የጠቅላይ ሚኒስትር ፅፈት ቤት የግድቡን ውሃ ሙሊት ለማራዘም ኢትዮጵያ አልተስማማችም የሚል መግለጫ አውጥቷል። ይህ እውነት ከሆነ ጥሩ ነው። ነገር ግን ይህንን ጉዳይ ግብፆች ለሚዲያ ፍጆታ አጣመው እስኪያቀርቡ ድረስ የመንግስት ሰዎች ዝም ማለታቸው ተገቢ ካለመሆኑም በላይ በዚህ ላይ ተመስርቶ ዜጎች ያላቸውን ስጋት መግለፃቸው ሊያስወግዛቸው አይገባም። ሁሉን ነገር በፓለቲካ አይን እያየን ምክንያታዊ ትችቶችን ዜጎች ሲያቀርቡ ዝም ብሎ በደፈናው መውቀስ የራስን የድብብቆሽ አካሄድ ስህተትን መካድ ነው። የግድቡ ጉዳይ የሁላችንም ነው፤ ማንም ከማንም የበለጠ ያገባኛል ሊልበት የማይችለው የሃገሪቱን ሁሉም ህዝቦች የሚያገናኝ ዋልታ ነው። መንግስት ብቻውን የግሉ ጉዳይ ሊያደርገው አይችልም። ሌላው መንግስት ያወጣው መግለጫ ትክክል ከሆነ በአስቸኳይ የግብፅን አምባሳደር ጠርቶ በጉዳዩ ላይ የግብፅ መንግስት ማብራሪያ ወይም ማስተባበያ እንዲሰጥ ሊደረግ ይገባል። የኢትዮጵያን አቋምም ለተለያዩ አለም አቀፍ ሚዲያዎች በቶሎ ማሳወቅ ያስፈልጋል። ለወደፊቱ ደግሞ እንዳሁኑ ሌላ ክስተት እንዳይፈጠርና ኢትዮጵያ በሚዲያው የተከፈተባትን ጦርነት ለመቋቋም እንድትችል በጉዳዩ ላይ በየጊዜው በተለያዩ ቋንቋዎች መግለጫ የሚሰጥበት ስርዓትና የህዝብ ግኑኝነት ስልት (Public Relations Strategy) ያስፈልጋታል። በተጨማሪም የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ሰዎችን ያቀፈ ቡድን መመስረት ተገቢ ነው።