አለሁ በመዳፉ!➡️➡️🗣️🗣️
ነፍስህን ለማረስረስ፣ ውስጥህን በሐሴት ለመሙላት፣ የአምላክህን በረከት በእጥፉ ለማትረፍ፣ ከዓለም ጫጫታ ፋታ ለመውሰድ፣ ምድራዊውን የማያልቅ መከራ ለመሻገር ይህን ንግግር ከእግዚአብሔር አምላክህ ጋር ተነጋገር። "በሃጢአት አዙሪት፣ በበደል እርካብ፣ በጥፋት ከበባ ውስጥ ውድቄ እንኳን ቢሆን ቀና ያደረከኝ አንተ ነህ፤ "አይዞህ ልጄ" ብለህ የደገፍከኝ አንተ ነህ። ጥፋት የለመደው ማንነቴ ከጥፋቱ ባይመለስ፣ በክፋት የታወረው ሃሳቤ በእራሱ ባይገራ፣ ሃጢያትን መስራት ያልታከቱ እጆቼ፣ የሰውን በደል መመልከት፣ የሰውን ለቅሶ ማማተር ያላቆሙ አይኖቼ፣ ክፋትን እየመረጠ የሚሰሙት ጆሮዎቼ፣ ከመልካሙ ይልቅ ለመጥፎው የሚነቃው፣ ወደክፋቱ የሚሳበው ልቤ ካንተ ቢያርቁኝም አንተ ልትፈልገኝ ሁሌም አብረሀኝ አለህ። አይተህ እንዳላየህ አልፈሀኛል፣ ሰምተህ እንዳልሰማህ ተተህልኛል፣ እንዳላጠፋው፣ እንዳልበደልኩ፣ እንዲሁ እንደፃድቅ አቅፈህ ደግፈህ በምህረትህ ቃኝተሀኛል፤ በይቅርታህ ጎብኝተሀኛል።
አዎ! እኔ እራሴን ካልጣልኩ፣ እኔ እራሴ ላይ ካልጨከንኩ፣ እኔ እራሴን ካልበደልኩ፣ እኔ ለእራሴ እንቅፋት ሆኜ ካልወደኩ አንተ በፍፁም ጥለሀኝ፣ ጨክነህብኝ፣ በድለሀኝ አታውቅም። እራሴን ያወኩ እየመሰለኝ ብዙ ሳትኩኝ፣ እራሴን የጠቀምኩ እየመሰለኝ ብዙ የማይሆን ጎዳናን መረጥኩኝ፣ የሚያዋጣ መንገድን የተከተልኩ እየመሰለኝ ለጥፋቴ ተቃረብኩኝ። በመሰለኝ እሳቤ ባልድንም፣ በሰበብ አስባቡ እራሴን መታደግ ባይቻለኝም፣ ከገዛ ጥፋቴ በፍጥነት ባልማርም፣ ከሳትኩት መንገድ ቶሎ ባልመለስም ባንተ ፍቃድና ይሁኝታ ግን እነሆ ዛሬ ከጥፋቴ ተምሬ፣ ከአጠፊዬ አምልጬ፣ ከመሰናክሌ አልፌ አንተ ፊት ቆሜያለሁ። በብዙ አንፀሀኛልና አመሰግንሃለሁ፤ እንደ አዲስ ሰርተሀኛልኛ አከብርሃለሁ፤ ከእኔ በላይ አንተ አውቅህልኛልና ዘወትር ስምህን አወድሳለሁ፣ ሁሌም ከፍ ሳደርግህ ከፍ እያልኩኝ እኖራለሁ።"
አዎ! ጀግናዬ..! ከአምላክህ ጋር ስትነጋገር እራስህን እንደ አዲስ ትሰራዋለህ፣ የእግዚአብሔር አምላክህን ድንቅ ተዓምርና ውለታ ስታስብ ውስጥህ በመረጋጋት ይሞላል፣ የእርሱን አዳኝነት፣ የእርሱን ይቅርባይነት፣ የእርሱን አዛኝነት ስታስታውስ የእርሱ ልጅ በመሆንህ ሐሴትን ታደርጋለህ። ድጋፍ ባጣህ ሰዓት እንደደገፈህ እንዳትረሳ፣ የምታዋየው ባጣህ ሰዓት ያዋየህ፣ ጭንቀትህን የሰማህ፣ ትኩረት ሰጥቶ የተመለከተህ እርሱ እንደሆነ አስታውስ። በምንም ሁኔታ ውስጥ ብትሆን እንኳን
"አለሁ በአምላኬ መዳፍ!" ማለትን አትፍራ። እምነትህ መሸሸጊያ ይሆንሃል፤ በእርሱ መታመንህ ከአጣብቂኙ ያወጣሃል፤ በእርሱ መደገፍህ ክንድህን ያበረታዋል፤ ማዳኑን መጠባበቅህ፣ ይቅርታውን መማፀንህ ፅናትን ይሰጥሃል፤ ትዕግስትን ያለብስሃል። በአምላክህ መታመንህን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር አስመስክር፤ ከንግግር በዘለለ በህይወትህ ውስጥ ገልጠህ አሳየው።
ውብ ምሽት ይሁንልን! 🌘🌒✨💫
✍️ (Epha A.)
ምክረ-አዕምሮ ለተሻለ ነገ! 🦋
#SHARE እንዳይረሳ ቤተሰቦች! 🙏
በ
YouTube አማራጭ ይቀላቀሉን!
🔺🔻
SUBSCRIBE NOW https://www.youtube.com/channel/UCIZv4h3iDx2C7CGbv9WIkVg?sub_confirmation=1ምክረ-አዕምሮ/
@mikre_aimro 😊 💪