😘አፍቄሜሌፅ (የፍቅር ቃል እድሜ)
(በላይ በቀለ ወያ)
.
.
ፍቅርን ያህል ነገር
ተሸክሜ ስኖር ፣ በልቤ ትከሻ
"ቃል አጠረኝ" የሚል
ቃል ካፌ አይወጣም ፣ ላወድስሽ ስሻ።
እንደውም ሳፈቅር ፣ ቃል ነው የሚተርፈኝ
እንኳንስ ቃል ሊያጥረኝ
ሁሉ ያጥርብኛል
በልብሽ ቅርፅ ውስጥ ፣ መውደድሽ ሲያገዝፈኝ
ቃልም ነው በመንፈስ
ልሳን እየሰጠ ፣ የሚያስለፈልፈኝ ።
ሻምጵራ ቅራንጳ
ወዘ ትሩሩጳ
አፍረንትረን ደስቴ
ፄፃቱ ጳፃቴ
ወኡዝ ሀአሪከ
አዝወረ ነባከ
ፊፀአ ነአቱ
ጀነወ ርዕቱ
ናፃ ፄላሟሜ
እናልሽ አለሜ
አዲስ ፊደል ባልቀርፅ ፣ አዲስ ቃል ቀምሜ
ትርጉሙ እንዲገባሽ
የልሳን ቃሎቼን ፣ በአንዲት ቃል ተርጉሜ
"አፍቄሜሌፅ" አልኩሽ!
አፍቄሜሌፅ ማለት ፣ በኔ ትርጓሜ
ሁሉ ያጥራል እንጂ
አያጥርም ማለት ነው ፣ የፍቅር ቃል እድሜ።
።።።።።።።
ሳፈቅርሽ ይህ ሆነ...
ሰፊ ያልሁት አለም ፣ ባንድ እርምጃ አለቀ
ሳልሄደው ሚደክመኝ...
ተራራና ጋራው ፣ ከግሬ ስር ጠለቀ።
"ሩቅ" ያልሁት ሰማይ..
ሩቅ የሚመስለኝ ፣ ነካሁት በስንዝር
ጨረቃና ፀሀይ....
ከኮከብ ያንሳሉ ፣ ከፍቅርሽ ግዝፈት ስር።
.......................................
ሳፈቅርሽ ይህ ሆነ...
ንጉስን ከዙፋን ፣ ማርከው የሚያወርዱ
የሀያላንን አቅም ፣ በጥቅሻ ሚያርዱ
ቆነጃጅት ሴቶች ...
"ቃል አጠረኝ" በሚል ቃላት የተሞሉ
ከፍቅርሽ ግዝፈት ስር..
ቃል ተገኝቶላቸው ፣ "ፋንጋዎች" ተባሉ።
.........................................
ሳፈቅርሽ ይህ ሆነ...
"ቃል አጠረኝ "በሚል...
ባፍቃሪ አንደበት ፣ ቃል ተትረፈረፈ
ሁሉን አሳንሶ...
በልቡ ቅርፅ ውስጥ ፣ ፍቅሩን አገዘፈ
አለሙን ሰርዞ ፣ ፍቅሩን ብቻ ፃፈ!!!
..........................................
ሳፈቅርሽ ይህን አልኩ...
ፍቅርን ተሸክሞ ፣ የሚኖር ልቦና
ሁሉም ከፍቅርሽ ስር ፣ መሆኑን አውቅና
አንቺን ለማወደስ .፣..እኔም ቃል ያጥረኛል
"ቃል አጠረኝ "ማለት...
ቃል እንደሆነ ግን ፣ ፍቅርሽ ይነግረኛል!!!
ሻምጵራ ቅራንጳ
ወዘ ትሩሩጳ
አፍረንትረን ደስቴ
ፄፃቱ ጳፃቴ
ወኡዝ ሀአሪከ
አዝወረ ነባከ
ፊፀአ ነአቱ
ጀነወ ርዕቱ
ናፃ ፄላሟሜ
እናልሽ አለሜ
አንደበት ዝም ቢል
ዝም አይልም አይኔ ፣ ዝም አይልም ጥርሴ
ቃል አለው ጆሮዬ ፣ ዝም ቢል ምላሴ።
ዝም አይልም እጄ ፣ ዝም አይልም እግሬ
እኔ ቃል ቢያጥረኝም
ሰማይና ምድሩ
ፈጣሪና ፍጡሩ
ለፍቅር ቃል አለው ፣ ይናገራል ፍቅሬ።
።።።።።
ትርጉም ብንሰጠው
ጥላቻ በራሱ ፣ ለፍቅር አለው ቋንቋ
"አፍቄሜሌፅ" አልኩሽ
የፍቅር ቃል እድሜ
ከዘላለም የሚያልፍ ፣ ዘላለም ነው በቃ።
ሀዘሩ ጣሪቃ
ሉፋሴ ጰኑቃ
ሪድዋ ሸዛጨ
አገቀ ጠየጨ
@momvsdad 👈