ትምህርተ ወንጌል


Гео и язык канала: не указан, не указан
Категория: не указана


ኢሳይያስ 43
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ አሁንም ያዕቆብ ሆይ፥ የፈጠረህ፥ እስራኤልም ሆይ፥ የሠራህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤ በስምህም ጠርቼሃለሁ፥ አንተ የእኔ ነህ።
“የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እናንተ ለእኔ #እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን? ይላል እግዚአብሔር። እስራኤልን ከግብጽ ምድር፥ ፍልስጥኤማውያንንም ከከፍቶር፥ ሶርያውያንንም ከቂር አላወጣሁምን?”
— አሞጽ 9፥7

Связанные каналы

Гео и язык канала
не указан, не указан
Категория
не указана
Статистика
Фильтр публикаций


+ የአባቶች ድንቅ ጥበብ የተሞሉ መልሶች +

ባለ ብዙ ታሪኩ የወሊሶው ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ ያጠምቁና ያስተምሩ በነበረበት ሥፍራ አንድ በትዕቢት መንፈስ የሚሰቃይ ወጣት መጣና መፈክርነት ያዘለ ቃል ተናገረ:: ክብር ይግባትና ንግግሩ የድንግል ማርያምን ዘላለማዊ ድንግልና የሚቃወም ነበር::

ወደ አባ ዲዮስቆሮስ ቀርቦ እንዲህ አላቸው :-
ወጣቱ :- "ድንግል ማርያም እኮ ብዙ ልጆች አሉአት"
አቡኑ :- "ባታውቀው ነው እንጂ ለአንተም እኮ እናትህ ናት!"

✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽

የቦሩ ሜዳው መምህር አካለ ወልድ ከሌሎች ሊቃውንት ጋር ኢየሩሳሌምን ሲሳለሙ ድንገት የሌላ ሀገር መነኮሳት መጥተው በዱላ አጣደፉአቸው:: ነገሩን ሲጠይቁ ለምን በእግዚአብሔር ሦስትነት እንደማያምን ሰባልዮሳዊ
አንድ ጣታችሁን ብቻ ወደላይ ጠቁማችሁ ታማትባላችሁ? ለምን እንደ እኛ ሦስት ጣቶቻችሁን (እንደሚጎርስ ሰው) በአንድ ገጥማችሁአታማትቡም?" አሉና በቁጣ ጮኹ::

መምህር አካለ ወልድ በፈሊጥ እንጂ በፍልጥ የሚሆን ነገር ስለሌለ ቁጭ ብለን እንነጋገር አሉ::

"እኛ በአንድ ጣት ብናማትብም ሦስትነቱን እናምናለን:: አንድዋ ጣትም እኮ ሦስት አንጉዋዎች አሉአት:: አንድ መሆንዋ አንድነቱን ሦስቱ አንጉዋ ሦስትነቱን ያስረዳል::
የታችኛው አንጉዋ መሠረት ነውና የወልድ የመንፈስ ቅዱስ መሠረት ይሆነው የአብ ምሳሌ ነው:: የመካከለኛው በሁለቱ ህልው የሆነ የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነው : የላይኛው ጥፍር የለበሰው ደግሞ ባዕድ ሥጋን የተዋሐደ የወልድ ምሳሌ ነው:: ሀገራችሁ ሔዳችሁ አስተምሩበት" አሉአቸው

(ይህ ትርጓሜ በወንጌል አንድምታ ላይ በእግዚአብሔር ጣት አጋንንትን አወጣለሁ የሚለው በተተረጎመበት ሥፍራ ይገኛል)

✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽

ንቡረ ዕድ ክፍለ ዮሐንስን ደግሞ አንድ ወጣት መጥቶ
"ለእግዚአብሔር የአምልኮ ለቅዱሳን የጸጋ ስግደት እንደሚሰገድ አውቃለሁ:: ግን በቅዱሳን ሥዕል ፊትና በፈጣሪ ፊት ስሰግድ እንዴት ለይቼ የጸጋ የአምልኮ እያልኩ መስገድ እችላለሁ?" አላቸው
ንቡረ ዕድ መለሱ
"አንተ ዝም ብለህ ስገድ እነርሱ የድርሻቸውን ይወስዳሉ!"

✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽

አቡነ ሺኖዳ ከሾፌራቸው ጋር ሲሔዱ ሾፌሩ መኪናውን ከመጠን በላይ አበረረው
ፓትርያርኩ እንዲህ አሉ
"ልጄ ስለምንቸኩል ቀስ በል”

✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽

አንድ ታላቅ የጉባኤ መምህር ተጠየቁ
"ካህናት ዶሮና በግ ወዘተ ማረድ የማይችሉት ለምንድን ነው?"
"የክርስቶስን ሥጋና ደም የሚፈትት ካህን እንደ ኦሪት ካህን የእንስሳ ደም አያፈስስም"
"ካህናቱስ መልካም ሴት ልጅስ ማረድ ለምን ትከለከላለች?"
"ሕይወት የምትሠጥ ሴት ሕይወት አታጠፋም"

✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽

አለቃ ለማ ልጃቸውን ለምን በጣም እንደሚገርፉት ተጠየቁ
"ልጄን እኔ ካልቀጣሁት እግዚአብሔር ይቀጣብኛል
የእግዚአብሔር ቅጣት ደግሞ ሞት ነው"

✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽

አንዱ መጥቶ አንድን የመጽሐፍ መምህር
"ጥምቀት ጋድ አለው ወይ?" አላቸው
እርሳቸውም መለሱ
"አምና ነበረው የዘንድሮን እንጃ"

✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽

አቡነ ዮሐንስ አንድን ሥራ ፈቶ የአብነት ተማሪዎችን
ሲማሩ ከሩቅ የሚያይ ወጣት አዩና
"አንተ አትማርም ወይ?" አሉት
"አይ አባቴ ምን እየበላሁ ልማር ብለው ነው?" አለ እየተቅለሰለሰ
አቡኑ መለሱ
"አሁን ምን እየበላህ ነው የምትደነቁረው?"

✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽

አቡነ ጎርጎርዮስ በዝዋይ ሳሉ አንድ ወጣት ሰርቆ ሲያመልጥ አባርረው ይዘው ሰዎች አመጡላቸው
ዕቃው ከተመለሰ በኁዋላ ሌባውን ለሕግ አሳልፈው ሊሠጡ ሲቸኩሉ አይሆንም አሉአቸው:: ሰዎቹ ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኝ ወደ ፖሊስ እንውሰደው አሉአቸው
እርሳቸውም መለሱ
"ኦርቶዶክሶች ተሰራርቀው ተካስሰው መጡ ከሚል ስም ውጪ ምንም አናተርፍም"

✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽

ብፁዕ አቡነ ሰላማን አንዱ ባለ ሥልጣን ጉዳይ ሊያስፈጽሙ በሔዱበት ቢሮው "አንተ" ብሎ በማናገር ሊያቃልላቸው ሞከረ::
እርሳቸው እንዲህ አሉት
"የቤተ ክርስቲያኔን ጉዳይ ፈጽምልኝ እንጂ እንኩዋን አንተ ቀርቶ አንቺም ብለህ ጥራኝ

✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽

የደርግ መንግሥት እንዳሻው ሊዘውራቸው ተስፋ ያደረገባቸው ፓትርያርክ አቡነ ተክለ ሃይማኖትን በመሪው አማካኝነት እንዲህ ሲል ጠየቃቸው
"የቅድስት ሥላሴ ካቴድራልን ወደ ሙዝየምነት የመቀየር ሃሳብ በመንግሥት በኩል ተይዞአል:: ይህንን ለማድረግም የእርስዎን ድጋፍ የግድ ነው"
ፓትርያርኩ መለሱ
"ምን ችግር አለ በቅርቡ የዓመቱ ሥላሴ ክብረ በዓል ስላለ ሕዝቡ ባለበት እናንተም ተገኝታችሁ አብረን ለምን አናወያየውም"
በዚህ ምላሽ ምክንያት እቅዱ ተሠረዘ

✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽✍🏽

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ


++ የአዲስ ዓመት ሥነጹሑፍ !!

( ይችን ዓመት ተወኝ ! )

ከዓመት እስከ አመት ፍሬን ሳላፈራ ደረቅ እንደሆንኩኝ፤
በራድ ወይም ትኩስ ሁለቱንም ሳልሆን እንዲያው ለብ እንዳልኩኝ፤
አለሁኝ በቤትህ ለሙን መሬትህን እያጎሳቆልኩኝ፤
አውቃለሁ አምላኬ ፍሬየን ለመልቀም እንዳመላለስኩህ፤
ዛሬም ሳላፈራ እሾህን አብቅየ ደርቄ ጠበኩህ ፤
ያልተደረገልኝ ያላፈሰስክብኝ ያልሰጠኸኝ የለም፤
ነገር ግን ይህ ሁሉ አላርምህ አለኝ አልለየኝም ከአለም።
የማትሰለቸኝ ሆይ ተነስቼ እስክቆም እባክህ ታገሰኝ፤
የኔን ክፋት ተወዉ መልአክህን ሰምተህ ይችን ዓመት ተወኝ።

አውቃለሁ ታውቃለህ ቀጠሮን ሰጥቼ እንደማላከብር፤
ብዙ ግዜ አቅጄ ብዙ ጊዜ ዝቼ በወሬ እንደምቀር።
ዘንድሮስ እንዳልኩኝ አምና ይኸ ጊዜ ሰምተኸኝ ነበረ፤
ምንም ሳልለወጥ ዘንድሮየ አልፎ ባዲስ ተቀየረ ።
ፍሬ የማይወጣኝ እኔን በመኮትኮት እጆችህ ደከሙ፤
እኔ ግን አለሁኝ ዛሬም አልበቃኝም በኃጢአት መታመሙ።
የቃልህን ውሐ በድንጋይ ልጅህ ላይ ሳትታክት ስታፈስ ዘመን ተቆጠረ፤
ወደልቤ ሳይሰርግ ህይወቴን ሳይለውጥ እንዲያው ፈስሶ ቀረ።
ቃልህን ጠግቤ እያገሳሁት ነው ሌሎች እስኪሰሙ፤
በቃልህ መኖር ግን አልያዝህ አለኝ ከበደኝ ቀለሙ።
ብዙ ጥቅስ አገኝሁ ከቅዱስ መጽሐፍህ ገልጬ አይቼ፤
ከራሴ ላይ ብቻ አንድ ጥቅስ አጣሁንኝ በበደል ተኝቼ ።
ውጤቴ ደካማ ትምህርት የማይሰርጸኝ ተማሪ ብሆንም፤
ይችን ዓመት ተወኝ ተደግሞ ትንሽ ልማር ታገሰኝ አሁንም።

እባክህ አልቆረጥ በቅዱስ መሬትህ ልቆይ ፍቀድልኝ፤
ያፈሩት ቅዱሳን የፍሬያቸው ሽታ መአዛ እንዲደርሰኝ።
የተሸከምከኝ ሆይ ዛሬም ተሸከመኝ አትሰልቸኝ አደራ፤
ማን ይታገሰኛል ጠላት እየሆንኩት እየሰሩ ስሰራ።
አታውጣኝ ከቤትህ ብዙ ቦታ አልይዝም ፍሬ ስለሌለኝ፤
ስፍራ የማያሻኝ ቤት የማላጣብብ ፍሬ አልባ በለስ ነኝ።
ቦታ የሚይዙት ባለምግባሮቹ ቅዱሳንህ ናቸው፤
ልክ እንደዘንባባ የተንዠረገገ ተጋድሎ ጽድቃቸው ።
ከሊባኖስ ዝግባ እጅጉን የበዛ ገድል ትሩፋታቸው፤
እኔ አይደለሁም ቦታስ የምትይዘው የአንተው እናት ናት፤
ስሮቿ በምድር ጫፎቿ በሰማይ ሲደርሱ ያየናት፤
ይችን አመት ተወኝ ከስሯ እሆናለሁ ባፈራ ምናልባት፤
ይቺን ዓመት ተወኝ እባክህ አምላኬ አንድ ዓመት ምንህ ናት፤
ሺህ ዓመት አንድ ቀን አይደለም ወይ ላንተ ዓመት ኢምንትህ ናት።
ይኸ ዓመት አልፎ ደግሞ ዓመት ስጠኝ እስከምልህ ድረስ፤
እባክህ ጌታየ ይችን ዓመት ተወኝ የወጉን እንዳደርስ።

ጸሐፊ - (ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ)


+ አባቶቻችን እንዲህ አሉ +

"በኃጢአት በወደቅህ ጊዜ ተስፋ ቆርጠህ ጸሎትህን እንዳታቆም። ንስሓ እስከምገባ ድረስ ብለህ ጸሎት ካቆምክ መቼም ንስሓ አትገባም። ምክንያቱም ጸሎት ራሱ የእውነተኛ ንስሓ መግቢያ በር ነው" ቅዱስ ቄርሎስ ሳድሳዊ

"ሰዎች አንድ ሰው ተነሥቶ ሌላውን ሲገድል ወንጀለኛ ነህ ይሉታል። አንድ ላይ ተሰባስበው ብዙ ሰዎችን ሲገድሉ ግን ውጊያ ይሉትና መግደላቸውን ጀግንነት ይሉታል" ቅዱስ ቆጵሮሳዊ

"ሰዎች የሚያብዱበትና እንደነሱ ያላበደ ሰው ሲያዩ "እንደኛ ስላልሆንክ አብደሃል" የሚሉበት ዘመን ይመጣል"
ቅዱስ እንጦንዮስ

"መካሪ አያስፈልገኝም የማለትን ያህል ታላቅ ትዕቢት የለም"
ቅዱስ ባስልዮስ

"ይህንን ካስታወስክ በሰው መፍረድ ታቆማለህ:: ይሁዳ ሐዋርያ ነበር:: ከጌታ ቀኝ የተሰቀለው ወንበዴ ነፍሰ ገዳይ ነበር" ቅዱስ ዮሐንስ ዘሰዋስው

"የክርስቲያኖች መሣሪያ በእጃቸው ሰይፍን መታጠቅ ሳይሆን እጃቸውን ወደላይ ለጸሎት መዘርጋት ነው"
ቅዱስ አትናቴዎስ ዘእስክንድርያ

"እግዚአብሔር ለአብርሃም "ከሀገርህ ውጣ ከወገኖችህ"ተለይ ብሎት ነበር። በዚህ ጥሪ እግዚአብሔር ሁላችንንም የተወለድንበት ዘር እንድንተው ይጠራናል። ሰማዕቱ ዮስጦስ (100 AD-165 AD)

"ክርስቶስ ጴጥሮስን "ሰይፍህን ወደ ሰገባው አስገባ" ሲለው ትጥቅ ያስፈታው ጴጥሮስን ብቻ ሳይሆን እንደ ጴጥሮስ በእርሱ የሚያምኑትን ሁሉ ነበር" ሊቁ ጠርጡለስ

‹‹ይጸልያል ነገር ግን የሌሎችን ጸሎትም ይሰማል፡፡ ያለቅሳል የሌሎችን ዕንባ ግን ያብሳል፡፡ ሰው ነውና አልዓዛር ወዴት እንደተቀበረ ጠየቀ፡፡ አምላክ ነውና አልዓዛርን ከሞት አስነሣ፡፡ እርሱ በርካሽ ዋጋ ያውም በሠላሳ ብር ብቻ ተሸጠ፡፡ ነገር ግን ዓለምን በውድ ዋጋ በከበረ ደሙ ገዛ፡፡ እንደ በግ ለመታረድ ተነዳ እርሱ ግን የእስራኤል እረኛ የዓለምም ሁሉ ጠባቂ ነበረ፡፡ እንደ በግ ዝም አለ ነገር ግን እርሱ በምድረ በዳ በሚጮኽ ሰው ድምፅ የተሰበከ ቃል ነበር፡፡ እርሱ የተሰቃየና የቆሰለ ነበር ፤ ሁሉንም በሽታና ቁስል ግን ይፈውስ ነበር›› ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ

"ለቤተ መቅደስህ ተክል ያደረግኸኝ፡፡ አቤቱ ሆይ የውጭ ተክል አታድርገኝ፡፡ የጽድቅ ተክል አድርገኝ፡፡ የኃጢአት አይደለም፡፡ የዕውነት ተክል አድርገኝ የሐሰት አይደለም የፍቅር ተክል አድርገኝ የጽል አይደለም፡፡

የመጻሕፍት መጀመሪያ የምትሆን ኦሪት ደመና የምትጋርደኝ፡፡ ከቅዱስ ወንጌል ፈሳሽ የምጠጣ ከጎንህ ከፈሰሰው ደም የምረካ ልሁን፡፡ በናትህ በድንግል ጸሎት የሃይማኖት አበባ ላብብ፡፡ የጽድቅ ፍሬን ላፍራ ከቅዱሳንህ ሐዋርያትም ከቃላቸው ፍሬ የተነሣ እስከ ዘለዓለሙ ድረስ የተባረከ የወይን ቦታ ልባል የጽድቅን ፍሬ የሚያስቀረውንም የኃጢአት እሾህ ጠምዝዘው ከደጁም አሜከላውን አረሙንም ሙጃውንም ንቀለው፡፡ አቤቱ ከኔም አርቀው ሥርዓትህን የሚሠሩትን ያበባቸውን ፍጻሜ እንዳፈራ አድርገኝ" ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ግንቦት 26 2011
ጅማ ፣ ኢትዮጵያ


+ እኔ ግን እኔ አይደለሁም +

አውግስጢኖስ ፈጣሪ የለም ባይ እና በዝሙት የተበላሸ ሕይወት ይኖር የነበረ ሰው ነው:: በቅዱስ አምብሮስ ስብከት ከተመለሰ በኁዋላ ግን ይህ ሰው ፍጹም በንስሓ ተለውጦ በምንኩስና መንገድ ሔዶ እስከ ጵጵስና ደረሰ:: ይህንን የንስሓ ሕይወት መኖር ከጀመረ በኁዋላ ቀድሞ በአመንዝራነት ሕይወት ሲኖር ወዳጁ የነበረች አንዲት ሴት መንገድ ላይ ከሩቅ አይታ ተከትላ ጠራችው::
ወደ ቀድሞ ትዝታውና ኃጢአቱ መመለስ ያልፈለገው ይህ አባትም ጥሪዋን እንዳልሰማ ሆኖ በፍጥነት መሔድ ጀመረ::
ይህች ሴትም እየሳቀች :-
አውግስጢኖስ እኔ እኮ ነኝ! ብላ ጮኸች

እርሱም ወደ እርስዋ ዞሮ :- "እኔ ግን እኔ አይደለሁም" አላት::

ክርስትና የወደቀ የሚነሣበት የረከሰው የሚነጻበት ሕይወት ነው:: በዚህ መስመር ያለፉ ሁሉ ትናንትን እየተዉ ሌላ ማንነትን ይለብሳሉ:: ትልቁ ፈተና ሰዎች ተነሥተህ እያዩህም እንኩዋን መውደቅህን አለመርሳታቸው ነው:: ፈጣሪ "ከእንግዲህ አትበድል" ብሎ ይቅር ቢልህም ሰዎች ግን ይቅር አይሉህም:: "ድመት መንኩሳ ዓመልዋን አትረሳ" እያሉ እየተረቱ ወደ ነበርክበት እንድትመለስ ይገፉሃል እንጂ እንድትለወጥ አይፈቅዱልህም::

ሳውል አሳዳጅ ነበረ ዛሬ ግን ሐዋርያ ነው:: ብዙ ክርስቲያኖች ግን እርሱን ለማመን ተቸግረው ነበር:: ከመመረጡ ጀምሮ "ኸረ እርሱ አይሆንም" ብለው ለፈጣሪ ምክር የሠጡም ነበሩ:: ከተመረጠ በኁዋላም ለመቀበል ተቸግረው ከሐዋርያት አሳንሰው ያዩት አልጠፉም:: እርሱም በትሕትና "ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ" ቢልም : "ጭንጋፍ" ብሎ ራሱን ያለ ጊዜው ከሚወለድ ጽንስ ጋር አነጻጽሮ ዘግይቶ የተጠራ መሆኑን ቢናገርም ከሐዋርያት በምንም የማያንስ ሐዋርያ ነበረ:: እነርሱ በትናንት ማንነቱ ሊያዩት ቢሹም እርሱ ግን "እርሱ አልነበረም" እርሱ መኖር አቁሞ በእርሱ ይኖር የነበረው ክርስቶስ ነበረ::

አንዳንድ ሰዎች የማያምኑህ ከክፋት ተመልሰህ መልካም ስትሆን ብቻ አይደለም:: በጣም መልካም ስትሆንላቸውም አያምኑህም:: ስታከብራቸው ምን አስቦ ነው? ብለው ይጠራጠራሉ:: መልካም ስታደርግላቸው "ምነው ደግነት አበዛሽ? ተንኮል አሰብሽ እንዴ? "ይህቺ ጠጋ ጠጋ ዕቃ ለማንሳት ነው" "there is no free lunch” ብለው ሊሰጉ ይችላሉ:: መልካም የሚያደርግላቸውን ሁሉ ሊያርድ የሚያሰባቸው የሚመስላቸው ሰዎች አሉ:: ፍቅር የትግል ስልት የሚመስላቸው ጨብጠውህ ጣታቸው እንዳልጎደለ የሚቆጥሩ ዓይነት ተጠራጣሪ ሰዎች አሉ::

ዮሴፍ የገጠመው ይህ ነበር:: በሃያ ብር ሸጠው ግብፅ ያወረዱት ወንድሞቹን ይቅር ብሎ በፍቅር ተቀበላቸው:: አባታቸውን ያዕቆብን አስመጥቶ በክብር በግብፅ እንዲኖሩ አደረጋቸው:: ከዓመታት በኁዋላ አረጋዊው ያዕቆብ ሞተ::
ይሄን ጊዜ የዮሴፍ ወንድሞች ድንገት ስብሰባ አደረጉ: "አባታችን ከሞተ በኁዋላ ቢበቀለንስ?!" ብለው ስጋታቸውን ተመካከሩ::
ስለዚህ ዶልተው መጡና እንዲህ አሉት :-
አባታችን ከመሞቱ በፊት እንዲህ ሲል ተናዝዞ ነበር:: እባክህን የወንድሞችህን በደል ይቅር በል:: (ዘፍ 50:15-21) ዮሴፍ ይኼን ሲሰማ አለቀሰ:: ይቅርታን አድርጎም አለመታመኑ አመመው::

እርሱ ለእነርሱ ድሮም ክፉ አልነበረም:: አሁን ደግሞ ላደረሱበት በደል እንኩዋን ፈጣሪውን የሚያመሰግን ሆኖአል:: "እናንተ ክፉ ነገርን አሰባችሁብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደ ሆነው ብዙ ሕዝብ እንዲድን ለማድረግ ለመልካም አሰበው" ነበር ያለው:: ምንም በደል ቢደርስበት እነርሱ አልተለወጡ ይሆናል እንጂ እርሱ ግን ትናንት የሚያውቁት ዮሴፍ አይደለም:: "እኔ ግን እኔ አይደለሁም" አላቸው::

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ታኅሣሥ 30 2012 ዓ ም
አዲስ አበባ


1ኛ ዮሐንስ 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ወዳጆች ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና።
² የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደ መጣ የሚታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፥
³ ኢየሱስ ክርስቶስም በሥጋ እንደ መጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም፤ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚው መንፈስ ነው፤ ይህም እንዲመጣ ሰምታችኋል፥ አሁንም እንኳ በዓለም አለ።
⁴ ልጆች ሆይ፥ እናንተ ከእግዚአብሔር ናችሁ አሸንፋችኋቸውማል፥ በዓለም ካለው ይልቅ በእናንተ ያለው ታላቅ ነውና።
⁵ እነርሱ ከዓለም ናቸው፤ ስለዚህ ከዓለም የሆነውን ይናገራሉ ዓለሙም ይሰማቸዋል።
⁶ እኛ ከእግዚአብሔር ነን፤ እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይሰማናል፤ ከእግዚአብሔር ያልሆነ አይሰማንም። የእውነትን መንፈስና የስሕተትን መንፈስ በዚህ እናውቃለን።
⁷ ወዳጆች ሆይ፥ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ፥ የሚወደውም ሁሉ ከእግዚአብሔር ስለ ተወለደ እግዚአብሔርንም ስለሚያውቅ፥ እርስ በርሳችን እንዋደድ።
⁸ ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና።
⁹ በዚህ የእግዚአብሔር ፍቅር በእኛ ዘንድ ተገለጠ፥ በእርሱ በኩል በሕይወት እንኖር ዘንድ እግዚአብሔር አንድ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታልና።
¹⁰ ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም።
¹¹ ወዳጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ አድርጎ ከወደደን እኛ ደግሞ እርስ በርሳችን ልንዋደድ ይገባናል።
¹² እግዚአብሔርን ማንም ከቶ አላየውም፤ እርስ በርሳችን ብንዋደድ እግዚአብሔር በእኛ ይኖራል ፍቅሩም በእኛ ፍጹም ሆኖአል።
¹³ ከመንፈሱ ስለ ሰጠን፥ በእርሱ እንድንኖር እርሱም በእኛ እንዲኖር በዚህ እናውቃለን።
¹⁴ እኛም አይተናል አባትም ልጁን የዓለም መድኃኒት ሊሆን እንደ ላከው እንመሰክራለን።
¹⁵ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በሚታመን ሁሉ እግዚአብሔር በእርሱ ይኖራል እርሱም በእግዚአብሔር ይኖራል።
¹⁶ እኛም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር አውቀናል አምነንማል። እግዚአብሔር ፍቅር ነው፥ በፍቅርም የሚኖር በእግዚአብሔር ይኖራል እግዚአብሔርም በእርሱ ይኖራል።
¹⁷ በፍርድ ቀን ድፍረት ይሆንልን ዘንድ ፍቅር በዚህ ከእኛ ጋር ተፈጽሞአል፤ እርሱ እንዳለ እኛ ደግሞ እንዲሁ በዚህ ዓለም ነንና።
¹⁸ ፍጹም ፍቅር ፍርሃትን አውጥቶ ይጥላል እንጂ በፍቅር ፍርሃት የለም፥ ፍርሃት ቅጣት አለውና፤ የሚፈራም ሰው ፍቅሩ ፍጹም አይደለም።
¹⁹ እርሱ አስቀድሞ ወዶናልና እኛ እንወደዋለን።
²⁰ ማንም፦ እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል?
²¹ እግዚአብሔርንም የሚወድ ወንድሙን ደግሞ እንዲወድ ይህች ትእዛዝ ከእርሱ አለችን።


+ የተቀደሰው የሩጫ ውድድር +

እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሩጫ ብሔራዊ ኩራት በሆነበት ሀገር መቼም የሩጫ ነገር ብናወራ ሰሚ አናጣም:: ሮጦ ሀገር ማስጠራት : ሮጦ ብዙ ሀብት ማፍራትና ለሀገር መትረፍ የቻሉ ውድ አትሌቶቻችንን በፍቅር እናያቸዋለን:: "በእሽቅድምድም ስፍራ የሚሮጡት፥ ሁሉ እንዲሮጡ ነገር ግን አንዱ ብቻ ዋጋውን እንዲቀበል አታውቁምን? እንዲሁም ታገኙ ዘንድ ሩጡ" የሚለው ቅዱስ ቃል ለነፍስ ቢነገርም ኢትዮጵያ ውስጥ ግን "ታገኙ ዘንድ ሩጡ" የሚለው መርሕ "ሮጬ ባለፈልኝ" በሚሉ ተስፈኞች ይተገበራል:: (1ቆሮ 9:24)

ዛሬ ግን በሁለት ሰዎች መካከል የተደረገ ቅዱስ ሩጫ ትዝ አለኝ:: በትንሣኤ ዕለት የተደረገ ቅዱስ እሽቅድምድም በዓይነ ሕሊናዬ መጣ::
ከዓሥራ ሁለቱ ሐዋርያት መካከል ሁለቱ የተሳተፉበት ዳኛም ተመልካችም የሌለበት የትንሣኤ ዕለት ሩጫ!!!

ሴቶች ወደ ጌታ መቃብር ደርሰው ሲመለሱ ጌታ በመቃብር እንደሌለ ለደቀ መዛሙርቱ ነገሩአቸው::
ስለዚህ ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ መቃብሩ ሔዱ::

"ሁለቱም አብረው ሮጡ፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ከጴጥሮስ ይልቅ ፈጥኖ ወደ ፊት ሮጠና አስቀድሞ ከመቃብሩ ደረሰ" ዮሐ 20:4

በዚህ ቀን በተደረገው ቅዱስ ሩጫ የ58 ዓመቱ ጎልማሳ ጴጥሮስ ከ28 ዓመቱ ወጣት ዮሐንስ ጋር ወደ ጌታ መቃብር ሮጡ:: ሐሙስ ማታ ጌታውን የካደው ጴጥሮስ እስከ መስቀል ድረስ ጌታውን ከተከተለው ዮሐንስ ጋር አብሮ ወደ መቃብሩ ሮጠ::

ጴጥሮስ ሆይ ወደ ጌታህ መቃብር በሩጫ ስትገሰግስ ምን እያሰብህ ይሆን? ሐሙስ በካድከው ጊዜ ቀና ብለው ያዩህ ዓይኖቹ በሕሊናህ መጥተው ይሆን?
ወደ መቃብሩ ስትሮጥ "ጌታ ሆይ በአፌ ክጄሃለሁ በእግሮቼ ግን አልክድህም" ብለህ አስበህ ይሆን? "በባሕር ላይ ያራመድኸው እግሬ : አጎንብሰህ ያጠብከው እግሬ ወደ አንተ ለመሮጥ አይደክመውም" ብለህ ይሆን? መቃብሩ ሥር ተደፍተህ ለማልቀስ የሐሙሱን ዕንባህን በመግነዙ ለማበስ አስበህ ይሆን?

ብቻ ጴጥሮስ ከዮሐንስ ጋር ወደ መቃብሩ ሮጠ:: ዮሐንስ በጉልበቱ ገና ወጣት ቢሆንም : እንደ ጴጥሮስ ጸጸት የማይቆጠቁጠው ድል አድራጊ ቢሆንም ጴጥሮስ አብሮ ከመሮጥ ወደኁዋላ አላለም::

ብቻ መቃብሩ ልድረስ እንጂ ቢቀድመኝም እከተለዋለሁ:: እንደርሱ እስከ መስቀል ባልጸናም ለመቃብሩ ግን ዳግም እታገላለሁ ብሎ ጴጥሮስ ሮጠ::

በዚህ ቅዱስ ሩጫ አርብ የወንድ ለቅሶን ያፈሰሰው ዮሐንስ በዕንባ በደከሙ ዓይኖቹ በኀዘን በጠቆረ ፊቱ እያማተረ ወደ ጌታ መቃብር ገሠገሠ:: በዚያች ዕለት ጌታን እንዴት እንደ ገረፉት አይቶአል:: እንዴት እንደ ቸነከሩት ተመልክቶአል:: አሁን ደግሞ መስቀል ሥር ቆመው በዋሉ እግሮቹ ወደ መቃብሩ እየሮጠ ነው::

ወንድሜ ሆይ ጴጥሮስና ዮሐንስን ወደ ጌታ መቃብር ሲሮጡ እያቸው:: አንተና ጉዋደኞችህስ ወዴት ትሮጣላችሁ? የእናንተ እሽቅድምድም ወደ ጌታ መቃብር ነው? የት ለመሔድ ትፎካከራላችሁ? የት እንገስግስ ትባባላላችሁ?

ወጣቱ ዮሐንስ ጎልማሳውን ጴጥሮስን ቀድሞ ከጌታ መቃብር ደረሰ:: የጌታን መግነዝም አየ:: ወደ ውስጥ ግን ሳይገባ ቆሞ ጴጥሮስን ጠበቀው:: ጴጥሮስ ዘግይቶ ቢደርስም ከዮሐንስ ቀድሞ ወደ መቃብሩ ገባ::

ከእኔ የበረታ መንፈሳዊ ጉልበት ያለህ ወንድሜ ሆይ ብትቀድመኝ እንኩዋን አትፍረድብኝ:: ጨክነህ ጥለኸኝ ወደ ጌታ ማረፊያ እንዳትገባ:: የዘገየሁት ኃጢአት እግሬን አስሮት ነውና ብርቱው ወንድሜ ሆይ እባክህን ጠብቀኝ:: ድክመቴን አይተህ አትናቀኝ መጎተቴን አይተህ አትፍረድብኝ:: አደራህን ብቻህን ወደ ጌታ ደስታ እንዳትገባ:: አደራህን በንስሓ እስክበረታ ጠብቀኝ:: እንኩዋን አንተ አብረኸኝ ሩጫ የጀመርክ ወንድሜ ቀርቶ ከእኔ ቀድመው ሩጫቸውን የጨረሱት እንኩዋን ብቻቸውን ወደ ዘላለማዊ ደስታ እንዳይገቡ በገነት ሆነው እኔን ይጠብቁኝ የለ?

ነቢዩ እንደተናገረ :-
አቤቱ፥ ስምህን አመሰግን ዘንድ፤
ነፍሴን ከወህኒ አውጣት፤
ዋጋዬን እስክትሰጠኝ ድረስ፡
ጻድቃን እኔን ይጠብቃሉ። (መዝ 142:7)

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ግንቦት 16 2013 ዓ.ም.
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ


የደብረ ታቦር/ቡሄ በዓል

ደብረ ታቦር ወይንም ቡሄ በመላው ሀገራችን በየዓመቱ ነሐሴ ፲፫ ቀን የሚከበር በዓል ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከምታከብራቸው ዓቢይ (ዋና) በዓላት አንዱ ይሄ 'ደብረ ታቦር' የምትለው የቡሄ በዓል ነው። የዚህ በዓል መሠረት የክርስቲያን እምነት ሲሆን፣ ደብረ ታቦር በግዕዝ የታቦር ተራራ ማለት ነው፡፡ የታቦር ተራራ የሚገኘው አሁን ፍልስጥኤም ተብሎ በሚጠራው ሀገር ነው፡፡ ደብረ ታቦር ወይንም የታቦር ተራራ ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስት ደቀመዛሙርቱን ይዞ ወደ ተራራው የወጣበትና ፊቱ እንደፀሐይ የበራበት ልብሱም እንደብርሃን ነጭ የሆነበት ቦታ ነው፡፡ ይህ ቦታ ጌታ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት ተራራ ነው። የማቴዎስ ወንገል ምዕራፍ ፲፯፦ ቁጥር ፩ እስከ ፭ " ከስድስት ቀንም በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስንና ያዕቆብን ወንድሙንም ዮሐንስን ይዞ ወደ ረጅም ተራራ ብቻቸውን አወጣቸው። በፊታቸውም ተለወጠ፥ ፊቱም እንደ ፀሐይ በራ፥ ልብሱም እንደ ብርሃን ነጭ ሆነ። እነሆም፥ ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። ጴጥሮስም መልሶ ኢየሱስን ጌታ ሆይ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነው፤ ብትወድስ፥ በዚህ ሦስት ዳስ አንዱን ለአንተ አንዱንም ለሙሴ አንዱንም ለኤልያስ እንሥራ አለ። እርሱም ገና ሲናገር፥ እነሆ፥ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፥ እነሆም፥ ከደመናው። በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።" ዓቢይ መሠረቱ ይሄ ሲሆን፣ በአገራችን የክረምቱ አፈና ተወግዶ የብርሃን ወገግታ የሚታየውም በዚህ በዓል አካባቢ ስለሆነ ይቺ ዕለት 'ቡሄ' የሚለውን ስያሜ አገኘች። ቡሄ ማለት ገላጣ፣ የተገለጠ ማለት ነው፡፡ በገጠርም ሆነ በየከተማው ልጆች ጅራፋቸውን ገምደው ሲያጮሁ (ሲያኖጉ) ይሰነብታሉ። እናቶችም ለበዓሉ ዝግጅት ስንዴ ሲለቅሙ፣ ሲፈትጉ፣ ሲፈጩ ይሰነብታሉ። ጌታችን ብርሃነ መለኮቱን በገለጠበት ዕለት ጊዜው ምሽት ነበር፡፡ እረኞችም ከብርሃኑ የተነሣ እየተገረሙና እየተደነቁ ወደ ቤት አልተመለሱም ነበር፡፡ የልጆቹን መዘግየት ያዩ ወላጆች ችቦ አብርተውና ዳቦ ይዘው ፍለጋ ወጡ፡፡ ታዲያ ያንን ማስታወሻ «ቡሄ» ለሚሉ ልጆች ሙልሙል ዳቦ የሚሰጠውና ችቦ በማብራት በዓሉን የምናከብረውም ከዚህ በመነሣት ነው፡፡
ከበዓሉ ረድኤት በረከትይክፈለን አሜን!!!


መዝሙር 28
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ አቤቱ፥ ወደ አንተ እጠራለሁ፤ ዝም ብትለኝ ወደ ጓድጓድ እንደሚወርዱት እንዳልመስል፥ አንተ አምላኬ፥ ዝም አትበለኝ።
² ወደ መቅደስህ ማደሪያ እጄን ባነሣሁ ጊዜ፥ ወደ አንተ የጮኽሁትን የልመናዬን ቃል ስማ።
³ ከኃጥኣንና ከክፉ አድራጊዎች ጋር ነፍሴን አትውሰዳት፤ ክፋትም በልባቸው እያለ ከባልንጀራቸው ጋር ሰላም ከሚናገሩት ጋር አትጣለኝ።
⁴ እንደ ሥራቸው እንደ አካሄዳቸውም ክፉት ስጣቸው ፤እንደ እጃቸውም ሥራ ስጣቸው፤ ፍዳቸውን ወደ ራሳቸው መልስ።
⁵ ወደ እግዚአብሔር ሥራ ወደ እጆቹም አደራረግ አላሰቡምና ያፈርሳቸዋል እንጂ አይሠራቸውም።
⁶ የልመናዬን ቃል ሰምቶኛልና እግዚአብሔር ይመስገን።
⁷ እግዚአብሔር ኃይሌና ጋሻዬ ነው፤ ልቤ በእርሱ ታመነ እኔም ተረዳሁ፤ ሥጋዬም ደስ ይለዋል፥ ፈቅጄም አመሰግነዋለሁ።
⁸ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ኃይላቸው ነው፥ ለቀባውም የመድኃኒቱ መታመኛ ነው።
⁹ ሕዝብህን አድን፥ ርስትህንም ባርክ ጠብቃቸው፥ ለዘላለሙም ከፍ ከፍ አድርጋቸው።


+ ጌታ ሆይ ይህን ውኃ ሥጠኝ +

ሳምራዊትዋ ሴት በጠራራ ፀሐይ ውኃ ልትቀዳ እንስራዋን ይዛ ከጉድጓድ አጠገብ ተቀምጣለች፡፡ በጠዋት ወይም በማታ ውኃ መቅዳት ስትልችል ፀሐይ አናት በሚበሳበት በስድስት ሰዓት መምጣት እንዴት ልትመርጥ ቻለች? ከጎረቤቶችዋ ጋር እየተጫወተች አብራ ቀድታ መመለስ አትችልም ነበር? ብቻዋን ለመቅዳት ለምን ፈለገች? ከሰው ፀሐይ ያስመረጣት ምንድነው? ዝርዝሩን እርስዋ ናት የምታውቀው፡፡ አምስት ባሎች የነበሩዋት እና አሁንም ባልዋ ካልሆነ ሰው ጋር የምትኖር ሴት መሆንዋ ግን ተጽፎአል፡፡ ለብዙ ወንዶች ሚስት በሆነች ቁጥር ስለራስዋ የሚኖራት ግምት እየወረደ መምጣቱ አይቀርም፡፡ በተደጋጋሚ አልሳካ ባላት ትዳር ምክንያት ልብዋ እየቆሰለ ተስፋ እየቆረጠች ሁሉን ነገር እየጠላች መምጣትዋ አይቀርም፡፡ እርስዋ ስላልተሳካው ትዳርዋና አሁንም ባልዋ ካልሆነ ሰው ጋር ስለመኖርዋ ሰዎች የሚያወሩት ግን ብዙ ነው፡፡ የእርስዋን ሕመም ሳይረዳ እንደ ርካሽ የሚቆጥራት ፣ ዝሙተኛ አድርጎ የሚያስባት ፣ ዕድለ ቢስ አድርጎ የሚፈርጃት በንቀት በአሽሙር ባለ አምስት ባሎች አድርጎ የሚነቁራት ሰው አይጠፋም፡፡ በግልጥ ባይነግሯትም በአስተያየት በአነጋገር የሚያሳቅቋት አይጠፉም፡፡ ስለዚህ ከሰው አፍ ፀሐይ ይሻለኛል ብላ መጣች፡፡ ሰዎች በነገር ከሚጠብሱኝ በፀሐይ ብትጠብሰኝ ይሻለኛል ብላ በበረሃማው ምድረ በዳ በአጉል ሰዓት ይህች ተስፋ ያጣች ምስኪን ውኃ ልትቀዳ ሔደች፡፡

“ኢየሱስም በሰማርያ ሊያልፍ ግድ ሆነበት” እርግጥ ነው ከይሁዳ ወደ ገሊላ ለመሔድ በሰማርያ ማለፍን መልክዓ ምድሩ ያስገድዳል፡፡ ክርስቶስ ግን ግድ የሆነበት በመልክዐ ምድሩ ብቻ አልነበረም፡፡ የጠፋውን የሰው ልጅ ሊያድን የመጣው መድኃኒት እርሱ ነውና አንዲትን በፀሐይ የምትለበለብ ነፍስ ፍለጋ ሊሔድ ግድ ሆነበት፡፡ ከሰው ሸሽታ ምድረ በዳ የመረጠችውን ተስፋ የቆረጠች ሴት የአሕዛብ ተስፋ ክርስቶስ ሊፈልጋት ተገኘ፡፡

ወደ እርስዋ ቀርቦ ውኃ አጠጪኝ አላት ፤ አባ ጊዮርጊስ ‘’አንተ የሕይወት ውኃ ስትሆን ከሳምራዊትዋ ሴት ውኃን ለመንህ ‘’ እንዳለ የሕይወት ውኃ ክርስቶስ ውኃ ለመናት፡፡ እርሱ የተጠማው ውኃ ሳይሆን የእርስዋን ነፍስ ነበረ፡፡

እርስዋም አንተ አይሁዳዊ ስትሆን ሳምራዊት ከምሆን ከእኔ ውኃ ትለምናለህ? አለችው፡፡ እንዲህ ነው ነገሩ፡፡ የቆሰለች ነፍስ ስለ ዘር ታወራለች፡፡ ተስፋ የቆረጠች ነፍስ የዘር ጉዳይ ሲሆን ልሳንዋ ይከፈታል፡፡ ውኃ ለማጠጣት ዘር መጠየቅን ምን አመጣው፡፡ ውኃው አይሁዳዊ ነው? ወይንስ ሳምራዊ? ውኃ ጠማኝ የሚል ሁሉ ውኃ ይገባዋል እንጂ ዘሩ አይጠየቅም፡፡ እርስዋ ግን ጠየቀችው፡፡ በእርግጥ ይህች ሳምራዊት ሴት ይህን ጥያቄ የጠየቀችው ክርስቶስ መሆኑን ከማወቅዋ በፊት ነበር፡፡ ክርስቶስ መሆኑን ካወቀች በኋላ ግን ስለ አይሁዳዊነትና ስለ ሳምራዊነት ስትናገር አልተሰማችም፡፡ ‘’አንተ አማራ ስትሆን ጉራጌ ከምሆን ከእኔ ውኃ ለምን ትለምናለህ?’’ ‘’አንቺ ኦሮሞ ስትሆኚ ትግሬ ከምሆን ከእኔ እንዴት ውኃ ትለምኛለሽ?’’ በሚል ጥያቄ ሀገሩን ያጨናነቁተ ክርስቶስን ያወቁ ክርስቲያኖች መሆናቸው ግን ልብን የሚሰብር እውነታ ነው፡፡ በዚህ ጠባያችን እንደ ክርስቲያን ሳንኖር እንደ ክርስቲያን ልንሞት መሆኑ ምንኛ ያሳዝናል?

ጌታችን የሴቲቱን የዘር ጥያቄ እንዳልሰማ አለፈውና ‘’ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑን ብታውቂ የሕይወትን ውኃ እንዲሰጥሽ ትለምኚው ነበር’’ አላት፡፡ አሁንም የተጠማው የእርስዋን መመለስ ነውና እርስዋ ያነሳችውን ርእስ ሳያነሳ የውኃ ጥያቄውን ቀጠለ፡፡ ውኃን የፈጠረ ጌታ የሴቲቱን በተሰበረ ልብ የሚፈስስ ዕንባ ተጠምቶ ውኃ ለመናት፡፡

‘’ጌታ ሆይ መቅጃ የለህም ጉድጓዱ ጥልቅ ነው’’ አለችው፡፡ እንዴት ያለ ንግግር ነው፡፡ የነፍስዋን መመለስ ለተጠማው ጌታ ይህ ምላሽ እንዴት ከባድ ነው?
እውነት ጌታ መቅጃ የለውም? እውነትስ ጉድጓዱ ጥልቅ ነው? አዎ ልክ ነው የለውም፡፡

ጌታ ሆይ መቅጃ የለህም ፤ ጉድጓዱም ትልቅ ነው፡፡ ብዙ ተስፋ የቆረጡ ነፍሳትን ፣ ወደ አንተ መመለስ የሚሹ አንተም የተጠማሃቸው ነፍሳት በጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ወድቀዋል፡፡ የገቡበት አዘቅት ጥልቅ ነው ፤ በጥላቻ ፣ በክፋት ፣ በብዙ ተስፋ ማጣት ጉድጓድ ውስጥ የገቡ አንተ የተጠማሃቸው ነፍሳት ብዙ ናችው፡፡ ነገር ግን ሳምራዊትዋ እንዳለችው ከጉድጓዱ ማውጫ መቅጃ የለህም፡፡ ካለህ እስቲ ንገረን፡፡ ሕዝብህን ከጉድጓድ ውስጥ የሚያወጣ የአንተን ፈቃድ የሚፈጽምልህ አገልጋይ አለህ? ሁሉም ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ የቀረ አይደለምን? ራሱ መቅጃ የሚፈልግ መቅጃማ ሞልቶሃል? እንደ ኢሳይያስ ዘመን ‘’ማንን እልካለሁ’’ ብለህ ብትጣራ ይሻልሃል እንጂ መቅጃስ የለህም፡፡ ወይ ሱራፊን ልከህ በእሳት ፍሕም ተኩሰህ ካላነጻኸን በቀር መቅጃ የለህም፡፡

ሴቲቱ የያዕቆብን አምላክ ክርስቶስን ‘አንተ ከያዕቆብ ትበልጣለህ?’’ አለችው፡፡ ተስፋ የቆረጠ ሰው ንግግሩ ሻካራ ነው፡፡ ‘’አንተ ከማን ትበልጣልህ? ከእገሌ ተሽለህ ነው?’’ የሚሉ ቃላት ነፍሱ የቆሰለ ሰው ንግግሮች ናቸው፡፡ ክርስቶስ አላስቀየማትም፡፡ አመል ያሳጣት የተመረረችበት ኑሮዋ እንደሆነ ያውቃል፡፡ የተጎዱ ሰዎች ሰውን ይጎዳሉ፡፡ ስለዚህ ክብሬን ላስጠብቅ ሳይል ታገሳት፡፡ ባል የለኝም ስትል እንኳን ‘’እውነት ተናገርሽ’’ አሁን ያለው ባልዋ ባለመሆኑ እንዲህ እንዳለች አድርጎ ከሐሰትዋ ውስጥ እውነት አወጣላት፡፡ የተቀጠቀጠ ሸንበቆ የማሰብረው የሚጤስ ጧፍ የማታጠፋው ትሑት አምላካችን ሆይ ክፉ ንግግሮቻችን የሚፈልቁት ከክፉ አኗኗራችን ነውና እባክህን እኛንም ታገሰን፡፡ ኢትዮጰያውያን ተሳዳቢዎች ፣ ዘረኞች ፣ ነውረኞች ያደረገን የተበላሸ ሕይወታችን ነውና ይቅር በለን፡፡ በመጥፎ ንግግሮቻችን የምናሳዝንህ ፣ በእርስ በእርስ መበላላት የምናስከፋህ ሳምራዊትዋ ሴት ባሎች እንደተፈራረቁባት ብዙ ፖለቲከኞች ተፈራርቀውብን ፣ ትዳር አልሳካ ብሎን ነውና እርስዋን እንደታግስህ ታገሰን፡፡

ሴቲቱን ጌታ ታግሶ የጎደላትን ሞላላት፡፡ ‘’እኔ ከምሠጠው ውኃ የሚጠጣ ለዘላለም አይጠማም ‘’ አላት፡፡ እርስዋም ‘ጌታ ሆይ እንዳልጠማ ውኃም ልጠጣ ወደዚህ እንዳልመጣ ይህን ውኃ ስጠኝ’’ አለችው፡፡ ይህ ውኃ ‘የሕይወት ውኃ እኔ ነኝ’’ ያለው ክርስቶስ ራሱ ነው፡፡ ሴቲቱም እርሱ መሆኑን ስታውቅ እንስራዋን ጣለች፡፡ እርሱን ካገኘች በኋላ እንደማትጠማ እርግጠኛ ነበረች፡፡

ወዳጄ ሆይ እንደ ሳምራዊትዋ ሴት መመላለስ የሰለቸህ መንገድ የለም? ስትጠጣው አሁንም ጨምር የሚያሰኝህ የማይቆርጥ ጥም የለህም? ልትቀዳ የምትመላለስበት ጉድጓድስ የለም? ሁለተኛ አልሔድም ብለህ ዝተህ የምሔድበት ቦታ የለም? ሁለተኛ አልጠጣውም ብለህ የምትጠጣው ሁሌ የሚጠማህ ውኃ ምንድር ነው? መላቀቅ እየፈለግህ ያልተውከው ፣ ዞረህ የምትሔድበት ፣ ታጥቦ ጭቃ ፣ አድሮ ቃሪያ ፣ ከርሞ ጥጃ የሆንህበት ልማድ የለህም? ክርስቶስ ቦታውንም ውኃውንም ያውቀዋል፡፡ ከዚህ መገላገል ከፈለግህ እንደ ሳምራዊትዋ ሴት እንዲህ በለው፦
‘ጌታ ሆይ እንዳልጠማ ውኃም ልጠጣ ወደዚህ እንዳልመጣ ይህን ውኃ ስጠኝ’’


ሐዋርያት 13
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ በአንጾኪያም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም በርናባስ፥ ኔጌር የተባለው ስምዖንም፥ የቀሬናው ሉክዮስም፥ የአራተኛው ክፍል ገዥ የሄሮድስም ባለምዋል ምናሔ፥ ሳውልም ነበሩ።
² እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ፦ በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ።
³ በዚያን ጊዜም ከጦሙ ከጸለዩም እጃቸውንም ከጫኑ በኋላ አሰናበቱአቸው።
⁴ እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ።
⁵ በስልማናም በነበሩ ጊዜ በአይሁድ ምኵራቦች የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ፤ አገልጋይም ዮሐንስ ነበራቸው።
⁶ ደሴቲቱንም ሁሉ እስከ ጳፉ በዞሩ ጊዜ፥ በርያሱስ የሚሉትን ጠንቋይና ሐሰተኛ ነቢይ የሆነውን አንድ አይሁዳዊ ሰው አገኙ፤
⁷ እርሱም አስተዋይ ሰው ከሆነው ሰርግዮስ ጳውሎስ ከሚባለው አገረ ገዥ ጋር ነበረ። ይህም በርናባስንና ሳውልን ወደ እርሱ ጠርቶ የእግዚአብሔርን ቃል ሊሰማ ፈለገ።
⁸ ጠንቋዩ ግን ኤልማስ፥ ስሙ እንዲሁ ይተረጐማልና፥ አገረ ገዡን ከማመን ሊያጣምም ፈልጎ ተቃወማቸው።
⁹ ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ትኵር ብሎ ሲመለከተው፦
¹⁰ አንተ ተንኰል ሁሉ ክፋትም ሁሉ የሞላብህ፥ የዲያብሎስ ልጅ፥ የጽድቅም ሁሉ ጠላት፥ የቀናውን የጌታን መንገድ ከማጣመም አታርፍምን?
¹¹ አሁንም፥ እነሆ፥ የጌታ እጅ በአንተ ላይ ናት፥ ዕውርም ትሆናለህ እስከ ጊዜውም ፀሐይን አታይም አለው። ያን ጊዜም ጭጋግና ጨለማ ወደቀበት፥ በእጁም የሚመራውን እየዞረ ፈለገ።
¹² በዚያን ጊዜ አገረ ገዡ የተደረገውን ባየ ጊዜ ከጌታ ትምህርት የተነሣ ተገርሞ አመነ።
¹³ ጳውሎስም ከጓደኞቹ ጋር ከጳፉ ተነሥቶ የጵንፍልያ ወደምትሆን ወደ ጴርጌን መጣ፤ ዮሐንስም ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።
¹⁴ እነርሱ ግን ከጴርጌን አልፈው የጲስድያ ወደምትሆን ወደ አንጾኪያ ደረሱ፤ በሰንበትም ቀን ወደ ምኵራብ ገብተው ተቀመጡ።
¹⁵ ሕግና ነቢያትም ከተነበቡ በኋላ የምኵራቡ አለቆች፦ ወንድሞች ሆይ፥ ሕዝብን የሚመክር ቃል እንዳላችሁ ተናገሩ ብለው ላኩባቸው።
¹⁶ ጳውሎስም ተነሣና በእጁ ጠቅሶ እንዲህ አለ፦ የእስራኤል ሰዎችና እግዚአብሔርን የምትፈሩት ሆይ፥ ስሙ።
¹⁷ የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ አባቶቻችንን መርጦ በግብፅ አገር በእንግድነት ሳሉ ሕዝቡን ከፍ ከፍ አደረጋቸው፥ ከፍ ባለችውም ክንዱ ከዚያ አወጣቸው።
¹⁸ በበረሀም አርባ ዓመት ያህል መገባቸው።
¹⁹ በከነዓንም አገር ሰባት አሕዛብን አጥፍቶ ምድራቸውን አወረሳቸው።
²⁰ ከዚህም በኋላ እስከ ነቢዩ እስከ ሳሙኤል ድረስ አራት መቶ አምሳ ዓመት ያህል መሳፍንትን ሰጣቸው።
²¹ ከዚያም ወዲያ ንጉሥን ያነግሥላቸው ዘንድ ለመኑ፥ እግዚአብሔርም ከብንያም ወገን የሚሆን ሰው የቂስን ልጅ ሳኦልን አርባ ዓመት ሰጣቸው፤
²² እርሱንም ከሻረው በኋላ ዳዊትን በእነርሱ ላይ እንዲነግሥ አስነሣው፥ ሲመሰክርለትም፦ እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ አለ።
²³ ከዚህም ሰው ዘር እግዚአብሔር እንደ ተስፋው ቃል ለእስራኤል መድኃኒትን እርሱም ኢየሱስን አመጣ።
²⁴ ከመምጣቱ በፊት ዮሐንስ አስቀድሞ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የንስሐን ጥምቀት ሰብኮ ነበር።
²⁵ ዮሐንስም ሩጫውን ሲፈጽም ሳለ፦ እኔ ማን እንደ ሆንሁ ታስባላችሁ? እኔስ እርሱን አይደለሁም፤ ነገር ግን እነሆ፥ የእግሩን ጫማ እፈታ ዘንድ ከማይገባኝ ከእኔ በኋላ ይመጣል ይል ነበር።
²⁶ እናንተ ወንድሞቻችን፥ የአብርሃም ዘር ልጆች ከእናንተ መካከልም እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሆይ፥ ለእናንተ የዚህ የመዳን ቃል ተላከ።
²⁷ በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሰዎችና አለቆቻቸው እርሱንና በየሰንበቱ የሚነበቡትን የነቢያትን ድምፆች ስላላወቁ በፍርዳቸው ፈጽመዋልና፤
²⁸ ለሞትም የሚያደርስ ምክንያት አንድ ስንኳ ባያገኙበት፥ ይገድለው ዘንድ ጲላጦስን ለመኑት፤
²⁹ ስለ እርሱም የተጻፈውን ሁሉ በፈጸሙ ጊዜ ከእንጨት አውርደው በመቃብር አኖሩት።
³⁰ እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው፤
³¹ በሕዝብም ዘንድ ምስክሮቹ ለሆኑት ከእርሱ ጋር ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም ለወጡት ብዙ ቀን ታያቸው።
³² እኛም ለአባቶች የተሰጠውን ተስፋ የምስራቹን ለእናንተ እንሰብካለን፤
³³ ይህን ተስፋ እግዚአብሔር በሁለተኛው መዝሙር ደግሞ፦ አንተ ልጄ ነህ እኔ ዛሬ ወለድሁህ ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ኢየሱስን አስነሥቶ ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞአልና።
³⁴ እንደገናም ወደ መበስበስ እንዳይመለስ ከሙታን እንደ አስነሣው፥ እንዲህ፦ የታመነውን የዳዊትን ቅዱስ ተስፋ እሰጣችኋለሁ ብሎአል።
³⁵ ደግሞ በሌላ ስፍራ፦ ቅዱስህን መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም ይላልና።
³⁶ ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ፥ ከአባቶቹም ጋር ተጨምሮ መበስበስን አየ፤
³⁷ ይህ እግዚአብሔር ያስነሣው ግን መበስበስን አላየም።
³⁸-³⁹ እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፥ በእርሱ በኩል የኃጢአት ስርየት እንዲነገርላችሁ፥ በሙሴም ሕግ ትጸድቁበት ዘንድ ከማይቻላችሁ ሁሉ ያመነ ሁሉ በእርሱ እንዲጸድቅ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን።
⁴⁰-⁴¹ እንግዲህ፦ እናንተ የምትንቁ፥ እዩ ተደነቁም ጥፉም አንድ ስንኳ ቢተርክላችሁ የማታምኑትን ሥራ በዘመናችሁ እኔ እሠራለሁና ተብሎ በነቢያት የተነገረው እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ።
⁴² በወጡም ጊዜ ይህን ነገር በሚመጣው ሰንበት ይነግሩአቸው ዘንድ ለመኑአቸው።
⁴³ ጉባኤውም ከተፈታ በኋላ ከአይሁድና ወደ ይሁዲነት ገብተው ከሚያመልኩ ብዙዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሉአቸው፥ እነርሱም ሲነግሩአቸው በእግዚአብሔር ጸጋ ጸንተው እንዲኖሩ አስረዱአቸው።
⁴⁴ በሁለተኛውም ሰንበት ከጥቂቶቹ በቀር የከተማው ሰው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰሙ ዘንድ ተሰበሰቡ።
⁴⁵ አይሁድም ብዙ ሕዝብ ባዩ ጊዜ ቅንዓት ሞላባቸው፥ እየተሳደቡም ጳውሎስ የተናገረውን ቃል ተቃወሙ።
⁴⁶ ጳውሎስና በርናባስም ገልጠው፦ የእግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ ለእናንተ ይነገር ዘንድ ያስፈልጋል፤ ከገፋችሁትና የዘላለም ሕይወት እንዳይገባችሁ በራሳችሁ ከፈረዳችሁ ግን፥ እነሆ፥ ወደ አሕዛብ ዘወር እንላለን።
⁴⁷ እንዲሁ ጌታ፦ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ለማዳን ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ ብሎ አዞናልና አሉ።
⁴⁸ አሕዛብም ሰምተው ደስ አላቸው የእግዚአብሔርንም ቃል አከበሩ፥ ለዘላለም ሕይወትም የተዘጋጁ ሁሉ አመኑ፤
⁴⁹ የጌታም ቃል በአገሩ ሁሉ ተስፋፋ።
⁵⁰ አይሁድ ግን የሚያመልኩትን የከበሩትንም ሴቶችና የከተማውን መኳንንት አወኩ፥ በጳውሎስና በበርናባስም ላይ ስደትን አስነሥተው ከአገራቸው አወጡአቸው።
⁵¹ እነርሱ ግን የእግራቸውን ትቢያ አራግፈውባቸው ወደ ኢቆንዮን መጡ።
⁵² በደቀ መዛሙርትም ደስታና መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው።




1ኛ ጴጥሮስ 4
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹-² ክርስቶስም በሥጋ ስለ እኛ መከራን ስለተቀበለ፥ ከእንግዲህ ወዲህ በሥጋ ልትኖሩ በቀረላችሁ ዘመን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሰው ምኞት እንዳትኖሩ፥ እናንተ ደግሞ ያን አሳብ እንደ ዕቃ ጦር አድርጋችሁ ያዙት፥ በሥጋ መከራን የተቀበለ ኃጢአትን ትቶአልና።
³ የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃልና።
⁴ በዚህም ነገር ወደዚያ መዳራት ብዛት ከእነርሱ ጋር ስለማትሮጡ እየተሳደቡ ይደነቃሉ፤
⁵ ግን እነርሱ በሕያዋንና በሙታን ላይ ሊፈርድ ለተዘጋጀው መልስ ይሰጣሉ።
⁶ እንደ ሰዎች በሥጋ እንዲፈረድባቸው በመንፈስ ግን እንደ እግዚአብሔር እንዲኖሩ ስለዚህ ምክንያት ወንጌል ለሙታን ደግሞ ተሰብኮላቸው ነበርና።
⁷ ዳሩ ግን የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦአል። እንግዲህ እንደ ባለ አእምሮ አስቡ፥
⁸ ትጸልዩም ዘንድ በመጠን ኑሩ፤ ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናልና ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ።
⁹ ያለ ማንጐራጐር እርስ በርሳችሁ እንግድነትን ተቀባበሉ፤
¹⁰ ልዩ ልዩን የእግዚአብሔርን ጸጋ ደጋግ መጋቢዎች እንደ መሆናችሁ፥ እያንዳንዳችሁ የጸጋን ስጦታ እንደ ተቀበላችሁ መጠን በዚያው ጸጋ እርስ በርሳችሁ አገልግሉ፤
¹¹ ማንም ሰው የሚናገር ቢሆን፥ እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢሆን፥ እግዚአብሔር በሚሰጠኝ ኃይል ነው ብሎ ያገልግል፤ ክብርና ሥልጣን እስከ ዘላለም ድረስ ለእርሱ በሚሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ፤ አሜን።
¹² ወዳጆች ሆይ፥ በእናንተ መካከል እንደ እሳት ሊፈትናችሁ ስለሚሆነው መከራ ድንቅ ነገር እንደ መጣባችሁ አትደነቁ፤
¹³ ነገር ግን ክብሩ ሲገለጥ ደግሞ ሐሤት እያደረጋችሁ ደስ እንዲላችሁ፥ በክርስቶስ መከራ በምትካፈሉበት ልክ ደስ ይበላችሁ።
¹⁴ ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ።
¹⁵ ከእናንተ ማንም ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ክፉ አድራጊ እንደሚሆን ወይም በሌሎች ጒዳይ እንደሚገባ ሆኖ መከራን አይቀበል፤
¹⁶ ክርስቲያን እንደሚሆን ግን መከራን ቢቀበል ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን እንጂ አይፈር።
¹⁷ ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት ተነሥቶ የሚጀመርበት ጊዜ ደርሶአልና፤ አስቀድሞም በእኛ የሚጀመር ከሆነ ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ መጨረሻቸው ምን ይሆን?
¹⁸ ጻድቅም በጭንቅ የሚድን ከሆነ ዓመፀኛውና ኃጢአተኛው ወዴት ይታይ ዘንድ አለው?
¹⁹ ስለዚህ ደግሞ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራን የሚቀበሉ፥ መልካምን እያደረጉ ነፍሳቸውን ለታመነ ፈጣሪ አደራ ይስጡ።


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!
በወልድ ውሉደ ብርሐን
በመንፈስ ቅዱስ መንፈሳውያን የተሰኛችሁ የእግዚአብሔር አብ ውድ ልጆች የድንግል ማርያም የእናታችን የቃልኪዳን ልጆች የቅዱሳኑ ሁሉ ቤተሰቦች በወደደን እና እስከ መስቀል ድረስ ባሳየው መተኪያ እና መለኪያ አሐድ ያልተገኘለት የማይገኝለትንም ትልቁን ዋጋ ከፍሎ ፍቅሩን ላሳየን ለእርሱ ለሐያሉ አምላካችን ክብር ምስጋና አምልኮትም ይድረሰው አሜን እንዴት ሰነበታችሁ?!

ቅዱስ ቁርባን ለመቀበል የምንቸገረው ለምንድነው?
ከተቀበልን(ከክርስቶስጋ አንድ ከሆንን )ቡኃላ ተመልሰንስ ለምን ተለየን?

===================

በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን ይፈጸማል ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የሆነው እና እጅግ እጅግ ለክርስቲያኑ የሚያስፈልገው #ምሥጢረ_ቁርባን ነው። ከዚሁጋ የምናየው ምስጢረ ቁርባን ማለት የክርስቶስ ሥጋ እና ደምን በመቀበል ከክርስቶስጋ መዋሃድ አንድ መሆን ማለት ነው። ታዳ ምስጢር ያሰኘው በሚታይ አገልግሎት የማይታይ( በአይነ ስጋ) በራቀ መልኩ በአይነ ህሊና የሚታይ መሆኑ ነው የማይታይ ጸጋ መሰጠቱም ነው።
ይህንን የቁርባን ሥርዓት ለመፈጸም አባታችን እግዚአብሔር ይርዳን አሜን።

#ለመቀበል ለምንስ ተቸገርን?

1ኛ ንሰሐ ለመግባት መቸግር
2ኛ ለሐጢያት ቅድሚያ መስጠታችን
3ኛ ቀጠሮ ላይ መሆናችን
4ኛ ችላ ማለት እና ማቃለላችን

""""""""""""""""

ለመቀበል የምንቸገርበት አንደኛው ምክንያት ለንሰሐ አባት ቀርቦ ለመናገር ከምንጊዜም በላይ ፍራቻ ማደር ዋናው ምክንያታችን ነው።
እንደምንም ደፍረን ከተጠጋን ደግሞ የሰራነውን በስርዓቱ እና በዓግባቡ ከመናገር ይልቅ ሸፈን አድርገን እናልፋለን ብቻ ከካህኑ አይን ፍራቻም ሊሆን ይችላል መናገር ያለብንን ሳንናገር ቀርተን ነገር ግን በውስጣችን እያመመን ወደ መጣንበት መመለሳችን አንዱ ተጠቃሽ ነው ምክንያቱም ካህኑ ሰው ስለሆነ የተነገረውን ብቻ ነው የሚረዳው ደግሞሞ መሉ በሙሉ እንደ ነጻችሁ ነው በሕሊናው የሚረዳው እኛ ግን አሁንም ቁስላችንን ይዘነው በውስጣችን እረፍት አጥተን መቁረብ የሚያስችል ንጽሕና እንደለለን አስበን መቀመጣችን ነው ።
ስለዚህ የምናደርገው የሰራነውን ቆሻሻ ስራ በትክክልና በአግባቡ ለካህኑ በሚገባው መልኩ ውስጥህን ውስጥሽን ማሳየት እንደ ፈቃድ ሳይሆን ኢየሱስ ክርስቶስም ትእዛዝ ሰጥቶናል
“አይቶም፦ ሂዱ፥ ራሳችሁን ለካህናት #አሳዩ አላቸው።”
— ሉቃስ 17፥14

ስለዚህ እራስን መደበቅ አያስፈልግም። ለምሳሌ አንድ እንመልከት።

ዝሙት ከባድ ሐጢያት መሆኑን ቅዱሱ እና ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ በደንብ ጽፏል ክርስቶስም አስተምሯል በወንጌል ማቴ5ላይ

ዝሙት ስንሰራ መቼም ከሰው እይታ በተቻለን አቅም ተሰውረን ነው አሁን አሁንማ ጭራሽ አደባባይ ላይም የሚታፈር አልሆነም። ስለዚህ ከሰው እይታ በጥንቃቄ ተሰውረን ስንረክስ መንፈስ ቅዱስ አልነበረም ወይ?
መንፈስ ቅዱስ በቦታ የተወሰነ ነው ወይ? እግዚአብሔር የለለበት የማይገኝበት እና ሰዓት አለ ወይ?
የት ቦታ እንዳስከፋችሁት ስለማያቅ ነውዴ? ታዳ ከመንፈስ ቅዱስ እና ከካህኑ ማንን አስበልጠን ነው መናገር ያልደፈርን? ተጨማሪ ለክርስቶስ በደል እየፈጸምን መሆናችንን ማወቅ ተገቢ ነው ካህኑን ከክርስቶስ አስበልጠን ማየታችን ስለዚህ በትክክል እና በተሰበረ በእውነት ዝቅ በማለት ሐጢያት(ቆሻሻ) እናስወግድ ።

2ኛው #ለሐጢያት_ቅድሚያ በማለት ነው ይሔ ደሞ አደገኛው ችግር ነው ከባዱም ይሔ ነው አንድሰው አለማዊነትን ይከለክለኛል በማለት ከቅዱስ ስጋወ ደሙ በርቀት አሻግሮ እያየ የእለት ተእለት እንቅስቃሴው ቆሻሻውን መከመር ሆኖ አሁንም አለ ከዚህ ይልቅ የሚደንቀው ውዳሴ ማርያም ለማድረስ ከሰኞ እስከ እሁድ ቢያንስ ጧት አንድ ጊዜ አለማድረጉ ነው በመቀጠል መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ ይጠላል ምክንያቱም ከልቡ ላይ ያለው መጽሐፍ ቅዱስ ክፉ ስራን እንደሚከለክል ያቃል ስለዚህ መጽሐፉን ሸፍኖ አስቀምጧል ቋሻሻውንም መከመሩን ቀጥሎበታል የሚገርመው ይሔ ሰው እያወቀ ነው ከእውቀት ማነስ አይደለም ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከለክል ካወቀ መጽሐፍ ማንበብ ካስጠላው ቅድሚያ ለርኩሰት ከሰጠ አያውቅም አይባልም ቢያነበውም እውነቱን ነው አትዘሙት(ች) ስለሚል ። አንድ ማንሳት ያለብን ነገር ቢኖር

ትላንት ለዝሙት ጊዜ ሰጠሽ(ህ) ያተረፍከው(ሽው) ምንድነው?
ትላንት ከቤተክርስቲያን ሸሸህ ያገኘህው ምንድነው?
ትላንት መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ጠላህ ምናገኘህ?
አባቶቻችን ሲጠቅሱልህም ማንበብ እና መስማት ተሳነህ ሸሸህም ምናገኘህ? ምንስ ጠቀመህ?
ደግሞምኮ ማንበብ እና መስማት ሸሽተህ ሐጢያቶችን አድርግ የሚል ጥቅስ ከየት አመጣህ?
ለሐጢያትህ ቅድሚያ ስጥና ከዛ ትመጣለህ ወደኔ ያለው ሐዋርያ ማን ይሆን? ነብይስ ነግሮክ ነው?
አላስተዋልክምጂ ለቆሻሻ ተግባር የምታውለውን ሰውነት ክርስቶስ ነው የሰጠህ ታዳ የተቀበልከው ለዝሙት ለሥርቆት መስሪያ አልነበረምኮ አንተም ታውቃለህ ደግሞስ መቼ እንደምትሞት አውቀህ ነው ይሕንን ሐጢያት ሰርቼ ከዛም እመለሳለሁ የምትለው? መቼስ ቸር ነው ይምረኛልም ስትልም ትሰማይሆናል ምነው ታዳ ይፈርዳል የሚለውን አያይዘህ ዘነጋህ? ሲጀመርኮ ገና በተወለዳችሁ 40 እና 80ቀን ሲሞላሽ የክርስቶስ ስጋ እና ደም በውስጥሽ(ህ) አለኮ ታዳ ንጹህነት ነበረህ አሁን ግን ቅድሚያ ለሐጢያት ሰውነትክን ሰዋህ ተገቢ አይደለም። ቸር ነው ስትል ትሰማ የለ አወ ቸር ነው ይበቃል ተመለስ

“የአሕዛብን ፈቃድ ያደረጋችሁበት በመዳራትና በሥጋ ምኞትም በስካርም በዘፈንም ያለ ልክም በመጠጣት ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን #ይበቃልና።”
— 1ኛ ጴጥሮስ 4፥3

3ኛው #ቀጠሮ መስጠት ነው
ይሔ ደሞ አስቸጋሪው ነው ቀጠሮ መስጠት አያስፈልግም አንተ አጠገብህ ያለው አፈር ሲገባ እያየህ ነውኮ አንተስ ምን ዋስትና አለህ የለህም ስለዚህ ዋስትና ከሌለውና መቼ አፈር እንደምገባ እማላውቅ ከሆነ እኔን ማን ቀጠሮ ሰጭ አደደረገኝ?

2ኛ ቆሮ 6
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ አብረንም እየሠራን የእግዚአብሔርን ጸጋ በከንቱ እንዳትቀበሉ ደግሞ እንለምናለን፤
² በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ #በመዳንም ቀን ረዳሁህ ይላልና፤ እነሆ፥ የተወደደው ሰዓት አሁን ነው፤እነሆ፥ የመዳን ቀን #አሁን ነው።

ስለዚህ ቀጠሮ አትስጥ ወደ ክርስቶስ ቅረብ አይዞህ አንተ ብቻ ጀምር አባትህ ወደ እቅፉ ያስጠጋሃል ይረዳሃል ከዛም አዲሱን ሰውነት ይዘህ በአዲስ አገልግሎት በአዲስ መንፈስ መዓዛ ክርስቶስን ለብሰክ ከክርስቶስጋ ፍጹም ተዋህዶ ይኖርካል ያኔ በውስጥህ ያለው ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ይሆናል

“ሥጋዬን የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ በእኔ ይኖራል እኔም በእርሱ #እኖራለሁ።”
— ዮሐንስ 6፥56

የማን መኖሪያ ነህ______?


በቀጣዩ አንድ ከፍል ይቀራል

ምስጋና ይድረሰው አንድ አምላክ ለሆነው ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ለቅድስት ለሥላሴ 🙏


ምሳሌ 8
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ በውኑ ጥበብ አትጮኽምን? ማስተዋልስ ድምፅዋን አትሰጥምን?
² በኮረብታ ላይ በመንገድ አጠገብ በጎዳና መካከል ትቆማለች።
³ በበሩ አጠገብ በከተማይቱም መግቢያ፥ በደጁ መግቢያ ትጮኻለች፦
⁴ እናንተ ሰዎች፥ እናንተን እጠራለሁ፥ ድምፄም ወደ ሰዎች ልጆች ነው።
⁵ እናንተ አላዋቂዎች፥ ብልሃትን አስተውሉ፤ እናንተም ሰነፎች ጥበብን በልባችሁ ያዙ።
⁶ የከበረች ነገርን እናገራለሁና ስሙ፤ ከንፈሮቼም ቅን ነገርን ለመናገር ይከፈታሉ።
⁷ አፌ እውነትን ይናገራልና፥ ከንፈሮቼም ክፋትን ይጸየፋሉ።
⁸ የአፌ ቃላት ሁሉ ጽድቅ ናቸው፤ ጠማማ ዘወርዋራም አይደሉም።
⁹ እነርሱ በሚያስተውሉ ዘንድ የቀኑ ናቸው፥ እውቀትንም ካገኙአት ሰዎች ጋር የተስማሙ ናቸው።
¹⁰ ተግሣጼን እንጂ ብርን አትቀበሉ፥ ከምዝምዝ ወርቅም ይልቅ እውቀትን ተቀበሉ።
¹¹ ጥበብ ከቀይ ዕንቍ ትበልጣለችና፤ የከበረ ነገር ሁሉ አይተካከላትም።
¹² እኔ ጥበብ በብልሃት ተቀምጫለሁ፥ እውቀትንም ጥንቃቄንም አግኝቻለሁ።
¹³ እግዚአብሔርን መፍራት ክፋትን ይጠላል፤ ትዕቢትንና እብሪትን ክፉንም መንገድ ጠማማውንም አፍ እጠላለሁ።
¹⁴ ምክርና መልካም ጥበብ የእኔ ነው፤ ማስተዋል እኔ ነኝ፥ ብርታትም አለኝ።
¹⁵ ነገሥታት በእኔ ይነግሣሉ፥ ሹማምቶችም የቀናውን ነገር ይደነግጋሉ።
¹⁶ አለቆች በእኔ ያዝዛሉ፥ ክቡራንና የምድር ፈራጆችም ሁሉ።
¹⁷ እኔ የሚወድዱኝን እወድዳለሁ፥ ተግተው የሚሹኝም ያገኙኛል።
¹⁸ ብልጥግናና ክብር በእኔ ዘንድ ነው፥ ብዙ ሀብትና ጽድቅም።
¹⁹ ፍሬዬም ከምዝምዝ ወርቅ ይሻላል፥ ቡቃያዬም ከተመረጠች ብር።
²⁰ እኔ በጽድቅ መንገድ እሄዳለሁ፥ በፍርድም ጎዳና መካከል፥
²¹ ለሚወድዱኝ ርስት አወርሳቸው ዘንድ ቤተ መዛግብታቸውንም እሞላ ዘንድ።
²² እግዚአብሔር የመንገዱ መጀመሪያ አደረገኝ፥ በቀድሞ ሥራው መጀመሪያ።
²³ ከጥንቱ ከዘላለም ጀምሮ ተሾምሁ ምድር ከመፈጠርዋ አስቀድሞ።
²⁴ ቀላያት ገና ሳይኖሩ እኔ ተወለድሁ፥ የውኃ ምንጮች ገና ሳይፈልቁ።
²⁵ ተራሮች ገና ሳይመሠረቱ፥ ከኮረብቶች በፊት እኔ ተወለድሁ፥
²⁶ ምድሪቱንና ሜዳውን ገና ሳይፈጥር የመጀመሪያውንም የዓለም አፈር።
²⁷ ሰማዮችን በዘረጋ ጊዜ አብሬ ነበርሁ፥ በቀላያት ፊት ክበብን በደነገገ ጊዜ፥
²⁸ ደመናትን በላይ ባዘጋጀ ጊዜ፥ የቀላይን ምንጮች ባጸና ጊዜ፥
²⁹ ለባሕርም ዳርቻን በወሰነ ጊዜ ውኃ ከትእዛዙ እንዳያልፍ፥ የምድርን መሠረት በመሠረተ ጊዜ፥
³⁰ የዚያን ጊዜ እኔ በእርሱ ዘንድ ዋና ሠራተኛ ነበርሁ፤ ዕለት ዕለት ደስ አሰኘው ነበርሁ፥ በፊቱም ሁልጊዜ ደስ ይለኝ ነበርሁ፥
³¹ ደስታዬም በምድሩ ተድላዬም በሰው ልጆች ነበረ።
³² አሁንም ልጆቼ ሆይ፥ ስሙኝ፤ መንገዴንም የሚጠብቁ ምስጉኖች ናቸው።
³³ ትምህርቴን ስሙ፥ ጠቢባንም ሁኑ፥ ቸል አትበሉትም።
³⁴ የሚሰማኝ ሰው ምስጉን ነው ዕለት ዕለት በቤቴ መግቢያ የሚተጋ፥ የደጄንም መድረክ የሚጠብቅ።
³⁵ እኔን ያገኘ ሕይወትን ያገኛልና፥ ከእግዚአብሔርም ሞገስን ያገኛልና።
³⁶ እኔን ያጣ ግን ራሱን ይጐዳል፤ የሚጠሉኝ ሁሉ ሞትን ይወድዳሉ።


ምሳሌ 7
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ጠብቅ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽግ።
² ትእዛዜን ጠብቅ በሕይወትም ትኖራለህ፤ ሕጌንም እንደ ዓይንህ ብሌን ጠብቅ፤
³ በጣቶችህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላት ጻፋቸው።
⁴ ጥበብን፦ አንቺ እኅቴ ነሽ በላት፥ ማስተዋልንም፦ ወዳጄ ብለህ ጥራት፥
⁵ ከጋለሞታ ሴት ትጠብቅህ ዘንድ፥ ቃልዋን ካለዘበች ከሌላይቱ ሴት።
⁶ በቤቴ መስኮት ሆኜ ወደ አደባባይ ተመለከትሁ፤
⁷ ከአላዋቂዎች መካከል አስተዋልሁ፤ ከጐበዛዝትም መካከል ብላቴናውን አእምሮ ጐድሎት አየሁ፥
⁸ በአደባባይ ሲሄድ በቤትዋም አቅራቢያ ሲያልፍ፤ የቤትዋን መንገድ ይዞ ወደ እርስዋ አቀና፥
⁹ ማታ ሲመሽ፥ ውድቅትም ሲሆን፥ በሌሊትም በጽኑ ጨለማ።
¹⁰ እነሆ፥ ሴት ተገናኘችው የጋለሞታ ልብስ የለበሰች፥ ነፍሳትን ለማጥመድ የተዘጋጀች።
¹¹ ሁከተኛና አባያ ናት፥ እግሮችዋም በቤትዋ አይቀመጡም፤
¹² አንድ ጊዜ በጎዳና፥ አንድ ጊዜ በአደባባይ፥ በማዕዘኑም ሁሉ ታደባለች።
¹³ ያዘችውም ሳመችውም፤ ፊትዋም ያለ እፍረት ሆኖ እንዲህ አለችው፦
¹⁴ መሥዋዕትንና የደኅንነት ቍርባንን ማቅረብ ነበረብኝ፤ ዛሬ ስእለቴን ፈጸምሁ።
¹⁵ ስለዚህ እንድገናኝህ፥ ፊትህንም በትጋት ለመሻት ወጥቻለሁ፥ አግኝቼሃለሁም።
¹⁶ በአልጋዬ ላይ ማለፊያ ሰርፍ ዘርግቼበታለሁ፥ የግብጽንም ሽመልመሌ ለሀፍ።
¹⁷ በመኝታዬ ከርቤንና ዓልሙን ቀረፋም ረጭቼበታለሁ።
¹⁸ ና፥ እስኪነጋ ድረስ በፍቅር እንርካ፥ በተወደደ መተቃቀፍም ደስ ይበለን።
¹⁹ ባለቤቴ በቤቱ የለምና፥ ወደ ሩቅ መንገድ ሄዶአልና፤
²⁰ በእጁም የብር ከረጢት ወስዶአል፤ ሙሉ ጨረቃ በሆነች ጊዜ ወደ ቤቱ ይመለሳል።
²¹ በብዙ ጨዋታዋ እንዲስት ታደርገዋለች፤ በከንፈርዋ ልዝብነት ትጐትተዋለች።
²² እርሱ እንዲህ ስቶ ይከተላታል፥ በሬ ለመታረድ እንዲነዳ፥ ውሻም ወደ እስራት እንዲሄድ፥
²³ ወፍ ወደ ወጥመድ እንደሚቸኩል፥ ለነፍሱ ጥፋት እንደሚሆን ሳያውቅ፥ ፍላጻ ጕበቱን እስኪሰነጥቀው ድረስ።
²⁴ ልጆቼ ሆይ፥ አሁን እንግዲህ ስሙኝ ወደ አፌም ቃል አድምጡኝ።
²⁵ ልብህ ወደ መንገድዋ አያዘንብል፤ በጎዳናዋ አትሳት።
²⁶ ወግታ የጣለቻቸው ብዙ ናቸውና፤ እርስዋም የገደለቻቸው እጅግ ብዙ ናቸው።
²⁷ ቤትዋ የሲኦል መንገድ ነው፤ ወደ ሞት ማጀት የሚወርድ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈልን ወደራሳችን አምጥተን ሒወታችንን ልናይበት ነው ልንመራበትም ጭምር ነው


አምላካችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋሪያቶቹ የተናገረው በአንድ ወቅት በጾለተ ሐሙስ እንዲህ ነበር ያለው።


#አይዟችሁ_ደስታችሁን_የሚወስድባችሁ_የለም!

ይህን ያለው ሐዋሪያቶቹ ስለ ክርስቶስ ብለው የሚቀበሉት መከራ ቀርቦ ነበርና ነገር ግን ኢየሱስ ሊያስገነዝባቸው ያሰበው

''በልብስ ደስ ይበለኝ ካልክ ልብሱን ፈላጊው ብዙ ነውና ይገፉሃል''
'' በሹመት ደስ ይበለኝ ካልክ ሹመት ፈላጊው ብዙ ነውና ይሽርሃል''
''በጤና ደስ ይበለኝ ካልክ መታመምህ አይቀርም''
''በመብል ደስ ይበለኝ ካልክ መራብህ አይቀርም''
''በውበት ደስ ይበለኝ ካልክ በጎስቀል እና ትቢያ አቧራ አፈር መሆንክ አይቀርም''
''በሐብት ደስ ይበለኝ ካልክ መዘረፍህ አይቀርም''
'' #በክርስቶስ_ደስ_ይበለኝ_ካልክ_የሚወስድብህ_የለም ። ''

መጋቢ ብሉይ ወሃዲስ አባ ገብረ ኪዳን

https://t.me/WE_ARE_ORTHODOX


⛪️...ንስሐ፡ግቡ...⛪️, [12.11.20 07:43]
☘️☘️☘️☘️☘️☘️☘️☘️☘️☘️

ምንም፡እንኳን፡በሳምንት፡ሁለት፡ቀናትን፡ቢጾምም፡ከቀራጩ፡አስበልጦ፡ራሱን፡በማየቱና፡በጾሙ፡በመመካቱ፡ብቻ፡ፈሪሳዊው፡አልበጀውም።እንዲህ፡ባለ፡የማይበጅ፡ጾም፡ውስጥ፡አትለፍ።

ቅዱስ፡አትናቴዎስ

#ብሂለ_አበው

💧 ስብሐት፡ለ እግዚአብሔር 💧

☘️☘️☘️☘️☘️☘️☘️☘️


ምሳሌ 27
¯¯¯¯¯¯¯¯¯¯
¹ ቀን የሚያመጣውን ምን እንደ ሆነ አታውቅምና ነገ በሚሆነው አትመካ።
² ሌላ ያመስግንህ እንጂ አፍህ አይደለም፤ ባዕድ ሰው እንጂ ከንፈርህ አይደለም።
³ ድንጋይ ከባድ ነው አሸዋም ሸክሙ ጽኑ ነው፤ ከሁለቱ ግን የሰነፍ ቍጣ ይከብዳል።
⁴ ቍጣ ምሕረት የሌለው ነው፥ መዓትም እንደ ጎርፍ ነው፤ በቅንዓት ፊት ግን ማን ይቆማል?
⁵ የተገለጠ ዘለፋ ከተሰወረ ፍቅር ይሻላል።
⁶ የወዳጅ ማቍሰል የታመነ ነው፤ የጠላት መሳም ግን የበዛ ነው።
⁷ የጠገበች ነፍስ የማር ወላላ ትረግጣለች፤ ለተራበች ነፍስ ግን የመረረ ነገር ሁሉ ይጣፍጣታል።
⁸ ስፍራውን የሚተው ሰው ቤቱን ትቶ እንደሚበርር ወፍ ነው።
⁹ ሽቱና ዕጣን ልብን ደስ ያሰኛሉ፤ እንዲሁ ነፍስ በወዳጁ ምክር ደስ ይላታል።
¹⁰ ወዳጅህንና የአባትህን ወዳጅ አትተው፤ በመከራህም ቀን ወደ ወንድምህ ቤት አትግባ፤ የቀረበ ወዳጅ ከራቀ ወንድም ይሻላል።
¹¹ ልጄ ሆይ፥ ጠቢብ ሁን፥ ልቤንም ደስ አሰኘው፥ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ።
¹² ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፤ አላዋቂዎች ግን አልፈው ይጐዳሉ።
¹³ ለማያውቀው ከተዋሰ ሰው ልብሱን ውሰድ፥ ለእንግዳ የተዋሰውንም እርሱን አግተው።
¹⁴ ባልንጀራውን በታላቅ ቃል ማለዳ የሚባርክ ሰው እንደሚራገም ያህል ነው።
¹⁵ በዝናብ ቀን የሚያንጠባጥብ ቤትና ጠበኛ ሴት አንድ ናቸው፤
¹⁶ እርስዋንም መከልከል ነፍስን መከልከልና ዘይትን በቀኝ እጅ መጨበጥ ነው።
¹⁷ ብረት ብረትን ይስለዋል፥ ሰውም ባልንጀራውን ይስላል።
¹⁸ በለሱን የጠበቀ ፍሬዋን ይበላል፥ ጌታውንም የሚጠብቅ ይከብራል።
¹⁹ ፊት በውኃ ላይ ለፊት እንደሚታይ፥ እንዲሁ የሰው ልብ ለሰው ይታያል።
²⁰ ሲኦልና ጥፋት እንዳይጠግቡ፥ እንዲሁ የሰው ዓይን አይጠግብም።
²¹ ብር በከውር ወርቅም በማቅለጫ ይፈተናል፤ ሰውም በሚያመሰገኑት ሰዎች አፍ ይፈተናል።
²² ሰነፍን በሙቀጫ ውስጥ ከእህል ጋር በዘነዘና ብትወቅጠው፥ ስንፍናው ከእርሱ አይርቅም።
²³ የበጎችህን መልክ አስተውለህ እወቅ፥ በከብቶችህም ላይ ልብህን አኑር፤
²⁴ ባለጠግነት ለዘላለም አይኖርምና፥ ዘውድም ለትውልድ ሁሉ አይጸናምና።
²⁵ ደረቅ ሣር በታጨደ ጊዜ፥ አዲስ ለምለም በታየ ጊዜ፥ ከተራራውም ቡቃያ በተሰበሰበ ጊዜ፥
²⁶ በጎች ለልብስህ ፍየሎችም የእርሻ ዋጋ ይሆናሉ።
²⁷ ለሲሳይህ ለቤተ ሰቦችህም ሲሳይ ለገረዶችህም ምግብ የፍየል ወተት ይበቃል።


+አረንጓዴ ጠርሙሶች +

ልጆች ሆነን ሂሳብ የተማርንበት መዝሙር ድንገት ትዝ አለኝ፡፡

‘ዐሥር አረንጓዴ ጠርሙሶች በግድግዳ ላይ
ድንገት አንዱ ወድቆ ሲሰበር ዘጠኝ ይቀራል...’

ይህ ምንጩ ከወደ እንግሊዝ እንደሆነ የሚነገርለት ዐሥር አረንጓዴ ጠርሙሶች /ten green bottles/ የተሰኘ የሕፃናት መዝሙር ቢያንስ ከአንድ እስከ ዐሥር መቀነስ የተማርንበት ነበረ፡፡

‘ዐሥር አረንጓዴ ጠርሙሶች በግድግዳ ላይ
ድንገት አንዱ ወድቆ ሲሰበር ዘጠኝ ይቀራል...’

እኔ የምለው ድንገት አንዱ ወድቆ ባይሰበርስ? ሂሳቡንስ ተማርንበት፡፡ አንዱ ወድቆ ሲሰበር የማየት አባዜ ግን አሁንም ድረስ የቀጠለ ይመስለኛል፡፡
የምንዘምርባቸው ጠርሙሶቹም ገና መዝሙሩ ሲጀመር መሳቀቅ እንደሚጀምሩ ግልጽ ነው፡፡ አንዱ ወድቆ ሲሰበር ሌሎቹ "ቀጥሎ በእኔ" እያሉ ይርበተበታሉ:: የጠርሙስ እጥረት ባለበት ሥፍራ ያውም ዐሥር ጠርሙሶች ብቻ ባሉበት ግድግዳ ላይ ያሉት እነዚህ ጠርሙሶች ቢሰነብቱ ምናለ? አጨብጭቦ መስበር እስቲ ምን ይባላል? ልጅነት ሆኖብን ነው መቼም::

ወዳጄ ከዐሥር አረንጓዴ ጠርሙሶች አንዱ አያድርግህ፡፡ አንዱ ከሆንክ ሰዎች እያጨበጨቡ ድንገት እስክትሰበር ይጠብቁሃል፡፡ ምናለ ዐሥር ጠርሙሶች ካሉ እነዚያን ተንከባክቦ መያዝ ቢቻል ጉዳት ነበረው? ካደግንስ በኁዋላ ስንት አረንጓዴ ጠርሙሶችን እያጨበጨብን ሰብረን ይሆን?

የሚገርመው ደግሞ ከዐሥሩ ተርፎ የቀረው የመጨረሻው ጠርሙስ አሸኛኘት ነው፡፡

‘አንድ አረንጓዴ ጠርሙስ በግድግዳ ላይ
ድንገት አንዱ ወድቆ ሲሰበር ዜሮ ይቀራል...👏👏👏 ዜሮ ይቀራል ... 👏👏👏 ዜሮ ይቀራል’ 👏👏👏
ጭብጨባው ይቀልጣል፡፡

የመጨረሻ ጠርሙስ እንደቀረ ሲታይ እንኳን እሱ እንኳን ይትረፍ አይባልም? በእልልታ በጭብጨባ ዜሮ ይቀራል ተብሎ ክፍሉ ይደበላለቃል፡፡ አጨብጭበን የሰበርናቸው ጠርሙሶች ግን ስንራመድ እግራችንን መውጋታቸው አይቀርም፡፡ በሌላው ውድቀት የሚደሰት ሁሉ መጨረሻው አያምርም፡፡

እባካችሁ ሕፃን ሆነን የተማርንበት መዝሙር ትልቅ ሆነን ይብቃን፡፡ አንድም ጠርሙስ ወድቆ አይሰበር ፤ እኛም በሌላው ስብራት አናጨብጭብ፡፡

"ጠላትህ ቢወድቅ ደስ አይበልህ፥
በመሰናከሉም ልብህ ሐሤት አያድርግ"
ምሳ 24:17

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ሐምሌ 2 2013 ዓ.ም.
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ


እመቤታችን ተወለደች ማለት ጌታ ሊወለድ 15 ዓመት ቀረው ማለት ነው:: እግዚአብሔር ከሴት የተወለደ ልጁን ሊልክ የዘመኑ ፍጻሜ ቀረበ ማለት ነበር። እግዚአብሔር ሃና እና ኢያቄምን ሳይወልዱ ያዘገያቸውም ለዚህ ታላቅ ክብር እንዲበቁ ነበር።
ቀድመው ልጅ ቢወልዱ ኖሮ ይህችን የፍጥረት ደስታ የሆነች ልጅ አይወልዱም ነበር:: የእርስዋ የልደት ቀን የፍጥረት ደስታ ቀን ነው::

ክርስቶስ ፀሐይ ከሆነ የዛሬው ዕለት ሰማይዋ የተዘረጋችበት ዕለት ነው።

ክርስቶስ የሕይወት ውኃ ከሆነ ዛሬ ምንጭዋ የፈለቀችበት ዕለት ነው።

ክርስቶስ መድኃኒት ከሆነ ዛሬ የመድኃኒቱ ሙዳይ የተገኘችበት ዕለት ነው::

ወንጌል በመጥምቁ ዮሐንስ መወለድ ብዙዎች ደስ ይላቸዋል ይላል። በእመቤታችን መወለድ ምን ያህል ሰዎች ደስ ይላቸው ይሆን? የእመቤታችን ልደት በብዙ ሀገራት ብሔራዊ በዓል ሆኖ ይከበራል።

እኛም በሊባኖስ ተራሮች (አድባረ ሊባኖስ) መወለድዋን በማሰብ ከደጅ ወጥተን ቅድም አያቶችዋ በጨረቃ ተመስላ በህልማቸው ያዩአትን የጨረቃችንን (በግሪኩ ሶልያና) ልደት ጨረቃን እያየን እናከብራለን። የልደትዋ ቀን ልደታችን ነው!

ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ

Показано 20 последних публикаций.

133

подписчиков
Статистика канала