🚫 ማን ነው በጂሃድ የሚያዘው ?
በመጀመሪያ ደረጃ ሁሉም ሊያወቀው የሚገባው ጂሃድ በኢስላም ትልቅ ቦታ ያለው ለአላህ ተብሎ አንገት የሚሰጥበት የአምልኮት አይነት ነው ። ጂሃድ ምእራባዊያን እንደሚያስቡት አላማው ዝም ብሎ የሰው ሕይወት ማጥፋት አይደለም ። ኢስላም ጂሃድን አስመልክቶ በጣም ግልፅ መርሕ ነው ያለው ።
እንደሚታወቀው በእስልምና የአምልኮ ድንጋጌ አይነቶች በሁለት ይከፈላሉ : –
↪️ በቀጥታ ለራሳቸው ተብለው የታዘዙ በመስፈርታቸው ሁሌም የሚሰሩ ( መቅሱድ ሊዛቲሂ ) የሆኑ እንደ ሶላትና ፆምና ሐጅ የመሳሰሉ የአምኮ አይነቶች እና
↪️ በቀጥታ ለራሳቸው ተብሎ ሳይሆን ለሌላ አምልኮ መዳረሻ ተብሎ የታዘዙ ( መቅሱድ ሊጘይሪሂ ) የሆኑ
ለምሳሌ ውዱእ ማድረግ :– ውዱእ የታዘዘው በዋነኝነት ለሶላት ሲሆን ያለ ውዱእ አይሰሩም ለተባሉ የአምልኮት አይነቶችም ይሆናል ። በመሆኑም አንድ ሰው ውዱእ ማድረግ ግዴታ የሚሆንበት ሶላት መስገድ በሚፈልግ ጊዜ ወይም የፈርድ ሶላት ወቅት ሲደርስ ይሆናል ። ይህ ማለት ውዱእ በራሱ ዒባዳ ከመሆኑ ጋር ። ነገር ግን የሚፈለገው በቀጥታ ለራሱ ሳይሆን ለሌላ የዒባዳ አይነት ነው ።
እንደዚሁ ጂሃድም በቀጥታ ለራሱ ሳይሆን የታዘዘው ለሌላ አምልኮት ነው ። እሱም አላህ ለሰው ልጆች የሕይወት መመሪያ ይሆን ዘንድ ቁርኣንን አውርዷል ። ይህንን መለኮታዊ የህይወት መመሪያ የሆነው ቁርኣን ለሰው ልጆች እንዲያደርሱ መልእክተኞችን ልኳል ። ይህ መለኮታዊ የሕይወት መመሪያ የሆነው የአላህ ቃል መልእክተኞቹ ለሰው ልጅ ሊያደርሱና የሰውም ልጅ ይህ መለኮታዊ የህይወት መመሪያ ሊደርሰው መብቱ ነው ። በሱና በመብቱ መካከል የሚቆም አካል ሊኖር አይገባም አይ ብሎ በዚህ መለኮታዊ የህይወት መመሪያ በማድረሱ መንድ ላይ የሚቆም አሜኪላ ወይም ጋሬጣ በሚኖር ጊዜ ይህን ለማስወገድ ነው ጂሃድ የታዘዘው ። ከመሆኑም ጋር እንደ ሌሎቹ ህግጋቶች ሁሉ የራሱ የሆነ መስፈርቶች አሉት ። ልክ ዘካ አቅም ያለው ሰው እንደሚያወጣውና ሐጅም አቅም ያለው ሰው ሌሎች መስፈርቶችን አሟልቶ እንደሚያደርገው ሁሉ ። ጂሃድም አቅም ያለው መሪ ነው የሚያዝበት ። ኢስላም አቅም የሌለውን ዘካ አውጣ ወይም ሐጅ አድርግ እንዳላለው ሁሉ በዳዕዋ መንገድ ላይ የተጋረጠውንም አሜኪላ ለማስወገድ አቅም የሌለውን ጂሀድ አድርግ አላለውም ።
ወደ ርእሴ ስመለስ የዚህ አይነቱ ትልቅ የሸሪዓ አካል የሆነውን ጂሃድ ማን ነው የሚያዝበት ከተባለ የሙስሊም መሪ መስላሐና መፍሰዳውን አይቶ አቅሙን መዝኖ በመንገዱ ላይ የቆመውን አሜኪላ አቅም አመዛዝኖ ከሚመለከታቸው የዲኑና የሀገር ህልውና አደራ ከተጣለባቸው አጋሮቹ ጋር በመሆን የሚያዝበት ነው ።
በመሆኑም በኢስላም ጂሃድ ማንም ሰው ተነስቶ የሚያውጀው ወይም ተነሱ የሚልበት ሳይሆን በጣም ትልቅ ጥንቃቄ የሚፈልግ ነው ። ለዚህ ነው የአላህ መልእክተኛ ወሕይ እየወረደላቸውም ሙሃጅሮችንንና አንሷሮችን ያወያዩበት የነበረው ። እነ አቡበከር ዑመር በዚሁ መልኩ ትላልቅ የሙሃጅርና የአንሷር ሶሓቦችን ሰብስበው ያወያዩ የነበረው ።
በጣም የሚገርመው ዛሬ ሀገራችን ላይ ማን እንደሆኑና የት ሆነው እንደሚያዙ የማይታወቁ አካላት ጂሃድ እያወጁና ተነሱ እያሉ ነው !!!!!! ። እነዚህ አካላት ሊያውቁት የሚገባው ወይ የኢስላም ጠላት ተላላኪዎች ናቸው ። ሙስሊሞችን ለማጥቃት ይህን ምክንያት አድርገው መንቀሳቀስ የሚፈልጉ የኢስላም ጠላቶች ወይም በስሜት ፈረስ የሚጋልቡ ከጂሃጅ ስሙን እንጂ ርቀቱንና ሸሪዓዊ ብይኑን የማያውቁ ። የሚያሳዝነው እነዚህ ሙስሊሙን ወጣት ለጂሀድ ተነስ የሚሉ አካላት ሚስቶቻቸው ወይም እህቶቻቸው በየወሩ ወይም በወሊድ ጊዜ ስለሚፈሳቸው ደም ሸሪዓዊ ብይን ቢጠይቁዋቸው መመለስ የማይችሉ ናቸው ‼። ነገር ግን በተሽከርካሪ ወንበር ላይ ቁጭ ብለው ማኪያቶ እየጠጡ በኡማው ደም ላይ ፈትዋ ይሰጣሉ ። ሙስሊሞች ሆይ በፖለቲካ ወይም በመሬት ስራ የከሰሩ ማንነታቸው የማይታወቁ የኢስላም ጠላት ተላላኪዎች ተነሱ ጂሃድ ስላሉዋችሁ ወይም በእንቅፋት አለያም ትንታ ትሞታላችሁ እቺን እርካሽ ህይወት ለዲን ሰጥታችሁ በጀነት በራፍ ላይ የጀነት ሙሽራ አበባ ይዛ ብተቀበላችሁ ይሻላችኋል ‼ ብለው እያሰከሩ እንዳይነዱዋችሁ ።
የወንድምነት ምክሬ መጀመሪያ ዲናችሁን እወቁ ተማሩ ስሩበት አውቃችሁ የሰራችሁበትን እውቀት ለሌሎች በማድረስና ከሽርክና ቢዳዓ እንዲወጡ ሰበብ በመሆን በነፍሳችሁ ላይ ጂሃድ አድርጉ ይህ ለናንተ ትልቅ ጂሃድ ነው ። ስለሺርክና ቢዳዓ ሳታውቁ ስለጣሃራና ሶላት ሳታውቁ ወደ አኼራ እንዳትሄዱ ተጠንቀቁ ።
የሱና ዑለሞች ፣ ኡስታዞችና ዱዓቶች ሙስሊሙን ከእነዚህ አካላት መጠበቅና ግንዛቤ ማስጨበት ወቅታዊ ግዴታችሁ ነውና አማናችሁን ተወጡ ኡማውን ታደጉ ።
አላህ ሐቅን አውቆን የምንሰራበትና ባጢልን አውቆን የምንርቀው ያደርገን ።
https://t.me/bahruteka