በበጎ ነገር ማዘዝ ከክፉ ነገር መከልከል ትልቁ የእስልምና መርህ ነው!!—————
ወደ አላህ ጠቃሚ በሆነ ኢስላማዊ እውቀት ላይ ሆነህ፣ የአላህን ፊትና የመጨረሻውን ሀገር ፈልገህበት በኢኽላስ ተጣራ!!። በመልካም ስታዝ ከመጥፎ ስትከለክል በተለይ ረድ ስታደርግና አለያም ለተደረጉ ረዶች ምላሽ ስትሰጥ ስሜታዊነት፣ ቡድንተኝነት፣ የግል ጥቅም፣ እልሀኝነትና ቂም በቀል ያልታከለበት ለአላህ ፊት መሆን መቻል አለበት!!። ይህ ሲሆን የምታደርገው ጥሪ ከመጥፎ መከልከሉ፣ በመልካም ማዘዙም ሆነ አለያም በጥፋት ባለ ቤቶች ላይ እርምት ስትሰጥ… ሌሎች የተቀደሱ ተግባሮችም ውጤታማ ይሆናሉ።
አላህ በተቀደሰው ቃሉ እንዲህ ብሏል:-
{وَمَنْ أَحْسَنُ قَوْلًا مِّمَّن دَعَا إِلَى اللَّهِ وَعَمِلَ صَالِحًا وَقَالَ إِنَّنِي مِنَ الْمُسْلِمِينَ}
«ወደ አላህ ከጠራና መልካምንም ከሠራ፣ እኔ ከሙስሊሞች ነኝ፣ ካለም ሰው ይበልጥ ቃሉ ያማረ ማን ነው?።» ፉሲለት 33
በሌላ የቁርኣን አንቀፅም አላህ እንዲህ ብሏል:-
{ادْعُ إِلَىٰ سَبِيلِ رَبِّكَ بِالْحِكْمَةِ وَالْمَوْعِظَةِ الْحَسَنَةِ ۖ وَجَادِلْهُم بِالَّتِي هِيَ أَحْسَنُ ۚ إِنَّ رَبَّكَ هُوَ أَعْلَمُ بِمَن ضَلَّ عَن سَبِيلِهِ ۖ وَهُوَ أَعْلَمُ بِالْمُهْتَدِينَ}
«ወደ ጌታህ መንገድ በብልሃትና በመልካም ግሳፄ ጥራ፡፡ በዚያችም እርሷ የበለጠ መልካም በሆነችው ተከራከራቸው፡፡ ጌታህ እርሱ ከመንገዱ የተሳሳተውን ሰው አዋቂ ነው፡፡ እርሱም ቅን የሆኑትን ሰዎች አዋቂ ነው፡፡» አን-ነህል 125
በመልካም ማዘዝ ከመጥፎ መከልከል ትልቅ የሆነ ኢስላማዊ መርህ ነው። ከመጥፎ መከልከል ውስጥ በጥፋት ባለ ቤቶች ላይ ምላሽ መስጠትም ይካተታል።
አምላካችን አላህ እንዲህ ብሏል:-
{يُؤْمِنُونَ بِاللَّهِ وَالْيَوْمِ الْآخِرِ وَيَأْمُرُونَ بِالْمَعْرُوفِ وَيَنْهَوْنَ عَنِ الْمُنكَرِ وَيُسَارِعُونَ فِي الْخَيْرَاتِ وَأُولَٰئِكَ مِنَ الصَّالِحِينَ}
«በአላህና በመጨረሻው ቀን ያምናሉ፡፡ በፅድቅ ነገርም ያዛሉ፡፡ ከመጥፎ ነገርም ይከለክላሉ፡፡ በበጎ ሥራዎችም ይጣደፋሉ፡፡ እነዚያም ከመልካሞቹ ናቸው፡፡» ኣል-ዒምራን 114
አላህ እንዲህ ብሏል:-
{وَالْمُؤْمِنُونَ وَالْمُؤْمِنَاتُ بَعْضُهُمْ أَوْلِيَاءُ بَعْضٍ ۚ يَأْمُرُونَ بِالْمَعْرُوفِ وَيَنْهَوْنَ عَنِ الْمُنكَرِ وَيُقِيمُونَ الصَّلَاةَ وَيُؤْتُونَ الزَّكَاةَ وَيُطِيعُونَ اللَّهَ وَرَسُولَهُ ۚ أُولَٰئِكَ سَيَرْحَمُهُمُ اللَّهُ ۗ إِنَّ اللَّهَ عَزِيزٌ حَكِيمٌ}
«ምእምናን ምእምናትም ከፊሎቻቸው ለከፊሉ ረዳቶች ናቸው፡፡ በመልካም ነገር ያዛሉ፤ ከክፉም ይከለክላሉ፡፡ ሶላትንም ይሰግዳሉ፡፡ ዘካንም ይሰጣሉ፡፡ አላህንና መልክተኛውንም ይታዘዛሉ፡፡ እነዚያን አላህ በእርግጥ ያዝንላቸዋል፡፡ አላህ አሸናፊ ጥበበኛ ነውና፡፡» አት-ተውባ 71
አላህ በሉቅማን ምላስ እንዲህ አለ:-
{يَا بُنَيَّ أَقِمِ الصَّلَاةَ وَأْمُرْ بِالْمَعْرُوفِ وَانْهَ عَنِ الْمُنكَرِ وَاصْبِرْ عَلَىٰ مَا أَصَابَكَ ۖ إِنَّ ذَٰلِكَ مِنْ عَزْمِ الْأُمُورِ}
«ልጄ ሆይ! ሶላትን አስተካክለህ ስገድ፡፡ በበጎ ነገርም እዘዝ፡፡ ከሚጠላም ሁሉ ከልክል፡፡ በሚያገኝህም መከራ ላይ ታገስ፡፡ ይህ በምር ከሚያዙ ነገሮች ነው፡፡» ሉቅማን 17
አላህ እንዲህ ብሏል:-
{لُعِنَ الَّذِينَ كَفَرُوا مِن بَنِي إِسْرَائِيلَ عَلَىٰ لِسَانِ دَاوُودَ وَعِيسَى ابْنِ مَرْيَمَ ۚ ذَٰلِكَ بِمَا عَصَوا وَّكَانُوا يَعْتَدُونَ۞ كَانُوا لَا يَتَنَاهَوْنَ عَن مُّنكَرٍ فَعَلُوهُ ۚ لَبِئْسَ مَا كَانُوا يَفْعَلُونَ}
«ከእስራኤል ልጆች እነዚያ የካዱት በዳውድና በመርየም ልጅ በዒሳ ምላስ ተረገሙ፡፡ ይህ ትእዛዝን በመጣሳቸውና ወሰንን የሚያልፉ በመሆናቸው ነው፡፡ ከሠሩት መጥፎ ነገር አይከላከሉም ነበር፡፡ ይሠሩት የነበሩት ነገር በእርግጥ ከፋ!።» አል-ማኢዳ 78-79
እንዲህም ብሏል:-
{فَلَمَّا نَسُوا مَا ذُكِّرُوا بِهِ أَنجَيْنَا الَّذِينَ يَنْهَوْنَ عَنِ السُّوءِ وَأَخَذْنَا الَّذِينَ ظَلَمُوا بِعَذَابٍ بَئِيسٍ بِمَا كَانُوا يَفْسُقُونَ}
«በእርሱም የተገሰፁበትን ነገር በተዉ ጊዜ እነዚያን ከክፉ የሚከለከሉትን አዳንን፤ እነዚያንም የበደሉትን ያምፁ በነበሩት ምክንያት በብርቱ ቅጣት ያዝናቸው፡፡» አል-አዕራፍ 165
ከኢብኑ መስዑድ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ተይዞ የአላህ መልእክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል:-
“በመልካም ነገር ያመላከተ ሰው ለርሱ የተገበረው ሰው አይነት ምንዳ አለው።” ሙስሊም ዘግበውታል።
ከአቢ ሁረይራ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ተይዞ ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል:-
“እውቀትን የሚማር ሰው አምሳያ ከዛም የማይናገርበት (ከመጥፎ የማይከለክልበት በመልካም የማያዝበት)፣ ልክ ካዝና ላይ ገንዘብን እንደሚያከማችና ከዛም ምንም ሶደቃ እንደማይሰጥ ሰው ነው።” ሶሂሁ'ል ጃሚዕ
ከኢብኑ መስዑድ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ተይዞ ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል:-
“ማንኛውም ሰው አላህ እውቀት ሰጥቶት ሲያበቀ ያን እውቀት የደበቀ ከሆነ፣ አላህ የቂያማ እለት በጀሀነም ልጓም ይለጉመዋል።” ሶሂሁ'ል ጃሚዕ
ከሁዘይፋ (ረዲየላሁ ዐንሁ) ተይዞ ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ ብለዋል:-
“ነፍሴ በእጁ በሆነው ይሁንብኝ! በመልካም ልታዙ ነው፣ ከመጥፎም ልትከለክሉ ነው፣ ይህ ካልሆነ ግን አላህ ከርሱ ዘንድ የሆነን ቅጣት ሊልክባችሁ ይቀርባል፣ ከዛም ትለምኑታላችሁ እሺ ብሎ ልመናችሁን አይቀበላችሁም!።” ኢማሙ አሕመድ በሙስነዳቸውና ትርሚዚይ በሱነናቸው የዘገቡት ሲሆን አልባኒ በሶሂህ አልጃሚዕ ሀሰን ብለውታል።
አሁን ካለንበት ተጨባጭ አንፃር ይህን ሀዲስ መለስ ብሎ ትኩረት ሰጥቶ ማስተንተኑ ለመንቃት ይበጃል!! አላህ ከልብ የርሱን ፊት ፈልገው፣ የአላህን ዲን (ሀቅን) የበላይ ለማድረግ ብለው ስሜታቸውን ወደ ኋላ አሽቀንጥረው ጥለው ወደ አላህ ከሚጣሩ ሰዎች ያድርገን!!።
✍🏻ኢብን ሽፋ [Ibn Shifa - text]
የተለያዩ ት/ቶችን ለማግኘት የቴሌግራም ቻናላችን ⤵️ #join ያድርጉና ይቀላቀሉ
https://telegram.me/IbnShifahttps://telegram.me/IbnShifa