ከሸዋል ወር ስድስት ቀናቶችን እንዲሁም ሰኞን እና ሐሙስን መጾም የተወደደ መሆኑን የሚናገሩ ሐዲሶችና ማብራሪያዎቻቸው
(በሸይኽ ብን ባዝ - ረሂመሁሏህ -)
عن أبي أيوب – رضي الله عنه - ، أن رسول الله ﷺ قال: من صام رمضان ثم أتبعه ستا من شوال كان كصيام الدهر " مسلم: ١١٦٤
አቡ አዩብ ከረሡል ﷺ ሰምተው የሚከተለውን ሐዲስ አስተላልፈዋል፡- “ረመዷንን የጾመ ከዚያም ከሸዋል ወር ስድስት ቃናቶችን ያስከተለ ልክ አንድ አመት እንደጾመ ይቆጠርለታል፡፡” ሙስሊም: 1164
عن أبي قتادة – رضي الله عنه - ، أن رسول الله ﷺ سئل عن صوم يوم الإثنين فقال : ذلك يوم ولدت فيه ، ويوم بعثت ، أو أنزل علي فيه" مسلم: ١١٦٢
አቡቀታዳህ እንዲህ ይላሉ፡- ሰኞን ቀን መጾምን በተመለከተ የአላህ መልክተኛ ﷺ ተጠየቁ “ይህ (ቀን) የተወለድኩበት ቀን ነው፤ (መልክተኛ ሆኘ) የተላኩበት ቀን ነው፤ ወይም (ቁርአን) በእኔ ላይ የተወረደበት ቀን ነው፡፡” በማለት ምላሽ ሰጡ፡፡ ሙስሊም: 1162
عن أبي هريرة – رضي الله عنه - عن رسول الله ﷺ قال: تعرض الأعمال يوم الإثنين والخميس ، فأحب أن يعرض عملي وأنا صائم" الترمذي: ٧٤٧، ورواه مسلم: ٢٥٦٥ بغير ذكر الصوم.
አቡሁረይራ - ረዲዬሏሁ ዓንሁ - ከረሡል ﷺ ሰምተው የሚከተለውን ሐዲስ አስተላልፈዋል፡- “ሰኞ እና ሐሙስ ስራዎች ይቀረባሉ፤ ጾመኛ ሆኘ ስራየ (ከአላህ ዘንድ) እንዲቀረብልኝ እወዳለሁ፡፡” (ቲርሚዝይ: 747, ጾምን ሳያወሱ ሙስሊም: 2565 በሌላ ዘገባ ዘግበውታል፡፡)
وعن عائشة رضي الله عنها ، قالت : كان رسول الله صلى الله عليه وسلم يتحرى صوم الإثنين والخميس" الترمذي: ٧٤٥
አኢሻ - ረዲዬሏሁ ዓንሃ - የሚከተለውን ተናግራለች፡- “የአላህ መልክተኛ የሰኞን እና የሐሙስን ጾም (ለመጾም በጉጉት) ይጠባበቁ ነበር፡፡” (ቲርሚዚይ: 745)
እነዚህን ሐዲሶች አስመልክቶ ሸይኽ ብን ባዝ - ረሂመሁሏህ - የሚከተለውን ትንታኔ ሰጠዋል፡-
ምስጋና ለአላህ ፤ ሶላትና ሰላምታ ደግሞ በአላህ መልክተኛ፣ በቤተሰቦቻቸው፣ በባልደረቦቻቸው እና በእርሳቸው መመሪያ በተመሩት ላይ ሁሉ ይስፈን፡፡
ከዚህ በመቀጠል፡
ከላይ የተጠቀሱት ሐዲሶች ከሸዋል ወር ስድስት ቀናቶችን እንዲሁም ሰኞና ሐሙስን መጾም የተወደደ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ አላህ - ሱብሃነሁ ወተዓላ - በእኛ ላይ ግዴታ ያደረገው ጾም የረመዷን ጾም ሲሆን እነዚህ ጾሞች ግን የሱና ጾሞች ናቸው፡፡ ከረመዷን ወር ጾም ውጭ ያለው ሁሉ ትርፍ ጾም ነው፡፡ ከትርፍ ጾሞች ሁሉ በላጩ የዳውድ ጾም በመባል የሚጠራው ሲሆን፤ እርሱም አንድ ቀን መጾም አንድ ቀን ማፍጠር ነው፡፡ ሰኞ እና ሐሙስ እንዲሁም በወር ሶስት ቀናቶችን መጾም ሱና ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ከሸዋል ስድስት ቀናቶችን መጾምም የተወደደ ነው፡፡ የሸዋል ስድስት ቀናቶችን መጾም የተወደደ ለመሆኑ አቡ አዩብ ከረሡል ﷺ ሰምቶ ያስተላለፈው የሚከተለው ሐዲስ ነው፡-
“ረመዷንን የጾመ ከዚያም ከሸዋል ወር ስድስት ቃናቶችን ያስከተለ ልክ አንድ አመት እንደጾመ ይቆጠርለታል፡፡” (ሙስሊም: 1164)
ይህ ሐዲስ ጥቅል የሆነ መልክት አለው፡፡ አንድ ሰው ረመዷንን ጾሞ ከሸዋል ወር ከመጀመሪያም ይሁን ከመካከል ወይም መጨረሻ አነጣጥሎም ይሁን አከታትሎ ስድስት ቀናቶችን ከጾመ አመቱን እንደጾመ ይቆጠርለታል፡፡
የመጨረሻዎቹ ሐዲሶች ደግሞ ሰኞ እና ሐሙስ ቀናቶችን መጾም ያለውን ደረጃ ይጠቁማል፡፡ በነዚህ ሁለት ቀናቶች ስራዎቻችን ወደአላህ የሚቀርቡበት በመሆኑ ከሌሎች ቀናቶች ለየት ይላሉ፡፡ በመሆኑም በእነዚህ ቀናቶች መልካም ስራን ማብዛት ይገባል፡፡ ከመልካም ስራዎች መካከል ጾም ይገኝበታል፡፡ ረሡል ﷺ በሆነ ስራ ካልተጠመዱ በቀር ጾም ለመጾም (ቀናቶችን) ይጠባበቁ ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜ ተራውን ይጾማሉ ፤ አንዳንድ ጊዜ በሆነ ነገር ከተጠመዱ ተራውን ያፈጥራሉ፡፡
ሙእሚን የሆነ ሰው ተስማሚውን እና ጥቅም ያለውን መርጦ ይሰራል፡፡ ጾም ከገራለት ይጾማል፤ በሌላ ነገር ከተጠመደ ቢያፈጥር ችግር የለውም፡፡ አንዳንድ ጃሂል የሆኑ ሰዎች አንድ አመት ሙሉ ትርፍ ጾሞችን በተከታታይ ከጾሙ በሁለተኛው አመት የግድ በተከታታይ ካልተጾመ ችግር የሚኖረው ይመስላቸዋል፡፡ እነዚህ ትርፍ ጾሞች እንደአመችነታቸው የሚጾሙ እንጅ ግዴታ አይደሉም፡፡ ሰኞን እና ሐሙስን የሚጾም በሆነ ምክንያት አልፎ አልፎ ቢያፈጥር ጉዳት የለውም፡፡ ዋናው ነገር መልካም ስራዎችን እንደአመችነታቸው ተጠባብቆ መፈጸም ነው፡፡
ሙእሚኖች ለመልካም ነገሮች ጉጉቱ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ሰኞ እና ሐሙስን መጾም፤ በየወሩ አስራ ሶስት፣ አስራ አራት እና አስራአምስተኛው ቀን መጾም፤ ከሸዋል ስድስት ቀናቶችን መጾም ፤ ዚክር (ተስቢህ ተህሊል ተህሚድ ማብዛት) ፤ ቁርአን መቅራት ፤ በሽተኛን መጠየቅ ፤ ወደተውሂድ ጥሪ ማድረግ ፤ ሰዎችን መልካም ነገር ማስተማር፤ በመልካም ማዘዝ፤ ከመጥፎ መከልከል የዘወትር ተግባራችን ሊሆን ይገባል፡፡
ሙእሚን አጋጣሚዎችን ይጠቀማል ፤ ጊዜውን ሳያባክን አላህ ለሚወደውና ወደርሱ ለሚያቃርበው ተግባር ይጠቀማል ፤ በቤቱም፤ በመንገዱም፤ በመስጅዱም ፤ በሁሉም ቦታ በሚሰራቸው ስራዎች ሁሉ የአላህን ሰዋብ (ምንዳ) ተስፋ ያደርጋል ፤ የአላህን ቅጣት ይፈራል፡፡
وفق الله الجميع
شرح رياض الصالحين لابن عثيمين بتعلق بن باز المجلد الثالث ص\٣٦٩-٣٧٠
የባህር ዳር አህለሱና መሻይኾች ገፅ
https://t.me/alateriqilhaqكن على بصيرة