ሕብረት ኢንሹራንስ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የተጣራ ትርፍ ማትረፉን አስታወቀ አርብ ጥቅምት 29 ቀን 2017 (አዲስ ማለዳ) ሕብረት ኢንሹራንስ በ2016 በጀት ዓመት 525.27 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማትረፉን አስታውቋል፡፡
ኩባኒያው ያተረፈው ትርፍ ከተጠናቀቀው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከግማሽ በላይ ወይም የ60.62 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ሕብረት ኢንሹራንስ ይህንን ያስታወቀው ዓመታዊ የባለአክስዮኖች ጠቅላላ ጉባኤውን በትላንትናው እለት ባካሄደበት ወቅት ነው።
ኩባንያው በበጀት ዓመቱ ከሁለቱም ከሕይወት እና ሕይወት ነክ ካልሆነው) የሰበሰበው አጠቃላይ አረቦን ገቢ ወደ 1.96 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ጠቅሷል።
ሕብረት ኢንሹራንስ ከሰበሰበው አጠቃላይ አረቦን መጠን ብር 1.7 ቢሊዮን ብር የተገኘው ሕይወት ነክ ካልሆነ የኢንሹራንስ ስራ መሆኑን በሪፖርቱ አመላክቷል።
የሕብረት ኢንሹራንስ የተከፈለ ካፒታል አንድ ቢሊዮን ብር መድረሱንና የኩባንያው ካፒታል ከባለፈው ዓመት በ2 መቶ 21 ሚሊዮን ብር እድገት አሳይቷል፡፡
የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ባለፈው አመት በአማካይ 23.72 በመቶ እድገት ማሳየቱን ኩባንያው ጠቅሶ በዚህም የሕብረት ኢንሹራንስ እድገት 30.19 በመቶ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
ሕብረት ኢንሹራንስ አክሎም በ2016 በጀት ዓመት 6 መቶ 93 ሚሊዮን ብር ካሳ መክፈሉን በሪፖርቱ አመላክቷል።
ምንጭ: አዲስ ማለዳ
@Etstocks