ኩኒስ ኒደርባ
~አንድ ወዳጄ ያጫወተኝን እየከተብኩ ነው። በጥንት ዘመን ወደ አንዲት የገጠር መንደር ጎራ ያለ መንገደኛ በሕይወት ዘመኑ አጋጥሞት የማያውቅ እንግዳ ነገር ይታዘባል ። ነገሩ እንዲህ ነው :-
መንገደኛው ዓይኖቹን አሻግሮ ሲመለከት አንድ ገበሬ ማሳውን በማረስ ላይ ነበር። ገበሬ ማረሱ ምን ይደንቃል? ዳሩ ግን የሚያርስበትን ቀንበር ተሸክመው ሞፈሩን የሚስቡት አንድ በሬና ሌላ አንድ ሰው ተጠምደው ማየቱ ነበር ዓይኖቹ ከቦታቸው ተበልጥጠው እንዲወጡ ያደረገው። መንገደኛው ክስተቱን እንደዋዛ ሊያልፈው አልቻለም። ወደተጠመደው ሰው ጠጋ አለና :-
"ምነው ወንድሜ እንዲህ ሆንክ? " ሲል ልቡ በሀዘን ተሞልቶ ይጠይቀዋል ። በባርነት ወይም በችግር ብዛት ሳቢያ ለዚህ መዳረጉን እያብሰለሰለ ትክክለኛ ምክንያቱን ለመስማት በጉጉት ተጠባበቀ። ከሰውየው የሰማው አጭር መልስ :- "ኩኒስ ኒደርባ " የሚል ነበር ። በኦሮምኛ ቋንቋ "ይሄም ያልፋል " እንደማለት ነው። መንገደኛው በመልሱ እየተገረመ ጉዞውን ቀጠለ ።
ከአመታት ቆይታ በኋላ በዛችው መንደር ሲያልፍ "ስለዛ ከበሬ ጋር ተጠምዶ ሲያርስ ስለነበረው መከረኛ ሰው ማጠያየቅ አለብኝ "ሲል አሰበ።
የመንደሯ ሰዎች የሚያስደንቅ ዜና አበሰሩት።
"ያሰውማ ያን ሁሉ መከራ አልፎ ንጉስ ለመሆን በቃ! "
ዜናውን ማመን አልቻለም ቤተመንግሥት ሄዶ ማግኘት እንዳለበት ወሰነ። በርግጥም ያሰው ለንግስና መብቃቱን በዓይኑ በብረቱ ማረጋገጥ ፈልጓል። ቤተመንግስቱ እልፍኝ ውስጥ በዙፋኑ ላይ ተሰይሞ የተመለከተው ሰው በርግጥም ከበሬ ጋር ተጠምዶ ሲያርስ የነበረው ሰው ሆኖ አገኘው። መንገደኛው በአክብሮት እጅ ከነሳ በኋላ ንጉሱ በአንድ ወቅት ከነበረበት አስከፊ ሁኔታ ተላቆ ለዚህ ታላቅ ክብር መብቃቱ በእጅጉ አስገራሚ መሆኑን ገለፀ። ንጉሱ ግርማ ሞገስ በተላበሰ ሁኔታ የመንገደኛውን ንግግር ካደመጠ በኋላ የሰጠው ምላሽ
"ኩኒስ ኒደርባ " የሚል ነበር።
"ይሄም ያልፋል " መንገደኛው ከዓመታት በፊት የሰማው አይነት መልስ በማድመጡ በመደነቅ ጉዞውን ቀጠለ ።ከተወሰኑ አመታት በኋላ ለስራ ጉዳይ ወደዛችው ግዛት ያቀናል። ስለ ንጉሱ ማጠያየቁ አልቀረም። ንጉሱ ከዚህ አለም መሰናበቱ ተነገረው። መንገደኛው ልቡ በሀዘን ተነክቶ "ኩኒስ ኒደርባ " የሚለውን ቃሉን እያሰበ ዓይኑ እንባ አቀረረ። "ይሄም ያልፋል "!
ሲል አሰበና የአካባቢውን ሰዎች ንጉሱ የተቀበረበትን የመቃብር ቦታ እንዲጠቁሙት ጠይቆ ወደዚያው አመራ። የንጉሱ መካነ መቃብር ላይ አንድ ጽሁፍ በጉልህ ተፅፎ ይታያል።በንጉሱ ኑዛዜ የተፃፈው ጽሁፍ " ኩኒስ ኒደርባ "
የሚል ነበር። መንገደኛውም በማለት እየቆዘመ መንገዱን ቀጠለ።
ከጥቂት ዓመታት ቆይታ በኋላ መንገደኛው ወደዛች ግዛት ጎራ ማለቱ አልቀረም። የንጉሱ መቃብር ይታወሰውና አካባቢውን ለመቃኘት ወደ መቃብር ቦታው ያቀናል ። የተመለከተው ነገር የሚያስገርም ነበር። አካባቢው ሙሉ ለሙሉ ተለውጧል። የመካነ መቃብሮቹ ፋና ሙሉ ለሙሉ ጠፍቶ በቦታቸው ሰፋፊ መንገዶች ወጥተዋል ፤በርካታ ቤቶች ተገንብተዋል ። መንገደኛው ባለፉት አመታት ውስጥ ያያቸው ለውጦች በህሊናው እያውጠነጠነ በዝምታ ተዋጠ። እነኚህን መንገዶችና ቤቶችም መለወጣቸው አይቀሬ እንደሆነ እርግጠኛ ሆነ። የርሱን ፈቃድ ሳይጠይቅ ምላሱ አንድ እውነታን አጉተመተመ :-
" ኩኒስ ኒደረባ " አለ ጭንቅላቱን ላይና ታች እየወዘወዘ። " ይሄም ያልፋል "
*
ለውጥ
@nejashin @nejashin@nejashin✧✧✧✧✧✧✧✧✧✧✧✧✧