ሁላችንም ልናወራው የማንፈልገው ታሪክ ይኖረናል፡፡ ምናልባትም ዋናው ታሪካችን ያ ልናወራው የማንፈልገው ታሪክ ይሆናል፡፡ መጠኑ ይለያይ እንጂ ሁሉም ዛፍ ሥር አለው፡፡ የደበቅነው ታሪካችን እንደ ዛፍ፣ አላፊ አግዳሚ ለሚያዬው ሕይወታችን የማይታይ ሥር ነው። አወራነውም- አላወራነውም፣ ታዬም አልታዬም እዚያ የተደበቀ የታሪክ ሥራችን ላይ ነው የምንቆመው። ወደ ፊት እስከቀጠልን ድረስ ተመልሶ መነካካቱ፣ ምናልባትም ዛሪያችንን ሊረብሽ ይችላልና ባለቤቱ ፈቅዶ እስኪተነፍሰው መተው ይሻላል ባይ ነኝ፡፡ ያለፈ ነገራችን እየተመለሰ ዛሪያችንን እስካልረበሼ ድረስ፣ ሥራችንን በነበረበት ትተን በሚታዩ ፍሬዎቻችን፣ በሚስቡ አበቦቻችን፤ መፋቀር፣ መዋደድ፣ መከባበር አንችልም ወይ?