Репост из: የሕይወት እምሻው ወጎች/ Hiwot Emishaw
"ቁርጥ"
========
ያኔ በፍቅር ብን ሲሉ እሱ ገና ለጋ ወጣት ሳለ፣ የአስራ አምስት አመት ታላቁ ነበረች፡፡
ለቁጥር የሚያዳግቱ ምሽቶችን እጆቻቸውን አቆላልፈው በጎዳና ላይ በመንሸራሸር አሳልፈዋል፡፡
ስንቱን ወሬ አፍ ለአፍ ገጥመው አውርተውታል፤ በስንቱ ነገር አውካክተዋል፡፡
ዓለም ከተፈጠረች አንስቶ ፍቅረኞች ያደረጉትን ሁሉ፣ የሚያደርጉት ነገር ሁሉ አድርገዋል፡፡
ስትስቅ መስመር እያወጣ እድሜዋን የሚያጋልጥ ብዙ ያየ ፊቷን ከእሱ የልጅነት ድምቡሽቡሽ ገጽታ ጋር እያስተያዩ አንገቶቻቸው እስኪጣመሙ ዞር ብለው ከሚገላምጡዋቸው እልፍ አይኖች፣
በሽሙጥ ከሚጣመሙ አፎች ፣
ለወሬ ከሰሉ ምላሶች መዋደዳቸውን ልትሸሽግ ከመድከሟ ውጪ ፍቅራቸው እንከን አልነበረውም፡፡
ፍቅር ከጀመሩ ሁለተኛ ዓመታቸውን ባከበሩ ማግስት ግን ቻው እንኳን ሳትለው በድንገት ከአይኑ ተሰወረች፡፡
እልም ብላ ጠፋች፡፡
ቆይቶ ቆይቶ አቻዬ ያለችውን ሰው እንዳገባች በወሬ ወሬ ሰማ፡፡
ባሏ የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ነው ሲሉም ሰምቷል፡፡
በሚወዱት መከዳትን የማያውቀው መንፈሱ ተሰብሮ፣ ሰባራ ልቡን ይዞ ለብዙ ጊዜ፣ በየሄደበት፣ ላገኘው ሰው ስሟን እያነሰ ረገማት፡፡
‹‹ ሴትን ያመነ…›› እያለ፡፡
---
ከአስራ ስድስት አመታት በኋላ፣ በአንዱ ተራ አመሻሽ ዓለም ሲኒማ ጋር፣ እሷ ከምትሄድበት ከተቃራኒው አቅጣጫ ቦርሳውን መስቀለኛ አንግቶ ጠደፍ ጠደፍ እያለ ሲመጣ ፊት ለፊት አየችው፡፡
‹‹ጌታ እየሱስ ድረስልኝ! …ብሩክ በሃይሉ…እውነት አንተ ነህ?›› ብላ ጮኸች፡፡
ስሙን ሲሰማ፣ድንገት ቆመ፡፡
ለአፍታ ፊቷን ቢመረምራትም ማንነቷ ጠፋበት፡፡
ክፉኛ አረጀችበት፡፡
በለጋነቱ እንደ ኳስ የተንደባለለበት ለግላጋ ገላዋ ገረጀፈበት፡፡
‹‹እንዴ! ወይንሸት…? በስመአብ! ከየት ተገኘሽ?”
ጠጋ ብላ ፊቷን ለመሳም ስትሰጠው በጉንጩ ፈንታ እጁን ሰጣት፡፡
ጨበጠችው፡፡
“አዲሳባ መጣሁ እኮ! ” አለችው አፈር ብላ.፡፡ “እዚህ ነው የምኖረው”
“ተይ እንጂ!” ፊቱ ላይ የትህትና ፈገግቶ ሰርቶ መለሰላት፤ ከዚያ ግን ወዲያው በአይኖቹ መሃከል በመኮሳተር የተፈጠረ ጉብታ እየታየ፡፡
“ወይ ብሩክ! ሁሌ አስብሃለሁ…የት ገብቶ ይሆን እያልኩ››
‹‹አይቲ ነው የምሰራው አሁን›› መለሰላት፡፡ ‹‹ክፍያ የሚባል ካምፓኒ ነው የምሰራው፡፡ ለገሃር አካባቢ››
‹‹ትዳርስ…?አገባህ?››
‹‹አዎ፡፡ ሁለት ልጆች አሉኝ››
‹‹ጎሽ…ጎበዝ››
በአዲስ መልክ ተምቦርቅቆ የተሰራውና ተቀራርበው የቆሙበት ጎዳና በሰዎች መሞላት ጀመረ፡፡
ከስራ ወደቤታቸው የሚሄዱ ሰዎች በግራም በቀኝም እያለፏቸው ይሄዳሉ፡፡
የጥቅምት ብርድ ምሽቱን ተገን አድርጎ አጥንት መሰርሰር ጀምሯል፡፡
‹‹አንቺስ…ባለቤትሽ ደህና ነው?›› ጠየቃት፡፡
‹‹ደህና ነው፡፡ ሶስት ልጆች አሉን›› መለሰችለት፡፡
‹‹እዚህ የከፈተው…ማለቴ የከፈትነው ትምህርት ቤት ነው የምሰራው አሁን…ምናልባት ታውቀው ይሆናል …ችልድረንስ ፓራዳይዝ?››
ትኩር ብሎ እያያት ነበር፡፡
‹‹እንዴ እሱማ በጣም ፌመስ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ክፍያውም ከባድ ነው ደግሞ…በጣም…እ…በጣም ተለወጥሽ…›› አላት፡፡
ተለወጥሽ ሲላት ሊላት የፈለገው አረጀሽ፣ ጨረጨስሽ ነው፡፡
እሷም ገብቷታል፡፡
እንዲህ ሲላት፣ አጠገቡ ቆማ፣ በሰው ጎርፍ መሃል ሆና ብቸኝነት ተሰማት፤ በጫጫታ እና ውክቢያ መሃከል አውቶቢስ ወይ አውሮፕላን ሳትሳፈር ወደ ድሮ ተመለሰች፡፡
ያን ጊዜ ፣ አዋሳ ሲገናኙም የስንት ታላቁ ነበረች፡፡
ግን በአንጻራዊ ሁኔታ ያኔ ወጣት ነበረች፡፡
ፊቷ ጥርት ሰውነቷ ጥብቅ ያለ ነበር፡፡
እሱ የአንደኛ አመት የዩኒቨርስቲው ተማሪ፣ እሷ ደግሞ ስንቱን ያየች የዩኒቨርስቲው አስተዳደር ክፍል ተቀጣሪ፡፡
አሁን ግን…ወጣትነቷና ውበቷ ተያይዘው፣ ላይመለሱ ጥለዋት ሄደዋል፡፡ ብሩክ ግን ወጣት ነው፡፡ አሁንም ወጣት፡፡
‹‹አያት አካባቢ ነው ቤታችን›› አለችው ባይጠይቃትም በመሃከላቸው የተሰነቀረው ዝምታ አስጨንቋት፡፡
‹‹እስቲ ና እና ጠይቀኝ…ጠይቀን…››
‹‹ደስ ይለኛል›› መለሰላት፡፡
‹‹አንቺና ባልሽ ደግሞ እኛ ቤት ትመጣላችሁ…የእኛም ቤት ሰሚት ነው…ቅርብ ለቅርብ ነን…ሉሲንም በዚያው ትተዋወቂያታለሽ››
ምሽቱ ደንገዝገዝና ቀዝቀዝ ሲል በመሃላቸው የነበረው ስሜትም ያንኑ መሰለ፡፡
‹‹ እኔም ደስ ይለኛል›› አለችው ታግላ፡፡
‹‹ልጆቼንም ታያቸዋለሽ፡፡እንዴት አሪፍ ልጆች መሰሉሽ!››
በድንገት የጎዳናው አዳዲስ የመንገድ መብራቶች ሁሉ በአንድነት ፏ ብለው በሩ፡፡
የአስራ ስድስት አመት የእድሜ ሰምበርን የተሸከመው ፊቷ ለብሩክ ፈራጅ አይኖች ይበልጥ ተመቻችቶ ሲሰጥ ተሰማት፡፡
ያበሩትን እጆች በሆዷ ረገመች፡፡
‹‹ይሄኔ ስንቱ ቤት እንጀራ መጋገሪያ መብራት የለም…ስንቱ ቤት ጨለማ ወርሶታል..ልጆች የቤት ስራ መስራት አልቻሉም እነሱ እዚህ እኔ ፊት ላይ ሚሊዮን ፓውዛ ያበራሉ…መብራት ሃይሎች…እርጉሞች…›› አለች አሁንም በሆዷ፡፡
‹‹በል ልሂድ›› አለች በድንገት፡፡
‹‹መኪና ደርቤ ነው ያቆምኩት፡፡ ይሄኔ ልጁ እየተበሳጨብኝ ነው….ስልክ እንኳን አልሰጠሁትም ፤ ቶሎ እመጣለሁ ብዬ››
‹‹እሺ በይ ቻው›› የቅድሙን እጁን ዘረጋላት፡፡
‹‹ታዲያ መቼ…›› ብላ ከመጀመሯ ግን እጇን ጥሎ ጉዞ ጀመረ፡፡
ቅድም ቦግ ያሉት መብራቶች አንዴ ብልጭ አንዴ ፍዝዝ ማለት ጀመሩ፡፡
ቃላት ለማውጣት አፏን ከፈተች ግን እምቢ አላት፡፡
‹‹ቻ…ው›› አለች ቆይታ፡፡ ጮክ ብላ፡፡
ብሩክ አልዞረም፡፡ መንገዱን አቋርጦ ወደ ሚሊኒየም አዳራሽ የሚወስደውን ጎዳና ይዞ በፍጥነት መራመድ ጀመረ፡፡
የተሻገረውን ሁለት መንገዶች ብዙ መኪኖች፣ እሷ ቆማ የቀረችበትን የእግረኛ ጎዳና ደግሞ ብዙ አላፊና አግዳሚ ከዚህም ከዚያም ሲሞላው በመሃላቸው ያለው ርቀት ሰፋ፡፡
ብሩክ ከአይኗ ተሰወረ፡፡
ያን ጊዜ ‹‹እንገናኛለን›› ተባባሉ እንጂ አድራሻ እንዳልተለዋወጡ፣ ስልኳን እንዳልሰጠችው አስታወሰች፡፡
ከዚያ ደግሞ የበኩር ልጇ፣
አስራ አምስት አመት የሞላው ጎረምሳ ልጇ፣ ቁርጥ እሱን እንደሚመስል ለብሩክ እንዳልነገረችው አስታወሰች፡፡