"የተወደደች የእግዚአብሔር ዓመት"
ሉቃ 4÷17
አዋጅ፣ አዋጅ፣ አዋጅ፣ ማቴዎስ ተሻረ ማርቆስ ተሾመ፡፡
እንኳን ለ፳፻፲፬.ዓ/ም በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን፡
ያሳለፍነው ዓመት ጥሩ አልነበረም፡
✔.በሞትና በሕይወት መካከል ያለፍንበት፡
✔.ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ የተነሳሳበት፡
✔.የኢትዮጵያ ምድር አኬልዳማ ሆና የደም ምድር የተባለችበት
✔.ወንድም ወንድሙን አባት ልጁን የገደለበት፡
✔.ዐባይን ስንገድብ አሳባችን አልገደብ ብሎ ደም የፈሰሰበት፡
✔.አንድነት እየሰበክን የተለያየንበት፡
✔.የእርሻ መሳሪያዎች የጦር መሳሪያ የሆኑበት
✔.የገበሬው እርሻ የጦር ማሳ የሆነበት፡ ✔.ከኢትዮጵያዊነት ርቀን ከሰውነት ወጥተን በባእድ ቁጥቋጦ ሥር የተደበቅንበት ሌላም ሌላም ሌላም የሆንበት ዓመት ነበረ፡፡
የ፳፻፲፫ ዓ/ም የአሮጌው ዓመት መጨረሻ ቀን ጳጉሜ ፭ ዐርብ ዕለት ዋለ:: ዐርብ ማለት መግቢያ፣ መካተቻ፣ የፍጥረት መጨረሻ ቀን፣ የሰው ልጆች ቀዳማዊና ደሀራዊ ልደት መጀመሪያ ቀን ሲሆን የአዳም ልጆች መከራ በመስቀል ላይ የተጠናቀቀበትና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተፈጸመ ብሎ ነፍሱን ለሰው ልጆች ቤዛ አድርጎ የሰጠበት ቀን ነው፡፡
ስለዚህ ዘንድሮ አዲሱ ዓመት ፳፻፲፬ ዓ/ም የመከራ ማብቂያ የደስታችን መጀመሪያ የተወደደች የእግዚአብሔር ዓመት ናት፡፡ የዓመቱ መጀመሪያ መስከረም ፩ ቀን ቅዳሜ ዕለት ዋለ፡፡ ቅዳሜ ደግሞ እግዚአብሔር ፍጥረትን ሁሉ ከእሑድ እስከ ዐርብ ድረስ በየወገኑ ፈጥሮ ከሥራ ሁሉ ያረፈባት ጥንተ ዕረፍት ናት፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው ወደ አይሁድ ምኩራብ ገብቶ የኢሳይያስን ትንቢት ተርጉሞ "የተወደደቺው የእግዚአብሔር ዓመት" እነሆ ብሎ የሰበከበት" ጥንተ ስብከት ነው፡፡
በዚህ በአዲሱ ዓመት የተሾመው መጋቢ ወንጌላዊው ቅዱሰ ማርቆስ ነው፡ ቅዱስ ማርቆስ ደግሞ ቁጥሩ ከ፸፪ቱ አርድዕት ሆኖ ከ፬ቱ ወንጌላውያን ፩ዱ ነው፡፡ የሚያስተምር፣ የሚገስጽ፣ የሚያጽናና መምህር ነው፡፡ ስለዚህ ዘንድሮ ከጦርነትና ከሞት፣ ከረሀብና ከስደት፣ ከመለያየትና እርስ በእርስ ከመገፋፋት፣ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ የምናርፍበት የተወደደ የእግዚአብሔር ዓመት ነው፡፡ዘንድሮ ዘመኑ የትምህርትና የንስሐ፣ የሰላምና የፍቅር፣ የመረጋጋትና የመጽናናት ዘመን ነው፡፡
ቅዱስ ማርቆስ በአንበሳ ይመሰላል፡፡ አንበሳ የእንስሳትና የአራዊት ሁሉ ንጉሣቸው ስለሆነ ጫካ ውስጥ ሲጮህ በሰሙ ጊዜ እንስሳት አራዊት ይሸበራሉ ይንቀጠቀጣሉ፡፡ ቅዱስ ማርቆስም ወደ ግብጽ ወርዶ ማስተማር በጀመረ ጊዜ የግብጽ ጣዖታት ሁሉ ተሰባበሩ፡ ሰዎችም የወንጌላዊው ማርቆስን ትምህርት ሰምተው ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፡ ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ተመልሰው የእግዚአብሔር ልጆች ሆነዋል፡፡
እኛም ኢትዮጵያውያን በአንበሳ እንመሰላለንና ዘንድሮ እራሳችንን የምናስከብርበት፣ ጭራ ከመሆን እራስ ወደመሆን የምናድግበት፣ ግብጻውያንና ሌሎችም አገራት ድምጻችንን ሰምተው፡ ተምረውና ተገስጸው ከኢትዮጵያ ጋር ከጥላቻ ይልቅ ለወዳጅነት የሚሠሩበት ዓመት እንዲሆን ይቺ ዓመት "የተወደደች የእግዚአብሔር ዓመት" ናት፡፡
በድጋሚ እንኳን ከዘመነ ማቴዎስ ወደ ዘመነ ማርቆስ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ፡፡
✍መ/ሃ/ብሥራት ገ/ሥላሴ
@MekuriyaM