Forward from: ༒⋆ ·٠•●Åđmïŋ●•٠· ⋆ ༒
ቀጣይ የቀረበ............
★ የወይን ጠጅ ጠግበዋል ★
መጠጥ እንኳን አዲስ ቋንቋ ሊገልጽ የምናውቀውንም እንደሚያስጠፋ የታወቀ ነው፡፡ ሐዋርያት በአዲስ ቋንቋ ሲናገሩ ካዩ ሰዎች ግን አንዳንዶቹ ‹የወይን ጠጅ ጠግበዋል› አሉ፡፡ ሐዋርያት ስኲራነ መንፈስ (በመንፈስ የሰከሩ) እንጂ በመጠጥ የሰከሩ አልነበሩም፡፡ ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም እንዳብራራው በእርግጥም ሐዋርያቱ ‹የወይን ጠጅ ጠግበዋል› ይህ የወይን ጠጅ ግን አይሁድ ለመዘበት የተናገሩት ዓይነት ጠጅ አልነበረም፡፡ ይህ የወይን ጠጅ አዲሱ የወንጌል ሕግ፣ አዲሱ ኪዳን ፣ በመንፈስ ቅዱስ የተሠራው የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሁሉ ነው፡፡ ይህ የወይን ጠጅ ጌታ ‹‹ደቀ መዛሙርትህ ለምን አይጾሙም?›› ተብሎ በተጠየቀ ጊዜ ‹‹በአሮጌ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር ማን ነው?›› ብሎ የመለሰ ጊዜ የተናገረው ወይን ጠጅ ነው፡፡ (ማቴ. 9፡17) ዛሬ በመንፈስ ቅዱስ የታደሱት አቁማዳዎች ሐዋርያት አዲስ የወይን ጠጅ የተባለች ሕገ ወንጌልን የጠገቡበት ዕለት ነውና መምህራቸው ቃል በገባው መሠረት በማግሥቱ ጾም ይጀምራሉ፡፡ ‹‹አዲሱን የወይን ጠጅ በአዲስ አቁማዳ ያኖረዋል፤ ሁለቱም ይጠባበቃሉ›› ያለው ቃልም ይፈጸማል፡፡
★ አንድ ሺህ ካሣ ★
ዛሬ ቅዱስ ጴጥሮስ የአደባባይ ስብከት ያለ ፍርሃት ሰበከ፡፡ ሐሙስ ዕለት ማታ በጥቂቶች ፊት ፈርቶ ጌታን አላውቀውም ብሎ የካደው ጴጥሮስ መንፈስ ቅዱስ ኃይል ሠጥቶት በበዓለ ሃምሳ ዕለት በአደባባይ አስተማረ፡፡ በሰበከው የመጀመሪያ ስብከቱም ሦስት ሺህ ሰዎችን ወደ ክርስትና መለሰ፡፡ ‹‹ጴጥሮስ በአንድ ስብከት ሦስት ሺህ ሰዎችን መለሰ ፤ እኛ ግን በሦስት ሺህ ስብከት አንድ ሰው መመለስ አቃተን›› ብለዋል አቡነ ሺኖዳ፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ የንስሓ ፍሬ ምን እንደሆነ አሳየን፡፡ ሐሙስ ማታ አላውቀውም ብሎ የካደው ሦስት ጊዜ ነበር፡፡ በዛሬው ዕለት ጴጥሮስ አንድ ጊዜ ጌታን ‹አላውቀውም› ላለበት ብቻ አንድ ሺህ ‹‹ጌታን አውቄዋለሁ›› የሚሉ ሰዎችን እጅ መንሻ አድርጎ ሦስት ሺህ ነፍሳትን የአገልግሎቱ በኩራት አድርጎ አቀረበ፡፡ ‹‹ኃጢአተኛን ከክፉ መንገዱ የሚመልሰው የኃጢአቱን ብዛት እንዲሸፍን ይወቅ›› ተብሎ እንደተጻፈ ጴጥሮስ ሦስቴ የመካዱን ታሪክ በሦስት ሺህ አማኞች ሸፈነው፡፡ (ያዕ 5:20) ከተሠጡት ብዙ ቋንቋዎች በአንዱ ብቻ ሰብኮ ሦስት ሺህ ከመለሰ በቀሩት ቋንቋዎች ምን ሠርቶ እንደሆን ባለቤቱ ይቁጠረው፡፡ በዛሬዋ ዕለት ግን የቤተ ክርስቲያን ልደትዋ ሲከበር የገሊላው ጴጥሮስ ሦስት ሺህ ሻማዎችን አብርቶላታል፡፡
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
በዓለ ጰራቅሊጦስ 2011 ዓ.ም
ጎተንበርግ ስዊድን