"ልጄ እኔ በዘመናት እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ፀሎት በአንድም በሌላም መንገድ ሲመልስ አይቻለሁ:: ያንቺ ግን ይለያል! (መገረማቸው ይሰማል) የዛሬ ሁለት ወር ገደማ የገብርኤል እለት ማግስት እዝህችው ቦታ እንደዝህችው ተቀምጠሽ 'ያለፈውን ሁሉ በላጲስ ማጥፋት ቢቻል እና እንደአዲስ ሀ ብዬ መኖር ብችል?' ነበር ያልሽኝ! 'በቃሉ: በንስሓ: በጌታችን ደም እንደአዲስ ስርየትን አጊንተሽ መኖር ትችያለሽኮ!' ብልሽ .... 'አይ አባ መች እንዲህ ቀሎ!' ነበር ያልሽኝ:: ልጄ የተመኘሽውን አዲስ ህይወትኮ ነው እግዚአብሔር የሰጠሽ!! " አሉኝ ትከሻዬን ዳበስ ዳበስ እያደረጉ.... እዚህችው መኖር አይቻልም?? ቤት አልፈልግም... ፀሃይም ዝናብም... ክረምትም በጋም ለምን እዝህችው እግራቸው ስር ሆኜ አያልፍም?
የጠየቅኩትን አዲስ ህይወት እንድፅፍ ጭንቅላቴን ነጭ ወረቀት አድርጎ እንደሰጠኝ ቢነግሩኝም ስለራሴ የነገርኳቸው ነገር ካለ እንዲነግሩኝ ጠየቅኳቸው::
"መጀመሪያ ያገኘሁሽ ቀን ... እርግጠኛ ቀኑን አላስታውሰውም... ሰባት ስምንት ወር ቢሆን ነው... እዝህችው ጋር ቆመሽ በአምላክሽ ተቀይመሽ ጮክ ብለሽ እየተጣላሽው ነበር:: እያለፍኩ ገርመም ሳደርግሽ 'ምን ያፈጣሉ? በእግዚአብሄር የተናደደ ሰው አይተው አያውቁም? ' ብለሽኝ ነው ያስቆምሽኝ.... የዛን እለት ለብዙ ዓመታት ፈልገሽ አስፈልገሽ ያገኘሻት እናትሽ ስታገኛት በማይድን በሽታ ልትሞት ወራት እንደቀራት የሰማሽ ቀን ነበር:: ... ዝርዝሩን አልጠየቅኩሽም... ሲጠይቁሽም አትወጂም.... ከዛን ቀን በሗላ ቢያንስ በሳምንት አልያም በሁለት ሳምንት አርብ አርብ ትመጫለሽ... ያሳለፍሽው ህይወት በዝርዝር ባትነግሪኝም ከባድ እንደሆነ ግልፅ ነው:: .... መጥተሽ እዚህጋ ትቀመጫለሽ... አንዳንዴ ታዋሪኛለሽ ሌላ ጊዜ በዝምታ ቆይተሽ ትሄጃለሽ.... "
"እናቴ ምን ሆነች ከዛ? የት እንደሆነች ነግሬዎታለሁ?"
"አልነገርሽኝም ልጄ! እናትሽ እኔ እስካገኘሁሽ ድረስ በህይወት ነበሩ:: ወንድም እንዳለሽ ነግረሽኛል:: ስለእናትሽ ለወንድምሽ መንገር ተጨንቀሽ ነበር:: አዝናለሁ ልጄ ከዚህ በላይ የማውቀው የለም!" አሉኝ አሁንም ትከሻዬን ዳበስ ዳበስ እያደረጉኝ..... እናት? የት ናት? ወንድም?? ታዲያ ለምንድነው ብቻዬን የምኖረው? ለምንድነው ጎንጤም ተናኜም ፖሊሶቹም የማያውቋቸው?? እነርሱስ ቢሆን እንዴት ሊፈልጉኝ አልመጡም? ....
...........ይቀጥላል.......
@kederasiyan