+ ወደ ኖኅ መርከብ ለመጨረሻ ጊዜ የገባችው እንስሳ +
የኖኅ መርከብ ጉዳይ በጣም አስገራሚ ከሚሆኑብኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች አንዱ ነው:: በዓለማችን አሁን ያሉ እንስሳት ሁሉ "ከነ ባለቤትዎ" እንዲገኙልን እንደሚባልበት ሰርግ ጥንድ ጥንድ ሆነው የገቡባት ትልቅ መርከብ ታሪክ : ዳግም ለሰው ልጆች ወላጆች ለመሆን የተመረጡ አራት ወንዶችና አራት ሴቶች ብቻ የተሳፈሩባት ትልቅ መርከብ ሁኔታ ትኩር ብሎ ላየው አስገራሚ እውነቶችን ያዘለ ነው::
ከሁሉም በላይ ግን መርከቢቱ የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ መሆንዋ ብዙ ነገር እንድናስብ ያግዘናል:: ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ "ወደ ኖኅ መርከብ ተኩላ ገብቶ ሲወጣም ተኩላ ሆኖ ይወጣል:: ወደ ቤተክርስቲያን ግን ተኩላ ሆነው ገብተው በግ ሆነው የወጡ ብዙዎች ናቸው" ብሎአል::
እውነትም ቤተ ክርስቲያን ወደ እርስዋ የገቡትን መለወጥ የምትችል መርከብ ናት:: ወደ ቤተ ክርስቲያን እንደ ጅብ ሆዳም ሆነው ገብተው ጾመኞች ሆነው የወጡ አሉ:: እንደ የሌሊት ወፍ በቀን መኖር አቅቶአቸው ሌሊቱን የልባቸው ዓይን ታውሮ በኃጢአት ጨለማ ሲደናበሩ የኖሩ ሰዎች ወደ መርከቢቱ ገብተው እንደ ንስር አርቀው አጥርተው ቀኑን የሚያዩ ሆነዋል:: ቤተ ክርስቲያን ወደ እርስዋ የገቡትን የምትለውጥ መርከብ ናት:: ውኃ ወደ እርስዋ ሲገባ ጠበል ይሆናል:: አፈር ወደ እርስዋ ሲገባ እምነት (እመት) ይሆናል:: ዘይት ወደ እርስዋ ሲገባ ቅዱስ ቅባት ይሆናል:: ኅብስትና ወይን ወደ እርስዋ ሲገባ ወደ ቅዱስ ቁርባን ይለወጣል::
ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ያልተለወጠ ሰው ግን ሲገባም ጅብ ሲወጣም ጅብ ሆኖአል:: ኖኅ ከመርከብ መልእክት ልኮት የቀረው የቁራ ነገርስ? ከቤተ ክርስቲያን ወጥተው ስንቶች በዚያው ቀርተዋል? ለዓለም ጨው እንዲሆኑ ተልከው በዚያው ሟሙተው የቀሩ ስንት አሉ:: ርግብ ግን ማረፊያ ስታጣ ተመልሳ ነበር:: ከመርከቢቱ የራቅን ሁላችን "ልባችን በእግዚአብሔር እስካላረፈ ድረስ ዕረፍት የለውም" እንዳለ ሊቁ ወደ መርከቢቱ ፈጥነን መመለስ አለብን::
ሰሞኑን ደግሞ አንድ ጥያቄ በአእምሮዬ ተመላለሰብኝ:: "ወደ ኖኅ መርከብ ለመጨረሻ ጊዜ የገባው እንስሳ ማን ሊሆን ይችላል?" የሚል:: ይህን ጥያቄ በግልም በጉባኤ ላይም ሰዎችን ጠይቄ ነበር:: መቼም ለዚህ ጥቅስ አያስፈልገውም:: ኖኅ ቆሞ እንስሳቱ እስኪገቡ ድረስ እንደጠበቀና ማንንም እንስሳ ጥሎ እንዳልገባ የታወቀ ነው::
በዚህ ምክንያት እንስሳቱ ወደ መርከቢቱ የሚገቡት እንደደረሱበት ቅደም ተከተል ነው:: ክንፍ ያላቸው በርረው ቀድመው ይገባሉ:: እንደ ጥንቸል እንደ ካንጋሮ እንደ ሚዳቁዋ ያሉትም እየዘለሉ ፈጥነው ይገባሉ::
ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ነፍሳቸውን ለማዳን ፈጥነው በርረው የገቡ እንደ ሚዳቋ ዘልለው የደረሱ ብርቱዎች አሉ:: እንደ ፒኮክ ያሉ ባለ ውብ ክንፎች : እንደ ቀጭኔ ያሉ ባለ ረዥም አንገቶች እንደ ጃርት ያሉ ሌላው ላይ የሚሰኩት እሾኽ የለበሱ እንስሳት ወደ መርከብዋ ገብተዋል:: በቤተክርስቲያን እንደ ፒኮክ አምሮ መታየት መዘባነን የሚወዱ ለታይታ የሚገዙ ብዙዎች ገብተዋል:: እንደ ቀጭኔ አንገታቸውን ከፍ አድርገው ሰውን ቁልቁል የሚመለከቱና "አንገታቸውን እንደሚያገዝፉ የዕብራውያን ሴቶች" ዓይነት ሕይወት ያላቸውም ገብተዋል:: እንደ ጃርት በክፉ ንግግር የሰው ልብ ላይ የሚሰኩት ጥላቻ የተላበሱ ሰዎችም ገብተዋል:: የኖኅ መርከብ ያልያዘችው እንስሳ እንደሌለ ቤተ ክርስቲያንም ያልተሸከመችው ዓይነት ሰው የለም::
ወደ ጥያቄው ስመለስ በእኔ ግምት ወደ መርከቡ በጣም ዘግይታ የገባችው ኤሊ ነበረች:: በላይዋ ድንጋይ የተጫናት እጅግ ቀርፋፋዋ ኤሊን የማይቀድም እንስሳ መቼም አይኖርም:: ምንም ብትዘገይም ኖኅ እስከመጨረሻው ጠብቆ አስገብቶ ለዘር አትርፎአታል:: የኤሊ ዘሮችም "ኖኅ ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ዳይኖሰር በጠፋን ነበር" ብለው ኖኅን ማመስገናቸው አይቀርም:: እግዚአብሔር ምንም ብትዘገይ ኤሊ ሳትገባ መርከቡን አልዘጋውም::
የኤሊ በመርከቡ መትረፍ በቤተ ክርስቲያን ልንተርፍ ተስፋ ለምናደርግ ለእኛ ትልቅ መጽናኛችን ነው::
ወዳጄ ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመምጣት እንደ ወፍ ትበርራለህ? እንደ ሚዳቋ ትዘልላለህ? ወይንስ እንደ ኤሊ ትጎተታለህ? እግሮችህ ለመንፈሳዊ ነገር ሲሆን አቅም እያጡ አልተቸገርህም?
ልብህ ቢፈልግም እንደ ኤሊዋ የተጫነህ የኃጢአት ድንጋይ አላንቀሳቅስ ብሎህ አልዘገየህም?
እንዲህ ከሆነ አትጨነቅ መርከብዋ ቤተ ክርስቲያን አንተን ሳትይዝ ጥላህ ወዴትም አትሔድም:: ጉዞህን እስካላቆምህ ድረስ ትጠብቅሃለች:: እየተጎተትህም እየተሳብህም ቢሆን አንተ ብቻ ወደ ደጁ ገስግስ::
አንተ ብቻ መንገድ ጀምር እንጂ ፈጣሪ በሩን የሚዘጋው አንተ እስክትገባ ጠብቆ ነው::
ከቅዱስ ኤፍሬም ጋር እንዲህ ብለህ ለምነው :-
"ብበድልህም እንኳን አሁንም በርህን እያንኳኳሁ ነው:: እየተጎተትሁም ቢሆን አሁንም የምጉዋዘው ወደ አንተ ለመምጣት ነው"
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ሚያዝያ 5 2013 ዓ ም
ለተጨነቀች ነፍስ ዕረፍት የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ለሁሉ ይዳረስ ዘንድ :: እኔም ለእናንተ ከሰበክሁ በኁዋላ የተጣልሁ እንዳልሆን ስለ እኔ ጸልዩ!