#ሸዋል
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ እጅግ በጣም አዛኝ በሆነው።
59፥7 *መልክተኛውም የሰጣችሁን ማንኛውንም ነገር ያዙት፡፡ ከእርሱም የከለከላችሁን ነገር ተከልከሉ*፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ አላህ ቅጣተ ብርቱ ነውና፡፡ وَمَا آتَاكُمُ الرَّسُولُ فَخُذُوهُ وَمَا نَهَاكُمْ عَنْهُ فَانتَهُوا ۚ وَاتَّقُوا اللَّهَ ۖ إِنَّ اللَّهَ شَدِيدُ الْعِقَابِ
ሚሽነሪዎች የማያውቁትን ከመጠየቅ ይልቅ፦ “ዘካህ ከመቶ 2.5% ስጡ የሚል መረጃ የለም፣ ሪባ ማለት አራጣ ማለት እንጂ ወለድ ማለት አይደለም፥ የቁርኣን አወራረድ ሁለት አይነት ነው የሚል መረጃ ከቁርኣንም ከሐዲስም መረጃ የለም” እያሉ ዲስኩራቸውን ሲደሶክሩ ነበር። ለእናንዳንዱ አርስት ከቁርኣና ከሐዲስ ከዚህ ቀደም ምላሽ ሰተናል። ዛሬ ደግሞ፦ “ሸዋልን ጹሙ! የሚል ቁርኣን ላይ የለም” እያሉ ይደሶክራሉ። ሚሽነሪዎች ሆይ! ጮቤ ረግጣችሁ አንባጒሮ አትፍጠሩ። ተረጋጉ! የጅብ ችኩል አትሁኑ! በሰላና በሰከነ መንፈስ ጠይቁ መልስ ይሰጣችኃል። ከሆያ ሆዬ ወደ አንቺ ሆዬ ትንሽ እንኳን እደጉ።
የወሮች ቁጥር አላህ ዘንድ በአላህ መጽሐፍ ዐሥራ ሁለት ወር ነው፥ እነዚህም፦
1ኛ ወር ሙሐረም
2ኛ ወር ሰፈር
3ኛ ወር ረቢዑል-አወል
4ኛ ወር ረቢዑ-ሣኒ
5ኛ ወር ጀማዱል-አወል
6ኛ ወር ጀማዱ-ሣኒ
7ኛ ወር ረጀብ
8ኛ ወር ሻዕባን
9ኛ ወር ረመዷን
10ኛ ወር ሸዋል
11ኛ ወር ዙል-ቀዒዳህ
12ኛ ወር ዙል-ሒጃህ ናቸው፦
9፥36 *የወሮች ቁጥር አላህ ዘንድ በአላህ መጽሐፍ ውስጥ ሰማያትንና ምድርን በፈጠረበት ቀን ዐሥራ ሁለት ወር ነው፡፡ ከእነርሱ አራቱ የተከበሩ ናቸው*፡፡ إِنَّ عِدَّةَ الشُّهُورِ عِندَ اللَّهِ اثْنَا عَشَرَ شَهْرًا فِي كِتَابِ اللَّهِ يَوْمَ خَلَقَ السَّمَاوَاتِ وَالْأَرْضَ مِنْهَا أَرْبَعَةٌ حُرُمٌ
ከእነዚህ አስራ ሁለት ወራት አንዱ 10ኛ ወር “ሸዋል” ነው፥ “ሸዋል” شَوَّال ማለት “ማንሳት” ወይም “መሸከም” ማለት ሲሆን የወር ስም ነው። ነቢያችን”ﷺ” እንድናደርገው ሙስተሐብ አድርገው ከሰጡት ሱና መካከል ከሸዋል ወር ስድስት ቀናትን መጾም ነው፦
ጃምዒ አት-ተርሚዚ መጽሐፍ 8, ሐዲስ 78
አቢ አዩብ እንደተረከው፦ “ነቢዩ”ﷺ” እንዲህ አሉ፦ *ማንም ረመዷንን የጾመ ከዚያም ከሸዋል ወር ስድስት ቀናትን ያስከተለ ዋጋው ዓመቱን ሙሉ እንደጾመ ነው”*። عَنْ أَبِي أَيُّوبَ، قَالَ قَالَ النَّبِيُّ صلى الله عليه وسلم ” مَنْ صَامَ رَمَضَانَ ثُمَّ أَتْبَعَهُ سِتًّا مِنْ شَوَّالٍ فَذَلِكَ صِيَامُ الدَّهْرِ
የረመዷን ሰላሳ ቀን እና የሸዋል ስድስት ቀን ጾም ጾመን ዓመት እንደጾምን የሚያስቆጥርበትን ስሌት ማወቅ ይቻላል። አምላካችን አላህ አንድ መልካም ሥራ ምንዳው አሥር እጥፍ እንደሆነ በቅዱስ ቃሉ ነግሮናል፦
6፥160 *”በመልካም ሥራ የመጣ ሰው ለእርሱ ዐሥር ብጤዎችዋ አሉት”*፡፡ በክፉ ሥራም የመጣ ሰው ብጤዋን እንጅ አይመነዳም፡፡ እነርሱም አይበደሉም፡፡ مَن جَاءَ بِالْحَسَنَةِ فَلَهُ عَشْرُ أَمْثَالِهَا ۖ وَمَن جَاءَ بِالسَّيِّئَةِ فَلَا يُجْزَىٰ إِلَّا مِثْلَهَا وَهُمْ لَا يُظْلَمُونَ
ስለዚህ አንድ መልካም ሥራ አሥር ብጤዎች ካሉት የረመዷን አንድ ወር መጾም የአሥር ወር ምንዳ አለው። 1×10=10 ወር ይሆናል። እንዲሁ የሸዋል ስድስት ቀን መጾም የስድሳ ቀን ምንዳ አለው፥ ስድስት ቀናት በአሥር እጥፍ ስድሳ ቀን ነውና፥ 6×10=60 ቀን ወይም 2 ወር ይሆናል። ሲጠቀለል የረመዷን የአሥር ወር ምንዳ እና የሸዋል ሁለት ወር ምንዳ 12 ወር ይሆናል፥ 10+2=12 ወር ይሆናል። አንድ ዓመት ደግሞ 12 ወር መሆኑ እሙን ነው። አሊያም ሠላሳ የረመዳን ቀን እና ስድስት የሸዋል ቀን በአስር ምንዳ ሲባዛ 360 ቀናት ይሆናሉ፥ 36×10= 360 ይሆናል። አንድ ዓመት ደግሞ በጸሐይ አቆጣጠር 360 ቀናት መሆኑ ቅቡል ነው።
አምላካችን አላህ በተከበረ ቃሉ፦ “መልክተኛውም የሰጣችሁን ማንኛውንም ነገር ያዙት” ይለናል፦
59፥7 *መልክተኛውም የሰጣችሁን ማንኛውንም ነገር ያዙት፡፡ ከእርሱም የከለከላችሁን ነገር ተከልከሉ*፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ አላህ ቅጣተ ብርቱ ነውና፡፡ وَمَا آتَاكُمُ الرَّسُولُ فَخُذُوهُ وَمَا نَهَاكُمْ عَنْهُ فَانتَهُوا ۚ وَاتَّقُوا اللَّهَ ۖ إِنَّ اللَّهَ شَدِيدُ الْعِقَابِ
ስለዚህ ኢሥላም ሰው ሰራሽ ሕግና ሥርዓት ሳይሆን ዐቂደቱ አር-ረባንያህ ነው። ይህንን ስንል አርቲ ቡርቲና ቶራ ቦራ የሆነ ስሑትና መሪር የቡና ወሬ ይዘን ሳይሆን ቁርኣንና ሐዲስን ያማከለ ስሙርና ጥዑም ማስረጃ ይዘን ነው።
✍ከወንድም ወሒድ ዑመር
@islamic_knowledg