በኢትዮጵያ የወሲብ ቪዲዮዎችን የሚያሰራጩ ድህረገጾችን ለማሳገድ በአንድ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባል ፊርማ ማሰባሰብ ተጀመረ!
በኢትዮጵያ የወሲብ ቪዲዮዎችን የሚያሰራጩ ድህረገጾችን ለማሳገድ ፊርማ ማሰባሰብ መጀመሩን የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባል የሆኑት የተከበሩ ዶ/ር ፈትሂ ማህዲ ከብስራት ራዲዮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።በአንድ ግለሰብ ተነሳሽነት የተጀመረዉ እንቅስቃሴዉ አሁን ላይ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባል በሆኑ 15 በሚደርሱ ሌሎች አባላትም ድጋፍ ማግኘቱን ጣቢያችን ሰምቷል።
የማስታወቂያ ባለሙያ በሆነዉ አለማየሁ አጥናፍሰገድ በተባለ ግለሰብ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ድህረገጾቹን ለማሳገድ እንዲሁም በህጻናት እና ወጣቶች አእምሮ ላይ የሚያደርሰዉን ጫና በማስተማር እና ማህበረሰብን የማንቃት እንቅስቃሴ አንድ ብሎ መጀምሩን ለብስራት ራዲዮ ተናግሯል።በበርካቶች ተቀባይነትን በማግኘት ላይ ያለዉ ግለሰቡ ፤ የሚያስተላልፋቸዉን መልእክቶች የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባል የሆኑት የተከበሩ ዶ/ር ፈትሂ ማህዲ ተመልክተዉ አጋርነታቸዉን እንዳሳዩት ገልጿል።
ጉዳዩ ከመንግስት በቂ ትኩረት አልተሰጠዉም ያለዉ ግለሰቡ ይህን አላማ የሚደግፉ አካላት በፊርማ ማሰባሰቡ ላይ እንዲሳተፉ እና ጉዳዩን በቂ ትኩረት እንዲሰጠዉ የራሳቸዉን አስተዋጽኦ ያድርጉ ሲል ጥሪ አቅርቧል።የህዝብ እንደራሴዎች ምክርቤት አባሉ የተከበሩ ዶ/ር ፈትሂ የወሲብ ምስእሎቹን በኢትዮጵያ ለማሳገድ ፊርማ ማሰባሰብ ላይ መሆናቸዉን ተናግረዋል። እንቅስቃሴው እስካሁን ድረስም 15 በሚጠጉ በምክርቤቱ አባላት ድጋፍ ማግኘቱንም አንስተዋል።
ተመሳዳይ እገዳን እና ህግን ከደነገጉ ሀገራት አንዷ ከሆነችዉ ዩጋንዳ እና ቱርክ ፤ በህጉ ዙሪያ ያስቀመጧቸዉን ድንጋጌዎች ለህዘብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግና ፍትህ ቋሚ ኮሚቴ አባላት ማስገባታቸውም የምክርቤቱ አባል ተናግረዋል።
በአለማችን ላይ በርካታ ሀገራት ክልከላዉን እና ትዉልዱን በመጠበቅ ላይ ሲሆኑ ከነዚህም ዉስጥ ሰሜን ኮሪያ በተለምዶዉ ቪፒኤን በተሰኘዉ (virtual protected network) አማካኝነትም ዜጎች ድህረገጾቹን እንዳይጠቀሙ ካገዱ ሀገራት ትጠቀሳለች። ሌላኛዋ የሩቅ ምስራቅ ቻይና ከፍተኛ በሚባል ደረጃ ድህረገጾቹን ሳንሱር ከሚያደርጉ ሀገራት ዉስጥ ስትሆን የሀገሪቷ አደገኛ አጥር በተሰኘ ፕሮጀክት ድህረገጾቹ ላይ ቁጥጥር እና ክትትል ታደርጋለች።
በተጨማሪነትም ኳታር ፣ ሶርያ ፣ ቱርክሜኒስታን ፣ ፓኪስታን ፣ ቱርክ ፣ ኦማን ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ጎረቤት ሀገር ኤርትራ ድህረገጾቹ ላይ እገዳ እና ቁጥጥር የሚያደርጉ ሀገራት ናቸዉ።ቼንጅ ዶት ኦርግ ላይ መሰባሰብ በጀመረዉ ፊርማ እስካሁን ከ 4መቶ በላይ ሰዎች ድጋፋቸዉን መግለጻቸዉ ተመልክቷል።
[ዳጉ ጆርናል/ብስራት ራዲዮ]
@addis_news@addis_news