ክራር እና ፍቅር
(ኤፍሬም ስዩም)
ትግስት በሌላት በጨከነች ሌሊት
ወዳጅ ለወዳጁ ደብዳቤ ፃፈላት
ከመፃፉ በፊት ...
ከጥቁር ሰማይ ላይ ሦስት ኮከቦች አየ
ለጥቂት ቅፅበታት ከከዋክብቱ ላይ ሀሳቡን አቆየ
አንደኛዋ ኮከብ እጅግ የደመቀ ብርሃን ትረጫለች
ሁለተኛዋ ግን ደመቅ ትላለች ካንዷ ትሻላለች
ሦስተኛዋ ደሞ እርሱን ትመስላለች
በሁለቱ መካከል ፈዛ ትታያለች
እርሱን ለምትመስለው ብዕሩን አነሳ
ሁለቱን ከዋክብት ልቡን አወረሳ
አሁንም ዳግመኛ ከመፃፉ በፊት
ከአንድ አመት ቀድሞ በርሷ የተፃፈ ደብዳቤዋን አየው
የደብዳቤው ሀሳብ የደም ዕንባ አስነባው
እንባው ማፍቀሯ ነው መፈቀሩም እንባው
የሀሳቧም ሀሳብ ለሁለት ዘላለሞች አፈቅርሃለሁ ነው
በትንሹ ታምኖ ብዙ ያልወደደ
ስለተፈቀረም ትንሽ ካላበደ
በትንሽነቱም ያልተወላገደ
ፍቅርን እንዴት ያውቃል እንዴት ይረዳዋል
ምን ነበር የፃፍሽው ምንድን ነበር ያልሽው
የሆነ መስመር ላይ አስተውለው ብለሽ ከታች ያሰመርሽው
ፊደል እስኪጠፋው እጁን ያሰርሽበት
የፍቅር ቀለማት የማይጠፉ ቃላት
የእውነት መገነዣ ሌላ ያንቺ እውነት
ያንቺ እውነት ፍቅር የርሱ ፍቅር ፊደል
ካፈቀረስ በቀር ፍቅርን ማን ይገልፃል
ማንበብ ክፉ ነገር መፃፍ መገላገል
ይሄ አይደል መታደል
ምን ነበር የፃፍሽው ምንድን ነበር ያልሽው
አስተውለው ብለሽ የሆነ መስመር ላይ ከታች ያሰመርሽው
ይልቅ ያን አስታውሰሽ የክራሩን ድምፅ አሰሚኝ
የዜማ ድምፅ ከዚያ ይውጣ
እኔም ክሩን ሆኜ ባንቺ ጣት ልቀጣ
እኔና አንቺ እንዲያ ነን በሁለት አንድነት ዝንት አለም የታሰርን በቅኝት ቢወጣ ጣት እና ክር ነን
ወይም ድምፅ እና ክር
ፍቅርን ጣት አርገነው ባንድነት ምንዘምር
ምን ነበር የፃፍሽው ምንድን ነበር ያልሽው
በፃፍሽው መስመር ላይ መብረቅ ፍቅር አለ
የዝናብ ድምፅ የለም ደመና ግን አለ
ከደመናው በፊት የደብዳቤሽ ቃላት
አንተ ማለት ባህር እኔ ማለት ትነት
በፀሀይ ፈገግታ ጨውን የምንፈጥራት
አንተ ማለት ጸጸት እኔ ማለት መዳፍ
የቀደመ ዕንባህን ካይንህ ላይ የምገፍ
አንተ ማለት ጥማት እኔ ደሞ እርካታ
በበርሀ ንዳድ የምገኝ ጠብታ
ማንበቡን ቀጠለ
የመብረቅ ብልጭታ የዝናብ ድምፅ አለ
በጥቁር ደመና ቀድሞ የታዘለ
ደብዘዝ ያለ ብርሃን የማትታይ ፀሀይ
የተኳረፈ ፍቅር ያረገፈ አደይ
በሁለታችን አዝኖ የተከፋ ሰማይ
ይህ ሁሉ ቢሆንም
መዳፍሽ እርቋል
ጨውነቱም ጠፍቷል
ቃሎችሽ ሰክረዋል
በዚያ ታላቅ ዝናብ ምድር ስትቀጣ
በመብረቅ ብልጭታ ነፍሳችን ስትወጣ
እኮ በምን እግሬ ከደጃፍሽ ልምጣ
አንቺ እንደሆን ንግስት የመኳንንት ልጅ
ህንፃ ፍቅር ልብሽ ጉብዝናን የሚያስረጅ
እኮ በምን ሀይሌ ልርገጠው ያንቺን ደጅ
ማን በምን ጉልበቱ በየት ጀግንነቱ
ዝም ባለ ቅፅርሽ ያንቺ ጉርፊያ ነግሶ
ፊትሽን ፍራቻ ልቦናዬ ፈርሶ
በሳምንት ዘመንሽ ዐይኔ ደም አልቅሶ
እኮ በምን አቅሙ እንዴትስ ተደፍሮ ደጅሽ ይረገጣል
አይኑስ እንዴት ደፍሮ ዕንባውን ጠራርጎ ያንቺን ዐይን ያያል
ምን ነበር የፃፍሽው ወይስ እኔ ፃፍኩኝ
ከፍቅርሽ ላይ ወይን ደብልቄ ጠጣኹኝ
ፍቅር እና ወይን
የሁለት አንድነቱን የጣትና ክሩን
በስልት የተቃኘ ክር ድምፅነትን
ፍቅርን ጣት አርገነው በተነካን ቁጥር
በስሱ ከላይዋ እንደተመታች ክር
በራሳችን ቃና በራሳችን መዝሙር
ለዘላለም እድሜ ባንድ ተገመድን
ወይስ ምንም ሆንን
እውነት ምንም ሆንን
ዜማ ሰጭ ፍቅራችን ተበጠሰ ላላ
የኛ ቅኝታችን በኔነት ተበላ
ያለሙያው ገብቶ ያለመጠን ነክቶ
ያለስልቱስ ቃኝቶ
ክራር ፍቅራችንን ክሩን ማን በጠሰ
በምን አይነት ስልትስ ዜማችን ታደሰ
ከሐሳቡ ነቃ
በራሱ ክር ላይ የራስ ስልቱን ቃኘ
ለደብዳቤዋ መልስ ሊመልስ ተመኘ
ላንተ ያለችውን ላንቺ ብሎ ፃፈ
በራስ የቃል ስልቷ ቃሉን አከነፈ
ረስቶት ነበረ ...
ከጠረቤዛው ስር በፅዋ ተሞልቶ ወይኑ ተቀምጧል
ጥቁር የወይን ደም ከፅዋው አንስቶ አንደዜ ጠጣለት
አንዱን ሳያጣጥም ፅዋዉ ወደቀበት
የፈሰሰው ወይን ልብሱን አረጠበው መሬቱን አራሰው
ፍንጥቅጣቂው ደሞ አይኑን አስለቀሰው
የብርጭቆው ፅዋ አልተሰባበረም
ሁሉም ፈሶበታል የተረፈ የለም
ለመፃፍ ከበደው
ደብዳቤው ቀፈፈው
መሬት አጎንብሶ እጁን ተንተርሶ
ስለሆነው ሁሉ ያስተውል ጀመረ
እንቆቅልሽ
የወደቀ ፅዋ ያልተሰባበረ
የፈሰሰ ወይን ባንድ ጉንጭ የቀረ
ያላለቀ ፅሑፍ በረቂቅ የኖረ
ያኮረፈች ፍቅር ደጇ የታጠረ
አራቱ ሚስጥሮች ሳይተረጎሙ ሳይመረመሩ
ባፍቃሪው ልቦና እንቆቅልሽ ሆነው ለዘላለም ቀሩ
@Yonny_Athan