ዶክተር ኢትዮጵያ | Doctor Ethiopia


Kanal geosi va tili: ko‘rsatilmagan, ko‘rsatilmagan
Toifa: ko‘rsatilmagan


✓ስለ ጤናዎ መረጃን እናካፍላለን፣
✓ጤናዎን የተመለከቱ ጥያቄዎችን በዶክተር የታገዘ ምላሽ እንሠጣለን እናማክራለን።
✓ያለወትን የጤና ነክ መረጃና ምክር @Yonase2323 ላይ ያካፍሉን፣ መልሰን ለአንባቢያን እናደርሳለን::

Bog‘liq kanallar  |  O‘xshash kanallar

Kanal geosi va tili
ko‘rsatilmagan, ko‘rsatilmagan
Toifa
ko‘rsatilmagan
Statistika
Postlar filtri


የጆሮ ታንቡር ሲቀደድ መፍትሔዉ ምንድን ነዉ?

ታንቡር ለመስማት የሚያገለግለን የሰዉነታችን አካል ሲሆን በጣም ስስ የሆነ ስጋ ነው። አገልግሎቱም ድምፅን ማጉላትና ሰብስቦ ለውስጠኛዉ የጆሮ ክፍል ማስተላለፍ ነው።

የጆሮ ታንቡር መቀደድ ምክንያቶች
1. አደጋና (ምት, ከፍተኛ ፍንዳታ)
2. ኢንፌክሽን
3. የተለያየ እባጮች

የጆሮ ታንቡር መቀደድ ምልክቶች እንደየ ምክንያቶቹ ቢለያይም ዋና ዋና ምልክቶቹ
1. የመስማት መቀነስና መስማት መቸገር
2. የጆሮ ፈሳሽና መግል
3. የጆሮ ጩኸትና ባላንስ መዛባት ናቸው።

የተቀደደ ታንቡር ያለበት ታካሚ
1. ዉሀም ሆነ ማንኛውም ፈሳሽ ጆሮ ውስጥ እንዳይገባ ጥንቃቄ ማድረግ
2. ጆሮ ውስጥ በማንኛውም ነገር አለመነካካት
3. ከጉንፋንና መሠል ኢንፌክሽኖች መጠንቀቅ ይኖርበታል።

የጆሮ ታንቡር መቀደድ ህክምና በዋናነት መቀደዱ ዘላቂ መቀደድ (Chronic Perforation) ነው ወይስ ጊዜያዊ (Acute Perforation) የሚለዉ ላይ ይወሰናል።

1. የመቀደዱ መንስዔ በምት ከሆነ ታንቡሩ በራሱ የመድፈን እድል አለው። ስለዚህ ህክምናዉ የሚሆነው ታንቡሩ ኢንፌክሽን እንዳይዝ ማድረግ ነዉ።

2. የመቀደዱ መንስዔ በኢንፌክሽን ምክንያት ሲሆን ደግሞ መቀደዱ ዘላቂ እና በራሱ የማይገጥም ይሆናል። ስለዚህ ህክምናዉ የተቀደደዉን ታንቡር በቀዶ ህክምና (Tympanoplasty) ማስተካከል ይሆናል።
በአጠቃላይ የጆሮ ታንቡር መቀደድ በህክምና ሊስተካከልና ከዘላቂ ጉዳት (Chronic Complication) ሊድን ይቻላል።

ዶ/ር ኦሊያድ ታረቀኝ, የአንገት በላይ ስፔሻሊስት



=================
https://t.me/ethiodoc


We save lives! Now it's time to save ours!
ህይወት ስናድን ኖረናል! አሁን ግን የራሳችንንም ህይወት ማዳን ይኖርብናል!

#HealthProfessionals #Ethiopia #FMOH #MOE #PMO
==========================




_
#Join @:

https://t.me/ethiodoc


ቀጣይነት ያለው የግሉኮስ ክትትል continious glucose monitoring (CGM) አጠቃቀም

ቀጣይነት ያለው የግሉኮስ ክትትል (CGM) የስኳር ህመምተኞች የደም ስኳራቸውን በየጊዜው ለመከታተል የሚረዳ መሳሪያ ነው። ከጣት ላይ ደም ወስዶ ከሚለካው ባህላዊ የደም ስኳር መለኪያ በተለየ፣ CGM ከቆዳው ስር የሚገባ ትንሽ ዳሳሽ (sensor) በመጠቀም በየደቂቃው የደም ስኳር መጠንን ይለካል።

የ CGM ጥቅሞች:

1. ቀጣይነት ያለው ክትትል: CGM የደም ስኳር መጠንን በየጊዜው ስለሚለካ፣ በደም ስኳር ውስጥ የሚደረጉ ለውጦችን በቅጽበት መከታተል ይቻላል።

2. የደም ስኳር አዝማሚያዎችን ማወቅ: CGM የደም ስኳር መጠን እንዴት እንደሚጨምር ወይም እንደሚቀንስ የሚያሳይ ግራፍ ያሳያል፣ ይህም ለወደፊቱ የደም ስኳር መጠንን ለመተንበይ ይረዳል።

3. የማስጠንቀቂያ ስርዓት: CGM የደም ስኳር መጠን በጣም ከፍ ወይም ዝቅ ሲል የማስጠንቀቂያ ድምጽ ያሰማል፣ ይህም አደገኛ ሁኔታዎችን ለመከላከል ይረዳል።

4. የተሻለ የስኳር ቁጥጥር: CGM ተጠቃሚዎች የደም ስኳራቸውን በተሻለ ሁኔታ እንዲቆጣጠሩ ስለሚረዳ፣ የረጅም ጊዜ የስኳር ህመም ችግሮችን ለመቀነስ ይረዳል።

5. የጣት መውጋት መቀነስ: CGM የጣት መውጋትን ስለሚቀንስ፣ ህመም እና ምቾት ማጣትን ይቀንሳል።

የ CGM አጠቃቀም:
■ ዳሳሽ (sensor) ማስገባት: ዳሳሹ ከቆዳው ስር ይገባል፣ አብዛኛውን ጊዜ በሆድ ወይም በክንድ ላይ።

■ ተቀባይ (receiver) ወይም ስማርትፎን: ዳሳሹ የሚለካውን የደም ስኳር መጠን ለተቀባዩ ወይም ለስማርትፎን ይልካል።

■ Data መተንተን: ተቀባዩ ወይም ስማርትፎኑ የደም ስኳር መጠንን በግራፍ መልክ ያሳያል፣ እና የማስጠንቀቂያ ስርዓትም አለው።

■ የኢንሱሊን መጠን ማስተካከል: CGM ተጠቃሚዎች የደም ስኳራቸውን መሰረት በማድረግ የኢንሱሊን መጠናቸውን እንዲያስተካክሉ ይረዳል።

Reference

1. The American Diabetes Association Releases the Standards of Care in Diabetes—2024

2. UpToDate online

ማስታወሻ: ስለ CGM አጠቃቀም ከሐኪምዎ ጋር መነጋገር አስፈላጊ ነው።

ዶ/ር አማኑኤል ወገብርኤል: የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት




https://t.me/ethiodoc


የፅንስ ፆታ ማወቅ የሚያስደስት ወይስ የሚያስጨንቅ⁉️🤔
============================

👉🏽 ጥንዶች የእርግዝና ጊዜ ከ18 ሳምንት እስከ 22 ሳምንት በደረሰ ጊዜ የልጃቸውን ፆታ ማወቅ ይችላሉ። በተሻለ አልትራሳውንድ ደግሞ ከ12 ሳምንት ጀምሮ የሚታወቅበት ጊዜ አለ።

👉🏽 ነገር ግን ረቀቅ ባሉ የዘረመል ምርመራዎች (genetic analysis) የፅንስ ፆታ ከ9 ሳምንት ጀምሮ ማወቅ ይቻላል።

👉🏽 በIVF (In Vitro Fertilization) እርዳታ የሚወልዱ ጥንዶች ደግሞ ገና ከመጀመሪያው ውጭ ላይ የተዳቀለው የወንድ ዘር (sperm cell) እና የሴት እንቁላል(egg) የፈጠረውን ፆታ ማህፀኗ ውስጥ ከመግባቱ በፊት ማወቅ ይቻላል።

👉🏽 የፅንስን ፆታ ቀድሞ ማወቅ ይጠቅማል የሚሉ ጥንዶች እንዳሉ ሁላ፤ ማወቁ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያይላል የሚሉም በርካታ ናቸው።

⚡️⚡️ የፅንስን ፆታ ቀድሞ ማወቅ ብዙ ጥቅም አለው የሚሉ ጥንዶች የተወሰኑት ምክንያቶችን ይዘረዝራሉ:-

✍️ስሜታዊ ዝግጅት:- ይህም በርግዝና ወቅት ከልጃቸው ጋር እንዲቀራረቡ ይረዳል ይላሉ

✍️ተግባራዊ ዝግጅት :- ስም እንደማውጣት፣ የልጅን ክፍል እንደማስጌጥ፣ ልብስ መግዛትን እና የመጨረሻ ሰዓት ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ ጭንቀቶችን ይቀንስልናል ይላሉ

✍️የመጓጓት ስሜትን መቀነስ :- ይህ ፆታን የማወቅ ጉጉት ጥርጣሬን ሊፈጥር ስለሚችል፤ ሌሎች እርግዝና ነክ የሆኑ ጉዳዬች ላይ ላያተኩሩ ስለሚችሉ ፥ ማወቃቸው ጉጉታቸውን ሊያረካ እንደሚችል እና እቅዶችን ማውጣት ላይ ጠንካራ እንደሚሆኑ ይናገራሉ

✍️ታላላቅ ወንድም ወይም እህት ካሉ ቀድመው ማወቃቸው የቅናት ስሜትን በተወሰነ መልኩ ሊቀንስላቸው እና እራሳቸውን በተወሰነ መልኩ እንዲያዘጋጁ ይረዳቸዋል ተብሎ መታሰብ

✍️ከፆታ ጋር የተያያዙ የዘር ውርስ በሽታዎች ለምሳሌ እንደ ሄሞፊሊያ ለመሳሰሉት ወላጆች ለሚገጥሟቸው ችግሮች ቀድመው ዝግጅት እንዲያደርጉ መርዳት

⚡️⚡️ ከላይ የተጠቀሱት ነጥቦች እንዳሉ ሆነው ፥ በተቃራኒው ደግሞ ያሉ ጥንዶች ፆታን አስቀድሞ ማወቅ የተወሰኑ ችግሮች አሉት ብለው ያስባሉ:- እነኚህም

✍️አንዲት እናት ወይም አባት ሴት ልጅ እንዲኖራቸው "ቢመኙም" ነገር ግን ወንድ ልጅ ሊወልዱ እንደሆነ አስቀድመው ቢረዱ ይህ ለወሊድ የሚሰማቸውን ደስታ እና ጉጉት ሊቀንስ ይችላል። ባልና ሚስቱ በሕፃኑ ጾታ ቢደሰቱም፣ የቤተሰብ አባላት ወይም ጓደኞች ቅር መሰኘታቸውን ሊገልጹ ይችላሉ፣ ይህ ደግሞ በጣም አስጨናቂ እና በእውነት የሚያበሳጭ ሊሆን ይችላል!

✍️የመገረም ስሜት - ብዙ ጥንዶች ህፃናቸውን በሚጠብቁበት  የመጨረሻይቱ ደቂቃ ፆታውን ማወቅ የግርምት፣ ልዩ እና አስደሳች ተሞክሮ እንደሆነ ያምናሉ

✍️የፆታ አመለካከትን መቀነስ - ጾታውን አለማወቅ ወላጆች ስለ ልብስ፣ መጫወቻዎች ወይም የሕፃናት ክፍል ማስጌጫዎች አስቀድሞ ግምቶችን ከመፍጠር ወይም ባህላዊ የፆታ-ተኮር የሚጠበቁ ነገሮችን ከመግዛት እንዲቆጠቡ ሊረዳቸው ይችላል።

✍️ሁሉን ያካተተ ዝግጅት፡ ወላጆች በፆታ ላይ በተመሰረቱ የሚጠበቁ ነገሮች ከመገደብ ይልቅ የሕፃኑን መምጣት በአካታች እና በሚስማማ መንገድ ለማዘጋጀት ማተኮር ይችላሉ።

⚡️⚡️ በመጨረሻም ፆታን የማወቅ ሁኔታን ለጥንዶቹ ልተውና ፤ የሕፃኑን ጾታ ከመወለዱ በፊት ማወቅ ትክክል ወይም ስህተት የሚባል ነገር የለውም - ይህ ለባልና ሚስት ፍጹም የሆነ የግል እና ሚስጥራዊ ውሳኔ ይሆናል። ዋናው እና ጠቃሚው ነጥብ ፣ ከሁሉም በላይ አስፈላጊው ጤናማ እርግዝና እና ጤናማ ህፃን መውለድ ስለሆነ።

ለደረሳችሁ ነፍሰ ጡሮች - የአጥር ወፍ አትስማሽ እያልኩ መልካም ጊዜን ተመኘሁ።




https://t.me/ethiodoc


የምራቅ እጢ ማበጥ ከምን ይመጣል?

የምራቅ እጢ በጆሯችን በአገጫችን በምላሳችን ስር እና በአፍችን የተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ሲሆን ምራቅ በማምረት የአፋችንን እርጥበት መጠበቅ ፣ ኢንፌክሽን መከላከል፣ ጥርስን ማጽዳት ፣ በምንመገብ ሠአት ምግብን ማርጠብና ለምግብ ቱቦ ምቹ የማድረግ ስራን ይሠራሉ።

እነዚህ ምራቅ የሚያመርቱ እጢዎች በተለያዩ ችግሮች ሊጠቁ ይችላሉ።

፨ኢንፌክሽን
፨የምራቅ እጢ ጠጠር
፨ሞኝ እባጭ
፨ካንሠር  በብዛት ከሚከሠቱ ችግሮች ዋነኞቹ ናቸው።

እነዚህ ህመሞች የየራሳቸው የሆነ የተለያየ የህመም ስሜት ሲኖራቸው ከላይ በተጠቀሡት ቦታዎች የሚከሠት እብጠት አንድ ያደርጋቸዋል።ስለዚህ ምራቅ እጢ አካባቢ የሚገኝ ማንኛውም እብጠት በአልትራሳውንድ ታይቶ እንዳስፈላጊነቱ በመርፌ እና ሌሎች ምርመራዎች ተሠርተው ዘላቂ መፍትሔ ሊያገኝ ይገባል።

መሪ ቃላችን እንደሚለው የተሻለ ሕክምና ይገባዎታል! እያንዳንዱን ታካሚ ተደራሽ የሚያደርግና በዘመናዊ መሳሪያ የታገዘ ሕክምናን ማቅረብ ደግሞ ተቀዳሚ ዓላማችን ነው!

ዶ/ር አለማየሁ እሸት, የአንገት በላይ ስፔሻሊስት

አድራሻችን: ቀበና አደባባይ, OLA ነዳጅ ማደያ ፊትለፊት, EPHA ሕንጻ 2ኛ ፎቅ





https://t.me/ethiodoc


"ልጄ 2 ወር ነበር አረንጓዴ ነገር በጣም ያስታውከው ነበር። ከ 3 ቀን በኋላ ወደ ሆስፒታል ወሰድኩት። በአፋጣኝ  ቀዶ ጥገና ተደረገለት። ነገር ግን አንጀቱ በመጠምዘዙ አብዛኛው አንጀት ከጥቅም ውጭ ሆኗል። ምንም ልናደርግለት አንችልም አሉኝ። ልጄ በሚቀጥለው ቀን ሞተብኝ።
ሌሎች እንዲማሩበት እባክዎን ስለዚህ ችግር ይንገሩን።" (የወላጅ ጥያቄ)

😢ውድ ጠያቂያችን በደረሰብዎት ሐዘን በጣም አዝኛለሁ።

✍ልጅን ማጣት የማይረሳ ከፍተኛ ህመም ነው እና ሌሎች እንዲማሩበት የእርስዎን ልምድ ለማካፈል ፈቃደኛ መሆንዎ በእውነት የሚደነቅ ነገር ነው።

🩺እርስዎ የገለጹት ችግር እንደ እርሶ አገላለፅ ከሆነ የአንጀት መጠምዘዝ (Midgut Volvulus) ሲሆን አዲስ በተወለዱ ሕፃናት እና ትናንሽ ሕፃናት ላይ ለሕይወት አስጊ የሆነ ድንገተኛ የአንጀት አደጋ ነው።

🌡🌡ከዚህ በታች :

🩺🩺ችግሩ ምን እንደሆነ፣
🩺🩺 ለምን እንደሚከሰት፣
🩺🩺እንዴት እንደሚታከም እና ለምን አስቸኳይ ሕክምና(ቀዶ ጥገና) አስፈላጊ እንደሆነ ለማብራራት እንሞክራለን።

🥇Midgut Volvulus ምንድን ነው?

🌡Midgut Volvulus ማለት አብዛኛው ትንሹ አንጀት እና የተወሰነ ትልቁ አንጀት በሚጠመዘዝበት (Twisting) ጊዜ የሚፈጠር አደገኛ ችግር ነው።

🌡ይህ ችግር የሚከሰተው  በተፈጥሮ የአንጀት አቀማመጥ ትክክል በማይሆንበት በህክምና ቃል Malrotation ባላቸው ህፃናት ላይ ነው።

💊በመደበኛ አፈጣጠር በፅንሱ እድገት ወቅት አንጀት ትክክለኛውን አቀማመጥ ለመያዝ ይዞራል (Rotation) እንዲሁም በሆድ እቃ ውስጥ ተስተካክሎ ይቀመጣል (Fixation)።

💉ነገር ግን ከላይ የተጠቀሰው ችግር ያለባቸው ሕፃናት አንጀት በትክክል ስለማይስተካከል ለአንጀት መጠምዘዝ በከፍተኛ መጠን  ይዳርጋቸዋል።

🩺አንጀቱ በሚጠመዘዝበት ወቅት  የደም አቅርቦቱ ይቋረጣል ይህም ወደ ጋንግሪን (የመበስበስ ) አደጋን ያስከትላል።

🌡💊ይህም በፍጥነት አንዳንድ ጊዜም በሰዓታት ውስጥ ሊከሰት ይችላል እና በጊዜ ካልታከመ ለሞት ሊዳርግ ይችላል።

🥈የMidgut Volvulus ምልክቶች ምን ምን ናቸው?

✏️በጣም አስፈላጊው እና ከሁሉም ምልክቶች ቀደሞ የሚከሰተው  ምልክት በድኖገት የሚከሰት አረንጓዴ ነገር ማስታወክ (Bilious Vomiting) ነው።

✒️ይህም ለአንጀት መዘጋት የሚጠቁም  አደገኛ  ምልክት (Red flag sign) ነው።

✍ሌሎች ምልክቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ:

• ከባድ የሆነ የሆድ ህመም (በጨቅላ ህጻናት ላይ ከመጠን በላይ ማልቀስ ሊያስከትል ይችላል)

• የሆድ መነፋት

• መፍዘዝ እና መድከም

• የአንጀት እንቅስቃሴ መቀነስ ወይም ሰገራ ወይም አየር አለማስወጣት።

😳ብዙ ወላጆች አረንጓዴ ትውከትን  አደገኛ ምልክት መሆኑን ላያውቁ ይችላሉ።
😳ይህም ወደ ሆስፒታል ለመውሰድ ይዘገያሉ።

🌡እንደ አለመታደል ሆኖ እርስዎ እንዳጋጠሙዎት መዘግየት አስከፊ እና ለሞት የሚዳርግ  ሊሆን ይችላል።

🥉ቀዶ ጥገና ከተደረገ ግን ለምን ምንም ነገር አልተሰራም?

🩺ይህ ችግር ያለባቸው ህፃናት ዋናው ህክም ቀዶ ጥገና(Surgery) ነው።

🩺በቀዶ ሕክምናው ጊዜ  የአንጀቱን የደም ዝውውር ጤነኛ ወይም ሕያው (viable) መሆኑን ወይም የበሰበሰ (Gangrene) እንደሆነ ለማወቅ ይረዳል።

🌡በጣም ብዙ አንጀት ከሞተ የመዳን እድል ላይኖራቸው ይችላል።

ምክንያቱም:

1. አጭር የአንጀት ሲንድሮም (Short Bowel Syndrome)

💊አብዛኛው አንጀት ከተወገደ ህፃኑ በሕይወት ለመቆየት በቂ ምግብ እና ንጥረ ነገሮችን  መውሰድ አይችልም።
በዚህም ምክንያት የመትረፍ እድሉን አደጋ ውስጥ ይከተዋል።

2. ከባድ ኢንፌክሽን (Sepsis) -

💊የሞተ አንጀት ወደ ደም ውስጥ መርዛማ ንጥረ ነገሮችን ፣ባክቴሪያዎችን ይለቃል።
💊ይህም ለሕይወት አስጊ የሆነ ኢንፌክሽን ያመጣል።

🩺ቀዶ ጥገናውን የሚሰሩት  ሐኪሞች አብዛኛው አንጀት መሞቱን ከተረዱ ልጁን ለማዳን ምንም ዓይነት የቀዶ ጥገና አማራጮች ላይኖር ይችላል።

😭ይህ ልብ የሚሰብር ውሳኔ ነው።
😭ዘግይተው ከመጡ ምንም ለማድረግ አለመቻል ለሐኪሙም ቢሆን ልብን የሚሰብር እውነታ ነው።

✍ሌሎች ወላጆች ከዚህ ምን ይማራሉ?

👉ከዚህ ተሞክሮ ወላጆች መማር ያለባቸው ዋናው ትምህርት ቀድሞ መረዳትና  እና አስቸኳይ ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ  ነው።

👉ወላጆች ልጃቸው አረንጓዴ ትውከት ካለበት ወዲያውኑ አስቸኳይ ሕክምና  ማግኘት አለባቸው።

😳ለጥቂት ሰዓታት እንኳን መዘግየት አንጀትን በማዳን እና በማጣት መካከል ያለውን ልዩነት ሊያመለክት ይችላል።

😳😳😳ማስታወስ ያለብን ቁልፍ ነጥቦች፡-

✓ ጨቅላ ሕፃናት  አረንጓዴ ነገር ካስታወኩ  ሁልጊዜ የድንገተኛና ቀዶ ጥገና የሚያስፈልገው የአንጀት ችግር ምልክት  ነው።

✓ የአንጀት አቀማመጥ ችግር ያለባቸው ህፃናት ምንም ምልክት ሳያሳዩ ጤናማ ሆነው  ቆይተው ድንገት የአንጀት መዞር ችግር ሊከሰትባቸው  ይችላል።

✓ አፋጣኝ ቀዶ ጥገና ቶሎ ከተሰራ አንጀትን ሊያተርፍ ይችላል።

✓ መዘግየት ወደ አንጀት መበስበስ (ጋንግሪን) ሊያመራ ይችላል። ይህም መዳን የማይቻል ያደርገዋል።

ይህንን ታሪክ ለማካፈል ያለዎት ድፍረት እና ተነሳሽነት  ሌሎች ወላጆች ምልክቶቹን ቀደም ብለው እንዲያውቁ እና ተመሳሳይ አሳዛኝ ሁኔታዎች እንዳይከሰቱ  ለመከላከል ሊረዳቸው ይችላል እና ላመሰግንዎ እፈልጋለሁ።

ለእርስዎ እና ለቤተሰብዎ የተሰማንን ጥልቅ ሀዘን ለመግለፅ እፈንፈልጋለን ፣ መፅናናትን ያድልልን ።

ህፃናት በሁሉም ቦታ በቂ እንክብካቤ እንዲያገኙ እንሰራለን!!!
 
አዘጋጅ: ዶ/ር ሳለአምላክ ጥጋቤ: የህፃናት ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ሐኪም
Dr. Saleamlak Tigabie: MD, Pediatric Surgeon

👉ለበለጠ መረጃ እና ነፃ የምክር አገልግሎት :

📱0911441651

👉Gmail: saleamlaksati@gmail.com
👉@DrSaleamlak(በግል ለማናገር እና  ምስል ለመላክ ይህን አድራሻ ይጠቀሙ)
 


https://t.me/ethiodoc


❤️መልካም ዜና ለታካሚዎቻችን❤️
=======================

የአዲስ አበባ ሀምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ ከመጋቢት 29,2017 ዓምእስከ ሚያዚያ 03,2017ዓም ድረስ ከወሊድ ጋር የተያያዘ #ሰገራ እና #አየር  #መቆጣጠር_አለመቻልን  ለማከም ዘመቻ አዘጋጅቷል።

ይህ የቀዶ ጥገና ዘመቻ የሚከናወነው ከውጭ አገር በሚመጡ የኮሎሬክታል የቀዶ ጥገና ሐኪሞች ቡድን እና በዩሮጂኔኮሎጂስት ቡድን ነው፡፡

እንደዚህ አይነት ህሙማን የምታውቁ ካላችሁ በአቅራቢያ ወደሚገኙ የሃምሊን ፊስቱላ ቅርንጫፍ ማእከላት ማለትም ወደ ይርጋለም፣ መቱ፣ ሀረር፣ ባህርዳር፣ መቀሌ እና አዲስ አበባ ማእከላት ይላኩላቸው።

-> ወደ አዲስ አበባ ለሕክምና እና ከሕክምና በኋላ ወደ ቤት በሁሉም  ማዕከላት መጓጓዣ ተዘጋጅቷል.

-> ሕክምናው የሚሰጠው በነፃ ሲሆን፤ በሕክምና ወቅት ለሚኖራቸው ቆይታም ምቹ ማረፊያ ቦታም በነፃ ነው።

-> ከታካሚው የሚጠበቀው ለሕክምና መምጧት ብቻ ነው።

ታካሚዎች ከመጋቢት 27 ,2017ዓም በፊት በአቅራቢያባቸው በሚገኙ የሀምሊን ፊስቱላ ማዕከላት ተገኝተው ቅድመ ምርመራ ማካሄድ ይኖርባቸዋል::



_
https://t.me/ethiodoc


ፈሳሽ ስላጠራቀመ የጆሮ ኢንፌክሽን ምን ያህል ያውቃሉ?
============================

የጆሮ ኢንፌክሽን አብዛኛውን ጊዜ በቫይረስ ወይም በባክቴሪያ ምክንያት የሚከሰት የህመም አይነት ነዉ፡፡ ብዙ ጊዜም የላይኛውን የአየር ቧንቧ የሚያጠቁ በሽታዎችን ተከትሎ ያከሰታል።

የላይኛውን የአየር ቧንቧ (እንደ ጉንፋንና አለርጂ የመሳሰሉት…) የሚያጠቁ በሽታዎች በሚኖሩ ጊዜ የጆሮን የመካከለኛውን ክፍል እና ጉሮሮን የሚያገናኘው ቱቦ (Eustachian Tube) ያብጥና ጤናማ አየር ወደ መካከለኛው የጆሮ ክፍል እንዳይተላለፍ ያደርጋል፡፡ ይኼም በመካከለኛው የጆሮ ክፍል ውስጥ ፈሳሽ እንዲጠራቀም፣ እንዲሁም ለባክቴሪያና ለቫይረስ  አመቺ የመራቢያ ሁኔታን ይፈጥራል። ይህም የመካከለኛው ጆሮ እንዲያብጥና መግል እንዲፈጠር ያደርጋል።

የጆሮ ኢንፌክሽን (Otitis Media) አይነቶች

1) አጣዳፊ የጆሮ ኢንፌክሽን (Acute Otitis Media) ፦ በቀናት ወይም በአጭር ሳምንታት ውስጥ የሚፈጠር የጆሮ ኢንፌክሽን ነው።

2) የቆየ የጆሮ ኢንፌክሽን (Chronic Otitis Media)፦ ለብዙ ሳምንታት ወይም ወራቶች የዘለቀ ኢንፌክሽን ሲሆን ብዙ ጊዜ በተደጋጋሚ መግል እንዲከሰት ያደርጋል።

3) ፈሳሽ ያጠራቀመ የጆሮ ኢንፌክሽን (Otitis Media with Effusion)፦ ይህ ከድንገተኛ የጆሮ ኢንፌክሽን ወይም ከተለያዩ ተጓዳኝ በሽታዎች በኋላ የሚከሰት ሲሆን ወደውጭ የማይፈስ ፈሳሽ በጆሮ መካከለኛው ክፍል እንዲከሰት ያደርጋል። ይህ በሽታ በአብዛኛው ሕጻናት ላይ ይስተዋላል።

ፈሳሽ ያጠራቀመ የጆሮ ኢንፌክሽን መንሴዎች
ይህ ችግር እንዲፈጠር የሚያደርጉ የተለያዩ መንሳኤዎች አሉ እነዚህም፦
-የሳይነስ በሽታ
-የቶንሲል ኢንፌክሽን
-የአፍንጫ ውስጥ ዕጢዎች
-አለርጂዎች
-ያልታከመ የጆሮ ኢንፌክሽን የመሳሰሉት ናቸው።

ምልክቶቹም፦

-ከወትሮ በተለየ ሁኔታ መነጫነጭና ማልቀስ
-እንቅልፍ ማጣት
--የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ማስመለስ፣ ትኩሳት
-ራስ ምታት፣ የጆሮ ህመም
-የመስማት ችሎታ መቀነስ
-የዘገየ የመናገር ችሎታ
-የጆሮ ህመም
-የሰውነት ሚዛንን መጠበቅ አለመቻል የመሳሰሉት ናቸው።

ህክምናዎቹም፦
- የህመም ማስታገሻዎች፣ ፈሳሽ በበቂ ሁኔታ መውሰድ፣ ተጓዳኝ ችግሮችን ማከምና በሐኪም የታዘዙ ፀረ ባክቴሪያ መድሃኒቶች በመስጠት እንዲሁም በቀዶ ህክምና ታምቡርን በመብሳት ፈሳሹን ማስወገድ (Myringotomy)  እንዲሁም ማፍሰሻ ቱቦ በጆሮ መካከለኛው ክፍል በማስቀመጥ (Myringotomy with Vent Tube) ማከም ይቻላል።

መሪ ቃላችን እንደሚለው የተሻለ ሕክምና ይግባዎታል! እያንዳንዱን ታካሚ ተደራሽ የሚያደርግና በዘመናዊ መሳሪያ የታገዘ ሕክምናን ማቅረብ ደግሞ ተቀዳሚ ዓላማችን ነው!

ዶ/ር ዋለ ልመንህ, የሕጻናት የአንገት በላይ ሰብስፔሻሊስትና የአንገት በላይ ስፔሻሊስት



https://t.me/ethiodoc


"ዒድ ሙባረክ!"

እንኳን ለ1446ኛው የዒድ አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ.


__
https://t.me/ethiodoc


የባህላዊ አጥንት ጠጋኞች (ወጌሻ) በኢትዮጵያ ህጻናት ህይወት ላይ የሚያሳድሩት ተጽእኖ
=========================

በኢትዮጵያ፣ ባህላዊ አጥንት ጠጋኞች ለረጅም ጊዜ የባህል አካል ሆነው ቆይተዋል፣ ቤተሰቦችም በተለምዶ ባላቸው ጥበብ እና ተደራሽነት ምክንያት ይፈልጓቸዋል።

ሆኖም፣ እንደ አጥንት ቀዶ ጥገና ሐኪም፣ በእነዚህ ተግባራት ምክንያት በብዙ ህጻናት ህይወት ላይ የሚደርሰውን አስከፊ መዘዝ እየተመለከትኩ ነው። በቀላሉ በዘመናዊ የህክምና ሊታከም የሚችል ቀላል ጉዳት፣ በባህላዊ ወጌሻ በተሳሳቱ ዘዴዎች ምክንያት ወደ ህይወት ዘመን አሳዛኝ ሁኔታ ይቀየራል።

በጣም የተለመዱት እና ልብ የሚሰብሩ ሁኔታዎች ህጻናት ቀላል ስብራት ወይም ጡንቻ ላይ ቀለል ያለ ጉዳት ሲደርስባቸው ስብራት ወይንም መገጣጠሚያ ዉልቃት እንዳላቸዉ ሁኖ በስህተት ሲታከሙ ነው። ባህላዊ ጠጋኞች የከፋ ጉዳት እንደሆነ በማሰብ "ስብራቱን ለመያዝ" በጥብቅ የታሰሩ የቀርከሃ እንጨቶችን ይጠቀማሉ። እነዚህ የቅርቅሃ እንጨቶች ብዙውን ጊዜ በጣም ጥብቅ ስለሆኑ ከጉዳቱ ቦታ በታች ያለውን የደም ፍሰት ይቀንሳል።

በመጀመሪያ፣ በህጻኑ ላይ የሚታየው ከፍተኛ ህመም እና ስቃይ በጠጋኞች እና በቤተሰቦች ህክምናው እየሰራ እንደሆነ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል። ሆኖም፣ እውነታው ከዚህ ፈጽሞ ተቃራኒ ነው። የደም ፍሰት እጥረት ወደ ደም መቋረጥ ይመራል፣ በመጨረሻም የተጎዳው እጅ ወይም እግር ጋንግሪን ይሆናል። በጣም የክፋዉ ነገር ደግሞ ፡ ይህ ሁሉ ከትፍጠረ በሆላ ወደ ጸበል መውሰዳቸዉ ነው፡፡

መጨረሻ ላይ ሆስፒታል ሲመጡ ጋንግሪን የፈጠረዉ አካል በስብሶ ኢንፌክሽን በሰዉነታቸዉ ተሰራጭቶ በጣም ተዳክመዉ እናገኛቸዋለን፡፡ አስቡት አንድ ህጻን በዚህ ሁሉ ሂደት ሚሳልፈዉን ስቃይ፡፡ (ከዚህ በታች ያሉትን ፎቶዎች ይመልከቱ)

አንድ ትልቅ ህልም ያለውን ትንሽ ልጅ ምናልባት ቀኝ እጁን ያጣ ልጅ ወይም እግሩን ያጣ ትንሽ ልጅ አስቡ። ይህ ልጅ በአካል ብቻ ሳይሆን በከባድ አዐምሮዊ ህመምም ይሰቃያል። ከጓደኞቹ ጋር ለመዋሃድ ይቸገራል እናም የልጅነት ጊዜዉን ልዩ የሚያደርጉትን አስደሳች ጊዜያት ያጣል።አድጎ ያለመዉን ሙያ ሳያሳካ ይቀራል፡፡

ይበልጥ የሚያሳዝነው ሕይወታቸው ላይ ጉዳት መድረሱ ብቻ ሳይሆን ልናስቅራቸዉ በምንችላቸው ችግሮች ምክንያት መምጣታቸው ነው። ብዙ ቤተሰቦች በጠንካራ የባህል እምነቶች ወይም ባለማወቅ ልጆቻቸውን ለመርዳት ሲሞክሩ የከፋ ጉዳት ያደርሳሉ።

ይህ ችግር ቀደም ሲል ዘመናዊ የህክምና አገልግሎት ውስን በሆነባቸው ሩቅ ከተሞች በስፋት ይታይ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን ይህ እየተቀየረ ነው። በጣም በቅርበት ርቀት በሚገኙ አካባቢዎች ላይ እንኳን የአጥንት ቀዶ ጥገና ሐኪሞች ይገኛሉ። ሆኖም፣ በባህላዊ ጠጋኞች ላይ ያለው እምነት አሁንም አልተቀየረም፣ ይህም በህዝብ ግንዛቤ እና ትምህርት ላይ ያለውን ወሳኝ ክፍተት ያሳያል።

የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከ BOSAD ኢትዮጵያ ጋር በመሆን ይህንን ጉዳይ ለመፍታት ቅድሚያ መስጠት አለበት። በትልልቅ ከትሞች ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ፣ ፍላጎቱ ከፍተኛ በሆነባቸው ራቅ ወዳሉ አካባቢዎች ላይ ጥረት መደረግ አለበት።

ይህን ችግር ለመፍታት የተቀናጀ ጥረት በጣም አስፈላጊ ሲሆን በመጀመሪያ፣ የጤና ሚኒስቴር ዘመናዊ ድንገተኛ የአደጋ ህክምና (trauma care) ውጤታማ አንዲሁም ተደራሽ መሆኑን ለማህበረሰቡ በማሳየት መደገፍ አለበት።

ሁለተኛ፣ ወጌሻዎች የሚሰጡት ህክምና ችግር እንዲረዱ በማሰልጠን እና ከአጥንት ቀዶ ህክምና ባለሙያዎች ጋር እንዲሰሩ መበረታታት አለባቸው። ይሄን በማድረገም ብዙ ህይወቶችን ለማዳን እና የአካል ጉዳተኛነትን ለመከላከል ያስችላል።

ሶስተኛ፣ የጤና ድርጅቶች ማህበረሰቡን የባህላዊ ህክምና የሚያመጣቸው ተጉአዳኝ ችግሮች አንዲሁም ስለ ዘመናዊ ህክምና ጥቅሞች ለማስተማር የግንዛቤ ማስጨበጫ (Awareness campaign) ፕሮግራሞችን ማካሄድ አለባቸው።

ኢትዮጵያ ዉስጥ ያሉ ህፃናት ሕይወት አደጋ ላይ ነው። እያንዳንዱ ህፃን እንዲህ አይነትችግሮች ሳይገጥሙት ጤናማ እና ደስተኛ ሆኖ የማደግ እድል ሊኖረው ይገባል። የቆዩ እና ደህንነታቸው ያልተጠበቁ ልማዶች አሁንም ጉዳት እያደረሱ ነው። ነገር ግን የአጥንት ቀዶ ህክምና ሐኪሞች፣ የጤና ባለሙያዎች እና መንግስት አንድ ላይ ከሰራን የህፃናትን ጤና መጠበቅ እና የተሻለ የወደፊት ተስፋ መስጠት እንችላለን::

#BOSAD#MOH#AHB#AO alliance # ESOT.

Dr Yonatan Abie: Assistant professor Orthopedic and Trauma Surgery, Debretabor University



https://t.me/ethiodoc


ስቲች (Episiotomy)
===============

✅️በተለምዶ ስቲች የምንለው ፣የብልትን የውጨኛውን ክፍል በመቀስ በመቁረጥ ማስፋት ነው።
✅️ከውጨኛው የብልት ከንፈር ላይ ፣ቀላል ማደንዘዣ በመርፌ በመውጋት ፣ ከፍ ያለ ቁርጠት፣እና መግፋት ሲኖር መቁረጥ ነው።


ለምን አስፈለገ?

👉በምጥ ሰዐት ለማዋለድ መሳሪያ መጠቀም ሲኖርብን
👉 ፅንስ ኪሎው ከፍ ያለ ሆኖ የበለጠ ጉዳት (tear )ያመጣል ተብሎ ከተገመተ።
👉የፅንስ ልብ ምት ጥሩ ሳይሆን ቀርቶ ቶሎ ለማዋለድ ሲያስፈልግ፣
👉በመቀመጫው ያለ ፅንስ ፣
🚫ለሁሉም ሴት አይደረግም ፣

ከስቲች ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች ምንድናቸው?

👉ህመም ፣(pain) ቁጭ ብሎ ማጥባትእስኪያቅትሽ ድረስ ህመም ሊኖርሽ ይችላል።
👉የቁስሉ መብገን(ኢንፌክሽን)
👉በግብረስጋ ግኑኝነት ጊዜ ህመም ፣(Dyspareunia)
👉ሽንትን መቆጣጠር አለመቻል ፣
👉ሰገራን መቆጣጠር አለመቻል ፣
👉ቶሎ ላይድን ይችላል።
👉ከ ታቀደው ከፍ ያለ መጠን ያለው ስቲች ( ይህ ሲሆን የፊንጢጣ ጡንቻ ጉዳት በተለያየ መጠን ይከሰታል )

ስቲች እንዴት ይድናል?

👉ስቲች ለመዳን ከ ስድስት እስከ ስምንት ሳምንት ይፈልጋል (6-8 ሳምንት )
✳️አሁን በብዛት ለመስፋት የምንጠቀመው ክር በራሱ ከሰውነት ጋር ይዋኻዳል ፣
👉ማስታገሻ መድኃኒት መውሰድ ።
👉በመጀምሪያዎቹ ቀናት እብጠቱን ለመቀነስ በረዶ ማድረግ (perineal cold pack ):
👉የሰገራ ድርቀት እንዳይኖር መጠንቀቅ ( ይህ አንድ በ እርግዝና ጊዜ ይባባሳል ፣ከወሊድ በኻላምይቀጥላል )እንዳይኖር
👉አመጋገብን ማስተካከል ፣
👉ውሃ መጠጣት፣
👉አንዳንድ የ ሰገራ ማለስለሻ መድኃኒቶችን መጠቀም ።
👉ቁስሉን በ ቀን አራት ጊዜ በ ንፁህ ውሃ መዘፍዘፍ (መታጠብ አደለም )


ግኑኝነት መች ነው ማድረግ የሚቻለው?

❤️ቁስሉ ከዳነ ከወር ካስራአምስት ቀን ጀምሮ ይቻላል::

ማስተዋል ያለብሽ!!!

✍ለጥቂት ወራት ህመም ይኖርሻል ፣ ✍በተጨማሪም ስለምታጠቢ የብልት መድረቅ ሊኖርሽ ይችላል ። ይሄንን ከግምት በማስገባት በግኑኝነት ጊዜ ማለስለሻ መጠቀም ጥሩ ነው።❤️❤️

ከስቲች ጋር በተያያዘ ህክምና መቼ መሄድ አለብኝ?

👉ህመሙ እይባሰ ሲሄድ ፣
👉መጥፎ ጠረን ያለው ፈሳሽ ከ ቁስሉ ሲወጣ
👉መግል ከቁስሉ ሲወጣ ፣
👉ቁስሉ ከደማ፣
👉ቁስሉ እያበጠ ሲመጣ ፣
👉ትኩሳት ፣ብርድ ብርድ ማለት ሲኖርሽ፣
👉ሰገራ መቆጣጠር ካቃተሽ

💜💜በስቲች ከወለድሽ ከወራት በኃላም ህመም( በግኑኝነት ጊዜ ፣) ይኖራል ፣ ይህ ከሆነ ሀኪምሽ ጋር መሄድ ፣ እናም በማማከር የተለያዩ መፍትሔዎችን መፈለግ ።

#በቅንነት#ሸር #አድርገው #ለሌሎችም #ያድርሱ፡፡

ምንጭ #ጤናዎ በእጅዎ



https://t.me/ethiodoc


አንጀት ካንሰር
=========

የአንጀት ካንሰር በትንሹ አንጀት : በትልቁ አንጀት እንዲሁም በፊንጢጣ ላይ የሚከሰት የካንሰር ህመምን ያጠቃልላል።

በሀገራችን ያለበት ሁኔታ ምን ይመስላል?

በወንዶች ላይ እንደአዲስ ከሚታወቁ (newly diagnosed) የካንሰር አይነቶች መሀከል በአንደኛነት እንዲሁ በሴቶች ላይ ደሞ (ከጡትና ከ ማህጸን በር ካንሰር በመቀጠል) በሶስተኛ ደረጃነት ይገኛል።

በአጠቃላይም በሀገራችን በ2020 አውሮፓውያን አቆጣጠር 6050 የሚሆኑ አዳዲስ የትልቁ አንጀት ካንሰር ታማሚዎች ተገኝተዋል። ይህም አሀዝ በሚቀጥሉት አመታት እንደሚጨምር ይጠበቃል።

ለትልቁ አንጀት ካንሰር አጋላጭ ነገሮች ምንድናቸው?

1.እድሜ
የአንጀት ካንሰር እድሜኣቸው ከ50 አመት በላይ የሆኑ ሰዎች ላይ የመከሰት እድሉ ከፍ ይላላል,ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የአንጀት ካንሰር በወጣቶችና በጎልማሶች ላይ ቁጥሩ እየጨመረ ነው።

በሀገራችን በሚገኝ አንድ ሆስፒታል በተሰራ ጥናትም 40% የሚሆኑት የትልቁ አንጀት ካንሰር ታማሚዎች እድሜኣቸው ከ40 አመት በታች ነው ይህም ከሌሎች የአለም ሀገራት በጣም የተለየና የትልቁ አንጀት ካንሰር በሀገራችንና ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገራት በብዛት በጎልማሶች ላይ የመከሰት እድሉ ከፍ ያለ ነው።

2.የቤተሰብ ታሪክ
የትልቁ አንጀት ካንሰር ወይም የሌላ የሰውነት ክፍል ካንሰር በቤተሰብ ውስጥ የተከሰተ ከሆነ ሌሎች የቤተሰብ ኣባላት ወደ ፊት የመያዝ እድላቸው ይጨምራል።

3.የቅድመ ካንሰርነት ደረጃ የደረሱ አንጀት ላይ የሚከሰቱ እባጮች (colonic polyps)

4.ለካንሰር አጋላጭ የሆኑ የዘረመል ለውጦች

5.ረጅም ጊዜ የቆዩ የአንጀት ቁስለት ህመሞች (inflamatory bowel disease)

6.የእንስሳት ተዋጽኦ የሆኑ ምግቦችን ማዘውተር

7.ሲጋራ ማጤስና አልኮል አብዝቶ መጠቀም

8.ከልክ ያለፈ የሰውነት ክብደት
9.አካላዊ እንቅስቃሴ አለማድረግ

ምልክቶቹስ?

የሰውነት ክብደት መቀነስ፣ የሆድ መነፋት፣ሰገራን እና ፈስን እንደተለመደው ሁኔታ ለማውጣት መቸገር፤ በፊንጢጣ በኩል ደም መፍሰስ፣ መጸዳጃ ቤት ከሄዱ በኋላ ያለመጨረስና የማስማጥ ስሜት ስሜት፣ በተደጋጋሚ የደም ማነስ ህመም መከሰት፣ ደረጃው ከፍ እያለ ሲሄድም የአንጀት ሙሉ በሙሉ መዘጋትን ሊያመጣ ይችላል ህመሙ በፊንጢጣ አካባቢ ከሆነም ሰገራ ና ፈስ የመቆጣጠር አለመቻል::

ምን ይደረግ?

1.እንድሜው/ዋ ከሀምሳ አመት በላይ የሆነ ሰው ወይም አጋላጭ ነገሮች ያሉት/ያላት አልያም ከላይ የተገለጹት ምልክቶች ካሉ አለመዘናጋትና በአፋጣኝ ወደሀኪም ቀርቦ መመርመር።

በሚያስቆጭ ሁኔታ አብዛኛዎቹ ታካሚዎቻችን የአንጀት ካንሰር ህመም ምልክቶች ከታዩ በኋላ ወደ ህክምና ዘግይተው እና ማዳን የማይቻልበት ሁኔታ ላይ ወደ ሀኪም ይመጣሉ። ከተለመዱት የመዘግየት ምክንያቶችም አሜባ ወይም የፊንጢጣ ኪንታሮት ተብለው በተደጋጋሚ መታከም አልያም እንደአማራጭ የተለያዩ መፍትሄዎችን መፈለግ ነው።

2. መቀየር የሚችሉ አጋላጭ ባህሪያት ካሉ ማስተካከል።

3. ህመሙ ከታወቀ በኋላም ከሀኪም ጋር ተመካክሮ በቀጣይ ህክምናዎችን በአግባቡ መከታተል።

ቸር እንሰንብት!

Dr. Binyam Yohannes: General surgeon, colorectal surgeon
ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ

ለህክምና መረጃ 📞 0911463939




https://t.me/ethiodoc


ኮሌራ ምንድነዉ?

👉ኮሌራ በቫይብሪዮ ኮሌራ ባክቴሪያ ምክንያት የሚመጣ አጣዳፊ የተቅማጥ በሽታ ሲሆን በሰዓታት ዉስጥ ለሞት የሚዳርግ አደገኛ በሽታ ነው።

👉ኮሌራ በተለይ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት እና በተፈጥሮ አደጋዎች ወይም በሰብአዊ ቀውሶች በተጠቁ አካባቢዎች አለም አቀፍ የጤና ስጋት ነው።

መንስዔዉ
👉በቫይብሪዮ ኮሌራ ባክቴሪያ የተበከለ ውሃ እና ምግብ
👉የአካባቢ ሁኔታዎች፡ የጎርፍ መጥለቅለቅ፥ የመሠረተ ልማት እጦት እና ደካማ የንጽህና አጠባበቅ, የውኃ ምንጮችን መበከል ሊያስከትል ይችላል

መተላለፊያ መንገዶች
👉የተበከለ ውሃ እና ምግብ
👉ከሰዉ ወደ ሰዉ
👉ከእጅ ወደ አፍ
👉ኮሌራ በፍጥነት ሊዛመት ይችላል
👉የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ውስንነት ባለባቸው አካባቢዎች ወረርሽኞች በፍጥነት እንዲዛመት ያደርጋል

የኮሌራ ምልክቶች
👉ውሃማ ተቅማጥ
📌ድንገተኛና አጣዳፊ
📌ብዛት ያለዉ
📌ሽታ የሌለዉ
📌የሩዝ ዉሃ የመሰለ ተቅማጥ
👉ማቅለሽለሽና ትውከት
👉በሰዉነት ዉስጥ ያለ ፈሳሽ በፍጥነት መቀነስ/ፈጣን የሰውነት ድርቀት/
📌የከንፈር መድረቅ
📌የቆዳ መድረቅ
📌የአይን መድረቅ
📌ዉሃ መጥማት
📌የሽንት መጠን መቀነስ
📌ፈጣን የልብ ምት
📌የደም ግፊት መቀነስና
📌ዕራስን እስከ መሳት ሊደርስ ይችላል
👉የሆድ ቁርጠት

ተያያዥ ጉዳቶች
👉በሰዉነት ዉስጥ ያለ ፈሳሽ በፍጥነት መቀነስ
👉ከፍተኛ የኤሌክትሮላይት መዛባት
👉ድንገተኛ የኩላሊት ጉዳት
👉ለሞት ሊዳርግ ይችላል
👉የተመጣጠነ ምግብ እጥረት
👉ስር የሰደደ ተቅማጥ

ህክምናዉ
የኮሌራ ህክምና በቤትም ሆነ በሆስፒታል ሊሰጥ ይችላል።

👉በቤት ውስጥ
🛖 የጠፉ ፈሳሾችን እና ኤሌክትሮላይቶችን ለመተካት
💊ORS
💊ግማሽ ማንኪያ ጨው እና 6 ማንኪያ ስኳር በ 1 ሊ ንፁህ ውሃ በመበጥበጥ በተደጋጋሚ መጠጣት
💊ተጨማሪ ፈሳሾችን እነዲወስዱ ማበረታታት
🛖 ካፌይን እና ከፍተኛ የስኳር ይዘት ያላቸውን መጠጦች ያስወግዱ
🛖 ግለሰቡ ፈሳሾችን መታገስ ከቻለ በኋላ በቀላሉ ሊፈጩ በሚችሉ እንደ (ሙዝ, ሩዝ, ፖም ወዘተ ባሉ ምግቦች ይጀምሩ
🛖በቂ እረፍት እንዲያደርጉ ማበረታታት

👉በጤና ተቑማት
🩺 ORS
🩺 ፈጣን ፈሳሽ ማጣትን ለመቆጣጠር የደም ሥር (IV) ፈሳሾች አስፈላጊ ሊሆኑ ይችላሉ
🩺 እንደ አስፈላጊነቱ ፀረ ባክቴሪያዎች ሊሰጡ ይችላሉ
🩺 የኩላሊት እጥበትና
🩺 የምግብ ድጋፍ ሊሰጣቸው ይችላል

መከላከያ መንገዶች
🧪የአካባቢ ጽዳትን መጠበቅ
🧪የግል እና የአካባቢ ንፅህናን መጠበቅ
🧪ንፁህ የመጠጥ ውሃን መጠቀም
🧪ዉሃን አፍልቶ በማቀዝቀዝ መጠጣት
🧪አትክልቶችንና ፍራፍሬዎችን ከመመገብዎ በፊት በደንብ ማጠብ
🧪ጥሬ ወይም ያልበሰሉ ምግቦችን አለመጠቀም
🧪ከመጸዳጃ ቤት በኋላ፣ ምግብ ከማዘጋጀትዎ በፊትና በኋላ፣ እጅን በንጹህ ውሃ እና ሳሙና መታጠብ
🧪ምግብ ከመመገብዎ በፊትና በኋላ፣ እጅን በንጹህ ውሃ እና ሳሙና መታጠብ
🧪የውሃ አቅርቦት ስርዓቶችን ማሻሻል
🧪ትክክለኛ የፍሳሽ ማስወገጃ መንገድን መከተል

ዶ/ር ዮናስ ጋሻዬ (MD, Nutritionist, Author of DREAM PEDIATRICS BOOK)

https://t.me/ethiodoc


💪 ጠንካራ ሴቶች፣ ጠንካራ አጥንቶች፡ ኦስቲዮፖሮሲስን በተመለከተ ዝምታን መስበር
===========================

በኢትዮጵያ በተለይም በሴቶች መካከል የአጥንት ጤና ችላ ይባላል። ኦስቲዮፖሮሲስ አጥንትን የሚያዳክም በሽታ ሲሆን ስብራት እስኪከሰት ድረስ በብዛት ያልታወቀ ነው።

ብዙ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ስለ አጥንት ጤና፣ ትክክለኛ አመጋገብ እና ቀደምት ምርመራ ግንዛቤ የላቸውም፣ ይህም በኋለኛው ህይወት ላይ ከባድ የጤና ችግሮች ያስከትላል።
ሴቶች ከወንዶች ይልቅ በተለይም ከማረጥ በኋላ በሆርሞን ለውጦች ምክንያት የአጥንት ጥንካሬን ስለሚቀንስ ኦስቲዮፖሮሲስ የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ሆኖም በትክክለኛ የአኗኗር ዘይቤ ምርጫዎች ሴቶች አጥንታቸውን ማጠናከር፣ ስብራትን መከላከል እና ጤናማ እና ንቁ ህይወት መምራት ይችላሉ።

💡 ሴቶች ለአጥንት ጤና ቅድሚያ መስጠት ያለባቸው ለምንድን ነው?

ብዙ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ለኦስቲዮፖሮሲስ ተጋላጭ የሆኑት በ፡
✅ ዝቅተኛ የካልሲየም እና የቫይታሚን ዲ መጠን – ብዙ ምግቦች በቂ የወተት ተዋጽኦ፣ ቅጠላማ አትክልቶች ወይም ሌሎች በካልሲየም የበለፀጉ ምግቦች የላቸውም።

✅ ለፀሀይ ብርሀን ውስን መጋለጥ – ቫይታሚን ዲ ለአጥንት ጤና ወሳኝ ነው፣ ነገር ግን ብዙ ሴቶች በቤት ውስጥ ይቆያሉ ወይም አብዛኛውን ቆዳቸውን ይሸፍናሉ።

✅ ከማረጥ በኋላ የሆርሞን ለውጦች – ኢስትሮጅን የአጥንትን ጥንካሬ ለመጠበቅ ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ከማረጥ በኋላ የኢስትሮጅን መጠን ይቀንሳል፣ ይህም ፈጣን የአጥንት መጥፋት ያስከትላል።

✅ የማይንቀሳቀስ የአኗኗር ዘይቤ – ክብደት የሚሸከሙ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች (መራመድ፣ መሮጥ፣ የጥንካሬ ስልጠና) አለመኖር ከጊዜ በኋላ አጥንትን ያዳክማል።

✅ ባህላዊ ምክንያቶች እና የተሳሳቱ አመለካከቶች – ብዙ ሴቶች ስብራት ወይም ህመም እስኪሰማቸው ድረስ የህክምና እርዳታ አይፈልጉም።

⚠️ የኦስቲዮፖሮሲስ ምልክቶች እና ምልክቶች
ኦስቲዮፖሮሲስ ብዙውን ጊዜ "ፀጥ ያለ በሽታ" ተብሎ ይጠራል ምክንያቱም ስብራት እስኪከሰት ድረስ ምልክቶች ሳይታዩ ያድጋል። ነገር ግን አንዳንድ የማስጠንቀቂያ ምልክቶች የሚከተሉትን ያካትታሉ፡

❌ በአከርካሪ አጥንት ላይ በትንንሽ ስብራት ምክንያት የጀርባ ህመም

❌ በአከርካሪ አጥንት መውደቅ ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁመት ማጣት

❌ የታጠፈ አቀማመጥ (የታጠፈ ጀርባ)፣ ይህም እንቅስቃሴን አስቸጋሪ ያደርገዋል

❌ ከትንንሽ ውድቀቶች ወይም እንደ መታጠፍ ወይም ማሳል ካሉ ቀላል እንቅስቃሴዎች እንኳን በተደጋጋሚ ስብራት

💡 ምልክቶች በሚታዩበት ጊዜ ከፍተኛ የአጥንት መጥፋት ተከስቷል። ለዚህ ነው ቀደምት መከላከል እና መደበኛ ምርመራዎች ወሳኝ የሆኑት!

🩺 አጥንትዎን ለህይወት ዘመን ጠንካራ ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?

1️⃣ በቂ ካልሲየም እና ቫይታሚን ዲ ያግኙ
💊 ካልሲየም፡ ሴቶች ከማረጥ በፊት በቀን 1,000 ሚ.ግ እና ከማረጥ በኋላ በቀን 1,200 ሚ.ግ መውሰድ አለባቸው።

ምንጮች፡
🥛 የወተት ተዋጽኦ (ወተት፣ እርጎ፣ አይብ)
🥬 ቅጠላማ አትክልቶች (ጎመን፣ ኬል)
🐟 ዓሳ (ሰርዲን፣ ሳልሞን)
🥜 ለውዝ እና ዘሮች (ለውዝ፣ ሰሊጥ)

🌞 ቫይታሚን ዲ፡ ካልሲየም እንዲዋሃድ ይረዳል። ሴቶች በየቀኑ 800-1,000 IU ያስፈልጋቸዋል።
ምንጮች፡
☀️ ለፀሀይ ብርሀን መጋለጥ (ቢያንስ በየቀኑ ከ15-30 ደቂቃዎች)
🐟 ዓሳ
🥚 እንቁላል
🍼 የተጠናከረ ወተት እና እህሎች
⚠️ ብዙ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ለፀሀይ ውስን በመጋለጣቸው የቫይታሚን ዲ እጥረት አለባቸው፣ ስለዚህ ተጨማሪ ምግብ ሊያስፈልግ ይችላል።

2️⃣ የአጥንት መሳሳት ምርመራ (DEXA Scan) ያድርጉ
🩻 የDEXA ቅኝት የአጥንትን ጥንካሬ የሚለካ እና ኦስቲዮፖሮሲስን ቀደም ብሎ ለመለየት ይረዳል።

✅ ከ50 ዓመት በላይ ለሆኑ ሴቶች ወይም የአደጋ መንስኤዎች ላላቸው (የቤተሰብ ታሪክ፣ ማረጥ፣ የቀድሞ ስብራት) ይመከራል።

✅ ኦስቲዮፖሮሲስ ከተገኘ ሐኪምዎ የአኗኗር ዘይቤ ለውጦችን፣ ተጨማሪ ምግቦችን ወይም መድሃኒቶችን የአጥንት መጥፋትን ለመቀነስ ሊመክር ይችላል።

3️⃣ ለጠንካራ አጥንቶች አዘውትረው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርጉ

💪 ክብደት የሚሸከሙ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች የአጥንትን ጥንካሬ ለማሻሻል እና የስብራት አደጋን ለመቀነስ ይረዳሉ።

🏃‍♀️ መራመድ፣ መሮጥ– የአጥንት ጥንካሬን ለመገንባት በጣም ጥሩ ናቸው።
🏋️‍♀️ የጥንካሬ ስልጠና – ቀላል ክብደት ማንሳት ጡንቻዎችን እና አጥንቶችን ያጠናክራል።

4️⃣ ጎጂ ልማዶችን ያስወግዱ
❌ አልኮልን ይገድቡ – ከመጠን በላይ መጠጣት አጥንትን ያዳክማል።
❌ ጨው እና ለስላሳ መጠጦችን ይቀንሱ – ከፍተኛ ጨው እና ካርቦናዊ መጠጦች የካልሲየም መምጠጥን ይረብሻሉ።

5️⃣ መድሃኒት መቼ እንደሚጀመር ይወቁ
ኦስቲዮፖሮሲስ እንዳለብዎ ከተረጋገጠ ሐኪምዎ የሚከተሉትን ሊመክር ይችላል፡
💊 ቢስፎስፎኔትስ – የአጥንት መጥፋትን ይቀንሳል እና አጥንትን ያጠናክራል።
💊 የሆርሞን ህክምና (HRT) – ከማረጥ በኋላ የአጥንትን ጥንካሬ ለመጠበቅ ይረዳል።
💊 ካልሲቶኒን፣ ዴኖሱማብ ወይም ቴሪፓራታይድ – ከፍተኛ ተጋላጭነት ላላቸው ታካሚዎች የላቁ ህክምናዎች።

🚨 ዛሬ እርምጃ ይውሰዱ!
✅ ከ50 ዓመት በላይ ከሆኑ ወይም ለአደጋ የተጋለጡ ከሆኑ የአጥንት ጤና ምርመራ ያድርጉ
✅ አስፈላጊ ከሆነ የካልሲየም እና የቫይታሚን ዲ ተጨማሪ ምግቦችን ይጀምሩ
✅ አጥንትዎን ጠንካራ ለማድረግ አዘውትረው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያድርጉ
✅ ቤተሰብዎን እና ጓደኞችዎን የአጥንት ጤናን ቅድሚያ እንዲሰጡ ያበረታቱ!


💪 ጠንካራ ሴቶች = ጠንካራ አጥንቶች = ጠንካራ ህይወት



https://t.me/ethiodoc


ጥፍርዎ ስለጤናዎ ምን ይላል?
====================

✍️ ጥፍር የተለያየ ጥቅም አለው ፣ ዋነኛው እና የመጀመሪያው የእጅ እና የእግር ጣቶቻችንን ከአደጋ መጠበቅ መሆኑን ነው ።

✍️ የሰው ልጅ ውበቱን ከሚገልጽባቸው ነገሮች መካከል አንዱም ጥፍር ነው።

✍️ ከዚህ ባሻገር ደግሞ የአካላችንን ሙቀት በመቆጣጠር ላይም ድርሻ አለው።

✍️ ታዲያ ይህንን የተለያየ ጥቅም ያለውን የሰውነታችንን ክፍል ጤና ለመጠበቅ ብዙ ትኩረት ስንሰጥ አይታይም።

✍️ በጥፍር ላይ የሚታዩ ለውጦች የጤና ችግርን ሊያመለክቱ ይችላሉ። ከንዚህም ዉስጥ ጥቂቶቹ

❗ ጥፍር ላይ ቡናማ ቀጥ ያለ መስመር (Hutchinson's sign)

✍️ ጥፍር ላይ ቡናማ ቀጥ ያለ መስመር የሜላኖማ ምልክት ሊሆን እንደሚችል ይነገራል፤ ይህም በጣም ገዳይ የሆነው የቆዳ ካንሰር በአብዛኛው በሰውነት ቆዳ ላይ ቢታይም ምልክቱ ጥፍር ላይ ሊጀምር ይችላል::

✍️ይህ በጣም አሳሳቢ የሚሆነው የአንድ ጣት ጥፍር ከሌላው ነጥሎ የሚጠቁር ከሆነ ነው።

❗ የሚሰባበር ጥፍር( brittle nail )

✍️ የሚሰባበር፣ ሾጣጣና የማንኪያ ቅርጽ ያለው ጥፍር የደም ማነስ ወይም የንቀርት በሽታን ሊያመለክት ይችላል ፤ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት የጥፍር መሳሳት እንዲከሰት ያደርጋል ፤ ከፍተኛ ኬሚካሎችና ከአሴቶን-ነጻ የጥፍር ቀለም ማስለቀቅያ ብዙ ጊዜ ጥቅም ላይ ማዋል ጥፍር እንዲሰባበር ሊያደርግ ይችላል።

❗ሸንተረር

✍️ በጣት ጥፍሮች ላይ ቀጥ ያሉ መስመሮች ወይም ሸንተረር ሰዎች በዕድሜ እየገፉ ሲሄዱ የተለመዱ ናቸው::

✍️ የቢው መስመሮች (Beau's lines) በመባል የሚታወቁት ጥልቅ አግድም ሸንተረሮች ግን ለጤና አስጊ ናቸው ::

✍️የቢው መስመሮች (Beau's lines) የአጣዳፊ ኩላሊት በሽታ ምልክት ሊሆኑ ይችላሉ፤ ትኩሳት፣ ኬሞቴራፒ፣ ከባድ ሕመም፣ ከባድ ቀዶ ህክምና፣ ደም መቀበል፣ የመኪና አደጋ ወይም ማንኛውም በሰውነት ስርዓታችን ላይ የሚደርስ ከባድ ውጥረት ምክንያትም በጥፍር ላይ ሸንተረር ሊከሰት ይችላል::

❗ ቢጫ ጥፍር (yellow nail)

✍️ ወፍራም እና ቀስ ብሎ የሚያድጉ በጣም ቢጫ ጥፍሮች ከሳንባ ችግሮች ጋር ሊዛመዱ ይችላሉ::

✍️ ቢጫ ጥፍር ሲንድረም (Yellow nail syndrome) ጥፍርዎን የሚያጠቃ ያልተለመደ በሽታ ነው። ቢጫ ጥፍር ሲንድረም ያለባቸው ሰዎች የሳንባ እና የሊምፋቲክ (lymphatic) ስርዓት ችግር ሊሆን ይችላል።

✍️ በዚህም የጥፍርዎን ለውጦች በማስተዋል ወደህክምና ተቋም በመሄድ አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ ስለጤናዎ ማወቅ አስፈለገ ነው:

Reference
https://ijdvl.com/nails-in-systemic-disease/

Dr. Fantahun A, Dermatologist



_
https://t.me/ethiodoc


MEDNOTE ||| VACANCY dan repost
👆Vacancy @YeWoyinnat General Hospital👆
==========================

Positions:-

1. Position: BioMedical Technologist

Required No: 1


2. Position: Medical Radiography Technologist

Required No: 1



Deadline: መጋቢት 11-19/2017



__
https://t.me/MedNotev


የኩላሊት ጠጠር ህክምና
=================

ትንንሽ የኩላሊት ጠጠሮች በግርድፉ ከ7 ሚ.ሜ (0.7 ሣ.ሜ) በታች ከሆኑ በቂ ፈሳሽ በመውሰድና እንቅስቃሴ በማድረግ ያለ ህክምና እርዳታ በራሳቸው ሊወጡ ይችላሉ፡፡

የኩላሊት ጠጠር መጠኑ ትልቅ ከሆነ፣ ለተደጋጋሚ የኩላሊት ኢንፌክሽን መንስኤ ከሆነ፣ ከፍተኛ የኩላሊት ህመም ካስከተለ እና የሽንት መውረጃ ቱቦዎችን ከዘጋ የግድ የህክምና እርዳታን ይፈልጋል፡፡ ለዚህም በልዩ ልዩ አይነት ዘዴዎች አሉ፡፡

1. የሞገድ ህክምና (በተለምዶ የጨረር ህክምና የምንለው)
ይህ አይነት ህክምና በአገራችን የጨረር ህክምና እየተባለ ይጠራል፤ ነገር ግን ጠጠሮቹን ለማፍረስ ምንም አይነት ጨረር የማይጠቀም የህክምና አይነት ነው፡፡ ይልቁንም ከፍተኛ ሃይል እንዲኖረው የተደረገና ጠጠሮቹ ላይ ተሰብስቦ የሚገኝ ሞገድ ጠጠሮቹ እንዲሰባበሩ እና በሂደት በሽንት እንዲወጡ የሚደረግበት ዘዴ ነው፡፡ ከሌሎቹ የጠጠር ህክምና አይነቶች እጅግ ያነሰ ተጓዳኝ ችግሮች ያሉትና አልጋ መያዝም ሆነ ማንኛውንም አይነት ሰመመን (ማደንዘዣ) የማይጠቀም ዘዴ ነው፡፡
ከ2 ሣ.ሜ በላይ ለሆኑ፣ በጣም ጠንካራ ለሆኑ፣ እና በታችኛው የኩላሊት ክፍል ላሉ የጠጠር አይነቶች ተመራጭ የህክምና ዘዴ አይደለም፡፡

2. የተጣጣፊ ኢንዶሰኮፒ እና ሌዘር ህክምና (Flexible URS and Laser Lithotrypsy)
ይህኛው አይነት ዘዴም ጠጠሮቹን ለመስበር ምንም አይነት ጨረር የማይጠቀም ዘዴ ሲሆን ሌዘር (ከፍተኛ ኃይል እንዲኖረው የተደረገ ብርሃን) ጠጠሮቹን ለመሰባበር ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ ዩሮሎጂስቱ ከሽንት መውጫ ቱቦ ጀምሮ በተጣጣፊ ኢንዶስኮፒ ኩላሊት ውስጥ በመግባት የሌዘሩን ኃይል በመጠቀም ጠጠሮቹን ያደቃቸዋል፡፡ ጠጠሮቹም በሂደት በሽንት መልኩ ይወጣሉ፡፡
ይህኛው ሙሉ ወይንም ከወገብ በታች ማደንዘዣ የሚያስፈልገውና አልጋ መያዝ የሚፈልግ ዘዴ ነው፡፡ ከህክምናው በኋላ ታካሚው ወደ ተለምዶአዊው እንቅስቃሴው በጥቂት ቀናት ውስጥ መመለስ ይችላል፡፡

3. በጎን በኩል በትንሽ ቀዳዳ በኩል ጠጠር መሰባበር
ይኸኛው ዘዴም ኢንዶስኮፒን ይጠቀማል፡፡ የጣት ያህል ብቻ በሚሰፋ ቀዳዳ ኩላሊቱ ውስጥ በመግባት ጠጠሮቹ ጋር መድረስ እና ጠጠሮቹን መሰባበር የሚቻልበት ዘዴ ነው፡፡ ይኸኛውም ማደንዘዣ እና የሆስፒታል አልጋ መያዝ ይፈልጋል፡፡ ለትላለቅ እና ውስብስብ የጠጠር አይነቶች ተመራጭ ዘዴ ነው፡፡ ታካሚው በአጭር ግዜ ውስጥ ማገገምና ወደ ስራው መመለስ ይችላል፡፡

4. በቀዶ ህክምና ከፍቶ ማውጣት
በዚህ ዘመን ይህ አይነት የኩላሊት ጠጠር ህክምና ብዙግዜ ጥቅም ላይ አይውልም፡፡ እጅግ በጣም ትልቅ እና የተወሳሰበ ጠጠር ብቻ በዚህ መንገድ ይወጣል፡፡ ሌሎቹ መንገዶች አይሳኩም ተብሎ ከታሰበ ወይንም በሌሎቹ መንገዶች ጠጠሩን ማውጣት ካልተቻለ ወይንም ቴክኖሎጂው በሌሉባቸው አካባቢዎች ብቻ የምንጠቀመው ዘዴ ነው፡፡
 
ማስታወሻ፡ ከላይ የተዘረዘሩት በጥቂት ቦታዎች ብቻ ይሁን እንጂ ሁሉም አይነት የህክምና ዘዴዎች በአገራችን ይገኛሉ፡፡




https://t.me/ethiodoc


ነብሰ ጡር እናት ወይም አጥቢ እናት መጾም ትችላለች?
=====================================

እንደሚታወቀው አንዲት እናት በእርግዝናዋ ጊዜ ወይም ጡት በምታጠባበት ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ የተሻሉ እና በዛ ያሉ ምግቦችን መመገብ እና ፈሳሾችን ማብዛት ይጠበቅባታል። ከሌላው የእድሜ ክፍል በተለየ ሁኔታ የተመጣጠነ ምግብ የሰፈልጋታል።

ነፍሰ ጡር እናት ከሆነች ደሞ በተለየ ሁኔታ የመጀመሪያዎቹ 3 ወራት ላይ በተደጋጋሚ ማቅለሽለሽ እና ማስመለስ ስለሚያጋጥሟት በአንጻሩ ደግሞ በመጨረሻዎቹ ወራት ቶሎ የመጥገብ እና የምግብ ፍላጎት መቀነስ ስለሚከሰትባት በ24 ሰአት ዉስጥ ከ 5 ጊዜያት በላይ መመገብ ሊያስፈልጋት ይችላል።

ይህም በመሆኑ አንዲት ነብሰ ጡር ወይም አጥቢ እናት ለመጾም ከመነሳቷ በፊት ቀጥሎ ያሉትን ህክምናዊ ጉዳዮችን ማወቅና አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ መውሰድ እንደሚገባት ለማስታወስ እንወዳለን ፦

በመጀመሪያዎቹ 3 ወራት የእርግዝና ጊዜ የሚገጥሙ ማስመለስ እና ማቅለሽለሽ ካለ በጾም እንደሚባባስ ማወቅ ያስፈልጋል

አንዲት ነብሰ ጡር ወይም አጥቢ እናት የስኳር በሽታ ካለባት ለእርሱም መድሃኒት የምትወስድ ከሆነ ጾም ላይ መጠንቀቅ ይገባታል

የደም ማነስ ፣ ተቅማጥ ፣ ደም ግፊት አንዲሁም ሌሎች ከእርግዝና ጋር ወይም ከ ማጥባት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ተጨማሪ ህመሞች አለመኖራቸውን ማወቅ ይኖርባታል

በጾም ምታሳልፈው የቀኑ እርዝመት ከ 12 ሰአት እንዳይበልጥ ይመከራል

የአካባቢው የአየር ሁኔታ በጣም ሞቃታማ ከሆነ አለመጾሙ ይመከራል

ሱሁር መመገብ ፣ ጨው የበዛበትን መግብ መቀነስ ፣ በአንጻሩ ደሞ በተለይ ስሁር ላይ ፕሮቲን ፣ ፋይበር ነክ የሆኑ ጥሩ ምግቦችን መመገብና ፈሳሽ ነገሮችን በብዛት መውሰድ ይመከራል

ለመጾም ሲወስኑ ሃኪሞን ሳያማክሩ በአርግዝና ወቅት የሚሰጡ መድሀኒቶችን ማቁአረጥ እንደማይገባ ማወቅ ግድ ይላል

መንታ ወይም ከዚያም በላይ ጽንስ ካለ ከአምስት ወር በኀላ አለመጾሙ ይመከራል

አሁን ላይ የምጥ ሰሜቱ ካለም መጾም አይመከርም

ከላይ የተዘረዘሩትን ቅድም ጥንቃቄዎችን ያረገች እናት ረመዳኑአን በየትኛውም የእርግዝና እድሜ ላይ ብትጾም ፅንሱ ላይ ችግር እንደሌለው በርካታ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ከዘጠኝ ወር ጊዜ ውስጥ አንድ ወር መፆም ጉዳት እንደሚያስከትል የሚአትት የጥናት ውጤት እንደሌለም ይታወቃል ። ሆኖም ግን እርግዝና ላይ ያለች እናት ከሚያስፈልጋት ጉልበት አኳያ ፆሙን ጀምራ ካልቻለች ወይም የድካም ስሜት ከተሰማት ቀጥሎም ራስ ምታት ከተሰማት በጾሙ መቀጠል አይገባትም። የመፆም ፍላጎቷ ካየለ ግን አንድ ቀን እየፆመችና አንድ ቀን እያፈጠረች አቅሟን እንድታይ ትመከራለች።

ፆመኛ የሆነች ነብሰ ጡር ወይም አጥቢ እናት እንዳትወስዳቸው የምትመከራቸው የምግብ አይነቶች
ጨው የበዛበት ምግብ ፣ ቅባትና ጮማ፣ ስኳር የበዛበት ምግብ

እንደማንኛውም ጊዜ ከሱስ ሁሉ መጠንቀቅ

ፆመኛ የሆነች ነብሰ ጡር ወይም አጥቢ እናት (በተለይ ስሑር ላይ) እንድተወስድ ምትመከራቸው የምግብ አይነቶች
በፕሮቲን የበለጸጉ የምግብ አይነቶችን (ለምሳሌ ለውዝ ፣ ምስር፣ አተር ወይም የባቄላ ፉል

በፋይበር የበለጸጉ የምግብ አይነቶችን (ለምሳሌ ተምር)

ፍራፍሬዎችን (ለምሳሌ የማንጎ ፣ የአቮካዶ ፣ የፓፓዬ ፣ ወዘተ ጭማቂዎችን

ሆልግረይን ምግቦችን (ለምሳሌ የቂንጬ ሾርባ ፣ ውሃ በወተት)

በፆመ ላይ የሆነች ነብሰ ጡር ወይም አጥቢ እናት የሚከተሉትን ምልክቶች ካየች ሀኪሟን እንድታማክር ትጠየቃለች
- የምጥ ምልክት
- ረዘም ላለ ሰአት የልጅ እንቅስቃሴ መቀነስ
- ከፍተኛ የሆነ ራስ ምታት ማጋጠም
-ከፍተኛ የሆነ ድካም ፣ የውሃ ጥም ፣ ረሃብና ማዞር መከሰት
በጥቅሉ በጾሙ ምክንያት የሚመጣ ምልክቶችን መገምገም

በዶ/ር ሰይድ አራጌ: የማህጸንና ፅንስ ስፔሻሊስት ሀኪም ፣ ረዳት ፕሮፌሰር ፣ ማተርናል ፌታል ሜድስን ሰብ ስፔሻሊስት በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል MFM unit እና በረካ የእናቶችና ህጻናት ህክምና ማዕከል
አዲስ አበባ


https://t.me/ethiodoc


የረመዳን ፆምን የማያበላሹ የህክምና ተግባራት
==========================

1, የአይን ጠብታና የጆሮ ጠብታ መድሀኒቶች ፆምን አያበላሹም።

2, የአስም በሽተኞች የሚነፋ መድሃኒታቸውን (Salbutamol puff) እየፆሙ ቢወስዱ ችግር የለውም።

3, ጥርስን ማስነቀል ወይም ጥርስን ማስሞላት ፆምን አያጠፋም።

4, በምላስ ስር የሚደረጉ ኪኒኖች: የልብ በሽታን (MI) ለማከም ... ለሌሎችም በሽታዎች የሚረዱ መድሀኒቶች እስካልተዋጡ ድረስ ፆምን አያበላሹም።

5, ፆመኛ ሰው የደም ምርመራ ለማስደረግ ብሎ ደሙን ቢሰጥ ፆሙ አይፈርስም።

6, በደምስር (IV) ወይም IM የሚሰጡ ምግብን የማይተኩ መድሀኒቶች (ማስታገሻዎች ፣ ክትባቶች ፣ Antibiotics) እንዲሁም ሲቲስካን (CT Scan) ወይም MRI ለመነሳት በደምስር የሚሰጡ መድሀኒቶች (Intravenous contrast) ፆምን አያበላሹም።

7, በበሽታ ወይም በማንኛውም ምክንያት ሳያውቁ ማስታወክ ፆምን አያጠፋም።

8, ሂጃማ (ዋግምት) ፆምን ያበላሻል ወይስ አያበላሽም በሚሉት ሀሳቦች በዑለማዎች (በዲን አዋቂዎች) መካከል ብዙ ሀሳቦች የተሰጠበት ሲሆን ለመጠንቀቅ ያክል በፆም ሰዓታት ዋግምት ከመደረግ ብንቆጠብ የተሻለ ነው። የሂጃማ (የዋግምት) ድንጋጌ በዘመናዊ የህክምና መንገድ ለምንጠቀመው Phelbotomy ይውላል።

9, ነስር ያለበት ሰው በብዛት እንኳን ደም ቢፈሰው ፆሙ አይበላሽም። እየፆመ ያለ ሰው በአደጋ ወይም በሌላ ምክንያት በብዛት ደም ቢፈሰው ፆሙ ላይ ችግር አይኖረውም። ነገር ግን በዚህ ምክንያት ከታመመና ከደከመ ፆሙን አጥፍቶ መመገብ ይችላል።

10, በጤናዋ ላይ ችግር የማያስከትልባት ከሆነ አንዲት ሴት የወር አበባ የሚያስቆም መድሀኒት ተጠቅማ ረመዳንን ብትፆም ችግር የለውም። አንዲት ሴት የረመዳን ቀናት ፆሞችን ፣ ለይለቱል ቀድር ፣ በሀጅና ዑምራ ላይ ያሉ አንዳንድ ተግባራት የመሳሰሉትን ዒባዳዎች እንዳያመልጧት የወር አበባን የሚያስቆም መድሀኒት መጠቀምዋ ጤናዋ ላይ ችግር የማይስከትል ከሆነ ችግር አይኖረውም። ነገር ግን መድሀኒቶቹ የጎኒዮሽ ጉዳት ስላላቸውና ሴቷ ራሷን ተከሉፍ (ራሷን ማስገደድ) ውስጥ ባታስገባ የተሻለ ይሆናል። ኪኒን ተጠቅማ ግን ብትፆምና ዒባዳዎችን ብትተገብር ተቀባይነት አለው።

11, በሴት ማህፀን ወይም ብልት ውስጥ የሚከተቱ የህክምና መሳሪያዎች ፣ ምርመራዎች ፣ መድሀኒቶችና የእርግዝና መከላከያዎች ፆምን አያበላሹም።

[ እነዚህ የረመዳን ፆምን የሚመለከቱ የህክምና ብያኔዎች ቁርዓንና ሀዲስን ብሎም የአራቱ አዒማዎች መዝሀቦችን ተመርኩዘው በዘመናችን ዑለማዎች (የዲን ዓዋቂዎች) የተሰጡና የተጠናቀሩ ናቸው።]

ሼር ያድርጉት ያላወቁትን ያሳውቁ
ዶ/ር መቅሱድ ሸምሱ
#ረመዳን_የእዝነት_ወር #ረመዳን_ሙባረክ


https://t.me/ethiodoc


አፈንጋጭ ወሲባዊ ስሜቶች | Paraphillia
=============================

Para- Next to
Phillia- Love

በዚህም መሰረት Paraphilia ማለት 'ከተለመደው ያፈነገጠ የወሲብ ስሜት' የሚል አንድምታ ይኖረዋል::

Diagnostic and Statistical Manual በ አምስተኛው እትሙ ስምንት የ Paraphilia Disorder/አፈንጋጭ የወሲብ ስሜት አይነቶችን አካቷል::

እነዚህም:-

1- Exhibitionistic disorder:- ሃፍረተ ገላቸውን ለእንግዳ ሰዎች በአደባባይ ማሳየት የሚወሰውሳቸው

2- Pedophilic disorder- ለአቅመአዳም/ሄዋን ያልደረሱ(ማለትም ከ13 አመት በታች በሆኑ) ሰዎች ላይ የፍትወት ስሜት የሚያይልባቸው

3- Voyeuristic disorder:- ሌሎች ሰዎች እርቃናቸውን ሲሆኑ ወይንም ወሲብ ሲፈጽሙ በመመልከት የፍትወት ስሜታቸውን የሚፈጽሙ

4- Fetishistic Disorder:- ግዑዝ ነገሮችን(እንደ ውስጥ ልብስ፣ ጡት ማስያዣ...) በመጠቀም የፍትወት ስሜታቸውን የሚፈጽሙ

5- Transvestic disorder:- እንደ ሌላ ጾታ በመልበስ የፍትወት ስሜታቸውን የሚፈጽሙ

6- Sexual Sadism Disorder :- ሌሎችን በማሰቃየት የፍትወት ስሜታቸውን የሚፈጽሙ

7- Sexual Masochism disorder :- ሌሎች እንዲያሰቃዩዋቸው በማድረግ የፍትወት ፍላጎታቸውን የሚፈጽሙ

8- Frotteuristic Disorder- ሰዎችን ካለፈቃዳቸው በመታከክ የፍትወት ፍላጎታቸውን የሚፈጽሙ

በፊት ላይ Homosexuality እንደ አንድ Paraphiliac Disorder ይቆጠር ነበር:: ከ1973 ጀምሮ ግን ከአዕምሮ ህመሞች ዝርዝር እንዲወጣ ተደርጓል::

ይህን ሃሳብ የሚሞግቱ ብዙዎች አሉ:: በዚህ ፍላጎታቸው ምክንያት የተለያዩ ማህበራዊ እና ስነልቦናዊ ጫናዎች የሚያጋጥማቸው ሰዎች ካሉ እና ወደህክምና ከመጡ: ችግራቸው ቢያንስ 'Culture Bound Syndrome' በሚለው ስር ተካቶ መታየት ይኖርበታል በማለት::

***

አሻም አሻም!

ዶ/ር እስጢፋኖስ እንዳላማው- የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስት

***
https://t.me/ethiodoc

20 ta oxirgi post ko‘rsatilgan.

1 444

obunachilar
Kanal statistikasi