የቢሻራው በር✍


Channel's geo and language: not specified, not specified
Category: not specified


በፍቅር ቀለማት ወደ ፍቅር ሐድራ!

Related channels  |  Similar channels

Channel's geo and language
not specified, not specified
Category
not specified
Statistics
Posts filter


ከመውሊድ ትሩፋቶች


1) የዕዉቀትና የዳዕዋ ፋይዳ፡-
✔✔✔✔✔✔✔✔✔

መዉሊድ በኛ አገር ትርጉምና ትግበራ (Semantic meaning) የግድ ዓመት ጠብቆ በረቢዑል አወል የሚደረግ ስብስብ አይደለም፡፡ በየትኛዉም ወቅት አርዶና ደግሶ ድሆችን መመገብ፣ መሻኢኾችን ወይም ዘመድ ወዳጅ ጠርቶ ዱዐ ማስደረግ፣ ደረሶችን መጋበዝ መዉሊድ ይባላል፡፡ ይህ የመዉሊድ ወይም የሶደቃ ሥርዓት ከተለያዩ ቤቶች እየተደረገ ዓመቱን በሙሉ የሚቀጥል በመሆኑ ለሀገራችን የዕዉቀት ቅብብሎሽ የላቀ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በሀገራችን ለዑለሞች ደመወዝ እየከፈለ፣ ለተማሪዎች ቀለብ እየሰፈረ የዕዉቀት ሂደቱን የሚመራ ተቋም ስላልነበረን የመዉሊድ ሥርዓት ለመሻኢኾች ቀለብ፣ ለደረሶች ደግሞ ማህበራዊ ስኮላርሺፕ በመሆን አገልግሏል፡፡ዓሊሞቻችን ከጠዋት እስከማታ ከዒልም ላይ ብቻ በማተኮር እንዲሠሩና የሀገራችን የዲን ዕዉቀት አስደናቂ ስፋትና ጥልቀት እንዲኖረዉ መዉሊድ ትልቅ ድርሻ አበርክቷል፡፡ የመዉሊድ ማዕዶች ማህበረሰቡ የምክርና የዳዕዋ አገልግሎት የሚያገኝባቸዉ መድረኮችም ነበሩ፡፡ ባጭሩ መዉሊድ ለመሻኢኾችና ለደረሶቻቸዉ የህልዉና ሰበብ (means of survival)፣ ለማህበረሰቡ ደግሞ የዲን ዕዉቀትና ተግሳጽ ማግኛ በመሆን የእስልምና ዕዉቀት ቅብብሎሽ ከትዉልድ ትዉልድ እንዲቀጥል አስችሏል፡፡
መዉሊድ ደረሶችን የመመልመያ መድረክም ነበር፡፡ ብዙ ልጆች ለዒልም ልባቸዉ የሚሸፍተዉ ከመዉሊድ መድረኮች ላይ ነበር፡፡ ቃለመጠይቅ ካደረግኩላቸዉ ዐሊሞች መካከል አንዱ የሆኑት ሸኽ ሲራጅ ማህሙድ፡- ‹‹ልቤ ለቂራአት የተነሳሳዉ ከመዉሊድ ላይ የደረሶችን ሥርዓት ሳይና የመንዙማዉ መሳጭነት ነበር›› የሚል ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡


ፈረሱ በናፍቆት ስካር ውስጥ በርካታ አመታትን አሳልፏል።

ከተኸለቀበት ቀን ጀምሮ ደማቁን የድግስ ምሽት በመናፈቅ፣የድግሱን ሙሽራ አዝሎ ለመጋለብ ልቡ ተሰቅሎ ለዓመታት በጉጉት ጠብቋል።የዚያ ሙሽራ ናፍቆት በሰላም የሚያስቀምጥም አልነበረም።ጀሰዱን በጀርባው ላይ አኑሮ የሚጋልብበት ቀጠሮ…ያን ሚስክ ገላ ጠረኑን የሚምግበትን የድግስ ሌሊት…ደስታና ሚርቃኑን ሲያብሰለሰል ጅስሙ አይከሱ ክሳት ቢከሳ ማን ሊፈርድበት?የሙሽራው ናፍቆት ከዚያም በላይ ያረጋልና።

የዚያ የ ከውኑ ሙሽራ ናፍቆትስ ከናፍቆትም ይብሳል።በመሸ ቁጥር ዛሬ በሆነ ቀኑ ሲል በምኞት ዳክሯል።ተርቧል የዚያ ንጉስ ገላን ማዘል፣ጀርባው ላይ ተቀምጦ "በል ሃያ ሙሽራህን ይዘህ ብረር"የሚባልበትን ቀን እንደ ውሃ ጥም ተጠምቶት እልፍ የናፍቆት ሌትና መዓልትን ኖረ…ናፍቆት ረኃብ…ናፍቆት…ጥማት…ናፍቆት ናፍቆት።


የዓለሙ ንጉስ ክቡር ገላውን መደብ ላይ አሳርፎ ጭልጥ ብሎ ተኝቷል።ሰይድ ጀብራኢል ደርሶ እግሩን ነካ ቢያረገው ነቃ፣ዙሪያ ግድሙን ቢያጤን ማንም የለም።ክስተቱ ሁለት ሶስት ጊዜ ተደጋገመ።ለሶስተኛ ጊዜ ሲሆን ግን ንጉሱ ብንን ብሎ ባለሟሉን ጅብሪል አገኘው። ይዞለት የመጣውንም ብስራቱን ነገረው…(አንተዬ በል ተነስ ጌታህ ከመናፈቅም በላይ ናፍቆሐልና በአርሹ ቀበሌ ለማንም ተደግሶ ማያውቅ ወደፊትም የማይደገስ የሆነ ድግስ ተዘጋጅቶ ይጠብቅሃል)ተባለ።በደስታ በፍቅር ብድግ ብሎ ካጃቢው ጂብሪል ጋር ወደ ደጅ ወጡ።

ደጁ ላይ የቆመ የተለየ ፍጥረት አለ።ፈረስም አይሉት መላዕክት ይመስል ክንፍ ያለው ነው…መላዕክት አይሉት ዛቱ ፈረስን የመሰለ የሆነ እንዲ ነው ብለው ማይወስፉት ኸልቅ ንጉሱን ይጠብቃል። "በል ሃያ ይሄን አፍቃሪህን እየጋለብክ ወደ ድግስ እንሂድ"አለው ሰይድ ጂብራዒል።

መርሃባ ብሎ ንጉሱም ያን ምስኪን ናፋቂ፣ፍቅሩ አብሰልስሎ ያከሳው፣ዘመናት የዚህን ቀጠሮ ቀን በመቁጠር እየባዘነ የኖረውን አሽክሩ ጀርባ ላይ ተቀመጠ…ሸውቀኛው ቡራቅ ስካሩ እንደምን አርጎት ይሆን??
………………………
(አሏሁመሰሊ ወሰሊም ዓላ ሰይዲና ወመውላና ሙሐመድ)

@zahid iqbal …2014


ሙሳ ዐሰ ተውራትን ሙሉ በሙሉ ካነበበ በኋላ አላህን እንዲህ ሲል ጠየቀው፡-‹‹ ያ አላህ በዚህ መጽሃፍ ውሰጥ ህዝቦች ይታዩኛል፤ በመጨረሻ የሚመጡ ሲሆኑ ግና ከሁሉም ህዝቦች ቀዳሚዎች ናቸው፡፡ እባክህ የኔ ህዝቦች አድርጋቸው፡፡››

አላህም አለ፡-‹‹እነሱማ የአህመድ ኡመቶች ናቸው››

ሙሳም ጠየቀ፡-‹‹ያ አላህ በዚህ መጽሀፍ ውስጥ ህዝቦች ይታዩኛል፤ ህግጋቶቻቸውን በልቦቻቻው ሸምድደው ያነበንቡታል፡፡ እባክህ የኔ ህዝብ አድርጋቸው፡፡››

አላህም አለ፡-‹‹እነሱማ የአህመድ ኡመቶች ናቸው››

ሙሳም ጠየቀ፡-‹‹ ያ አላህ በዚህ መጽሀፍ ውሰጥ ህዝቦች ይታዩኛል ፤ ምርኮን ፈቅደህላቸዋል፡፡ እባክህ ህዝቦቼ አድርጋቸው፡፡››

አላህም አለ፡-‹‹እነሱማ የአህመድ ኡመቶች ናቸው››

ሙሳም ጠየቀ፡-‹‹ያ አላህ በዚህ መጽሀፍ ውስጥ ህዝቦች ይታዩኛል፤ ምጽዋትን ይለጋገሳሉ በሱም ትመነዳቸዋለህ፡፡ እባክህ ህዝቦቼ አድረጋቸው፡፡››

አላህም አለ፡-‹‹እነሱማ የአህመድ ኡመቶች ናቸው››

ሙሳም ጠየቀ፡-‹‹ ያ አላህ በዚህ መጽሃፍ ውስጥ ህዝቦች ይታዩኛል፤ ጽድቅን ለመስራት አስበው ባይሳካለቸው አንድ ምንዳ ትመዘግብላቸዋለህ፡፡ ከተሳካላቸውም በ10 ታባዛላቸዋለህ፡፡ እባክህ ህዝቦቼ አድርጋቸው፡፡››

አላህም አለ፡-‹‹እነሱማ የአህመድ ኡመቶች ናቸው››

ሙሳም ጠየቀ፡- ‹‹ያ አላህ በዚህ መጽሃፍ ውስጥ ህዝቦች ይታዩኛል ፤ ለማመጽ ሲያስቡ ምንም አትመዘግብባቸውም፡፡ ግና ሲያምጹ አንዲትን ብቻ ትመዘግብባቸዋለህ፤ እባክህ የኔ ህዝብ አድርጋቸው፡፡››

አላህም አለ፡-‹‹እነሱማ የአህመድ ኡመቶች ናቸው››

ሙሳም ጠየቀ፡-‹‹ ያ አላህ በዚህ መጽሃፍ ውሰጥ ህዝቦች ይታዩኛል ፤ የቀደምትን እና የመጺኣንን ትውልዶች ዕውቀት በሙሉ አሸክመኃቸዋል፤ መሲሁ ደጃልንም ይገድሉታል፡፡ እባክህ የኔ ህዝብ አድርጋቸው፡፡››

አላህም አለ፡-‹‹እነሱማ የአህመድ ኡመቶች ናቸው››

ሙሳም አለ፡-‹‹ በል እንግድያ እኔንም የሙሐመድ ህዝብ አድርገኛ፡፡››
ሙሳም ንግግሩን ቀጠለ፡-‹‹ ቆይ ግን ጌታዬ ከኔ ህዝብ እሚልቅ ህዝብ አለን››

አላህም አለ፡-‹‹ሙሳ ሆይ በሙሀመድ ህዝቦች እና በሌላው ህዝብ መካል ያለው ልዩነት በኔ እና በፍጥረቴ መከካል እንዳለው ልዩነት እንደሆነ አታውቅምን፡?>>

ሙሳም አለ፡-‹‹እንደው ይኸን የጉድ ህዝብ እንኳን አንዴ አሳየኝ››

አላህም አለ፡-‹‹ልታያቸው አይቻልህም፤ ግና ድምጻቸውን ላሰማህ፡፡››

ከፍጥረት አድማስ ወድያ ከሩሆች ስብስብ ከመናፍስት አለም ያሉ የሙሀመድ ህዝቦችን አላሀ ተጣራ፡፡

ህዝቦችም በአንድ ድምጽ፡-‹‹ለበይከላሁማ ለበይክ›› ይሉ ጀመር።

አላህም አለ፡-‹‹በረከቴ በእናንተ ላይ ይስፈን ፤ እዝነቴ እናንተ ላይ ቁጣዬን ቀደመ ፤ ማርታዬ ስለናንተ ቅጣቴን ቀደመው፡፡

እናንተ ሳትጠይቁኝ አኔ እሰጣችኋለሁ ፤ ከእናንተ ውስጥ የኔን ጌትነት አምኖ በሙሀመድ መለዕክተኝነትም ያመነ መላ ሀጽያቶቹን እሽርለታለሁ፡፡››

Sefwan sheik Ahmedin
----------------------------------------------------------
ነቢ ልቀው እኛን አላቁን (ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም)
----------------------------------------------------------

ምንጭ፦
المواهب اللدنية
حلية الأولياء


እንደ እሳት እራት ወደ መጥፊያ፣የምክለፈለፍ ፈጣን ተጓዥ ነኝ።ወደ ተጠመደልኝ የጥፋት ወጥመድ ስሮጥ እግሮቼ ይበረታሉ።ጉልበቴ ይፈረጥማል።እርምጃዎቼ የግልቢያ ያህል ይነጉዳሉ።የሚያደናቅፈኝን የትኛውንም እንቅፋት እሻገራለሁ።መንገዴ ላይ መሰናክል የሚሆኑ አያሌ ጥሻን መንጥሬ፣ወደ ማስበውና ወደ ምጓጓለት ስርፋ አፈተልካለው።

"ኣይበጅህም! ተው ተመለስ!" ዓይነት መልዕክት ያላቸው መውደቆችን ቀምሻለሁ።የሚታየኝ ግን የመድረሻዬ ብልጭልጭታ ነው።በቁስ ቅበ ቅዱሳት ስለደመቀው ጉጉቴ የተደሰኮሩትን ይትብሃሎችን ብቻ ነው የማደምጠው።
የማስተውለው ከመሻቴ ማዕድ ላይ መድረሴን ቢቻ ነው።
እናም ላበቴ እስቲጎርፍ እታገላለሁ።አሞቴ እስኪፈስ ጣጥሬ ወደ ምኞቴ ኣፈተልካለሁ።ጋራ ጥሼ፣አለት ምሼ፣
ባላሰለሰ ጥረት እሮጣለሁ።ከምከስምበት ገደል ቋፉ ላይም እደርሳለሁ።ደርሼ ግን ወደ መጥፊያዬ እገባበትን አቅም ይነሳኛል።ይሃ ሁላ የታገልኩለት ምኞቴ አይሰምርልኝም።

የምኞቴ መኮላሸትም ሰበብ ጌታዬ እንደሆነ አስቤ
አብዝቼ አማርረዋለው።የጠላኝ ያኽል ይሰማኛል።ተስፋ ቆርጬም እሰባበራለሁ።የስብራቴ ጉዳቱ ለሌሎች መልካም አጋጣሚዎቼንም የመታገል ጥንካሬዬን ይቀማኛል።

እንዲ እንዲያ እያለ ቀናቶች ይነጉዳሉ። ሕይወትም ይቀጥላል።አንድ ቀንም ይመጣል።በዚያ ቀን ያኔ… ጓጉቼ የሮጥኩለት ጉዳይ፣ያልሰመረው ምኞቴ እውነተኛ ገፅታው ተገልጦ አየዋለሁ።የቁሳዊ መጌጫው ተገልቦ ኣስተውለዋለሁ።በእርግጥም መጥፊያዬ እንደነበር እገነዘባለሁ።የማልወጣበት አዘቅት ውስጥ ለመግባት እየተፍጨረጨርኩ እንደነበርም ይገባኛል።

ከዚያም ጌታዬን አስባለሁ።እኔ ወደ እሳት እየተጣደፍኩ ሳለሁ፣እሱ ከቋፉ ላይ ደርሶ እንደመለሰኝ ይገባኛል።
እሱ ከክፉ ነገር እየጠበቅ ሳለ፣እኔ "ምኞቴ ተደናቀፈ"ብዬ ያማረርኩትን ኣስታውሳለሁ።ሐፍረት ይጠፈንገኛል።
የሳትኩኝ አመፀኛ ብሆንም ፍቅሩን አልነፈገኝም ነበር።የሚበጀኝን ሊሰጠኝ አስቦ፣የማይበጀኝን ፍለጋ ብታትርም እኔን ለራሴ ጥሎ አልጣለኝም።በራሕመቱ ከለለኝ።ሁሉም ነገር የገባኝ ጊዜም ፍቅሩ ለሕሊናዬ ይከብደኛል።ሀተታው ለቃላት ይርቃል።

እውነታው በገባኝ ልክ አብዝቼ አፈቅረዋለሁ።የማፈቅረውን ያህል አስባለሁ።የሚያፈቅረኝን ያህል ማሰብ ግን ለአቅሌ ይጠናኛል።«ካልሰመሩ እያንዳንዱ ምኞቶች ጀርባ የአሏህ እዝነትና ጥበቃው አለ!»ብዬም ለራሴ እነግራለሁ።ባሰብኩት ቁጥር ፍቅሩ ያይልብኛል።

የምለው ሳጣም እንዲሁ ስሙን እደጋግማለሁ!

አሏህ!!


ሲማሩም ሲያስተምሩም አደበኛነታቸው ገዝፎ ይንፀባረቃል።ለተመልካች የሚማርክ የፈገግታ ፀዳል ነበራቸው።የታዳሚን አትኩሮት የሚስቡ፣የ ርቱዕ አንደበተ ባለቤት ነበሩ።ለቀረባቸው ሰው ኹሉ በሚቸሩት የነበረ ፍቅርም ይወሳሉ።ወዳጅ ጠላት የማይሉ ሰው አክባሪ ነበሩ።ግሳፄዎቻቸው በትህትና፣በልዝብ ልሳን ይታጀባሉ።
ብስራቶችን ቀልብን በሚገዛ አገላለፅ፣ኣጣፍጠው ማውጋትንም ያውቁበታል።በሚያስተመሩበት እያንዳንዱ መድረክ ላይ ማራኪ ትዝታዎችን፣ጥልቅ የፍቅር አሻራዎችን አኑረው ያልፋሉ።

መውላና ሼኽ ሙሐመድ ረመዷን አል ቡጥይ…መስጂድ ውስጥ ደርስ እየሰጡ ነው።በድንገት አንድ የሰከረ ወጣት፣በዝግታ ወደ መስጂድ ገባ።ከተኮለኮለው ደረሳ መሀል ተቀመጠ።አፍታም ሳይቆይ ስካሩን ያወቀው ምዕመን ተረበሸ።ታዳሚዎችም ወጣቱን ከስፍራው ለማስወጣት ትግል ጀመሩ።ሸይኽ ረመዷን ድርጊቱን ባፅንዖት ነቀፉ።ተግሳፃቸውም ከለሰለሱ ቃላት ጋር የሚደመጥ ነበር።

«እሱ ከነበረበት ሀጥያት ሸሽቶ፣ወደ አላህ ቤት የመጣ ሆኖ ሳለ፣እናንተ ስለምን ትቆጡት? ለምን ሲባልስ ታመናጭቁታላችሁ?።በዚህ ግለሰብ እና በሸሸበት፣
በተጠጋው አምላኩ መሐል የናንተ ጣልቃ መግባት ምን ሚሉት ነው!?።ምናልባትም እዚህ በመገኘቱ ሰበብ፣አዛኙ ጌታ አላህ ከክፉ ድርጊቱ ይመልሰዋል።
ከጊዜያት በኋላም፣ከእኔም፥ከእናንተም ከሁላችንም በላይ የላቀ ሰው ሆኖ ሊገኝ ይችላል።»

ቀደሰሏሁ ሲረሁ!💚
https://t.me/z_bishara


#ከሙሒቦቹ_አንደበት ♥

የሀ~ያእ~ዐይን~ሷድ (كهيعص) ትርጉም!

ማሊክ ቢን ዲናር (ረዲየላሁ ዓንሁ) እንዲህ ይላሉ፦ አንድ ጊዜ ወደ አላህ ቤት ሐረም ለሐጅ አቀናሁ። መንገድ ላይ ሳለሁ አንድ ሰው ያለ ምንም ስንቅ ሲጓዝ አየሁትና ሰላምታ ሰጠሁት እርሱም መለሰልኝ። ቀጥዬ ከየት ነው የምትመጣው? ብዬ ጠየቅኩት
"ከእርሱ" ብሎ መለሰልኝ
እንዲህ አልኩት፦ ወደ የት መሄድ ፈልገህ ነው?
"ወደ ርሱ ቤት" ብሎ መለሰልኝ
እንዲህ አልኩት፦ የታለ ስንቅህና ጓዝህ?
እንዲህ አለ፦ እርሱ ዘንድ አለኝ!

ጥያቄው ቀጠለ

— ይህ መንገድ ያለ ምግብና ያለመጠጥ አይዘለቅም ምን ይዘሀል?
— አዎን ይዣለሁ። ከሀገሬ ስወጣ አምስት ፊደሎችን ተሰንቄነው የወጣሁት።
— ምንድናቸው እነርሱ?
— የአላህ ቃላት ሲኾኑ በሱረቱል መርየም መጀመሪያ ላይ የሚገኙትን ፊደላት ጠቀሰለት (كهيعص)
— ምን ማለት ነው?
– "ካፍ" ማለት ካፊ (በቂ) ነው፣ "ሀእ" ደግሞ ሀዲ (ቅናቻ መንገድ የሚመራ) ማለት ነው፣ "ያእ" ደግሞ መእዊያ ማለት ሲኾን ስንቅን፣ ምግብን የመሳሰሉ መጠቃቀሚያዎችን የሚያስተናብር ነው። "ዓይን" ደግሞ ዓሊም (ዐዋቂ) ነው ማለት ነው። "ሷድ" ሳድቅ (እውነተኛ) ማለት ነው።
አላህ ቢቂዬ ነው ብሎ በርሱ የተመራ ከእርሱም ስንቅን ከርሱ የጠበቀ እርሱ ደግሞ ዐዋቂና እውነተኛ መሆኑን የተረዳ አይጠፋም አይፈራም። ለጉዞውም ስንቅ ማጣትን አይሰጋም።

ማሊክ እንዲህ አለ፦ ይህን ቃላት ስሰማ ቀሚሴን አውልቄ ላለብሰው ስል እምቢ አለኝና እንዲህ አለ፦ ሸይኽ ሆይ! ቅዝቃዜው ካንተ ቀሚስ ለእኔ መልካም ነው። “ ይህች ዓለም (ዱንያ) ሐላሏ (የተፈቀደ ነገሯ) ሒሳብ ነው። ሐራሟ (የተከለከለ ነገሯ) ደግሞ ቅጣት ነው።”

ለሊቱ ሲጨልም ራሱን ወደ ሰማይ ቀና አድርጎ እንዲህ ይላል፦

አንተን ብንታዘዝ የማትጠቀመው ብናምጽህ የማትጎዳው ለአንተ የማትጠቀምበትን ሥጠኝ የማትጎዳበትን ምሕረታህን ለግሰኝ።

ሰዎች በሐጅ ለይ "ለበይክ" ሲሉ ይህ ሰው አይለም ነበር። ለምን "ለበይክ" አትልም?

እንዲህ አለ፦ ሸይኽ ሆይ! አላህ ጥሪህንም አልተቀበልኩም ንግግርህን አልሰማም አልመለከትህም። (ላ ለበይክ ወላ ሳዕደይክ ...) እንዳይለኝ ፈርቼ!

ከዚያም ከእኔ ዕይታ ተሰወረብኝ። ሚና ላይ እንዲህ ብሎ በግጥም ስንኝ ሲያለቅስ ግን አየሁት።

إﻥ ﺍﻟﺤﺒﻴﺐ ﺍﻟﺬﻱ ﻳﺮﺿﻴﻪ ﺳﻔﻚ ﺩﻣﻲ -- ﺩﻣﻲ ﺣﻼ‌ﻝ ﻟﻪ ﻓﻲ ﺍﻟﺤﻞ ﻭﺍﻟﺤﺮﻡ""
ﻭﺍلله ﻟﻮ ﻋﻠﻤﺖ ﺭﻭﺣﻲ ﺑﻤﻦ ﻋﺸﻘﺖ -- ﻗﺎﻣﺖ ﻋﻠﻰ ﺭأﺳﻬﺎ ﻓﻀﻼ‌ ﻋﻠﻰ ﺍﻟﻘﺪﻡ""
ﻳﺎ ﻻ‌ﺋﻤﻲ ﻻ‌ ﺗﻠﻤﻨﻲ ﻓﻲ ﻫﻮﺍﻩ ﻓﻠﻮ -- ﻋﺎﻳﻨﺖ ﻣﻨﻪ ﺍﻟﺬﻱ ﻋﺎﻳﻨﺖ ﻟﻢ ﺗﻠﻢ""
ﻳﻄﻮﻑ باﻟﺒﻴﺖ ﻗﻮﻡ ﺑﺠﺎﺭﺣﺔ --ولو بالله ﻃﺎﻓﻮﺍ ﻷ‌ﻏﻨﺎﻫﻢ ﻋﻦ ﺍﻟﺤﺮﻡ""
ﻟﻠﻨﺎﺱ ﺣﺞ ﻭﻟﻲ ﺣﺞ ﺇﻟﻰ ﺳﻜﻨﻲ -- ﺗﻬﺪى الأ‌ﺿﺎﺣﻲ ﻭأﻫﺪﻱ ﻣﻬﺠﺘﻲ ﻭﺩﻣﻲ


ከዚያም እንዲህ አለ

ጌታዬ ሆይ! ሰዎች በዕርድና በሰጠሀቸው ነገር ወደአንተ ለመሄድና ተቃረቡህ። እኔ በነፍሴ እንጂ ወደ አንተ የምቃረብበት ነገር የለኝምና ተቀበለኝ። ከዚያም ወደ ሰማይ እየተመለከተና በብርቱ ሆኔታ እያለቀሰ ወደ አላህ ዘንድ በሞት ተሻገረ። አላህ ይዘንለት።

ይህን ለሊት ይህን ጉዳይ እያሰብኩ በሕልሜ አገኘሁትና ጠየቅኩት ይላሉ ታሪኩን የሚዘግቡልን ታላቅ ሰው።

አላህ በአንተ ላይ ምን አድርጎ ነው?

እንዲህ አለኝ፦ በበድር ዕለት የተሰዉት ላይ እንዳደረገው። ለእኔ ግን ከዚያም በላይ ጨመረልኝ።

ምንድነው ጭማሬው? ሰል ጠየቅኩት

እንዲህ አለ፦ እነርሱ የተገደሉት በከሐዲያን ሰይፍ ሲኾን እኔ ግን የተገደልኩት በጀባር መሐባ ነው።

(ከ ረውድ አል ሪያሒይን መጽሐፍ)
ኢማሙ ሻፍዒይ (ራዐ)

አላህ ሙሒቦች ከቀመሱት ያቅምሰና ♥

✍best kerim


የጀማሉዲን አልዐኒ ደረሳ የነበሩት ሸኽ አህመደል ሀዲ የዓለማትን እዝነት በማፍቀር ይታወቁ ነበር፡፡ ፍቅራቸዉ በየግጥሞቻቸዉ በጉልህ ይታያል፡፡ ‹‹አሽረፈል ኸልቅን›› አወድሰዉ አይጠግቡም፡፡ ካጠገባቸዉ ለመገኘት ብዙ ጊዜ ተመኝተዋል፡፡

ምኞታቸዉ ተሳክቶ ለሀጅ ተጓዙ፡፡ ወደመዲና አምርተዉም ወዳጃቸዉን ዘየሩ፡፡ሆኖም ወዳገርቤት አልተመለሱም፡፡ እዚያዉ መዲና ዉስጥ ሞት አስቀራቸዉ፡፡ ከወዳጃቸዉ አጠገብም ተቀበሩ፡፡ ይህ እድላቸዉ ባገር ቤት የነበሩ ዑለሞችን ሁሉ አስቀንቶ ነበር፡፡ ከታላቁ ሰዉ አጠገብ መሆንን የማይመኝ ማን አለ?

ይህ ምኞት ያቃጥላቸዉ ከነበሩ ሊቃዉንት መካከል ሸኽ ሰይድ ኢብራሂም (የጫሌ ሸኽ) አንዱ ነበሩ፡፡ ዕድል ቀንቷቸዉ ለሀጅ ሲነሱ ሀገሬዉ ተጨነቀ፡፡ ፍቅራቸዉ ጽኑ ነበርና ልክ እንደሸኽ አህመደል ሀዲ እዚያዉ እንዳይቀሩ ሰጋ፡፡ እናም ለዱዐ ተቀመጠ፡፡ እስኪመለሱ ድረስ የዱዐ ማዕዱ አልተነሳም፡፡

ሸኽ ጫሌ ለወራት ተጉዘዉ መካ ደረሱ፤የሀጅ ሥርዓታቸዉን አከናወኑ፤ ወዳጃቸዉን ለመዘየርም ወደመዲና አመሩ፤እዚያ ደርሰዉ ናፍቆታቸዉን ተወጡ፡፡ አላህ ሽቶት መዲና ዉስጥ ቢሞቱና ከወዳጃቸዉ አጠገብ ቢቀበሩ ምኞታቸዉ ነበር፡፡ ግና ይህ አልሆነም፡፡ ወደአገር ቤት ተመለሱ፡፡

የሚከተለዉን ስንኝም ቋጠሩ፡-

የኛማ ዚያራ ተዉ የለዉም ለዛ፤
እንዳህመደልሀዲ ፍግም ሳንል እዛ፤


[…የኸሚስ ውዳሴ…]

የፍቅርን ህመም በ ’ፍቅር ማከም፣
የናፍቆት ቁስልን በመውደድ ማገም፣
በኩስስ ጫንቃ ሰማይ መሸከም።
እንዲያ አይደለም ልኩ!
ልኩ…? ልኬትን ያልፋል፣
ለመገንበር ቃል ይሰንፋል።
ያን ድብቁ ሉል በኻሊቅ ቅጥር፣
ኑር ፅጌረዳ ሽሽጉ ሚስጥር፣
አይገለጥም በጁድ መነጥር።

ቀዋም ነው ሑሌ
ምዑድ ምሶሶ አበድ እ’ማይዘም፣
በደህኔ ተረት!
የግብሩ ሻማ አልደበዘዘም፣
በትምክህት ሙሾ
የቃሉ ሰነድ አልተበረዘም፣
በ’ርኩስ ይትብሃል
አደብ ምግባሩ አልተመረዘም።

ከማር ልሳኑ!
የፉርቃን ዶግማ የሚግተለተል፣
የኑር ፏፏቴ
ጉተናው መሐል ሰርክ የሚንፏለል።
ዓይኑን ተኩሎ በቀመር ሂላል፣
እንደ ፍል ውሃ ይንተከተካል፣
የሳቁ ጨረር!
ሩህ ይነድላል በፍቅር ሾተል፣
የሚስኩ ሽታ
የነፍስ ክርፋት ያሻል በመፍተል።

ጥርሱ እንደ’ባሩድ እሳት ይተፋል፣
ሳቁን ያየ’ዜ ሰው መች ይተርፋል?።
በኩኑ መቀስ!
እኩል ከርክሞት የተሰደረው፣
ቅንድቡን አይቶት
ስንቱን ቀልብ ነው የመነጠረው፣

እንዲያም ኣይደለ!
ዳሩ ይርቃል የወስፉ ድንበር፣
ተመልከት ቅኔ ቀለም ሲሰበር።
ዋሪዳ ታጥቀው!
ላስራሩ መንገድ ለውሕ የጨበጡት፣
መጅሊሱ ቅብቅብ
ሶፍ ደምድመው የተቀመጡት።
በአያት ሱራ ነዝሙን ረተቡት፣
ዚክሩን በምዕራፍ በጁዝ ከተቡት፣
ኩልል ሙጀለድ መድሕ አነበቡት፣
አነበነቡት።
ኺያላ ገቡ’ንጂ!
በሱካራ ቅጂ ተግተው መደድ፣
ጀዝቡ እያማታ
ሀዋ ለግጋቸው በገራም ገመድ፣
ሲራ ላይ ፈሉ አበድ ለመንደድ።

እንዲያም ኣይገራም!
ሰንሰል ለቸረው
ከጁድ አዳራሽ ሰህም የመለከው፣
ላ’ህባቦች ሻኛ!
ሸውቅ አደባባይ ጧት ለሰለከው፣
እንዲያም አልገራም አልተመለከው።

ይጠናል ወሰፉ!
ሀርፍ ቢሰድር ታ’ርሽ እስተ ሰራ፣
ተክራር ቢደለቅ አበድ ቢቀራ፣
ይጠናል ወስፉ እንዲያም አይገራ።

የኪኑን ፈረስ
ኮርቻ ጭነው የገሰገሱት፣
እርካብ ጨብጠው
ጋለቡት እንጂ ዳር አልደረሱት።
ቅኔው ሲር ነው
ልኩ አይለካም ልኩ አይገኝም፣
ቀድሩን ያወቀ
ወስፉን መዓበር ሰርክ አይመኝም።
"ወረፈእና ለክ"ኻሊቅ አልቆት
መድ አይሻገር
ባ’ሊፍ ይደክማል ቀለም መሰላል፣
ሰው ነው እንዳይሉት ሰው መች ይመስላል።
ቀለም ሰነፈ!
እ’መብለጉ ላይ
ነው ኣሉት "በሸር፣
ላ ከል በሸር።"
……………………………
አሏሁመሶሊ አላ ሰይዲና ሙሐመድ
ወአላ አሊ ሰይዱና ሙሐመድ።

Zahid Iqbal ኸሚስ ……2014


#ዓሪፎቹ

ሰይደቲ ራቢዓ (አላህ መልካም ሥራዋን ይውደድላት) ተጠየቀች

አንድ ባሪያ አላህ ዘንድ ለመወደድ የሚያደርሰውን ደረጃ የሚያገኘው በምንድን ነው?

[ አንድ ሰው መጥፎ የሚለው ነገር ገጥሞት ልክ ጥሩ ጸጋ እንደገጠመው መደሰት ሲችል፤ በሚሰጠው ስጦታ የሚያርፈውን ያክል በሚገጥመውም አደጋ በመረጋጋት እረፍት ማድረግ የቻለ ጊዜ!]

ስትል መለሰች ...

እርሱ የሰራው ሁሉ ውብ ነው ብሎ አምኖ መቀበል ውቡ ኢማን ነው። ግና የዘመን ትግል ይጠይቃል። ቀደምቶቻችን በዕውቀት አልያ በተለያዩ ነገሮች በልጠውን አይደልም። ከአላህ ጋር በመወዳጀት ባገኙት እርካታና ሥጦታ እንጂ። የተሰጡን ዕድሎች ሁሌ መጥፎ አይደሉም ምን አልባትም ከአላህ ጋር የሚያቃርበንም ልዩ መንገዳችን ይሆናል። በመንገዳችን ከውስጣችን አላህን ላለማስወጣት ከታገልን ይህቺን አጭር ግና ውስብስብ ዓለም መወጣት እንችላለን። አላህን ወደ ውስጣችን ለማስገባት ደግሞ መላልሶ ከርሱ ጋር ማውጋት (ሙናጃት) ማድረግና እርሱኑ አብዝቶ ማስታወስ (ዚክር) ወሳኙ መንገድ ነው። " እንደ ዓሪፎቹ ባትኾኑ ከእነርሱ ጋር ተመሳሰሉ" እንደሚሉት ደጋጎቹን አብዝቶ ማንሳት ኒያን ያድሳል።

አላህ ፋህሙን ይረዝቀና ♥

መልካም የኸሚስ ዕለት ተመኘሁ ♥

✍best kerim




እነሆ! #መጽሐፈ#ዓምደ-ሀገር በዛሬው ዕለት ለንባብ ቀርቧል!

መጽሐፉ የሼህ ዓሊ-ጎንደርን መዋዕለ-ሕይዎትና የኢትዮጵያን 18/19ኛ ክ/ዘመናትን ይቃኛል።
ሼህ ዓሊ-ጎንደር - ከ18ኛው አጋማሽ እስከ 19ኛው ክ/ዘመን አጋማሽ ነበር የኖሩ፡፡ ወሎ ተወልደው፣ ዓለምን ዙረው፣ በጎንደር ታጠሩ፡፡ በመማር ማስተማር፣ በሥነ-ጽሁፍ፣ በኪነ-ጥበብ፣ በንግድ፣ በሥነ-ምህንድስና፣ በፍልስፍና፣ በምንፍሥና፣ በሥነ-ምድር እና በሥነ-ተፈጥሮ ምርምር፣ በውትድርና እና በአስተዳደር፣ በሌሎች መስኮች ተጨባጭ ዓለማቀፋዊና ሀገራቀፋዊ ትሩፋት አበርክተዋል፡፡ መሠረታቸው ጠብቆ፣ ልህቀታቸው እርቆ ከ፬፻(አራት-መቶ) በላይ የዓለም መዲናዎችን ጎብኝተዋል፡፡ ከሱዳን፣ ከግብጽ፣ ከቱርክ ነገሥታት ጋር ግልጽ(ነጻ) ግንኙነት ፈጥረዋል፡፡ የእንግሊዝን ንግሥት፣ የህንድን መንግሥት፣ የሱዳንን ምስለኔ በአማካሪነት አግዘዋል፡፡ ፋናቸውን በከፊል የኤሮጳና የኤዥያ አህጉራዊ ግዛቶች አዝልቀው አነጥበዋል፡፡

ለኢትዮጵያ መሣፍንትና ንጉሦች ሥነ-መንግሥታዊ ትምህርት በመስጠት፣ ገንቢ ተሞክሮና ምክር፣ ድልብ ዕውቀትና ልምድ በማካፈል ክህሎታትን አበልጽገዋል፡፡ የእርስ-በርስ ግጭቶችን በዕርቅ በማቃለል ደሚቅ አሻራ አሳርፈዋል፡፡ በአጤ ዮሐንስ-፫ኛ፣ በእቴጌ መነን፣ በራስ ዓሊ(ትንሹ/አስጘር)፣ በደጃች ጎሹ እና በአጤ ቴወድሮስ ላይ በጎ አበርክቶ አትመዋል፡፡ በሐበሻ ክርስቲያኖች መካከል “የጸጋ ልጅ”፣ “ቅባት” እና “ተዋህዶ” ተሰኝተው የተከሰቱ ልዩነቶች የእርስ-በርስ እልቂት ከማስከተላቸው በፊት፣ ጣልቃ በመግባት አሸማግለዋል፡፡ የእሥልምና ሊቃውንትን ሕብረትና አስተሳሰብ በአግራሞታዊ የተሀድሶ ሥርዓት አበልጽገዋል፡፡

በአጠቃላይም የዚያንዬዋ ሐበሻ የፍቅር አጉራዋ ሲደርቅ፣ የጥል ካስማዋ ሲደምቅ በመታዘባቸው በትውልዱ ዘንድ ሠላምና አብሮነትን በዕውቀት በማስፋፋት፣ ሥልጣኔና ህብረትን በማስፀናት፣ ፍቅርና ሥርዓትን በጥበብ በመዝራት፣ ጸሎትና ተሲያታቸውን ለሀገር በማበርከት ህልውናዊ ስኬት አፈንጥቀዋል፡፡ ስዊዲናዊው የታሪክ ሊህቅ Sven Rubenson(d-2005) እንደገለፀውም በዘመኑ፦ ‹‹ሰላምና ሥርዓት አስጠባቂ!(Safeguard Peace and Order)›› ተሰኝተው ወላዊ ከበሬታ ተችረዋል፡፡ መጽሐፈ ዓምደ-ሀገር ይኽንን የሼህ ዓሊ-ጎንደርን መዋዕለ-ሕይዎት(በአመዛኙ ዓለማዊ ኑረት)፣ የዘመናቸውን ተዛማጅ ጭብጥ እና ሥነ-ኑረት(Ontology Of history) አጠንጥኖ ይቃኛል!

መጽሐፉ በአዲስ-አበባ፦
~ ጃዕፈር መጽሐፍት መደብር፣ ለገሀር
~ አልተውባ መጽሐፍት መደብር፣ ጎጃም በረንዳ - ይገኛል።

ማስታወሻ፦
ይህ ልጥፍ(Post) ለመጽሐፍት አፍቃሪያን እንዲዳረስ (Share)በማድረግ እረገድ መተባበር ያስመሰግናል። መልካም ንባብ!!!

Kedir Taju


የአብሬት ሸኾች 3ኛ መሪ ሲሆኑ በ1907 ተወለዱ፤ በዒልምና ተርቢያ ቤት ውስጥ አደጉ፤ የአብሬትን ማእከል ይበልጥ ያሳደጉና ከፍተኛ የማህበረሰብ ትስስር የፈጠሩ ታላቅ ሸይኽ ናቸው።

ሰይድ ቡደላ ( አበራሙዝ)

በፖለቲካው መስክ አፄ ኃይለስላሴ ከፍተኛ የሀገር ጉዳዮችን ለማማከር ከመረጧቸው ታዋቂ ሰዎች መካከል አበራሙዝ አንዱ ሲሆኑ፡ በየጊዜው ብልህና ጥበባማ ምክር በመለገስ ሀገርን አገልግለዋል። ለምሳሌ በአንድ ወቅት በብሄራዊ ቲያትር አዳራሽ በመኮንን ሀብተወልድ በተጠራ የምክክር መድረክ የኤርትራ ጉዳይ ተነስቶ ሌሎች ተሰብሳቢዎች የጦርነትን አቋም . ሲደልቁ አበራሙዝ "ኤርትራውያን ወገኖቻችን ናቸው፤ አንድ ሰው እግሬ ትንሽ ታመመ ብሎ ቆርጦ አይጥለውም። ካላከምነው ተቆርጦ ይወድቃል፤ ካከምነው ግን ሊድን ይችላል።" በማለት የጦርነት ስሜቱን አቀዝቅዘዋል።

*
በኃይለስላሴ ዘመን መጨረሻ ተማሪዎች የተቃውሞ እንቅስቃሴ በተጋጋመ ጊዜ ንጉሱ በጠሩት የምክክር መድረክ በተማሪዎች ላይ የሃይል እርምጃ እንዲወሰድ ከአንዳንድ መኳንንት የቀረበውን ሀሳብ በፅኑ ተቃውመዋል።
አበራሙዝ በፍትህ ዘርፉ የጉራጌ አካባቢ የሸሪዐ ፍርድቤት ፕሮዚደንት በመሆን ሙስሊሙንም ሙስሊም ያልሆኑ ወገኖችንም ለአመታት ዳኝተዋል። ፍርዳቸው አንድም ቀን ይግባኝ ተብሎ አይታወቅም። በፍርዱ ሂደት ሙስሊም ያልሆኑ የሀገር ሽማግሌዎችን ሳይቀር በአማካሪነት ያሳትፉ ነበር።

*
በጣልያን ወረራ ወቅት ያሳዩት ጥበብ የተሞላበት ተሳትፎም ሊጠቀስ ይበቃል፤ በአንድ በኩል አርበኞችን በገንዘብ ስለ ጣልያን እንቅስቃሴ መረጃ እንዲደርሳቸው በማድረግና በሌሎች መንገዶች ሲደግፉ፤ በሌላ በኩል ጣልያን ያልተገባ እርምጃ በመውሰድ ህዝብ እንዳይጨርስ የዲፕሎማሲ ሚና ተጫውተዋል። በወረራው ወቅትም የውስጥ አርበኛ በመሆን የጠላትን ሀይል ቁምስቅሉን አሳይተውታል፤ ከነዚህ መሀል ቀጭኔ አስና የተባለው ሙሪድ አርበኛ ይጠቀሳል። እስከ 200 የሚደርሱ የጠላት ወታደሮችን እንደደመሰሰ ይነገራል። (ረ.ዐ)

* በልማቱ ዘርፍ ድሆች መሬትና የማረሻ በሬዎችን እንዲያገኙ በማድረግ ብዙ ቤተሰቦችን ታድገዋል።
* በትምህርት ዘርፍም ጉልህ ሚና አላቸው። ህዝበ ጉራጌ የዐረብኛ ትምህርት እንዲማርና ከመሀይምነት ነፃ እንዲወጣ ታግለው ስኬትን አስመዝግበዋል።

የጉራጌን ህዝብ ባህል በማስተዋወቅ ድርሻቸውም የጎላ ነው፤ ለምሳሌ ከቃጫ የሚሰራውን የጉራጌዎች የጥበብ አሻራ ያረፈበት የቤት ውስጥ ምንጣፍ በማሰራት በየሶስት ወሩ ከአፄ ኃይለስላሴ ጋር በሚያደርጉት ስብሰባ ይዘው ይሄዱና ለንጉሱ ያበረክቱ ነበር፤ ይህ ድርጊት ሁለት አላማዎችን አሳክቷል
1. የጉራጌን ባህል፣ ጥበብና ብርታት አስተዋውቋል።
2. ለጉራጌ ህዝብ በጎ አመለካከት እንዲኖራቸው አስችሏል።


[ የሶሓቦች አሻራ…]

በሰይዲና ዑመር (ረዐ) የኸሊፋነት ቆይታ ኢስላማዊ እሳቦቶች አብበዋል።ቁርዓናዊ ስልጣኔ በዓለም ዙርያ የጎመራበት ዘመን ነበር።በነብያዊ አስተምሕሮቶት የተገሩት ሶሓቦች በየደረሱበት መልካም ዜጋን ስለመፍጠር ታግለዋል።በሰው ልጅ ላይ የተጫነውን የዘረኝነት መርዝ አክመው፣
የእኩልነት መርሆዎችን አስገንዝበዋል።
በሰብዓዊነት ላይ የተከናነቡ ዝንባሌዎችን በፍትህ ተክተዋል።በዳዕዋቸውም ፍጡርን ከፈጣሪ ጋር አዛምደዋል።ለፈጣሪም ለፍጡርም የመታመን ባህልን አዳብረዋል።ለችግር ሲባል እርስ በርስ መጣረስን በማስቆም፣በፍቅርና በሶብር የማለፍ እሴቶችን አውርሰዋል።
ኢስላማዊ ትምሕርቶችም በተቀናጀ ሁናቴ የደሩበት ወርቃማ ዘመን ነበር።

ዘርፈ ብዙ አበርክቶዎችን ማደል የቻለው ይሃ ዘመን በከተሞች ምስረታና እድገት ላይ ያኖረው አሻራ በቀዳሚነት ይዘከራል።ዛሬ ላይ በዓለም ዙርያ ከሚታወቁ እና የጎላ የኋሊት ታሪክና ስልጣኔን ከተቋደሱት ከተሞች ጀርባ የሶሃቦች የጥበብና የትግል ሚናቸው በሰፊው ይነበባል።

"ፋስጠጥ"በመባል የምትታወቀው ጥንታዊቷ ካይሮም ታሪኳ ላይ ተሃድሶን ካስገኙላት መሪዎች መሐል አምር ኢብኑል አስ አንዱ ናቸው።ሶሃቦች ሚስር(ግብፅ)ን ከቶጣጠሩ በኋላ፣አምር ቢን አስ የግዛቲቱ ሚንስቴር ተደርገው ተሾሙ።ባለ ታሪኳን አሌክሳንድሪያ ከተማን መናገሻቸው አደረጉ።
በሒደትም ከጠቅላይ አዛዡ ሰይዲና ዑመር ጋር በመምከር፣የማዕከላዊ መንግስታቸውን መቀመጫ ወደ ያኔዋ "ፋስጣጥ"የዛሬዋ ካይሮ ለወጡ።ከተማይቱ ጥንታዊ ብትሆንም በሶሓቦቹ እጅ ከገባች በኋላ ግን በርካታ መሰረታዊ ልማቶችን፣የንግድ መንገዶችን፣የግንባታና
የምህንድስና ጥበባትን ማግኘት ችላለች።
ሶሓቦች በሰፈሩበት ከተሞች ሁሉ ቀዳሚ ተግባራቸው የነበረው የመስጂድ ግንባታ መሆኑን በታሪክ ያወሷል።ለዚያም በቀዳሚነት የ(አምር ኢብንል አስ)መስጂድ ተገንብቷል።

በቀጣይነትም በወቅቱ በነበሩ ሶሓቦች ስም የተሰየሙ ሌሎች በርካታ መስጂዶችም በሀገሪቱ አራቱም አቅጣጫ ተዋቅረዋል።እሰከ 220 የሚደርሱ መስጂዶችና መድረሳዎችን በወቅቱ መመስረታቸውም ድርሳናት ያትታሉ።በዚህም ሰበብ በሀገሪቱና አጎራባች ክፍለ ግዛቶች ላይ የኢስላማዊ እውቀት ስርጭት ተደራሽ ሆኗል።

ከቆይታም በኋላ የሚንስትሩ አምር ወኪሎች ወደ ሊቢያ በመገስገስ፣ሰርጥ የተሰኘችን ከተማ መያዝ ችለዋል።ከተማዋን በምህንድስና ጥበባቸው እንዳዲስ አስዋቡ።እና መንገዶችን፣
መኖሪያ ቤቶች፣ለሚኒስትሮች መቀመጫ ቢሮዎችን፣እንዲሁም የጦር ካምፕን ጨምሮ መዝናኛ ስፍራዎችን ሰርተዋል።በግዛቶች ያልተያ መንፈሳዊና ቁሳዊ ስልጣኔን ማስረፅ ችለዋል።


Forward from: ABRET PRO
ፋጢመቱ-ዘህራእ ቢንት ሙሐመድﷺ

ፋጢመቱ ዘህራእ ቢንት ሙሐመድ የነብዩ ሙሐመድ ﷺ እና የእመት ኸዲጃ (ረ.ዐ) አራተኛ ሴት ልጅ ናት። ፋጢማ (ረ.ዐ) የተወለደችው ሙሐመድﷺ ነብይና መልእክተኛ ከመሆናቸው አምስት ዓመት በፊት ወይም ከሂጅራ አስራ ስምንት ዓመታት በፊት ነበር።" "መሪየም ፣ እመት ኸዲጃ ፣ አሲያ እና ፋጢማ(ረ.ዐ) በምድር ላይ ካሉ ሴቶች ሁሉ ንጹህና በላጭ ናቸው " በማለት ነብዩﷺ መስክረውላቸዋል።

ፋጢማ(ረ.ዐ) የአምስት ዓመት ታዳጊ እያለች አባቷﷺ ለሰው ዘር በሙሉ ነብይ ተደርገው ተላኩ። በዚህም የተነሳ ፋጢማ (ረ.ዐ) ገና በለጋ እድሜዋ ቁረይሾች በአባቷ ላይ በየጊዜው በሚያደርሱት ግፍ ክፉኛ መሳ^ቀቅና ሃዘን ደርሶባታል። በይበልጥም ደግሞ ከሁሉም የከፋ መከራ የደረሰባት ከመላ ቤተሰቧና የበኒ ሃሽምና የዐብድመናፍ አባላት ጋር የአቡ ጧሊብ ሸለቆ የሚባለው ስፍራ ገና በለጋ እድሜዋ ሶስት የመከራ ዓመታትን በገፉበት ጊዜ ነበር። በዚያ ሳለች ብዙ የርሀብና የጥም ዕለታትን አስተናግዳለች። ያንን የመከራ ጊዜ ተገላግላ ብዙም ሳትቆይ ነበር ተወዳጇን እናቷን ኸድጃን(ረ.ዐ) በሞት ያጣችው። ይሁን እንጂ ሌላ ምርጫ ስላjልነበራት የእናቷን ፍቅር ደርባ ለክቡሩ አባቷ በመስጠት በሁሉም ጉዳያቸው ከጎናቸው መቆሟን በተግባር ለማሳየት ትጥር ነበር።

ነብዩﷺ ሙስሊሞች ሁሉ ከመካውያን ግፍ ለማምለጥ ይችሉ ዘንድ ወደ መዲና እንዲሰደዱ ባዘዙበት ጊዜ እሷና እህቷ እሙ ኩልሡም ወደ መዲና የሚወስዳቸው ሰው እስኪላክላቸው ድረስ መካ ውስጥ ቆይተው ነበር። ፋጢማ(ረ.ዐ) አስራ ስምንት አመት እንደሆናት አቡበክርና ዑመርን(ረ.ዐ) የመሳሰሉ በርካታ ታላላቅ ሶሀባዎች ለትዳር ፈልገዋት ነበር። ሆኖም ግን ነብዩﷺ በታላቅ ትህትና ይቅርታ እንዲያደርጉላቸው እየጠየቁ ጋብቻውን ውድቅ አድርገውታል። ከዚያም ነብዩﷺ ለአሊ(ረ.ዐ) ዳሯት። በጊዜው ዐሊ(ረ.ዐ) ለመህር የሚሆን ገንዘብ ስላልነበራቸው ነብዩﷺ ያበረከቱላቸውን ጋሻ ለዑስማን(ረ.ዐ) በአራት መቶ ሰባ ዲርሀም ሸጡላቸው። ከዚያም ገንዘቡን ወስደው ለነብዩﷺ ሲሰጧቸው እርሳቸው ደግሞ ቢላል ጥቂት ሽቶ እንድገዛ ካደረጉ ቡኋላ የቀረውን ለሙሽራዋ የሚያስፈልጋትን ነገሮች ትገዛላት ዘንድ ለኡሙ ሰለማ(ረ.ዐ) ሰጧት። ከዚያ ነብዩﷺ ተከታዮቻቸውን ጋብዘው የጋብቻቸውን ሥነ-ሥርዓት አደረጉ። የዒሻእ ሰላት ተሰግዶ እንዳበቃም ወደ ሙሽሮቹ ሄደው ውሃ እንዲሰጧቸው ጠየቁ። ከዚያም ውዱእ ካደረጉ ቡኋላ ውሃውን በእነርሱ ላይ እየረጩ እንድህ አሉ፦ "አላህ ሆይ! ባርካቸው እንዲሁም ከእነርሱ የሚወጡትን ልጆችም ባርክ።" ይህ ከሆነ ከዓመት ቡኋላ ፋጢማ(ረ.ዐ) የመጀመሪያ ልጇን ለነብዩምﷺ የመጀመሪያ የልጅ ልጅ የሆነውን አል-ሐሰንን በሂጅራ የዘመን አቆጣጠር ሦስተኛው አመት ላይ ወለደች። ነብዩﷺ በሁኔታው በጣም የተደሰቱ በመሆናቸው በህፃኑ ልጅ ጆሮ ላይ አዛን አደረጉበት። ከዚያ ቴምር በአፋቸው ካላመጡ ቡኋላ በአፉ ላይ አደረጉበት። ስሙንም አል-ሐሰን ብለው ከሰየሙት ቡኃላ ጸጉሩን ላጭተው በጸጉሩ ሚዛን ልክ ብር ሶደቃ አከፋፈሉ። ቡኃላ ደግሞ ፋጢማ አል-ሑሰይን የሚባል ወንድ ልጅ ተገላገለች። ነብዩﷺ አል-ሐሰንና አል-ሑሰይንን በጣም የሚወዷቸው ከመሆኑ የተነሣ ሁልጊዜም ከአጠገባቸው አይለዩዋቸውም ነበር። ሀያሉ አላህ፦

"የነብዩ ቤተሰቦች ሆይ! አላህ የሚሻው፤ ከናንተ ላይ እርክሰትን ሲያስወግድና፤ ማጥራትንም ሲያጠራችሁ ብቻ ነው።" (አል-አሕዛብ፡33)

የሚለውን የቁርኣን አንቀጽ ባወረደ ጊዜ ነብዩﷺ በኡሙ ሰለማ ቤት ዓሊን ፣ ፋጢማን ፣ አል-ሐሰንና አል-ሑሰይንን ሰብስበው በመጎናጸፊያቸው ከሸፈኗቸው ቡኃላ እንደሚከተለው በማለት አላህን ለመኑ፦ "አላህ ሆይ! እነዚህ ቤተሰቦቼ ናቸው። ከእነርሱ ላይ ርክስነትን አስወግድ። ንጹህና ነውር የሌለባቸውም አድርጋቸው" ይህንን ለሦስት ጊዜያት ያክል ከደጋግሙ ቡኃላ እንዲህ አሉ፦ "አላህ ሆይ! ሶላትና በረከትን በኢብራሂም ቤተሰቦች ላይ አድርግ በእርግጥ ምስጋና የሚገባህና ታላቅ የሆንክ ጌታ ነህና።» በአምስተኛው የሂጅራ ዓመት ፋጢማና አሊ(ረ.ዐ) አያቷ ነብዩ ሙሐመድﷺ ዘይነብ በማለት ስም ያወጡላትን ልጅ ወለዱ። ቆመው ይቀበሏትና ይስሟታል። እርሷም እንደዚያው ታደርጋለች።" አንድ ጊዜ ሚንበር ላይ ሆነው ንግግር እያደረጉ ለፋጢማ ያላቸውን ፍቅር ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦

"ፋጢማ የእኔ አካል ነች እሷን ያስቆጣ እኔንም አስቆጥቷል።» በሌላ የሀድስ ዘገባ ነብዩ(ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም) እንደሚከተለው ማለታቸው ተጠቅሷል፦ "ፋጢማ የእኔ አካል ነች እሷን ያስቆጣ እኔን አስቆጥቷል። እሷን የጎዳ እኔን ጎድቷል። (ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)

ይሁን እንጂ ነብዩﷺ ተወዳጇን ልጃቸውን ፋጢማን(ረ.ዐ) ሌሎችንም የሚቀርቧቸውን መልካም ስራዎችን የመስራትን አስፈላጊነት በመግለጽ ትኩረት እንዲሰጡት ይገፋፉ ነበር። አንድ እለት እንዲህ አሉ፦

"የቁረይሽ ሕዝቦች ሆይ! ነፍሶቻችሁን አድኑ። የአላህን ሀቅ በተመለከተ ምንም የማደርግላችሁ ነገር የለኝም። የሙሐመድ ልጅ ፋጡማ ሆይ! እኔ ዘንድ ካለው ነገር የፈለግሽውን ነገር ጠይቂኝ። የአላህን ሀቅ በተመለከተ ግን ምንም ላደርግልሽ አልችልም። በሌላ ዘገባ እንደሚከተለው ብለዋል፦ "ፋጢማ ቢንት ሙሐመድ ሆይ! እራስሽን ከጀሀነም እሳት ጠብቂ። ከአላህ ፍቃድ ውጭ ልጎዳሽም ሆነ ልጠቅምሽ አልችልምና።" ( ቡኻሪ ዘግበውታል)


ተማሪው ጠየቀ።
«መምህር ሆይ! ፍቅርን የማገኝበት መንገድን አመላክተኝ?»

መመህሩ ጀላሉዲን ሩሚ መለሰ!

«ፍቅርን መፈለግ ያንተ ድርሻ ኣይደለም።ኣንተ በልብህ የተገነባው እና ፍቅርን እንዳታገኘው የሚያግድህን የጥላቻን ካብ ቀድመህ ኣፍርሰው።
ከዚያም አንተ ወደ ፍቅር መሔድ ኣይጠበቅብህም።ፍቅር ወዳንተ ይመጣል!።»


የሰው ጉዳይ ለማስፈፀም ታጥቀው የተነሱ፣ ጭንቅ ለመፈረጅ የማይሳሱ፣ ማንም የትም ቢወስዳቸው አብረው የሚንከላወሱ ናቸው። ታላቁ ዓሊም የእውቀት ቋት ሙፍቲ ዳውድ አቡበክር። ታላላቅ መሻኢኾችን ነው የሚያቀሩት፡ ከኪታብና ዒልም ጋር ነው ውለው የሚያድሩት

አንዲት አገልጋይ ሴት ወንዝ ወርዳ ውሃ ስትቀዳ እንስራዋ ተሰበረባት። እመቤቴ አታስገባኝም ትቆጣብኛለች ስትል ሰጋችና መላ ስታሰላስል ቆይታ አንድ መሻርያ አገኘች፡ ግራ ቀኝ ሳትል ከሙፍቲ ዳውድ መስጂድ ገባች። ከሁለት መቶ ደረሳ በላይ እያቀሩ ባሉበት "ያ ሰዪዲ፡ እኔ አዳልጦኝ እንስራ ሰበርኩና እመቤቴን ፈራኋት፡ ቤቷ አታስገባኝም እስዎ ያስታርቁኝ" አለቻቸው
ታላቁ ሙፍቲ "መርሐባ" ብለው ብድግ አሉ፡ እሳቸው ሲነሱ ያ ሁላ ደረሳ "ምን ሲደረግ! እኛ እያለን ለዚች ትንሽ ጉዳይ እስዎ አይለፉም እናስታርቅልዎ" ቢሏቸው
"እሷ እናንተን መች ለመነች፡ የጠየቀችው እኔን ነው እኔው እሄድላታለሁ" አሉ ሁሉም ተከትለዋቸው ወጡ
***

እመቤቲቱ በደስታ እልልታዋን አቀለጠችው፡ ገና ደጃፏ ሲዘልቁ "ሙፍቲን ይዛልኝ መጣች፡ በረካ ትሁን እንኳን ልቆጣት ካሁን በኋላ ነፃ አድርጌያታለሁ። የምን እንስራ! ሑር ብያለሁ" አለች ደስታ አቅበጥብጧት። የመንደሩ ሰዎችም እመቤቲቱ ብቻዋን ሰርታ መብላት ስለማትችል ገንዘብ አዋጥተው አዲስ አገልጋይ አመጡላት።

ማንንም ከማንም ሳይለዩ ሴት ወንድ፣ ባለሀብት ድሃ፣ ሹም ተራ፣ ሳይሉ ለሰው ሀጃ ይቆማሉ። ተምሳሌቶቻችን ይሁኑ 💚 አላህ ከነሱ የምንጠቀም ያድርገን።


[እርሱም ተወቃሽ ሲሆን ዐሳው ዋጠው፡፡ እርሱ ለጌታው ከአወዳሾቹ ባልሆነም ኖሮ፤ እስከሚቀሰቀሱበት ቀን ድረስ በሆዱ ውስጥ በቆየ ነበር፡፡] ሷፋት፤142–144

ነብዩላሂ ዩኑስ ተሕሊል (ላ ኢላሀ ኢለላህ) እና ተስቢሕ (ሱብሓን አላህ) ባያደርግ ኖሮ እስከ ዕለተ ትንሳኤ ቀን ድረስ በዓሳ ነባሪው ሆድ ውስጥ ይቆየ ነበር።

ቢዳየቱ ወኒሐያ 2/21

ሙሰቢሒን (አወዳሾች) የሚለውን የቁርአን ቃል ሙፈሲሮቹ የተለያየ ትርጓሜ ሰጥተውታል። ከፊሎቹ ሰጋጅ ሌሎች ደግሞ ዐቢድ (ተገዢ)፣ መልካም ሥራ፣ አመስጋኝም ያሉት አሉ። በጥቅሉ እነዚህ መልካም ነገሮች በአንድ ባሪያ ላይ ከተሰባሰቡ ከፈተና መውጫ መሆናቸውን የቁርአኑ አንቀጽ ያስተምራል።

ዑለማዎች ዊርዱን የማይጠብቅና ዊርድ የሌለው ሰው ምንም የሚወርድ ነገር (ዋሪዳ) የለውም ይላሉ።

ከዊርዶች ሁሉ ዋናው ሰላት ሲኾን ከርሱ በመቀጠል በየዕለቱ የምናከናውናቸው ሱናዎች እንዲሁም የጥዋትና የምሽት ውዳሴዎች በየዕለቱ ከቁርአን ድርሻን በማንበብና በለሊት ስገደት ላይ መበርታት ዋናዎቹ ናቸው። እነዚህ ክንዋኔዎች በአግባቡና በጥሞና ሲከወኑ በእነዚህም ክንዋኔዎች ኢማን ለማግኘት ጥረት ስናደርግ ከአላህ የሚሰጡ ብዙ ሥጦታዎች ይኖራሉ።

ዚክር (አላህን ማስታወስ) እና አላህን ማወደስ በልብ ጥሞና ሲኾን የሚሰጠን ልዩ ስሜትም አለው። ተውሒድም የሚጠበቀው በዚክርና በአምልኮ ነው። ዛኪሮችና ዓቢዶች ለአላህ ቅርቦቹ ናቸው።

አላህ አብዝተው ከሚያወድሱት ባሪያዎች ውስጥ ያድርገና!

✍best kerim🙏


ማጆር አጎሊኒ አዉገሥቶ በፈረሱ እንደተቀመጠ እስላሞች ወደተሰየሙበት ሄደና ድምጹን ከፍ አድርጎ ‹ እናንት የትልቁን ነብይ የመሐመድን ሃይማኖት የተከተላችሁ እስላሞች፤ ኢትዮጵያ አገራችሁ ስትሆን በሃይማኖት ልዩነት የተነሣ ክርስቲያን ነን የሚሉት ሃበሾች የበታች አድርገዉ ከርስት ነቅለዉ ሲገዙአችሁና ሲቀጠቅጧችሁ ይኖሩ ነበር ፡፡ አሁን ግን ጩኸትና ብሶታችሁን ታላቁ የኢጣልያ መንግሥት ስለሰማችሁ እናንተን ነፃ ለማዉጣት... ከእንግዲህ ወዲህ ካሁን ቀደም ተጭኖ የነበረዉ መከራችሁና ችግራችሁ ጭንቀትና ዉርደታችሁ ከናንተ ተወገደ› እያለ ይጮህ ጀመር።

ሸይኽ ሰይድ ሷዲቅ
‹‹ . .ምንም ስፍራ ቢቸግረኝ ቢጠበኝ ፤ ከአገሬም ድሎት ባላገኝ ፤ ተወልደዉ ያደጉበትን አገር መዉደድ የተፈጥሮ ልማድ ስለሆነ ያገር ፍቅር ወደፊት እየገፋኝ የስልጣኔና የነጻነት መሠረት ‹አንድነት› መሆኑን አዉቃለሁና በገሃድ ለአንድነት ስራ በየጊዜዉ ከመጻፍ አልሰነፍሁም. . . ››

በጊዜዉ በነበረዉ ‹ብርሃንና ሰላም› ጋዜጣ ላይ ተመሳሳይ አርቲክሎችን እያቀረቡ እንደ አንድ የትግል ዘርፍ ይጠቀሙ የነበሩት ታላቁ ‹ሸይኽ ሰይድ ሷዲቅ› ፤ በ15/8/1935 ከዚሁ ጋዜጣ ካስነበቡት ጹሕፍ ዉስጥ የተወሰደ

በሀገር ፍቅር የተማረኩ ነበሩና ፋሽስቱን ተፃርረዉ ይፅፉ ነበር ፤በዚህም ምክንያት ለሁለት አመታት በእስር አሳልፈዋል።




[ አሕመድ ዑሉን ሆስፒታል…]

በተቋማት ደረጃ የተመሰረተና የተዋቀረ የህክምና አገልግሎት ጅማሮ ከ ረሱለሏህ ዘመን እንደሆነ ታሪክ ያትታል።በተለይም በጦር አውድማዎች ላይ የተጎዱ ወገኖችን፣አስቸኳይ የህክምና አገልግሎት ይሰጥ ነበር።ከዋግምት አንስቶ የአጥንት ስብራት፣የስጋዊ ቁስለትን የማከም ስራን የሚከውኑ መደበኛ ሶሃቦች እንደነበሩ ይታመናል።በዋና ጦቢብነትም ስፔሻሊስት የነበሩት ረሶለሏህ ሲሆኑ፣አስተምሕሮታቸውን የቀዱ ዶክተር ሶሃቦችም ነበሩ።የባህል ህክምና ጥበብ በጥንታዊ ህዝቦችም ዘንድ ሲተገበር የኖረ ቢሆንም በረሱለሏህ ዘመን ላቅ ወዳለ ደረጃ መሻገሩም ያምኗል።

በተለያዪ ጊዜያቶችም ለህክምና መስጫነት ሲባል የሚገነቡ ድንኳኖችና (ጊዚያዊ የጤና ተቋማት)
መጠለያዎችም እንደበሩ ከታሪክ ምንባባት ይቀዳል።
በተጨማሪም ደግሞ፣በጊዜው የነበሩና የህክምና አገልገሎት የሚደረግባቸው ቁሳቁሶችን የመጠቀም ባህል ተለምዷል።በርካታ መድሃኒቶችም ከማር፣ከጥቁር አዝሙድ እና ከቴምር ጨምሮ ከሌሎች ቅመማ ቅመሞች፣እና እፀዋቶች የመቀመም የኬሚስትሪያዉ የቅመማ ሳይንስም በወቅቱ ተንፀባርቋል።የቅመማ ግብዓቶችም ቁርዓናዊና ሐዲሳዊ ምክረ ሀሳቦች ላይ ተመርኩዘው የሚዘጋጁ ነበሩ።

ይኼንን ጥበብ (ጢብ አል ነበዊይ)፣ የተማረውም የኢስላም ትውልድ ጥበቡን ከዘመን ዘመን እየተቀባበለ ተጓዘ።በሒጅሪያ የዘመን ስሌት ወደ 220 ኛው አመተ ሒጅራ ገደማ ደግሞ፣የሆስፒታል ግንባታን መፈፀሙም ድርሳናት ይነገሯል።በአውሮፓዊያን የዘመን ቀመር በ’ 870 (አካባቢ) ላይ የሀገረ ሚስር (አሁናዊቷ ግብፅ)፣ገዢ የነበረው አሚር ማንሱሪ(?) የሆስፒታል ግንባታ አስፈላጊነት ላይ አፅንዖት ሰጥቶ ብቁ ተቋምን መመስረት አሰበ።

ቀጥሎም በሐገሪቱ እና አጎራባች ሀገራት የሚኖሩ የጢብ አል ነበውይ ምሁራንን ሰብስቦ እንዲመክሩም አደረገ።
ከግንባታው አስቀድመው የሚገነባበትን፣ብቁ የሆነና ተገቢነት ያለው፣እንዲሁም የአካባቢው አየር ሁኔታ ለሆስፒታል ማረፊታነት ምቹ የሆነ ስፍራ መኖሩን ለይቶ የመመርመር ተግባርን ከወኑ።

የስፔሻሊስቶቹ ቡድን ዋና ፊት አውራሪ የነበሩት ጠቢብም በቦታ ጥናት ዘመቻው ላይ ልዩ ፍልስፍናቸውን ተጠቀሙ።
አዲስ እና ባለንበት ዘመን ጨምር፣አፅንዖት ተሰጥቶ የማይታሰብ የሆነውን ተግባር ነበር።በዘመናቸው ያልታየና ድንቅ የጥናት መንገድ ማስገኘትም ቻሉ።

ይህም የሐገሪቱ ክፈለ ግዛቶች ውስጥ ያለውን የአየር ምጣኔ እና የስውር ትላትሎች፣በሽታ አምጪ ህዋሳትን ጀርሞችን መቃኛ ሳይንስ ከማወቃቸው ጋር የተዛመደ ነበር።
ጠቢቡም መጀመሪያ ጥሬ ትኩስ ስጋ አዘጋጁ።
ስጋውን ቆርጠውም ለ አራት ቦታ ከፈሉት።ከዚያም በከተማዋ በአራቱም አቅጣጫ፣ማዕከላዊ ቦታዎች ላይ ስጋው ተጥሎ እንዲያድር አዘዙ።በማግስቱም ስጋው ተሰበሰበ፣ተመረመረ።ምርመራውም ላይ ባገኙት ውጤት መሰረት ከአራቱ መሀል በጀርሞች ብዙ ያልተጠቃውን ለይተው በማጤን መረጡ።ይህም የሆነው ይሃ ስጋ ያደረበት ቦታ ላይ ያለው ነባራዊ አየር፣ ከሌሎቹ በተሻለ ከህዋሳት ጥቃት የፀዳ ወይም የሚቀንስ መሆኑን በማስገንዘብ ነበር።በውሳኔያቸውም መሰረት በተመረጠው ስፍራ፣የ “አሕመድ ዑሉን"ሆስታል ለመገንባት በቃ።

ሆስፒታሉም ከክፍያ ነፃ አገልግሎት የሚሰጥበት ነበር።
የወንዶች እና ሴቶች መፀዳጃ እና የሻወር ቤት፣እንዲሁም የአልባሳት ትጥበት አገልግሎት ይሰጣል።
ተኝተው ለሚታከሙ ህሙማን በቂ አልጋና ረዳት ነርሶችም ነበሩት።የሀኪሞች ቦርድ፣የምርምር ማዕከላትን ጨምሮ፣በየ ሴክተራቸው አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎችም ቀጥሮ ለማህበረሰብ ሰፊ የሆነ አግል ግሎትን ማበርከት ቻለ።

አሁን ላይ በዘመናዊ የህክምናው ጥበብ ውስጥ የሚንፀባረቁ ምርምሮች እና አሰራሮችም ከዚህ ጥንታዊ ሆስፒታል የተወሰዱ በርካታ ተሞክሮዎች መኖራቸውም ይነገረሯል።

(ምስል…በካይሮ ከተማ ነበረው ጥንታዊው የዑሉን መስጂድ እና ሆስፒታል።)

✍ የቢሻራው በር

20 last posts shown.

1 084

subscribers
Channel statistics