ወንጀል (ሀጢኣት) ደረጃው ይለያያል!!
———
ይህን ለይቶ ሳይገነዘቡ አቃቂር ለመለቃቀም መሞከር ጅህልናን ቁልጭ አድርጎ ማሳየት ነው።
———
ማንኛውም ወንጀል እንደ ሸሪዓችን ደረጃው ይለያያል። ይህን እጅግ በጣም ጅህልናው የበረታበት ወይም ሰዎች ዘንድ አዋቂ መስሎ መሃይም ካልሆነ በስተቀር ብዙሃን ልዩነቱን ያውቃሉ። ሺርክና ኩፍርም ደረጃው ይለያያል። ሺርክ ወይም ኩፍር ሆኖ ከእስልምና የሚያስወጣ አለ የማያስወጣም አለ። እንዲሁ ከእስልምና የማያስወጡ ወንጀሎችም ከባባድ ወንጀልና ትናንሽ ወንጀል በመባል ደረጃቸው ይለያያል። አላህ በቁርኣኑ ትላልቅ ወንጀልና ትናንሽ ወንጀል እንዳለ ገልፆ በተለየ መልክ ትላልቁን እንድንጠነቀቅ አዞናል:-
إِن تَجْتَنِبُوا كَبَائِرَ مَا تُنْهَوْنَ عَنْهُ نُكَفِّرْ عَنكُمْ سَيِّئَاتِكُمْ وَنُدْخِلْكُم مُّدْخَلًا كَرِيمًا
«ከእርሱ ከተከለከላችሁት ታላላቆቹን (ኀጢአቶች) ብትርቁ (ትናንሾቹን) ኀጢአቶቻችሁን ከእናንተ እናብሳለን፡፡ የተከበረንም ስፍራ (ገነትን) እናገባችኋለን፡፡» አን-ኒሳእ 31
ታላላቅ የሚባሉ ወንጀሎችም ደረጃቸው እንደ ሁኔታው ይለያያል። ለምሳሌ ዝሙትን ብንወስድ እንደ አይነቱ ይለያያል።
1ኛ, አግብቶ የሚያውቅ ሆኖ ዝሙት ቢሰራ ሸሪዓዊ ብይኑ አግብቶ የማያውቅ ሆኖ ዝሙት ከሰራው ጋር እኩል አይደለም!። አግብቶ የሚያውቅ ሆኖ ዝሙት ከሰራ ሸሪዓዊ ብይኑ ተቀጥቅጦ ይገደል የሚል ሲሆን፣ አግብቶ የማያውቅ ሆኖ ዚና የሰራ ሰው ደግሞ 100 ጊዜ ይገረፍ ነው የሚለው። ይህ የቁርኣንና የሀዲስ ማስረጃ የመጣበት ግልፅ ጉዳይ ነው።
ግልፅ ጉዳይ ከመሆኑም አንፃር ለማሳጠር ሲባል ማስረጃዎችን አልጠቀስኩም።
2ኛ, የተለያየ ሲስተም ተጠቅሞ የሚሰርቅ ሌባ፣ ሰዎችን ከንብረታቸው አልፎ ህይወታቸውን አደጋ ላይ ሊጥል በሚችል መልኩ ሺፍታ (ቁጣዑ ጠሪቅ) ሆኖ የሚዘርፍ ሌባ ደረጃው ይለያያል። ብይኑ ላይም አንዱ እጁ ሲቆረጥ ሌላኛው ሊገደል የሚችልበት ሁኔታ አለ።
3ኛ, አንድ ሰው በጎረቤቱ ሚስት የሚሰራው ዚና ከሌላው ጋር እኩል አይደለም!፣ ደረጃው ይለያያል። ይህንም ነቢዩ ﷺ እንዲህ በማለት ገልፀውታል:-
እጅግ በጣም ከባዱ ወንጀል ምንድነው? ተብለው ተጠየቁ፣ “ለአላህ ብጤ ማድረግህ ነው አሉ… ቀጠል አደረጉና በጎረቤትህ ሰው ሚስት ላይ ዝሙት መስራትህ ነው።” አሉ፣ ሙስሊም ዘግበውታል።
ኢማሙ ነወዊይ (ረሂመሁላህ) የሶሂህ ሙስሊምን ኪታብን ሸርህ ሲያደርጉ እዚህ ሀዲስ ላይ እንዲህ አሉ:-
"ይህ ተግባር ከዚናነቱ ባሻገር ሚስትን በባሏ ማበላሸት፣ ልቧንም ከባሏ ዝሙት ወደሰራባት ሰው እንዲዘነበል ማድረግን ያካትታል፣ በመሆኑም እጅግ በጣም ቆሻሻና ፀያፍ ተግባር ነው!፣ ከወንጀል አይነቶችም እጅግ በጣም የከበደ ነው!…” ይላሉ።
ኢብኑል ቀይምም (ረሂመሁላህ) አል-ጀዋቡል ካፊ… በተሰኘው ኪታባቸው በተመሳሳይ ስለ ዝሙት ፀያፍነት ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል:-
“ባል ባላት ሴት ላይ ዝሙት መስራት ባል በሌላት ሴት ላይ ከመስራት ወንጀሉም ቅጣቱም እጅግ በጣም የከበደ ነው!። ምክንያቱም በዚህ ላይ የባልዬውን ፍራሽ ማበላሸትና የእርሱ ያልሆነን ዘር ወደ እርሱ ማስጠጋትም አለበት…” እያሉ የተለያዩ ምክንያቶችን ይጠቅሳሉ።
ሌሎችም መሰል ደረጃቸው የሚለያዩ የወንጀል አይነቶች አሉ። እንግዲህ እነዚህ ወንጀሎች ታላላቅ ወንጀሎች ለመሆናቸው ምንም ጥርጥር የለውም!። ከፍ ዝቅ ያሉት እንደ አፈፃፀማቸው ሁኔታ ነው። ታዲያ በዚህ መልኩ ሌሎችም ወንጀሎች እንደ አፈፃፀማቸው የሚለያዩበት ሁኔታ አለ። ይህን ያህል ከተገነዘብን ዘንድ፣ አንድ ሰው ኡስታዝ ወይም ሸይኽ የሆነ አካል ሙስሊም ሴት ከካፊር ወንድ ጋር መኖር ትችላለች ወይ?! ተብሎ ቢጠየቅና ሲመልስም “አትችልም! በምንም መልኩ አይሆንም ዚና ነው!። ዚና እንኳ ቢሆን ከካፊር ጋር ከማድረግ ሙስሊሙ ጋር ማድረጉ የቀለለ ነው፣ ምክንያቱም ካፊር በዚና ሀራምነት አያምንም፣ በጭለማ ላይ ጭለማ ነው…።” ብሎ ቢመልስ ምኑ ላይ ነው ስህተቱ? ወይም ምኑ ላይ ነው ነውሩ?!።
ይህ ማለት ሁለቱ ሙስሊም የሆኑ ተቃራኒ ፆታዎች ዚና ላይ ቢወድቁ ሀራም ነው የሚለው ነገር ልባቸው ውስጥ ስላለ አንድ ቀን እንኳን አላህ የአንዳቸውን ወይም የሁለታቸውን ልብ ከፍቶት ተውበት ሊያደርጉ ይችላሉ ማለት ነው። ከሀዲው ወንድ ደግሞ የታወቀ ነው ሙስሊሟ ሴት ተውበት ልታደርግ ብትፈልግ አለያም ብታደርግ እንኳ ይጎተጉታታል፣ ተውበት የማድረግ እድል አይሰጣትም፣ ጭራሽ ወደባሰው ኩፍር ይዟት ሊሄድም ይችላል ለማለት ነው። ይህ ደግሞ በተጨባጭ የታየ እውነታ ነው። ስንቶች ናቸው ከሀዲ ወንድ ጋር በዚና ከተጨመላለቁ በኋላ ወደ ኩፍር የጎረፉት?!። አዎን እውነት ነው ይህ በጭለማ ላይ ጭለማ ነው!። ይህ ወንጀሉ የሚበላለጥበት ምክንያት ደግሞ እነ ኢብኑል ቀይም ከላይ እንተቀመጠው ከጠቀሱት ምክንያት ጋር ተመሳሳይ ነው።
የወንጀሉን ክብደት ደረጃ አስቀመጠ እንጂ ዚና ይቻላል አላለም!። አይ ደረጃውን መግለፅ በራሱ ሀላል እንደማድረግና እንደ ማቅለል ነው የሚል ደፋር ጃሂል ካለ፣ አላህ አግብቶ የሚያውቅን ያውም በዲንጋይ ተወግሮ እንዲገደል ሲያዝ አግብቶ የማያውቅ ደግሞ 100 ጊዜ እንዲገረፍ ሲያዝ ለላጤዎች አቅሎ ዚና እንዲሰሩ እየገፋፋ ነው ማለት ነው?! አዑዙ ቢላህ!!። አለያም ከላይ በተቀመጠው አንቀፅ ላይ ታላላቁን ወንጀል በእጅጉ እንድንጠነቀቅ ሲያዝ በአንፃሩ አነስተኛ የሚባሉትን ብትሰሩም ግድ የለም ማለቱ ነውን?! በጭራሽ!! ይህን ከማለት የጠራ ጌታ ነው!!። ነቢዩ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) በጎረቤት ሚስት ላይ ዚና ማድረግ ከሌላው እጅግ በጣም የከበደ ነው ማለታቸው ሌላው ላይ ማቅለላቸው ነው?! በጭራሽ!! ይህን ሀዲስም ሲተነትኑ የከበደበትን ምክንያት ያስቀመጡ ዓሊሞችስ በአንተ ግንዛቤ እነሱንም በሌላ ልትፈርጃቸው ነው?!።
አንዳንድ በጥላቻ አዕምሮው የታወረበት ጅህልናው ለከት ያጣ ሰው በሰዎች ላይ አቃቂር ሲፈልግ መውጫ ወደ ሌላው ጉርጓድ በአፍጢሙ ተዘቅዝቆ ቁልቁል ወርዶ ሲፈጠፈጥ ስታየው ሀቂቃ በጣም ያሳዝንሃል!!።
አላህ ሁላችንም ሀቅን በሀቅነቱ የምንከተል ባጢልን በትክክል አውቀን የምንርቅ ያድርገን!! በዲኑ ላይ ትክክለኛ ግንዛቤም ይስጠን!!
✍🏻ኢብን ሽፋ: ሸዕባን 11/1442 ዓ. ሂ
የተለያዩ ት/ቶችን ለማግኘት የቴሌግራም ቻናላችን ⤵️ #join ያድርጉና ይቀላቀሉ
https://telegram.me/IbnShifahttps://t.me/abujuleybibb