ከ“ወሃብዮች” በፊት የነበሩ የመውሊድ ተቃዋሚዎች
~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~~
በዚህ ነጥብ ላይ ማተኮር የፈለግኩበት ምክንያት መውሊድን መቃወም የጀመሩት ከ200 አመታት ወዲህ የመጡ የነቢዩ ﷺ ጠላቶች ናቸው የሚል አሕባሽ ስላየሁ ነው። ከከሃዲያን ዘንድ ተለጥፎ ሙስሊሞችን ሲያንገላታ የነበረው ቡድን ምንም ቢል አይደንቅም። ከመሆኑም ጋር ጉዳዩን በውል የማያውቁ አንዳንድ የዋሃን እንዲረዱት ያክል ከ200 አመታት በፊት መውሊድን የኮነኑ ዑለማዎችን እጠቅሳለሁ።
1. ኢብኑ ተይሚያህ (728 ሂ.)፡- የሳቸውን አቋም እራሱን ችሎ ስለዳሰስኩኝ በዚህ ሊንክ ከፍተው ማየት ይችላሉ።
https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=3380210602050387&id=1000018444239382. ታጁዱን ዑመር ኢብኑ ዐሊይ አልፋኪሃኒ (734 ሂ.)፡-
ሌላኛው መውሊድ ላይ ብርቱ ትችት የሰነዘሩት ፋኪሃኒ ናቸው፣ በዚህ ላይ አንድ ኪታብ ፅፈዋል። እንዲህ ይላሉ፡- “ለዚህ መውሊድ በቁርኣንም በሱናም መሰረት አላውቅለትም። በዲን ላይ ተምሳሌት የሆኑትና የቀደምቶችን ትውፊቶች አጥብቀው የያዙ ከሆኑት የሙስሊሙ ህዝብ ምሁራኖች ከአንዳቸውም ተግባሩ አልተወሰደም። ይልቁንም ቦዘኔዎች የፈጠሩት ቢድዐ ነው!! ሆዳሞች ያተረፉበት የሆነ የነፍስ ዝንባሌ ነው!! … ይሄ (መውሊድ) ግን ሸሪዐው አልፈቀደበትም። ሶሐቦችም አልሰሩትም። ታቢዒዮችም እንዲሁ። እስካወቅኩት ድረስ ዲን የተላበሱ ዑለማዎችም አልሰሩትም። ይህ ነው ከሱ ከተጠየቅኩ ከአላህ ፊት የምመልሰው። የተፈቀደም ሊሆን አይችልም። ምክንያቱም በዲን ውስጥ ፈጠራ መፍጠር በሙስሊሞች ኢጅማዕ የተፈቀደ አይደለምና።
ስለዚህ የተጠላ ወይም የተከለከለ ከመሆን ውጭ የቀረ የለም!! የዚህን ጊዜ ወሬያችን ሁለት ክፍሎች ይኖሩታል ማለት ነው፣ ሁለት የተለያዩ ሁኔታዎች ጋር:-
አንዱ፡- አንድ ሰው ከራሱ ገንዘብ ለባለቤቱ፣ ለጓደኞቹና ለቤተሰቡ የሚያዘጋጀው ነው። በዚህም ጉባዔ ላይ ምግብን ከመብላት ሊያልፍና ወንጀሎችን የማይፈፅሙ ከሆነ ነው። ይህንን ነው የተጠላ ቢድዐና አስቀያሚ ነገር እንደሆነ የገለፅነው። ምክንያቱም የዘመናት መብራት፣ የሃገራት ውበት የሆኑት ምሁራኖችና የኢስላም ሊቃውንት የሆኑት ቀደምት የአላህ ታዛዦች አልሰሩትምና።
ሁለተኛ፡- ወንጀል የሚቀላቀለውና (ይህን ቢድዐ ለማክበር ገንዘብ ለመሰብሰብ) ትኩረት የሚበረታበት ነው። አንዳንድ ነፍሱ የተንጠለጠለ ሆኖ፣ ከግፉ ህመም የተነሳ ልቡ እያሳመመው የሆነን ነገር እስከሚሰጥ የሚደርስበት ነው። ዑለማዎችን አላህ ይማራቸውና ‘እፍረት አስይዞ ገንዘብን መውሰድ በሰይፍ እንደመውሰድ ነው’ ይላሉ።
በተለይ ደግሞ በዚህ ላይ ከጠገቡ ሆዶች ጋር እንደ ድቤና ዋሽንት ያሉ በከንቱ መሳሪያዎች የታጀበ ዘፈን ካለ፣ እንዲሁም ወንዶች ከወጣቶችና ከዘፋኝ ሴቶች ጋር መቀላቀል ከኖረ ወይ ከወንዶቹ ጋር ተቀላቅለው ወይ ደግሞ ከከፍታ ላይ ዘልቀው፣ እየተጣጠፉ በመጨፈር፣ ከዛዛታ ውስጥ መስመጥና አስፈሪውን (የቂያማ) ቀን መዘንጋት የሚደረስበት ነው።
ልክ እንዲሁ ሴቶች ብቻቸውን ሲሰባሰቡ ያለምንም ሀፍረት ድምፃቸውን በዘፈንና በነሺዳ ከፍ ያደርጋሉ። ከተለመደው የቁርኣን አቀራርና ዚክር አልፈው ከሸሪዐው ይወጣሉ። የላቀው ጌታ {ጌታህ በመጠባበቂያ ላይ ነውና} ማለቱን ይዘነጋሉ። ይሄ ክልክል በመሆኑ ላይ ሁለት ሰዎች አይወዛገቡበትም። ስርኣት ያላቸው አስተዋዮች በጥሩ አያዩትም። ይሄ የሚፈቀደው የሞቱ ቀልቦችን ከያዘና ወንጀልንና ሃጢኣትን ከሚያበዙ ሰዎች ዘንድ ነው። እንዲያውም ልጨምርህና እነሱ እንደ ዒባዳዎች እንጂ እንደ መጥፎና ክልክል ነገሮች አይደለም የሚቆጥሩት። ኢና ሊላሂ ወኢና ኢለይሂ ራጂዑን!! ‘ኢስላም እንግዳ ሆኖ ነው የጀመረው። እንግዳ ሆኖም ይመለሳል።’ ሸይኻችን (ኢብኑ ደቂቀል ዒድ) አልቁሸይሪ ረሑመሁላህ እንዲህ ማለቱ ምንኛ እውነት ነው?!
‘በከባዱ ዘመናችን ሚዛን በተዘነጋበት
እኩይ ምግባር ተወዶ በጎው በክፉ ታየበት
ምሁራኑ ተዋርደው መሀይም ወጣ ከመድረክ
ሐቅም ካለው እርባና ቢስ ከቀደሙት ጋር ሲተረክ
ለደጋጎች እላለሁ ፈተናው ቢከፋም አትዘኑ
ተራችሁ ቢደርስ ነው ባይተዋርነት ሲነግስ በዘመኑ።’
አልኢማም አቡ ዐምር ብኑል ዐላእ ረሑመሁላሁ ተዓላ ‘በሚያስደንቅ ነገር መደነቅ እስካለ ድረስ ሰዎች ከመልካም ነገር አይወገዱም’ ሲል በርግጥም ጥሩ ብሏል። ይህ እንግዲህ ነብዩ ﷺ የተወለዱበት ረቢዐል አወል ወር የሞቱበትም ከመሆኑ ጋር ነው። መደሰቱ በሱ ውስጥ ከማዘን ቅድሚያ የሚሰጠው አልነበረም።” [አልመውሪድ ፊ ዐመሊል መውሊድ፡ 2-8]
3. ኢብኑል ቀዪም (751 ሂ.)፡-
ሌላኛው መውሊድን የሚነቅፍ መልእክት ያስተላለፉት ታላቁ ዓሊም ኢብኑል ቀዪም ናቸው። እንዲህ ይላሉ፡- “ኢስራእ ነብዩ ﷺ ከታደሏቸው ታላላቅ ትሩፋቶች ከመሆኑም ጋር ያንን ጊዜ ወይም ያንን ቦታ በሸሪዐዊ ዒባዳ መለየት አልተደነገገም። እንዲያውም ወሕይ መውረድ የጀመረበት የሒራእ ዋሻ ከነብይነታቸው በፊት ያተኩሩበት የነበረ ከመሆኑ ጋር ከነብይነት በኋላ እራሳቸውም መካ ላይ በቆዩ ጊዜ፣ እንዲሁም ከሶሐቦች አንድም ያሰበው የለም። ወሕይ የወረደበት ቀንም እንዲሁ በዒባዳም ይሁን በሌላ ተለይቶ አልተያዘም። ወሕዩ የተጀመረበት ቦታም ይሁን ዘመኑ እንዲሁ በምንም ነገር ተለይቶ አልተያዘም። የሆኑ ቦታዎችን ወይም ጊዜዎችን ከራሱ በዒባዳዎች ለዚህና መሰል አላማ የለየ ሰው የመፅሐፉ ሰዎች አምሳያ ሆኗል። እነዚያ የመሲሕን (የዒሳን) ሁኔታዎች፣ ጊዜዎችና መሰባሰቢያዎች በዓላት አድርገው እንደያዙት። ለምሳሌ የልደት ቀኑን፣ የጥምቀት ቀኑንና መሰል ሁኔታዎቹን ለይተው እንደያዙት። ዑመር ኢብኑል ኸጧብ ረዱየላሁ ዐንሁ የሆኑ ሰዎችን ወደ አንድ ቦታ ለሶላት ሲቻኮሉ ያዩዋቸዋል። ‘ምንድነው ይሄ?’ ሲሉ ጊዜ ‘የአላህ መልእክተኛ ﷺ የሰገዱበት ቦታ ነው’ አሉ። ‘የነብዮቻችሁን ፋናዎች መስገጃዎች አድርጋችሁ ልትይዟቸው ትፈልጋላችሁን? ከናንተ በፊት የነበሩት ሰዎች የጠፉት በዚህ ነው። እዚያ እያልለ ሶላት የደረሰበት እዚያው ይስገድ። ያለበለዚያ ግን ጉዞውን ይቀጥል’ አሉ።” [ዛዱል መዓድ፡ 1/59]
4. አቡል ዐባስ አሕመድ ኢብኑል ቃሲም አልቁባብ (778 ሂ.)፡-
በመውሊድ ቀን ልጆችን ሰብስቦ ሻማ ስለመለኮስ፣ በነብዩ ﷺ ላይ ሶለዋት ስለማለት፣ ድምፁ ያማረውን ከውስጣቸው በመምረጥ አስር የቁርኣን ሱራዎችን እንዲያነብ ስለማድረግና ነብዩን ﷺ የሚያወድሱ ግጥሞችን ስለመነሸድ፣ በዚህ ሰበብም ወንዶችና ሴቶች መሰባሰባቸውን እንዲሁም አስተማሪው ሻማዎችን መቀበል የሚፈቀድለት ስለመሆኑ ሲጠየቁ እንዲህ ሲሉ ነበር የመለሱት፡-
“የገለፅካቸው በሙሉ ቢድዐ የሆኑ መጤ ፈሊጦች ናቸው። ስለሆነም የግድ ሊቋረጡ ይገባል። እነዚህን ነገሮች የሚፈፅም ወይም በነዚህ ላይ የሚያግዝ ወይም እንዲቀጥሉ የሚተጋ ሰው በቢድዐና በጥመት ላይ ነው እየተጋ ያለው። እሱ ግን በድንቁርናው ሳቢያ በዚህ ተግባሩ የአላህ መልእክተኛን - ﷺ - የሚያከብርና መውሊዳቸውን የሚያከብር እንደሆነ ያስባል። እሱ ግን ሱናቸውን እየጣሰና ክልከላቸውን እየፈፀመ ነው። ይህንን በይፋ እየፈፀመ ዲን ያልሆነን እንግዳ ነገር እየፈጠረ ነው። እውነተኛ የሆነን ማክበር ቢያከብራቸው ኖሮ ትእዛዛቸውን ባከበረና በዲናቸው ውስጥ እንግዳ ነገር ባልፈጠረ ነበር። እንዲሁም አላህ {እነዚያም ትእዛዙን የሚጥሱ መከራ እንዳይደርስባቸው ወይም አሳማሚ ቅጣት እንዳያገኛቸው ይጠንቀቁ} ሲል ካስጠነቀቀው ጋር ባልተላተመ ነበር።