አንድ አምላክ በሆነ በአብ በወልድ በመንፈስቅዱስ ስም ህዳር 15 በዚህች ቀን ከዐበይት ሰማእታት የሚቆጠር፣ ተአምራትን የሚያደርግና ስሙን ለሚጠሩ፣ ለሚማጸኑት ሁሉ መልስ ለመስጠት የሚፋጠን ቅዱስ/ማር ሚናስ በሰማእትነት አረፈ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን እኛንም በቅዱስ ሚናስ ጸሎት ይማረን፣ የወዳጁ የቅዱስ ቄርሎስ ሳድሳዊም በረከቱ አይለየን አሜን።
ዳግመኛም በዚህች ቀን ከእግዚአብሔር ጋር ገጽ በገጽ የተናገሩ፣ ጸጋና ሃይማኖት በተዳከመበት ግዜ አካሄዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረጉ፣ ስለ ሕዝብ ምሕረትና ይቅርታ በብዙ መከራ ውስጥ ያለፉ ቅዱሳን ነብያት እናቶቻችን እና አባቶቻችን ፣ "ክርስቶስ ሆይ ውረድ ተወለድ፣ ወደዚህም ምድር መጥተህ አድነን" ብለው የጾሙትን ጾም፣ የጸለዩትን ጸሎት እናስብ ዘንድ ከህዳር 15 ጀምሮ ልደትን እስከምናከብርባት ታህሳስ 29 ቀን የምትዘልቅ ጾምን እንድንጾም የቤተክርስቲያን መምህራን ስርአትን ሰሩ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ እኛንም በቅዱሳን ነቢያት ጸሎት ይማረን፣ በረከታቸውም ከኛ ጋር ትኑር።
እንኳን ለጾመ ነብያት በሰላም አደረሳችሁ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፣ በቸርነቱ ደግሞ ጾሙን በሰላም አሳልፈን ብርሃነ ልደቱን ለማየት የበቃን የተዘጋጀን ያድርገን አሜን።