በይዞታ ላይ ሁከት ማድረስ የሚያስከትለው የፍትሐብሄር እና የወንጀል ሀላፊነት
****************************ይዞታ በፍትሐ-ብሄር ህጋችን ላይ ትርጉም የተሰጠው ሲሆን ይህም ይዞታ ማለት አንድ ሰው አንድን ነገር በእጁ አድርጎ በእውነት የሚያዝበት ሆኖ ሲገኝ እንደሆነ በአንቀፅ 1140 ስር ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በ1996 ዓ.ም የወጣው የወንጀል ህግ ለይዞታ ትርጉም ባይሰጥም የተከለከለ ቦታ ወይም የግል ይዞታን መድፈር በህግ እንደሚያስቀጣ ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም የግል ይዞታን መድፈር ወይም በሰው ይዞታ ላይ ሁከት መፍጠር የወንጀል እና የፍትሀ ብሄር ሀላፊነት እንደሚያስከትል ከህጎቹ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በዚህ አጭር ፅሁፍ በይዞታ ላይ ሁከት መፍጠር ወይም መድፈር የሚስከትለውን የፍትሀ ብሄር እና የወንጀል ሀላፊነት በአጭሩ እንዳስሳለን፡፡
የይዞታ ምንነትና የሚገኝበት መንገድ
በፍትሀ ብሄር ህጉ ለይዞታ ከተሰጠው ትርጉም መረዳት እንደሚቻለው አንድ ሰው ባለይዞታ ነው የሚባለው የሚንቀሳቀስ እና የማይንቀሳቀስ ንብረት በማያሻማ መልኩ ወይም ድብቅ ባልሆነ ሁኔታ ይዞ ሲገኝ ነው፡፡ የይዞታ መብት የህግ ጥበቃ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት እያንዳንዱ ዜጋ ወይም ህብረተሰብ በአጠቃለይ ንብረቱን በሰላም እንዲጠቀምበት ለማድረግ ነው፡፡
ይዞታ በሁለት መንገድ ሊገኝ ይችላል፡፡ ይህም እቃውን በአካል በመቆጣጠር እና እንደባለይዞታ የመጠቀም እና የመገልገል ሀሳብ ሲኖር ሆኖ ሁለቱ ላይሟሉ የሚችሉበት ሁኔታ አለ፡፡ ለምሳሌ፡- በወካይ እና በተወካይ መካከል ባለ የመያዝ ሁኔታ ተወካይ ይዘታውን የእርግጥ የያዘው ቢሆንም የመጠቀም ወይም የመገልገል ሀሳብ ላይኖረው ይችላል፡፡ እንዲሁም የአእምሮ ጉድለት ያጋጠመው ሰው ሙሉ ሀሳብ ላይኖረው ይችላል፡፡
አንድ ሰው በእጁ ያለ ይዞታ በተለያየ ሁኔታ ሊቀር ይችላል፡፡ ይህም፡-
• ንብረቱ ለሌላ ሰው ሲተላለፍ፣
• ሰነዱን ለሌላ ሰው በማስተላለፍ(የማያንቀሳቀሱ እና ልዩ ተንቀሳቃሽ ንብረቶች ላይ)፣
• ንብረቱ ሲጠፋ ወይም ባለንብረቱ አያስፈልገኝም ብሎ ሲጥለው፣
• ባለይዞታ የመሆን ሀሳብ ጠፍቶ ንብረቱ ግን ከእጅ ሳይወጣ ሲቀር፡-ለምሳሌ ንብረት ሸጦ ወደ ገዢ ሳያስተላልፍ ሲቀር/ስመ ሀብት ሳይቀየር ሲቀር/ ፣
ባለይዞታ በይዞታው ለራሱ የመጠቀም እንዲሁም ለሌላ ሰው ከማስተላለፍ መብት በተጨማረ በባለይዞታነቱ ክስ የማቅረብ እና ባለሀብት ሆኖ የመገመት መብት ባለይዞታነት የሚያስከትላቸው ውጤቶች ይገኙበታል፡፡
ይዞታ ጉድለት ያለበት እንዲሆን የሚያደርጉ ምክንያቶች በፍትሀ ብሄር ህጉ የተዘረዘሩ ሲሆን እነዚህም ይዞታው ቀጣይነት የሌለው ከሆነ (መቋረጡ ለተራዘመና ላልተለመደ ጊዜ የቆየ እንደሆነ)፣ ይዞታው በሀይል የተገኘ እንደሆነ (የፍትሃ ብሄር ህግ ቁጥር 1142)፣ ይዞታው በድብቅ የተያዘ እንደሆነ (የፍትሃ ብሄር ህግ ቁጥር 1146/2)፣ እውነተኛ ይዞታ ስለመሆኑ የሚያጠራጥር እንደሆነ (የፍትሃ ብሄር ህግ ቁጥር 1146/3) ናቸው፡፡
1. የፍትሀ ብሄር ሀላፊነት
በይዞታው ላይ ሁከት የተደረገበት ሰው መብቱን በሁለት መንገድ ማስከበር ይችላል፡፡
https://t.me/NegereFej@NegereFej1. ሀይል ተጠቅሞ በመከላከል (extra-judicial remedy)፡-ባለይዞታ መብቱን በዚህ መንገድ የሚያስከብረው ወደ ፍትህ አካል ወይም ወደ ፍርድ ቤት መሄድ ሳያስፈልገው ንብረቱን ከነጣቂ ወይም በድብቅ ከሚወስድ ሰው በማስለቀቅ ነው፡፡ ይሁንና ሁከትን በሀይል በማስወገድ ጊዜ ከግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህም፡-
• በፍትሀ ብሄር ህጉ አንቀፅ 1148/1 እና 2 ላይ እራስን መርዳት በሚል ርዕስ እንደተቀመጠው ባለይዞታው ወይም ስለባለይዞታው የያዘው ሰው በይዞታው ላይ የሚደረግን መንጠቅ ወይም ሁከት በሀይል መከላከል የሚችል ሲሆን ይህም ወዲያውኑ በጉልበት በማስለቀቅ የተወሰደበትን በማስመለስ መሆን አለበት፡፡ ሀይልን ሐይል በመጠቀም የመመለሱ ሁኔታ በተለይም ጉዳዩን ለፍርድ ቤት ማቅረብ እና ዳኝነት ለመጠየቅ ጊዜ በማይኖርበት አጋጣሚ ብቸኛው አማራጭ ይሆናል፡፡ ይሀንና የሀይል ድርጊቱ ሁከቱን በፈጠረው ሰው ላይ እንጂ በሶስተኛ ወገን ላይ መሆን የለበትም፡፡ እንዲሁም የሚወሰደው የሀይል እርምጃ ከደረሰው ችግር ጋር ተመጣጣኝ መሆን አለበት፣
• የመከላከል ሀይል መጠቀም የሚቻለው ድርጊቱ እንደተፈፀመ ወዲያውኑ መሆን እንዳለበት ከወንጀል ህግ አንቀፅ 78 መረዳት ይቻላል፡፡ ይህም የራሱን ወይም የሌላን ሰው መብት ህገወጥ ከሆነ ጥቃት ወይም በቅርቡ ከሚደርስ ሕገወጥ ጥቃት ለማዳን ጥቃቱ እንዳይደርስ ለማድረግ ሌላ መንገድ ሳይኖር ከመጠን ባለማለፍ የተፈፀመ ድርጊት እንደማያሰቀጣ ያስቀምጣል፡፡ በመሆኑም መብትን ተመጣጣኝ በሆነ ሀይል ማስከበር ይቻላል ማለት ነው፡፡
2. ሁከትን በፍርድ ማስወገድ (በፍትሀ ብሄር ህግ አንቀፅ 1149)
ባለይዞታው ሁከት እንዲወገድለት፣ የተወሰደበት ንብረት እንዲመለስለት ወይም ለደረሰው ጉዳት/ኪሳራ ካሳ እንዲከፈለው ለፍርድ ቤት ክስ ማቅረብ የሚችል ሲሆን ይህም ክሱ በሁለት ዓመት ውስጥ ካቀረበ በይርጋ ይታገዳል፡፡ ማለትም ይህ ጊዜ ካለፈ ክስ ማቅረብ አይችልም፡፡
2. የወንጀል ሀላፈነት
የግል ቤቶችን ወይም የተከለሉ ቦታዎችን መድፈር በወንጀል ህጉ የሚያስቀጣ ተግባር ነው፡፡ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 604 እና 605 ስር እንደተደነገገው ማንም ሰው ከህግ ወጪ፡-
1. ህጋዊ ነዋሪ የሆነ ሰው እየተቃወመ ወደ አንድ ቤት፣ግቢ፣ጀልባ ወይም ለመኖሪያ ወደ ሚያገለግል ማናቸውም ሌላ ቦታ ወይም ከቤቱ ጋር ወደ ተያያዘና ወደ ተከለለ ቦታ ወይም የአትክልት ቦታ ወይም የግል ይዞታ ወደ ሆነ ማናቸውም ሌላ ንብረት የገባ እንደሆነ ወይም
2. ሰው ባይኖርበትም ወደ አንድ መሥረያ ቤት፣ድርጅት፣ኩባንያ ወይም ሕጋዊ ሰውነት ያለው ማኅበር ሕንፃ፣ቢሮዎች ፣ግምጃ ቤት/መጋዘን/ ወይም አጥር ግቢ ሳይፈቀድለት በሀይል የገባ እንደሆነ ወይም
3. ሕጋዊ ነዋሪው ሳይቃወም ወይም ፈቅዶለት ከገባ በኃላ እንዲወጣ ሲጠይቀው ያልወጣ እንደሆነ ከሶስት ዓመት በማይበልጥ እስራት ወይም በመቀጮ ይቀጣል፡፡
ወንጀሉን ያደረገው እንዲህ ዓይነት ድርጊት እንዲፈፅም ያልተፈቀደለት ወይም ቢፈቀድለትም ሊከተለው የሚገባን ሕግ፣ ጥንቃቄ ወይም ሥነ ሥርዓት ያልተከተለ የመንግስት ሠራተኛ እንደሆነ፣ የሰውን ንብረት የመበርበር ወይም የመያዝ ሥልጣንን ያለአግባብ በመገልገል በህግ ይጠየቃል፡፡ ይሀውም በወንጀል ህጉ አንቀፅ 422 መሰረት ማንኛውም የመንግስት ሠራተኛ በሕግ ስልጣን ሳይኖረው የሰውን ንብረት የበረበረ፣ የያዘ ወይም ንብረቱን የወሰደ እንደሆነ፤ ከሰባት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ይቀጣል፡፡ እንዲሁም ለመበርበር ወይም ለመያዝ በሕግ ሥልጣን የተሰጠው ቢሆንም ተገቢ ከሆነው ኃይል በላይ ተጠቅሞ ወደ ሌላ ሰው ቤት ወይም ግቢ የገባ እንደሆነ ወይም በሕግ ከታዘዘው ወይም ከተፈቀደው ሥርዓት ውጪ የሰውን ንብረት የበረበረ፣ የያዘ ወይም የወሰደ እንደሆነ፣ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና በመቀጮ ይቀጣል፡፡