ኅዳር 12
~ ለውጦ ማክበር ~
ንግሥት ክሌዎፓትራ "ሳተርን" ለሚባል ጣዖት ያሠራችው ቤት በእስክንድርያ ነበር። ይህ ቤተ ጣዖት እስከ እለ እስክንድሮስ ፓትርያርክ ዘመን 212-326 ድረስ ነበር። እለእስክንድሮስም ሊያጠፋ ሲነሣ በሕዝቡ ልቡና ገና አምልኮ ጣዖት ስላልጠፋላቸው 18 ፓትርያሪኮች ያልነኩትን አንተ ለምን ታፈርስብናለህ ብለው ተቃወሙት። እለእስክንድሮስም ሕዝቡን መክሮና አስተምሮ የሳተርን በዓል ይውልበት የነበረበትን ዕለት ወደ ቅዱስ ሚካኤል የበዓል ዕለት አደረገው። (ስንክ ሳር ኅዳር 12፣ Coptic Encyclopedia, Vi S.p 1617)።
ከእምልኮ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር የእስክንድርያ ሰዎች በእለ እስክንድሮስ በኩል እየበረሩ ገቡ። የጣዖት መክበሪያ የነበረው በእለ እስክንድሮስ ጸሎት የቅዱስ ሚካኤል መክበሪያ የእግዚአብሔር መመስገኛ ኾነ። ይህን ቤተ ጣዖት ሳስብ ምናልባት በኃጢአታችን ምክንያት የእኛን ሰውነት የሚወክል ይኾን እላለሁ። ብዙዎቻችን የእግዚአብሔር መቅደስ የኾነውን ሰውነታችንን የአጋንንት መርኪያ ቤተ ዘፈን አድርገነዋልና።
የሰው ልቡና የእግዚአብሔር ቤተ መንግሥት ነው። ኾኖም ሰዎች ሰውነታቸውን እያረከሱና ከእግዚአብሔር ፍቅር እየራቁ ሲሄዱ የአጋንንት መኖሪያ ሊያደርጉት ይችላሉ። በመኾኑም የሕይወታችን ዋና ጉዳይ መኾን ያለበት መቅደስ ሰውነታችንን መጠበቅ ነው። በእለእስክንድሮስ አምሳል በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለአገልግሎት የሚፋጠኑ ካህናትን በቅዱስ መስቀል ባርከው እንዲያነጹን መቅረብ ነው። ዝሙት የተባለ ጣዖት በልቡናችን ውስጥ የያዘውን ቦታ በካህናት ፊት ተናዘን እንድንነጻ የሚያደርገውን የንስሐን ቀኖና መቀበል ነው። ሕይወታችንን እያዛጉ ያሉትን ማናቸውንም ባዕድ የኾኑ ነገሮች በልቡናችን ውስጥ ሥር እንዳይዙ መጠንቀቅ ነው።
በእርጥም እኛ ፈቃዳችንን ለእለእስክንድሮሳዊ ፈቃድ ካስገዛን ሰውነታችን የቅዱሳን መላእክት በዓል መክበሪያ ወደ መኾን ይታደሳል። ቅዳሴ፣ ማኅሌትና ልዩ አገልግሎት ያለማቋረጥ የሚቀርብበት ንጹሕ መቅደስ ይኾናል። እንግዲያውስ ኹላችንም በሰውነታችን ውስጥ ቅዱስ ሚካኤልን እንፈልገው፤ በበዓልነት በእኛ ውስጥ እንዲከብር እንፍቀድ። ሰዎች የቅዱስ ሚካኤልን ያማረ የምልጃ ሽታ በእኛ ሰውነት ውስጥ እንዲያሸቱት እናድርግ! ወደ ቅዱስ ሚካኤላዊ የአገልግሎት ሕይወት ለመግባት እንመኝ፤ ደጋግመንም እንሻ!
( "ዲ/ን ዮሐንስ ጌታቸው" fb የተወሰደ ።)
እንኳን አደረሳችሁ!!
#ኦርቶዶክሳዊ_አእምሮ