↘️↙️↘️↙️↘️↙️↘️↙️↘️↙️
#አምስት_ነገሮችን_ከረመዷን_በፊት!!
በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩኅሩህ በጣም አዛኝ በሆነው
ክብርና ምስጋና ለዓለማቱ ጌታ ለአላህ የተገባ ይሁን፡፡(አል-ፋቲሓ 2)
የአላህ ሰላምና ውዳሴ የሰው ዘር ታላቅ መሪ ለሆኑት ለነቢዩ ሙሐመድ (አል-አሕዛብ 56)
ለመላው የአላህ መልእክተኞች (አል-ሷፍፋት 181)
የሐቅንም መንገድ በተከተለ ሁሉ ላይ ይሁን (ጣሀ 47)፡፡
እነዚህን #አምስት ነገር ምን እንደሆኑ ከመዘርዘሬ በፊት አንድ የነቢያችንን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ሐዲሥ #መጥቀስ እፈልጋለሁ፡፡ ሐዲሡ እንዲህ ይላል፡-
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- "የጀነት ደጃፎች ሰኞና ሐሙስ ይከፈታሉ፡፡ በአላህ ቅንጣትንም ለማያጋራ የአላህ ባሪያ ሁሉ ኃጢአቱ ይሰረዝለታል፡፡ በእሱና በወንድሙ መሐል ቁርሾ(ቂም) ያለባቸው ሰዎች ብቻ ሲቀሩ፡፡ እነዚህን ሰዎች እስኪታረቁ ድረስ መልሷቸው ይባላል" (ቲርሚዚይ 2023)፡፡
የአደም ልጅ በጠቅላላ ተሳሳች ነው! በማለት ውዱ ነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) አስተምረውናል፡፡ ይህ ኃጢአት የውርስ ኃጢአት ሳይሆን የግብር (ራሳችን የፈጸምነው) ኃጢአት ነው፡፡ ታዲያ ከመሀከላችን ኃጢአት የሌለበት ይኖራልን? ካለብንስ የኃጢአት ስረዛንስ አንፈልግም? ከፈለግን ደግሞ እኛም ዐፍው እንባባል፡፡ ጌታችንም ይቅር ይለን ዘንድ፡፡ ሐዲሡም፡- ‹‹በምድር ያላችሁ ሆይ! ለመሰሎቻችሁ እዘኑ፡ ከሰማይ በላይ ያለው (አላህ) ያዝንላችሁ ዘንድ›› አይደል የሚለው? አሁን ወደ ተነሳሁበት አምስት ጉዳዮች ልመለስ፡-
1⃣ኛ. የረመዷን ወር ከመጣልህና በበሩም ደጅ ላይ ከደረስህ፡ አላህ ላንተ በማሰብ የዚህ ወር ተካፋይ እንድትሆን የላከልህ ጸጋ መሆኑን ልታስብ ይገባሀል፡፡ ዕድሜና ጤናን ሰጥቶህ ይህን የተባረከ ወር እንድትቋደስ ማድረግ ትልቅ ኒዕማ (ጸጋ) ነውና፡፡ ስንትና ስንት ልቦች ይህን ወር ተመኝተውት ነበር? የቀደር ጉዳይ ሆኖ ግን ስንቶች ወደ አኼራ ተሸኙ? አሁን እነሱ ከአፈር በታች በቀብር ይገኛሉ፡፡ አንተ ግን ሕያው ኾነህ የረመዷንን ወር ከተገኘህ፡ የጌታህ ጸጋ መሆኑን ዐውቀህ፡ ለዚህ ያደረሰህን አላህ አመስግነው፡፡ በልብህም በአንደበትህም፡- "ጌታዬ አምላኬ አላህ ሆይ! የረመዷንን ወር በሰላም በጤና ስላደረስከኝ፡ እንዲሁም ስለማይቆጠረው ውለታህ ከልቤ አመሰግንሀለሁ" በል፡፡ ይህንን ካልህ፡ ከልብህም ለወሩ ከተዘጋጀህ፡ ጌታህ ደግሞ ሌላንም እንደሚጨምርልህ እንዲህ በማለት በቃሉ አስታውቆሀል፡-
"ጌታችሁም፦ ብታመሰግኑ በእርግጥ እጨምርላችኋለሁ ብትክዱም (እቀጣችኋላሁ)፤ ቅጣቴ በእርግጥ ብርቱ ነውና በማለት ባስታወቀ ጊዜ (አስታውሱ)።" (ሱረቱ ኢብራሂም 14፡7)፡፡
በተጨማሪም ሌላ ልታስታውሰው የሚገባህ ነገር፡ እንዳንተው ስንቶች ረመዷንን ተገኝተው፡ ግን ህመምና እርጅና እንዲሁም ሌላ ምክንያት ከጾምና ከቂያሙ-ለይል ያገዳቸው መኖራቸውን ነው፡፡ ታዲያ አንተ ጤናማና ጠንካራ ከሆንክ ጌታህን አመስግነውና፡ በዚህ አካልህም ጾሙንና ዒባዳውን በአግባቡ እንድታከናውን ጌታህን እገዛ ለምነው፡፡ ያለሱ እገዛ የትም እንደማትደርስም እንዲህ በማለት ይነግርሀል፡-
"አንተን ብቻ እንግገዛለን፤ አንተንም ብቻ እርዳታን እንለምናለን (በሉ)።" (ሱረቱል ፋቲሓ 5)፡፡
2⃣ኛ. በዚህ ወር ንግግርህና ስራህ እጅጉን ያማረና የተዋበ ይሆን ዘንድ ከልብህ ወስን (ኒያ አድርግ)፡፡ ገና ከወሩ ጅማሬ፡ በአንተና በአላህ መሐል ወደሱ ሊያቃርብህ የሚችልን ነገር ለመስራት ቆራጥነት ይኑርህ፡፡ ይህ ደግሞ መተግበር ያለበት ገና ከጅምሩ ነው፡፡ ስንትና ስንቶች ናቸው ረመዷኑን ተገኝተው፡ ነገር ግን፡ ገና በተጀመረ በቀናት ውስጥ ወደ አኼራ የሚሸኙት? እንደኒያቸው ግን ጌታቸው አላህ ሙሉ አጅር ይሰጣቸዋል፡፡
3⃣ኛ. ይህ ደግሞ የነቢያችን (ዐለይሂ-ሶላቱ ወስ-ሰላም) ምክር ነው፡፡ እንዲህ ይላሉ፡-
አቢ ሁረይራህ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- "አንዳችሁ ጾመኛ በሆነበት ወቅት፡ መጥፎን ቃል አይናገር፣ ድምጹን ከፍ አድርጎ አይጩኽ፣ ማንም ሰው ቢሳደበው ወይም ቢጋደለው፡ እኔ ጾመኛ ነኝ! ይበል፡፡" (ቡኻሪና ሙስሊም)፡፡
ምክንያቱም ጾም፡- ከምግብና ከመጠጥ መቆጠብ ላይ ብቻ አይገደብምና፡፡ ምላስና እጅም አላህን ከሚያስቆጣ መጥፎ ተግባር መታቀባቸው የጾሙ አንድ አካል ነውና፡፡
4⃣ኛ. ይህ ወር የተውበት፣ የንሰሀና የምሕረት ወር ነው፡፡ ስለዚህ በተውበትና በኢስቲግፋር መበርታት ይጠበቅብሀል፡፡ በሐዲሥም እንደተገለጸው፡-
አቢ ሙሰል-አሽዐሪይ (ረዲየላሁ ዐንሁ) እንደነገረን የአላህ መልክተኛ (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንዲህ አሉ፡- "አላህ የቀን ጥፋተኞችን ሊምራቸው በለሊት የራሕመት እጁን ይዘረጋል፡፡ የለሊትን ጥፋተኞችን ሊምራቸው በቀንም የራሕመት እጁን ይዘረጋል፡፡ ይህም የሚሆነው ጸሀይ ከመግቢያዋ በኩል ብቅ እስክትል ነው" (ሙስሊም 7165)፡፡
በሌላም ሐዲሡል ቁድሲይ ላይ ጌታችን፡- ‹‹የአደም ልጆች ሆይ! እናንተ በቀንም በለሊትም ኃጢአት ትፈጽማላችሁ፡፡ እኔ ደግሞ ኃጢአትን በመላ እምራለሁና፡ እምራችሁ ዘንድ ማረን በሉኝ!›› ይለናል (ሙስሊም)፡፡
በተጨማሪም በሌላ ዘገባ ይኸው ጌታችን አላህ፡- ‹‹የአደም ልጅ ሆይ! ኃጢአትህ በዝቶ ሰማይ ጣሪያ ቢደርስና ከዛም ‹ጌታዬ ሆይ! ማረኝ› ብለህ ምሕረትን ብትጠይቀኝ፡ ምንም ሳይቸግረኝና ምንም ሳይመስለኝ እምርሐለሁ›› ይላል (ቲርሚዚይ 3540)፡፡
ታዲያ ዛሬ በረመዷን ወር ተውበት ያልገባህ መቼ ነው የምትቶብተው? በዚህ ወር ወደ አላህ ካልተመለስክ መቼ ነው የምትመለሰው?
5⃣ኛ. ሌላው ረመዷንን በተመለከተ ያሉ ሸሪዓዊ ድንጋጌዎችን ልታውቅ ይገባሀል፡፡ የጾም መስፈርቶች፣ ማእዘናቶች፣ ተወዳጅ (ሱና) ተግባራቶች፣ አፍራሽና የተጠሉ ተግባራቶች እንዲሁም የተፈቀዱ ተግባራቶች ምን ምን እንደሆኑ ከሚያውቁ ወንድምና እህቶች ጠይቀህ መማር አለብህ፡፡ የአላህ መልክተኛም (ሶለላሁ ዐለይሂ ወሰለም) እንደተናገሩት፡- "አላህ ኸይር የሻለትን ሰው የዲን ግንዛቤን ይለግሰዋል" ነውና ለማወቅ መጣር ይጠበቅብሀል (ቡኻሪይ)፡፡
አላህ ይወፍቀን
➿➿➿➿➿➿➿➿➿➿➿➿
ጆይን ⤵️⤵️⤵️ join
↪️
https://t.me/AbuImranAselefy ጆይን ⤵️⤵️⤵️ join
↪️
https://t.me/AbuImranAselefy ጆይን ⤵️⤵️⤵️ join
↪️
https://t.me/AbuImranAselefy〰〰〰〰〰〰〰〰〰〰〰〰
t.me/AbuImranAselefy