ጊዜ አንድ ሰው ብቻ ነው የሚፈቅዱት›› አልኳት፡፡

ፊቷ ላይ ያለውን የቅሬታ ስሜት ሳይ ግን፣
‹‹እሺ…እኔ እዚያ ልሁንና እሱ ይግባ..ሲወጣ እመጣለሁ›› ብያት ልጠራው ወረድኩ፡፡


ታች ስደርስ እስካሁን ሳይነቃነቅ ቁጭ ብሎ የነበረበት ቦታ የለም፡፡

ሪሴፕሽኒስቷን አይታው እንደሆን ስጠይቃት ወደ ውጪ አመለከተችኝ፡፡

ስልክ እያወራ ነበር፡፡




አጠገቡ ስደርስ ጀርባውን ለእኔ ሰጥቶ እንዲህ ሲል ሰማሁት፣

‹‹የኔ ቆንጆ…እንደዚህማ አታምርሪብኝ…እማዬን ከክሊኒክ ቤት ላድርስና እመጣለሁ፡፡ ቀን የጠፋሁትን ሌሊቱን ሙሉ እክስለሁ እሺ…?››


የኋልዮሽ መራመድ ፈለግሁ፡፡ እግሮቼ ግን አሻፈረኝ አሉ፡፡

ሃሃ ሂሂ ኪኪ እያለ ሲስቅ ግን እንደምንም አቅሜን አሰባሰብኩና ዞሬ ወደ መጣሁት ተመለስኩ፡፡


አሁን ደረጃዎቹን በፍጥነት እንድወጣ የሚነዳኝ ስሜት ንዴት ነው፡፡

ወደ ክፍሏ ስገባ በትኩስ ውርጃ የቆሰለ አካልና መንፈሷን ይዛ የተኛችውን ጓደኛዬን ሳያት የባሰ በንዴት ጦፍኩ፡፡

የሰማሁትን መንገር አሁን ካለችበት ህመም በሺህ እጥፍ የሚያሳምማት ስለመሰለኝ ስሜቴን ዋጥ አድርጌ አጠገቧ ተቀመጥኩ፡፡

‹‹ ሁሉን ነገር የከፈለው እሱ ነው›› ያለችን እያስታወስኩ፣

‹‹ዋናውን ነገር የከፈልሽው ግን አንቺ ነሽ›› ብዬ ልነግራት ተመኘሁ፡፡
ቀን ጠብቄ፣ ከእዚህኛው ቁስል ስታገግም፡፡

3.5k 0 13 13 104

‹‹ለዚህ ይሆን?››
____






ቅዳሜ ፡፡


የሰረጎደ ሶፋዋ ላይ ተቀምጣ ቆሎዋን እያሻመደች ቴሌቪዥን ላይ የመዝናኛ ዝግጅት ታያለች፡፡

የማስታወቂያ ሰአት ነው፡፡


ትልቅ መስታወት ፊት ተቀምጣ ራሷን በጥልቅ ቅሬታና መከፋት የምትመለከት በእድሜ እኩያዋ የምትመስል ወጣት ሴት ትታያለች፡፡


ኩርፊያዋ ሳይለቃት፣‹‹ፌር ኤንድ ብራይት›› የተባለ ክሬምን ከነጭ እቃ ውስጥ በጣቶቿ እንደ ጉድ፣ ቶሎ ቶሎ እየደነቆለች ፊቷን ትለቀልቃለች፡፡


ጥድፊያዋ።


ከዚያ…



ክሬሙን ባዳረሰችበት ቦታ ሁሉ ቀደም ሲል ቆሻሻ ይመስል የነበረው ጥቁር ፊቷ ሲቀላ፣
ጸሃይ በምትቀናበት መጠን ፏ ብሎ ሲያበራና፣ ባንድ ጊዜ ሲፈካ ይታያል፡፡



ይሄን ጊዜ…



ቅድም በትካዜ ተውጣ የነበረችው ወጣት፣ ፊቷ ከመቅላቱ ከየት መጣ የተባለ ውብ ፈገግታ አጥለቀለቀው፡፡


ከዚያ…


‹‹ለውብና ለእንከን አልባ ፊትሽ፣
በሁኔታ ለማይደበዘዝ ቁንጅና እና ፈገግታሽ
ፌር ኤንድ ብራይት አለልሽ››


የሚል አስገምጋሚ የወንድ ድምፅ ከክሬሙ ምስል ጋር ቴሌቭዥኑን ሞላው፡፡




ይሄን ጊዜ ማስታወቂያውን በሚያስገርም ትኩረት ስትከታተል የቆየችው ወጣት፣


በቀኝ እጇ የያዘችውን ቆሎ ስሃኑ ላይ ደፍታ፣ የስልኳን ካሜራ ከፈተችና ራሷን ፊት ለፊት እያየች፣


እንደ ማስታወቂያዋ ልጅ ተከፍታ፣ጠይምና ሻካራ ፊቷን ዳበሰች፡፡





‹‹ለዚህ ይሆን ቶሎ ቶሎ የማልስቀው?›› በሚል ሃሳብ እየዋለለች፡፡


‹‹እምጳ!››
——————————-
ጠፋ በተባለ በሁለተኛው ቀን ከሰፈሩ ብዙ ሳይርቅ፣ ከዋናው መንገድ ጀርባ የሚገኝ ትልቅ ቱቦ ውስጥ ወድቆ አገኙት፡፡


ፊቱ ላይ የሚታየው ጥልቅ ሰላም ነበር፡፡

አስቦበት ‹‹እስቲ ትንሽ እዚህች ጋር ጋደም ልበል››  ብሎ የተኛ እስኪመስል፡፡ ያም ሆኖ ሲያገኙት ፊቱ በጸሃይና በውርጭ ፈረቃ ገርጥቶ ነበር፡፡



ፖሊሶች የአካባቢው ሰው አስክሬኑን ካላየሁ ብሎ እንዳያስቸግር የሰው አጥር ሰርተው ከበውት መቆየታቸው ምን ሆኖ ነው የሚለውን መላ ምት በሺህ አባዝቶት በየቤቱ የሚጀምረው አሉባልታ ከተማውን አዳረሰው፡፡


ሚስቱ ፣ ‹‹ ትላንት ከሰአት ወደ አስር ሰአት አካባቢ አስቤዛ ግዛ ብዬ ስልከው እየተነጫነጨ ወጥቶ ቀረብኝ›› ብላ ነበር፡፡

ሳይመለስ ሲመሽ ደጋግማ ደወለችለት፡፡

ምሽቱ ለእኩለ ሌሊት ሲቀርብ ለምታውቀውና ለሚያውቁት ሰዎች ሁሉ ደውላ ‹‹ባሌ ጠፋብኝ›› ብላ ማልቀስ ጀመረች፡፡ ሲነጋ የት ገባ ብሎ የተጨነቀው ጓደኛና ዘመድ በየፊናው ፍለጋ ወጣ፣ ስልኩን ለሚያውቀው ሰው ሁሉ መምታት ያዘ፡፡


የበላው ጅብ አልጮህ ያየው ሰው አልተነፈስ ሲል ግን ከጭንቀቱ ስር ስር አሉባልታውና ሃሜቱ ጀመረ፡፡


ዘመድና ጎረቤቶቹ ተፈጠረ ያሉትን ነገር አፍ ለአፍ ሲቀባብሉ መላ ምት ሳይሆን በማስረጃ የተደገፈ ሰነድ ይለዋወጡ ይመስል እርግጠኛ ነበሩ፡፡

አንዳንዶቹ ‹‹አምስት አመት ያልሞላው ትዳሩ ችግር ላይ ነበር፤ በዚያ ላይ ሁለት ልጅ ባናት ባናቱ ወልዳበት ሶስተኛ አረገዘችበት›› ይላል፡፡ ( ያለ እሱ ያረገዘቻቸው ይመስል)

ሌሎቹ ከእናትና አባቱ ወርሶ የሚያስተዳድረው የኤሌክትሮኒክስ ሱቅ ከስሮበት ከባድ ጭንቀት ላይ ነበር ይላሉ፡፡

‹‹አባትና እናቱ እድሜ ልካችንን የለፋንበትን ስራ አበላሸህ ብለው አዝነውበት ነጋ ጠባ ያስጨንቁት ነበር›› ብለው ነገር እያዳመቁ፡፡


የቅርብ ጓደኞቹ ‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መፍዘዝና መደንዘዝ አብዝቶ ነበር…በጨዋታ መሃል በሃሳብ ጥሎን ይነጉዳል፣ አንዳንዴም ብቻውን ያወራል›› እያሉ አወሩ፡፡

ከእነዚህ አንዱ ሚስጥረኛ ነኝ ባይ ደግሞ ከሰሞኑ አግኝቼው ‹ እንደው ልጆቼ ያሳዝኑኛል እንጂ  ራሴን ሲጥ አድርጌ በተገላገልኩ› ብሎኝ ነበር›› ብሎ ጨመረ፡፡


ከዚያ ደግሞ በየቤቱ፣ በመንገዱ የሚሰሙ ሹክሹክታዎች በረከቱ፡፡

‹‹ የባንክ እዳ ተቆልሎበት መክፍል አቅቶት ሱቁን ሊወስዱበት ነው..ብስጭቱ ክፉ አሳስቦት ይሆን››
‹‹ የቤቲንግ ሱስ ይዞት ትልቅ ማጥ ውስጥ ገብቶ ነው..አንዱ አበዳሪው ደፍቶት እንዳይሆን››
‹‹ ብዙ ደባል ሱስ አለበት…ከባዱንም ይወስዳል አሉ››
‹‹ለነገሩ ገና በለጋ እድሜው ሃላፊነቱ በዝቶ ጫንቃውን ቢከብደው ምን ይገርማል››
‹‹ምስኪን በቀረበት…››
‹‹ምስኪን ምኑንም አላወቀበት›› እያሉ፡፡


--
አስክሬኑ ሲገኝ የድብደባም ሆነ ሌላ ጉዳት እንዳልደረሰበት ግልጽ ነበር፡፡
ስልኩ አጠገቡ ወድቋል፡፡
የገንዘብ ቦርሳው የጀርባ የሱሪ ኪሱ ውስጥ ከእነ ገንዘቡና የባንክ ኤቲኤም ካርዶቹ ተገኝቷል፡፡

መታወቂያውም አለ፡፡
‹‹ኤርምያስ ምትኩ፡፡ የትውልድ ቀን ጥቅምት 14/1984 ዓ.ም›› የሚልና ሌሎች መረጃዎችን ይዞ፡፡
ሰላሳ ሶስት አመቱ ነበር፡፡ ለቤቱ አስቤዛ ሊገዛ እንደዋዛ ወጥቶ እዚህ ቱቦ ውስጥ ሞቶ ተገኘ፡፡


ፓሊስ ምርመራውን ቶሎ አጠናቀቀ፡፡

የአስክሬን ምርመራው ያልታወቀ የልብ ድካም እንደነበረበት ተናግሯል፤ የሞተውም በዚህ ሳቢያ ነው ብሎ ፋይሉን ዘጋ፡፡

በቤተሰቡ ላይ የወደቀው ሃዘን ከባድ ቢሆንም ፖሊሶችም ሆነ ቤተሰቡ ልብ ያላለው ሃዘኑን ይበልጥ የሚያከብድ ቡጫቂና የተጨማደደ ወረቀት ከጃኬት ኪሱ ተገኝቶ ነበር፡፡
ወረቀቱ ላይ ብዙ በማያምር የእጅ ጽሁፍ የተጻፈ ዝርዝር ነበር፡፡ እንዲህ ይላል፡፡


‹‹ማሬ-
ሁለት ጣሳ የቤቢ ዱቄት ወተት (ደህናውን ግዛ ደግሞ፡፡ አትስቆንቆን )
አንድ ኪሎ ስጋ (አስከትፍልኝ፡፡ ጊዜ የለኝም)
ቤቢ ፓውደር (ቶሎ ቶሎ እያለቀብን ነው፡፡ በዚያ ላይ ዋጋው በየቀኑ ይጨምራል፡፡
(ብሩ ከበቃህ አራት ግዛ )
አሳ ዘይት (ይህንን ከፋርማሲ ግዛ አደራህን የኔ ሰነፍ)
ኢሊፖፕ ለያኔትዬ ግዛላት፡፡ ቀኑን ሙሉ ስትነጫነጭ ነው የዋለችው፡፡

ከዝርዝሩ በኋላ አንድ የሃዘን ማቁን ይበልጥ የሚያጠቁርና የሚያከብድ ቃል አለ፡፡
አጭር ስለሆነ ብዙዎች ላያዩትና ሊያልፉት ይችላሉ፡፡ ላስተዋለው ግን እንዲህ ይላል፤

‹‹እምጳ!››


‹‹አራተኛው ባል››

———————————————-
ከገፋ እድሜዋ ጋር የማይሄደውን ነጻ መንፈሷን የምወድላት አክስቴን ሶስት ጊዜ ባል አግብታ መፍታቷን አስመልክቼ ‹‹ምን አድርገውሽ ነው? እስቲ አንድ በአንድ ንገሪኝ ›› ብዬ አወጣጣኋት፡፡

“እንዲያው ግን አራተኛስ ማግባት አትፈልጊም?” ብዬ ጠየቅኳት፡፡



የሚያምር፣ ካንጀት የሚመነጭ ሳቋን ሳቀችና እንዲህ አለችኝ፡፡


‹‹የመጀመሪያው ባሌ ምስኪን ነበር፡፡ በዚያ ላይ ታማኝ፡፡ ግን ሆዱን ስለሚወድ ከተጋባን ዓመት ሳይሞላን ሁለመናው ጮማ በጮማ ሆነ፡፡ በፊቱንም አጭር ነበር፤ የቁመቱ ነገር እየከነከነኝ ጥሩ ሰው ነው ብዬ ነበር ያገባሁት:: ካለመጠን ሲወፍር ግን ጭራሽ ለመሬት ቀረበ፡፡ ፈታሁት፡፡

ሁለተኛው ተክለ ሰውነቱ የሰጠ፣ ቁመቱ ሰንደቅ የሚያሰቅል ነበር፡፡ ወንድ፣ የወጣለት ወንድ ነበር፡፡ ግን ሲተኛ በሃይል እያንኮራፋ ሰላም ነሳኝ፡፡ በዚያ ላይ ይልከሰከሳል፤ ይባስ ብሎ …የንቀቱ ንቀት ፣ ቡና አጣጭ ጎረቤቴን ሲወሽም ፈታሁት፡፡

ሶስተኛው እንደመጀመሪያው አጭር፣ ወፍራም ነበር፡፡ እሱም ያንኮራፋ ነበር፣ በዚያ ላይ ሌላ ሴት ጋር ይሄዳል፡፡ ጭራሽ በእሱ ብሶ እገሌ አየሽ እያለ ይቀናል፤ ሲጠጣማ ይደበድበኝ ነበር፡፡ ፈታሁት፡፡

አየሽ..እናታችን…አያትሽ.. የመጀመሪያ ባል እንደ ወንድም ነው፣ ሁለተኛው ባል ነው፣ ሶስተኛው ደግሞ ጠላት ነው ትለን ነበር››


‹‹አያቴ ስለ አራተኛ ባልስ ምን ትላችሁ ነበር?›› አልኩ በጉጉት፡፡
‹‹ምንም አላለችንም፡፡ ያው መቼስ ሰው ከጠላቱ ከነነፍሱ ከተፋታ በኋላ ዳግም አያገባም ብላ ይሆናል…የድሮ ሰው እኮ የዋዛ አይመስልሽ…ብዙ ያውቃል፡፡ ለዚያ ነው እኔም አራተኛ ያልሞከርኩት ሃሃሃሃ››


አጅቢያት ሳቅኩና እንዲህ ብዬ ጠየቅኳት-


‹‹ግን እኮ አክስቴ…አራተኛው እንደ መጀመሪያው ባል የወንድም አይነት ቢሆንስ?››
‹‹ከሶስተኛው የባሰ ደመኛዬ ቢሆንስ?›› ቶሎ መለሰችልኝ፡፡

ድጋሚ አብረን ሳቅን፡፡

4.1k 0 14 5 106
Показано 20 последних публикаций.